ምዕራፍ 1
ለዘላለም መኖር ሕልም አይደለም
1, 2. ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እየተደሰቱ መኖር ይችላሉ ብሎ ማመን ለምን ያዳግታል?
ለአጭር ጊዜም ቢሆን በምድር ላይ ደስታ አግኝቶ መኖር የሚቻል አይመስልም። ጥቂቶቹን ችግሮች ለመጥቀስ ያህል በሽታ፣ እርጅና፣ ረሀብና ወንጀል የሰውን ሕይወት አስከፊ አድርገውታል። በመሆኑም ምድር ገነት ሆና በእርስዋ ላይ ለዘላለም መኖር ይቻላል ብሎ መናገሩ እውነቱን ላለማየት ዓይንን እንደመጨፈን ነው ብለህ ትናገር ይሆናል። ስለዚሁ ነገር ማውራት ጊዜን ማባከን እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ለዘላለም መኖር እንዲያው ሕልም ብቻ ነው ብለህ ታስብ ይሆናል።
2 አብዛኞቹ ሰዎች ከአንተ አባባል ጋር እንደሚስማሙ አያጠራጥርም። ታዲያ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ ብለን ለመናገር እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘት ሕልም አይደለም ብለን ለማመን የምንችለው ለምን ይሆን?
ለማመን የምንችልበት ምክንያት
3. ሰዎች በምድር ላይ ደስተኞች ሆነው እንዲኖሩ አምላክ እንደሚፈልግ የሚያሳየው ምንድን ነው?
3 ማመን እንችላለን ምክንያቱም ከሁሉም የበለጠ ኃይል ያለውና ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ ምድርን ፍላጎታችንን ማርካት በሚችሉ ነገሮች ሞልቶ አዘጋጅቷታል። ምድርን ለእኛ ፍጹም ተስማሚ አድርጎ ሠርቷታል! ወንድንና ሴትን የፈጠረው በዚች ምድራዊት መኖሪያቸው ለዘላለም እየተደሰቱ መኖር በሚችሉበት ከሁሉ በተሻለው መንገድ ነው።—መዝሙር 115:16
4. የሰው አካል ለዘላለም እንዲኖር ሆኖ እንደተሠራ የሚያሳይ ሳይንቲስቶች በምርምር የደረሱበት ነገር ምንድን ነው?
4 የሰው አካል ራሱን በራሱ የማደስ ኃይል እንዳለው ሳይንቲስቶች ከረጅም ዘመን ጀምረው አውቀዋል። የሰውነት ሴሎች አስደናቂ በሆነ መንገድ እንደ አስፈላጊነቱ በሌላ ሴል ይተካሉ ወይም ይጠገናሉ። ይህ ውስጣዊ የመታደስ ሂደት ለዘላለም መቀጠል ያለበት መስሎ ይታያል፤ ግን ሁኔታው እንደዚያ አይደለም። ሳይንቲስቶች የዚህን ምክንያት ማስረዳት አልቻሉም። ሰዎች የሚያረጁበትን ምክንያት አሁንም ሳይንቲስቶቹ ገና ሙሉ በሙሉ አልተረዱትም። ሁኔታዎቹ ቢስተካከሉላቸው ሰዎች ለዘላለም መኖር መቻል አለባቸው ብለውም ይናገራሉ።—መዝሙር 139:14
5. አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
5 ታዲያ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ በእርግጥ የአምላክ ዓላማ ነውን? ዓላማው ከሆነ የዘላለም ሕይወት እንዲሁ ምኞት ወይም ሕልም ብቻ መሆኑ ቀርቶ እርግጠኛ ነገር ነው ማለት ነው! ስለ አምላክ ዓላማዎች የሚናገር መጽሐፍ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን ይላል አምላክ “ምድርን የሠራና ያደረገ“ መሆኑን ይገልጽና “ያጸናትም፣ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ“ እንደሆነ ይናገራል።—ኢሳይያስ 45:18
6. (ሀ) ዛሬ በምድር ላይ እንዴት ያሉ ሁኔታዎች አሉ? (ለ) አምላክ ነገሩ እንደዚሁ እንዲሆን ይፈልጋልን?
6 በአሁኑ ጊዜ ምድር አምላክ ባሰበው መንገድ ሰዎች እየኖሩባት ያሉ ይመስልሃልን? እርግጥ ነው አብዛኛው የምድር ገጽ ሰዎች ይኖሩበታል። ይሁን እንጂ ፈጣሪያቸው ለእነርሱ ባሰበው ጥሩ መንገድ እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነው አብረው በደስታ እየኖሩ ናቸውን? ዛሬ ዓለም የተከፋፈለች ናት፤ ጥላቻ አለ፤ ወንጀል አለ፤ ጦርነት አለ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይራባሉ፤ ይታመማሉ። ሌሎች ደግሞ ስለ መኖሪያ ቤት፣ ስለ ሥራና ስለ ገንዘብ ወጪ በየቀኑ ይጨነቃሉ። ከእነዚህ ነገሮች አንዱም ቢሆን ለአምላክ ክብር አያመጣለትም። እንግዲያው ምድር ሁሉን የሚችለው አምላክ በመጀመሪያ ባሰበው መንገድ ሰዎች እንዳልኖሩባት በግልጽ የሚታይ ነው።
7. አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት በፈጠረ ጊዜ ለምድር ምን ዓላማ ነበረው?
7 አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ከፈጠረ በኋላ በምድራዊት ገነት አስቀመጣቸው። በሕይወታቸው እየተደሰቱ በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ፈልጎ ነበር። ገነታቸውን በመላዋ ምድር ላይ እንዲያስፋፉ ዓላማው ነበር። “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም“ ሲል የሰጣቸው መመሪያ ይህንን ያሳያል። (ዘፍጥረት 1:28) አዎን፣ የአምላክ ዓላማ ከጊዜ በኋላ ጠቅላላዋ ምድር በሰላምና በደስታ አብሮ በሚኖር ጻድቅ ሰብዓዊ ቤተሰብ ቁጥጥር ሥር እንድትሆን ነበር።
8. የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት አምላክን ሳይታዘዙ ቢቀሩም አምላክ ለዚች ምድር የነበረው ዓላማ እንዳልተለወጠ ለምን እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
8 ምንም እንኳን የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት አምላክን ባለመታዘዝ ለዘላለም ለመኖር ብቁ አለመሆናቸውን ቢያሳዩም የመጀመሪያው የአምላክ ዓላማ አልተለወጠም። የግድ መፈጸም ይኖርበታል! (ኢሳይያስ 55:11) መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ“ ሲል ተስፋ ይሰጠናል። (መዝሙር 37:29) አምላክ ለሚያገለግሉት ሰዎች የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ዝግጅት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ላይ ይናገራል።—ዮሐንስ 3:14-16, 36፤ ኢሳይያስ 25:8፤ ራዕይ 21:3, 4
ለዘላለም የመኖር ምኞት አለ፤ ግን የት?
9. (ሀ) ሰዎች በተፈጥሮአቸው ምን ምኞት አላቸው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ’አምላክ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ዘላለምነትን አስቀምጧል’ ሲል ምን ማለቱ ነው?
9 ለዘላለም እንድንኖር የአምላክ ዓላማ በመሆኑ በእውነቱ ደስ ሊለን ይችላል። እስቲ አስበው፤ ውሳኔው የአንተ ቢሆን ኖሮ በየትኛዋ ቀን ለመሞት ትመርጥ ነበር? አንዷንም ቀን አትመርጥም። ለመሞት አትፈልግም። መጠነኛ ጤንነት ያለው ማንኛውም ሌላ ሰውም ቢሆን ለመሞት አይፈልግም። አምላክ ሲፈጥረን በውስጣችን የመኖር እንጂ የመሞት ፍላጎት አላሳደረብንም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሰዎችን እንዴት አድርጎ እንደፈጠራቸው ሲናገር “በአእምሯቸው ውስጥ ዘላለምነትን አስቀምጧል“ ይላል። (መክብብ 3:11 ባይንግተን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ) ይህ ምን ማለት ነው? ሰዎች በተፈጥሮአቸው ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ምን ጊዜም ሳይሞቱ በሕይወት ለመኖር ይፈልጋሉ ማለት ነው። ሰዎች ፍጻሜ ለሌለው ዘመን ለመኖር ይህ ፍላጎት ስላላቸው ዘላለም ወጣት ሆነው የሚኖሩበትን መንገድ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲመረምሩ ቆይተዋል።
10. (ሀ) ሰው በተፈጥሮው ለዘላለም ለመኖር የሚፈልገው የት ላይ ነው?(ለ) አምላክ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር እንደሚያስችለን ለምን እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን?
10 ሰዎች በተፈጥሮአቸው ለዘላለም መኖር የሚፈልጉት የት ነው? ሲኖሩበት በቆዩት ሥፍራ ይኸውም እዚህ ምድር ላይ ነው። ሰው የተፈጠረው ለምድር ነው፤ ምድርም ለሰው። (ዘፍጥረት 2:8, 9, 15) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት“ ይላል። (መዝሙር 104:5) ምድር ለሁልጊዜው እንድትቆይ ሆና ስለተሠራች ሰውም ለዘላለም መኖር አለበት ማለት ነው። በእውነቱ አፍቃሪው አምላክ ሰዎችን ለዘላለም የመኖር ምኞት በውስጣቸው ቀርጾ ከፈጠረ በኋላ ያንን ምኞት መፈጸም እንዳይችሉ አያደርጋቸውም።—1 ዮሐንስ 4:8፤ መዝሙር 133:3
የምትመኘው ምን ዓይነት ኑሮ ነው?
11. ሰዎች ፍጹም ጤንነት አግኝተው ለዘላለም መኖር እንደሚችሉ ለማሳየት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
11 ቀጥሎ ያለውን ገጽ ተመልከት። እነዚህ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት አግኝተው እየተደሰቱ ነው? አንተስ ከእነርሱ አንዱ ለመሆን ትፈልጋለህን? እንዴታ! ብለህ ትናገር ይሆናል። እንዴት ጤነኞችና ለጋ ወጣት እንደሚመስሉ ተመልከት! እነዚህ ሰዎች እኮ ለብዙ ሺህ ዓመታት የኖሩ ናቸው ተብሎ ቢነገርህ ታምን ነበርን? መጽሐፍ ቅዱስ አረጋውያን ወደ ወጣትነት እንደሚመለሱ፣ በሽተኞች እንደሚድኑ፣ አንካሶች፣ ዕውሮች፣ ደንቆሮዎችና ዲዳዎችም እንደሚፈወሱ ይናገራል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሕመምተኞችን በመፈወስ ብዙ ተአምራት ሠርቷል። እንደዚያ ሲያደርግ ሩቅ ያልሆነው ክብራማ ጊዜው ሲመጣ በሕይወት ያሉ ሁሉ ፍጹም ጤንነት እንደሚመለስላቸው ማሳየቱ ነበር።—ኢዮብ 33:25፤ ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6፤ ማቴዎስ 15:30, 31
12. በእነዚህ ስዕሎች ላይ ምን ሁኔታዎች እንመለከታለን?
12 ይህ መኖሪያ የሆነ የአትክልት ሥፍራ እንዴት ደስ እንደሚል ተመልከት! ልክ ክርስቶስ እንደሰጠው ተስፋ የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ባለመታዘዛቸው ካጡት ገነት ጋር የሚመሳሰል እውነተኛ ገነት ነው። (ሉቃስ 23:43) በሰዎቹ መሃል ያለውን ሰላምና ስምምነት ልብ ብለህ ተመልከት። ሁሉም ዓይነት ዘሮች ይኸውም ጥቁሮች፣ ነጮችና ቢጫ የቆዳ ቀለም ያላቸው ሁሉ እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነው ይኖራሉ። ሌላው ቀርቶ እንስሶች እንኳን ሰላማውያን ናቸው። ሕፃኑ ከአንበሳው ጋር ሲጫወት ተመልከት። ይሁን እንጂ የሚያስፈራ ምንም ነገር የለም። ይህን በሚመለከት ፈጣሪያችን እንዲህ ብሏል፦ “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። . . . አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፤ የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል።”—ኢሳይያስ 11:6-9
13. የአምላክ ዓላማዎች ሲፈጸሙ ከምድር ምን ነገሮች ይወገዳሉ?
13 አምላክ ለሰዎች በሚያዘጋጀው ገነት ውስጥ ደስታን የሚሰጥ ነገር ሁሉ ይኖራል። ምድር ለመብል የሚያገለግሉ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን በብዛት ታፈራለች። ዳግመኛ የሚራብ ሰው አይኖርም። (መዝሙር 72:16፤ 67:6) ጦርነቶች፣ ወንጀል፣ ዓመጽ፣ ጥላቻና ስግብግብነት ጊዜ ያለፈባቸው ነገሮች ይሆናሉ። አዎን፣ ለዘላለም ይጠፋሉ። (መዝሙር 46:8, 9፤ 37:9-11) ይህ ሁሉ ይቻላል ብለህ ታምናለህ?
14. አምላክ መከራን ወደ ፍጻሜው ያመጣዋል ብለህ እንድታምን የሚያደርግህ ምንድን ነው?
14 እስቲ አስበው፤ ኃይል ቢኖርህ ኖሮ በሰዎች ላይ መከራ የሚያመጡትን ነገሮች በሙሉ ታጠፋቸው ነበርን? ደግሞስ የሰው ልብ የምትናፍቃቸውን ሁኔታዎች ታመጣ ነበርን? እንደዚያ እንደምታደርግ አያጠራጥርም። አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ልክ ይህንን ነገር ያደርጋል። የሚያስፈልጉንንና የምንፈልጋቸውን ነገሮች በመስጠት ያረካናል ምክንያቱም መዝሙር 145:16 ስለ አምላክ እንዲህ ይላል፣ “አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ።” ታዲያ ይህ የሚፈጸመው መቼ ነው?
ታላላቅ በረከቶች በቅርቡ ይመጣሉ
15. (ሀ) የዓለም ፍጻሜ ለምድር ምን ትርጉም ይኖረዋል? (ለ) ለክፉ ሰዎችስ ምን ትርጉም ይኖረዋል? (ሐ) የአምላክን ፈቃድ ለሚያደርጉትስ ምን ማለት ይሆናል?
15 እነዚህ መልካም በረከቶች በምድር ላይ መምጣት እንዲችሉ አምላክ ክፋትንና የክፋት መንስዔ የሆኑትን ሰዎች ለማጥፋት ቃል ገብቷል። በዚያም ላይ ግን የሚያገለግሉትን ይጠብቃቸዋል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ይላል። (1 ዮሐንስ 2:17) ይህ እንዴት ያለ ትልቅ ለውጥ ይሆናል! የዓለም ፍጻሜ የምድራችን ፍጻሜ ማለት አይሆንም። ከዚህ ይልቅ በኖህ ዘመን ዓለም አቀፍ ጎርፍ በመጣ ጊዜ እንደሆነው ሁሉ አሁንም ክፉ ሰዎችና አኗኗራቸው ይጠፋሉ ማለት ይሆናል። አምላክን የሚያገለግሉ ግን ከዚያ ጥፋት ይተርፋሉ። ከዚያ በኋላ ሊጎዷቸውና ሊጨቁኗቸው ከሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ነፃነት አግኝተው በጸዳች ምድር ላይ ደስ እያላቸው ይኖራሉ።—ማቴዎስ 24:3, 37-39፤ ምሳሌ 2:21, 22
16. በእነዚህ “መጨረሻ ቀኖች“ ምን ነገሮች ይፈጸማሉ ተብሎ ትንቢት ተነግሯል?
16 ነገር ግን አንድ ሰው ‘ሁኔታዎች እየከፉ እንጂ እየተሻሻሉ አይደሉም፤ ይህ ታላቅ ለውጥ በቅርቡ እንደሚመጣ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?’ ብሎ ይናገር ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፊት የሚመጡ ተከታዮቹ ነቅተው ሊጠብቋቸው የሚገቡ ዓለምን ወደ ፍጻሜው ለማምጣት የአምላክ ጊዜ መድረሱን የሚያውቁባቸው ብዙ ትንቢቶች ተናግሯል። ኢየሱስ በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ላይ እንደ ታላላቅ ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረት፣ ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ እየጨመረ የሚሄድ ዓመፀኝነትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የሚሄድ ፍቅር እንደሚኖሩ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3-12) በተጨማሪም ‘ሰዎች መውጫው ጠፍቷቸው እንደሚጨነቁ’ ገልጿል። (ሉቃስ 21:25) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን” ይመጣል ይላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በአሁኑ ጊዜ የምናያቸው ሁኔታዎች እነዚሁ አይደሉምን?
17. የሚመራመሩ ሰዎች ዛሬ በምድር ላይ ስላሉት ሁኔታዎች ምን ብለዋል?
17 የዓለምን ሁኔታ የሚያጠኑ ብዙ ሰዎች አንድ ታላቅ ለውጥ በመምጣት ላይ እንዳለ ይናገራሉ። ለምሳሌ ሔራልድ የተባለ በአሜሪካ በማያሚ ከተማ የሚታተም የአንድ ጋዜጣ አዘጋጅ እንዲህ ሲሉ ጻፉ፦ “ግማሽ የማመዛዘን ችሎታ ያለው ማንኛውም ሰው ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተፈጸሙትን እንደ መቅሰፍት የሆኑ ነገሮች አዳምሮ ዓለም በታሪካዊ ደፍ ላይ መቆሟን ለማየት ይችላል። . . . ሰዎች የኖሩበት መንገድ ለዘላለም ይለወጣል።” በተመሳሳይም አሜሪካዊው ፀሐፊ ሎወስ መምፎርድ እንዲህ አሉ፦ “ያለምንም ጥርጥር ሥልጣኔ እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ነው። . . . ባለፉት ዘመናት ታላላቅ ሥልጣኔዎች በወደቁ ጊዜ ችግሩ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ ነበር . . . አሁን ግን በዘመናዊ መገናኛ ዘዴዎች የተነሳ ዓለም ከበፊቱ የበለጠ ስለተቀራረበችና ስለተሳሰረች የዓለም ሥልጣኔ ከወደቀ መላዋ ፕላኔታችን አብራ ትወድቃለች።”
18. (ሀ) የዓለም ሁኔታዎች ስለወደፊቱ ጊዜ ምን ያሳያሉ? (ለ) አሁን ያሉት መንግሥታት በምን ይተካሉ?
18 ዛሬ በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች የዚህ ጠቅላላ የነገሮች ሥርዓት ጥፋት በሚመጣበት ጊዜ ላይ እንደምንኖር ያሳያሉ። አዎን፤ በቅርቡ አምላክ ምድርን የሚያበላሿትን ሁሉ ጠርጎ በማስወገድ ያጸዳታል። (ራዕይ 11:18) የጽድቅ መንግሥቱ መላዋን ምድር መግዛት የሚችልበት መንገድ ክፍት እንዲሆን በአሁኑ ጊዜ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ ያስወግዳቸዋል። ክርስቶስ ተከታዮቹ ይምጣ ብለው እንዲጸልዩለት ያስተማረው ንጉሣዊ መንግሥት ይህ ነው።—ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10
19. ለዘላለም ለመኖር ከፈለግን ምን ማድረግ አለብን?
19 ሕይወትን የምታፈቅርና በአምላክ አገዛዝ ሥር በምድር ለዘላለም ለመኖር የምትፈልግ ከሆነ ስለ አምላክ፣ ስለ ዓላማዎቹና ስለ ሕጎቹ ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት መጣደፍ ይኖርብሃል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “የዘላለም ሕይወትም ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3 የ1980 ትርጉም) በምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንደምንችል፣ ይህም ነገር ሕልም እንዳልሆነ ማወቁ እንዴት ደስ ይላል! ይሁን እንጂ ይህንን ከአምላክ የሚመጣ ጥሩ በረከት አግኝተን ለመደሰት ከፈለግን ይህንን በረከት እንዳናገኝ ለማደናቀፍ ስለሚጥረው ስለ አንድ ጠላት መማር ያስፈልገናል።
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዓለም እንደዚህ እንዲሆን አምላክ አስቦ ነበር?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]