ወደ አምላክ ቅረብ
‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት ትችላለህ
ይሖዋ አምላክ በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ሀብት ከፊታችን ያስቀመጠልን ከመሆኑም በላይ ይህን ሀብት እንድናገኝ ልባዊ ፍላጎት አለው። ይህ ሀብት ቁሳዊ ብልጽግና አያስገኝልንም፤ ከዚህ ይልቅ በዓለም ላይ ያለው ገንዘብ በሙሉ ሊገዛው የማይችለውን ነገር ይኸውም ውስጣዊ ሰላም፣ እርካታና ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲኖረን ያስችለናል። ይህ ውድ ሀብት ምንድን ነው? በምሳሌ 2:1-6 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን የተናገራቸው ቃላት የዚህን ውድ ሀብት ምንነት በግልጽ ያስረዳሉ።
ሰለሞን ይህ ውድ ሀብት ‘የአምላክ እውቀት’ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘው ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸው እውነት እንደሆነ ገልጿል። (ቁጥር 5) ይህ ውድ ሀብት የተለያዩ ገጽታዎች አሉት።
እውነተኛ ትምህርቶች፦ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፦ የአምላክ ስም ማን ነው? (ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም) ከሞትን በኋላ ምን እንሆናለን? (መዝሙር 146:3, 4) የተፈጠርነው ለምንድን ነው? (ዘፍጥረት 1:26-28፤ መዝሙር 115:16) እንደ እነዚህ ላሉት ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ምን ያህል ዋጋ ትከፍላለህ?
ጥበብ ያዘለ ምክር፦ መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንዴት መምራት እንደምንችል ይነግረናል። ትዳርህ የሰመረ እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? (ኤፌሶን 5:28, 29, 33) ልጆችህን ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርገህ ማሳደግ የምትችለው እንዴት ነው? (ዘዳግም 6:5-7፤ ኤፌሶን 6:4) በሕይወትህ ደስታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? (ማቴዎስ 5:3፤ ሉቃስ 11:28) በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እምነት የሚጣልበት ምክር ብታገኝ ምን ያህል ዋጋ ትከፍላለህ?
ስለ አምላክ ማንነትና ባሕርያት ጥልቅ ማስተዋል፦ አምላክን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት የሚቻልበት ዋነኛ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አምላክ ምን ዓይነት አካል ነው? (ዮሐንስ 1:18፤ 4:24) ስለ እኛ ያስባል? (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ላቅ ብለው ከሚታዩት ባሕርያቱ መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? (ዘፀአት 34:6, 7፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ስለ ፈጣሪያችን እውነተኛ መረጃ ማግኘት በዋጋ ቢተመን ምን ያህል ያወጣል ትላለህ?
‘የአምላክ እውቀት’ በእርግጥም ውድ የሆነ መንፈሳዊ ሀብት ነው። ታዲያ ይህን ሀብት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ምዕራፍ 2 ቁጥር 4 ላይ ይህን ማድረግ የሚቻልበት ፍንጭ ተጠቅሷል፤ እዚህ ቁጥር ላይ ሰለሞን ይህን እውቀት ‘ከተሸሸገ ሀብት’ ጋር አነጻጽሮታል። እስቲ ይህን አስብ፦ አንድ የተሸሸገ ሀብት ተሰውሮ ከተቀመጠበት ስፍራ ዘሎ በመውጣት ድንገት እጅህ ላይ ዱብ አይልም። ይህን ሀብት ለማግኘት ጥረት ማድረግ አለብን። የአምላክን እውቀት ከማግኘት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይህ ውድ ሀብት በምሳሌያዊ አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተቀብሯል ሊባል ይችላል። በመሆኑም ይህን ሀብት ለማግኘት ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።
ሰለሞን ‘የአምላክን እውቀት ለማግኘት’ ምን ማድረግ እንዳለብን ገልጿል። “ቃሌን ብትቀበል” እንዲሁም “ልብህንም . . . ብትመልስ” የሚሉት አገላለጾች እሺ ባይ ልብ እንደሚያስፈልገን የሚያሳዩ ናቸው። (ቁጥር 1, 2) “ብትጣራ፣” “ብትፈልጋት” እንዲሁም “ብትሻት” የሚሉት ሐሳቦች ከፍተኛ ጥረት ማድረግና ልባዊ ተነሳሽነት ማሳየት እንደሚያስፈልገን ይጠቁማሉ። (ቁጥር 3, 4) እንግዲያው ይህን ውድ ሀብት ለማግኘት በቅን ልብ ተነሳስተን መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት ያስፈልገናል።—ሉቃስ 8:15
እኛ ቀዳሚ በመሆን ጥረት ካደረግን ይሖዋ የቀረውን ነገር ያሟላልናል። ቁጥር 6 “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣል” ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ሙሉ በሙሉ መረዳት የምንችለው በአምላክ እርዳታ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 6:44፤ የሐዋርያት ሥራ 16:14) ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፦ የአምላክን ቃል ለመመርመር ልባዊ ጥረት የምታደርግ ከሆነ ‘የአምላክን እውቀት’ ታገኛለህ፤ ይህ ደግሞ ልትገምተው ከምትችለው በላይ ሕይወትህን የሚያበለጽግ ውድ ሀብት ነው።—ምሳሌ 2:10-21a
በጥቅምት ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን መማር ለሚፈልጉ ሰዎች ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጣሉ። ታዲያ በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ለምን አታነጋግርም? አሊያም በዚህ መጽሔት ገጽ 4 ላይ ከሚገኘው አድራሻ መካከል ለአንተ አመቺ ወደሆነው መጻፍ ትችላለህ።