እረኞች፣ ከሁሉ የላቁትን እረኞች አርዓያ ተከተሉ
‘ክርስቶስ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ለእናንተ መከራ ተቀብሏል።’—1 ጴጥ. 2:21
1, 2. (ሀ) በጎች ጥሩ እንክብካቤ ሲያገኙ ውጤቱ ምን ይሆናል? (ለ) በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች እረኛ እንደሌላቸው በጎች የነበሩት ለምንድን ነው?
አንድ እረኛ ለበጎቹ ደህንነት ከልብ የሚያስብ ከሆነ በጎቹ ተመችቷቸው ያድጋሉ። የበግ እርባታን አስመልክቶ የተጻፈ አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “እረኛው መንጋውን አንዴ በግጦሽ ስፍራ ካሰማራ በኋላ ዞር ብሎ የማያይ ወይም ግድ የማይሰጠው ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በጎቹ የሚታመሙ ከመሆኑም ሌላ ለኪሳራ ይዳረጋል።” ይሁን እንጂ እረኛው ለበጎቹ ተገቢውን እንክብካቤ የሚያደርግ ከሆነ መንጋው ጤናማ ይሆናል።
2 የአምላክን መንጋ የሚጠብቁ እረኞች በአደራ ለተሰጣቸው ለእያንዳንዱ በግ የሚሰጡት እንክብካቤና ትኩረት በመላው ጉባኤ መንፈሳዊ ጤንነት ላይ ለውጥ ያመጣል። ኢየሱስ ሕዝቡ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር” እንዳዘነላቸው ታስታውስ ይሆናል። (ማቴ. 9:36) እንዲህ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ሊወድቁ የቻሉት ለምንድን ነው? የአምላክን ሕግ የማስተማር ኃላፊነት ተጥሎባቸው የነበሩት ሰዎች ጨካኝ፣ በቀላሉ የማይረኩና ግብዝ ስለነበሩ ነው። የእስራኤል መንፈሳዊ መሪዎች በመንጋው ውስጥ ያሉትን በጎች ከመርዳትና ከመንከባከብ ይልቅ በትከሻቸው ላይ “ከባድ ሸክም” ይጭኑ ነበር።—ማቴ. 23:4
3. የጉባኤ ሽማግሌዎች የእረኝነት ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
3 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን እረኞች ማለትም የተሾሙ ሽማግሌዎች ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። በእነሱ ጥበቃ ሥር የሚገኙት በጎች የይሖዋና የኢየሱስ ንብረት ናቸው፤ ኢየሱስ ደግሞ “እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ” ብሏል። (ዮሐ. 10:11) ኢየሱስ የራሱን “ውድ ደም” በመክፈል ‘በዋጋ ገዝቷቸዋል።’ (1 ቆሮ. 6:20፤ 1 ጴጥ. 1:18, 19) በጎቹን በጣም የሚወዳቸው ከመሆኑ የተነሳ ሕይወቱን ለእነሱ በፈቃደኝነት መሥዋዕት አድርጓል። ሽማግሌዎች፣ “ታላቅ የበጎች እረኛ” ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ አመራር የሚገዙ የበታች እረኞች መሆናቸውን ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርባቸዋል።—ዕብ. 13:20
4. በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
4 ታዲያ ክርስቲያን እረኞች በጎቹን ሊይዟቸው የሚገባው እንዴት ነው? የጉባኤው አባላት “በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ” የሚል ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያን ሽማግሌዎች “የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ [ሥልጣናቸውን]” ከማሳየት እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (ዕብ. 13:17፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3ን አንብብ።) ታዲያ የተሾሙ ሽማግሌዎች በመንጋው ላይ ሥልጣናቸውን ከማሳየት በመቆጠብ አመራር መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው? በሌላ አባባል፣ ሽማግሌዎች አምላክ ለበላይ ተመልካቾች ከሰጠው ሥልጣን ሳያልፉ በጎቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት የሚችሉት እንዴት ነው?
‘በዕቅፉ ይይዛቸዋል’
5. ኢሳይያስ 40:11 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ስለ ይሖዋ ምን ያስገነዝበናል?
5 ነቢዩ ኢሳይያስ ይሖዋን በተመለከተ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤ ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በዕቅፉም ይይዛቸዋል፤ የሚያጠቡትንም በጥንቃቄ ይመራል።” (ኢሳ. 40:11) ይህ ጥቅስ ይሖዋ ደካማ የሆኑና ለአደጋ የተጋለጡ የጉባኤው አባላት ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ትኩረት እንደሚሰጥ ያሳያል። አንድ እረኛ በመንጋው ውስጥ ያለው እያንዳንዱ በግ የሚያስፈልገውን ነገር እንደሚገነዘብና ያንን ለማሟላት ዝግጁ እንደሆነ ሁሉ ይሖዋም በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ያውቃል እንዲሁም አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርጋል። አንድ እረኛ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ አንዲትን ግልገል በዕቅፉ እንደሚሸከም ሁሉ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው” ይሖዋም የሚያጋጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች ተቋቁመን እንድናልፍ ይረዳናል። ከባድ ፈተና ሲደርስብን ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን ያጽናናናል።—2 ቆሮ. 1:3, 4
6. አንድ ሽማግሌ የይሖዋን ምሳሌ መከተል የሚችለው እንዴት ነው?
6 አንድ መንፈሳዊ እረኛ በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ግሩም ትምህርት ማግኘት ይችላል! ልክ እንደ ይሖዋ እሱም በጎቹ ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ትኩረት መስጠት ይኖርበታል። አንድ ሽማግሌ በጎቹ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንዳሉባቸውና የትኞቹ ጉዳዮች አፋጣኝ ትኩረት እንደሚያሻቸው የሚገነዘብ ከሆነ አስፈላጊውን ማበረታቻና ድጋፍ መስጠት ይችላል። (ምሳሌ 27:23) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አንድ ሽማግሌ ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ሊያደርግ ይገባል። በግል ጉዳያቸው ጣልቃ ከመግባት የሚቆጠብ ቢሆንም በጉባኤው ውስጥ ለሚያየውና ለሚሰማው ነገር ትኩረት ይሰጣል፤ እንዲሁም በፍቅር ተነሳስቶ ‘ደካማ የሆኑትን ለመርዳት’ ጥረት ያደርጋል።—ሥራ 20:35፤ 1 ተሰ. 4:11
7. (ሀ) በሕዝቅኤልና በኤርምያስ ዘመን የነበሩት የአምላክ በጎች ምን ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር? (ለ) ይሖዋ ታማኝ ያልሆኑትን መንፈሳዊ እረኞች ማውገዙ ምን ያስገነዝበናል?
7 በሕዝቅኤልና በኤርምያስ ዘመን የአምላክን ሕዝብ የመንከባከብ ኃላፊነት ተጥሎባቸው የነበሩት እረኞች ምን ዓይነት አመለካከት እንደነበራቸው እንመልከት። እነዚህ እረኞች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሳይወጡ በመቅረታቸው ይሖዋ አውግዟቸዋል። በጎቹ የሚጠብቃቸው አንድም ሰው ባለመኖሩ ለአደጋ ተጋልጠውና ተበታትነው ነበር። እነዚህ እረኞች በጎቹን ከመመገብ ይልቅ ይበዘብዟቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ‘ራሳቸውን ይንከባከቡ’ ወይም ይመግቡ ነበር። (ሕዝ. 34:7-10፤ ኤር. 23:1) የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት መሪዎችም ተመሳሳይ ድርጊት በመፈጸማቸው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጥተዋል። ከዚህ አንጻር ሲታይ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለይሖዋ መንጋ ተገቢ ትኩረት መስጠታቸውና ፍቅራዊ እንክብካቤ ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነው።
“አርዓያ ሆኜላችኋለሁ”
8. ኢየሱስ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማረም ረገድ ግሩም ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?
8 አንዳንድ የአምላክ በጎች ከሰብዓዊ አለፍጽምና የተነሳ ይሖዋ የሚጠብቅባቸውን ነገር ቶሎ አይረዱ ይሆናል። እንዲህ ያሉ የመንጋው አባላት ቅዱስ ጽሑፉ ከሚሰጠው ምክር ጋር የሚስማማ እርምጃ ሳይወስዱ ሊቀሩ ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ መንፈሳዊ ጉልምስና እንደሚጎድላቸው የሚያሳይ ድርጊት ይፈጽሙ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያሳየውን ዓይነት ትዕግሥት ማንጸባረቅ ይኖርባቸዋል፤ ደቀ መዛሙርቱ ‘በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከመካከላችን ታላቅ የሚሆነው ማን ነው?’ የሚል ክርክር አንስተው ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ከመበሳጨት ይልቅ ደቀ መዛሙርቱን ማስተማሩንና ትሑት መሆንን በተመለከተ ፍቅራዊ ምክር መስጠቱን ቀጥሏል። (ሉቃስ 9:46-48፤ 22:24-27) ኢየሱስ እግራቸውን በማጠብ ትሑት መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አሳይቷቸዋል። በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችም ትሕትናን ሊያንጸባርቁ ይገባል።—ዮሐንስ 13:12-15ን አንብብ፤ 1 ጴጥ. 2:21
9. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው አበረታቷል?
9 ኢየሱስ መንፈሳዊ እረኞች ያላቸውን ሚና በተመለከተ ያለው አመለካከት፣ በአንድ ወቅት ያዕቆብና ዮሐንስ ካሳዩት አመለካከት የተለየ ነበር። እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በመንግሥቱ ውስጥ ላቅ ያለ ቦታ ለማግኘት ፈልገው ነበር። ኢየሱስ ግን እንዲህ በማለት አመለካከታቸውን እንዲያስተካክሉ ረድቷቸዋል፦ “የባዕድ አገር ገዢዎች በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችን ማዘዝ እንደሚወዱ ታውቃላችሁ። ታላላቅ መሪዎቻቸውም በሚገዟቸው ሰዎች ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን አላቸው። እናንተ ግን እንደ እነሱ አትሁኑ። ታላቅ መሆን የምትፈልጉ ከሆነ የሌሎቹ ሁሉ አገልጋይ መሆን አለባችሁ።” (ማቴ. 20:25, 26 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን) ሐዋርያቱ በባልንጀሮቻቸው ላይ ‘ሥልጣናቸውን ለማሳየት’ ወይም ‘በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችን ለማዘዝ’ ያላቸውን ፍላጎት ማስወገድ አስፈልጓቸው ነበር።
10. ኢየሱስ ሽማግሌዎች መንጋውን በምን መንገድ እንዲይዙ ይፈልጋል? በዚህ ረገድ ጳውሎስ ምን ምሳሌ ትቷል?
10 ኢየሱስ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መንጋውን እሱ በያዘበት መንገድ እንዲይዙ ይፈልጋል። በባልንጀሮቻቸው ላይ እንደ ጌታ ከመሠልጠን ይልቅ የእነሱ አገልጋይ ለመሆን ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት የትሕትና ባሕርይ አንጸባርቋል፤ በኤፌሶን ጉባኤ ለነበሩ ሽማግሌዎች የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ ይህን ያሳያል፦ “በእስያ አውራጃ እግሬ ከረገጠበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ በዚያ በቆየሁበት ጊዜ ሁሉ ከእናንተ እንዳልተለየሁ ታውቃላችሁ፤ . . . በታላቅ ትሕትናና በእንባ ጌታን አገለግል ነበር።” ሐዋርያው እነዚህ ሽማግሌዎች ሌሎችን ከልብ በመነጨ ስሜትና በትሕትና እንዲያገለግሉ ይፈልግ ነበር። “እናንተም እንዲሁ እየሠራችሁ ደካማ የሆኑትን መርዳት እንዳለባችሁ በሁሉም ነገር አሳይቻችኋለሁ” ብሏል። (ሥራ 20:18, 19, 35) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን “በእምነታችሁ ላይ የምናዝ አይደለንም” ሲል ገልጾላቸዋል። ከዚህ ይልቅ ለደስታቸው ከእነሱ ጋር አብሮ እንደሚሠራ ተናግሯል። (2 ቆሮ. 1:24) ጳውሎስ ትሕትና በማሳየትና ተግቶ በመሥራት ረገድ በዛሬው ጊዜ ላሉ ሽማግሌዎች ግሩም ምሳሌ ትቷል።
‘የታመነውን ቃል አጥብቃችሁ ያዙ’
11, 12. አንድ ሽማግሌ የእምነት ባልንጀራውን ውሳኔ እንዲያደርግ እንዴት ሊረዳው ይችላል?
11 አንድ የጉባኤ ሽማግሌ “ከማስተማር ጥበቡ ጋር በተያያዘ የታመነውን ቃል አጥብቆ የሚይዝ ሊሆን ይገባል።” (ቲቶ 1:9) ይሁንና ይህን የሚያደርገው “በገርነት መንፈስ” ነው። (ገላ. 6:1) አንድ ጥሩ መንፈሳዊ እረኛ የጉባኤው አባላት የሆነ ነገር እንዲያደርጉ ለማስገደድ ከመሞከር ይልቅ ልባቸውን ማርኮ ለተግባር ለማነሳሳት ይጥራል። ለምሳሌ ያህል አንድ ሽማግሌ፣ አንድ ወንድም ትልቅ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት የትኞቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርበት ሊገልጽለት ይችላል። በተጨማሪም ስለ ጉዳዩ የሚያብራሩ ጽሑፎችን አብሮት ሊከልስ ይችላል። ግለሰቡ ያሉት የተለያዩ አማራጮች ከይሖዋ ጋር ባለው ዝምድና ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉም ቆም ብሎ እንዲያስብ ሊያበረታታው ይችላል። ሽማግሌው፣ ግለሰቡ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት የአምላክን አመራር በጸሎት መጠየቁ ያለውን ጠቀሜታ አበክሮ ሊገልጽለት ይችላል። (ምሳሌ 3:5, 6) ሽማግሌው እነዚህን ጉዳዮች አንስቶ ከእምነት ባልንጀራው ጋር ከተወያየ በኋላ ውሳኔውን ለግለሰቡ ይተወዋል።—ሮም 14:1-4
12 ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የሚሰጡት አመራር ምንጊዜም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ መጠቀማቸውና በውስጡ የያዘውን ሐሳብ በጥብቅ መከተላቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ሽማግሌዎች እንዲህ ማድረጋቸው በሥልጣናቸው አላግባብ ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ይረዳቸዋል። መቼም ቢሆን የበታች እረኞች መሆናቸውን መዘንጋት የለባቸውም፤ እያንዳንዱ የጉባኤው አባል ለሚያደርጋቸው ውሳኔዎች በይሖዋና በኢየሱስ ዘንድ ተጠያቂ ነው።—ገላ. 6:5, 7, 8
“ለመንጋው ምሳሌ” ሁኑ
13, 14. አንድ ሽማግሌ ለመንጋው ምሳሌ መሆን የሚገባው በየትኞቹ መስኮች ነው?
13 ሐዋርያው ጴጥሮስ የጉባኤ ሽማግሌዎች በተሰጣቸው ‘መንጋ ላይ መሠልጠን’ እንደሌለባቸው ምክር ከሰጠ በኋላ “ለመንጋው ምሳሌ” እንዲሆኑ አበረታቷቸዋል። (1 ጴጥ. 5:3) አንድ ሽማግሌ ለመንጋው ምሳሌ መሆን የሚችለው እንዴት ነው? “የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ማንኛውም ሰው” ሊያሟላቸው ከሚገቡ ብቃቶች መካከል ሁለቱን እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ “ጤናማ አስተሳሰብ ያለው” መሆን አለበት፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “የራሱን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድር ሊሆን ይገባዋል።” አንድ ሽማግሌ ቤተሰብ ያለው ከሆነ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት መንገድ ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን ይገባል፤ “ደግሞስ አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ እንዴት እንደሚያስተዳድር ካላወቀ የአምላክን ጉባኤ እንዴት ሊንከባከብ ይችላል?” (1 ጢሞ. 3:1, 2, 4, 5) አንድ ወንድም ለበላይ ተመልካችነት ኃላፊነት ብቁ ለመሆን ጤናማ አስተሳሰብ ሊኖረው ይገባል ሲባል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚገባ ይረዳል እንዲሁም በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጋቸው ያውቃል ማለት ነው። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በረጋ መንፈስ ያስባል እንጂ ለውሳኔ አይቸኩልም። የጉባኤው አባላት እነዚህን ባሕርያት በሽማግሌዎች ላይ ማየታቸው በእነሱ እንዲተማመኑ ያደርጋቸዋል።
14 በተጨማሪም የበላይ ተመልካቾች በመስክ አገልግሎት ግንባር ቀደም በመሆን ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ለበላይ ተመልካቾች ግሩም ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበኩ ሥራ ትልቅ ቦታ ሰጥቷል። ከዚህም ሌላ ሥራው እንዴት መከናወን እንዳለበት ለደቀ መዛሙርቱ አሳይቷቸዋል። (ማር. 1:38፤ ሉቃስ 8:1) በዛሬው ጊዜ አስፋፊዎች ከሽማግሌዎች ጋር አብረው ሲያገለግሉ፣ ሽማግሌዎች ለዚህ ሕይወት አድን ሥራ ያላቸውን ቅንዓት ሲመለከቱና የሚያስተምሩበትን መንገድ በትኩረት በመከታተል ትምህርት ሲቀስሙ በጣም ይበረታታሉ! የበላይ ተመልካቾች የተጣበበ ፕሮግራም ቢኖራቸውም ምሥራቹን ለመስበክ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን መሥዋዕት ለማድረግ የሚያሳዩት ቁርጠኝነት ጉባኤው በአጠቃላይ ተመሳሳይ ቅንዓት ለማሳየት እንዲነሳሳ ያደርጋል። በተጨማሪም ሽማግሌዎች ለጉባኤ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና ተሳትፎ በማድረግ እንዲሁም የመንግሥት አዳራሹን እንደ ማጽዳትና መጠገን በመሳሰሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች በመካፈል ለወንድሞቻቸው ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላሉ።—ኤፌ. 5:15, 16፤ ዕብራውያን 13:7ን አንብብ።
“ደካሞችን ደግፏቸው”
15. ሽማግሌዎች የእረኝነት ጉብኝት የሚያደርጉባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
15 አንድ ጥሩ እረኛ በመንጋው መካከል ያለ አንድ በግ በሚጎዳበት ወይም በሚታመምበት ጊዜ ለመርዳት አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል። በተመሳሳይም ሽማግሌዎች አንድ የጉባኤ አባል ችግር ላይ በሚወድቅበት ወይም መንፈሳዊ ድጋፍ በሚያስፈልገው ጊዜ እርዳታ ለመስጠት ፈጣን መሆን አለባቸው። በዕድሜ የገፉና የጤና እክል ያለባቸው ወንድሞች ካለባቸው ችግር አንጻር ለየት ያለ ትኩረት ያሻቸው ይሆናል፤ ከምንም በላይ ግን መንፈሳዊ እርዳታና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። (1 ተሰ. 5:14) በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወጣቶች ደግሞ ‘ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ምኞቶችን’ እንደ መቋቋም ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ ይሆናል። (2 ጢሞ. 2:22) በመሆኑም የእረኝነት ሥራ የጉባኤው አባላት እየተጋፈጧቸው ያሉትን ሁኔታዎች ለመረዳትና ተስማሚ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመስጠት ለማበረታታት እነሱን በየተወሰነ ጊዜ ሄዶ መጎብኘትን ያካትታል። እንዲህ ያሉ ጉዳዮች በወቅቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ብዙ ችግሮች ሥር ከመስደዳቸው በፊት መፍትሔ ሊያገኙ ይችላሉ።
16. አንድ የጉባኤ አባል መንፈሳዊ እርዳታ በሚያስፈልገው ጊዜ ሽማግሌዎች ምን ዓይነት እርዳታ መስጠት ይችላሉ?
16 ይሁንና አንድ የጉባኤ አባል ያሉበት ችግሮች እየተባባሱ ሄደው መንፈሳዊ ጤንነቱ ለአደጋ ቢጋለጥስ? የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ “ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ፤ እነሱም በይሖዋ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ይሖዋም ያስነሳዋል። በተጨማሪም ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባልለታል።” (ያዕ. 5:14, 15) በመንፈሳዊ የታመመው ሰው ‘ሽማግሌዎችን ባይጠራ’ እንኳ እነሱ ሁኔታውን እንደተረዱ ግለሰቡን ለመርዳት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎች ከወንድሞቻቸው ጋር ሆነው ሲጸልዩና ስለ እነሱ ጸሎት ሲያቀርቡ እንዲሁም በአስቸጋሪ ጊዜያት ድጋፍ ሲያደርጉላቸው በእነሱ ጥበቃ ሥር ላሉት የመንጋው አባላት በመንፈሳዊ ሁኔታ የእረፍትና የብርታት ምንጭ ይሆናሉ።—ኢሳይያስ 32:1, 2ን አንብብ።
17. ሽማግሌዎች “ታላቅ የበጎች እረኛ” የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ መከተላቸው ምን ውጤት ያስገኛል?
17 ክርስቲያን እረኞች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በሚያከናውኑት ሥራ ሁሉ “ታላቅ የበጎች እረኛ” የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ። ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲህ ያሉ ወንዶች የሚሰጡት መንፈሳዊ እርዳታ መንጋውን በእጅጉ የሚጠቅመው ከመሆኑም ሌላ ጉባኤው እየተጠናከረ እንዲሄድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ለዚህ ሁሉ አመስጋኝ ከመሆናችንም በተጨማሪ ታላቅ እረኛ የሆነውን ይሖዋን ለማወደስ እንገፋፋለን።