ፍጥረት የይሖዋን ጥበብ በግልጽ ያሳያል
“የማይታዩት . . . ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።”—ሮም 1:20
1. በዛሬው ጊዜ የዓለም ጥበብ ብዙዎችን ለምን ዳርጓቸዋል?
በዛሬው ጊዜ “ጥበብ” የሚለው ቃል ያላግባብ ሲሠራበት ይታያል። አንድ ሰው ብዙ እውቀት ስላካበተ ብቻ ጠቢብ እንደሆነ ይነገራል። ይሁን እንጂ በዓለም ላይ አዋቂዎች የሚባሉት ሰዎች የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ የሚያስችል አስተማማኝ መመሪያ መስጠት አይችሉም። እንዲያውም እንዲህ ያሉ ግለሰቦች የሚሰጡትን መመሪያ የሚከተሉ ሰዎች ‘በማዕበል የሚነዱ ይመስል በማንኛውም የትምህርት ነፋስ የሚንገዋለሉና ወዲያና ወዲህ የሚሉ’ ይሆናሉ።—ኤፌ. 4:14
2, 3. (ሀ) ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ከአምላክ የሚገኘው ጥበብ ከዓለም ጥበብ የሚለየው እንዴት ነው?
2 ከይሖዋ አምላክ የሚመነጨውን እውነተኛ ጥበብ የሚያገኙ ሰዎች የሚመሩት ሕይወት ግን ምንኛ የተለየ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” እንደሆነ ይነግረናል። (ሮም 16:27) ይሖዋ የእያንዳንዱን ፍጥረት አሠራርና ታሪክ ጨምሮ ስለ አጽናፈ ዓለም ሁሉን ነገር ጠንቅቆ ያውቃል። ሰዎች ለሚያካሂዱት ምርምር መሠረት የሚሆኑትን የተፈጥሮ ሕጎች የደነገገው ይሖዋ ነው። በመሆኑም የሰው ልጆች በምርምር የሚደርሱባቸው ግኝቶችም ሆኑ የላቀ ግምት የሚሰጣቸው ሰብዓዊ ፍልስፍናዎች ይሖዋን አያስደንቁትም። የአምላክ ቃል “የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት ነው” በማለት ይናገራል።—1 ቆሮ. 3:19
3 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ “ጥበብን ይሰጣል” ይላል። (ምሳሌ 2:6) ከሰብዓዊ ፍልስፍና በተለየ መልኩ ከአምላክ የሚገኘው ጥበብ ግራ የሚያጋባ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ የሚንጸባረቅበት እንዲሁም በትክክለኛ እውቀትና በማስተዋል ላይ የተመሠረተ ነው። (ያዕቆብ 3:17ን አንብብ።) ሐዋርያው ጳውሎስ በይሖዋ ጥበብ እጅግ ከመደነቁ የተነሳ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!” (ሮም 11:33) ይሖዋ በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ በመሆኑ ሕጎቹ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ሕይወታችንን ለመምራት እንደሚረዱን እርግጠኞች ነን። ደግሞስ ደስተኞች እንድንሆን የሚያስችለን ምን እንደሆነ ከይሖዋ በተሻለ የሚያውቅ ማን አለ!—ምሳሌ 3:5, 6
“ዋና ሠራተኛ” የሆነው ኢየሱስ
4. የይሖዋን ጥበብ ማስተዋል የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
4 የይሖዋ ጥበብ እንዲሁም ተወዳዳሪ የሌላቸው ሌሎች ባሕርያቱ በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ በግልጽ ይታያሉ። (ሮም 1:20ን አንብብ።) የይሖዋ ፍጥረታት ከትልቅ እስከ ትንሽ የተለያዩ ባሕርያቱን ያንጸባርቃሉ። በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ማንኛውንም ነገር ብንመለከት ፈጣሪያችን እጅግ ጠቢብና አፍቃሪ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች እናገኛለን። አምላክ የሠራቸውን ነገሮች በመመርመር ስለ እሱ ብዙ መማር እንችላለን።—መዝ. 19:1፤ ኢሳ. 40:26
5, 6. (ሀ) ከይሖዋ ጋር በፍጥረት ሥራ ላይ የተካፈለው ማን ነው? (ለ) ከዚህ ቀጥለን ምን ነገሮችን እንመረምራለን? ለምንስ?
5 ይሖዋ ‘ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት’ ጊዜ ብቻውን አልነበረም። (ዘፍ. 1:1) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ግዑዛን ነገሮችን ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት አንድ መንፈሳዊ አካል እንደፈጠረ ይጠቁማል። “ሌሎች ነገሮች በሙሉ” የተፈጠሩት በዚህ መንፈሳዊ ፍጡር በኩል ነው። ይህ መንፈሳዊ ፍጡር የአምላክ አንድያ ልጅና “የፍጥረት ሁሉ በኩር” ነው፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሰው ሆኖ በምድር ላይ የኖረ ሲሆን ኢየሱስ ተብሎ ተጠርቷል። (ቆላ. 1:15-17) እንደ ይሖዋ ሁሉ ኢየሱስም ጥበበኛ ነው። እንዲያውም በምሳሌ ምዕራፍ 8 ላይ በጥበብ ተመስሏል። በዚሁ ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ የአምላክ “ዋና ሠራተኛ” (የ1954 ትርጉም) ተብሎ ተጠርቷል።—ምሳሌ 8:12, 22-31
6 በመሆኑም ግዑዝ የሆኑት ፍጥረታት የይሖዋንም ሆነ የእሱ ዋና ሠራተኛ የሆነውን የኢየሱስን ጥበብ ያንጸባርቃሉ። ከይሖዋ ፍጥረታት ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በምሳሌ 30:24-28 ላይ “እጅግ ጠቢባን” እንደሆኑ የተገለጹ አራት ፍጥረታትን እንደ ምሳሌ እንመልከት።a
ትጉ ሠራተኛ ስለመሆን የምናገኘው ትምህርት
7, 8. ጉንዳኖች ከሚያከናውኗቸው ነገሮች ውስጥ አንተን ይበልጥ ያስደነቀህ ምንድን ነው?
7 በምድር ላይ ስላሉት “ትንንሽ” የሚባሉ ፍጥረታት አፈጣጠርና ስለሚያደርጓቸው ነገሮች በመመርመር ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ለምሳሌ በደመ ነፍስ የሚመሩት ጉንዳኖች ያላቸውን ጥበብ እንመልከት።—ምሳሌ 30:24, 25ን አንብብ።
8 አንዳንድ ተመራማሪዎች በዓለም ላይ ያሉት ጉንዳኖች ብዛት ከሰው ልጆች በ200,000 እጥፍ እንደሚበልጥ ይገምታሉ። እነዚህ ሁሉ ጉንዳኖች በምድር ላይ ወይም አፈር ውስጥ ሥራቸውን በትጋት ያከናውናሉ። ጉንዳኖች በቡድን የተደራጁ ሲሆኑ አብዛኞቹ የጉንዳን ሠራዊቶች ንግሥቶች፣ አውራዎችና ሠራተኛ ጉንዳኖች ተብለው የሚጠሩ ሦስት የጉንዳን ዓይነቶችን ያቀፉ ናቸው። በሠራዊቱ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ጉንዳን ለሁሉም የጋራ ጥቅም የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል። በደቡብ አሜሪካ የሚገኘውን ቅጠል በጣሽ ጉንዳን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህ ጉንዳን በጣም የተዋጣለት አትክልተኛ ነው ሊባል ይችላል። መሬት ውስጥ የተከለው ፈንገስ ለምግብነት የሚውል ብዙ ምርት እንዲሰጠው ሲል ማዳበሪያ ያደርግለታል፣ ወደ ሌላ ቦታ ያዛውረዋል እንዲሁም ይገርዘዋል። ተመራማሪዎች፣ ይህ የተዋጣለት “አትክልተኛ” ሥራውን የሚያከናውነው ሠራዊቱ የሚያስፈልገውን የምግብ መጠን ከግምት በማስገባት መሆኑን ደርሰውበታል።b
9, 10. ትጉ ሠራተኛ በመሆን ረገድ ጉንዳኖችን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
9 ከጉንዳኖች ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ጥሩ ውጤት ማግኘት ከፈለግን ተግተን መሥራት እንዳለብን ያስተምሩናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንተ ታካች፤ ወደ ጕንዳን ሂድ፤ ዘዴውን አስተውለህ ጠቢብ ሁን፤ አዛዥ የለውም፤ አለቃም ሆነ ገዥ የለውም፤ ሆኖም ግን በበጋ ምግቡን ያከማቻል፤ በመከርም ወቅት ቀለቡን ይሰበስባል።” (ምሳሌ 6:6-8) ይሖዋም ሆነ የእሱ ዋና ሠራተኛ የሆነው ኢየሱስ ትጉ ሠራተኞች ናቸው። ኢየሱስ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም መሥራቴን እቀጥላለሁ” ሲል ተናግሯል።—ዮሐ. 5:17
10 እኛም አምላክንና ክርስቶስን በመምሰል ትጉ ሠራተኞች መሆን ይኖርብናል። በአምላክ ድርጅት ውስጥ ያለን የሥራ ድርሻ ምንም ይሁን ምን ሁላችንም ‘የጌታ ሥራ የበዛልን’ ልንሆን ይገባል። (1 ቆሮ. 15:58) በመሆኑም ጳውሎስ “በሥራችሁ አትለግሙ። በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ። ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ” ሲል ለሮም ክርስቲያኖች የሰጠውን ማሳሰቢያ መከተላችን ተገቢ ነው። (ሮም 12:11) መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” የሚል ዋስትና ስለሚሰጠን፣ የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም የምናደርገው ጥረት መና እንደማይቀር እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዕብ. 6:10
ከመንፈሳዊ አደጋ ራሳችንን መጠበቅ
11. ስለ ሽኮኮ አንዳንድ እውነታዎችን ግለጽ።
11 በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ትንሽ የሆነው ሌላው ፍጥረት ደግሞ ሽኮኮ ሲሆን ከዚህም ፍጥረት ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። (ምሳሌ 30:26ን አንብብ።) የሽኮኮ ጆሮዎች ክብና ትንንሽ ሲሆኑ እግሮቹ ደግሞ አጫጭር ናቸው። ይህ ትንሽ እንስሳ የሚኖረው አለታማ በሆኑ አካባቢዎች ነው። ከፍተኛ የማየት ችሎታ ያለው መሆኑ ጠላቶቹን ከርቀት ለመለየት ያስችለዋል። አለታማ በሆነው መኖሪያው ያሉት ጉድጓዶችና ስንጥቆች ደግሞ ከጠላቶቹ መሸሸጊያ ይሆኑለታል። ሽኮኮዎች በርከት ብለው አንድ ላይ መኖራቸው በጠላቶቻቸው እንዳይደፈሩ የሚረዳቸው ከመሆኑም ሌላ በክረምት ወራት እርስ በርስ ለመሟሟቅ ያስችላቸዋል።c
12, 13. ከሽኮኮ ምን ትምህርት እናገኛለን?
12 ከሽኮኮ ምን ትምህርት እናገኛለን? በመጀመሪያ፣ ይህ እንስሳ ራሱን ለአደጋ እንደማያጋልጥ ልብ በል። አጥርቶ የማየት ችሎታውን በመጠቀም ጠላቶቹን ከርቀት የሚያይ ሲሆን መሸሸጊያ ከሚሆኑለት ጉድጓዶችና ስንጥቆች ርቆ አይሄድም። በተመሳሳይ እኛም በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉትን አደገኛ ሁኔታዎች ማስተዋል እንድንችል ጥሩ መንፈሳዊ እይታ ሊኖረን ይገባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የማስተዋል ስሜቶቻችሁን ጠብቁ፤ ንቁዎች ሆናችሁ ኑሩ። ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል” ሲል ክርስቲያኖችን አሳስቧል። (1 ጴጥ. 5:8) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሰይጣን ታማኝነቱን ለማጉደፍ በሚያደርገው በማንኛውም ጥረት ላለመሸነፍ ነቅቶ ይኖር ነበር። (ማቴ. 4:1-11) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል።
13 ንቁ ሆነን መኖር የምንችልበት አንደኛው መንገድ ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ በሚያደርጋቸው ዝግጅቶች መጠቀም ነው። የአምላክን ቃል ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ችላ ሊባሉ የማይገባቸው ነገሮች ናቸው። (ሉቃስ 4:4፤ ዕብ. 10:24, 25) በተጨማሪም ሽኮኮዎች በርከት ብለው አንድ ላይ መኖራቸው እንደሚጠቅማቸው ሁሉ እኛም “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” ከክርስቲያን ወንድሞቻችን መራቅ የለብንም። (ሮም 1:12) ይሖዋ እኛን ከአደጋ ለመጠበቅ ባደረጋቸው ዝግጅቶች በመጠቀም “[ይሖዋ] ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤ አምላኬ የምሸሸግበት ዐለቴ . . . ነው” በማለት ከጻፈው መዝሙራዊ ጋር እንደምንስማማ እናሳያለን።—መዝ. 18:2
ተቃውሞ ቢኖርም መጽናት
14. አንድ አንበጣ በተናጠል ሲታይ ብዙም የሚያስደንቅ ባይሆንም ስለ አንበጣ መንጋ ምን ማለት ይቻላል?
14 ከአንበጣም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። አምስት ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አንድ አንበጣ በተናጠል ሲታይ ብዙም አያስደንቅ ይሆናል፤ በመንጋ ሲታይ ግን እጅግ ያስገርማል። (ምሳሌ 30:27ን አንብብ።) በልተው የማይጠግቡ በመሆናቸው የሚታወቁት አንበጦች፣ በመንጋ ሆነው ሲሰማሩ ለመሰብሰብ የደረሰን ሰብል በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዳልነበረ ሊያደርጉት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንበጣም ሆነ ሌሎች ነፍሳት በመንጋ ሆነው ሲመጡ የሚያሰሙትን ድምፅ ከሠረገሎች ድምፅና ገለባ ከሚበላ ከሚንጣጣ እሳት ድምፅ ጋር ያመሳስለዋል። (ኢዩ. 2:3, 5) ሰዎች የአንበጣ መንጋን ለማገድ በእሳት ቢጠቀሙም ይህ ዘዴ በአብዛኛው አልተሳካላቸውም። ለምን? በእሳቱ የተበሉት አንበጦች እሳቱን ስለሚያጠፉት ከኋላቸው የሚከተሉት አንበጦች ምንም ሳያግዳቸው ጉዟቸውን መቀጠል ይችላሉ። የአንበጣ መንጋ ንጉሥ ወይም መሪ ባይኖረውም እንኳ በሚገባ እንደተደራጀ የጦር ሠራዊት ከፊት ለፊቱ የሚያጋጥመውን ማንኛውንም እንቅፋት መወጣት ይችላል።d—ኢዩ. 2:25
15, 16. በዘመናችን ያሉት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ከአንበጣ መንጋ ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
15 ነቢዩ ኢዩኤል የይሖዋ አገልጋዮች የሚያከናውኑትን ሥራ አንበጦች ከሚያደርጉት ነገር ጋር አመሳስሎታል። ኢዩኤል እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እንደ ተዋጊዎች ድንገት አደጋ ይጥላሉ፤ እንደ ወታደሮችም ቅጥርን ይዘላሉ፤ ከመንገዳቸውም ሳይወጡ፣ አቅጣጫ ይዘው ይጓዛሉ። እርስ በርሳቸው አይገፋፉም፤ እያንዳንዱ መስመሩን ጠብቆ ይሄዳል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ከመካከላቸው አንዳንዶቹ በሚወረወሩት ፍላጻዎች መካከል ቢወድቁ እንኳ ሌሎቹ ግስጋሴያቸውን አያቋርጡም።” (NW)—ኢዩ. 2:7, 8
16 ይህ ትንቢት በዘመናችን ያሉትን የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች በጥሩ ሁኔታ ይገልጻል። ምንም ዓይነት የተቃውሞ “ቅጥር” የስብከት ሥራቸውን ሊያስቆመው አልቻለም። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ብዙዎች ቢንቁትም እንኳ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ የጸናውን የኢየሱስን ምሳሌ ይኮርጃሉ። (ኢሳ. 53:3) እውነት ነው፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች ‘በሚወረወሩት ፍላጻዎች መካከል በመውደቃቸው’ ለእምነታቸው ሰማዕት ሆነዋል። ያም ሆኖ የስብከቱ ሥራ የቀጠለ ከመሆኑም ሌላ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። እንዲያውም በአብዛኛው ስደት፣ በሌላ በምንም መንገድ ምሥራቹ ሊደርሳቸው ለማይችል ሰዎች መልእክቱ እንዲሰበክ መንገድ ከፍቷል። (ሥራ 8:1, 4) አንተስ ሰዎች ግድየለሽ ቢሆኑም ወይም ተቃውሞ ቢያጋጥምህም በአገልግሎትህ የአንበጦችን ዓይነት ጽናት ታሳያለህ?—ዕብ. 10:39
“ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቃችሁ ያዙ”
17. የጌኮ እግር ልሙጥ የሆኑ ነገሮችን ሙጭጭ አድርጎ መያዝ የሚችለው ለምንድን ነው?
17 ጌኮ በሚባለው ትንሽ እንሽላሊት ላይ የስበት ኃይል የሚሠራ አይመስልም። (ምሳሌ 30:28ን በNW አንብብ።e) የሳይንስ ሊቃውንት፣ ይህ ትንሽ ፍጥረት ባለው በግድግዳ ላይ የመሮጥና ልሙጥ በሆነ ኮርኒስ ላይ ተገልብጦ የመሄድ ችሎታ በእጅጉ ይደነቃሉ። ጌኮ እንዲህ ለማድረግ ያስቻለው ምንድን ነው? ይህን ማድረግ የቻለው እግሮቹ ላይ ሙጫ ስላለው አይደለም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ የጌኮ ጣት ተረተር የመሰሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ፀጉር መሰል ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ፀጉር መሰል ነገር ደግሞ ጫፋቸው የስኒ ማስቀመጫ ቅርጽ ያለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ጭረቶች አሉት። እነዚህ ጭረቶች እርስ በርስ በመሳሳብ የሚያመነጩት ኃይል ከእንሽላሊቱ የበለጠ ክብደት ያለውን ነገርም እንኳ መሸከም ይችላል። እንሽላሊቱ በመስተዋት ላይ ተገልብጦ መሮጥ የሚችለው ለዚህ ነው። ጌኮ ባለው ችሎታ በጣም የተደነቁ ተመራማሪዎች ከዚህ እንሽላሊት እግሮች ጋር በሚመሳሰል መንገድ የተሠሩ ነገሮች ከፍተኛ የማጣበቅ ኃይል ሊኖራቸው እንደሚችል ይናገራሉ።f
18. ምንጊዜም ‘ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቀን መያዝ’ የምንችለው እንዴት ነው?
18 ጌኮ ከተባለው እንሽላሊት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ የሆነውን ነገር ተጸየፉ፤ ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቃችሁ ያዙ” በማለት ይመክረናል። (ሮም 12:9) በሰይጣን ዓለም ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘው መጥፎ ተጽዕኖ የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ እንዳንከተል ሊያደርገን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ ቦታ ወይም ጤናማ ባልሆነ መዝናኛ አማካኝነት የአምላክን ሕጎች ከማይከተሉ ሰዎች ጋር የምንወዳጅ ከሆነ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ያለን ቁርጥ አቋም ሊዳከም ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዳይደርስብህ ጥንቃቄ አድርግ። የአምላክ ቃል “በራስህ አስተያየት ጠቢብ ነኝ አትበል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 3:7) ሙሴ በጥንት ዘመን ለነበረው የአምላክ ሕዝብ የሰጠውን የሚከተለውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ አድርግ፦ “አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ አምልከውም፤ ከእርሱም ጋር ተጣበቅ።” (ዘዳ. 10:20) ከይሖዋ ጋር የምንጣበቅ ከሆነ “ጽድቅን ወደድክ፣ ዓመፅን ጠላህ” የተባለለትን ኢየሱስን እንመስላለን።—ዕብ. 1:9
ከፍጥረት የምናገኘው ትምህርት
19. (ሀ) አንተ በግልህ በፍጥረት ሥራዎች ላይ የትኛውን የይሖዋ ባሕርይ ተመልክተሃል? (ለ) ከአምላክ የሚገኘው ጥበብ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
19 እስካሁን እንደተመለከትነው የይሖዋ ባሕርያት እሱ በሠራቸው ነገሮች ላይ በግልጽ የሚታዩ ከመሆናቸውም ሌላ ስለ ፍጥረት ሥራዎቹ በማጥናት ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ስለ ይሖዋ ሥራዎች ይበልጥ ምርምር ባደረግን መጠን የዚያኑ ያህል በጥበቡ እንደነቃለን። ከአምላክ ለሚገኘው ጥበብ ትኩረት መስጠታችን በአሁኑ ጊዜ ይበልጥ ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል፤ ለወደፊቱ ደግሞ ጥበቃ ያስገኝልናል። (መክ. 7:12) አዎን፣ በምሳሌ 3:13, 18 ላይ የሚገኘው የሚከተለው ሐሳብ እውነት መሆኑን በራሳችን ሕይወት መመልከት እንችላለን፦ “ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው ቡሩክ [“ደስተኛ፣” NW] ነው፤ ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ [“ደስተኛ ይባላሉ፣” NW]።”
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በተለይ ልጆች በግርጌ ማስታወሻዎቹ ላይ የተጠቀሱትን ጽሑፎች አንብበው ይህ መጠበቂያ ግንብ በጉባኤ በሚጠናበት ወቅት ሐሳብ መስጠት ይችላሉ።
b ስለ ቅጠል በጣሽ ጉንዳን ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት የመጋቢት 22, 1997 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 31ን እንዲሁም የግንቦት 22, 2002 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 31ን ተመልከት።
c ስለ ሽኮኮ ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት የመስከረም 8, 1990 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 15-16ን ተመልከት።
d ስለ አንበጣ ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት የሐምሌ 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 23ን እንዲሁም የጥቅምት 22, 1976 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 11ን ተመልከት።
f ስለ ጌኮ ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት የሚያዝያ 2008 ንቁ! ገጽ 26ን ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
• ከጉንዳን
• ከሽኮኮ
• ከአንበጣ
• ከጌኮ
ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ቅጠል በጣሽ ጉንዳን ትጉ ሠራተኛ ነህ?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽኮኮዎች በርከት ብለው አንድ ላይ መኖራቸው በጠላቶቻቸው እንዳይደፈሩ ይረዳቸዋል። አንተስ ከክርስቲያን ወንድሞችህ ጋር ተቀራርበህ ትኖራለህ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ አንበጦች ሁሉ ክርስቲያኖችም በአገልግሎታቸው ይጸናሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጌኮ የሚሄድበትን ነገር ሙጭጭ አድርጎ እንደሚይዝ ሁሉ ክርስቲያኖችም ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቀው ይይዛሉ
[የሥዕል ምንጭ]
Stockbyte/Getty Images