ጥሩ የሥራ አጋር ነህ?
“የተዋጣለት ሠራተኛ ሆኜ ከጎኑ ነበርኩ። . . . እኔም በፊቱ ሁልጊዜ ሐሴት አደርግ ነበር።” (ምሳሌ 8:30) ይህ ጥቅስ የአምላክ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዓመታት ከአባቱ ጋር በሠራበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ይገልጻል። ጥቅሱ ኢየሱስ የአምላክ የሥራ አጋር በመሆኑ ምን እንደተሰማውም ያሳያል። ኢየሱስ “በፊቱ . . . ሐሴት አደርግ ነበር” ብሏል።
ኢየሱስ በሰማይ በነበረበት ወቅት ጥሩ የሥራ አጋር ለመሆን የሚረዱትን ባሕርያት ተምሯል፤ እነዚህ ባሕርያት ወደ ምድር ከመጣ በኋላም አብረውት ለሚሠሩት ሰዎች ጥሩ የሥራ አጋር ለመሆን ረድተውታል። እኛስ ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መመርመራችን፣ ጥሩ የሥራ አጋር ለመሆን የሚረዱንን ሦስት መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማስተዋል ያስችለናል። እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከወንድሞቻችን ጋር ይበልጥ በአንድነትና በትብብር ለመሥራት ያስችሉናል።
መሠረታዊ ሥርዓት 1፦ ‘አንዳችሁ ሌላውን አክብሩ’
ጥሩ የሥራ አጋር ትሑት ነው፤ ለሥራ ባልደረቦቹ ትልቅ ቦታ ይሰጣል፤ እንዲሁም ልታይ ልታይ አይልም። ኢየሱስ እንዲህ ያለውን የትሕትና ዝንባሌ ከአባቱ ተምሯል። ይሖዋ፣ ፈጣሪ ተብሎ ሊጠራ የሚገባው እሱ ብቻ ቢሆንም ልጁ ከእሱ ጋር አብሮ በመሥራት ለተጫወተው ሚና እውቅና ሰጥቷል። አምላክ “ሰውን በመልካችን . . . እንሥራ” ማለቱ ይህን ይጠቁማል። (ዘፍ. 1:26) ይሖዋ እንዲህ ብሎ በመናገሩ ኢየሱስ፣ አባቱ ትሑት መሆኑን ተገንዝቦ መሆን አለበት።—መዝ. 18:35
ኢየሱስም ምድር ላይ በነበረበት ወቅት እንዲህ ያለ ትሕትና አሳይቷል። ላከናወናቸው ነገሮች ሌሎች ሲያመሰግኑት፣ ውዳሴ የሚገባው አባቱ እንደሆነ ገልጿል። (ማር. 10:17, 18፤ ዮሐ. 7:15, 16) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረው ጥረት ያደረገ ከመሆኑም ሌላ እንደ ባሪያ ሳይሆን እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (ዮሐ. 15:15) እንዲያውም ትሕትናን ሊያስተምራቸው ስለፈለገ እግራቸውን አጥቧል። (ዮሐ. 13:5, 12-14) እኛም የራሳችንን ፍላጎት ከማስቀደም ይልቅ ለሥራ አጋሮቻችን ትልቅ ቦታ ልንሰጥ ይገባል። ‘ለሥራው የሚመሰገነው ማን ነው?’ የሚለው ላይ ከማተኮር ይልቅ ‘አንዳችን ሌላውን ካከበርን’ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንችላለን።—ሮም 12:10
በተጨማሪም ትሑት የሆነ ሰው “የታቀደው ነገር በብዙ አማካሪዎች [እንደሚሳካ]” ይገነዘባል። (ምሳሌ 15:22) ብዙ ልምድና የላቀ ችሎታ ቢኖረንም እንኳ ሁሉንም ነገር የሚያውቅ ማንም ሰው እንደሌለ ማስታወስ ይኖርብናል። ኢየሱስም እንኳ የማያውቀው ነገር እንዳለ ተናግሯል። (ማቴ. 24:36) በተጨማሪም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ሐሳባቸውን እንዲያካፍሉት ይፈልግ ነበር። (ማቴ. 16:13-16) የሥራ ባልደረቦቹ ከእሱ ጋር መሆን ያስደስታቸው የነበረው ለዚህ ነው! እኛም በተመሳሳይ አቅማችን ውስን መሆኑን አምነን ስንቀበልና የሌሎችን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ ስንሆን ከእነሱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይኖረናል፤ እንዲሁም የታቀደው “ይሳካል።”
በተለይ ሽማግሌዎች አብረው በሚሠሩበት ጊዜ በዚህ ረገድ ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነው። መንፈስ ቅዱስ በሽማግሌዎች አካል ውስጥ የሚገኝን ማንኛውንም ሽማግሌ ሊመራው እንደሚችል ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ እያንዳንዱ ሽማግሌ ነፃነት ተሰምቶት አመለካከቱን መግለጽ እንዲችል ካደረጉ፣ መላውን ጉባኤ የሚጠቅም ውሳኔ ላይ መድረስ ይችላሉ።
መሠረታዊ ሥርዓት 2፦ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን”
ጥሩ የሥራ አጋር አብረውት ከሚሠሩት ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ምክንያታዊ ነው። አመለካከቱን ለመቀየር ፈቃደኛ ነው፤ እንዲሁም እሺ ባይ ነው። ኢየሱስ አባቱ ምክንያታዊ መሆኑን ለመመልከት የሚያስችሉ ግሩም አጋጣሚዎች ነበሩት። ይሖዋ የሰው ዘሮችን ለማዳን የወሰደውን እርምጃ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ የሰው ልጆች ሞት የሚገባቸው ቢሆኑም ይሖዋ እነሱን ለመቤዠት ሲል ልጁን ወደ ምድር ልኮታል።—ዮሐ. 3:16
ኢየሱስም አስፈላጊ ወይም ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ እሺ ባይ መሆኑን አሳይቷል። ኢየሱስ የተላከው ለእስራኤል ቤት ቢሆንም ፊንቄያዊቷን ሴት እንደረዳት እናስታውሳለን። (ማቴ. 15:22-28) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ በሚጠብቀው ነገርም ምክንያታዊ ነበር። የቅርብ ወዳጁ የሆነው ጴጥሮስ በሕዝብ ፊት ቢክደውም እንኳ ኢየሱስ እሱን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነበር። በኋላም ለጴጥሮስ ትልቅ ኃላፊነት ሰጥቶታል። (ሉቃስ 22:32፤ ዮሐ. 21:17፤ ሥራ 2:14፤ 8:14-17፤ 10:44, 45) ኢየሱስ የተወው ምሳሌ እኛም እሺ ባዮች በመሆን ‘ምክንያታዊነታችን በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ እንዲሆን’ ለማድረግ መጣር እንዳለብን በግልጽ ያስተምረናል።—ፊልጵ. 4:5
ምክንያታዊ መሆናችን ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ተስማምተን ለመሥራት ስንል አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግም ያነሳሳናል። ኢየሱስ ምሥራቹን የተቀበሉ ሰዎችን ጥሩ አድርጎ ይይዛቸው ስለነበር በእሱ የቀኑት ጠላቶቹ “የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ” በማለት ከሰውታል። (ማቴ. 11:19) እኛስ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ተባብረን በመሥራት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ እንችል ይሆን? ሉዊስን እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ይህ ወንድም በተጓዥ የበላይ ተመልካችነትና በቤቴል ባገለገለበት ወቅት የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ካላቸው ወንድሞች ጋር ሠርቷል። ሉዊስ እንዲህ ብሏል፦ “ፍጹማን ካልሆኑ የተለያዩ ሰዎች ጋር መሥራት፣ የተለያየ መጠን ባላቸው ድንጋዮች ተጠቅሞ ግንብ እንደመገንባት ነው። ድንጋዮቹ የተለያየ መጠን ያላቸው መሆኑ ሥራውን አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል። ያም ቢሆን ቀጥ ያለ ግንብ መገንባት ይቻላል። እኔም ከሌሎች ጋር በሰላም ተባብሬ መሥራት እንድችል አንዳንድ ማስተካከያዎችን አድርጌያለሁ።” ይህ እንዴት ያለ ግሩም አመለካከት ነው!
ጥሩ የሥራ አጋር የሆነ ሰው ተፈላጊነቱን እንዳያጣ በመስጋት፣ መረጃ ከማካፈል ወደኋላ አይልም
በጉባኤያችን ውስጥ የትብብር መንፈስ ለማሳየት የሚያስችሉ ምን አጋጣሚዎች አሉን? ከወንድሞቻችን ጋር አንድ ላይ በምናገለግልበት ጊዜ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን። ከእኛ ጋር በተመሳሳይ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከማይገኙ ወይም ከእኛ የተለየ የቤተሰብ ኃላፊነት ካለባቸው አስፋፊዎች ጋር እንድናገለግል እንመደብ ይሆናል። አብረውን የተመደቡት አስፋፊዎች አገልግሎታቸው ይበልጥ አስደሳች እንዲሆንላቸው ስንል የምናገለግልበትን መንገድ ለመቀየር ወይም እነሱ በለመዱት መንገድ ለማገልገል ፈቃደኞች እንሆናለን?
መሠረታዊ ሥርዓት 3፦ “ለማካፈል ዝግጁ” ሁኑ
ጥሩ የሥራ አጋር “ለማካፈል ዝግጁ” ነው። (1 ጢሞ. 6:18) ኢየሱስ ከአባቱ ጋር በሚሠራበት ወቅት ይሖዋ ምንም ነገር እንዳልደበቀው አስተውሎ መሆን አለበት። ይሖዋ “ሰማያትን ባዘጋጀ ጊዜ” ኢየሱስ ‘በዚያ ስለነበር’ ከእሱ መማር ችሏል። (ምሳሌ 8:27) ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ ራሱ ‘ከአባቱ የሰማውን ነገር’ ለደቀ መዛሙርቱ ለማካፈል ፈቃደኛ ነበር። (ዮሐ. 15:15) እኛም የይሖዋን ምሳሌ በመከተል፣ አብረውን ለሚሠሩት ሰዎች እውቀታችንን እና ተሞክሯችንን ለማካፈል ፈቃደኞች ልንሆን ይገባል። ጥሩ የሥራ አጋር የሆነ ሰው ተፈላጊነቱን እንዳያጣ በመስጋት፣ ጠቃሚ ወይም አስፈላጊ የሆነን መረጃ ከማካፈል ወደኋላ አይልም። እንዲያውም እሱ የተማራቸውን መልካም ነገሮች ለሌሎች ማካፈል ያስደስተዋል።
በተጨማሪም አብረውን ለሚሠሩት ሰዎች ማበረታቻ መስጠት እንችላለን። አንድ ሰው ያደረግነውን ጥረት ተመልክቶ ከልቡ ሲያመሰግነን ደስ አይለንም? ኢየሱስ የሥራ አጋሮቹን መልካም ጎን ጠቅሶ አመስግኗቸዋል። (ከማቴዎስ 25:19-23 እና ከሉቃስ 10:17-20 ጋር አወዳድር።) እንዲያውም ከእሱ “የበለጡ ሥራዎች” እንደሚሠሩ ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 14:12) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ታማኝ ሐዋርያቱን “እናንተ በፈተናዎቼ ከጎኔ ሳትለዩ ቆይታችኋል” በማለት አመስግኗቸዋል። (ሉቃስ 22:28) ይህን ማለቱ ምን ያህል ልባቸውን ነክቶት እና ለሥራ አነሳስቷቸው እንደሚሆን አስቡት! እኛም የሥራ ባልደረቦቻችንን የምናመሰግናቸው ከሆነ ይበልጥ ደስተኛ እንደሚሆኑ ጥያቄ የለውም፤ በሥራቸውም ይበልጥ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ።
ጥሩ የሥራ አጋር መሆን ትችላለህ
ካዮዴ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው ጥሩ የሥራ አጋር ለመሆን ፍጹም መሆን አይጠበቅበትም፤ ሆኖም የሥራ አጋሮቹ ደስ ብሏቸው እንዲሠሩና ሥራው ከባድ እንዳይሆንባቸው ያደርጋል።” አንተስ እንዲህ ዓይነት የሥራ አጋር ነህ? አብረውህ የሚሠሩትን ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ስለ አንተ ምን አመለካከት እንዳላቸው ለምን አትጠይቃቸውም? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከእሱ ጋር መሥራት ያስደስታቸው እንደነበረ ሁሉ ክርስቲያን ባልንጀሮችህም ከአንተ ጋር መሥራት የሚያስደስታቸው ከሆነ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን” ማለት ትችላለህ።—2 ቆሮ. 1:24