አምላክን መፍራት “ጥበብን መማር ነው”
እውነተኛ ጥበብ ድል ያለ ድግስ አዘጋጀች። “ሴት አገልጋዮቿንም ላከች፤ ከከተማዪቱም ከፍተኛ ቦታ ተጣራች። እርሷም ማመዛዘን ለጐደላቸው፣ ‘ማስተዋል የሌላችሁ ሁሉ ወደዚህ ኑ!’ አለች። ‘ኑ፤ ምግቤን ተመገቡ፤ የጠመቅሁትንም የወይን ጠጅ ጠጡ። የሞኝነት መንገዳችሁን ተዉ፤ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ በማስተዋልም መንገድ ተመላለሱ።’”—ምሳሌ 9:1-6
ከጥበብ ማዕድ መመገብ መጥፎ ወይም ጎጂ ወደ ሆነ ነገር አይመራም። በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረውን አምላካዊ ጥበብ ማዳመጥ ብሎም የሚሰጠውን ተግሣጽ መቀበል ያማረ ውጤት ይኖረዋል። በምሳሌ 15:16-33 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት ጥበብ ያዘሉ ምክሮችም የዚህ አምላካዊ ጥበብ ክፍል ናቸው።a እጥር ምጥን ብለው የተጻፉትን እነዚህን ምክሮች መስማትና መቀበል ባለን ጥቂት ነገር እንድንረካ፣ እድገት እንድናደርግ ብሎም በሕይወታችን ደስተኞች ሆነን እንድንኖር ይረዳናል። በተጨማሪም ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ ከመርዳቱም ባሻገር በሕይወት ጎዳና ጸንተን እንድንጓዝ ያስችለናል።
ጥቂት ነገር ይበልጣል
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን “እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር፣ ሁከት ካለበት ትልቅ ሀብት ይበልጣል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 15:16) አንድ ግለሰብ ፈጣሪን ችላ ብሎ በሕይወቱ ውስጥ ዋነኛ ግቡ ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድ ቢሆን ምንኛ ሞኝነት ነው! እንዲህ ያለው ሕይወት አድካሚና በጭንቀት የተሞላ ነው። አንድ ሰው ሲሸመግል ዕድሜውን በሙሉ የሠራው ነገር ባዶና ዋጋ ቢስ መሆኑን ቢረዳ እንዴት የሚያሳዝን ነው! ‘ከሁከት’ ጋር ብዙ ሀብት ማካበት በእውነትም የጥበብ እርምጃ አይደለም። ባለን ነገር ረክቶ የመኖርን ምስጢር ማወቅና በዚህ መሠረት መኖር ምንኛ የተሻለ ነው! እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ይሖዋን በመፍራትና ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና በመጠበቅ እንጂ ቁሳዊ ሀብትን በማካበት አይደለም።—1 ጢሞቴዎስ 6:6-8
ሰሎሞን፣ ከሌሎች ጋር የሚኖረን መልካም ግንኙነት ከተትረፈረፈ ቁሳዊ ሀብት እንደሚሻል ሲያጎላ “ፍቅር ባለበት ጐመን መብላት፣ ጥላቻ ባለበት የሰባ ፍሪዳ ከመብላት ይሻላል” ብሏል። (ምሳሌ 15:17) እውነት ነው፣ በቤት ውስጥ ምርጥ ምግብ ከሚትረፈረፍ ይልቅ በቤተሰቡ መካከል ፍቅር ቢኖር ይሻላል። በአንድ ወላጅ ብቻ በሚተዳደሩ ቤተሰቦች ውስጥ ሁሉን ነገር ማሟላት ከባድ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ሰዎች ሊያገኙት የሚችሉት የዕለት ጉርስ ብቻ ይሆናል። ይሁን እንጂ በቤታቸው ውስጥ ፍቅር ካለ ቤተሰቡ በሙሉ ደስተኛ ይሆናል።
ፍቅር በሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ችግሮች መነሳታቸው አይቀርም። አንደኛው የቤተሰቡ አባል ሌላኛውን ግለሰብ የሚያስከፋ ነገር ሊናገር ወይም ሊያደርግ ይችላል። ታዲያ ቅር የተሰኘው ሰው ምላሽ መስጠት ያለበት እንዴት ነው? ምሳሌ 15:18 እንዲህ ይላል:- “ግልፍተኛ ሰው ጠብ ያነሣሣል፤ ታጋሽ ሰው ግን ጠብን ያበርዳል።” በቁጣ ሳይሆን በለዘበ አንደበት የተሰጠ መልስ ሰላምና ደስታ እንዲሰፍን ያደርጋል። በዚህ ምሳሌ ውስጥ የሚገኘው ምክር የጉባኤ እንቅስቃሴዎችንና አገልግሎትን ጨምሮ በሌሎች የሕይወት ዘርፎች ላይም ይሠራል።
“የተጠረገ አውራ ጐዳና”
ቀጣዩ ምሳሌ ጥበብ የምትሰጠውን ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ በሆኑና ባልሆኑ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳይ ነው። “የሀኬተኛ መንገድ በእሾህ የታጠረች ናት፤ የቅኖች መንገድ ግን የተጠረገ አውራ ጐዳና ነው።”—ምሳሌ 15:19
የእሾህ አጥር መሰናክል የሚሆን ነገር ነው። ሀኬተኛ የሆነ ሰው የተለያዩ ዓይነት መሰናክሎች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ ስለሚያስብ የተሰጠውን ሥራ እንዳይሠራ ምክንያት የሆኑት እነዚህ መሰናክሎች እንደሆኑ ይናገራል። ከዚህ በተቃራኒ ግን ቅኖች መሰናክል ሊሆኑባቸው የሚችሉ ነገሮች አያስጨንቋቸውም። በሥራቸው ታታሪ ከመሆናቸውም በላይ እየሠሩ ላሉት ነገር ትኩረት ይሰጣሉ። ስለዚህም በቸልታ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ በእሾህ የተመሰሉ ችግሮችን ያስወግዳሉ። በየጊዜው ለውጥ ስለሚያደርጉ መንገዳቸው “የተጠረገ አውራ ጐዳና ነው” ተብሏል። ሥራቸውን ለመጀመር ስለማያመነቱ በሚያገኙት ውጤት ይደሰታሉ።
ስለ አምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት በማግኘት እድገት ማድረግን እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። ይህን ለማድረግ ጥረት ወሳኝ ነገር ነው። አንድ ግለሰብ ትጋት የተሞላበት የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዳያደርግ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃን፣ ጥርት አድርጎ የማንበብ ችግርን ወይም የመረዳት ችሎታ ውስንነትን ሰበብ አድርጎ ማቅረብ ይችል ይሆናል። ሆኖም እነዚህን ነገሮች እውቀት ለማግኘት በሚደረገው ጉዞ ላይ እንዳሉ እንቅፋቶች አድርጎ አለማሰቡ ምንኛ የተሻለ ነው! ያሉን ችሎታዎች ውስን ቢሆኑም የማንበብም ሆነ ያነበብነውን የመረዳት አቅማችንን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ እንችላለን። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም መዝገበ ቃላትን መጠቀም እንችል ይሆናል። አዎንታዊ አመለካከት መያዝ እውቀት እንድንቀስምና መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ይረዳናል።
‘አባት ደስ ሲለው’
ንጉሥ ሰሎሞን “ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ተላላ ሰው ግን እናቱን ይንቃል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 15:20) ወላጆች ልጆቻቸው በጥበብ ጎዳና ሲመላለሱ ማየት እንደሚያስደስታቸው የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ ይህን መሰሉን ጥሩ ውጤት ለማግኘት ወላጆች የሚሰጡት ሥልጠናና ተግሣጽ አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 22:6) ጠቢብ ልጅ ለወላጆቹ የደስታ ምንጭ ነው! ተላላ ልጅ ግን ለወላጆቹ የዕድሜ ልክ ሐዘን ነው።
ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ‘ደስ መሰኘት’ የሚለውን አገላለጽ ከሌላ አቅጣጫ ሲያብራራው እንዲህ ብሏል:- “ማመዛዘን የጐደለው ሰው ቂልነት ያስደስተዋል፤ አስተዋይ ሰው ግን ቀጥተኛውን መንገድ ይከተላል።” (ምሳሌ 15:21) ማመዛዘን የጎደላቸው ሰዎች እውነተኛ እርካታ ወይም ደስታ በማይሰጥ የሰነፍ ሰው ቀልድ ወይም ጨዋታ ደስ ይሰኛሉ። ይሁን እንጂ አስተዋይ ሰው ‘ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን መውደድ’ ከንቱ መሆኑን ይገነዘባል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 4) ጻድቅ ሰው አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አጥብቆ መከተሉ ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርግና ቀጥተኛውን መንገድ እንዲከተል ይረዳዋል።
‘ምክር የሚሳካው’ እንዴት ነው?
ከመለኮታዊ መመሪያ ጋር ተስማምቶ መኖር በሌሎች የሕይወት ዘርፎችም ጥቅም ያስገኝልናል። ምሳሌ 15:22 እንዲህ ይላል:- “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።”
እዚህ ላይ ምክር የተባለው ቃል የልብን አውጥቶ በግልጽ መወያየትን ያመለክታል። “ምክር” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የልብ ወዳጅ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚደረግ የሐሳብ ልውውጥን ለመግለጽ ይሠራበታል። ምክር፣ ላይ ላዩን ብቻ ከሚደረግ ጭውውት በተለየ መልኩ እውነተኛ ስሜትንና ሐሳብን አውጥቶ መነጋገርን ያመለክታል። ባልና ሚስትም ሆኑ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር እንዲህ የመሰለ ግልጽ ውይይት የሚያደርጉ ከሆነ በመካከላቸው ሰላምና አንድነት ይኖራል። ነገር ግን ምክር ከሌለ ቤተሰቡ ሰላም የሌለውና ችግር የሞላበት ይሆናል።
ከባድ ውሳኔ በምናደርግበት ወቅት “በብዙ አማካሪዎች ግን [ዕቅድ] ይሳካል” የሚለውን ምክር ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ የሚሰጠንን የሕክምና ዓይነት በምንመርጥበት ወቅት፣ በተለይ ከበድ ያለ ውሳኔ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ሁለት ወይም ሦስት የሕክምና ባለሙያዎችን ማማከር ጥበብ አይደለም?
መንፈሳዊ ጉዳዮችን በማከናወን ረገድም ቢሆን ከብዙዎች ጋር መመካከር ጠቃሚ ነው ቢባል አልተጋነነም። ሽማግሌዎች እርስ በርሳቸው ሲመካከሩም ሆነ ያላቸውን ችሎታ በአንድነት ሲጠቀሙበት የሚሠሩት ሥራ ‘ይሳካላቸዋል።’ ከዚህም በላይ አዲስ የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች በዕድሜ ከገፉትና ብዙ ተሞክሮ ካካበቱት ሽማግሌዎች ምክር ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት አይኖርባቸውም። በተለይ ደግሞ ጉዳዩ ከከበዳቸው እንዲህ ማድረጋቸው ወሳኝ ነው።
“ተገቢ መልስ” ለደስታ ምክንያት ሲሆን
በማስተዋል የቀረበ ንግግር ምን ጥቅም አለው? “ሰው ተገቢ መልስ በመስጠት ደስታን ያገኛል፤ በወቅቱም የተሰጠ ቃል ምንኛ መልካም ነው!” (ምሳሌ 15:23) ሰዎች የሰጠናቸውን መልስ ወይም ምክር ተግባራዊ በማድረጋቸው ስኬታማ ሲሆኑ ስንመለከት አንደሰትም? የምንሰጠው ምክር ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ግን ሁለት መሥፈርቶችን ያሟላ መሆን ይገባዋል።
በመጀመሪያ ምክሩ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። (መዝሙር 119:105፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እንዲሁም በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ መሆን አለበት። እውነትነት ያላቸው ቃላትም ቢሆኑ በመጥፎ ጊዜ ከተነገሩ ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድን ሰው የደረሰበትን ችግር ሳንሰማው ምክር ብንሰጠው ጥበብ ካለመሆኑም በተጨማሪ ግለሰቡን አይጠቅመውም። ‘ለመስማት የፈጠንን፣ ለመናገር የዘገየን’ መሆናችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው!—ያዕቆብ 1:19
‘የሕይወት መንገድ ወደ ላይ ትመራለች’
ምሳሌ 15:24 “ወደ ሲኦል ከመውረድ እንዲድን፣ የሕይወት መንገድ ጠቢቡን ሰው ወደ ላይ ትመራዋለች” በማለት ይናገራል። ጠቢብ ሰው ከሲኦል ማለትም ከመቃብር እንዲርቅ በሚረዳው መንገድ ላይ ይጓዛል። ልቅ ከሆነ የጾታ ብልግና፣ አደገኛ ዕፆችን አላግባብ ከመጠቀምና ከስካር ስለሚርቅ ያለዕድሜው አይቀጭም። በዚህም ምክንያት አካሄዱ ወደ ሕይወት መንገድ ይመራዋል።
ከዚህ በተቃራኒ ማስተዋል የጎደላቸው ሰዎች ሕይወት ምን እንደሚመስል እንመልከት:- “እግዚአብሔር የትዕቢተኛውን ቤት ያፈርሰዋል፤ የመበለቲቱን ዳር ድንበር ግን እንዳይደፈር ይጠብቃል። እግዚአብሔር የክፉውን ሰው ሐሳብ ይጸየፋል፤ የንጹሓን ሐሳብ ግን ደስ ያሰኘዋል። ስስታም ሰው በቤተ ሰቡ ላይ ችግር ያመጣል፤ ጕቦን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል።”—ምሳሌ 15:25-27
የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ሰሎሞን ብዙዎች ከሚወድቁበት ወጥመድ እንዴት መራቅ እንደሚቻል ሲገልጽ “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል፤ የክፉ ሰው አፍ ግን ክፋትን ያጐርፋል” ብሏል። (ምሳሌ 15:28) ይህ ምሳሌ እንዴት ግሩም ምክር የሚሰጥ ነው! ሳይታሰብበት የሚሰጥ የማይረባ መልስ መልካም ነገር ሊያስገኝ አይችልም። ከአንድ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ነገሮችን እንዲሁም የሰዎችን ሁኔታና ስሜት ግምት ውስጥ ማስገባታችን በኋላ ላይ የሚያስቆጨን ነገር እንዳንናገር ያደርገናል።
ታዲያ አምላክን መፍራት እንዲሁም የሚሰጠውን ተግሣጽ መቀበል ምን ጥቅም አለው? ጠቢቡ ሰው እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣል:- “እግዚአብሔር ከክፉዎች ሩቅ ነው፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።” (ምሳሌ 15:29) እውነተኛው አምላክ ወደ ክፉ ሰዎች አይቀርብም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕግን ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን፣ ጸሎቱ እንኳ አስጸያፊ ነው” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 28:9) አምላክን የሚፈሩና በእርሱ ዓይን ትክክል የሆነውን ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች ግን እንደሚሰማቸው እርግጠኛ ሆነው ያለ ፍርሃት ወደ እርሱ መቅረብ ይችላሉ።
“ልብን ደስ” የሚያሰኘው ምንድን ነው?
ሰሎሞን ትኩረት የሚስብ ንጽጽር በመጠቀም እንዲህ አለ:- “ብሩህ ገጽታ ልብን ደስ ያሰኛል፤ መልካም ዜናም ዐጥንትን ያለመልማል።” (ምሳሌ 15:30) ዐጥንት በመቅኒ ሲሞላ ‘ይለመልማል’። ይህም መላውን ሰውነት ያበረታል፤ እንዲሁም ልብን ደስ ያሰኛል። በተመሳሳይም ብሩሕ ገጽታ የልብ ደስታን ያንጸባርቃል። መልካም ዜና መስማት እንዲህ ያለ ደስታ ያስገኛል!
የይሖዋ አምልኮ በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋ እንዳለ ስንሰማ ትልቅ ማበረታቻ አይሆንልንም? በእርግጥም የአምላክን መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እየተከናወነ ያለውን ነገር ማወቃችን እኛም በአገልግሎት ይበልጥ እንድንካፈል ያበረታታናል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ይሖዋን አምላካቸው አድርገው እውነተኛውን አምልኮ የተከተሉ ሰዎችን ተሞክሮ ስንሰማ ልባችን በደስታ ይሞላል። “ከሩቅ የሚመጣ መልካም ዜና” ይህን ያህል ተጽዕኖ ካለው፣ በአገልግሎት ላይ ያሳለፍነውን ትክክለኛውን ሰዓት በጥንቃቄ ሪፖርት ማድረጋችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው!—ምሳሌ 25:25
“ትሕትናም ክብርን ትቀድማለች”
ጠቢቡ ንጉሥ በተለያየ መልኩ የሚሰጠንን ተግሣጽ የመቀበልን አስፈላጊነት ሲገልጽ “ሕይወት ሰጪ የሆነውን ተግሣጽ የሚሰማ፣ በጠቢባን መካከል ይኖራል። ተግሣጽን የሚንቅ ራሱን ይንቃል፤ ዕርምትን የሚቀበል ግን ማስተዋልን ያገኛል” ብሏል። (ምሳሌ 15:31, 32) እርምት ወይም ተግሣጽ የግለሰቡን ልብ በመንካት እንዲስተካከል ከማስቻሉም በላይ አስተዋይ እንዲሆን ይረዳዋል። “የተግሣጽ በትር” ‘በሕፃን ልብ ውስጥ የታሰረውን ሞኝነት’ ማስወገዱ የሚያስደንቅ አይደለም! (ምሳሌ 22:15) እርምትን የሚቀበል ማስተዋልን ያገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ተግሣጽን የሚንቅ ሕይወቱን እንደናቀ ይቆጠራል።
በእርግጥም ጥበብ የምትሰጠውን ተግሣጽ መቀበል ብሎም በትሕትና በተግባር ላይ ማዋል ጠቃሚ ነው። እንዲህ ማድረጋችን እርካታ እንድናገኝ፣ እድገት እንድናደርግ እንዲሁም ደስተኞችና ስኬታማ እንድንሆን የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ክብርና ሕይወት ያስገኝልናል። ምሳሌ 15:33 “እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብን መማር ነው፤ ትሕትናም ክብርን ትቀድማለች” በማለት ይደመድማል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በምሳሌ 15:1-15 ላይ የቀረበውን ማብራሪያ ለማግኘት የሐምሌ 1, 2006 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13-16 ተመልከት።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቤት ውስጥ ምርጥ ምግብ ከሚትረፈረፍ ይልቅ በቤተሰቡ መካከል ፍቅር ቢኖር ይሻላል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምንም እንኳ ያሉን ችሎታዎች ውስን ቢሆኑም አዎንታዊ አመለካከት መያዝ እውቀት እንድናገኝ ይረዳናል
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምክር የልብን አውጥቶ መወያየትንም ያመለክታል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘መልካም ዜና ዐጥንትን የሚያለመልመው’ እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?