‘እውነትን ገዙ’!
“እውነትን ግዛ አትሽጣትም።” (ምሳሌ 23:23) ጠቢቡ ሰሎሞን ይህን ምክር ሰጥቷል። በአጠቃላይ እውነትን በተመለከተ እንዲህ ለማለት የሚቻል ቢሆንም ይህ አባባል ይበልጥ ተስማሚ የሆነው በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ነው። ይህ እውነት የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ ይችላል! (ዮሐንስ 17:3, 17) ሆኖም ይህ እውነት ያለ ዋጋ የሚገኝ አለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። አንድ ሰው ይህን እውነት ‘ለመግዛት’ ፈቃደኛ መሆን አለበት፤ ይህ ደግሞ እውነትን ለማግኘት ሲል አንዳንድ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረግ ወይም መተው አለበት ማለት ነው። (ከማቴዎስ 13:45, 46 ጋር አወዳድር።) አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ አይደሉም። ሆኖም በብዙ አገሮች የሚገኙ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ደፋር ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ዋጋ ቢጠይቅባቸውም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እየገዙ ነው።
ለምሳሌ ያህል በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በጋና የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ተመልከት። በሰኔ 1989 በዚህች አገር ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበሉና ይህን እውነት በትጋት ለሌሎች የሚያካፍሉ ከ34,000 በላይ ሰዎች ነበሩ። ከዚያም ለሕዝብ በሚሰጠው የምስክርነት ሥራ ላይ ሕጋዊ እገዳዎች ተጣሉ። የሆነ ሆኖ ሕግ ነክ ዕንቅፋቶች ቢኖሩም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ‘እውነትን መግዛታቸውን’ ቀጥለው ነበር። እገዳው በጥቅምት 31, 1991 የተነሳ ሲሆን ይህ ከሆነ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ማለትም በ1995 አጋማሽ ላይ በጋና የሚያገለግሉ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ወደ 46,104 ከፍ ብሏል! በዚህ ዓመት ደግሞ ቁጥሩ ከ52,800 በላይ ሆኗል።
ሰዎችን ወደ አምላክ ቃል እውነት የሳባቸው ነገር ምንድን ነው? አንዳንዶች ‘እውነትን ለመግዛት’ ሲሉ ምን መሥዋዕቶች መክፈል አስፈልጓቸዋል? ለዚህ መልስ እንዲሆነን የጋና ተወላጅ የሆኑ የሦስት ክርስቲያኖችን ተሞክሮ እንመልከት።
በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መሳብ
በቅድሚያ በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘውን ወጣት ሁኔታ እስቲ እንመልከት። አባቷ ቄስ ነበር፤ ያም ሆኖ ክርስቲያና የአባትዋን ሃይማኖት ለመተው ወሰነች። በምን ምክንያት? ለእውነት በነበራት ፍቅር የተነሳ ነው።
በአንድ ወቅት እንዲህ ስትል ተናግራ ነበር:- “ምሥክሮቹ ከቤት ወደ ቤት በሚያገለግሉበት ጊዜ ቤታችን ይመጡ ነበር። ከእነርሱ ጋር ለጥቂት ጊዜያት ከተወያየሁ በኋላ የሚያስተምሩት ነገር ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ያለው መሆኑን ተገነዘብኩ። ሥላሴን፣ እሳታማ ሲኦልን፣ የነፍስ አለመሞትንና በተለይ ደግሞ የእምነት ፈውስን በተመለከቱ ርዕሶች ላይ ጥያቄዎች አነሳሁ። እነዚህ መሠረተ ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኙ ናቸው የሚል ከፍተኛ እምነት ነበረኝ። ሆኖም ምሥክሮቹ እውነታው ይህ አለመሆኑን እንድገነዘብ ረዱኝ።”—በእነዚህ ርዕሶች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ለማወቅ እባክህ ማርቆስ 13:32፤ ሮሜ 6:23፤ ሥራ 10:40 እና 1 ቆሮንቶስ 13:8-10ን ተመልከት።
ይህች ወጣት በመቀጠል እንዲህ ብላለች:- “ከቤተሰቦቼ በይበልጥ ደግሞ ከአባቴ ጠንካራ ተቃውሞ ነበረብኝ። የተታለልኩ መስሎ ተሰማው። እኔ ግን ከይሖዋ ምሥክሮች የምማረው ነገር እውነት መሆኑን አውቄ ነበር። ትምህርቶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማሳየት አባቴን ለማስረዳት ሞከርኩ፤ እርሱ ግን ለማዳመጥ ፈቃደኛ አልነበረም። እንዲያውም ተቃውሞው እየከረረ መጣ።
“ሆኖም ከአቋሜ ፍንክች አላልኩም። በገነት ውስጥ ወደሚገኘው የዘላለም ሕይወት የሚያመራው ትክክለኛ እውቀት ብቻ መሆኑን ስላወቅሁ ይህን አጥብቄ ለመያዝ ቆርጬ ነበር። በአካባቢው የነበሩ ምሥክሮች ስለ ሚደርስብኝ ስደት ሲሰሙ እኔን በማበረታታትና የሚያስፈልጉኝን አንዳንድ ነገሮች በመስጠት ረዱኝ። ያደረጉልኝ ነገር በዮሐንስ 13:35 ላይ ‘እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ’ የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ እንድገነዘብ ረድቶኛል። የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛውን ሃይማኖት እንደሚከተሉ የነበረኝ እምነት ይበልጥ ተጠናከረ። ከጊዜ በኋላ ወላጆቼ ያደረግሁት ለውጥ እንደጠቀመኝ ሲገነዘቡ ባዩት ለውጥ ከመደሰታቸውም በላይ ለእኔ የነበራቸው አመለካከት ተለወጠ፤ አልፎ ተርፎም ታላቅ ወንድሜን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኑት አባቴ ምሥክሮቹን ጠይቋቸዋል!”
እውነትን ፈትኖ መያዝ
የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች ላሳደጓቸው አንዳንድ ልጆችም ‘እውነትን መግዛት’ ተፈታታኝ ነው። አንዳንድ ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አቅልለው ይመለከቱታል። እውነትን የራሳቸው ካላደረጉት እምነታቸው ደካማና ሥር ያልሰደደ ይሆናል። (ከማቴዎስ 13:20, 21 ጋር አወዳድር።) በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው የጋና ተወላጅ የሆነው ናትናኤል ገና በልጅነቱ እንዴት ‘እውነትን እንደገዛ’ ይናገራል።
“ወላጆቼ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተማሩኝ ገና ከሕፃንነቴ ጀምሮ ነበር” በማለት ያስታውሳል። “እያደግሁ ስሄድ በስብከቱ ሥራ አብሬአቸው መሳተፍ ብጀምርም ምሥክር ለመሆን ከልቤ ወስኜ አላውቅም ነበር። ውሎ አድሮ ነገሮቹን በግሌ መመርመር እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ።
“በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ እንጂ ሌላ የሃይማኖት ቅዱስ መጽሐፍ እንዳልሆነ አሳማኝ ነጥብ ማግኘት ነበረብኝ። መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል የተፈጸሙ ግልጽ የሆኑ በርካታ ትንቢቶችን የያዘ ብቸኛ ቅዱስ መጽሐፍ መሆኑን በግል ጥናት አማካኝነት ተገነዘብኩ። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ሳይንሳዊ እውነቶች እንደያዘ፣ ለምሳሌ ያህል ምድር ‘ያለ አንዳች ድጋፍ መንጠልጠልዋን’ እንደሚናገር አወቅሁ። (ኢዮብ 26:7) እነዚህ ቃላት የተጻፉት ሳይንቲስቶች እኛ ስላለንበት ሥርዓተ ፀሐይ ከማወቃቸው ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ነበር። እነዚህን ነገሮች እንዲጽፉ ሰዎችን በመንፈስ ሊያነሳሳ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው!a
“ቀጥሎ መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸውን እውነቶች የሚያስተምርና በተግባር የሚያውል የትኛው ሃይማኖታዊ ድርጅት እንደሆነ ለማወቅ ፈለግሁ። አብዛኞቹ ሃይማኖቶች እሳታማ ሲኦልን፣ ሥላሴንና ከሞት በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ መኖሯን ያስተምራሉ። ሆኖም እነዚህ መሠረተ ትምህርቶች ለእኔ ትርጉም አልሰጡኝም። ለመቅጣት ብሎ የልጁን እጅ የፈላ ውኃ ውስጥ የሚከት አባት ክፉ አይደለምን? ብዬ በምክንያታዊነት አሰብኩ። ታዲያ አፍቃሪ የሆነው አምላክ ልጆቹን እሳታማ ሲኦል ውስጥ ጥሎ እንዲሰቃዩ እንዴት ያደርጋቸዋል? ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ‘የኃጢአት ደሞዝ ሞት’ እንጂ እሳታማ ሲኦል አለመሆኑን ከሚናገሩት እንደ ሮሜ 6:23 ከመሳሰሉት ጥቅሶች ጋር የሚስማማ ትምህርት ያስተምራሉ። ይህን ትርጉም ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
“ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች አባሎቻቸው ባጠቃላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደረጃ ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ እንደሚጠብቁባቸውና የንስሐ መንፈስ ሳያሳዩ ኃጢአት መስራታቸውን የሚቀጥሉትን እንደሚያስወግዱ ተገነዘብኩ። ይህን ሁሉ ከተመለከትኩ በኋላ እውነት የሚገኘው በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ መሆኑን ከማረጋገጤም በላይ ከእነርሱ እንደ አንዱ ለመሆን በግል ወሰንኩ። ተጠምቄ ምሥክር ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት በትጋት ጣርኩ።”—1 ቆሮንቶስ 5:11-13
በክርስቲያን ወላጆች ያደጉ ልጆችም እንኳ ሳይቀር ‘እውነትን መግዛት’ እንደሚኖርባቸው የናትናኤል ተሞክሮ በግልጽ ያሳያል። የጉባኤ ስብሰባዎችን እንዲያው ለነገሩ በመሰብሰብ ብቻ ማብቃት የለባቸውም። ልክ እንደ ጥንቶቹ የቤርያ ሰዎች ‘ነገሩ እንደተባለው መሆኑን ለማረጋገጥ ዕለት ዕለት ቅዱሳን መጻሕፍትን መመርመር’ ይኖርባቸዋል። (ሥራ 17:11) ይህን ለማድረግ ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ጠንካራና ጽኑ እምነት ያስገኛል።—ከኤፌሶን 3:17-19 ጋር አወዳድር።
በሐሰት ሃይማኖት ግራ መጋባት
ጋናዊ የሆነው ጋድዊን ከፕሪስባይቴርያን ቤተ ክርስቲያንና አባል ከነበረበት የወንድማማች ማኅበር በወጣበት ጊዜ እድሜው 70 ዓመት አካባቢ ነበር። “በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የሚታዩ አንዳንድ የማልስማማባቸው ነገሮች ነበሩ” በማለት ተናግሯል። “ለምሳሌ ያህል እርስ በርስ የከረረ ግጭት ብዙ ጊዜ ይከሰታል። እንዲያውም አንዳንዴ ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር ፖሊሶች የግድ የሚያስፈልጉበት ሁኔታ አለ! ይህ ዓይነቱ ድርጊት የክርስቶስ ተከታዮች ነን ለሚሉ ሰዎች ተገቢ መስሎ አልታየኝም። ከዚያም በእኔና በአንድ የእምነት ባልደረባዬ መካከል ችግር ተፈጠረ። ጉዳያችን ፍርድ ቤት ከታየ በኋላ ሰውየው ጥፋተኛ ሆኖ ስለተገኘ ተፈረደበት። ሆኖም የቤተ ክርስቲያኑ ቄስ ለሰውየው በመወገን በጠቅላላ ጉባኤው ፊት እኔን ለማውገዝ ሞከረ! ስለ ጉዳዩ የተሰማኝን ስሜት በግልጽ ነገርኩትና ሁለተኛ ላልመለስ ቤተ ክርስቲያኑን ትቼ ወጣሁ።
“ይህ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቴ መጡ። በመጀመሪያ ስለ አምላክ የሚናገሩ ሰዎችን ላለማባረር ስል ብቻ ዝም ብዪ ሰማኋቸው። ሆኖም ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ፕሪስባይቴርያን ብሆንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የማላውቃቸው ነገሮች እንዳሉ ማስተዋል ጀመርኩ። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖርን ተስፋ እንደሚገልጽ አላውቅም ነበር።b በተጨማሪም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ መገኘት በጀመርኩበት ጊዜ ሥርዓታማነታቸውና በተለይ ደግሞ በመካከላቸው የሚገኙት ወጣቶች አለባበስና የፀጉር አያያዝ በጣም ማረከኝ። እነዚህ በትክክል በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመሩ ሰዎች ናቸው!”
አሁንም ቢሆን ‘እውነትን መግዛት’ በሕይወቱ ውስጥ አንዳንድ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቁ ማስተካከያዎች ማድረግን ጠይቆበታል። ጋድዊን እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “የአንድ የወንድማማቾች ማኅበር አባል ነበርኩ። ምንም እንኳ ይህ ማኅበር የሚታወቀው ለአባሎቹ እርዳታ እንደሚሰጥ ቢሆንም በራስ ቅልና በአጥንቶች መጠቀምና መናፍስትን መለማመንን የሚጨምር ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት እንደሚከናወን አስተዋልኩ። እነዚህ መናፍስት በመንፈሳዊ ለማደግ ፈልገው ከእነርሱ ጋር የሚገናኙትን ሰዎች ይረዳሉ ተብሎ ይታመን ነበር።
“መናፍስታዊ ሥራዎች አንድን ሰው በሰይጣንና እርሱ በሚቆጣጠራቸው ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ተጽዕኖ ስር እንዲያዝ ስለሚያደርጉ ይሖዋ አምላክ በማንኛውም መናፍስታዊ ሥራ ተሳትፎ ማድረግን እንደሚጠላ ከጥናቴ ልገነዘብ ቻልኩ።c ምሥጢራዊ አምልኮውን እየተከተልኩ የማኅበሩ አባል ሆኜ ልቀጥል ወይስ ከእዚያ በመውጣት ይሖዋን ላስደስት? ከማኅበሩ መውጣትን መረጥሁ። ማኅበሩ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ የምለብሰውን የተለየ ልብስ ጨምሮ በሃይማኖቱ እጠቀምባቸው የነበሩትን ሌሎች የግል መገልገያዎቼን አቃጠልኩ። ኢየሱስ ‘እውነት አርነት ያወጣችኋል’ ብሎ በተናገረ ጊዜ የሰጠውን ተስፋ እውነተኝነት ቀመስኩ! (ዮሐንስ 8:32) ባሁኑ ጊዜ የተማርኳቸውን ነገሮች ለሌሎች በደስታ እያካፈልኩ እገኛለሁ። ባደረግሁት ውሳኔ ምንም የምጸጸትበት ነገር የለም።”
በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ‘እውነትን ለመግዛት’ ሲሉ በተመሳሳይ መንገድ ከፍተኛ መሥዋዕቶችን ከፍለዋል። ከላይ ተሞክሯቸው እንደተጠቀሰው ሦስት ክርስቲያኖች እነርሱም ባደረጉት ለውጥ የሚጸጸቱበት ምንም ነገር የለም። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ‘እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እንዲሰበስቡ’ አስችሏቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:18, 19) “እውነትን ከገዛህ” ‘እውነተኛውን ሕይወት’ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጋር ተያይዘው የሚመጡትንም በረከቶች ለዘላለም ማግኘት ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።
b ለምሳሌ ያህል መዝሙር 37:9-11, 29ን ተመልከት።
c ዘዳግም 18:10-12 እና ገላትያ 5:19-21ን ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ናትናኤል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጋድዊን