ከጣዖት አምልኮ መጠበቅ የሚገባን ለምንድን ነው?
“ልጆች ሆይ፣ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።” —1 ዮሐንስ 5:21
1. የይሖዋ አምልኮ ከጣዖት አምልኮ የጸዳው ለምንድን ነው?
ይሖዋ ከብረታብረት፣ ከእንጨት ወይም ከድንጋይ የተሠራ የጣዖት አምላክ አይደለም። እርሱ በምድር ላይ በተሠራ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሊኖር አይችልም። ለሰው ዓይን ሊታይ የማይችልና ሁሉን ማድረግ የሚቻለው መንፈሳዊ አካል ስለሆነ እርሱ ይህን ይመስላል ተብሎ ምስል ሊሠራለት አይቻልም። ስለዚህ የይሖዋ ንጹህ አምልኮ ከማንኛውም የጣዖት አምልኮ የጸዳ ሊሆን ይገባዋል።—ዘጸአት 33:20፤ ሥራ 17:24፤ 2 ቆሮንቶስ 3:17
2. ትኩረት ሰጥተን መመርመር የሚገባን የትኞቹን ጥያቄዎች ነው?
2 ስለዚህ አንተም የይሖዋ አምላኪ ከሆንክ ‘የጣዖት አምልኮ ምንድን ነው? ባለፉት ጊዜያት የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች ከጣዖት አምልኮ ሊርቁ የቻሉት እንዴት ነው? ራሳችንን ከጣዖት አምልኮ መጠበቅ የሚገባንስ ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
የጣዖት አምልኮ ምንድን ነው?
3, 4. ለጣዖት አምልኮ ምን ዓይነት ፍቺ መስጠት ይቻላል?
3 ብዙውን ጊዜ የጣዖት አምልኮ የሚከናወነው አንድ ዓይነት የአምልኮ ሥነ ሥርዓትን በመከተል ነው። የጣዖት አምልኮ አንድን ጣዖት ቅዱስ አድርጎ መመልከት፣ ማፍቀር፣ ማምለክ፣ ወይም ማክበር ነው። ታዲያ ጣዖት ምንድን ነው? አንድን ነገር የሚወክል ምስል ወይም አምልኮ የሚቀርብለት ምልክት ነው። አብዛኛውን ጊዜ የጣዖት አምልኮ የሚቀርበው ከሰው የበለጠ ኃይል ላለው ወይም አለው ተብሎ ለሚታሰብ ሕያው ሰው፣ እንስሳ ወይም ድርጅት ነው። ይሁን እንጂ እንደ ተፈጥሮ ኃይሎች ላሉት ሕይወት ለሌላቸው ነገሮችም አምልኮ ሊቀርብ ይችላል።
4 በቅዱሳን ጽሑፎች ጣዖታትን ለማመልከት የሚሠራባቸው የዕብራይስጥ ቃላት አጉልተው የሚገልጹት የማይረባ ነገርን ወይም ወራዳ መሆንን ነው። ከነዚህ ቃላት መካከል የተቀረጹ ምስሎችን (ቃል በቃል ተቀርጸው የተሠሩ)፣ ቀልጠው የተሠሩ ምስሎች፣ አስከፊ ጣዖታት፣ ከንቱ ጣዖት፣ እርኩስ ጣዖት ተብለው ይተረጎማሉ። ኤይዶሎን የተባለው የግሪክኛ ቃልም አብዛኛውን ጊዜ በእንግሊዝኛ “አይደል” ወይም ጣዖት ተብሎ ይተረጎማል።
5. ሁሉም ምስሎች ጣዖት ናቸው ሊባል የማይቻለው ለምንድን ነው?
5 ምስሎች ሁሉ ጣዖቶች አይደሉም። አምላክ ራሱ ለእስራኤላውያን ለቃል ኪዳኑ ታቦት ሁለት የወርቅ ኪሩቦችን እንዲሠሩ እንዲሁም በማደሪያው ድንኳን አሥር መጋረጃዎችና ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ በሚለየው መጋረጃ በውስጠኛው ክፍል ላይ ኪሩቤሎችን በጥልፍ እንዲሠሩ አዝዞ ነበር። (ዘጸአት 25:1, 18፤ 26:1, 31-33) እነዚህን የሰማያዊ ኪሩቤሎች ምስል ለማየት የሚችሉት ተረኞቹ ካህናት ብቻ ነበሩ። (ከዕብራውያን 9:24, 25 ጋር አወዳድር) በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩት የኪሩቤል ምስሎች ቅዱስ ተደርገው የሚታዩና የሚመለኩ እንዳልነበሩ ግልጽ ነው። ምክንያቱም ጻድቅ የሆኑት መላእክት ራሳቸው አምልኮ ለመቀበል አይፈልጉም ነበር።—ቆላስይስ 2:18፤ ራእይ 19:10፤ 22:8, 9
ይሖዋ ለጣዖት አምልኮ ያለው አመለካከት
6. ይሖዋ ለጣዖት አምልኮ ምን ዓይነት አመለካከት አለው?
6 የይሖዋ አገልጋዮች ራሳቸውን ከጣዖታት ሁሉ ይጠብቃሉ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ይቃወማል። አምላክ እስራኤላውያንን ማንኛውንም ዓይነት ምስል ሠርተው እንዳያመልኩ አዝዞአቸው ነበር። በአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ የሚከተሉት ቃላት ይገኛሉ:- “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸውም፣ አታምልካቸውምም በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወድዱኝ፣ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።” —ዘጸአት 20:4-6
7. ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት የጣዖት አምልኮ የሚቃወመው ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት የጣዖት አምልኮ የሚቃወመው ለምንድን ነው? በመሰረቱ ከአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ በሁለተኛው ትእዛዝ ላይ እንደተገለጸው እርሱ ለማንም የማይሰጥ አምልኮ የሚገባው አምላክ ስለሆነ ነው። ከዚህም በላይ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት:- “እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት ] ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።” (ኢሳይያስ 42:8) በአንድ ዘመን እስራኤላውያን በጣዖት አምልኮ በጣም ተጠምደው ስለነበረ ‘ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት እስከ መሰዋት ደርሰው ነበር።’ (መዝሙር 106:36, 37) ጣዖት አምላኪዎች ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ከመካዳቸውም በላይ የይሖዋ ዋነኛ ጠላት የሆነውን ሰይጣንና አጋንንቱን ያገለግላሉ፤ የእነርሱንም ፈቃድ ይፈጽማሉ።[1]
በፈተና ጊዜ ታማኝ ሆኖ መቆም
8. ሲድራቅ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉ ሦስት ዕብራውያን ምን ዓይነት ፈተና አጋጥሟቸው ነበር?
8 በተጨማሪም ለይሖዋ በታማኝነት ለመቆም ያለን ፍላጎት ከጣዖት አምልኮ እንድንጠበቅ ያደርገናል። ለዚህ ማስረጃ የሚሆን በዳንኤል ምዕራፍ 3 ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ያሠራውን ታላቅ የወርቅ ምስል ለማስመረቅ አስቦ በመላው ግዛቱ ያሉት ባለሥልጣኖች እንዲሰበሰቡ አደረገ። የንጉሡ ትእዛዝ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ እና አብደናጎ የሚባሉ በባቢሎን አውራጆች ላይ የተሾሙ ሦስት ዕብራውያንንም ይመለከት ነበር። በስፍራው የተገኙ ሁሉ አንድ ዓይነት የሙዚቃ ድምፅ ሲሰሙ ለምስሉ ወድቀው መስገድ ነበረባቸው። ይህም በእርግጥ የባቢሎን አምላክ የነበረው ሰይጣን እነዚህ ሦስት ዕብራውያን የባቢሎንን ግዛት በሚወክለው ምስል ፊት እንዲሰግዱ ያደረገው ሙከራ ነበር። አንተ ራስህ በዚያ ቦታ እንደነበርክ አድርገህ ገምት።
9, 10. (ሀ) ሦስቱ ዕብራውያን ምን ዓይነት አቋም ያዙ? ለዚህስ አቋማቸው ምን ዋጋ አገኙ? (ለ) የይሖዋ ምስክሮች ከእነዚህ ሦስት ዕብራውያን ምን ዓይነት ማበረታቻ ሊያገኙ ይችላሉ?
9 እነሆ ሦስቱ ዕብራውያን ቆመዋል! አምላክ ምስል ስለ መሥራትና ጣዖትን ስለ ማምለክ ወይም ለተቀረጹ ምስሎች ስለመስገድ የሰጠው ሕግ ትዝ ይላቸዋል። ናቡከደነፆር ሁለት ምርጫ ሰጥቶአቸዋል። መስገድ ወይም መሞት። እነርሱ ግን ለይሖዋ ታማኝ ሆነው በመቆም እንደሚከተለው አሉት:- “የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይቸላል፤ ከእጅህም ያድነናል፣ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፣ ንጉሥ ሆይ እርሱ ባያድነን፣ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።”—ዳንኤል 3:16–18
10 እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በጣም ወደሚነደው የእቶን እሳት ተወረወሩ። ይሁን እንጂ ናቡከደነፆር በእቶኑ እሳት ውስጥ አራት ግለሰቦች ሲመላለሱ በማየቱ ተደንቆ ሦስቱ ዕብራውያን እንዲወጡ ጠራቸው። ሲወጡ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም ነበር። በዚህ ጊዜ ንጉሡ እንደሚከተው አለ:- “መልአኩን የላከ፣ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፣ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ። . . . እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና . . .።” (ዳንኤል 3:28, 29) እነዚህ ሦስት ዕብራውያን ያሳዩት የፍጹም አቋም ጠባቂነት አርአያ በዚህ ዘመን የሚኖሩት ታማኝ የይሖዋ ምስክሮችም ከዓለም ገለልተኛ ሆነው እንዲኖሩና ከጣዖት አምልኮ እንዲርቁ ያበረታታቸዋል።—ዮሐንስ 17:16
ጣዖታት በፍርድ ቤት ተረቱ
11, 12. (ሀ) ኢሳይያስ ይሖዋንና የጣዖት አማልክትን የሚመለከት ምን መዝገብ አስፍሮአል? (ለ) የአሕዛብ አማልክት ከይሖዋ ግድድር በቀረበባቸው ጊዜ እንዴት ሆነው ተገኙ?
11 ከጣዖት አምልኮ ራሳችንን የምንጠብቅበት ሌላው ምክንያት ጣዖታትን ቅዱስ አድርጎ ማምለክ ከንቱ ስለሆነ ነው። ሰው ሰራሽ የሆኑ አንዳንድ ጣዖታት ብዙውን ጊዜ አፍ፣ ዓይንና ጆሮ ስለሚደረግላቸው ሕይወት ያላቸው መስለው የሚታዩ ቢሆኑም መናገር፣ ማየት፣ መስማት ወይም ለአምላኪዎቻቸው አንዳች ነገር ማድረግ አይችሉም። (መዝሙር 135:15-18) ይህም ነቢዩ ኢሳይያስ ከዘአበ በስምንተኛው መቶ ዘመን በይሖዋ እና በጣዖት አማልክት መካከል ስለተደረገ የፍርድ ቤት ሙግት በኢሳይያስ 43:8–28 በተጻፈው ላይ ተገልጾአል። በዚህ ሙግት ላይ በአንድ ወገን የአምላክ ሕዝቦች፣ እስራኤላውያን፤ በሌላ ወገን ደግሞ ዓለማዊ ብሔራት እንደተሰለፉ ተገልጿል። ይሖዋ የብሔራቱን የሐሰት አማልክት “የመጀመሪያውን ነገር” ማለትም ትክክለኛ ትንቢት እንዲናገሩ ፈተና አቀረበላቸው። አንዳቸውም ሊናገሩ አልቻሉም። ከዚያም ወደ ሕዝቦቹ ዞር በማለት ይሖዋ:- “እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፣ . . . እኔም አምላክ ነኝ” አለ። አሕዛብ ወይም ብሔራት አምላኮቻቸው ከይሖዋ በፊት እንደነበሩ ወይም ትንቢት ሊናገሩ እንደሚችሉ ለማረጋገጥ አልቻሉም። ይሖዋ ግን ባቢሎን እንደምትጠፋና ሕዝቦቹ ከምርኮ ነፃ እንደሚወጡ ትንቢት ተናገረ።
12 በተጨማሪም ከምርኮ የሚመለሱት የአምላክ አገልጋዮች በኢሳይያስ 44:1–8 ላይ እንደተገለጸው “እኛ የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት ] ነን” ብለው የሚናገሩበት ጊዜ መምጣት ነበረበት። እርሱ ራሱ:- “እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፣ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም” ብሏል። ጣዖት ከሆኑ አማልክት ይህንን ሊያስተባብል የሚችል አልተገኘም። ይሖዋ አሁንም በድጋሚ “እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ” ካለ በኋላ “ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? አምባ የለም፤ ማንንም አላውቅም” ብሏል።”
13. የጣዖት አምልኮ ያንን አምልኮ ስለሚፈጽመው ሰው ምን የሚገልጽልን ነገር አለ?
13 ከጣዖት አምልኮ ራሳችንን መጠበቅ አለብን፤ ምክንያቱም በጣዖት አምልኮ መካፈል ጥበብ የጎደለን መሆናችንን ስለሚያሳይ ነው። አንድ ጣዖት አምላኪ አንዱን የዛፍ ክፍል ይመርጥና አምላክ ሠርቶ ያመልካል፤ የዛፉን ሌላ ክፍል ደግሞ አንድዶ ምግቡን ያበስልበታል። (ኢሳይያስ 44:9-17) እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! አንድ የጣዖታት ሠሪ እና አምላኪ የሆነ ሰው ጣዖታቱ አምላክ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊያቀርብ ስለማይችል ያፍራል። የይሖዋ አምላክነት ግን በምንም መንገድ የሚያጠያይቅ አይደለም፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ከባቢሎን እንደሚወጡ አስቀድሞ ከመናገሩም ሌላ ትንቢቱ እንዲፈጸም አድርጓል። ኢየሩሳሌም እንደገና የሰው መኖሪያ ሆነች፣ የይሁዳ ከተሞች እንደገና ተቆረቆሩ፣ የባቢሎን “ቀላዮች” ጥልቅ ውኃ ማለትም የባቢሎን መከላከያ የነበረው የኤፍራጥስ ወንዝ ተነነ። (ኢሳይያስ 44:18-27) በተጨማሪም አምላክ አስቀድሞ እንደተናገረው ፋርሳዊው ቂሮስ ባቢሎንን ወረራት።—ኢሳይያስ 44:28 እስከ 45:6
14. በጽንፈ ዓለሙ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለዘላለም የሚረጋገጠው ምን ነገር ይሆናል?
14 ጣዖት የሆኑት አማልክት ስለ አምላክነት በተነሳው ክርክር ተሸንፈዋል። በጥንትዋ ባቢሎን የደረሰው ነገር አምሳያዋ በሆነችው በዘመናዊትዋ ባቢሎን ማለትም የሐሰት ግዛት በሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን ላይ እንደሚደርስ የተረጋገጠ ነው። ታላቂቱ ባቢሎንም ሆነ አምላኮችዋ ከነ ሃይማኖታዊ ግሳንግሳቸው እና ጣዖቶቻቸው ለዘላለም ይጠፋሉ። (ራእይ 17:12 እስከ 18:8) በዚያ ጊዜ ይሖዋ ብቻ ሕያው እና እውነተኛ አምላክ እንደሆነና ትንቢታዊ ቃሉን እንደሚፈጽም በጽንፈ ዓለሙ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለዘለቄታው ይረጋገጣል።[9]
ለአጋንንት መሰዋት
15. የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካልና መንፈስ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሕዝቦችና ስለጣዖት አምልኮ ምን አመልክተዋል?
15 በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች በአምላክ መንፈስና በአምላክ ድርጅት ስለሚመሩ ራሳቸውን ከጣዖታት ይጠብቃሉ። የመጀመሪያው መቶ ዘመን የይሖዋ አገልጋዮች የአስተዳደር አካል ለክርስቲያኖች የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቶ ነበር:- “ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።”—ሥራ 15:28, 29
16. ጳውሎስ ለጣዖታት ስለተሰዉ ነገሮች የተናገረውን በራስህ አነጋገር እንዴት ብለህ ታስረዳለህ?
16 ራሳችንን ከጣዖት አምልኮ የምንጠብቅበት ሌላው ምክንያት ከአጋንንት ለመራቅ ስለምንፈልግ ነው። ሐዋሪያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ ጌታ እራት ሲናገር የሚከተለውን ጽፏል:- “ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። . . . የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፣ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና። በሥጋ የሆነውን እስራኤል ተመልከቱ ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ ምናምን ነው ትላላችሁን? ወይስ ጣዖት ምናምን እንዲሆን እላለሁን? አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሰዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኀበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? ”—1 ቆሮንቶስ 10:14-22
17. በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ አንድ ክርስቲያን ለጣዖታት የተሰዋ ሥጋ ሊበላ የሚችለው እንዴት ባለ ሁኔታ ነበር? ለምንስ?
17 የአንድ ከብት ሥጋ ግማሹ ለጣዖት ይሰዋል፤ ግማሹ ለካህናቱ ይሰጣል ግማሹ ደግሞ የጣዖቱ አምላኪ ግብዣ እንዲያደርግበት ይሰጠው ነበር። ከሥጋው ከፊሉ ደግሞ በሥጋ ገበያ ቀርቦ ይሸጥ ነበር። አንድ ክርስቲያን በአምልኮ ሥርዓቱ ላይ ባይገኝም እንኳን ሥጋ ለመብላት ብሎ ወደ ጣዖት ቤተ መቅደስ ቢሄድ ሌሎች ወደ ሐሰት አምልኮ እንዲሳቡ በማድረግ ሊያደናቅፋቸው ስለሚችል ይህ ትክክል አይሆንም ነበር። (1 ቆሮንቶስ 8:1-13፤ ራእይ 2:12, 14, 18, 20) አንድ ከብት ለጣዖት የተሰዋ መሆኑ ሥጋውን ሊለውጠው ስለማይችል አንድ ክርስቲያን ከገበያ ሥጋ ሊገዛ ይችል ነበር። በተጨማሪም ሰው እቤት ተጋብዞ የሚቀርብለትን ሥጋ ከየት የመጣ ነው ብሎ መጠየቅ አያስፈልገውም ነበር። ይሁን እንጂ ለመስዋዕት ቀርቦ የነበረ ሥጋ እንደሆነ ቢነገረው አይበላውም። ምክንያቱም ሌሎችን ሊያደናቅፍ ይችላል። —1 ቆሮንቶስ 10:25-29
18. ለጣዖት የተሠዋን ነገር የሚበሉ ሰዎች ከአጋንንት ጋር ኅብረት ሊኖራቸው የሚችለው እንዴት ነበር?
18 የመስዋዕቱ ሥነ ሥርዓት ካለቀ በኋላ መስዋዕት የቀረበለት አምላክ በሥጋው ውስጥ እንደሚሰርጽና በጣዖት አምላኪዎቹ ግብዣ ላይ ሥጋውን በሚበሉት ሰዎች ውስጥ ገብቶ እንደሚያድር ይታመን ነበር። በአንድ ላይ የሚበሉት ሰዎች በመካከላቸው አንድ ዓይነት የኅብረት ሰንሰለት እንደሚፈጥሩ ሁሉ መስዋዕት ከቀረበው ሥጋ የሚካፈሉ ሁሉ በመሰዊያው ከመካፈላቸውም በተጨማሪ በጣዖቱ ከተወከለው አጋንንት አምላክ ጋር ኅብረት እና አንድነት ይኖራቸዋል። አጋንንት እንዲህ ባለ የጣዖት አምልኮ አማካኝነት ሰዎች እርሱ ብቻ እውነተኛ የሆነውን አምላክ እንዳያመልኩ ያደርጉ ነበር። (ኤርምያስ 10:1–15) የይሖዋ ሕዝቦች ለጣዖት ከተሠዉ ነገሮች ራሳቸውን ይጠብቁ የነበሩ መሆናቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ዛሬም ለአምላክ ታማኝ ሆነን መቆማችን በመንፈስ ቅዱስ እና በድርጅቱ የሚሰጠውን መመሪያ መቀበላችንንና ከማንኛውም አጋንንታዊ ትስስር ተካፋዮች ላለመሆን መወሰናችን ከጣዖት አምልኮ እንድንጠበቅ የሚገፋፉን ጠንካራ ምክንያቶች ናቸው።[2]
ራሣችንን መጠበቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
19. በጥንቷ ኤፌሶን ምን ዓይነት የጣዖት አምልኮ ነበር?
19 ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከጣዖት አምልኮ ለመጠበቅ ይተጋሉ ምክንያቱም የጣዖት አምልኮ ብዙ ዓይነት መልኮች አሉት። እንዲሁም አንድ ጊዜ ብቻ የተፈጸመ የጣዖት አምልኮ ድርጊት እንኳን የእምነት አቋማቸውን ሊያበላሽባቸው ይችላል። ሐዋሪያው ዮሐንስ ለእምነት ባልደረቦቹ:- “ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ” ብሏል። (1 ዮሐንስ 5:21) ይህ ምክር አስፈላጊ ነበር፤ ምክንያቱም በአካባቢያቸው ብዙ ዓይነት የጣዖት አምልኮ ነበር። ዮሐንስ ደብዳቤውን የጻፈው በአስማታዊ ሥራዎችና በሐሰት አማልክት በተጥለቀለቀው የኤፌሶን ከተማ ሆኖ ነው። የኤፌሶን ከተማ በዓለም ካሉት ሰባት አስደናቂ ነገሮች አንዱ የሆነው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ የሚገኝበት ከተማ ነበር። ይህ ከተማ የወንጀለኞች መጠለያና የሥነ ምግባር ርኩሰት ሥነ ሥርዓቶች የሚከናወኑበት ማዕከል ነበር። ሂራቅሌጢስ የተባለው የኤፌሶን ፈላስፋ ወደዚህ ቤተ መቅደስ መሰዊያ የሚወስደውን የጨለማ መተላለፊያ መንገድ ከብልግና ጨለማ ጋር አመሳስሎታል። በተጨማሪም የቤተ መቅደሱ ስነ ምግባር ከእንስሳት ምግባር የከፋ እንደነበረ ተናግሯል። ስለዚህ የኤፌሶን ክርስቲያኖች በአጋንንት አምልኮ፣ በሥነ ምግባር ርኩሰትና በጣዖት አምልኮ ላይ የጸና አቋም መያዝ ነበረባቸው። [5]
20. ማንኛውንም ጥቃቅን የጣዖት አምልኮም እንኳ ማስወገድ አስፈላጊ የሚሆነው ለምን ነበር?
20 ክርስቲያኖች ማንኛውንም ዓይነት ጥቃቅን የጣዖት አምልኮ እንኳን ለማስወገድ ጠንካራ አቋም መውሰድ ያስፈልጋቸዋል፤ ምክንያቱም ለዲያብሎስ የሚቀርብ አንድ የአምልኮ ስግደት ብቻ እንኳን ሰዎች ፈተና ቢደርስባቸው ታማኝ ሆነው ሊቆሙ አይችሉም ለሚለው ግድድር ድጋፍ የሚሰጥ ሊሆንለት ይችላል። (ኢዮብ 1:8-12) ሰይጣን ለኢየሱስ “የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም” ባሳየው ጊዜ:- “ወድቀህ [አንድ ጊዜ አዓት] ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” ብሎት ነበር። ክርስቶስ ይህን ለማድረግ እምቢ በማለት የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ደግፏል፤ ዲያብሎስንም ሐሰተኛ አድርጎታል።—ማቴዎስ 4:8-11፤ ምሳሌ 27:11
21. ታማኝ ክርስቲያኖች የሮማን ንጉሠ ነገሥት በተመለከተ ምን ለማድረግ እምቢተኛ ሆነዋል?
21 የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮቹም ቢሆኑ በግድድሩ ውስጥ የሰይጣን ደጋፊ የሚያደርጋቸውን የአንድ ጊዜ ስግደት እንኳ አላደረጉም። ለመንግሥታዊ የበላይ ባለሥልጣኖች ትክክለኛ አመለካከት ቢኖራቸውም እንኳ በሕይወታቸው ቆርጠው ለሮማ ንጉሠ ነገሥት ክብር ዕጣን ለማጨስ እምቢ አሉ። (ሮሜ 13:1-7) ዳንኤል ፒ ማኒክስ ስለዚህ ጉዳይ የሚከተለውን ጽፈዋል:- “እሳት የሚነድበት መሰዊያ በትርዒት መድረክ ውስጥ ለክርስቲያኖቹ በሚያመች አካባቢ ሁሉ ቢደረግም አቋማቸውን ያላሉትና በዚህ ድርጊት የተካፈሉት በጣም ጥቂት ክርስቲያኖች ብቻ ነበሩ። አንድ እስረኛ እንዲያደርግ የሚፈለገው ጥቂት ዕጣን በእጁ ቆንጥሮ በእሳቱ ላይ እንዲበትን ብቻ ነበረ። ይህን ካደረገ መስዋዕት ስለማቅረቡ የምስክር ወረቀት ይሰጠውና ነፃ ይለቀቅ ነበር። በተጨማሪም ንጉሠ ነገሥቱን ማምለኩ እንዳልሆነና የንጉሠ ነገሥቱን መለኮታዊነት መቀበሉንና የሮማ ብሔር መሪ መሆኑን ማመኑን ለማመልከት ብቻ እንደሆነ ተደርጐ በጥንቃቄ ይገለጽለት ነበር። ያም ቢሆን በዚህ ነፃ የመውጣት አጋጣሚ የተጠቀመ ክርስቲያን አልነበረም ለማለት ይቻላል።” (ለመሞት የተዘጋጁት፣ ገጽ 137) አንተስ ይህን ዓይነት ፈተና ቢደርስብህ ማንኛውንም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ትቃወማለ ህን?
ራስህን ከጣዖት አምልኮ ትጠብቃለህን?
22, 23. ከጣዖት አምልኮ ራስህን መጠበቅ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?
22 ክርስቲያኖች ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ግልጽ ነው። ይሖዋ እርሱ ብቻውን እንዲመለክ ይፈልጋል። ሦስቱ ታማኝ ዕብራውያን የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ያሠራውን ታላቅ ምስል ለማምለክ እምቢ በማለታቸው ጥሩ ምሳሌ ትተውልናል። ነቢዩ ኢሳይያስ በመዘገበው ጽንፈ ዓለማዊ ፍርድ ቤት ላይ እውነተኛና ሕያው አምላክ ይሖዋ ብቻ ሆኖ ቀርቧል። የጥንት ክርስቲያን ምስክሮቹም ለጣዖት ከተሰዋ ራሳቸውን መጠበቅ ነበረባቸው። ከእነኚህ ታማኝ ክርስቲያኖች መካከል ብዙዎቹ ይሖዋን እንደካዱ የሚያሳይ ማንኛውንም ዓይነት አምልኮ አንድ ጊዜ ብቻ እንኳ እንዲፈጽሙ የተደረገባቸውን ተጽዕኖ ተቋቁመዋል።
23 ታዲያ አንተስ ከጣዖት አምልኮ ራስህን ትጠብቃለህን? ለይሖዋ ለእርሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ትሰጠዋለህን? የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት በመደገፍ እርሱ ብቻ እውነተኛና ሕያው አምላክ መሆኑን ከፍ አድርገህ ታሳያለህን? አቋምህ እንደዚያ ከሆነ በዚህ ከጣዖት አምልኮ ድርጊቶች በመራቁ አቋምህ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔህ መሆን ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ እንድትጠበቅ የሚረዱህ ምን ተጨማሪ ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥቦች ይኖራሉ?
ምን ሐሳብ ትሰጣለህ?
◻ የጣዖት አምልኮ ምንድን ነው?
◻ ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት የጣዖት አምልኮ የሚቃወመው ለምንድን ነው?
◻ ሦስቱ ዕብራውያን የጣዖት አምልኮን በተመለከተ ምን አቋም ወስደው ነበር?
◻ ለጣዖት የተሰዉ ነገሮችን የሚበሉ ሰዎች ከአጋንንት ጋር ኅብረት ሊኖራቸው የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ራሳችንን ከጣዖት አምልኮ መጠበቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሦስቱ ዕብራውያን ሕይወታቸው በአደጋ ላይ ቢወድቅም በጣዖት አምልኮ ለመሳተፍ እምቢተኞች ሆነዋል