ምን ዓይነት ስም እያተረፍክ ነው?
ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለየ ሰው የሚገልጽ የሕይወት ታሪክ አንብበህ ወይም ሲነገር ሰምተህ ታውቃለህ? በዚህ ወቅት ‘እኔስ ስሞት ስለ እኔ ምን ይነገር ይሆን’ የሚል ጥያቄ ወደ አእምሮህ መጥቶ ነበር? ብዙዎች በሕይወቴ ምን ዓይነት ስም አትርፌ አልፍ ይሆን ብለው አያስቡም። እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው:- ትናንት ሞተህ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሰዎች ስለ አንተ ምን ብለው ይናገሩ ነበር? አሁን በሕይወት ሳለህ ምን ዓይነት ስም እያተረፍክ ነው? በሚያውቁህ ሰዎችም ሆነ በአምላክ ፊት ምን ዓይነት ስም አትርፈህ ማለፍ ትፈልጋለህ?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የመክብብ መጽሐፍ የጻፈው ጠቢብ ሰው “ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፣ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል” በማለት ተናግሯል። (መክብብ 7:1) ከመወለድ ቀን የሞት ቀን የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንድ ሰው ሲወለድ እንዲህ ነው ተብሎ ሊነገር የሚችል ምንም የሕይወት ታሪክ አይኖረውም። ጥሩ ወይም መጥፎ ስም ሊያተርፍ የሚችለው በሕይወት ዘመኑ በሚያከናውነው ነገር ነው። በሕይወት ዘመናቸው መልካም ስም ላተረፉ ሰዎች በእርግጥም ከተወለዱበት ቀን ይልቅ የሞቱበት ቀን የተሻለ ነው።
መልካም ስም ማትረፍ አለማትረፋችን በእኛ ላይ የተመካ ነው። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምናደርጋቸው ነገሮች በሰዎች በተለይ ደግሞ በአምላክ ዘንድ ምን ዓይነት ስም አትርፈን እንደምናልፍ ይወስናሉ። በዚህም የተነሳ ከላይ የተጠቀሰው ጠቢብ ዕብራዊ “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፤ የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 10:7) በአምላክ ዘንድ ለበረከት መታሰብ ምንኛ ታላቅ ክብር ነው!
ብልሆች ከሆንን የአምላክን ሕግና ሥርዓት በመጠበቅ እሱን ለማስደሰት እንጥራለን። ይህም ክርስቶስ የሰጠውን ቀጥሎ የሰፈረውን መመሪያ እንከተላለን ማለት ነው:- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፣ እርስዋም:- ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።”—ማቴዎስ 22:37-40
አንዳንዶች በበጎ አድራጊነታቸው፣ በሰብአዊ መብት ተሟጋችነታቸው አሊያም በንግዱ ዓለም፣ በሳይንስ፣ በሕክምና ወይም በሌሎች መስኮች ባከናወኗቸው ተግባራት ሲዘከሩ ይኖራሉ። አንተስ ምን ዓይነት ስም አትርፈህ ማለፍ ትፈልጋለህ?
ስኮትላንዳዊው ገጣሚ ሮበርት በርንስ (1759-96) ሌሎች እኛን በሚያዩን መንገድ ራሳችንን የማየት ችሎታ ተሰጥቶን ቢሆን ኖሮ ምንኛ መልካም ነበር ሲል ምኞቱን ገልጿል። በሰዎችም ይሁን በአምላክ ዘንድ መልካም ስም አትርፌያለሁ ብለህ በሐቀኝነት መናገር ትችላለህ? የኋላ ኋላ በሕይወታችን ውስጥ የላቀ ድርሻ የሚኖረው በስፖርቱ ወይም በንግዱ ዓለም የምናገኘው ጊዜያዊ ዝና ወይም ክብር ሳይሆን ከሌሎች ጋር የሚኖረን ጥሩ ወዳጅነት ነው። ስለዚህ አሁን የሚነሳው ጥያቄ ንግግራችን፣ ጠባያችንና መላው ድርጊታችን በሌሎች ላይ የሚያሳድረው ስሜት ምን ዓይነት ነው? የሚለው ይሆናል። ሰዎች ለእኛ ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው? በቀላሉ ይቀርቡናል ወይስ ይፈሩናል? ሌሎች የሚያውቁን በደግነታችን ነው ወይስ በኃይለኝነታችን? በእሺ ባይነታችን ወይስ በግትርነታችን? በአሳቢነታችንና በርኅሩኅነታችን ወይስ በግድየለሽነታችን? የምንታወቀው ሰዎችን በመተቸትና በማንኳሰስ ነው ወይስ በአሳቢነት በመምከርና በማበረታታት? በጥንት ዘመንም ሆነ በዛሬው ጊዜ ኖረው ያለፉ የአንዳንድ ሰዎችን ታሪክ በመመርመር ከእነሱ ምሳሌ ምን ትምህርት ልናገኝ እንደምንችል እንመልከት።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮበርት በርንስ ሌሎች እኛን በሚያዩን መንገድ ራሳችንን የማየት ችሎታ ተሰጥቶን ቢሆን ኖሮ ምንኛ መልካም ነበር ሲል ምኞቱን ገልጿል
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
From the book A History of England