ድሃ ግን ሀብታም እንዴት?
ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት አንድ ጠቢብ ሰው ድሃ እንዳይሆን ጸልዮ ነበር። እንዲህ ያለ ልመና ያቀረበው ለምን ነበር? ድህነቱ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና አደጋ ላይ ወደሚጥሉ ዝንባሌዎችና ድርጊቶች እንዳይመራው ስለፈራ ነው። ይህንንም ከሚከተለው ንግግሩ በግልጽ መረዳት ይቻላል:- “የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ . . . ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፣ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።” —ምሳሌ 30:8, 9
ታዲያ ይህ ማለት አንድ ድሃ የሆነ ሰው አምላክን የታመነ ሆኖ ማገልገል አይችልም ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም! ባለፉት የታሪክ ዘመናት ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ድህነት የሚያስከትለው ፈታኝ ሁኔታ ቢኖርባቸውም ለእሱ ያላቸውን የጸና አቋም አሳይተዋል። በአጸፋው ይሖዋ በእርሱ ላይ የሚታመኑትን ሰዎች ይወዳቸዋል፤ የሚያስፈልጋቸውንም ያሟላላቸዋል።
ጥንት የነበሩት የታመኑ ሰዎች
ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ የተቸገረባቸው ጊዜያት ነበሩ። (2 ቆሮንቶስ 6:3, 4) ከዚህም ሌላ በዙሪያችን ‘እንደ ደመና ካሉት ብዙ ምሥክሮች’ መካከል አንዳንዶቹን አስመልክቶ “የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ . . . በምድረ በዳና በተራራ፣ በዋሻና በምድር ጒድጓድ ተቅበዘበዙ” ሲል ተናግሯል።—ዕብራውያን 11:37, 38፤ 12:1
ከእነዚህ የታመኑ ሰዎች መካከል አንዱ ነቢዩ ኤልያስ ነው። ሦስት ዓመት ተኩል በቆየው ድርቅ ወቅት ይሖዋ ያለማቋረጥ መግቦታል። በመጀመሪያ ቁራዎች እንጀራና ሥጋ እንዲያመጡለት አድርጓል። (1 ነገሥት 17:2-6) ከዚያም ይሖዋ ለኤልያስ ምግብ ታዘጋጅ የነበረችው መበለት ያላት ዱቄትና ዘይት በተዓምር እንዳያልቅ አደረገ። (1 ነገሥት 17:8-16) ምግቡ የቅንጦት ባይሆንም ነቢዩን፣ መበለቲቱንና ልጇን በሕይወት እንዲቆዩ አስችሏቸዋል።
ይሖዋ ነቢዩ ኤርምያስንም እንዲሁ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር በነበረበት ወቅት ደግፎታል። ሰዎች “እየፈሩ እንጀራን በሚዛን” ይበሉ በነበረበት ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በከበቡበት ወቅት ኤርምያስ በሕይወት ተርፏል። (ሕዝቅኤል 4:16) ከጊዜ በኋላ በከተማው ውስጥ የነበረው ረሃብ በጣም እየከፋ በመሄዱ አንዳንድ ሴቶች የገዛ ልጆቻቸውን ሥጋ እስከ መብላት ደርሰዋል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:20) ኤርምያስ በድፍረት በመስበኩ ምክንያት በግዞት ቤት ቢከተትም ይሖዋ “ዳቦ ከከተማይቱ ጨርሶ እስከጠፋም ድረስ ከዳቦ መጋገሪያዎች አንድ ዳቦ በየቀኑ” እንዲሰጠው አድርጓል።—ኤርምያስ 37:21 የ1980 ትርጉም
በመሆኑም ኤርምያስም እንደ ኤልያስ የሚያገኘው ነገር ጥቂት ብቻ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች ዳቦም ሁሉ ከኢየሩሳሌም ከጠፋ በኋላ ኤርምያስ ምን ይመገብ ወይም ምን ያህል ጊዜ ይበላ እንደነበረ አይነግሩንም። ሆኖም ይሖዋ ይደግፈው እንደነበርና ያን አሠቃቂ የረሃብ ዘመን በሕይወት እንዳለፈ እናውቃለን።
ዛሬም ድህነት በሁሉም የዓለም ክፍል የሚታይ ነገር ነው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ መሠረት ከፍተኛ የድሆች ቁጥር ያለው በአፍሪካ ነው። በ1996 የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫ “ከመላው አፍሪካውያን መካከል ቢያንስ ግማሽ የሚሆኑት ድህነት የደቆሳቸው ናቸው” ብሏል። እያደር እየከፋ የሚሄድ አስቸጋሪ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ቢኖርም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ አፍሪካውያን አምላክ እንደሚደግፋቸው በመተማመን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ ሥራ ላይ በማዋል የታመኑ ሆነው እያገለገሉት ነው። በችግር ከተሞላው ዓለማችን ከአንደኛው ክፍል የመጡትን ጥቂት ምሳሌዎች ተመልከት።
ሐቀኛ ሆኖ መኖር
በናይጄሪያ የሚኖረው ማይክልa በግብርና ሥራ የሚተዳደርና የስድስት ልጆች አባት ነው። ማይክል እንዲህ ይላል:- “ለቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት የምትችልበት ገንዘብ ሳይኖርህ ሐቀኛ መሆን በጣም አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ ሐቀኝነቴን እንዳጎድል የሚፈትን ነገር ሲገጥመኝ ኤፌሶን 4:28 ላይ የሚገኘውን ‘የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፣ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጐደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም’ የሚለውን ጥቅስ አስታውሳለሁ። በመሆኑም ፈተና በሚገጥመኝ ጊዜ ‘ይህ የደከምኩበት ገንዘብ ነውን?’ በማለት ራሴን እጠይቃለሁ።”
ማይክል ጨምሮ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ለምሳሌ ያህል አንድ ቀን በመንገድ ላይ ስሄድ ከአንድ ሞተር ብስክሌት ጀርባ ቦርሳ ሲወድቅ አየሁ። ሞተረኛውን ላስቆመው ስላልቻልኩ ቦርሳውን አንስቼ ሳየው በውስጡ ብዙ ገንዘብ ነበረው! ቦርሳው ውስጥ ባገኘሁት መታወቂያ አማካኝነት ቦርሳውን ለባለቤቱ መለስኩለት።”
የመንፈስ ጭንቀትን መዋጋት
በሰሜን አፍሪካ የሚኖር አንድ ሰው እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “ድህነት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ብርሃኑንና በአካባቢው በነፃነት የሚዘዋወሩትን ሰዎች ብቻ እያየ ነገር ግን ለእርዳታ መጮህ ወይም መውጫ መሰላል መጠየቅ ከማይችል ሰው [ጋር ይመሳሰላል]።” ድህነት የመንፈስ ጭንቀትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ቢያስከትል ብዙም አይደንቅም! ሌላው ቀርቶ የአምላክ አገልጋዮች እንኳ የሌሎች ሰዎችን ብልጽግና በማየት የጸና አቋም ይዞ መኖር እርባና የሌለው ነገር እንደሆነ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። (ከመዝሙር 73:2-13 ጋር አወዳድር።) አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቶቹን ስሜቶች መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው?
በምዕራብ አፍሪካ የሚኖረው ፒተር ለ19 ዓመታት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ካገለገለ በኋላ ጡረታ ይወጣል። አሁን ኑሮውን የሚገፋው ከጡረታ በሚያገኛት ጥቂት ገንዘብ ነው። እንዲህ ብሏል:- “ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በሚሰማኝ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ያነበብኳቸውን ነገሮች አስታውሳለሁ። ይህ አሮጌ ሥርዓት በቅርቡ የሚያልፍ ሲሆን እኛ ደግሞ የተሻለ ሥርዓት እየጠበቅን ነው።
“እንዲሁም ‘በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ [ሰይጣንን] ተቃወሙት’ የሚለውን 1 ጴጥሮስ 5:9 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አስባለሁ። እንግዲያውስ መከራ የሚደርስብኝ እኔ ብቻ አይደለሁም። እነዚህ ማሳሰቢያዎች ተስፋ የሚያስቆርጡና የሚያስጨንቁ ሐሳቦችን ለማስወገድ ረድተውኛል።”
“ከዚህም ሌላ” ይላል ፒተር “ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ ብዙ ተአምራት ፈጽሟል። ሆኖም ለማንም ሰው ቁሳዊ ብልጽግና አልሰጠም። ታዲያ እኔንስ ሀብታም እንዲያደርገኝ የምጠብቅበት ምን ምክንያት አለ?”
ጸሎት ያለው ኃይል
አፍራሽ አስተሳሰቦችን ለመዋጋት የሚያስችለን ሌላው መንገድ ደግሞ በጸሎት ወደ ይሖዋ አምላክ መቅረብ ነው። ማሪ በ1960 የይሖዋ ምሥክር ስትሆን ቤተሰቦቿ ካዷት። ዛሬ በነጠላነት የምትኖረውና በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ማሪ አቅመ ደካማ ከመሆኗም ሌላ ኑሮዋ ዝቅተኛ ነው። ያም ሆኖ በክርስቲያናዊ አገልግሎት በቅንዓት ትካፈላለች።
ማሪ እንዲህ ብላለች:- “የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲያድርብኝ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። ከእርሱ የበለጠ ሊረዳኝ የሚችል ሰው እንደሌለ አውቃለሁ። ይሖዋ የሚታመኑበትን ሰዎች እንደሚረዳ ተምሬአለሁ። ‘ጎለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም’ የሚሉትን በመዝሙር 37:25 ላይ የሚገኙትን የንጉሥ ዳዊት ቃላት ሁልጊዜ አስባለሁ።
“እንዲሁም መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡት በዕድሜ የገፉ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ተሞክሮዎች ያበረታቱኛል። ይሖዋ አምላክ እነርሱን ረድቷቸዋል፤ እኔንም መርዳቱን እንደሚቀጥል አውቃለሁ። ፉፉ [ከካሳቫ ተክል የሚሠራ ምግብ ነው] እየሸጥኩ የምተዳደርባትን ሥራዬን ባርኮልኛል፤ የዕለት ጉርሴን አገኛለሁ። አንዳንድ ጊዜ እጄ ላይ ምንም ገንዘብ ሳይኖር ይቀርና ግራ ገብቶኝ ምን እንደማደርግ ሳስብ ‘እህት፣ እባክሽ ይህች ለአንድ ነገር ትሆንሻለች’ የሚለኝ ሰው ይልክልኛል። ይሖዋ አሳፍሮኝ አያውቅም።”
ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከፍ ያለ ግምት መስጠት
የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትን ከፍ አድርገው ይመለከታሉ፤ ድሆችም ቢሆኑ የሚያደርጉት ነገር ከዚህ የተለየ አይደለም። የስልሳ ዓመቱ ጃን በጉባኤ ውስጥ አቅኚ (የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪ) እና የጉባኤ አገልጋይ ነው። 13 ቤተሰቦች በጋራ በሚኖሩበት ሊፈርስ የደረሰ በሚመስል ባለ ሁለት ደርብ ቤት ውስጥ ይኖራል። እርሱ የሚያድረው በአንደኛው ፎቅ ኮሪደር ላይ በኮምፖንሳቶ በተከለለች ከፍል ውስጥ ነው። በክፍሉ ውስጥ ሁለት አሮጌ ወንበሮችና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች የተቆለሉበት አንድ ጠረጴዛ አለ። የሚተኛው በሰሌን ምንጣፍ ላይ ነው።
ጃን ዳቦ በመሸጥ በቀን አንድ ዶላር ያህል ያገኝ የነበረ ሲሆን በኋላ ስንዴ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ሲታገድ መተዳደሪያ ሥራውን አጣ። ጃን እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎቹ አስቸጋሪ ይሆኑብኛል፤ ሆኖም በአቅኚነቴ ቀጥያለሁ። ደጋፊዬ ይሖዋ ነው። በጉባኤ ያሉት ወንድሞች በጣም ተባባሪ ቢሆኑም የትኛውም ሰው እንዲረዳኝ ወይም እንዲመግበኝ ሳልጠብቅ ያገኘሁትን ሥራ ሁሉ እሠራለሁ። ወንድሞች ሥራ በማፈላለግ ይረዱኛል፤ አንዳንድ ጊዜም በስጦታ መልክ ገንዘብ ይሰጡኛል።
“መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎችን የማነብበት ጊዜ እመድባለሁ። ማለዳ ቤቱ ፀጥ በሚልበት ወቅት ተነስቼ አጠናለሁ፤ እንዲሁም መብራት ካለ ማታ እያመሸሁ አነባለሁ። በግል ጥናቴ መቀጠል እንዳለብኝ አውቃለሁ።”
ልጆችን ለሕይወት እንዲበቁ ማሠልጠን
ሚስቱ በሞት የተለየችው ዳንኤል ስድስት ልጆች አሉት። በ1985 ለ25 ዓመታት ሲሠራበት ከነበረበት መሥሪያ ቤት ቢወጣም ሱቅ ውስጥ መሥራት ጀመረ። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ቤተሰባችን የኢኮኖሚ ችግር አለበት። አሁን የምንመገበው በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በአንድ ወቅት ለሦስት ቀናት እህል ሳንቀምስ ቆይተናል። ሕይወታችንን ለማቆየት ስንል ውኃ ከመጠጣት ሌላ አማራጭ አልነበረንም።”
ዳንኤል በጉባኤው ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። “ከክርስቲያን ስብሰባዎች ፈጽሞ ቀርቼ አላውቅም፤ እንዲሁም ራሴን በቲኦክራሲያዊ ሥራዎች አስጠምዳለሁ” በማለት ተናግሯል። “በመንግሥት አዳራሹ አካባቢ የሚሠራ ማንኛውም ዓይነት ሥራ ካለ ሁልጊዜ በዚያ እገኛለሁ። ነገሮች ዓይናቸውን አፍጥጠው ሲመጡ በዮሐንስ 6:68 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ጴጥሮስ ለኢየሱስ የተናገራቸውን ‘ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን?’ የሚሉትን ቃላት አስታውሳለሁ። ይሖዋን ማገልገል ባቆም ወዴት እሄዳለሁ? በሮሜ 8:35-39 ላይ የምናገኛቸው የጳውሎስ ቃላትም ከአምላክና ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል ነገር እንደሌለ ስለሚናገሩ በቆራጥነት ወደፊት እንድገፋ ያበረታቱኛል። በልጆቼ ልብ ውስጥ የምኮተኩተውም ዝንባሌ ይኸው ነው። ይሖዋን ፈጽሞ መተው እንደሌለብን ሁልጊዜ እነግራቸዋለሁ።” ዳንኤል ያለው ቅንዓትና በቤታቸው የሚያካሂዱት ቋሚ የሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በልጆቹ ላይ በጎ የሆነ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የሰጪነት መንፈስ
አንድ ሰው በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማራመድ የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ አይችሉም ብሎ ያስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሐቁ ከዚህ የተለየ ነው። (ከሉቃስ 21:1-4 ጋር አወዳድር።) ጋና ውስጥ በግብርና የሚተዳደሩ አንዳንድ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ፍላጎቶች ለማራመድ እንዲያግዝ በማሰብ ከእርሻ መሬታቸው ከፊሉን ለብቻ ከልለዋል። ከተከለለው የእርሻ መሬት የሚገኘው ምርት ተሸጦ ገንዘቡ ለዚያ ዓላማ ብቻ ይውላል፤ ይህም በአካባቢው ባለው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ መዋጮ ማድረግን ይጨምራል።
በማዕከላዊ አፍሪካ የምትኖረው ጆዋን አቅኚ ሆና ታገለግላለች። ሽባ የሆነውን ባሏንና በእርሷ ሥር ያሉትን ሌሎች አራት ሰዎች ለማስተዳደር ስትል ዳቦ ትሸጣለች። ጉባኤዋ ለመንግሥት አዳራሹ የሚሆን አግዳሚ ወንበር ባስፈለገው ጊዜ የጆዋን ቤተሰብ በቤት ውስጥ የነበረውን ገንዘብ በሙሉ ለመለገስ ተስማማ። ይህንም በማድረጋቸው በእጃቸው ምንም ገንዘብ አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ቀን ከተበደረ ረጅም ጊዜ የሆነው አንድ ሰው ተስፋ ቆርጠው ትተውት የነበረውን ገንዘብ መለሰላቸው!
ጆዋን ሁልጊዜ ደስተኛ ናት፤ ለገንዘብ ከልክ በላይ አትጨነቅም። “ሁኔታዬን ለይሖዋ በጸሎት እነግረውና ወደ አገልግሎት እወጣለሁ። በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ሆኖም ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያሟላልን እንገነዘባለን።”
ታታሪ መሆን
የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር ተለይተው ይታወቃሉ። (ዮሐንስ 13:35) ገንዘብ ያላቸው ወንድሞች ችግር ላይ ያሉትን መሰል ክርስቲያኖች ይረዳሉ። ብዙውን ጊዜ የሚረዷቸው በስጦታ መልክ አንዳንድ ጊዜም ደግሞ ሥራ በማስገባት ነው።
በኮንጎ የሚኖረው ማርክ የሥጋ ደዌ በሽታ አለበት። በሽታው የእግሮቹንና የእጆቹን ጣቶች አበላሽቷቸዋል። በመሆኑም የሚሄደው በምርኩዝ ነው። ማርክ ይሖዋን ለማገልገል ሲወስን በሕይወቱ ከፍተኛ ለውጦችን ማድረግ ጀመረ። ቀደም ሲል ያደርግ እንደነበረው ምግቡን ለማግኘት ከመለመን ይልቅ ለምግብ የሚሆነውን ነገር መትከል ጀመረ። ከዚህም ሌላ ጡብ እየሠራ ይሸጣል።
ማርክ የአካል ችግር ቢኖርበትም በትጋት መሥራቱን ቀጠለ። ከጊዜ በኋላ መሬት ገዛና መለስተኛ ቤት ሠራ። በዛሬው ጊዜ ማርክ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ሲሆን በሚኖርበት ከተማም የተከበረ ሰው ሆኗል። አሁን ችግር ያለባቸውን ሌሎች ሰዎች ይረዳል።
እርግጥ ነው በብዙ ቦታዎች ሥራ የማግኘቱ አጋጣሚ በጣም ጠባብ ይመስላል። በማዕከላዊ አፍሪካ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግል አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እዚህ ብዙ ወንድሞች ሥራ የላቸውም። አንዳንዶቹ የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር ይጥራሉ፤ ግን ይህም ቢሆን አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቹ ምንም ሠራን ምን ከችግራችን መላቀቅ ካልቻልን አቅኚ ሆነን ቁሳዊ ጥቅማችንን ብንሰዋ ይሻላል ብለው አስበዋል። ይህንንም በማድረጋቸው ብዙዎቹ በጥቂት ክፍያ ወይም አለምንም ክፍያ ከሚሠሩት ሥራ ይበልጥ በእጅጉ ተባርከውበታል።”
ይሖዋ ሕዝቡን ይደግፋል
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለራሱ ሲናገር “ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፣ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” ብሏል። (ሉቃስ 9:58) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ “እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፣ እንጠማለን፣ እንራቆታለን፣ እንጐሰማለን፣ እንከራተታለን” በማለት ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 4:11
ኢየሱስና ጳውሎስ ይበልጥ በተሟላ መንገድ አገልግሎታቸውን ማከናወን ይችሉ ዘንድ በመጠነኛ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሥር መኖርን መርጠዋል። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች አማራጭ በማጣታቸው ምክንያት በድህነት ይኖራሉ። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ያደርጋሉ፤ አምላክንም በቅንዓት ለማገልገል ይጣጣራሉ። “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ [ቁሳዊ ነገሮች] ይጨመርላችኋል” ሲል ኢየሱስ የሰጠውን ማረጋገጫ በሕይወታቸው ውስጥ ሲሠሩበት በይሖዋ ዘንድ እጅግ የተወደዱ እንደሚሆኑ ያውቃሉ። (ማቴዎስ 6:25-33) ከዚህም በላይ የድህነት ኑሮ የሚገፉት እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ‘የይሖዋ በረከት ባለጠጋ እንደምታደርግ’ እርግጠኞች ናቸው።—ምሳሌ 10:22
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተለውጠዋል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘የቃሉ አድራጊዎች’ እነማን ናቸው?
በ1994 የተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት እንደሚጠቁመው 96 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን “በአምላክ ወይም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ባለ አንድ መንፈስ ያምናሉ።” ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት “ከሕዝብ ብዛት አንጻር ሲታይ ከማንኛውም ሌላ አገር ይበልጥ ከፍተኛ የአብያተ ክርስቲያናት ቁጥር ያለው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ” መሆኑን ገልጿል። ይህን የመሰለ የሃይማኖተኛነት መልክ ቢያሳዩም የሕዝብ አስተያየት በማሰባሰብ የብዙ ዓመት ልምድ ያካበቱት ጆርጅ ጋለፕ ጁንየር እንደሚሉት “ሐቁ አብዛኞቹ አሜሪካውያን ምን እንደሚያምኑና ለምን እንደሚያምኑ አለማወቃቸው ነው።”
በብዙዎቹ ሰዎች ሃይማኖታዊ እምነቶችና በድርጊቶቻቸው መካከል ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን ስታትስቲካዊ መረጃዎች ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል ጸሐፊው ጀፈሪ ሺለር እንደተናገሩት “ከፍተኛ ወንጀል የሚፈጸምባቸው የአገሪቱ ግዛቶች ሃይማኖታዊ እምነቶችና ልማዶች እጅግ በስፋት የሚካሄዱባቸው ቦታዎች መሆናቸውን የማኅበራዊ ጉዳይ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።”
ይህ ምንም ሊያስገርመን አይገባም። ለምን? ምክንያቱም ገና በአንደኛው መቶ ዘመን እንኳን ሐዋርያው ጳውሎስ መሰል ክርስቲያኖችን ‘እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ከሚናገሩ ዳሩ ግን በሥራቸው ከሚክዱት’ ሰዎች እንዲጠበቁ አሳስቧቸዋል። (ቲቶ 1:16) በተጨማሪም ጳውሎስ ‘የመጨረሻው ቀን’ ‘የአምልኮ መልክ ባላቸው ኃይሉን ግን በካዱ’ ሰዎች እንደሚሞላ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ ነግሮታል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 5
እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን “ሂዱና አሕዛብን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን የኢየሱስን ትእዛዝ ለመከተል የተቻላቸውን ያህል ይጥራሉ። (ማቴዎስ 28:19) በዚህ መንገድ ‘ቃሉን የሚያደርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ አይሆኑም።’—ያዕቆብ 1:22
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዓለም ዙሪያ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከፍ ያለ ግምት ያላቸው ሰዎች አሉ