ድህነት ለዘለቄታው ይወገድ ይሆን?
ድህነትን በተመለከተ በዓለም ዙሪያ አሳዛኝ ዘገባዎች ቢኖሩም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንደሚቻል የሚሰማቸው ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል ማኒላ ቡሌቲን የተባለው መጽሔት “እስያ በ25 ዓመታት ውስጥ ድህነትን ልታስወግድ ትችላለች” በማለት የእስያ ልማት ባንክ ያቀረበውን ሪፖርት በርዕሰ አንቀጹ ላይ አስፍሯል። ባንኩ ሕዝቡን ከድህነት ማጥ ውስጥ ለማውጣት እንደ መፍትሔ ያቀረበው ኢኮኖሚያዊ እድገትን ነው።
ሌሎች ድርጅቶችና መንግሥታትም ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ የመፍትሔ ሐሳቦችን አቅርበዋል እንዲሁም እቅዶችን ነድፈዋል። መፍትሔ ይሆናሉ ከተባሉት ሐሳቦች መካከል የማኅበራዊ ዋስትና ፕሮግራምና የተሻለ የትምህርት ዕድል እንዲኖር ማድረግ፣ የታዳጊ አገሮችን ዕዳ መሰረዝ፣ አብዛኛው ሕዝባቸው ድሃ የሆነ አገሮች ምርቶቻቸውን በቀላሉ መሸጥ እንዲችሉ የውጭ ንግድ እንቅፋቶችን ማስወገድ እንዲሁም ኑሯቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች መኖሪያ ቤት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት የሚሉት ይገኙበታል።
በ2000 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እስከ 2015 ድረስ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ግቦችን አውጥቶ ነበር። እነዚህ ግቦች የከፋ ረሃብንና ድህነትን ማስወገድን እንዲሁም በአገሮች መካከል የሚታየውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ልዩነት ማጥበብን ያካትታሉ። ምንም እንኳን እንደነዚህ ያሉት ግቦች የሚደነቁ ቢሆኑም በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ እውን ሊሆኑ መቻላቸውን ብዙዎች ይጠራጠራሉ።
ድህነትን ለመቋቋም የሚረዱ ተግባራዊ እርምጃዎች
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጨባጭ ለውጥ ይገኛል የሚለው ተስፋ የመነመነ ከሆነ አንድ ሰው መፍትሔ ለማግኘት ወዴት ዘወር ማለት ይችላል? ቀደም ብለን እንደገለጽነው በዛሬው ጊዜም እንኳን ሰዎችን ሊረዳ የሚችል ጠቃሚ ምክር የያዘ መጽሐፍ አለ። ይህ መጽሐፍ የትኛው ነው? የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
የመፍትሔ ሐሳብ ከሚሰጡ ሌሎች ምንጮች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? ከመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ማለትም ከፈጣሪያችን የመጣ መሆኑ ነው። ፈጣሪ ለማንኛውም ሰው፣ በሁሉም ቦታና በየትኛውም ዘመን ሊሠሩ የሚችሉ እንደ እንቁ የሆኑ ጥበብ አዘል መመሪያዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። በድህነት የሚኖሩ ሰዎች እነዚህን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ዛሬም እንኳን የተሻለ ኑሮ መኖር ይችላሉ። እስቲ ከእነዚህ መመሪያዎች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት።
ስለ ገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ። መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው” በማለት ይናገራል። (መክብብ 7:12 አ.መ.ት) ይህ ጥቅስ የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው? ገንዘብ ሁሉን ነገር ሊገዛ አይችልም። እርግጥ ነው፣ በተወሰነ መጠን ከስጋት ሊያሳርፍ ይችላል። አንዳንድ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለመግዛት ቢያስችለንም ገንዘብ ሁሉን ማድረግ ይችላል ማለት ግን አይደለም። ገንዘብ ሊገዛቸው የማይችላቸው ውድ ነገሮች አሉ። ይህንን መገንዘባችን ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንድንይዝ የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ገንዘብ ለማከማቸት የሚሮጡ ሰዎች ከሚያጋጥማቸው ብስጭት ይጠብቀናል። ገንዘብ ሕይወትን ሊገዛ አይችልም፤ ጥበብ ግን በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችንን ሊጠብቅልን ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝልን ይችላል።
እንደ አቅማችን መኖር። እንዲኖሩን የምንፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ለመኖር የግድ ያስፈልጉናል ማለት አይደለም። ቅድሚያ መስጠት ያለብን የግድ ለሚያስፈልጉን ነገሮች ነው። አንድ ነገር በሕይወት ለመኖር የግድ የሚያስፈልገን ባይሆንም እንደሚያስፈልገን አድርገን ራሳችንን እናሳምን ይሆናል። አስተዋይ የሆነ ሰው ገንዘቡን በቅድሚያ የሚያውለው እንደ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ ለመሳሰሉት በጣም አንገብጋቢ ለሆኑ ነገሮች ነው። ከዚያም ሌላ ወጪ ከማውጣቱ በፊት የቀረው ገንዘብ ተጨማሪ ነገሮች ለመግዛት ያስችለው እንደሆነና እንዳልሆነ ያሰላል። ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ ‘አስቀድሞ ተቀምጦ ኪሳራን ማስላት’ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።—ሉቃስ 14:28
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ባለቤቷ ጥሏት ስለሄደ ሦስት ልጆቿን ያለ አባት የምታሳድገው በፊሊፒንስ የምትኖረው ዩፍሮሲና ገንዘብ ማግኘትም ሆነ ያገኘቻትን አብቃቅታ መኖር ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ተገንዝባለች። ቤተሰቡ ያገኘውን ገንዘብ በቅድሚያ ለየትኞቹ ነገሮች ማዋል እንደሚገባው ልጆቿን አሰልጥናቸዋለች። ለምሳሌ ያህል ልጆቹ አንድ ነገር እንዲገዛላቸው ይፈልጉ ይሆናል። በዚህ ወቅት አይሆንም ከማለት ይልቅ እንደሚከተለው በማለት በምክንያት ታስረዳቸዋለች:- “ከፈለጋችሁ ሊገዛላችሁ ይችላል፤ ሆኖም አንድ ነገር ማወቅ አለባችሁ። ያለን ገንዘብ የሚበቃው አንድ ነገር ለመግዛት ብቻ ነው። የጠየቃችሁትን ነገር አሊያም ለዚህ ሳምንት የሚበቃንን ለሩዝ ማባያ የሚሆን ስጋ ወይም አትክልት መግዛት እንችላለን። የቱ እንደሚሻል እናንተ ምረጡ።” አብዛኛውን ጊዜ ልጆቹ ወዲያው ሐሳቡ ስለሚገባቸው ሌላ ነገር ከሚገዛላቸው ይልቅ ምግብ ቢገዛ የተሻለ እንደሚሆን ይስማማሉ።
ባለን መርካት። ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ገንዘብ በራሱ ደስታ አያስገኝም። ሀብታም የሆኑ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው ደስታ የራቀው ነው፤ በአንጻሩ ደግሞ ድሃ የሆኑ በርካታ ሰዎች ደስተኞች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን መሠረታዊ ነገሮች ካገኙ በዚህ ይረካሉ። ኢየሱስ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ ያተኮረ ‘ቀና ዓይን’ ሊኖረን እንደሚገባ ምክር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 6:22 NW) ይህ ምክር አንድ ሰው ባለው እንዲረካ ይረዳዋል። ድሃ የሆኑ ብዙ ሰዎች ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና በመመሥረታቸውና አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት ስላላቸው ረክተው ይኖራሉ። እነዚህን ደግሞ በገንዘብ ልንገዛቸው አንችልም።
እስካሁን ያየነው ድሃ የሆኑ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ መቋቋም እንዲችሉ ከሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክሮች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ነው። ሌሎች በርካታ ምክሮችም አሉ። ለምሳሌ ያህል እንደ ሲጋራ ወይም ቁማር ካሉ ገንዘብን ከሚያባክኑ መጥፎ ልማዶች እንድንርቅ፣ በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ማለትም መንፈሳዊ ነገሮችን ለይተን እንድናውቅና ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነባቸው ቦታዎች ለሰዎች አንድ ዓይነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የሥራ መስክ እንድንፈጥር ይመክረናል። (ምሳሌ 22:29 አ.መ.ት፤ 23:21፤ ፊልጵስዩስ 1:9-11) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጥበብንና ማስተዋልን’ እንድንጠቀምባቸው ያበረታታናል፤ እንደዚህ ማድረጋችን የሚያስገኘውን ጥቅም ሲገልጽም “ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ” ይላል።—ምሳሌ 3:21, 22
መጽሐፍ ቅዱስ ከድህነት ጋር እየታገሉ የሚኖሩ ሰዎች ችግሮቻቸውን እንዲያቃልሉ የሚረዷቸው ጠቃሚ ምክሮች ይሰጣል። ይሁን እንጂ ድህነት ዘላቂ መፍትሔ የለውም ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በድህነት እየማቀቁ ያሉ ሰዎች ዕጣ ፈንታቸው ይኸው ነው? በጣም ሀብታም በሆኑትና የመጨረሻ ድሃ በሆኑት ሰዎች መካከል ያለው ሰፊ የኑሮ ልዩነት የሚስተካከልበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? እስቲ ብዙዎች የማያውቁትን አንድ መፍትሔ እንመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ
ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ መጽሐፍ መሆኑን ቢስማሙበትም በቅርቡ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚመጣ የሚገልጽ ዝርዝር ሐሳብ እንደያዘ አይገነዘቡም።
አምላክ ድህነትን ጨምሮ የሰው ልጆችን ችግሮች በሙሉ ለማስወገድ እርምጃ የመውሰድ ዓላማ አለው። ሰብዓዊ መንግሥታት እንደዚህ የማድረግ ችሎታውም ሆነ ፈቃደኝነቱ ስለሌላቸው አምላክ እነዚህን መንግሥታት በሌላ መንግሥት ይተካቸዋል። ይህንን የሚያደርገው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በዳንኤል 2:44 ላይ እንዲህ በማለት በግልጽ ይናገራል:- “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”
አምላክ እነዚህን “መንግሥታት” ካጠፋ በኋላ እርሱ ራሱ የሾመው ገዢ ሥራውን ይጀምራል። ይህ ገዢ ሰብዓዊ ፍጡር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ዛሬ የሚታየውን የኑሮ ልዩነት ማስወገድ የሚችል እንደ አምላክ ያለ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ነው። አምላክ ይህንን ኃላፊነት የሰጠው ለልጁ ነው። (ሥራ 17:31) መዝሙር 72:12-14 ይህ ገዢ ምን እንደሚያከናውን ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው በፊቱ ክቡር ነው።” ይህ እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው! ከድህነትም ሆነ ከሌላ ከማንኛውም ችግር እፎይ የምንልበት ጊዜ ይመጣል! አምላክ የሾመው ገዢ በድህነትና በችግር የሚኖሩትን ከመከራ ይገላግላቸዋል።
በዚያን ወቅት ከድህነት ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ። መዝሙር 72 ቁጥር 16 [አ.መ.ት] “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ” ይላል። በድርቅ፣ በገንዘብ እጦት ወይም ብልሹ በሆነ አስተዳደር ሳቢያ የምግብ እጥረት አይከሰትም።
ሌሎች ችግሮችም መፍትሔ ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ዛሬ አብዛኞቹ ሰዎች የራሴ የሚሉት ቤት የላቸውም። ይሁን እንጂ አምላክ እንዲህ የሚል ተስፋ ሰጥቷል:- “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተ[ክ]ሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፣ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።” (ኢሳይያስ 65:21, 22) እያንዳንዱ ሰው የራሱ ቤት ይኖረዋል፤ በሚሠራውም ሥራ እርካታ ያገኛል። አምላክ ድህነትን ዘላቂ በሆነ መልኩ ከሥረ መሠረቱ ለማስወገድ ቃል ገብቷል። ከዚያ በኋላ ድሃና ሀብታም የሚባል የኑሮ ልዩነት አይኖርም፤ እንዲሁም ማንም ሰው ከእጅ ወዳፍ የሆነ ኑሮ ለመግፋት አይገደድም።
አንድ ሰው እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰማ ይህ ሊሆን የማይችል ነገር ነው ብሎ ያስብ ይሆናል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ስንመረምር ከዚህ ቀደም አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ እንደተፈጸሙ እንገነዘባለን። (ኢሳይያስ 55:11) እንግዲያው ይህ ተስፋ ምናልባት ከተፈጸመ የምንለው ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ ተስፋ ከሚፈጸምላቸው ሰዎች አንዱ ለመሆን ምን ማድረግ አለብኝ? ብለህ ራስህን ብትጠይቅ የተሻለ ነው።
ከዚህ ተስፋ ተካፋይ ለመሆን ትበቃ ይሆን?
ይህንን የሚያደርገው የአምላክ መንግሥት ስለሆነ በዚህ መንግሥት ሥር አምላክ የዜግነት መብት የሚሰጠን ዓይነት ሰዎች መሆን አለብን። ለዚህ መብት መብቃት የምንችለው እንዴት እንደሆነ በግልጽ አስቀምጦልናል። መመሪያዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረዋል።
የዚህ መንግሥት ንጉሥ የሆነው የአምላክ ልጅ ጻድቅ ነው። (ኢሳይያስ 11:3-5) በመሆኑም በዚህ መንግሥት ሥር እንዲኖሩ የሚፈቀድላቸው ሰዎች ጻድቅ ሊሆኑ ይገባል። ምሳሌ 2:21, 22 እንዲህ ይላል:- “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”
እነዚህን ብቃቶች እንዴት ማሟላት እንደምትችል የምትማርበት መንገድ ይኖር ይሆን? አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና መመሪያዎቹን ተግባራዊ በማድረግ ይህንን አስደሳች ተስፋ ከሚወርሱት ሰዎች መካከል መሆን ትችላለህ። (ዮሐንስ 17:3) የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስጠኑህ ፈቃደኞች ናቸው። ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ድህነትና የኑሮ ልዩነት ፈጽሞ በማይኖርበት ኅብረተሰብ ውስጥ ለመኖር የሚያስችልህን እውቀት እንድትገበይ እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ማሟላት የቻልነው ያለችንን ገቢ በጥንቃቄ አብቃቅተን በመጠቀም ነው”—ዩፍሮሲና
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረትና አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት ገንዘብ የማይገዛቸው ነገሮች ናቸው