ከተስፋይቱ ምድር የሚገኙ ጠቃሚ ትምህርቶች
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው የተስፋይቱ ምድር ገጽታ በእርግጥም ልዩ ነው። ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር መጠኑ አነስተኛ በሆነ በዚህ ቦታ የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እናገኛለን። በሰሜን በኩል በበረዶ የተሸፈኑ ተራሮች፣ በደቡብ በኩል ሞቃታማ ቦታዎች ይገኛሉ። ለም የሆኑ ቆላማ ቦታዎች፣ ሰው የማይኖርባቸው ምድረ በዳዎችና የፍራፍሬ እርሻ ለማልማትና ለከብት ግጦሽ ተስማሚ የሆኑ ኮረብታማ ቦታዎች አሉ።
የተለያየ ከፍታ፣ የአየር ጠባይና የአፈር ዓይነት መኖሩ ብዛት ያላቸው የተለያዩ ዛፎች፣ ቁጥቋጦዎችና ሌሎች ተክሎች እንዲኖሩ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ቀዝቃዛ የሆነ አካባቢ የሚስማማቸው፣ ሌሎች ደግሞ ሞቃታማ በሆኑ በረሃዎች፣ ደለል በተከማቸባቸው ወይም ዓለት በበዛባቸው አምባዎች ላይ የሚበቅሉ ናቸው። አንድ የአዝእርትና አትክልት ጥናት ተመራማሪ በእነዚህ አካባቢዎች 2,600 የሚያክሉ የእጽዋት ዓይነቶች እንደሚገኙ ገምተዋል! ይህን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጡት እስራኤላውያን መሬቱ ለም መሆኑን ለማረጋገጥ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ከአንድ ሸለቆ ያመጡት የወይን ዘለላ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ሁለት ሰዎች በዘንግ መሸከም አስፈልጓቸው ነበር! ሸለቆው ኤሽኮል የሚል ተስማሚ ስያሜ የተሰጠው ሲሆን “[የወይን] ዘለላ” የሚል ትርጉም አለው።a—ዘኁልቁ 13:21-24
አሁን ግን ልዩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያለውን የዚህን ደቡባዊ ምድር ክፍል እንመልከት።
ሼፌላህ
የተስፋይቱ ምድር ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ የሜዲትራኒያን ባሕር ጠረፍ ነው። 40 ኪሎ ሜትር ወደ መሃል ገባ ብሎ ሼፌላህ ይገኛል። “ሼፌላህ” የሚለው ቃል ትርጉሙ “ቆላ” ማለት ቢሆንም ይህ አካባቢ ግን ኮረብታማ ቦታ ነው። ይሁን እንጂ በምሥራቅ በኩል ከሚገኙት የይሁዳ ተራሮች ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ ቦታ ያሰኘዋል።
እዚህ ላይ ያለውን ካርታ ተመልክተህ ሼፌላህ በአካባቢው ካሉት ሌሎች ቦታዎች ጋር ያለውን ተዛምዶ ልብ በል። በምሥራቅ በኩል የይሁዳ ተራሮች ሲገኙ በምዕራብ በኩል ደግሞ የተንጣለለው የፍልስጥኤም የባሕር ጠረፍ ይገኛል። ስለዚህ ሼፌላህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩትን የአምላክ ሕዝቦች ከጠላቶቻቸው የሚለያቸው እንደ ጥብቅ ቀጠና ሆኖ የሚያገለግል ድንበር ነበር። በምዕራብ በኩል የሚመጣ ማንኛውም ወራሪ ጦር የእስራኤል ዋና ከተማ ወደሆነችው ኢየሩሳሌም ከማምራቱ በፊት የግድ ሼፌላህን አቋርጦ ማለፍ ነበረበት።
እንዲህ ያለው ሁኔታ በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ተከስቶ ነበር። “የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ወጥቶ ጌትን [የሼፌላህ አዋሳኝ ሳይሆን አይቀርም] ወጋ፣ ያዘውም፤ አዛሄልም ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት ፊቱን አቀና” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይዘግባል። ንጉሥ ኢዮአስ በቤተ መቅደሱና በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ይገኙ የነበሩትን ውድ እቃዎች ጉቦ በመስጠት የአዛሄል ጉዞ እንዲገታ አድርጓል። ያም ሆነ ይህ የኢየሩሳሌምን ደህንነት ለማስጠበቅ ሼፌላህ ወሳኝ የሆነ ቦታ ላይ እንደሚገኝ ይህ ዘገባ ያሳያል።—2 ነገሥት 12:18, 19
ከዚህ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። አዛሄል ኢየሩሳሌምን ድል አድርጎ ለመያዝ ፈለገ፤ ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ሼፌላህን አቋርጦ ማለፍ ነበረበት። በተመሳሳይም ሰይጣን ዲያብሎስ የአምላክን አገልጋዮች ‘ሊውጣቸው ይፈልጋል፤’ ሆኖም ጠንካራ የሆነውን ጥብቅ ቀጠና ማለትም ስለ መጥፎ ጓደኝነትና ስለ ፍቅረ ነዋይ ከሚናገሩት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ያላቸውን ቁርኝት ጥሶ ማለፍ አለበት። (1 ጴጥሮስ 5:8፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:10) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ቸል ማለት አብዛኛውን ጊዜ ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸም የሚመራ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ስለዚህ ይህ ጥብቅ ቀጠና እንዳይጣስ መጠበቅ ይኖርብናል። ነገ የአምላክን ሕግ እንዳታፈርስ ዛሬ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ጠብቅ።
ኮረብታማው የይሁዳ ምድር
ከሼፌላህ ቀጥሎ ወደ መሐል አገር ሲዘልቁ ኮረብታማው የይሁዳ ምድር ይገኛል። ይህ አካባቢ ጥራጥሬ፣ የወይራ ዘይትና ወይን በጥሩ ሁኔታ የሚመረትበት ተራራማ ቦታ ነው። በተጨማሪም ይሁዳ ከፍ ያለ በመሆኑ በጣም ጥሩ ምሽግ ነበር። ስለዚህም ንጉሥ ኢዮአታም “አምባዎችንና ግንቦችን” በዚህ ቦታ ሠራ። ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ጥበቃ ለማግኘት ሰዎች ወደዚህ ቦታ መሸሽ ይችሉ ነበር።—2 ዜና መዋዕል 27:4
ጽዮን በሚል መጠሪያም የምትታወቀው ኢየሩሳሌም የኮረብታማው የይሁዳ አገር ታዋቂ ከተማ ነበረች። ኢየሩሳሌም በሦስት አቅጣጫዎች በሸለቆ የተከበበች ከመሆኗም በተጨማሪ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ እንደጻፈውም በሰሜን በኩል በሦስት እጥፍ በቅጥር የታጠረች ስለነበረች ደህንነቷ የተጠበቀ ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ደህንነቱ እንዲጠበቅ ከቅጥርና ከጦር መሣሪያ የበለጠ ነገር ያስፈልገዋል። ውኃም ሊኖረው ይገባል። አንድ አገር በጦር ኃይል ቢከበብና በአገሪቱ ውስጥ የውኃ እጥረት ቢኖር በቁጥጥር ሥር የዋሉት የአገሩ ሰዎች እጃቸውን ለመስጠት ይገደዳሉ።
ኢየሩሳሌም ውኃ የምታገኘው ከሰሊሆም የውኃ ኩሬ ነበር። ሆኖም በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ንጉሥ ሕዝቅያስ የአሦራውያንን ከበባ በመፍራት ከከተማው ውጭ ቅጥር ሠርቶ በማጠር ኩሬው ከከተማው ጋር እንዲቀላቀል አደረገ። በተጨማሪም ከከተማው ውጭ ያለውን የውኃ ምንጭ ስለደፈነው መሽገው የያዙት አሦራውያን ውኃ እንዳያገኙ አደረገ። (2 ዜና መዋዕል 32:2-5፤ ኢሳይያስ 22:11) ይህ ብቻ አይደለም። ሕዝቅያስ ተጨማሪ ውኃ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲገባ የሚያስችል መንገድ ቀይሷል።
ሕዝቅያስ ከግዮን የውኃ ምንጭ አንስቶ እስከ ሰሊሆም ኩሬ ድረስ የቆፈረው ዋሻ እጅግ አስደናቂ የሆነ ታላቅ የምህንድስና ሥራ ነው።b ይህ ዋሻ በግምት 1.8 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን 533 ሜትር ርዝመት ነበረው። ግማሽ ኪሎ ሜትር የሚደርስ ከዓለት የተፈለፈለ ዋሻ ማየት እንዴት የሚያስደንቅ ነው! በአሁኑ ጊዜ ከ2,700 ዓመት በኋላ ኢየሩሳሌምን ለመጎብኘት የሚሄዱ ጎብኚዎች በተለምዶ የሕዝቅያስ ዋሻ ተብሎ በሚታወቀው አስደናቂ የምህንድስና ውጤት በሆነው በዚህ ዋሻ ውስጥ ለውስጥ ሊሄዱ ይችላሉ።—2 ነገሥት 20:20፤ 2 ዜና መዋዕል 32:30
ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም የሚፈሰውን ውኃ ለመጠበቅና መጠኑን ለመጨመር ካደረገው ጥረት ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። ይሖዋ “የሕይወት ውኃ ምንጭ” ነው። (ኤርምያስ 2:13 የ1980 ትርጉም) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት የእርሱ ሐሳቦች ሕይወትን ጠብቀው የሚያቆዩ ናቸው። የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የግድ አስፈላጊ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ ለጥናት የሚሆን የተመቻቸ ሁኔታና በጥናት አማካኝነት የሚገኘው እውቀት ያለምንም ጥረት ወደ አንተ አይፈስም። በየቀኑ በምታደርገው እንቅስቃሴ ሥራ የበዛብህ ብትሆንም የተወሰነ ጊዜ ለማግኘት ‘ዋሻዎችን መቆፈር’ ይኖርብህ ይሆናል። (ምሳሌ 2:1-5፤ ኤፌሶን 5:15, 16) አንዴ ከጀመርክ ለግል ጥናትህ የመጀመሪያውን ቦታ በመስጠት ካወጣኸው ፕሮግራም ጋር የሙጥኝ በል። ይህን ከሁሉ የላቀ ውኃ ማንም ሰው ወይም ምንም ነገር እንዲሰርቅብህ አትፍቀድ።—ፊልጵስዩስ 1:9, 10
ምድረ በዳው አካባቢ
ከይሁዳ ተራሮች በስተ ምሥራቅ ሴሞን በመባል ጭምር የሚታወቀው የይሁዳ ምድረ በዳ ይገኛል። ሴሞን “በረሃ” ማለት ነው። (1 ሳሙኤል 23:19 አዓት የግርጌ ማስታወሻ) ዓለታማ ሸለቆና ጭልጥ ያለ ገደል የበዛበት ይህ ጠፍ መሬት በጨው ባሕር አቅራቢያ ይገኛል። 24 ኪሎ ሜትር ባልበለጠ ርቀት ውስጥ ወደ 1,200 ሜትር ወደ ታች ዝቅ የሚለው የይሁዳ ምድረ በዳ በምዕራብ በኩል ዝናብ አዝሎ ከሚመጣው ነፋስ ስለተከለለ የሚያገኘው የዝናብ መጠን ዝቅተኛ ሊሆን ችሏል። በዓመታዊው የስርየት ቀን ለዓዛዜል የሆነው ፍየል የሚሰደደው ወደ እዚህ ምድረ በዳ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። ዳዊትም ከሳኦል ፊት የሸሸው ወደዚህ ቦታ ነው። ኢየሱስም ለ40 ቀናት የጾመውና በዲያብሎስ የተፈተነው እዚህ ነው።—ዘሌዋውያን 16:21, 22፤ መዝሙር 63 ከምዕራፉ ቀጥሎ ያለው ዓረፍተ ነገር፤ ማቴዎስ 4:1-11
ከይሁዳ ምድረ በዳ ደቡባዊ ምዕራብ በኩል በግምት 160 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ የፋራን ምድረ በዳ ይገኛል። እስራኤላውያን ከግብፅ ተነስተው ወደ ተስፋይቱ ምድር ላደረጉት 40 ዓመት የፈጀ ጉዞ በርካታ ጊዜ የሠፈሩት በዚህ ክልል ውስጥ ነበር። (ዘኁልቁ 33:1-49) ሙሴ ስለዚህ ቦታ “እባብና ጊንጥ ጥማትም ባለበት፣ ውኃም በሌለባት፣ በታላቂቱና በምታስፈራው” ሲል ጽፏል። (ዘዳግም 8:15) በሚልዮን የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በሕይወት መትረፋቸው በጣም የሚያስደንቅ ነው! ሆኖም ሕይወታቸውን ጠብቆ ያቆየው ይሖዋ ነበር።
ይህ ታሪክ በዚህ በመንፈሳዊ ጠፍ በሆነ ዓለምም ይሖዋ ሕይወታችንን ጠብቆ ሊያቆየን እንደሚችል ያሳስበናል። ምንም እንኳ ቃል በቃል ባይሆንም እኛም በእባቦችና በጊንጦች መካከል እናልፋለን። አስተሳሰባችንን በቀላሉ ሊያበላሽ የሚችል መርዘኛ ንግግር ከሚያዥጎደጉዱ ሰዎች ጋር በየቀኑ መገናኘታችን የግድ ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 5:3, 4፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:20) እነዚህ መሰናክሎች እያሉባቸው አምላክን ለማገልገል የሚጣጣሩ ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። የሚያሳዩት ታማኝነት ጠንካራ በመሆኑ ምክንያት በእርግጥም ይሖዋ ሕይወታቸውን ጠብቆ ያኖራቸዋል።
የቀርሜሎስ ኮረብታ
በእንግሊዝኛ ካርሜል የሚለው ስም ትርጉም “ፍሬያማ” ማለት ነው። በሰሜን በኩል 50 ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት ያለው ለም መሬት በወይን ተክል፣ በወይራ እርሻና በፍራፍሬ ዛፎች የተሸፈነ ነው። የዚህ ኮረብታማ ሸንተረር ግርማና ውበት የማይረሳ ነው። ኢሳይያስ 35:2 እንደገና የተቋቋመው የእስራኤል ምድር ምርታማ በመሆኑ ምክንያት ያገኘውን ክብር ለማመልከት ‘የቀርሜሎስ ግርማ’ በማለት ይገልጸዋል።
በቀርሜሎስ ሲታወሱ የሚኖሩ ክንውኖች ተፈጽመዋል። ኤልያስ የበኣል ነቢያትን ያሳፈረውና “የእግዚአብሔርም እሳት ወድቆ” የይሖዋን ታላቅነት ያረጋገጠው በዚህ ሥፍራ ነበር። በተጨማሪም በእስራኤል የተከሰተውን ድርቅ በተዓምር እንዲያበቃ ያደረገው ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ታናሽ ደመና እንደሚመጣ ኤልያስ የተናገረው በዚህ በቀርሜሎስ አናት ላይ ሆኖ ነበር። (1 ነገሥት 18:17-46) ሱነማይቷ ሴት በልጅዋ ሞት ምክንያት እርዳታ እንዲያደርግላት ለመጠየቅ በመጣች ጊዜ የኤልያስ ተተኪ የሆነው ኤልሳዕ በዚህ በቀርሜሎስ ተራራ አናት ላይ ነበር። ከዚያም ኤልሳዕ ልጅዋን ከሞት አስነሳላት።—2 ነገሥት 4:8, 20, 25-37
የቀርሜሎስ ሸንተረር አሁንም በፍራፍሬዎች፣ በወይራ ዛፎችና በወይን ተክሎች የተሸፈነ ነው። በጸደይ ወራት እነዚህ ሸንተረሮች በሚያማምሩ አበቦች ይሸፈናሉ። ሰሎሞን የሚያምረውን ጠጉሯን ወይም ውብ የሆነውን የራሷን ቅርጽ ለመግለጽ “የራስሽ ቅርጽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ ነው” በማለት ሱላማጢሷን ሴት በማድነቅ ሰሎሞን ተናግሯል።—መኃልየ መኃልይ 7:5 የ1980 ትርጉም
ኮረብታማው ቀርሜሎስ የተላበሰው ውበት ይሖዋ በዘመናዊ የአምልኮ ድርጅቱ ላይ አትረፍርፎ ያፈሰሰውን መንፈሳዊ ውበት እንድናስታውስ ያደርገናል። (ኢሳይያስ 35:1, 2) በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ይኖራሉ። ንጉሥ ዳዊት “ለእኔ የለገሥኸው ስጦታ እንዴት ድንቅ ነው! እጅግም መልካም ነው” በማለት ከገለጸው አባባል ጋር ይስማማሉ።—መዝሙር 16:6 የ1980 ትርጉም
የጥንት እስራኤላውያን ከአምላክ ጠላቶች የማያቋርጥ ተቃውሞ ያጋጥማቸው እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ያሉትም የአምላክ መንፈሳዊ ሕዝቦች ፊት ለፊት የሚጋፈጧቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉባቸው። ቢሆንም ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋ እያዘነበ ያለውን በረከት፣ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄደውን የመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን ጨምሮ ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነትንና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘትን አጋጣሚ በቀላሉ አይመለከቱትም።—ምሳሌ 4:18፤ ዮሐንስ 3:16፤ 13:35
“እንደ እግዚአብሔር ገነት”
የጥንቱ የተስፋይቱ ምድር ገጽታ ለእይታ የሚማርክ ነበር። “ወትትና ማር የምታፈስስ” በሚል ጥሩ አነጋገር ተገልጿል። (ዘፍጥረት 13:10፤ ዘጸአት 3:8) ሙሴም “መልካም ምድር፣ ከሸለቆና ከኮረብታ የሚመነጩ የውኃ ጅረቶችና ፈሳሾች ምንጮችም ወዳሉባት ምድር፣ ስንዴ ገብስም ወይንም በለስም ሮማንም ወይራም ማርም ወደ ሞሉባት ምድር፣ ሳይጎድልህ እንጀራን ወደምትበላባት አንዳችም ወደማታጣባት ምድር ድንጋይዋ ብረት ወደ ሆነ፣ ከተራራዋም መዳብ ወደሚማስባት ምድር” በማለት ጠርቶታል።—ዘዳግም 8:7-9
ይሖዋ ለጥንት ሕዝቦቹ እንዲህ የመሰለ ውብ መኖሪያ መስጠት ከቻለ ለዘመናዊ ታማኝ ሕዝቦቹም ተራሮች፣ ሸለቆዎች፣ ወንዞችና ሐይቆች የሞሉበትን ምድር አቀፍ ገነት እንደሚሰጣቸው ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲያውም የተለያየ ገጽታ የነበረው የጥንቱ ተስፋይቱ ምድር በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ላገኙት መንፈሳዊ ገነትና ወደፊት በአዲሱ ዓለም ለሚያገኙት ገነት የቅምሻ ያህል ብቻ ነው። በዚያን ጊዜ በመዝሙር 37:29 ላይ የተመዘገበው “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚለው ተስፋ ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል። ይሖዋ ያንን ገነታዊ መኖሪያ ታዛዥ ለሆኑት የሰው ልጆች በሚሰጥበት ጊዜ “ክፍሎቹን” ሲጎበኙና ለዘላለምም ተጠልለው ሲኖሩ ምን ያህል ይፈነድቁ ይሆን!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ከዚህ አካባቢ የተገኘ አንድ የወይን ዘለላ 12 ኪሎ ግራም ክብደት ሲኖረው፣ ሌላኛው ደግሞ ከ20 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት እንደነበረው ተመዝግቧል።
b የግዮን የውኃ ምንጭ ከኢየሩሳሌም ምሥራቃዊ ድንበር በኩል ባለው ውጫዊ ቦታ ላይ ይገኛል። ይህ ምንጭ የሚገኘው በዋሻ ውስጥ ስለነበር አሦራውያን የምንጩን መኖር ለማወቅ ተስኗቸዋል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ገሊላ
የቀርሜሎስ ተራራ
የገሊላ ባሕር
ሰማሪያ
ሼፌላህ
የይሁዳ ተራሮች
የጨው ባሕር
[ምንጭ]
NASA photo
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሼፌላህ በአምላክ ሕዝቦችና በአምላክ ጠላቶች መካከል የሚገኝ ድንበር ነበር
ሚሜ 0 5 10
ኪሜ 0 8 16
የፍልስጥኤም ሜዳ
ሼፌላህ
ኮረብታማው የይሁዳ ምድር
የይሁዳ ምድረ በዳ
ስምጥ ሸለቆ
የጨው ባሕር
የአሞንና የሞአብ ምድር
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የሕዝቅያዝ ዋሻ፦ ከዓለት ተፈልፍሎ የተሠራው 533 ሜትር ርዝማኔ ያለው ዋሻ
ታይሮፒዮን ሸለቆ
ሰሊሆም
የዳዊት ከተማ
ኪድሮን ሸለቆ
ግዮን
[በገጽ 6 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዳዊት ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በይሁዳ ምድረ በዳ ተሸሽጓል። ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ እዚሁ ቦታ በዲያብሎስ ተፈትኗል
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኤልያስ የበኣል ነቢያትን ያሳፈረበት የቀርሜሎስ ተራራ
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መልካም ምድር፣ ከሸለቆና ከኮረብታ የሚመነጩ የውኃ ጅረቶችና ፈሳሾች ምንጮችም ወዳሉባት ምድር . . . ያገባሃል።”—ዘዳግም 8:7