የወደፊት ሕይወትህ በዕድል የተወሰነ ነው?
ሞት ከሚያስከትል አደጋ ለማምለጥ ችለህ ብትሆን ዕድል እንዳደላልህ ይሰማህ ነበርን? ወይስ በተገቢው ሰዓት ተገቢ ቦታ ላይ ልትሆን በመቻልህ አምላክን ታመሰግን ነበር?
ጥበበኛው ሰለሞን እንዲህ አለ፦ “እኔም ተመለስሁ፤ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፣ ሰልፍም ለኃያላን፣ እንጀራ ለጠቢባን፣ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።” (መክብብ 9:11) ብዙውን ጊዜ ያልተጠበቀ ነገር ይደርሳል። ጎበዝ ነው የሚባለው ሯጭ ይቆስልና ይሸነፋል የተባለው ያሸንፋል። ሐቀኛ የሆነው ነጋዴ በድንገተኛ አደጋ ሲከስር አጭበርባሪ የሆነው ተፎካካሪው ሀብታም የሚሆንበት አጋጣሚ ያገኛል። ታዲያ ሰለሞን እንደዚህ ያሉት ያልተጠበቁ ነገሮች የሚሆኑት በዕድል ምክንያት ነው ብሏልን? ፈጽሞ አላለም። “ጊዜና ያልታሰበ ኣጋጣሚ” የሚያመጡአቸው ውጤቶች ናቸው።”
ኢየሱስ ክርስቶስም ተመሳሳይ ነገር ገልጿል። አድማጮቹ በሙሉ በጋራ የሚያውቁትን አንድ ሁኔታ ጠቀሰና እንዲህ በማለት ጠየቀ፦ “ወይስ በሰሊሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሏችኋልን?” (ሉቃስ 13:4) ኢየሱስ በእነዚህ ሰዎች ላይ የደረሱትን የሞት አደጋዎች በአንድ ዓይነት ምሥጢራዊ ዕድል ላይ ወይም በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ አላላከከውም። ወይም ደግሞ የአደጋው ሰለባዎች ከሌሎቹ ይበልጥ ተነቃፊዎች ናቸው ብሎ አላመነም። አሳዛኙ አደጋ ጊዜና ያልተጠበቀ አጋጣሚ ስለሚያደርሰው ሁኔታ የሚያሳይ ምሳሌ ብቻ ነበረ።
መጽሐፍ ቅዱስ የትም ቦታ ላይ አምላክ የምንሞትበትን ቀን አስቀድሞ ወስኗል የሚለውን ሐሳብ አይደግፍም። መክብብ 3:1,2፦ “ለሁሉ ዘመን አለው፣ ለመወለድ ጊዜ አለው፣ ለመሞት ጊዜ አለው፣ ለመትከል ጊዜ አለው፣ የተተከለውን ለመንቀል ጊዜ አለው”የሚል መሆኑ እውነት ነው። ሆኖም ሰለሞን እዚህ ላይ ፍጽምና የጎደለውን የሰው ዘር የሚያጠቃውን የማያቋርጠውን የሕይወትና የሞት ዑደት ብቻ መናገሩ ነበር። እንወለዳለን፤ ጊዜው ሲደርስና ልንደርስበት የምንችለው የዕድሜ ገደባችን ይኸውም አብዛኛውን ጊዜ 70 ወይም 80 ዓመት ሲደርስ እንሞታለን። ያም ሆኖ አንድ ገበሬ “የሚተክልበትን” ወይም “የተከለውን ሚነቅልበትን” ዕለት አስቀድሞ እንደማይወስን ሁሉ የምንሞትበትንም ቀን አምላክ አስቀድሞ አልወሰነም።
እንዲያውም ሰለሞን ቆየት ብሎ አንድ ሰው ያለ ጊዜው ሊሞት እንደሚችል እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “እጅግ ክፉ አትሁን፤ እልከኛም አትሁን፤ ጊዜህ ሳይደርስ እንዳትሞት።” (መክብብ 7:17) የአንድ ሰው ዕለተ ሞት ሊለወጥ በማይችል ሁኔታ ተወስኖ ከሆነ ይህ ምክር ምን ትርጉም ይኖረዋል? ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የዕድልን መሠረተ ሐሳብ አይቀበልም። ይህን አረማዊ አስተሳሰብ የተቀበሉትን ከሐዲ እሥራኤላውያን አምላክ በጥብቅ አውግዟቸዋል። ኢሳይያስ 65:11 “እናንተ ግን ይሖዋን የተዋችሁትን ቅዱሱንም ተራራዬን የረሳችሁትን ጉድ ለተባለ ጣዖትም ማዕድ ያዘጋጃችሁትን ዕድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን የቀዳችሁትን” ይላል።
ስለዚህ አደጋ ወይም መጥፎ አጋጣሚ ሲያጋጥም በዕድል ማመካኘት ይባስ ብሎም በአምላክ ላይ ማላከክ በጣም ሞኝነት ነው!“እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ይላል መጽሐፍ ቅዱስ። የሰው ልጅ መከራ ምንጭ አምላክ ነው ማለት ይህን መሠረታዊ እውነት በቀጥታ ይቃረናል።—1 ዮሐንስ 4:8
አምላክ ለመጪው ጊዜ ያወጣው ዓላማ
የሆነ ሆኖ የመዳን ተስፋችን ጉዳይ እንዴት ነው?ሊለወጥ የማይችል ዕድል ሕይወታችንን የማይቆጣጠረው መሆኑ ያለ አንዳች ዓላማ እንዋልላለን ማለት ነውን? ፈጽሞ አይደለም። ምክንያቱም አምላክ በአጠቃላይ የሰው ልጆችን የወደፊት ሕይወት ሁኔታ ወስኗል፤ መጽሐፍ ቅዱስ “ጽድቅ ስለሚኖርባት አዲስ ምድር” መፈጠር ይናገራል።—2 ጴጥሮስ 3:13
ይህንንም ለመፈጸም አምላክ በቀጥታ በሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ይገባል። “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን”የሚለውን ጸሎት ደጋግመህ በመጸለይ ሳይታወቅህ ለዚያች ጽድቅ የሚኖርባት አዲስ ምድር መፈጠር ጸልየህ ይሆናል። (ማቴዎስ 6:10) ይህች መንግሥት በሰማይ የተቋቋመች እውነተኛ መንግሥት ናት። እንድትመጣ ስትጸልይ ያች መንግሥት የምድርን አስተዳደር ባሁኑ ጊዜ ካሉት መንግሥታት እንድትረከብ እየጸለይክ ነው።—ዳንኤል 2:44
የራስህን የወደፊት ሕይወት አስተማማኝ ማድረግ
እነዚህ አስደናቂ ሁኔታዎች የወደፊት ሕይወትህን የሚነኩበት መንገድ የሚመካው በዕድል፣ በጊዜና ባልታሰበ አጋጣሚም ላይ ሳይሆን አሁን ልትከተለው በምትመርጠው የሕይወት ጎዳና ላይ ነው። በሰሊሆሙ ግንብ ምክንያት የደረሰውን አሳዛኝ አደጋ አስታውስ። ኢየሱስ ያን ሁኔታ ትልቅ ትርጉም ያለው ትምህርት ለማስተማር ተጠቅሞበታል። ያ ግንብ የወደቀባቸው ሰዎች ከደረሰባቸው ሞት ማምለጥ አልቻሉም። ባንፃሩ የኢየሱስ አድማጮች ከመለኮታዊ ቁጣ የሚመጣባቸውን ጥፋት ማስወገድ ይችሉ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ አስጠነቀቃቸው፦ “ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።” (ሉቃስ 13:4,5) በግልጽ እንደምናየው የወደፊት ሕይወታቸውን ሁኔታ ሊመርጡ ይችሉ ነበር።
ዛሬም ለእኛ ተመሳሳይ አጋጣሚ ማለትም የራሳችንን መዳን የመፈጸም አጋጣሚ ተዘርግቶልናል። (ፊልጵስዩስ 2:12) አምላክ “ሰዎች ሁሉ ... እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ”ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) እያንዳንዳችን ከወላጆቻችን በወረስነው ባሕርይና ባስተዳደጋችን በመጠኑ የተነካን ቢሆንም አምላክ ነፃ ምርጫ ማለትም ሕይወታችንን እንዴት ልንጠቀምበት እንደምንፈልግ የመወሰን ችሎታ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 7:13,14) ትክክል የሆነውን ወይም ስሕተት የሆነውን ነገር ልናደርግ እንችላለን። ምርጫችን ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ አቋም አትርፈን ሕይወት ማግኘት ወይም እሱን ክደን መሞት ሊሆን ይችላል።
ብዙ ሰዎች ከአምላክ ነፃ ሆነው መኖር ይመርጣል። ሕይወታቸውን ቁሳዊ ሐብትን፣ ተድላን ወይም ዝናን ለማሳደድ ያውሉታል። ኢየሱስ ግን እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፤ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ።” (ሉቃስ 12:15) ታዲያ ሕይወታችን የሚመካው በምን ላይ ነው? በ1 ዮሐንስ 2፡15-17 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ። በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ይገልጻል።
ሕይወትን መምረጥ
በእውነት የአምላክን ፈቃድ እየፈጸምክ እንዳለህ እንዴት እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንክ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3) ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው ትክክለኛ እውቀት ለእምነት መሠረት ይሰጣል። “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም። ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ እርሱ እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል።” (ዕብራውያን 11:6) የሚያስፈልግህ እውቀት ቀርቧል። የይሖዋ ምስክሮች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት በቀላሉ አስፈላጊውን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ረድተዋል።a
አምላክን ለማስደሰት አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ይኖርብሃል። ልታሸንፈው የሚገባህ አንዳንድ መጥፎ ልማድ ወይም ልትተወው የሚገባህ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት ሊኖርብህ ይችላል። ለመለወጥ የማትችል መስሎህ ተስፋ አትቁረጥ። ነገሮች ሊለወጡ አይችሉም የሚለው አስተሳሰብ ሐሰተኛ ከሆነው የዕድል እምነት መሠረተ ትምህርት የመጣ ነው። ማንም ሰው በይሖዋ እርዳታ “አእምሮው ሊታደስና” “አዲሱን ሰውነት” ወይም ባሕርይ ሊያገኝ ይችላል። (ሮሜ 12:2፤ ኤፌሶን 4:22-24) አምላክን ለማስደሰት የምታደርገው ጥረት ዋጋ ሳያስገኝልህ አይቀርም። አምላክ ፈቃዱን የሚያደርጉትን ሰዎች ለመባረክ ዝግጁ ነው።
እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስን መማር ችግሮችህን በሙሉ አያቃልልም። የአምላክ አገልጋዮች እንደ ማንኛውም ሰው አደጋና ጎጂ ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ መከራን የምንቋቋምበትን ጥበብ ሊሰጠን ይችላል። (ያዕቆብ 1:5) በተጨማሪም አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዳለው ማወቁ ደስታ ያስገኝለታል። “በይሖዋ የሚታመን ሰው ደስተኛ ነው” ይላል ምሳሌ 16:20።
በአምላክ መንግሥት ሥር በምትመለሰው ገነት ውስጥ ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ ስለሚያመጣቸው ነገሮች አንሰጋም። በእርግጥ አምላክ ባሁኑ ጊዜ የሰውን ደስታ የሚረብሹትን ነገሮች ሁሉ ያስወግዳል። “እንባዎችንም ከዓይኖቻቸው ያብሳል፤ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም። ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጠናል። (ራእይ 21:4) ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የአደጋ ሰለባዎች ትንሣኤ ያገኛሉ።—ዮሐንስ 5:28,29
ይህንን ክብራማ የወደፊት ሕይወት ትወርስ ይሆን? እሥራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ በተቃረቡበት ጊዜ ሙሴ እንዲህ አላቸው፦ “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ። እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ። ... እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን ይሖዋን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።”—ዘዳግም 30:19,20
በምሕረት የለሹ የዕድል መዳፎች ውስጥ የተያዝን መከላከያ የሌለን የዕድል አሻንጉሊቶች አይደለንም። የወደፊት ደስታህና መጪው የዘላለም ሕይወትህ በእጅህ ውስጥ ነው። ሕይወትን እንድትመርጥ አጥብቀን እናሳስብሃለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች በመጻፍ የዚህ ዓይነቱ ጥናት ዝግጅት ሊደረግልህ ይችላል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ዓረማዊውን የዕድል ጽንሰ ሐሳብ የተቀበሉ ከሐዲ እሥራኤላውያን በአምላክ ተወግዘው ነበር