ይሖዋን በቃሉ አማካኝነት እወቀው
“እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” — ዮሐንስ 17:3
1, 2. (ሀ) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ባላቸው አጠቃቀም መሠረት “ማወቅ” እና “እውቀት” የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም አላቸው? (ለ) ይህን ትርጉም ግልጽ የሚያደርጉት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?
አንድን ሰው በመልክ ብቻ ማወቅ ወይም ስለ አንድ ነገር ያለን ላይ ላዩን ብቻ የሆነ እውቀት ቅዱሳን ጽሑፎች የተጠቀሙባቸውን “ማወቅ” እና “እውቀት” የሚሉትን ቃላት ትርጉም ሙሉ በሙሉ አያስተላልፍም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት እነዚህ ቃላት አንድን ነገር “በተሞክሮ አማካኝነት ማወቅን” እና “በሰዎች መካከል ያለውን በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት” የሚያሳይ እውቀትን ይጨምራሉ። (ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ ) ይህም በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ‘እኔ ይሖዋ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ’ በማለት በክፉ አድራጊዎች ላይ አምላክ ያስፈጸማቸውን የቅጣት ፍርዶች የመሰሉ ድርጊቶቹን በመመልከት ይሖዋን ማወቅን ይጨምራል። — ሕዝቅኤል 38:23
2 “ማወቅ” እና “እውቀት” የሚሉትን ቃላት በተለያዩ መንገዶች መጠቀም የሚቻል መሆኑን በጥቂት ምሳሌዎች ግልጽ ማድረግ ይቻላል። ኢየሱስ በስሙ በመጠቀም ብዙ ነገር አድርገናል ያሉትን ሰዎች “ከቶ አላወቅኋችሁም” ሲላቸው ከእነርሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ያልነበረው መሆኑን መግለጹ ነበር። (ማቴዎስ 7:23) ሁለተኛ ቆሮንቶስ 5:21 ክርስቶስ ‘ኃጢአትን አላወቀም’ ይላል። ይህም ክርስቶስ ስለ ኃጢአት ምንም ዓይነት ግንዛቤ አልነበረውም ማለት ሳይሆን እርሱ ኃጢአት አላደረገም ማለት ነው። በተመሳሳይም ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ሲል ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ አንዳንድ ነገሮችን ብቻ ከማወቅ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። — ከማቴዎስ 7:21 ጋር አወዳድር።
3. ይሖዋ እውነተኛውን አምላክ ለይቶ የሚያሳውቀውን ምልክት እንደሚያሳይ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?
3 ብዙዎቹን የይሖዋ ባሕርያት በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ማወቅ ይቻላል። ከእነርሱም አንዱ በትክክል ለመተንበይ ያለው ችሎታው ነው። ይህ ችሎታ እውነተኛው አምላክ ተለይቶ የሚታወቅበት ምልክት ነው። “ያምጡ፣ የሚሆነውንም ይንገሩን፤ ልብም እናደርግ ዘንድ ፍጻሜአቸውንም እናውቅ ዘንድ፣ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ተናገሩ፣ የሚመጡትንም አሳዩን። አማልክትም መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ በኋላ የሚመጡትን ተናገሩ፤ . . . እናይ ዘንድ መልካሙን ወይም ክፉውን አድርጉ።” (ኢሳይያስ 41:22, 23) ይሖዋ ስለ ምድር አፈጣጠርና በላይዋ ስላለው ሕይወት አጀማመር በቃሉ አማካኝነት ነግሮናል። ወደፊት የሚፈጸሙትን ነገሮች አስቀድሞ ተናግሯል፤ እነዚህንም ነገሮች ተፈጽመዋል። አሁንም ቢሆን በተለይ በእነዚህ ‘መጨረሻ ቀኖች ውስጥ’ ወደፊት ስለሚሆኑት አሳውቆናል። — 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5, 13፤ ዘፍጥረት 1:1–30፤ ኢሳይያስ 53:1–12፤ ዳንኤል 8:3–12, 20–25፤ ማቴዎስ 24:3–21፤ ራእይ 6:1–8፤ 11:18
4. ይሖዋ ኃይሉን ሲጠቀምበት የቆየው እንዴት ነው? ወደፊትስ ምን ለማድረግ ይጠቀምበታል?
4 ሌላው የይሖዋ ባሕርይ ደግሞ ኃይል ነው። በሰማያት ያሉ ከዋክብት ባንድነት እንደ አንድ ታላቅ እቶን በመሆን ብርሃንና ሙቀት የሚሰጡ መሆናቸው ግልጽ ነው። ዓመፀኛ ሰዎች ወይም መላእክት የይሖዋን ሉዓላዊነት በሚገዳደሩበት ጊዜ “ተዋጊ” በመሆን ኃይሉን ተጠቅሞ ጥሩውን ስሙንና የጽድቅ አቋም ደረጃዎቹን ያስከብራል። በኖህ ዘመን እንደደረሰው የውኃ መጥለቅለቅ፣ በሰዶምና በገሞራ እንዳመጣው ጥፋትና እስራኤላውያንን በቀይ ባሕር በኩል ባዳነበት መንገድ ኃይሉን በመጠቀም እንዲህ ባሉት ጊዜያት ከማጥፋት ወደ ኋላ አይልም። (ዘጸአት 15:3–7፤ ዘፍጥረት 7:11, 12, 24፤ 19:24, 25) በቅርቡም አምላክ “ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች” ለመቀጥቀጥ በኃይሉ ይጠቀማል። — ሮሜ 16:20
5. ይሖዋ ከኃይሉ ጋር አብሮ የሚሄድ ምን ተጨማሪ ባሕርይ አለው?
5 ሆኖም ይህ ሁሉ ገደብ የለሽ ኃይል ቢኖረውም ትሑት ነው። የ1980 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በመዝሙር 18:35, 36 ላይ እንዲህ ይላል:- “የአንተም ክብካቤ [ትህትና አዓት] ታላቅ ያደርገኛል። . . . እርምጃዬን አስፍተሃል።” የአምላክ ትህትና ‘ሰማይንና ምድርን ወደታች እንዲመለከትና ድኾችን ከትቢያ እንዲያነሣቸው’ ያደርገዋል። — መዝሙር 113:6, 7 የ1980 ትርጉም
6. ሕይወት አድን የሆነው የይሖዋ ባሕርይ ምንድን ነው?
6 ይሖዋ ከሰው ጋር ባለው ግንኙነት ያሳየው ምሕረት ሕይወት አድን ነው። ምናሴ አሰቃቂ የሆኑ ብዙ የጭካኔ ድርጊቶችን የፈጸመ ቢሆንም ይቅር በተባለ ጊዜ እንዴት ያለ ምሕረት ተደረገለት! ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “እኔም ኃጢአተኛውን:- በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፣ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፣ የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።” (ሕዝቅኤል 33:14, 16፤ 2 ዜና መዋዕል 33:1–6, 10–13) ኢየሱስ 77 ጊዜ፣ በአንድ ቀን 7 ጊዜም እንኳ ቢሆን ይቅርታ ስለማድረግ አጥብቆ በተናገረበት ጊዜ የይሖዋን ባሕርይ ማንጸባረቁ ነበር። — መዝሙር 103:8–14፤ ማቴዎስ 18:21, 22፤ ሉቃስ 17:4
ሁኔታዎች የሚሰሙት አምላክ
7. ይሖዋ ከግሪክ አማልክት የሚለየው እንዴት ነው? ምን ክቡር መብትስ ተከፍቶልናል?
7 እንደ ኤፊቆሮሳውያን ያሉት የግሪክ ፈላስፎች በአማልክት ያምኑ ነበር፤ ሆኖም ስለ ሰው ምንም ደንታ የሌላቸው ወይም ሰው ባለው ስሜት የማይነኩ ከምድር በጣም የራቁ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። በይሖዋና በታማኝ ምስክሮቹ መካከል ያለው ግንኙነት ከዚህ ምንኛ የተለየ ነው! “እግዚአብሔር በሕዝቡ ደስ ይለዋል።” (መዝሙር 149:4 1980 ትርጉም ) ከጥፋት ውኃ በፊት የነበሩት ክፉ ሰዎች እንዲጸጸትና ‘በልቡም እንዲያዝን’ አድርገውት ነበር። የእስራኤል ሕዝብ ታማኝ አለመሆን ይሖዋን አስመርሮትና አሳዝኖት ነበር። ክርስቲያኖች ታዛዥ ባለመሆናቸው የይሖዋን መንፈስ ሊያሳዝኑ ታማኝ ሲሆኑ ደግሞ ሊያስደስቱት ይችላሉ። እዚህ ግባ የማይባለው በምድር ላይ ያለ ሰው የአጽናፈ ዓለሙን ፈጣሪ ሊያስደስት ወይም ሊያሳዝን ይችላል ብሎ ማሰቡ እንዴት የሚያስገርም ነው! እርሱ ካደረገልን ነገሮች አንፃር ሲታይ እርሱን ለማስደስት የመቻል ክቡር መብት ማግኘታችን እጅግ በጣም የሚያስደንቅ ነው! — ዘፍጥረት 6:6፤ መዝሙር 78:40, 41፤ ምሳሌ 27:11፤ ኢሳይያስ 63:10፤ ኤፌሶን 4:30
8. አብርሃም በንግግር ነፃነቱ ተጠቅሞ ከይሖዋ ጋር የተነጋገረው እንዴት ነው?
8 የይሖዋ ፍቅር ‘በነፃነት ለመናገር’ የሚያስችል ትልቅ መብት የሰጠን መሆኑን የአምላክ ቃል ያሳያል። (1 ዮሐንስ 4:17 አዓት) ይሖዋ ሰዶምን ሊያጠፋ ሲል አብርሃም ያደረገውን ተመልከት። አብርሃም ይሖዋን እንዲህ አለው:- “በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን? አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን? . . . እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?” ለአምላክ እንዲህ ደፍሮ መናገሩ ምንኛ አስገራሚ ነው! ሆኖም ይሖዋ እዚያ 50 ጻድቃን ከተገኙ ሰዶምን ላለማጥፋት ተስማማ። አብርሃም ንግግሩን በመቀጠል የሰዎቹን ቁጥር ከ50 ወደ 20 ዝቅ አደረገው። አብርሃም ከመጠን በላይ ልመና አብዝቼ ይሆናል የሚል ስጋት ሳያድርበት አልቀረም። እርሱም:- “እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ፤ ምናልባት ከዚያ አሥር ቢገኙሳ?” በማለት ጠየቀ። አሁንም ይሖዋ በሐሳቡ በመስማማት “ስለ አሥሩ አላጠፋትም አለ።” — ዘፍጥረት 18:23–33
9. አብርሃም በዚያ መንገድ እንዲናገር ይሖዋ የፈቀደለት ለምን ነበር? ከዚህስ ምን ልንማር እንችላለን?
9 አብርሃም እንዲህ ባለ መንገድ በነፃነት እንዲናገር ይሖዋ የፈቀደለት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት አብርሃም ያደረበትን የጭንቀት ስሜት ይሖዋ ስለተገነዘበ ነው። የአብርሃም የወንድም ልጅ የሆነው ሎጥ በሰዶም ይኖር ስለነበር አብርሃምን ያሳሰበው ጉዳይ የሎጥ መትረፍ እንደሆነ ይሖዋ አውቋል። በተጨማሪም አብርሃም የአምላክ ወዳጅ ነበር። (ያዕቆብ 2:23) አንድ ሰው በተለይም ወዳጃችን የሆነ ሰው ስሜቱ በሆነ ነገር ተነክቶ በኃይለ ቃል በሚናገርበት ጊዜ ከንግግሩ በስተጀርባ ያሉትን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ስሜቱን ለመረዳት እንሞክራለንን? ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ሲነጋገር እንዳደረገው እኛም ከእርሱ ጋር በነፃነት ስንነጋገር ስሜታችንን የሚረዳልን መሆኑን ማወቃችን አያጽናናንምን?
10. የንግግር ነፃነት በጸሎት ጊዜ የሚረዳን እንዴት ነው?
10 በተለይ በከባድ ኃዘንና በከባድ የጭንቀት ስሜት ስንዋጥ ይህንን በነፃነት የመናገር መብታችንን በመጠቀም ‘ጸሎታችንን እንዲሰማልን’ የልባችንን ሁሉ አፍስሰን የመናገር ጽኑ ፍላጎት ያድርብናል። (መዝሙር 51:17፤ 65:2, 3) በእነዚህ ጊዜያት ቃላት ቢያጥሩንም “መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤” ይሖዋም ይሰማናል። እርሱ አሳባችንን ለማወቅ ስለሚችል “አንተ የማደርገውን ሁሉ ታውቃለህ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ ሆነህ ታስተውላለህ። ገና ከመናገሬ በፊት ምን ለማለት እንደማስብ ታውቃለህ” ብለን ልንናገር እንችላለን። ቢሆንም መለመናችንን፣ አጥብቀን መፈለጋችንንና ማንኳኳታችንን መቀጠል ይኖርብናል። — ሮሜ 8:26፤ መዝሙር 139:2, 4 1980 ትርጉም፤ ማቴዎስ 7:7, 8
11. ይሖዋ በእርግጥ የሚያስብልን መሆኑ የታየው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ ያስብልናል። እርሱ ለፈጠራቸው ፍጥረቶቹ የሚያስፈልጋቸውን አዘጋጅቶላቸዋል። “የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ። አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ።” (መዝሙር 145:15, 16) ይሖዋ በደን ውስጥ የሚኖሩ ወፎችን እንዴት እንደሚመግባቸው እንድናይ ተጋብዘናል። የሜዳ አበቦችን እንዴት ባለ ያማረ ልብስ እንዳስዋባቸው ተመልከት። አምላክ ለወፎችና ለአበቦች እንዳደረገው እንዲያውም ከዚያ የበለጠ እንደሚያደርግልን ኢየሱስ ጨምሮ ተናግሯል። ታዲያ ለምን ብለን እንጨነቃለን? (ዘዳግም 32:10፤ ማቴዎስ 6:26–32፤ 10:29–31) አንደኛ ጴጥሮስ 5:7 “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” በማለት ያበረታታሃል።
‘ትክክለኛው የባሕርዩ ምሳሌ’
12, 13. በፍጥረት ሥራውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት ሥራዎቹ በተጨማሪ ይሖዋን ለማየትና ለመስማት የምንችለው በምን ሌላ መንገድ ነው?
12 ይሖዋ አምላክን በፍጥረት ሥራው አማካኝነት ልናየው እንችላለን፤ ስላደረጋቸው ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ ልናየው እንችላለን፤ በተጨማሪም ተመዝግበው በሚገኙት ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች አማካኝነት እርሱን ለማየት እንችላለን። ኢየሱስ ራሱ በዮሐንስ 12:45 ላይ “እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል” ብሏል። በዮሐንስ 14:9 ላይም “እኔን ያየ አብን አይቶአል” በማለት ተናግሯል። ቆላስይስ 1:15 እንዲህ በማለት ይናገራል:- “እርሱም [ኢየሱስ] የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው።” ዕብራውያን 1:3 “እርሱም [ኢየሱስ] የክብሩ [የአምላክ ክብር] መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ” ነው ይላል።
13 ይሖዋ ልጁን የላከው ቤዛ እንዲሆን ብቻ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ በቃልም ሆነ በድርጊት ልንከተለው የሚገባንን ምሳሌ እንዲተውልንም ጭምር ነው። ኢየሱስ ይናገር የነበረው የአምላክን ቃል ነበር። በዮሐንስ 12:50 ላይ “የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ” ብሏል። የራሱን ሳይሆን አምላክ እንዲያደርግ የነገረውን ነገር ያደርግ ነበር። በዮሐንስ 5:30 ላይ “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም” ብሏል። — ዮሐንስ 6:38
14 (ሀ) ኢየሱስ እንዲያዝን ያደረጉት ምን የተመለከታቸው ነገሮች ናቸው? (ለ) የኢየሱስ የአነጋገር ዘዴ ሰዎች እርሱን ለመስማት እንዲጎርፉ ያደረጋቸው ለምንድን ነበር?
14 ኢየሱስ ለምጻሞችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ደንቆሮችን፣ ዕውሮችን፣ አጋንንት ያደረባቸውንና ስለሞቱ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው የሚያለቅሱትን ሰዎች ተመልክቷል። በአዘኔታ ተገፋፍቶ የታመሙትን ፈውሷል፤ የሞቱትንም አስነስቷል። ብዙ ሰዎች በመንፈሳዊ ተራቁተውና ተጥለው ስላያቸው ብዙ ነገሮችን ያስተምራቸው ጀመር። በተጨማሪም ትክክለኛ ብቻ ሳይሆን አስደሳችና የሌሎችን ልብ በቀጥታ ሊነኩ በሚችሉ ከልብ በተነገሩ ቃላት አስተምሯቸዋል። ይህም ወደ እርሱ እንዲሳቡ ስላደረጋቸው ማልደው ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲሄዱና በደስታ ትምህርቱን መከታተላቸውንና ማዳመጣቸውን እንዲቀጥሉ አስችሏቸዋል። ‘እንደዚህ ሰው የተናገረ ከቶ ማንም የለም’ እያሉ የሚናገረውን ለመስማት ይጎርፉ ነበር። በትምህርት አሰጣጡም እጅግ ይገረሙ ነበር። (ዮሐንስ 7:46፤ ማቴዎስ 7:28, 29፤ ማርቆስ 11:18፤ 12:37፤ ሉቃስ 4:22፤ 19:48፤ 21:38) ጠላቶቹ በጥያቄ ሊያጠምዱት በፈለጉ ጊዜ ወጥመዱን መልሶ በእነርሱ ላይ እንዲገለበጥ በማድረግ ጸጥ ያሰኛቸው ነበር። — ማቴዎስ 22:41–46፤ ማርቆስ 12:34፤ ሉቃስ 20:40
15. የኢየሱስ ስብከት ዋና መልእክት ምን ነበር? ሌሎች ይህን መልእክት በማስፋፋቱ ሥራ እንዲካፈሉ ያደረጋቸው እስከምን ድረስ ነው?
15 ኢየሱስ በየቦታው “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” እያለ ያስታውቅ ነበር። እንዲሁም አድማጮቹ ‘ከሁሉ አስቀድመው መንግሥቱን እንዲፈልጉ’ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። ሌሎች ደግሞ የክርስቶስ ምስክሮች በመሆን ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች እያሉ እስከ ምድር ዳር ድረስ በመስበክ ከሁሉም ሕዝቦች የተውጣጡ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ልኳቸዋል። በዛሬው ጊዜ እነዚህን ነገሮች እያደረጉ ፈለጉን ተከትለው በመሄድ ላይ የሚገኙ ወደ አራት ሚልዮን ተኩል የሚጠጉ የይሖዋ ምስክሮች ይገኛሉ። — ማቴዎስ 4:17፤ 6:33፤ 10:7፤ 28:19፤ ሥራ 1:8
16. የይሖዋ ባሕርይ የሆነው ፍቅር በከባድ ፈተና ውስጥ ወድቆ የነበረው እንዴት ነው? ሆኖም ፍቅሩ ለሰው ዘር ምን አከናውኗል?
16 “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት 1 ዮሐንስ 4:8 ይነግረናል። አንድያ ልጁ ወደ ምድር መጥቶ እንዲሞት በላከው ጊዜ ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚታየው የፍቅር ባሕሪው ምን ያህል ከፍተኛ ፈተና ላይ እንደወደቀ መገመት ይቻላል። በምድር ያሉ ሰዎች ከባድ ፈተና ሲያጋጥማቸው ለይሖዋ ያላቸውን ንጹሕ አቋም አጽንተው ለመያዝ አይችሉም የሚለው የሰይጣን ግድድር ሐሰት መሆኑን ኢየሱስ ያረጋገጠ ቢሆንም የሚወደው ልጁ የደረሰበት ሥቃይና ለሰማያዊ አባቱ ያቀረበው ልመና ይሖዋን በጣም አሳዝኖትና አስጨንቆት መሆን አለበት። ለእኛ እንዲሞትልን አምላክ ወደዚህ ምድር ሲልከው ኢየሱስ ለከፈለው ከፍተኛ መሥዋዕትም አድናቂዎች መሆን ይኖርብናል። (ዮሐንስ 3:16) ይህም ቀላልና በፍጥነት የተከናወነ ሞት አልነበረም። አምላክም ሆነ ኢየሱስ የጠየቀባቸውን ከፍተኛ ዋጋ ለመገንዘብ እንችል ዘንድ የመሥዋዕቱን ታላቅነት የሚያሳዩ ምን ሁኔታዎች እንደተከናወኑ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እስቲ እንመልከት።
17–19. ኢየሱስ የተደቀነበትን የመከራ ጊዜ የገለጸው እንዴት ነበር?
17 ኢየሱስ ስለሚደርስበት ነገር ቢያንስ አራት ጊዜ ለሐዋርያቱ ገልጾላቸው ነበር። ነገሩ ሊፈጸም ጥቂት ቀኖች ብቻ ሲቀሩት እንዲህ አላቸው:- “እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፣ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፣ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፣ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፣ ይዘብቱበትማል ይተፉበትማል ይገርፉትማል ይገድሉትማል።” — ማርቆስ 10:33, 34
18 ኢየሱስ አሰቃቂ የሆነው የሮማውያን ግርፋት እንደሚጠብቀው ስለገባው ተጨንቋል። ግርፋቱ በቀጠለ መጠን የሚገረፈው ሰው ጀርባውና እግሩ ደም የቋጠረ ሰንበር እንዲያወጣና እንዲተለተል ተብሎ በጅራፉ ጠፍሮች ላይ የብረት ቁርጥራጮችና የበግ አጥንቶች ይሰካባቸዋል። ይህ ከመሆኑ ከጥቂት ወራት በፊት ኢየሱስ በሉቃስ 12:50 ላይ እንደምናነበው “ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፣ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ?” በማለት የሚደርስበት መከራ ያስከተለበትን ጭንቀት አመልክቷል።
19 ጊዜው እየቀረበ ሲሄድ የጭንቀቱ መጠን ጨመረ። ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ ስለ ጉዳዩ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ።” (ዮሐንስ 12:27) ይሖዋ አንድያ ልጁ ባቀረበለት በዚህ ልመና ምን ያህል ተነክቶ ይሆን! ኢየሱስ ለመሞት ጥቂት ሰዓቶች ሲቀሩት በጣም ተጨንቆ ነበር፤ ስለዚህ በጌቴሰማኒ ለጴጥሮስ፣ ለያቆብና ለዮሐንስ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች” አላቸው። ከዚያ በኋላ ጥቂት ደቂቃዎች ቆይቶ ስለ ጉዳዩ የመጨረሻውን ጸሎት እንዲህ ሲል ለይሖዋ አቀረበ:- “አባት ሆይ! ፈቃድህ ቢሆን ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን። ልቡም በጣም ተጨንቆ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ሆኖ ወደ መሬት ይንጠባጠብ ነበር።” (ማቴዎስ 26:38፤ ሉቃስ 22:42, 44 1980 ትርጉም ) ይህ በሕክምና ሄማቲድሮሲስ በመባል የሚታወቀው ሁኔታ ነው። ይህ በአብዛኛው የማይከሰት ቢሆንም በከፍተኛ የስሜት መረበሽ ወቅት ሊደርስ የሚችል ነገር ነው።
20. ኢየሱስ የደረሰበትን መከራ ችሎ እንዲያልፍ የረዳው ምን ነበር?
20 በጌቴሰማኒ ያሳለፈውን ጊዜ በተመለከተ ዕብራውያን 5:7 እንዲህ ይላል:- “እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፣ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት።” “ከሞት ሊያድነው” የሚችለው እንዳይሞት እስካላደረገው ድረስ ጸሎቱ ተሰማለት ሊባል የሚችለው በምን መንገድ ነው? ሉቃስ 22:43 “ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታው መልአክ ታየው” በማለት መልሱን ይነግረናል። ኢየሱስ የሚደርስበትን መከራ እንዲችለው የሚያበረታውን መልአክ በመላክ አምላክ ለጸሎቱ መልስ ሰጥቷል።
21 (ሀ) ኢየሱስ የደረሰበትን መከራ በድል አድራጊነት እንደተወጣ የሚያሳየው ምንድን ነው የሚደርሱብን ፈተናዎች እየተባባሱ ሲሄዱ ምን ብለን ለመናገር እንድንችል እንፈልግ ይሆናል?
21 ይህም ከተገኘው ውጤት ግልጽ ሆኖ ታይቷል። በውስጡ የነበረው ትግል ካበቃ በኋላ ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ተመልሶ “ተነሡ፣ እንሂድ” አላቸው። (ማርቆስ 14:42) ኢየሱስ ይህን ሲል ‘በመሳም አልፌ ለመሰጠት፣ በጭፍራ ተከብቤ ለመያዝ፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሬ ወደ ፍርድ ለመቅረብ፣ የሞት ፍርድ ለመቀበል፣ እንዲዘበትብኝ፣ እንዲተፋብኝ፣ እንድገረፍና በመከራ እንጨት ላይ እንድቸነከር ልሂድ’ ማለቱ ነበር። ለስድስት ሰዓት ያህል ተሰቅሎ በመቆየት ከፍተኛ ስቃይ ያለበትን ህመም ችሎ እስከ መጨረሻው ጸና። በሚሞትበት ጊዜም በድል አድራጊነት በታላቅ ድምፅ “ተፈጸመ” አለ። (ዮሐንስ 19:30) በአቋሙ በመጽናትና የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ ፍጹም አቋም ያለው መሆኑን አስመስክሯል። ኢየሱስ ይሖዋ ወደ ምድር ሲልከው እንዲሠራ ያዘዘውን ሁሉ ፈጽሟል። በምንሞትበት ጊዜ ወይም አርማጌዶን ሲጀምር ይሖዋ የሰጠንን ትእዛዝ በተመለከተ “ተፈጸመ” ለማለት እንችል ይሆን?
22. የይሖዋ እውቀት ምን ያህል እንደሚሰራጭ የሚያሳየው ምንድን ነው?
22 ያም ሆነ ይህ በፍጥነት እየቀረበ በመምጣት ላይ ባለው ይሖዋ በወሰነው ጊዜ ውስጥ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ” እንደምትሞላ እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን። — ኢሳይያስ 11:9
ታስታውሳለህን?
◻ ማወቅና እውቀት ማግኘት ማለት ምን ማለት ነው?
◻ የይሖዋ ምሕረትና ይቅር ባይነት በቃሉ በኩል የተገለጸልን እንዴት ነው?
◻ አብርሃም ከይሖዋ ጋር ለመነጋገር በንግግር ነፃነቱ የተጠቀመው እንዴት ነበር?
◻ ኢየሱስን በመመልከት የይሖዋን ባሕርያት ማወቅ የምንችለው ለምንድን ነው?