‘የሰው ሁለንተናዊ ግዴታ’
“ይህ የሰው ሁለንተናው [“ሁለንተናዊ ግዴታው፣” NW] ነውና እግዚአብሔርን ፍራ ትእዛዛቱንም ጠብቅ።”— መክብብ 12:13
1, 2. በአምላክ ፊት ስላለብን ግዴታ ማሰባችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
“እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድን ነው?” ይህን ጥያቄ ያነሣው በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ነቢይ ነው። ከዚያም ፍትሕን ታደርግ ዘንድ ደግነትንም ትወድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር ቦታህን ጠብቀህ ትሄድ ዘንድ ነው በማለት ይሖዋ ምን እንደሚፈልግ በግልጽ አስቀምጦታል።— ሚክያስ 6:8
2 ግላዊነትና በራስ የመመራት መንፈስ በገነነበት በአሁኑ ጊዜ አምላክ ከእናንተ የሚፈልገው ነገር አለ የሚለው ሐሳብ ለብዙዎቹ ሰዎች አይዋጥላቸውም። ግዴታ ውስጥ መግባት አይፈልጉም። ይሁን እንጂ ሰሎሞን በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ የደረሰበትን መደምደሚያ የገለጸው እንዴት ነው? “የነገሩን ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ግዴታው ነውና እውነተኛውን አምላክ ፍራ ትእዛዛቱንም ጠብቅ።”— መክብብ 12:13 NW
3. ለመክብብ መጽሐፍ ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን ለምንድን ነው?
3 ያለንበት ሁኔታና ስለ ሕይወት ያለን አመለካከት ምንም ይሁን ምን ወደዚህ መደምደሚያ ያደረሱትን ነገሮች መመርመራችን በእጅጉ ይጠቅመናል። ይህን መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ንጉሥ ሰሎሞን የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ክፍል የሆኑትን አንዳንድ ነገሮች በጥሞና ተመልክቷል። አንዳንዶች በችኮላ እርሱ የሰጠው ትንተና ፈጽሞ አሉታዊ ነው ብለው ይደመድሙ ይሆናል። ይሁንና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ እንደመሆኑ መጠን የምንሠራቸውን ሥራዎችና በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች እንድንገመግም ይረዳናል። ይህም ደስታችን እንዲጨምር ያደርጋል።
የሕይወትን ዋነኛ ፍላጎቶች ማሟላት
4. ሰሎሞን በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ የመረመረውና የተናገረው ስለ ምን ነገር ነው?
4 ሰሎሞን ‘የሰው ልጆችን ሥራ’ ከሥረ መሠረቱ መርምሯል። “ከሰማይም በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ እፈልግና እመረምር ዘንድ ልቤን አተጋሁ” ብሏል። ሰሎሞን ‘ሥራ’ ሲል ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በአጠቃላይ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የሚጠመዱባቸውን ተግባሮች መጥቀሱ እንጂ ስለ አንድ ሰው ሙያ ወይም ተቀጥሮ ስለመሥራቱ እየተናገረ አልነበረም። (መክብብ 1:13 NW ) እስቲ ዋና ዋናዎቹን የሰው ልጅ ፍላጎቶች ወይም ሥራዎች እንመልከትና ራሳችን ከምንሠራቸውና ቅድሚያ ከምንሰጣቸው ነገሮች ጋር እናወዳድር።
5. የሰው ልጅ ከተጠመደባቸው ዋነኛ ሥራዎች አንዱ ምንድን ነው?
5 ገንዘብ አብዛኞቹን የሰው ልጅ ፍላጎቶችና እንቅስቃሴዎች ለማሳካት በጣም አስፈላጊ ነገር እንደሆነ እሙን ነው። ሰሎሞን እንደ አንዳንድ ባለጠጋ ሰዎች ለገንዘብ የግዴለሽነት አመለካከት ነበረው ብሎ ሊወቅሰው የሚችል አይኖርም። የተወሰነ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጿል፤ ተቸግሮ ወይም በድህነት ተቆራምዶ ከመኖር በቂ ገንዘብ ማግኘት የተሻለ ነው። (መክብብ 7:11, 12) ይሁን እንጂ ገንዘብም ሆነ ገንዘብ የሚገዛቸው ንብረቶች ድሃ ሀብታም ሳይል የሁሉም ሰው ዋነኛ የሕይወት ግብ ሊሆኑ እንደሚችሉ አንተም ሳታስተውል አትቀርም።
6. ኢየሱስ ከተናገረው ምሳሌና ከሰሎሞን ተሞክሮ ስለ ገንዘብ ምን ልንማር እንችላለን?
6 ኢየሱስ ተጨማሪ ነገር ለማካበት ስለሚጣጣር አልጠግብ ባይ ባለጠጋ የተናገረውን ምሳሌ አስታውስ። አምላክ ይህ ሰው ምክንያታዊ እንዳልሆነ ተናግሯል። ለምን? ምክንያቱም ‘ሕይወት የምናገኘው በንብረታችን ብዛት አይደለም።’ (ሉቃስ 12:15-21) ሰሎሞን በዚህ ረገድ ከእኛ የበለጠ ሰፊ ተሞክሮ ሳይኖረው አይቀርም። ይህ ተሞክሮው ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት እውነተኛነት የሚያረጋግጥ ነው። በመክብብ 2:4-9 ላይ የሰጠውን መግለጫ አንብብ። ሰሎሞን ለተወሰነ ጊዜ ሀብት ለማካበት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በጣም የሚያማምሩ ቤቶችንና የመናፈሻ ቦታዎችን ሠርቷል። በጣም ውብ የሆኑ የሴት ጓደኞችን ማግኘት ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ ሀብትና ሀብት ሊያስገኝ የሚችላቸውን ነገሮች ማግኘቱ ውስጣዊ እርካታ እንዲኖረው፣ ጥሩ ነገር እንዳከናወነ እንዲሰማው አድርጎታልን? እንደሚከተለው በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፣ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፣ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም።”— መክብብ 2:11፤ 4:8
7. (ሀ) የገንዘብን ጥቅም በተመለከተ እስካሁን የታየው ተሞክሮ ምን ያረጋግጥልናል? (ለ) አንተ በግልህ ሰሎሞን የደረሰበትን መደምደሚያ የሚያረጋግጥ ምን ነገር አይተሃል?
7 ይህ በብዙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚታየውን እውነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሐቅ ነው። ብዙ ገንዘብ ማግኘት ችግሮችን ሁሉ እንደማይፈታ አምነን መቀበል ይኖርብናል። ምግብና ልብስ በቀላሉ እንድናገኝ ስለሚያስችለን አንዳንዶቹን ችግሮች ሊፈታ ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ የሚለብሰው ልብስ አንድ ብቻ ከመሆኑም በላይ የሚበላውና የሚጠጣውም የተወሰነ መጠን ነው። በፍቺ፣ በአልኮል መጠጥ ወይም አደንዛዥ ዕፆችን አለአግባብ በመጠቀም እና ከቤተ ዘመድ ጋር በሚፈጠር ግጭት ሕይወታቸው ስለተመሰቃቀለባቸው ሀብታም ሰዎች ታሪክ ሳታነብ አትቀርም። ቱጃሩ ጄ ፒ ጌቲ “ገንዘብ ከደስታ ማጣት ጋር ካልሆነ በስተቀር ከደስታ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ላይኖረው ይችላል” ብለዋል። ሰሎሞን ብርን መውደድ ከንቱ እንደሆነ የተናገረው ያለ ምክንያት አይደለም። ይህንን እውነታ ሰሎሞን ከታዘበው ነገር ጋር አነጻጽር:- “እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል።”— መክብብ 5:10-12
8. የገንዘብን ጥቅም ከመጠን በላይ አጋንነን የማናየው ለምንድን ነው?
8 በተጨማሪም ገንዘብና ቁሳዊ ንብረት ለወደፊቱም ቢሆን የእርካታ ስሜት አያስገኙም። ብዙ ገንዘብና ንብረት ካለህ ያንን ለመጠበቅ ተጨማሪ ጭንቀት መሸመትህ አይቀርም፤ ነገ ምን እንደሚያመጣ ደግሞ አታውቅም። ንብረትህን በሙሉ ምናልባትም ሕይወትህን ጭምር ታጣ ይሆን? (መክብብ 5:13-17፤ 9:11, 12) ይህም በመሆኑ ሕይወታችን ወይም ሥራችን ገንዘብና ንብረትን ከማፍራት የበለጠ ዘላቂ ትርጉም ሊኖረው የሚገባው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግተንም።
ቤተሰብ፣ ዝናና ሥልጣን
9. ሰሎሞን የቤተሰብንም ሕይወት መመርመሩ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ሰሎሞን ስለ ሕይወት ያደረገው ግምገማ በቤተሰብ ጉዳይ መጠመድንም ያካተተ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን መውለድንና ማሳደግን ጨምሮ ለቤተሰብ ሕይወት ትኩረት ይሰጣል። (ዘፍጥረት 2:22-24፤ መዝሙር 127:3-5፤ ምሳሌ 5:15, 18-20፤ 6:20፤ ማርቆስ 10:6-9፤ ኤፌሶን 5:22-33) ይሁንና ይህ የሕይወት የመጨረሻው ግብ ነው ማለት ነውን? በአንዳንድ ባሕሎች ጋብቻ፣ ልጆችና የቤተሰብ ትስስር ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ስንመለከት ብዙ ሰዎች እንደዚህ ብለው የሚያስቡ ይመስላል። ይሁን እንጂ መክብብ 6:3 መቶ ልጆች እንኳ መውለድ በሕይወት ውስጥ እርካታን ለማግኘት ቁልፍ እንዳልሆነ ይገልጻል። ልጆቻቸው በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉና ሕይወት ቀላል እንዲሆንላቸው ለማድረግ ሲሉ ምን ያህል ወላጆች መሥዋዕትነት እንደከፈሉ እስቲ አስበው። ይህን ማድረግ ጥሩ እንደሆነ ባይካድም ፈጣሪ የመኖራችን ዋና ዓላማ ሕይወትን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ብቻ ነው እንዳላለ የተረጋገጠ ነው፤ ይህንን እንስሳትም እንኳ በደመ ነፍስ ያደርጉታል።
10. በቤተሰብ ላይ ከመጠን በላይ ትኩረት ማድረግ ከንቱ የሆነው ለምንድን ነው?
10 ሰሎሞን ስለ ቤተሰብ ሕይወት አንዳንድ እውነታዎችን ማስተዋል ችሎ ነበር። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ለልጆቹና ለልጅ ልጆቹ ጥሪት በማከማቸት ላይ ያተኩር ይሆናል። ይሁን እንጂ ልጆቹ ጥበበኛ ሆነው ይገኛሉ? ወይስ ለእነርሱ ለማጠራቀም ሲል ጥሮ ግሮ ያገኘውን ነገር በመያዝ በኩል ሰነፎች ይሆናሉ? ሰነፎች ሆነው ከተገኙ እንዴት ያለ ‘ከንቱነትና ትልቅ መከራ’ ይሆናል!— መክብብ 2:18-21፤ 1 ነገሥት 12:8፤ 2 ዜና መዋዕል 12:1-4, 9
11, 12. (ሀ) አንዳንዶች በሕይወታቸው ውስጥ ምን ነገሮችን በማሳደድ ላይ አተኩረዋል? (ለ) ታዋቂነትን ለማትረፍ መጣጣር “ነፋስን እንደ መከተል ነው” ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
11 በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶች በሌሎች ዘንድ ዝና ወይም ሥልጣን የማግኘት ሕልማቸውን ለማሳካት ሲሉ የዕለት ተዕለት የቤተሰብ ሕይወታቸውን ወደጎን ገሸሽ አድርገውታል። ይህ ብዙ ወንዶች የሚሠሩት ስህተት ሳይሆን አይቀርም። የክፍልህ ተማሪ፣ የሥራ ባልደረባህ ወይም ጎረቤትህ እንዲህ ሲያደርግ አልተመለከትህምን? ብዙዎች በሰዎች ዘንድ እውቅና ለማግኘት፣ ስማቸውን ለማስጠራት ወይም በሌሎች ላይ ሥልጣን ለመቆናጠጥ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ ይህ በእርግጥ ምን ያህል ትርጉም ያለው ነገር ነው?
12 አንዳንዶች አነሰም በዛ እንደ አቅማቸው ስማቸውን ለማስጠራት እንዴት ትግል እንደሚያደርጉ እስቲ አስብ። ይህ በትምህርት ቤት፣ በሠፈራችንና በተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች የምናየው ነው። በሥነ ጥበብ፣ በመዝናኛና በፖለቲካ ታዋቂ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎችንም ቢሆን የሚገፋፋቸው ይህ ነው። ይሁንና ይህ በመሠረቱ ከንቱ ጥረት አይደለምን? ሰሎሞን “ነፋስን እንደ መከተል ነው” ማለቱ ትክክል ነው። (መክብብ 4:4) አንድ ወጣት በአንድ ክለብ፣ የስፖርት ቡድን ወይም ደግሞ የሙዚቃ ጓድ ውስጥ ታዋቂ ቢሆን ወይም አንድ ወንድ አለዚያም አንዲት ሴት በመሥሪያ ቤት ውስጥ ወይም በኅብረተሰቡ ዘንድ ዝና ቢያተርፉ ይህን የሚያውቅላቸው ምን ያህል ሰው ነው? በሌላኛው የምድራችን ክፍል (ወይም እዚያው አገር) የሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሰው እንዲያው ከነመፈጠሩስ ያውቃሉ? ወይስ እርሱ ወይም እርሷ ይህችን ጥቂት ዝና ማግኘታቸውን እንኳ ጭራሽ ሳያውቁ ኑሯቸውን መምራታቸውን ይቀጥላሉ? አንድ ሰው በሥራ ቦታው፣ በከተማ ውስጥ ወይም በተወሰኑ ሰዎች ላይ ስለሚያገኘውም ሥልጣን ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል።
13. (ሀ) መክብብ 9:4, 5 ታዋቂነትና ሥልጣን ለማግኘት ስለ መጣጣር ተገቢ አመለካከት እንድንይዝ የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ሕይወት ይህ ብቻ ከሆነ የትኞቹን እውነታዎች መቀበል ይገባናል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
13 እንዲህ ያለው ታዋቂነት ወይም ሥልጣን በመጨረሻ ምን ያስገኛል? አንዱ ትውልድ አልፎ ሌላው ሲተካ ታዋቂ ወይም ባለ ሥልጣን የነበሩት ሰዎች ከዓለም መድረክ ያልፋሉ፤ በኋላም ይረሳሉ። እንደ አብዛኞቹ ፖለቲከኞችና የጦር መሪዎች ሁሉ በአንድ ወቅት የሕንጻ ባለ ሙያዎች፣ ሙዚቀኞችና ሌሎች አርቲስቶች እንዲሁም የማኅበራዊ አንቅስቃሴ አራማጆች የነበሩት ሁሉ ሁኔታቸው ከዚህ የተለየ አይደለም። ከ17ኛው እስከ 18ኛው መቶ ዘመን ባሉት ዓመታት መካከል በእነዚህ ሙያዎች ካገለገሉት ግለሰቦች ምን ያህሎቹን ታስታውሳለህ? ሰሎሞን ይህን ጉዳይ እንዲህ በማለት መቋጨቱ ተገቢ ነው:- “ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና . . . ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቷልና።” (መክብብ 9:4, 5) ሕይወት ይህ ብቻ ከሆነ በእርግጥም ታዋቂነት ለማትረፍ ወይም ሥልጣን ለመጨበጥ መሯሯጥ ከንቱ ነው።a
የትኩረት አቅጣጫችንና ግዴታችን
14. የመክብብ መጽሐፍ በግል ሊጠቅመን ይገባል የምንለው ለምንድን ነው?
14 ሰሎሞን ሰዎች በሕይወታቸው የትኩረት አቅጣጫቸውን ስላሳረፉባቸው ብዙ ሥራዎች፣ ግቦችና ተድላዎች አልተነተነም። ሆኖም የጻፈው ነገር በቂ ነው። ይህን መጽሐፍ ስንመረምር ይሖዋ አምላክ ለጥቅማችን ሲል ሆነ ብሎ በመንፈስ አነሳሽነት ያስጻፈውን መጽሐፍ መመርመራችን ስለሆነ ተስፋ ሊያስቆርጠን ወይም አሉታዊ እንደሆነ አድርገን ልንመለከተው አይገባም። እያንዳንዳችን ስለ ሕይወት ያለንን አመለካከትና የትኩረት አቅጣጫችንን እንድናስተካክል ሊረዳን ይችላል። (መክብብ 7:2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ይህ በተለይ ሰሎሞን በይሖዋ እርዳታ ከደረሰባቸው መደምደሚያዎች አንጻር ሲታይ እውነት ነው።
15, 16. (ሀ) ደስተኛ ሆኖ መኖርን በተመለከተ ሰሎሞን ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? (ለ) ሰሎሞን ደስተኛ ሆኖ ለመኖር ምን ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል?
15 ሰሎሞን በተደጋጋሚ ያነሳው አንዱ ነጥብ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች በፊቱ በሚሠሩት ሥራ ደስ ሊላቸው ይገባል የሚል ነው። “ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምም ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።” (መክብብ 2:24፤ 3:12, 13፤ 5:18፤ 8:15) ሰሎሞን ፈንጠዝያን ማበረታታቱ እንዳልነበር ልብ በል፤ ‘ዛሬ እንብላና እንጠጣ እንደሰት ነገ እንሞታለን’ የሚለውን አመለካከት መደገፉም አልነበረም። (1 ቆሮንቶስ 15:14, 32-34) ‘በሕይወት ዘመናችን መልካም እያደረግን’ እንደ መብላትና መጠጣት ባሉት የተለመዱ ነገሮች መደሰት አለብን ማለቱ ነበር። ይህም ሕይወታችን በእርግጥ መልካም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ በሚወስነው በፈጣሪያችን ፈቃድ ላይ ያተኮረ እንዲሆን እንደሚያደርግ ምንም አያጠራጥርም።— መዝሙር 25:8፤ መክብብ 9:1፤ ማርቆስ 10:17, 18፤ ሮሜ 12:2
16 ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና ሂድ፣ እንጀራህን በደስታ ብላ፣ የወይን ጠጅህንም በተድላ ጠጣ።” (መክብብ 9:7-9) አዎን፣ ይሖዋን በሚያስደስት ሥራ የሚካፈል ወንድ ወይም የምትካፈል ሴት ጥሩና አርኪ ሕይወት ይመራሉ። ይህም ሁልጊዜ እርሱን ማሰብን የሚጠይቅ ነው። ሕይወትን በሰብዓዊ ዓይን ከሚያዩት ከአብዛኞቹ ሰዎች አመለካከት ይህ ምንኛ የተለየ ነው!
17, 18. (ሀ) ብዙ ሰዎች በሕይወት ውስጥ ላሉት ነባራዊ እውነታዎች ምን ምላሽ ይሰጣሉ? (ለ) ሁልጊዜ ልንዘነጋው የማይገባን የትኛውን ውጤት ነው?
17 አንዳንድ ሃይማኖቶች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ቢያስተምሩም ብዙ ሰዎች እርግጠኛ የሆኑት ስለ አሁኑ ሕይወት ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሰሎሞን የገለጸው ዓይነት ምላሽ እንደሚሰጡ አስተውለህ ይሆናል:- “በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመሥራት ጠነከረ።” (መክብብ 8:11) በክፉ ድርጊቶች ውስጥ ያልተዘፈቁ ሰዎችም ቢሆኑ በመሠረቱ የሚያሳስባቸው የአሁኑ ሕይወታቸው ነው። ለገንዘብ፣ ለንብረት ባለቤትነት፣ ክብር ለማግኘት፣ ለሥልጣን፣ ለቤተሰብ ወይም ሌሎች እነዚህን ለመሳሰሉ ነገሮች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡበት ምክንያት ይህ ነው። ይሁንና ሰሎሞን በዚህ ብቻ ሐሳቡን አልቋጨም። እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል:- “ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፣ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት ደህንነት እንዲሆን አውቃለሁ፤ ለኀጥእ ግን ደኅንነት የለውም፣ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም።” (መክብብ 8:12, 13) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሰሎሞን ‘እውነተኛውን አምላክ’ ብንፈራ መልካም እንደሚሆንልን ያምን ነበር። እንዴት? በማነጻጸር ከተናገረው ሐሳብ መልሱን ማግኘት እንችላለን። ይሖዋ ሕይወታችንን ‘ሊያረዝምልን’ ይችላል።
18 በተለይ ገና ወጣት የሆኑ ሁሉ አምላክን ቢፈሩ መልካም እንደሚሆንላቸው የሚናገረውን ፍጹም አስተማማኝ የሆነ እውነታ ሊያስቡበት ይገባል። በጣም ፈጣን የሆነ ሯጭ አንድ ነገር አደናቅፎት በውድድሩ ሊሸነፍ እንደሚችል አንተ ራስህ አይተህ ይሆናል። ብርቱ የነበረው ሠራዊት ሽንፈት ሊገጥመው ይችላል። ብልህ ነጋዴ ጨርሶ ሊደኸይ ይችላል። እነዚህና ሌሎችም አስተማማኝ ያልሆኑ ሁኔታዎች ሕይወትን ተለዋዋጭ አድርገዋታል። ይሁን እንጂ ስለ አንድ ነገር ፍጹም እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፤ ይኸውም:- ከሁሉ ይበልጥ ጥበብ የሞላበትና አስተማማኝ የሆነው ጎዳና በአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች እየተመሩና ፈቃዱን እያደረጉ በመልካም ሥራ መኖር ነው። (መክብብ 9:11) ይህም የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ መማርንና ሕይወትን ለእርሱ መወሰንን እንዲሁም የተጠመቁ ክርስቲያኖች መሆንን ይጨምራል።— ማቴዎስ 28:19, 20
19. ወጣቶች ሕይወታቸውን እንዴት ሊጠቀሙበት ይችላሉ? ይሁን እንጂ ምን ማድረጉ ብልህነት ነው?
19 ፈጣሪ ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች መመሪያውን እንዲከተሉ አያስገድድም። ወጣቶች ራሳቸውን በትምህርት ሊያስጠምዱ ይችላሉ፤ ምናልባትም ሰብዓዊ ጥበብ የያዙ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን መጻሕፍት ዕድሜ ልካቸውን ሊማሩ ይችላሉ። ይህ ትርፉ ሥጋን ማድከም ነው። ወይም ፍጹም ያልሆነው ሰብዓዊ ልባቸው በሚመራቸው መንገድ ወይም ሲያዩት የሚማርካቸውን ጎዳና ተከትለው ሊመላለሱ ይችላሉ። ይህም ሐዘንን እንደሚያስከትል ምንም ጥርጥር የለውም፤ በዚህ መንገድ ያሳለፉት ሕይወት ደግሞ ከንቱ ነው። (መክብብ 11:9-12:12፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) በመሆኑም ሰሎሞን ለወጣቶች አንድ ጥሪ አቅርቧል፤ በየትኛው ዕድሜ ላይ ብንገኝ ይህንን ጥሪ በቁም ነገር ልናስብበት ይገባል:- “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ።”— መክብብ 12:1
20. በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው መልእክት የያዘው ሚዛናዊ አመለካከት ምንድን ነው?
20 እንግዲያውስ ምን ብለን መደምደም እንችላለን? ሰሎሞን የደረሰበት መደምደሚያ ምንድን ነው? “ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ” ተመልክቷል ወይም መርምሯል፤ “እነሆም፣ ሁሉ ከንቱ ነው፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።” (መክብብ 1:14) በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ቃላት አንድ ስህተት የሚፈላልግ ወይም በኑሮው ያልረካ ሰው የተናገራቸው ቃላት አይደሉም። ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል ናቸው።
21, 22. (ሀ) ሰሎሞን ግምት ውስጥ ያስገባቸው የሕይወት ዘርፎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ሰሎሞን ምን ጥበብ የተሞላበት መደምደሚያ ላይ ደርሷል? (ሐ) የመክብብን መጽሐፍ ይዘት መመርመርህ እንዴት ነክቶሃል?
21 ሰሎሞን ስለ ሰው ልጆች ልፋት፣ ችግሮችና ምኞቶች አጥንቷል። በተለመደው የሕይወት ጉዞ ውስጥ ነገሮች ምን መልክ ይዘው ብቅ እንደሚሉ በሌላ አባባል ብዙ ሰዎች ስለሚገጥማቸው ከንቱና ተስፋ አስቆራጭ ውጤት አሰላስሏል። የሰብዓዊ አለፍጽምናንና ይህ አለፍጽምና የሚያስከትለውን ሞት ነባራዊ እውነታ መርምሯል። ሙታን ስላሉበት ሁኔታ አምላክ የሚሰጠውን እውቀትና የወደፊቱን ሕይወት ተስፋዎች ጨምሮ ተናግሯል። አዎን፣ በመለኮታዊ እርዳታ የጥበብ አድማሱን በማስፋቱ እስከ ዛሬ ከኖሩት በጣም ጥበበኛ ሰዎች አንዱ የሆነው ይህ ሰው እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ገምግሟል። በመጨረሻ የደረሰበት መደምደሚያም እውነተኛ ዓላማ ያለው ሕይወት ለማግኘት ለሚፈልጉ ሰዎች ጥቅም ሲባል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግቦ ተቀምጧል። በዚህ ልንስማማ አይገባንምን?
22 “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው [“ሁለንተናዊ ግዴታው፣” NW] ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ ትእዛዛቱንም ጠብቅ። እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፣ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፣ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።”— መክብብ 12:13, 14
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በአንድ ወቅት መጠበቂያ ግንብ የሚከተለውን አስተዋይነት የተሞላበት አስተያየት ሰንዝሮ ነበር:- “ሕይወታችንን ከንቱ ነገሮችን በማሳደድ ልናሳልፈው አይገባም፤ . . . ሕይወት ይህ ብቻ ከሆነ ሁሉ ነገር ከንቱ ነው ማለት ነው። ይህ ሕይወት ወደ አየር ተወርውሮ ተመልሶ ትቢያ ላይ እንደሚወድቅ ኳስ ነው። ታይቶ እንደሚጠፋ ጥላ፣ እንደሚረግፍ አበባ፣ ሲቆረጥ ወዲያው ጥውልግ እንደሚል ቅጠል ነው። . . . የሕይወታችን ርዝማኔ በዘላለማዊነት ሚዛን ስትለካ ከቁጥርም የማትገባ ቅንጣት ነች። በዘመናት ጅረት ውስጥ እንደ አንድ ጠብታ እንኳን አትሆንም። በእርግጥም [ሰሎሞን] በሕይወት ውስጥ ያሉትን ብዙ ሰብዓዊ ፍላጎቶችና የሥራ እንቅስቃሴዎች ከገመገመ በኋላ ከንቱ ናቸው ማለቱ ትክክል ነው። ሕይወታችን በቅጽበት ያልፋል፤ መወለዳችን ምንም ፋይዳ ያለው አይመስልም፤ ወደፊትም ተወልደው ከሚሞቱት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ጭራሽ በሕይወት እንደነበርን እንኳን የሚያውቁት እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው። ይህ አፍራሽ አስተሳሰብ የተጠናወተው ወይም ተስፋ የቆረጠ ሰው አስተያየት አይደለም። ሕይወት ይህ ብቻ ከሆነ ይህ አስተያየት እውነት ነው፤ ልንቀበለው የሚገባ ሐቅና እውነታውን መሠረት ያደረገ አመለካከት ነው።”— ነሐሴ 1, 1957 ገጽ 472
ታስታውሳለህን?
◻ ንብረት በሕይወትህ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና በሚመለከት የተደረገው ጥበብ የተሞላበት ግምገማ የትኛው ነው?
◻ ለቤተሰብ፣ ዝናን ለማትረፍ ወይም በሌሎች ላይ ሥልጣን ለመያዝ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት መስጠት የማይገባን ለምንድን ነው?
◻ ሰሎሞን ደስታን በተመለከተ ምን አምላካዊ ዝንባሌ እንዲኖረን አበረታቷል?
◻ የመክብብን መጽሐፍ በመመርመርህ የተጠቀምኸው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገንዘብና ንብረት እርካታ ለማግኘት ዋስትና አይሆኑም
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቶች አምላክን ቢፈሩ መልካም እንደሚሆንላቸው እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ