አምላክ ‘በተጣመመ’ መንገድ ይሠራልን?
“ዴኡስ ኤስክሪቪ ሴርቱ ፖር ሊንዮሰ ቶርቶስ” (“አምላክ በወልጋዳ መሥመሮች ላይ በትክክል ይጽፋል”) የሚባል አንድ የብራዚል አባባል አለ። ይህ ምሳሌ አምላክ የሚሠራቸው ነገሮች ሁሉ ሁልጊዜ ትክክል ሆነው ሳሉ አንዳንድ ጊዜ ለሰዎች የተጣመሙ መስለው እንደሚታዩ የሚያመለክት ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ገና በወጣትነት ዕድሜው እያለ ሲሞት ብዙዎች ‘አምላክ ወደ ሰማይ ጠራው’ ብለው ይናገራሉ። አንድ ሰው የአካል ጉዳተኛ ቢሆን ወይም አንድ ዓይነት አደጋ ቢደርስበት ‘አምላክ ፈርዶበት ነው’ ይላሉ። ሞት፣ አካላዊ ጉዳትና ሌሎች ሃዘን የሚያስከትሉ ነገሮች በሚደርሱበት ጊዜ አምላክ እንዳመጣቸው ተደርገው ስለሚነገሩ እንደነዚህ ያሉት አነጋገሮች አምላክ ‘አጣምሞ ይጽፋል’ የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ። ይህም አምላክ ሰዎች በማይገነዘቡት መንገድ ነገሮችን ያከናውናል እንደማለት ነው።
ይሁን እንጂ ብዙ የሃይማኖት ሰዎች ለሞትም ሆነ ለችግር ተጠያቂው አምላክ ነው የሚል እምነት ያላቸው ለምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው እምነት የሚመጣው በተናጥል ያሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ነው። እስቲ አንዳንዶቹን በአጭሩ እንመልከት።
● “ዲዳስ ደንቆሮስ የሚያይስ ዕውርስ ያደረገ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን?”—ዘጸአት 4:11
ታዲያ ይህ ማለት የተለያየ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች በኃላፊነት የሚጠየቀው አምላክ ነው ማለት ነውን? አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ፈጽሞ ከአምላክ ባሕርያት ጋር አይጣጣምም። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና” በማለት ይነግረናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:4) አንድ ሰው ማየት፣ መናገር ወይም መስማት የተሳነው ሆኖ ቢወለድ ተጠያቂው አምላክ አይደለም። እርሱ ‘የመልካም ስጦታና የፍጹምም በረከት ሁሉ’ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ለፍጥረታቱ የሚመኘው ሁልጊዜ መልካም የሆነውን ነገር ብቻ ነው።—ያዕቆብ 1:17
ሆነ ብለው በራሳቸው ምርጫ በአምላክ ላይ በማመፅ ፍጽምናቸውን ያጡትና በዚህም የተነሳ ፍጹም የሆኑ ልጆችን የመውለድ ችሎታቸውን ያጡት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ናቸው። (ዘፍጥረት 3:1-6, 16, 19፤ ኢዮብ 14:4) ዝርያዎቻቸውም ተጋብተው ልጅ በሚወልዱበት ጊዜ አካላዊ ጉድለትን ጨምሮ የአለፍጽምና ውጤቶች በሰዎች ላይ መታየት ጀመሩ። ይህ ነገር እንዲከሰት ያደረገው አምላክ ባይሆንም እንዲደርስ ግን ፈቅዷል። ስለዚህ ዲዳ፣ ደንቆሮ ወይም ዕውር ‘ያደረገው’ እርሱ እንደሆነ አድርጎ ስለ ራሱ ሊናገር ችሏል።
● “ጠማማ ይቀና ዘንድ አይችልም።”—መክብብ 1:15
ነገሮችን የተጣመሙ አድርጎ የሠራው አምላክ ነውን? ፈጽሞ ሊሆን አይችልም። መክብብ 7:29 “እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው፣ . . . እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ” በማለት ይናገራል። ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን ይህን ጥቅስ ቀለል ባለ አገላለጽ እንደተረጎመው “አምላክ ሲፈጥረን ፍጹም ሐቀኛ ነበርን፤ አሁን ግን አስተሳሰባችን ተዛብቷል።” ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች መሠረት ከመመላለስ ይልቅ ብዙውን ጊዜ በራሳቸው እቅድ፣ ውጥን፣ ዘዴ ወይም መንገድ ለመመላለስ መረጡ። ይህ ደግሞ ውድቀት አስከትሎባቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:14
በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳመለከተው በሰው ዘሮች ኃጢአት ምክንያት “ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአል።” (ሮሜ 8:20) ይህም ቢሆን በሰው ልጆች ጥረት ‘ሊቃና የሚችል’ አይደለም። በምድር ላይ ያሉ ጠማማና ከንቱ የሆኑ ነገሮች በሙሉ ሊወገዱ የሚችሉት በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ብቻ ነው።
● “የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፤ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል?”—መክብብ 7:13
በሌላ አባባል ንጉሥ ሰሎሞን ‘አምላክ እንዲሆን የፈቀደውን ጉድለትና አለፍጽምና ከሰው ልጆች መካከል ማን ሊያስተካክል ይችላል?’ ብሎ መጠየቁ ነበር። ይሖዋ እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱ የፈቀደበት ምክንያት ስላለው ማንም ሰው ይህን ሊያስተካክል አይችልም።
ስለዚህም ሰሎሞን “በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፤ በክፉም ቀን ተመልከት፤ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንም ያንም እንደዚያ ሠርቶአል” በማለት መክሯል። (መክብብ 7:14) አንድ ሰው በጥሩ መንገድ ያሳለፈውን ቀን ማድነቅና ይህንንም አድናቆቱን ጥሩነትን በማንጸባረቅ ማሳየት ይኖርበታል። አንድን መልካም ቀን እንደ አምላክ ስጦታ አድርጎ መመልከት ይኖርበታል። ይሁን እንጂ በቀኑ ውስጥ አንድ ዓይነት መከራ ቢያጋጥመውስ? አምላክ መከራው እንዲደርስ እንደፈቀደ ግለሰቡ ለመገንዘብ ወይም ‘ለመመልከት’ ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል። ታዲያ አምላክ እንዲህ ያለው ነገር እንዲደርስ የሚፈቅደው ለምንድን ነው? “ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ” ለማድረግ እንደሆነ ሰሎሞን ይናገራል። ይህ ምን ማለት ነው?
አምላክ ደስታንም ችግርንም እንድናይ መፍቀዱ የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚያመጣ መናገር የማንችል የመሆናችንን ሃቅ እንድንገነዘብ ያደርገናል። መከራ በጻድቁም በኃጢአተኛውም ላይ ይደርሳል። ማንንም አይለይም። ይህም በራሳችን ላይ ሳይሆን ‘አምላክ ፍቅር’ መሆኑን በማስታወስ በእርሱ ላይ የመደገፍን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ያደርገናል። (1 ዮሐንስ 4:8) አንዳንድ ነገሮች ለምን እንደሚደርሱ በአሁኑ ጊዜ ለመረዳት ቢቸግረን እንኳ ሁሉም ነገር ሂደቱን ጨርሶ ፍጻሜውን ካገኘ በኋላ አምላክ የፈቀዳቸው ነገሮች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ ጥቅም የሚያመጣ እንደሚሆን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
አምላክ ምንም ነገር እንዲደርስብን ይፍቀድ ልበ ቅን በሆነ ሰው ላይ ዘላለማዊ የሆነ ጉዳት አይደርስበትም። ሐዋርያው ጴጥሮስ በጊዜው በነበሩት የእምነት ባልደረቦቹ ላይ ይደርሱ ስለነበሩ ሥቃዮች ሐሳብ ሲሰጥ “ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል” ብሎ በተናገረ ጊዜ ሁኔታውን ግልጽ አድርጎታል።—1 ጴጥሮስ 5:10
ነገሮች የሚቃኑበት ጊዜ
ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች መቋቋም እንድንችል ኃይል ይሰጠናል። በተጨማሪም ‘ሁሉን ነገር አዲስ’ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል። (ራእይ 21:5) አዎን፣ በአካላዊ ጉዳት ምክንያት ለሚሠቃዩ ሰዎች በሰማያዊ መንግሥቱ በኩል ሙሉ ጤና መስጠትና የሞቱ ሰዎችን ማስነሳት ዓላማው ነው። በተጨማሪም ይህ መስተዳድር መንገዱ ሁሉ ጠማማ የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስንም ፈጽሞ ያጠፋል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሮሜ 16:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:26፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) አምላክ ነገሮችን የሚያቃናበት ጊዜ ሲመጣ በመላው ምድር ላይ ለሚኖሩ ፈሪሃ አምላክ ላላቸው ሰዎች እንዴት ያለ በረከት ይሆናል!
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Job Hearing of His Ruin/The Doré Bible Illustrations/Dover Publications