የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 20—ምሳሌ
የተናገሩት:- ሰሎሞን፣ አጉር፣ ልሙኤል
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም
ተጽፎ ያለቀው:- 717 ከክ.ል.በፊት ገደማ
የዳዊት ልጅ የሆነው ሰሎሞን በ1037 ከክርስቶስ ልደት በፊት የእስራኤል ንጉሥ በሆነበት ወቅት፣ “ይህን ታላቅ ሕዝብ [ለመግዛት]” የሚያስችለው “ጥበብና ዕውቀት” እንዲሰጠው ወደ ይሖዋ ጸልዮ ነበር። ይሖዋም “ጥበብና ዕውቀት” እንዲሁም “አስተዋይ ልቡና” ሰጠው። (2 ዜና 1:10-12፤ 1 ነገ. 3:12፤ 4:30, 31) በዚህም የተነሳ ሰሎሞን “ሦስት ሺህ ምሳሌዎችን” ሊናገር ችሏል። (1 ነገ. 4:32) ሰሎሞን ከተናገራቸው ጥበብ ያዘሉ ምሳሌዎች ውስጥ የተወሰኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ። ይህ ንጉሥ የተናገረው ‘እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበብ’ በመሆኑ የምሳሌን መጽሐፍ ማጥናት ከይሖዋ አምላክ የሚገኘውን ጥበብ የማጥናት ያህል ነው። (1 ነገ. 10:23, 24) እነዚህ ምሳሌዎች ጊዜ የማይሽራቸውን እውነቶች እጥር ምጥን አድርገው የያዙ ከመሆናቸውም በላይ በተነገሩበት ጊዜ የነበሩትን ያህል በዚህ ዘመንም ወቅታዊ ናቸው።
2 የሰሎሞን የግዛት ዘመን እንዲህ ያለ መለኮታዊ መመሪያ ለመስጠት ተስማሚ ወቅት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ሰሎሞን ‘በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ እንደተቀመጠ’ ይናገራል። ይህ ጊዜ በአምላክ የሚመራው የእስራኤል መንግሥት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ሲሆን ሰሎሞንም የላቀ “ንጉሣዊ ክብር” ተጎናጽፎ ነበር። (1 ዜና 29:23, 25) ሕዝቡ በሰላምና በብልጽግና ተረጋግቶ የሚኖርበት ጊዜ ነበር። (1 ነገ. 4:20-25) ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በአምላክ አገዛዝ ሥር ቢሆኑም እንኳ የግል ችግሮችና ከሰብዓዊ አለፍጽምና የሚመነጩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥሟቸው ነበር። በመሆኑም ሕዝቡ ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዲያግዛቸው የጠቢቡን ሰሎሞን እርዳታ መጠየቃቸው አያስገርምም። (1 ነገ. 3:16-28) ንጉሥ ሰሎሞን እንደዚህ ባሉት አጋጣሚዎች ፍርድ በሚሰጥበት ወቅት በሕይወት ውስጥ በየዕለቱ ከሚያጋጥሙ በርካታ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ምሳሌዎችን ተናግሯል። ሕይወታቸውን ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ መምራት የሚፈልጉ ሰዎች እነዚህን አጫጭር ሆኖም ድንቅ አባባሎች ከፍ አድርገው ይመለከቷቸዋል።
3 ዘገባው ምሳሌዎቹን የጻፈው ሰሎሞን መሆኑን አይገልጽም። ሆኖም ምሳሌዎችን “ተናገረ” ተብሏል፤ እንዲሁም “በጥልቅ አሰበ፤ ተመራመረም፤ ብዙ ምሳሌዎችንም በሥርዐት አዘጋጀ” መባሉ ምሳሌዎቹ ለኋለኞቹ ትውልዶች እንዲተላለፉ ፍላጎት እንደነበረው ያሳያል። (1 ነገ. 4:32፤ መክ. 12:9) በዳዊትና በሰሎሞን ዘመን በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ከነበሩት ባለ ሥልጣናት መካከል ጸሐፊዎችም ይገኙ ነበር። (2 ሳሙ. 20:25፤ 2 ነገ. 12:10) የሰሎሞንን ምሳሌዎች የጻፏቸውና ያሰባሰቧቸው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የነበሩት እነዚህ ጸሐፊዎች ይሁኑ ወይም ሌላ ሰው የምናውቀው ነገር የለም፤ ሆኖም የእርሱ ዓይነት ተሰጥኦ የነበረው የማንኛውም መሪ አባባሎች ከፍ ተደርገው የሚታዩ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ በጽሑፍ ይሰፍሩ ነበር። መጽሐፉ ከሌሎች ስብስቦች ተወስዶ የተጠናቀረ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል።
4 የምሳሌ መጽሐፍ በአምስት ቦታዎች ሊከፈል ይችላል። እነዚህም:- (1) “የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች” የሚል መግቢያ ያላቸው ከ1-9 ያሉት ምዕራፎች፣ (2) “የሰሎሞን ምሳሌዎች” የተባሉት ከ10-24 ያሉት ምዕራፎች፣ (3) “እነዚህ የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የቀዷቸው ሌሎች የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው” በሚል መግቢያ የሚጀምሩት ከ25-29 ያሉት ምዕራፎች፣ (4) “የያቄ ልጅ የአጉር ቃል” በማለት የሚጀምረው ምዕራፍ 30 እንዲሁም (5) “ንጉሥ ልሙኤልን እናቱ ያስተማረችው ቃል” የሚገኝበት ምዕራፍ 31 ናቸው። ከዚህ መመልከት እንደምንችለው አብዛኞቹን ምሳሌዎች የተናገረው ሰሎሞን ነው። የአጉርንና የልሙኤልን ማንነት በተመለከተ በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም። አንዳንድ ተንታኞች ልሙኤል የሰሎሞን ሌላ ስም ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል።
5 የምሳሌ መጽሐፍ የተጻፈውና የተሰባሰበው መቼ ነው? አብዛኛው ክፍል የተጻፈው በሰሎሞን የግዛት ዘመን (ከ1037-998 ከክርስቶስ ልደት በፊት) ንጉሡ የክህደት ጎዳና ከመከተሉ በፊት እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። አጉርና ልሙኤል ማን እንደሆኑ በእርግጠኝነት ማወቅ ስላልተቻለ ምሳሌዎቹን መቼ እንደጻፏቸው ማወቅ አይቻልም። ከምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የተወሰነው ክፍል የተሰባሰበው በሕዝቅያስ የግዛት ዘመን (ከ745-717 ከክርስቶስ ልደት በፊት) በመሆኑ መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ ተሰባስቦ ያለቀው ከሕዝቅያስ የግዛት ዘመን በፊት ሊሆን አይችልም። የመጨረሻዎቹ ሁለት ክፍሎችም የተሰባሰቡት በንጉሥ ሕዝቅያስ መሪነት ይሆን? በባለማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ላይ የሚገኘው የምሳሌ 31:31 የግርጌ ማስታወሻ ፍንጭ የሚሰጥ ማብራሪያ ይዟል:- “አንዳንድ የዕብራይስጥ እትሞች፣ ንጉሥ ሕዝቅያስ በእርሱ ጸሐፊዎች በተገለበጠው ጽሑፍ ላይ ሥራው መጠናቀቁን ለማመልከት የሚያሰፍረውን ፊርማ ይኸውም ትሪግራማተን ወይም ቼሀተ፣ ዛይን፣ ቆሀፈ (חזק) የሚባሉትን ሦስት ፊደላት ይዘዋል።”
6 በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ መጽሐፉ መጀመሪያ ላይ የሚጠራው በመግቢያው ላይ ባለው ሚሽለህ በሚለው ቃል ነበረ፤ ትርጉሙም “ምሳሌዎች” ማለት ነው። ሚሽለህ የሚለው ቃል ማሻል የሚለው የዕብራይስጥ ስም ብዙ ቁጥር ሲሆን ማሻል “ተመሳሳይ መሆን” ወይም “ተነጻጻሪ መሆን” የሚል ትርጉም ካለው መሠረታዊ ቃል የተገኘ እንደሆነ ይታሰባል። እነዚህ ቃላት የመጽሐፉን ይዘት ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ፤ ምክንያቱም የምሳሌ መጽሐፍ ብዙውን ጊዜ ነገሮችን በማመሳሰል ወይም በማነጻጸር የተገለጹ እጥር ምጥን ያሉና አድማጩ እንዲያስብ ለማድረግ ታቅደው የተነገሩ አባባሎችን የያዘ ነው። ምሳሌዎቹ አጫጭር መሆናቸው ለመረዳት ቀላልና ማራኪ ያደርጋቸዋል፤ ከዚህም በላይ በዚህ መልክ መቀመጣቸው ለማስተማር፣ ለማጥናትና ለማስታወስ ያመቻል። ነጥቡም ከአእምሮ አይጠፋም።
7 በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ነጥቦቹ የተገለጹበት መንገድም በጣም ማራኪ ነው። የተጻፈው በዕብራይስጥ የግጥም አጻጻፍ ስልት ሲሆን የመጽሐፉ አብዛኛው ክፍል በንጽጽር መልክ የተቀመጠ ነው። በዚህ የአጻጻፍ ዘይቤ የስንኞቹ የመጨረሻ ቃላት ቤት አይመቱም። ከዚህ ይልቅ ወጥ የሆነ ምት ያላቸው ስንኞች ተነጻጻሪ ሐሳቦችን ያስተላልፋሉ። መጽሐፉ ውበትና የማስተማር ኃይል ሊኖረው የቻለውም ሐሳቡ በዚህ ዓይነት ወጥ የሆነ ሥርዓት ተከትሎ በመገለጹ ነው። በምሳሌዎቹ ላይ የሚገለጹት ሐሳቦች ተመሳሳይ ወይም ተቃራኒ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ያም ቢሆን ንጽጽሩ ሐሳቡን ለማስፋትና ለማዳበር እንዲሁም ነጥቡን ለማስተላለፍ ያስችላል። ተመሳሳይ የሆኑ ነገሮች የተነጻጸሩባቸው አባባሎች በምሳሌ 11:25፤ 16:18 እንዲሁም 18:15 ላይ የሚገኙ ሲሆን በመጽሐፉ ውስጥ በብዛት የተሠራበት ተቃራኒ ነገሮችን የማነጻጸር ስልት ደግሞ በምሳሌ 10:7, 30፤ 12:25፤ 13:25 እና 15:8 ላይ ይታያል። በመጽሐፉ መደምደሚያ ላይ ደግሞ ሌላ ዓይነት ስልት ተንጸባርቋል። (ምሳሌ 31:10-31) እነዚህ 22 ቁጥሮች የተቀናበሩት እያንዳንዱ ቁጥር በዕብራይስጡ ሆሄያት ቅደም ተከተል መሠረት እንዲጀምር ተደርጎ ነው፤ ይህ ዓይነቱ ስልት በበርካታ መዝሙሮች ላይም ተሠርቶበታል። ይህ ዓይነቱ አጻጻፍ በጥንቶቹ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ በውበቱ ተወዳዳሪ የለውም።
8 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የሥነ ምግባር ሕግጋትን ለመግለጽ በምሳሌ መጽሐፍ በሰፊው የተጠቀሙ መሆኑም የመጽሐፉን ትክክለኛነት ያረጋግጣል። ያዕቆብ የምሳሌን መጽሐፍ ጠንቅቆ ከማወቁም በላይ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን አስመልክቶ በሰጠው ግሩም ምክር ላይ የመጽሐፉን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅሞባቸዋል። (ምሳሌ 14:29 እና 17:27ን ከያዕቆብ 1:19, 20፤ ምሳሌ 3:34ን ከያዕቆብ 4:6፤ ምሳሌ 27:1ን ከያዕቆብ 4:13, 14 ጋር አወዳድር።) ከምሳሌ መጽሐፍ በቀጥታ የተወሰዱ ሐሳቦችም በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ ይገኛሉ:- ሮሜ 12:20—ምሳሌ 25:21, 22፤ ዕብራውያን 12:5, 6—ምሳሌ 3:11, 12፤ 2 ጴጥሮስ 2:22—ምሳሌ 26:11።
9 ከዚህም በላይ የምሳሌ መጽሐፍ ከቀሪው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር መስማማቱ ‘የቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ’ ክፍል መሆኑን ያረጋግጣል። ከሙሴ ሕግ፣ ከኢየሱስ ትምህርት እንዲሁም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትና ሐዋርያት ከጻፏቸው መጻሕፍት ጋር ሲነጻጸር የሚያስደንቅ የሐሳብ ስምምነት አለው። (ምሳሌ 10:16—1 ቆሮንቶስ 15:58 እና ገላትያ 6:8, 9፤ ምሳሌ 12:25—ማቴዎስ 6:25፤ ምሳሌ 20:20—ዘፀአት 20:12 እና ማቴዎስ 15:4ን ተመልከት።) ሌላው ቀርቶ ምድር ለሰው ልጅ መኖሪያነት መዘጋጀቷን በመሳሰሉ ነጥቦች ላይ እንኳ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ ይዟል።—ምሳሌ 3:19, 20፤ ዘፍ. 1:6, 7፤ ኢዮብ 38:4-11፤ መዝ. 104:5-9
10 መጽሐፉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ የሚያረጋግጠው ሌላው ማስረጃ በኬሚካልም ሆነ በሕክምና ወይም በጤና መስክ፣ ከሳይንስ አንጻር ትክክለኛ ሐሳብ የያዘ መሆኑ ነው። ምሳሌ 25:20 ሶዳ ከአሲድ ጋር ሲዋሃድ ምን እንደሚሆን ይናገራል። ምሳሌ 31:4, 5 ደግሞ የአልኮል መጠጥ አስተሳሰብን እንደሚያዛባ ከሚገልጸው ዘመናዊ የሳይንስ ግኝት ጋር ይስማማል። በርካታ ሐኪሞችና ጤናማ አመጋገብን በተመለከተ ምክር የሚሰጡ ባለሞያዎች ማር ለጤና ጠቃሚ መሆኑን ይስማማሉ፤ ይህም “ልጄ ሆይ፤ መልካም ነውና ማር ብላ” የሚለውን ምሳሌ እንድናስታውስ ያደርገናል። (ምሳሌ 24:13) ከስሜት ጋር የተያያዙ ችግሮች ስለሚያስከትሉት አካላዊ ሕመም፣ ዘመናዊ ምርምሮች ያገኙት ውጤትም ቢሆን አዲስ አይደለም። የምሳሌ መጽሐፍ “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው” ይላል።—17:22፤ 15:17
11 በእርግጥም የምሳሌ መጽሐፍ እያንዳንዱን የሰው ልጅ ፍላጎትና ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የሚዳስስ በመሆኑ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል:- “በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ተስማሚ የሆነ መመሪያ ያልተሰጠበት ጉዳይ የለም፤ ተገቢው ማበረታቻ ያልተሰጠው መልካም ምግባር ወይም እርማት ያልተሰጠበት ክፉ ድርጊት የለም። . . . በዚህ ጥንታዊ መጽሐፍ ውስጥ ሰዎች የሚያንጸባርቁት ማንኛውም ዓይነት ባሕርይ ተገልጿል፤ ከተጻፈ ሦስት ሺህ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ጸሐፊው አሁን የተናገረው ያህል ሐሳቡ ዛሬም ትክክል ነው።”—የስሚዝ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል፣ 1890 ጥራዝ 3፣ ገጽ 2616
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
19 በምሳሌ መጽሐፍ መግቢያ ላይ መጽሐፉ የተጻፈበት ጠቃሚ ዓላማ በሚከተሉት ቃላት ተገልጿል:- “ጥበብንና ተግሣጽን ለመቀበል፤ ጥልቅ ሐሳብ የሚገልጡ ቃላትን ለማስተዋል፤ ጽድቅን፣ ፍትህንና ሚዛናዊ ብያኔን በማድረግ፣ የተገራ ጠቢብ ልቦናን ለማግኘት፤ ብስለት ለሌላቸው አስተዋይነትን፣ በዕድሜ ለጋ ለሆኑት ዕውቀትንና ልባምነትን ለመስጠት።” (1:2-4) መጽሐፉ ከዚህ ዓላማው ጋር በሚስማማ መልኩ እውቀትን፣ ጥበብንና ማስተዋልን ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ሲሆን እነዚህ ሦስት ባሕርያት በየበኩላቸው ጠቃሚ ናቸው።
20 (1) እውቀት ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ሰው በድንቁርና መኖር አይበጀውም። የእውቀት መጀመሪያ ይሖዋን መፍራት ስለሆነ ማንም ሰው ይሖዋን ካልፈራ ትክክለኛ እውቀት ሊያገኝ አይችልም። እውቀት ምርጥ ከሆነ ወርቅ እንኳ ይበልጥ ተፈላጊ ነው። ለምን? ጻድቃን በእውቀት ከጥፋት ይጠበቃሉ፤ እውቀት በችኮላ ወደ ኃጢአት ከማምራት ያድነናል። ስለዚህ እውቀትን መፈለጋችንና መረዳታችን በጣም አስፈላጊ ነው! እውቀት በጣም ውድ ነገር ነው። ስለዚህ “ጆሮህን አዘንብለህ የጠቢባንን ቃላት ስማ፣ ልብህንም ወደ እውቀቴ አድርግ።”—22:17 የ1954 ትርጉም፤ 1:7፤ 8:10፤ 11:9፤ 18:15፤ 19:2፤ 20:15
21 (2) ጥበብ ሲባል እውቀትን ለይሖዋ ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ በትክክል የመጠቀም ችሎታ ማለት ሲሆን እርሱም “ታላቅ ነገር” ነው። ስለዚህ ጥበብን አግኙ። የጥበብ ምንጭ ይሖዋ ነው። ሕይወት ሰጪ የሆነውን ጥበብ ለማግኘት በመጀመሪያ ይሖዋ አምላክን ማወቅና መፍራት ያስፈልጋል። ታላቁ የጥበብ ምሥጢር ይህ ነው። ስለዚህ ሰውን ሳይሆን አምላክን ፍሩ። ጥበብ፣ የራስዋ ስብዕና ያላት መስላ በመቅረብ ሰው ሁሉ አካሄዱን እንዲያስተካክል ማሳሰቢያ ትሰጣለች። ጥበብ በጎዳናዎች ላይ ትጮሃለች። ይሖዋ፣ ብስለት የጎደላቸውና ማስተዋል የሌላቸው ሁሉ ከመንገዳቸው እንዲመለሱና የጥበብን እንጀራ እንዲበሉ ጥሪ ያቀርባል። እንዲህ ካደረጉ የይሖዋ ፍርሃት ስለሚያድርባቸው ድሆች ቢሆኑም ደስተኞች መሆን ይችላሉ። ጥበብ የምታስገኛቸው በረከቶች በጣም ብዙ ናቸው፤ ከጥበብ የሚገኙት ውጤቶችም በጣም ጠቃሚ ናቸው። ከጉዳት የሚጠብቀን የማሰብ ችሎታ ለማዳበር የሚያስፈልጉን መሠረታዊ ነገሮች ጥበብና እውቀት ናቸው። ጥበብ እንደ ማር ጠቃሚና ጣፋጭ ናት። ከወርቅ የበለጠ ውድ ዋጋ ያላት ሲሆን የሕይወት ዛፍም ተብላለች። ጥበብ ሕይወትን ከአደጋ ስለምትጠብቅ ሰዎች ጥበብ በማጣታቸው ይጠፋሉ፤ ጥበብ ከሕይወት ተለይታ አትታይም።—4:7፤ 1:7, 20-23፤ 2:6, 7, 10, 11፤ 3:13-18, 21-26፤ 8:1-36፤ 9:1-6, 10፤ 10:8፤ 13:14፤ 15:16, 24፤ 16:16, 20-24፤ 24:13, 14
22 (3) ከእውቀትና ከጥበብ በተጨማሪ ማስተዋል በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህም የተነሳ “ያለህን ሁሉ ብታስከፍልህም ማስተዋልን ገንዘብህ አድርጋት” ተብሏል። ማስተዋል ማለት አንድን ነገር ከሌሎች ተዛማጅ ክፍሎቹ ጋር አገናዝቦ የመረዳት ችሎታ ነው። የሰው ልጅ በራሱ ማስተዋል ሊተማመን ስለማይችል ነገሮችን ሁልጊዜ በአምላክ ዓይን መመልከት ማለት ነው። አንድ ሰው በሚያደርገው ነገር ይሖዋን የሚቃወም ከሆነ ማስተዋል ወይም የማመዛዘን ችሎታ ፈጽሞ ሊኖረው አይችልም! አስተዋዮች መሆን ከፈለግን ይህን ባሕርይ እንደ ተቀበረ ሀብት አጥብቀን ልንፈልገው ይገባል። ነገሮችን ለማስተዋል እውቀት ማግኘት ይኖርብናል። አስተዋይ ሰው እውቀት ለማግኘት የሚያደርገው ፍለጋ ብዙ በረከት ያስገኝለታል፤ ጥበብንም ያገኛል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ቁጥር ሥፍር ከሌላቸው የዚህ ዓለም እንቅፋቶች (ለአብነት ያህል፣ ሰዎችን አጥምደው ከእነርሱ ጋር በጨለማ መንገድ እንዲጓዙ ለማድረግ ከሚሞክሩ በርካታ መጥፎ ሰዎች) ይጠበቃል። ሕይወት የሚያስገኝ እውቀት፣ ጥበብና ማስተዋል መስጠት የሚችለው ይሖዋ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!—4:7፤ 2:3, 4፤ 3:5፤ 15:14፤ 17:24፤ 19:8፤ 21:30
23 የምሳሌ መጽሐፍ፣ ካሉት ጠቃሚ ዓላማዎች ጋር በሚስማማ መልኩ ማስተዋል ለማግኘት እንዲሁም “የሕይወት ምንጭ” የሆነውን ልባችንን ለመጠበቅ የሚረዱን ጥበብ ያዘሉና በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ በርካታ ምክሮችን ይሰጠናል። (4:23) ከዚህ ቀጥሎ በመጽሐፉ ውስጥ ጎላ ብለው ከተገለጹት ጥበብ ያዘሉ ምክሮች አንዳንዶቹ ቀርበዋል።
24 በክፉዎችና በጻድቃን መካከል ያለው ልዩነት:- ክፉ ሰው በጠማማ መንገዱ ይጠመዳል፤ እንዲሁም በቁጣ ቀን ሀብቱ አያድነውም። ጻድቅ ሰው ግን ሕይወት በሚያስገኝ ጎዳና ላይ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ወሮታ ይከፍለዋል።—2:21, 22፤ 10:6, 7, 9, 24, 25, 27-32፤ 11:3-7, 18-21, 23, 30, 31፤ 12:2, 3, 7, 28፤ 13:6, 9፤ 14:2, 11፤ 15:3, 8, 29፤ 29:16
25 የንጹሕ ሥነ ምግባር አስፈላጊነት:- ሰሎሞን ከሥነ ምግባር ብልግና እንድንርቅ ተደጋጋሚ ምክር ሰጥቷል። አመንዝሮች መቅሰፍትና ውርደት ይደርስባቸዋል፤ የሚደርስባቸው ነቀፋም ሊሻር አይችልም። አንድ ወጣት “የስርቆት ውሃ” ጣፋጭ ሆኖ ይታየው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ጋለሞታ ሴት ራሷንም ሆነ ያጠመደችውን ብስለት የጎደለው ሰው ይዛ ወደ ሞት ትወርዳለች። ይሖዋ በሥነ ምግባር ርኩሰት የሚወድቁትን ሁሉ ያወግዛል።—2:16-19፤ 5:1-23፤ 6:20-35፤ 7:4-27፤ 9:13-18፤ 22:14፤ 23:27, 28
26 ራስን የመግዛት አስፈላጊነት:- ሰካራምነትና ሆዳምነት በጥብቅ ተወግዘዋል። የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ በምግብም ሆነ በመጠጥ ረገድ ልከኞች መሆን ይኖርባቸዋል። (20:1፤ 21:17፤ 23:21, 29-35፤ 25:16፤ 31:4, 5) ለቁጣ የዘገዩ ሰዎች ታላቅ ማስተዋል ያላቸው ከመሆኑም በላይ ከተማን ከሚማርክ ኃያል ሰው ይበልጣሉ። (14:17, 29፤ 15:1, 18፤ 16:32፤ 19:11፤ 25:15, 28፤ 29:11, 22) አጥንት ከሚያነቅዘው ቅናትና ምቀኝነት ለመራቅም ራስን መግዛት አስፈላጊ ነው።—14:30፤ 24:1፤ 27:4፤ 28:22
27 ጥበብ የተሞላበትና ጥበብ የጎደለው አነጋገር:- ጠማማ ንግግር፣ ስም ማጥፋት፣ በሐሰት መመሥከርና ውሸት መናገር በይሖዋ ዘንድ የተጠሉ በመሆናቸው መጋለጣቸው አይቀርም። (4:24፤ 6:16-19፤ 11:13፤ 12:17, 22፤ 14:5, 25፤ 17:4፤ 19:5, 9፤ 20:17፤ 24:28፤ 25:18) አንድ ሰው በአንደበቱ መልካም ነገሮችን ብቻ የሚናገር ከሆነ የሕይወት ምንጭ ይሆንለታል፤ የሞኝ ሰው አንደበት ግን ጥፋት ያመጣበታል። “አንደበት የሞትና የሕይወት ኀይል አላት፤ የሚወዷትም ፍሬዋን ይበላሉ።” (18:21) ስም ማጥፋት፣ አታላይ ንግግር፣ መሸንገልና ቸኩሎ መናገር ተወግዘዋል። አምላክን ለማስከበር እውነት መናገር የጥበብ መንገድ ነው።—10:11, 13, 14፤ 12:13, 14, 18, 19፤ 13:3፤ 14:3፤ 16:27-30፤ 17:27, 28፤ 18:6-8, 20፤ 26:28፤ 29:20፤ 31:26
28 ኩራት የሚያስከትለው ውድቀትና የትሕትና አስፈላጊነት:- ኩሩ ሰው ከሆነው በላይ ራሱን ከፍ ከፍ ስለሚያደርግ ለውድቀት ይዳረጋል። ኩሩ ልብ ያላቸው በይሖዋ ዘንድ የተጠሉ ሲሆን ለትሑታን ግን ጥበብ፣ ክብር፣ ሀብትና ሕይወት ይሰጣቸዋል።—3:7፤ 11:2፤ 12:9፤ 13:10፤ 15:33፤ 16:5, 18, 19፤ 18:12፤ 21:4፤ 22:4፤ 26:12፤ 28:25, 26፤ 29:23
29 ታካችነትን አስወግዶ ትጉ መሆን:- ሰነፍ ሰው በብዙ መንገዶች ተገልጿል። ሰነፍ ሰው ከጉንዳን ትምህርት መውሰድና ጠቢብ መሆን ይኖርበታል። ትጉህ ሰው ግን ይበለጽጋል!—1:32፤ 6:6-11፤ 10:4, 5, 26፤ 12:24፤ 13:4፤ 15:19፤ 18:9፤ 19:15, 24፤ 20:4, 13፤ 21:25, 26፤ 22:13፤ 24:30-34፤ 26:13-16፤ 31:24, 25
30 ጥሩ ባልንጀራ መምረጥ:- ይሖዋን ከማይፈሩ፣ ከኃጢአተኞች ወይም ከተላሎች፣ ከግልፍተኞች፣ ከወሬኞች ወይም ከሆዳሞች ጋር መወዳጀት ትልቅ ስህተት ነው። ከዚህ ይልቅ ከጠቢባን ጋር ብትወዳጁ ይበልጥ ጠቢብ ትሆናላችሁ።—1:10-19፤ 4:14-19፤ 13:20፤ 14:7፤ 20:19፤ 22:24, 25፤ 28:7
31 የተግሣጽና የእርማት አስፈላጊነት:- ‘እግዚአብሔር የሚወደውን ይገሥጻል፤’ ስለዚህ የአምላክን ተግሣጽ የሚቀበሉ ሁሉ ክብርና ሕይወት ያገኛሉ። እርማት የሚጠላ ሰው ግን ውርደት ይከናነባል።—3:11, 12፤ 10:17፤ 12:1፤ 13:18፤ 15:5, 31-33፤ 17:10፤ 19:25፤ 29:1
32 ጥሩ ሚስት ስለመሆን የተሰጠ ምክር:- የምሳሌ መጽሐፍ ሚስቶች ተጨቃጫቂና አሳፋሪ እንዳይሆኑ ደጋግሞ ይመክራል። ልባም የሆነችና ፈሪሃ አምላክ ያላት ጠባየ መልካም ሚስት በአንደበቷ ፍቅራዊ ደግነት አለ፤ እንዲህ ያለችውን ሚስት የሚያገኝ ሁሉ የይሖዋን ሞገስ ያገኘ ያህል ነው።—12:4፤ 18:22፤ 19:13, 14፤ 21:9, 19፤ 27:15, 16፤ 31:10-31
33 ልጆችን ማሳደግ:- የአምላክን ትእዛዛት ‘እንዳይረሱ’ አዘውትራችሁ አስተምሯቸው። ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የይሖዋን ቃል አስጠኗቸው። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በበትር ከመምታት ወደኋላ አትበሉ፤ በትርና እርማት የፍቅር መግለጫ ከመሆናቸውም ሌላ ልጆች ጥበበኛ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። ልጆችን በአምላክ መንገድ የሚያሳድጉ ሁሉ አባትና እናታቸውን የሚያስደስቱ ጥበበኛ ልጆች ይኖሯቸዋል።—4:1-9፤ 13:24፤ 17:21፤ 22:6, 15፤ 23:13, 14, 22, 24, 25፤ 29:15, 17
34 ሌሎችን የመርዳት ኃላፊነት:- ይህ ጉዳይ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ጊዜ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። ጠቢብ ሰው ሌሎችን ለመጥቀም ሲል እውቀትን ማስፋፋት ይኖርበታል። በተጨማሪም አንድ ሰው ለድኾች ለጋስ መሆን አለበት፤ ይህን ሲያደርግም ብድራት ለሚከፍለው ለይሖዋ እንዳበደረ ይቆጠራል።—11:24-26፤ 15:7፤ 19:17፤ 24:11, 12፤ 28:27
35 በይሖዋ መታመን:- የምሳሌ መጽሐፍ በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድንታመን በመምከር የችግሮቻችንን ዋነኛ መንስኤ ይጠቁማል። በመንገዳችን ሁሉ ይሖዋን ማወቅ ይኖርብናል። ሰው እቅድ ያወጣ ይሆናል፤ ሆኖም እርምጃውን ሊመራለት የሚገባው ይሖዋ ነው። የይሖዋ ስም፣ ጻድቅ ሰው ሮጦ ከአደጋ የሚጠለልበት ጽኑ ግንብ ነው። ይሖዋን ተስፋ አድርጉ፤ አመራር ለማግኘትም ቃሉን ተመልከቱ።—3:1, 5, 6፤ 16:1-9፤ 18:10፤ 20:22፤ 28:25, 26፤ 30:5, 6
36 የምሳሌ መጽሐፍ ራሳችንንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ለማስተማርና ለመምከር የሚረዳ በጣም ጠቃሚ መጽሐፍ ነው! በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሳይጠቀስ የታለፈ የሰብዓዊ ግንኙነት ዘርፍ የለም። ራሱን ከእምነት ባልንጀሮቹ የሚያገል ሰው አለ? (18:1) ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ሰው አንድን ጉዳይ ከሁለቱም ወገን ከመስማቱ በፊት ውሳኔ ላይ ይደርሳል? (18:17) በሌሎች ላይ ጉዳት በማድረስ የሚቀልድ ሰው አለ? (26:18, 19) የማዳላት ዝንባሌ ያለው ሰው አለ? (28:21) ነጋዴው ስለ ንግዱ፣ ገበሬው ስለ እርሻው እንዲሁም ባል፣ ሚስትና ልጆች ጠቃሚ የሆነ ምክር ተሰጥቷቸዋል። ወላጆች፣ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ወጥመዶች እንዲያስወግዱ መርዳት የሚችሉበት መንገድ ተነግሯቸዋል። ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ብስለት የሚጎድላቸውን ሊያስተምሩ ይችላሉ። የምሳሌ መጽሐፍ በየትኛውም የዓለም ክፍል ብንኖር ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር ይሰጠናል፤ መጽሐፉ የሚሰጣቸው መመሪያዎችና ምክሮች በፍጹም ጊዜ አያልፍባቸውም። ዊልያም ሊዮን ፌልፕስ የተባሉ አሜሪካዊ የትምህርት ባለሞያ “የምሳሌ መጽሐፍ ዛሬ ጠዋት ከወጣው ጋዜጣ የበለጠ ወቅታዊ ነው” በማለት ተናግረዋል።a የምሳሌ መጽሐፍ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ስለሆነ ወቅታዊ፣ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልና ጠቃሚ ነው።
37 በአብዛኛው በሰሎሞን የተነገረው የምሳሌ መጽሐፍ ነገሮችን ለማቅናት የሚጠቅም በመሆኑ የሰውን ዘር ሁሉን ወደሚችለው አምላክ ይመልሳል። በማቴዎስ 12:42 ላይ “ከሰሎሞን የሚበልጥ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስም ሰዎችን ወደ አምላክ መልሷል።
38 ይሖዋ ታላቅ ጥበብ ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን የመንግሥቱ ዘር እንዲሆን በመምረጡ በጣም አመስጋኞች መሆን ይገባናል! ግዛቱ ከንጉሥ ሰሎሞን እንኳ የበለጠ አስደሳችና ሰላም የሰፈነበት ስለሚሆን ዙፋኑ “በጽድቅ ትጸናለች።” የዚህን መንግሥት አገዛዝ በተመለከተ “ፍቅርና ታማኝነት ንጉሥን ይጠብቁታል፤ በፍቅርም ዙፋኑ ይጸናል” ይባልለታል። ይህ መንግሥት የሰው ልጅ ዘላለማዊ የሆነ የጽድቅ መስተዳደር የሚያገኝበትን ዘመን ያመጣል፤ የምሳሌ መጽሐፍ ይህን መንግሥት በተመለከተ “ንጉሥ ለድኻ ትክክለኛ ፍርድ ቢሰጥ፣ ዙፋኑ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ይላል። በዚህ መንገድ የምሳሌ መጽሐፍ እውቀት፣ ጥበብ፣ ማስተዋል አልፎ ተርፎም የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ መንገዳችንን የሚያበራልን መሆኑን ማወቃችን ያስደስታል። ከዚህም በላይ መጽሐፉ ይሖዋ የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ መሆኑንና ይህንን ጥበብ የመንግሥቱ ወራሽ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል እንደሚያስተላልፍ ይገልጻል። የምሳሌ መጽሐፍ ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ስለሚያስተዳድርባቸው የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል።—ምሳሌ 25:5፤ 16:12፤ 20:28፤ 29:14
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ትሬዠሪ ኦቭ ዘ ክርስቺያን ፌዝ፣ 1949፣ በስተበር እና በክላርክ የተዘጋጀ፣ ገጽ 48