ሕያው የሆነ የአምላክ ቃል ትርጉም
“የአምላክ ቃል ሕያው . . . ነው።”—ዕብ. 4:12
1. (ሀ) አምላክ ለአዳም ምን ሥራ ሰጥቶት ነበር? (ለ) ከዚያን ጊዜ ወዲህ የአምላክ ሕዝቦች የቋንቋ ችሎታቸውን የተጠቀሙበት እንዴት ነው?
ይሖዋ አምላክ ለፍጡራኑ ሐሳብን የመግለጽ ስጦታ ሰጥቷቸዋል። አምላክ አዳምን በኤደን የአትክልት ስፍራ ካስቀመጠው በኋላ የቋንቋ ችሎታውን መጠቀም የሚጠይቅ ሥራ ሰጠው፤ ይህም ለእንስሳቱ ስም ማውጣት ነበር። አዳም የፈጠራና የማሰብ ችሎታውን በመጠቀም ለእያንዳንዳቸው ተስማሚ ስም አወጣላቸው። (ዘፍ. 2:19, 20) ከዚያን ጊዜ አንስቶ የአምላክ ሕዝቦች የመናገር ይኸውም በቋንቋ የመጠቀም ችሎታቸውን ይሖዋን ለማወደስና ፈቃዱን ለሰዎች ለማሳወቅ እያዋሉት ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በቋንቋ አማካኝነት ንጹሑን አምልኮ ማስፋፋት የተቻለበት ዋነኛ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው።
2. (ሀ) የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ ሥራውን ሲያከናውን የትኞቹን መመሪያዎች ተከትሏል? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
2 በሺዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ቢኖሩም በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኘውን መልእክት በታማኝነት የሚያስተላልፉት ግን ሁሉም አይደሉም። በ1940ዎቹ ዓመታት የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት ሆነው የሚያገለግሉ መመሪያዎችን አዘጋጀ፤ እነዚህን መመሪያዎች ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተግባራዊ አድርገናል። መመሪያዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (1) የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቀድሞ በነበረበት ትክክለኛ ቦታ ላይ መልሶ እንዲገባ በማድረግ የአምላክን ስም ያስቀድሳል። (ማቴዎስ 6:9ን አንብብ።) (2) የቋንቋው ሥርዓት እስከፈቀደለት ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ውስጥ ለሚገኘው ሐሳብ ቀጥተኛ ፍቺ ይሰጣል፤ ቃል በቃል መተርጎም ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት የሚያዛባ ከሆነ ግን የቃሉን ወይም የሐረጉን ትክክለኛ መንፈስ ለማስተላለፍ ይጥራል። (3) ለማንበብ የሚማርክና ለመረዳት የማያስቸግር ቋንቋ ይጠቀማል።a (ነህምያ 8:8, 12ን አንብብ።) እነዚህ መመሪያዎች በ2013 ተሻሽሎ ከወጣው የእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም እንዲሁም በሌሎች ቋንቋዎች ከተዘጋጁ ትርጉሞች ጋር በተያያዘ እንዴት እንደተሠራባቸው እንመልከት።
የአምላክን ስም ማክበር
3, 4. (ሀ) ቴትራግራማተን በየትኞቹ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ ይገኛል? (ለ) ከአምላክ ስም ጋር በተያያዘ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ምን አድርገዋል?
3 በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎችን (ለምሳሌ የሙት ባሕር ጥቅልሎችን) የሚያጠኑ ምሁራን፣ ቴትራግራማተን በእነዚህ ጽሑፎች ላይ በብዛት የሚገኝ መሆኑ አስገርሟቸዋል።b መለኮታዊው ስም፣ በእነዚያ ጥንታዊ የዕብራይስጥ ቅጂዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ከሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እስከ አንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ በተገለበጡ አንዳንድ የግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ቅጂዎች ላይም ይገኛል።
4 የአምላክ የግል ስም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መግባት እንዳለበት ግልጽ ማስረጃ ቢኖርም በርካታ ተርጓሚዎች ቅዱስ የሆነውን መለኮታዊ ስም ከትርጉም ሥራዎቻቸው ውስጥ ሙሉ በሙሉ አውጥተውታል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) በ1950 በወጣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርዥን የተባለው ትርጉም ወጣ። ይህ ትርጉም በ1901 ከወጣው አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን ላይ ተሻሽሎ የተዘጋጀ ሲሆን የአሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን አዘጋጆች የተከተሉትን ፖሊሲ በመሻር የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጥቶታል። ለምን? መቅድሙ እንዲህ ይላል፦ ‘አንድና ብቸኛ የሆነውን አምላክ በተጸውኦ ስም መጥራት ለዓለም አቀፉ የክርስትና እምነት ፈጽሞ ተገቢ አይደለም።’ ከዚያ በኋላ በእንግሊዝኛም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን አካሄድ ተከትለዋል።
5. የአምላክ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳይወጣ መደረጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 የአምላክ ስም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መግባት አለመግባቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ የተዋጣለት ተርጓሚ፣ የደራሲውን ሐሳብ መረዳቱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያውቃል፤ እንዲህ ያለው እውቀት ከትርጉም ሥራው ጋር በተያያዘ በሚያደርጋቸው በርካታ ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። የአምላክ ስምና የስሙ መቀደስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ የሚያሳዩ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። (ዘፀ. 3:15፤ መዝ. 83:18፤ 148:13፤ ኢሳ. 42:8፤ 43:10፤ ዮሐ. 17:6, 26፤ ሥራ 15:14) የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው ይሖዋ አምላክ፣ ጸሐፊዎቹ ስሙን በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዲጠቀሙበት በመንፈሱ መርቷቸዋል። (ሕዝቅኤል 38:23ን አንብብ።) በጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ውስጥ በሺዎች በሚቆጠሩ ጊዜያት የሚገኘውን ስም ማውጣት ለመጽሐፉ ባለቤት አክብሮት ማጣት ነው።
6. ተሻሽሎ የወጣው የእንግሊዝኛው አዲስ ዓለም ትርጉም የአምላክን ስም ተጨማሪ ስድስት ቦታዎች ላይ ያስገባው ለምንድን ነው?
6 የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁሙት ማስረጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል እንጂ አልቀነሱም። በ2013 ተሻሽሎ በወጣው የእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የአምላክ ስም 7,216 ጊዜ የሚገኝ ሲሆን ይህ ቁጥር በ1984 በተዘጋጀው እትም ላይ ካለው በ6 ይበልጣል። የአምላክ ስም የገባባቸው አምስት ተጨማሪ ቦታዎች 1 ሳሙኤል 2:25፤ 6:3፤ 10:26፤ 23:14, 16 ናቸው። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የአምላክ ስም ቀድሞ በነበረበት ቦታ እንዲገባ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት፣ ማሶሬቶች ከገለበጡት የዕብራይስጥ ቅጂ 1,000 ዓመት በፊት በተዘጋጁት የሙት ባሕር ጥቅልሎች ላይ ስሙ ስለሚገኝ ነው። ከዚህም ሌላ በጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ በተደረገ ተጨማሪ ጥናት ምክንያት መሳፍንት 19:18 ላይ የአምላክ ስም እንዲገባ ተደርጓል።
7, 8. ይሖዋ የሚለው ስም ትርጉም ምንድን ነው?
7 የይሖዋ ስም በእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ ትልቅ ቦታ አለው። በ2013 ተሻሽሎ የወጣው የእንግሊዝኛው አዲስ ዓለም ትርጉም ተጨማሪ ክፍል፣ ከአምላክ ስም ጋር በተያያዘ አሁን ያለንን ግንዛቤ ይዟል። የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ የአምላክ ስም ሐዋሕ ከሚለው የዕብራይስጥ ግስ የተገኘ እንደሆነና የግሱ አገባብ አስደራጊነትን እንደሚያመለክት ተገንዝቧል፤ በመሆኑም ስሙ “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም አለው።c ከዚህ ቀደም ጽሑፎቻችን ይህን የአምላክ ስም ትርጉም በዘፀአት 3:14 ላይ ከሚገኘው “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” ከሚለው ሐሳብ ጋር ያያይዙት ነበር። በዚህም የተነሳ በ1984 በወጣው አዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) ላይ መለኮታዊው ስም፣ ይሖዋ “ዓላማውን ዳር ለማድረስ እሱ መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል” የሚል ትርጉም እንዳለው ተገልጾ ነበር።d ይሁንና በ2013 ተሻሽሎ የወጣው እትም ተጨማሪ መረጃ ሀ4 እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ የሚለው ስም ይህን ሐሳብ የሚያጠቃልል ቢሆንም እንኳ የስሙ ትርጉም እሱ መሆን የሚፈልገውን እንደሚሆን የሚገልጽ ብቻ አይደለም። የስሙ ትርጉም፣ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ፍጥረታቱ እሱ የሚፈልገውን እንዲሆኑ እንደሚያደርግም ያመለክታል።”
8 ይሖዋ፣ ፍጥረታቱ እሱ የሚፈልገውን እንዲሆኑ ያደርጋል። አምላክ ከስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ ኖኅን መርከብ ሠሪ፣ ባስልኤልን የተዋጣለት የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣ ጌድዮንን ኃያል ተዋጊ እንዲሁም ጳውሎስን የአሕዛብ ሐዋርያ አድርጓቸዋል። በእርግጥም የአምላክ ሕዝቦች መለኮታዊው ስም ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይገነዘባሉ። የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴም ቢሆን መለኮታዊውን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማውጣት ለአምላክ ስም አክብሮት እንደጎደለው የሚያሳይ ድርጊት አይፈጽምም።
9. መጽሐፍ ቅዱስን ወደተለያዩ ቋንቋዎች ለመተርጎሙ ሥራ ቅድሚያ የተሰጠበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?
9 ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሶች የአምላክ ስም በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ በትክክለኛው ቦታ ላይ እንዲገባ በማድረግ ለስሙ አክብሮት አሳይተዋል። (ሚልክያስ 3:16ን አንብብ።) ከዚህ በተቃራኒ በአሁኑ ጊዜ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መለኮታዊውን ስም በማውጣት በምትኩ “ጌታ” የሚለውን ማዕረግ ወይም በአካባቢው የሚታወቀውን አምላክ መጠሪያ የማስገባት ልማድ አላቸው። የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል፣ የአምላክን ስም የሚያስከብር የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች እንዲደርስ ለማድረግ ቅድሚያ የሰጠበት ዋነኛ ምክንያት ይህ ነው።
ግልጽና ትክክለኛ ትርጉም
10, 11. አዲስ ዓለም ትርጉምን የተረጎሙ አንዳንድ ቋንቋዎች ምን ችግሮች አጋጥመዋቸው ነበር?
10 ቅዱስ ጽሑፉን በብዙ ቋንቋዎች ለማዘጋጀት በሚደረገው ጥረት ከትርጉም ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች ያጋጥማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንደሚያደርጉት ሁሉ የእንግሊዝኛው አዲስ ዓለም ትርጉምም “ሲኦል” የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል እንደ መክብብ 9:10 ባሉ ጥቅሶች ላይ ይጠቀም ነበር። በመሆኑም ጥቅሱ “አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለም” ይል ነበር። ይህም ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የሚተረጉሙ ተርጓሚዎች እንዲቸገሩ ያደርጋል፤ ምክንያቱም “ሲኦል” የሚለውን ቃል አንባቢዎች ቢያውቁትም የሥቃይና የመከራ ቦታ እንደሆነ አድርገው ያስቡታል። ስለሆነም “ሲኦል” የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል እና “ሐዲስ” የሚለውን ተመሳሳይ ፍቺ ያለው የግሪክኛ ቃል “መቃብር” ብሎ በትክክል በመተርጎም መልእክቱን ግልጽ ለማድረግ ተወስኗል።
11 ከዚህም በተጨማሪ ነፈሽ የሚለውን የዕብራይስጥ ቃልና ፕስኺ የተባለውን የግሪክኛ ቃል በሁሉም ቦታዎች ላይ “ነፍስ” ብሎ መተርጎም በአንዳንድ ቋንቋዎች ግራ መጋባት ፈጥሯል። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ቃላት “ነፍስ” ተብለው ሲተረጎሙ “ነፍስ” በሰው ውስጥ ያለች ረቂቅ ነገር እንደሆነች ሊታሰብ ይችላል። በመሆኑም ነፍስ የሚለው ቃል አንድን ግለሰብ ራሱን ሳይሆን ከውስጡ የሚወጣ መንፈስን እንደሚያመለክት ተደርጎ በስህተት ሊወሰድ ይችላል። ስለዚህ “ነፍስ” የሚለውን ቃል እንደየአገባቡ ለመተርጎም ፈቃድ ተሰጠ፤ ይህ አተረጓጎም በባለማጣቀሻው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) ተጨማሪ መረጃዎች ላይ ስለ ነፍስ ከቀረበው ማብራሪያ ጋር ይስማማል። በእርግጥም ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ጽሑፉ በቀላሉ የሚገባ እንዲሆን ማድረግ ነው፤ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦች ብዙውን ጊዜ በግርጌ ማስታወሻ ላይ ተቀምጠዋል።
12. በ2013 ተሻሽሎ ከወጣው የእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም ጋር በተያያዘ ምን ለውጦች ተደርገዋል? (“በ2013 ተሻሽሎ የወጣው እንግሊዝኛው አዲስ ዓለም ትርጉም” የሚለውን በዚህ እትም ላይ የሚገኝ ርዕስም ተመልከት።)
12 ተርጓሚዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎችም የተሳሳተ መልእክት ሊያስተላልፉ የሚችሉ ሌሎች ጥቅሶች እንዳሉ ጠቁመዋል። በመሆኑም የበላይ አካሉ የእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ ተሻሽሎ እንዲዘጋጅ መስከረም 2007 ፈቃድ ሰጠ። ይህን የትርጉም ሥራ ያከናወኑት ሰዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ያነሷቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ጥያቄዎች መርምረዋል። ስለሆነም ጊዜ ያለፈባቸው የእንግሊዝኛ አባባሎች ተለውጠዋል፤ እንዲሁም ትክክለኛው መልእክት ሳይቀየር ጽሑፉን ግልጽና ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ሌሎች ቋንቋዎች ሲተረጎሙ የተገኘውን ተሞክሮ በተግባር በማዋል የእንግሊዝኛውን ጽሑፍ ‘መሳል’ ወይም የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።—ምሳሌ 27:17
ከፍተኛ አድናቆት
13. ብዙዎች በ2013 ተሻሽሎ ስለወጣው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ተሰምቷቸዋል?
13 ብዙዎች ተሻሽሎ ስለወጣው የእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም ምን ተሰምቷቸዋል? በሺዎች የሚቆጠሩ የአድናቆት ደብዳቤዎች በብሩክሊን ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተልከዋል። አንዲት እህት የሰጠችው የሚከተለው ሐሳብ የብዙዎችን ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው፦ “መጽሐፍ ቅዱስ፣ ውድ በሆኑ ጌጣጌጦች እስከ አፍጢሙ እንደተሞላ ሣጥን ነው። በ2013 ተሻሽሎ በወጣው መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ቃል ማንበብ፣ እያንዳንዱን ጌጣጌጥ እያወጡ የተለያዩ ገጽታዎቹን፣ ጥራቱን፣ ቀለሙን ብሎም ውበቱን ከማድነቅ ጋር ሊወዳደር ይችላል። ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቤ ይሖዋን ይበልጥ እንዳውቀው አድርጎኛል፤ ይሖዋ እቅፍ አድርጎኝ በሚያረጋጋ መንገድ ቃሉን እንደሚያነብልኝ አባት ነው።”
14, 15. አዲስ ዓለም ትርጉም በሌሎች ቋንቋዎች መዘጋጀቱ ምን ጥቅም አስገኝቷል?
14 የአንባቢዎችን አድናቆት ያተረፈው ተሻሽሎ የወጣው የእንግሊዝኛው አዲስ ዓለም ትርጉም ብቻ አይደለም። በሶፊያ፣ ቡልጋሪያ የሚኖሩ አንድ አረጋዊ፣ በቡልጋሪያኛ ስለተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገሩ “ለበርካታ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ያነበብኩ ቢሆንም እንዲህ ያለ ለመረዳት ቀላል የሆነና ልብ የሚነካ ትርጉም አይቼ አላውቅም” ብለዋል። በተመሳሳይም አንዲት አልባኒያዊት እህት ሙሉውን አዲስ ዓለም ትርጉም ካገኘች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “የአምላክ ቃል በአልባኒያኛ ምንኛ ደስ ይላል! ይሖዋ በራሳችን ቋንቋ የሚያናግረን መሆኑ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!”
15 በብዙ አገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ዋጋ ውድ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ አይገኝም፤ ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት በራሱ በረከት ነው። ከሩዋንዳ የተላከ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠኗቸው ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለሌላቸው ለረጅም ጊዜ እድገት ሳያደርጉ ቆይተዋል። በአካባቢያቸው የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን የሚያዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ውድ ስለሆነ ለመግዛት አቅማቸው አይፈቅድላቸውም። በዚያ ላይ ደግሞ ብዙውን ጊዜ የአንዳንድ ጥቅሶችን ትርጉም መረዳት ይከብዳቸዋል፤ ይህም ለእድገታቸው እንቅፋት ሆኗል።” አዲስ ዓለም ትርጉም በአካባቢያቸው በሚነገረው ቋንቋ ሲዘጋጅ ግን ሁኔታዎች ይለወጣሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አራት ልጆች ያሏቸው በሩዋንዳ የሚኖሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት እንዲህ ብለዋል፦ “ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ስለሰጡን ይሖዋን እንዲሁም ታማኝና ልባም ባሪያን በእጅጉ እናመሰግናቸዋለን። በጣም ድሆች ስለሆንን ለእያንዳንዱ የቤተሰባችን አባል መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት ገንዘብ የለንም። አሁን ግን ሁላችንም የየራሳችን መጽሐፍ ቅዱስ አለን። አመስጋኝነታችንን ለይሖዋ ለመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ ሆነን በየዕለቱ እናነባለን።”
16, 17. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቡ ምን እንዲያገኝ ይፈልጋል? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
16 ተሻሽሎ የወጣው የእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም ውሎ አድሮ በሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎችም ይዘጋጃል።e ሰይጣን በዚህ ረገድ የሚደረጉትን ጥረቶች ለማደናቀፍ ቢሞክርም ይሖዋ ግልጽ በሆነና በሚገባ ቋንቋ የሚያስተላልፈውን መልእክት ሕዝቦቹ በሙሉ እንዲሰሙ እንደሚፈልግ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኢሳይያስ 30:21ን አንብብ።) “ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድርም በይሖዋ እውቀት [የምትሞላበት]” ጊዜ ይመጣል።—ኢሳ. 11:9
17 የአምላክን ስም የሚያስከብረውን ይህን ትርጉም ጨምሮ ይሖዋ ካቀረበልን ማንኛውም ስጦታ ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት በየዕለቱ እንዲያነጋግራችሁ ፈቃደኛ ሁኑ። ይሖዋ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ችሎታ ስላለው ጸሎቶቻችንን በትኩረት ያዳምጣል። በዚህ መንገድ ከእሱ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋችን ይሖዋን ይበልጥ በቅርበት እንድናውቀው ይረዳናል፤ ለእሱ ያለን ፍቅርም እያደገ ይሄዳል።—ዮሐ. 17:3
a አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ተጨማሪ መረጃ ሀ1ን እንዲሁም በግንቦት 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ተመልከት።
b ቴትራግራማተን የአምላክን ስም የሚወክሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ናቸው።
c አንዳንድ የማመሳከሪያ ጽሑፎች ይህን ሐሳብ ይዘዋል፤ በእርግጥ በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት ሁሉም ምሁራን አይደሉም።
d ባለማጣቀሻው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) ተጨማሪ መረጃ 1A ላይ “መለኮታዊው ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ” የሚለውን በገጽ 1561 ላይ የሚገኝ ርዕስ ተመልከት።
e ተሻሽሎ በወጣው የእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀው የአማርኛው አዲስ ዓለም ትርጉም ታኅሣሥ 13, 2014 ወጥቷል።