መጻሕፍት፣ መጻሕፍት፣ መጻሕፍት!
ጥንት የነበረው ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም” ሲል ጽፏል። (መክብብ 12:12) በብሪታንያ በ1995 በአማካይ አንድ አዲስ መጽሐፍ 580 ለሚያክሉ ሰዎች የታተመ ሲሆን ይህ ደግሞ አገሪቱን አዳዲስ መጻሕፍት በማሳተም ረገድ በዓለም የመሪነቱን ቦታ እንድትይዝ አድርጓታል። ብሪታንያ 95,015 መጻሕፍት ስታሳትም ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላት ቻይና ደግሞ 92,972 መጻሕፍትን በማሳተም በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በመቀጠል ጀርመን 67,206 መጻሕፍት፣ ዩናይትድ ስቴትስ 49,276 እና ፈረንሳይ 41,234 መጻሕፍትን አሳትመዋል። የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ጋዜጣ “ብሪታንያ በዓለም የመሪነቱን ቦታ በቀላሉ ለመያዝ የቻለችው እንግሊዝኛ በስፋት የሚሠራበት ቋንቋ በመሆኑ ምክንያት ነው” ሲል ገልጿል።
የመጽሐፍ ሽያጭ ንግድ ለበርካታ ዓመታት የቀነሰ መሆኑን ሪፖርቶች ሲያሳዩ በአሁኑ ጊዜ በብሪታንያ በዓመት ውስጥ አንድ ወይም ከአንድ በላይ መጻሕፍት የሚገዙት 80 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ ሰዎች የሚገዟቸውን መጻሕፍት በሙሉ ያነቧቸዋል?
መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት መሰራጨቱንም ሆነ መነበቡን የቀጠለ መጽሐፍ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ከ2,120 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። እስካሁን መጽሐፍ ቅዱስ ከሌለህ በአቅራቢያህ ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጋር በመገናኘት እንዲኖርህ አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ ካለህ ደግሞ አውጣውና በዚህ መጽሔት ውስጥ ባሉት የጥናት ርዕሶች ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያዎች ትክክል መሆናቸውን አረጋግጥ። ይህን ስታደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት ሰጪ እውቀት ታገኛለህ።