ምዕራፍ ስድስት
ይሖዋ—‘ጻድቅ አምላክና አዳኝ’
1, 2. በኢሳይያስ ምዕራፍ 45 ውስጥ ምን ዋስትናዎች ተሰጥተዋል? የምንመረምራቸው ጥያቄዎችስ የትኞቹ ናቸው?
ይሖዋ የሚሰጠው ተስፋ አስተማማኝ ነው። ራእይ የመግለጥ ችሎታ ያለው ከመሆኑም በላይ ሁሉን የፈጠረ አምላክ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ጻድቅ አምላክ እንደሆነና የየትኛውንም ብሔር ሕዝብ ሊያድን እንደሚችል በተደጋጋሚ ጊዜያት አሳይቷል። በኢሳይያስ ምዕራፍ 45 ውስጥ ከተገለጹት አስደሳች ዋስትናዎች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው።
2 በተጨማሪም ኢሳይያስ ምዕራፍ 45 ይሖዋ ትንቢት የመናገር ችሎታ ያለው መሆኑን የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ይዟል። የአምላክ መንፈስ ኢሳይያስ በሩቅ ያሉ አገሮችን በአንክሮ እንዲመለከትና በመጪዎቹ መቶ ዘመናት የሚከናወኑትን ሁኔታዎች ጠለቅ ብሎ እንዲመረምር አስችሎታል። ከዚህም ሌላ እውነተኛ ትንቢት የመናገር ችሎታ ያለው አምላክ ማለትም ይሖዋ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ማንም በትክክል ሊተነብየው የማይችለውን ክስተት እንዲዘግብ አነሳስቶታል። ይህ ክስተት ምንድን ነው? በኢሳይያስ ዘመን በነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ላይ ምን ሁኔታ ያስከትላል? በአሁኑ ዘመን ለምንኖረው ሰዎችስ ምን ትርጉም አለው? እስቲ ነቢዩ የተናገራቸውን ቃላት እንመርምር።
ይሖዋ በባቢሎን ላይ የተናገረው ቃል
3. ኢሳይያስ 45:1-3 ቂሮስ የሚቀዳጀውን ድል ሥዕላዊ በሆነ መንገድ የሚገልጸው እንዴት ነው?
3 “እግዚአብሔር ለቀባሁት፣ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ወገብ እፈታ ዘንድ፣ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፣ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል:- በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም ትክክል አደርጋለሁ፣ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፤ . . . በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ።”—ኢሳይያስ 45:1-3
4. (ሀ) ይሖዋ ቂሮስን ‘የቀባሁት’ ሲል የጠራው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ቂሮስ ድል እንዲቀዳጅ የሚያደርገው እንዴት ነው?
4 ቂሮስ ኢሳይያስ በኖረበት ዘመን ገና ያልተወለደ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ በትንቢት ልክ በሕይወት እንዳለ አድርጎ አነጋግሮታል። (ሮሜ 4:17) ይሖዋ ቂሮስን አንድ የተለየ ተልእኮ እንዲፈጽም አስቀድሞ የሾመው በመሆኑ ቂሮስ በአምላክ ‘ተቀብቷል’ ሊባል ይችላል። በአምላክ አመራር እየታገዘ ነገሥታት ምንም መከላከል እንዳይችሉ አቅማቸውን በማሽመድመድ ሕዝባቸውን በቁጥጥሩ ሥር ያደርጋል። በባቢሎን ላይ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ ደግሞ ይሖዋ የከተማይቱ በሮች ሳይዘጉ እንዲቀሩ ስለሚያደርግ በሮቹ ልክ እንደ ተሰባበሩ መዝጊያዎች ዋጋቢስ ይሆናሉ። ይሖዋ በቂሮስ ፊት በመሄድ እንቅፋቱን ሁሉ ያስወግድለታል። በመጨረሻም የቂሮስ ወታደሮች ከተማይቱን ድል በማድረግ ጨለማ በሆኑ ግምጃ ቤቶች ውስጥ ‘በስውር የተደበቀውን ሀብት’ ይወስዳሉ። ኢሳይያስ ይህ ሁኔታ እንደሚፈጸም አስቀድሞ ተናግሯል። ታዲያ እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋልን?
5, 6. በባቢሎን ላይ የሚደርሰውን ውድቀት አስመልክቶ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው መቼና እንዴት ነው?
5 ኢሳይያስ ይህን ትንቢት ከመዘገበ ከ200 ዓመታት ገደማ በኋላ በ539 ከዘአበ ቂሮስ በባቢሎን ከተማ ላይ ጦሩን አዘመተ። (ኤርምያስ 51:11, 12) ይሁንና ባቢሎናውያን ከተማቸው በማንም ልትደፈር እንደማትችል አድርገው ያስቡ ስለነበር ሐሳባቸውን ጥለው ተቀምጠዋል። ከተማይቱ በጠላት ኃይል እንዳትደፈር ሲባል ከኤፍራጥስ ወንዝ በተጠለፈ ውኃ ዙሪያዋን ከመከበቧም በላይ በጣም ግዙፍ በሆኑ ግንቦች ታጥራለች። ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት ባቢሎንን በድንገት ወርሮ መቆጣጠር የቻለ አንድም የጠላት ኃይል የለም። እንዲያውም በወቅቱ ባቢሎንን በመግዛት ላይ የነበረው ብልጣሶር ምንም እንደማይደርስበት በመተማመን ከቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች ጋር ድል ያለ ድግስ ላይ ነበር። (ዳንኤል 5:1) ያን ቀን ሌሊት ማለትም ጥቅምት 5/6 ሌሊት ቂሮስ እጅግ የረቀቀ ወታደራዊ ስልት ተጠቀመ።
6 የቂሮስ መሐንዲሶች ከባቢሎን ከተማ ውጪ የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር ወደ ከተማይቱ እንዳይፈስ አደረጉት። ብዙም ሳይቆይ ወደ ከተማይቱ ውስጥም ሆነ በከተማይቱ ዙሪያ ይፈስ የነበረው ውኃ በእጅጉ በመቀነሱ የቂሮስ ወታደሮች በወንዙ ውስጥ በመሻገር ወደ ከተማይቱ እምብርት ዘለቁ። (ኢሳይያስ 44:27፤ ኤርምያስ 50:38) የሚገርመው ነገር ኢሳይያስ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት በወንዙ ዳርቻ ያሉት በሮች አልተዘጉም ነበር። የቂሮስ ሠራዊት ባቢሎንን በአንድ ጊዜ በመውረር ቤተ መንግሥቱን ከመቆጣጠራቸውም በላይ ንጉሥ ብልጣሶርን ገደሉት። (ዳንኤል 5:30) በአንድ ሌሊት ሁሉ ነገር አበቃ። ባቢሎን ወደቀች፤ ትንቢቱም አንድም ሳይቀር ተፈጸመ።
7. ኢሳይያስ ቂሮስን አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት በአስደናቂ ሁኔታ መፈጸሙ የክርስቲያኖችን እምነት የሚያጠነክረው እንዴት ነው?
7 ይህ ትንቢት አንድም ሳይቀር በትክክል መፈጸሙ በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖችን እምነት ያጠነክራል። ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ሙሉ በሙሉ እንዲተማመኑ ያደርጋቸዋል። (2 ጴጥሮስ 1:20, 21) የይሖዋ አገልጋዮች በ539 ከዘአበ በባቢሎን ላይ የደረሰው ውድቀት በ1919 ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ላይም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደተፈጸመ ያውቃሉ። ይሁንና ይህች ዘመናዊ የሃይማኖት ድርጅት የምትጠፋበትን እንዲሁም አስቀድሞ በተነገረው መሠረት በሰይጣን የሚመራው የፖለቲካ ሥርዓት የሚወገድበትን፣ ሰይጣን ወደ ጥልቁ የሚጣልበትንና ይሖዋ አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር የሚያመጣበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ራእይ 18:2, 21፤ 19:19-21፤ 20:1-3, 12, 13፤ 21:1-4) ይሖዋ የተናገራቸው ትንቢቶች የማይጨበጡ ከንቱ ተስፋዎች ሳይሆኑ ወደፊት በእርግጠኝነት የሚፈጸሙ ሁኔታዎችን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ መግለጫዎች እንደሆኑ ይገነዘባሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ኢሳይያስ የባቢሎንን ውድቀት አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት አንድ በአንድ መፈጸሙን መለስ ብለው ሲያስቡ ጠንካራ እምነት ያድርባቸዋል። ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚጠብቅ ያውቃሉ።
ይሖዋ ቂሮስን የመረጠበት ምክንያት
8. ይሖዋ፣ ቂሮስ በባቢሎን ላይ ድል እንዲቀዳጅ ያደረገበት አንደኛው ምክንያት ምንድን ነው?
8 ይሖዋ ባቢሎንን ድል የሚያደርገው ማን እንደሚሆንና ከተማይቱን እንዴት እንደሚቆጣጠር ካመለከተ በኋላ ድሉን ለቂሮስ የሚሰጥበት አንደኛው ምክንያት ምን እንደሆነ ገልጿል። ትንቢታዊ በሆነ መንገድ ለቂሮስ ሲናገር “በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ” ነው ብሎታል። (ኢሳይያስ 45:3) በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተጠቀሰው አራተኛ የዓለም ኃያል መንግሥት ገዥ ታላቁን ድል የሚያቀዳጀው የእሱ የበላይ የሆነው የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ይሖዋ መሆኑን መገንዘቡ የተገባ ነው። ቂሮስ የጠራው ወይም ልዩ ተልእኮ የሰጠው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ መሆኑን አምኖ መቀበል ያስፈልገው ነበር። በእርግጥም ደግሞ ቂሮስ ያን ታላቅ ድል ያቀዳጀው ይሖዋ መሆኑን አምኖ እንደተቀበለ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ያረጋግጥልናል።—ዕዝራ 1:2, 3
9. ይሖዋ ቂሮስን በባቢሎን ላይ ያስነሳበት ሁለተኛው ምክንያት ምንድን ነው?
9 ይሖዋ፣ ቂሮስ በባቢሎን ላይ ድል እንዲቀዳጅ የሚያደርግበትን ሁለተኛ ምክንያት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፣ ስለ መረጥሁት ስለ እስራኤል፣ አንተ ባታውቀኝ እንኳ፣ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ የክብርም ስም ሰጥቼሃለሁ።” (ኢሳይያስ 45:4 አ.መ.ት ) ቂሮስ በባቢሎን ላይ የተቀዳጀው ድል ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው። አንድ የዓለም ኃያል መንግሥት ወድቆ በእሱ ቦታ ሌላ መተካቱን ያመላከተ ከመሆኑም ሌላ ለመጪዎቹ ትውልዶች የማይረሳ ታሪክ ጥሎ አልፏል። ሆኖም ሁኔታውን በከፍተኛ ትኩረት ይከታተሉ የነበሩት በአካባቢው ያሉ ብሔራት ይህ ሁሉ የተፈጸመው የያዕቆብ ዘሮች ለሆኑትና በባቢሎን በግዞት ለነበሩት በጥቂት ሺህዎች የሚቆጠሩ “ተራ” አይሁዳውያን መሆኑን ሲረዱ በጣም ሳይገረሙ አልቀሩም። ይሁን እንጂ ከጥንቱ የእስራኤል ብሔር የተረፉት እነዚህ ሰዎች በይሖዋ ዓይን እንደ ተራ የሚታዩ አልነበሩም። በምድር ላይ ካሉ ብሔራት ሁሉ ‘የመረጣቸው ባሪያዎቹ’ ነበሩ። ምንም እንኳ ቂሮስ ቀደም ሲል ይሖዋን የማያውቅ ሰው የነበረ ቢሆንም ይሖዋ ከተማይቱን ድል አድርጎ ምርኮኞቹን እንዲያስለቅቅ ቀብቶታል። አምላክ የመረጣቸው ሕዝቦቹ ለዘላለም በባዕድ አገር እየማቀቁ እንዲኖሩ ፍላጎት አልነበረውም።
10. ይሖዋ የባቢሎን ኃያል መንግሥት እንዲንኮታኮት ለማድረግ ቂሮስን መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመበት ከሁሉ የላቀው ምክንያት ምንድን ነው?
10 ይሖዋ የባቢሎንን መንግሥት ለመገልበጥ ቂሮስን መሣሪያ አድርጎ መጠቀም የፈለገበትን ሦስተኛና ከሁሉ የላቀ ምክንያት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ፣ አንተ ግን አላወቅኸኝም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔም ሌላ ማንም የለም።” (ኢሳይያስ 45:5, 6) አዎን፣ የባቢሎን ኃያል መንግሥት መውደቁ መመለክ ያለበት እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ መሆኑን የሚያረጋግጥ ጥሩ ማስረጃ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ነፃ መውጣታቸው ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ባሉ በርካታ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ መሆኑን አምነው እንዲቀበሉ ያደርጋል።—ሚልክያስ 1:11
11. ይሖዋ በባቢሎን ላይ ለማምጣት ያሰበውን ጥፋት ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል ያለው መሆኑን ግልጽ በሆነ መንገድ ያስረዳው እንዴት ነው?
11 ኢሳይያስ ይህን ትንቢት የመዘገበው ታሪኩ ከመፈጸሙ ከ200 ዓመት ገደማ በፊት መሆኑን አስታውስ። አንዳንዶች ይህን ትንቢት ሲሰሙ ‘ይሖዋ በእርግጥ ይህን ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል አለው?’ የሚል ጥርጣሬ አድሮባቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህን መፈጸም የሚችል መሆኑን ታሪክ በሚገባ ያረጋግጣል። ይሖዋ የተናገረውን የመፈጸም ችሎታ ያለው አምላክ መሆኑን የሚያሳይ አሳማኝ ነጥብ ጠቅሷል:- “ብርሃንን ሠራሁ፣ ጨለማውንም ፈጠርሁ፤ ደኅንነትን እሠራለሁ፣ [ጥፋትን አመጣለሁ፣ (የ1980 እትም ) ] እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።” (ኢሳይያስ 45:7) ከብርሃን አንስቶ እስከ ጨለማ ድረስ ያለው ማንኛውም የፍጥረት ሥራም ሆነ ደህንነትንና ጥፋትን ጨምሮ በታሪክ ዘመናት ሲፈራረቁ የኖሩት ነገሮች ሁሉ በይሖዋ ቁጥጥር ሥር ያሉ ናቸው። የቀንን ብርሃንና የሌሊትን ጨለማ እንደፈጠረ ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥፋት በማምጣት ለእስራኤል ሰላምን ያጎናጽፋል። ይሖዋ አጽናፈ ዓለምን መፍጠርም ሆነ ትንቢቶቹን ዳር ማድረስ የሚያስችል ኃይል አለው። ይህ በዘመናችን የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትጋት የሚመረምሩትን ክርስቲያኖች በእጅጉ የሚያጽናና ነው።
12. (ሀ) ይሖዋ ምሳሌያዊዎቹ ሰማያትና ምድር ምን እንዲያስገኙ ያደርጋል? (ለ) በኢሳይያስ 45:8 ላይ ያሉት ቃላት ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ምን አጽናኝ ተስፋ ይዘዋል?
12 ይሖዋ የተለመዱ የተፈጥሮ ዑደቶችን እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም በግዞት ያሉት አይሁዳውያን የሚጠብቃቸውን ነገር እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እናንተ ሰማያት ከላይ አንጠባጥቡ ደመናትም ጽድቅን ያዝንቡ፤ ምድርም ትከፈት መድኃኒትንም ታብቅል፣ ጽድቅም በአንድነት ይብቀል፤ እኔ እግዚአብሔር ፈጥሬዋለሁ።” (ኢሳይያስ 45:8) ግዑዞቹ ሰማያት ለሕይወት አስፈላጊ የሆነውን ዝናብ እንደሚሰጡ ሁሉ ይሖዋ ምሳሌያዊዎቹ ሰማያት ለሕዝቡ የጽድቅ መመሪያዎችንና በረከቶችን እንዲሰጡ ያደርጋል። በተጨማሪም ግዑዟ ምድር የተትረፈረፈ ምርት እንደምትሰጥ ሁሉ ይሖዋ ምሳሌያዊው ምድር ትክክለኛ ከሆነው ዓላማው ጋር የሚስማሙ ሁኔታዎችን በተለይ ደግሞ በባቢሎን በግዞት ላሉት ሕዝቦቹ መዳንን እንዲያስገኝ ያደርጋል። በ1919 ይሖዋ በተመሳሳይ መንገድ ‘ሰማይ’ እና “ምድር” ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንዲያስገኙ አድርጓል። በዘመናችን የሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን መመልከታቸው እጅግ ያስደስታቸዋል። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ሁኔታዎች በሰማያት የተመሰለው የአምላክ መንግሥት ወደፊት ጽድቅ በሚሰፍንበት ምድር ላይ የተትረፈረፉ በረከቶችን እንደሚያፈስ ያላቸውን እምነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ በመሆናቸው ነው። በዚያን ጊዜ በምሳሌያዊዎቹ ሰማያትና ምድር በኩል የሚገኘው ጽድቅና መዳን የጥንቷ ባቢሎን በወደቀችበት ጊዜ ከተገኘው ጽድቅና መዳን እጅግ የላቀ ይሆናል። ያ ጊዜ ሲደርስ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት እጅግ አስደናቂ በሆነ መንገድ የመጨረሻ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ!—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1
የይሖዋን ሉዓላዊነት አምኖ መቀበል የሚያስገኛቸው በረከቶች
13. ሰዎች የይሖዋን ዓላማዎች ለመገዳደር መሞከራቸው ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው?
13 ኢሳይያስ ወደፊት የሚመጡትን አስደሳች በረከቶች ሲገልጽ ከቆየ በኋላ ድንገት የትንቢቱን ይዘት በመለወጥ ሁለት ወዮታዎችን ይናገራል:- “ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት! በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው። ጭቃ ሠሪውን:- ምን ትሠራለህ? ወይስ ሥራህ:- እጅ የለውም ይላልን? አባትን:- ምን ወልደሃል? ወይም ሴትን:- ምን አማጥሽ? ለሚል ወዮ!” (ኢሳይያስ 45:9, 10) የእስራኤል ልጆች ይሖዋ የተናገረውን ትንቢት ሳይቃወሙ አልቀሩም። ምናልባትም ይሖዋ ሕዝቡን ለግዞት አሳልፎ ይሰጣል ብለው ለማመን ተቸግረው ይሆናል። ወይም ደግሞ የዳዊት ዘር ያልሆነ የአረማውያን ንጉሥ እንዴት እስራኤልን ነፃ ያወጣል ብለው አስበውም ሊሆን ይችላል። ኢሳይያስ ተቃውሞ ያነሱትን ሰዎች የሠሪውን ችሎታ አጠያያቂ ለማድረግ ከቃጣ የተጣለ የሸክላ ጓል ወይም ስብርባሪ ጋር በማነጻጸር እንዲህ ያለ ተቃውሞ ማንሣት ምን ያህል ቂልነት እንደሆነ ገልጿል። የሸክላ ዕቃው ሠሪውን መልሶ እጅ የለውም ወይም መሥራት አይችልም ይለዋል። ይህ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! ተቃዋሚዎቹ የወላጆቻቸውን ሥልጣን ለመንቀፍ ከሚዳዳቸው ትንንሽ ልጆች የሚለዩ አልነበሩም።
14, 15. “ቅዱስ” እና “ሠሪው” የሚሉት ቃላት ይሖዋን በተመለከተ ምን ነገር ጎላ አድርገው ይገልጻሉ?
14 ይሖዋ ለእነዚህ ተቃዋሚዎች የሰጠውን መልስ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የእስራኤል ቅዱስ ሠሪውም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ስለሚመጣው ነገር ጠይቁኝ፣ ስለ ልጆቼና ስለ እጄ ሥራም እዘዙኝ። እኔ ምድርን ሠርቻለሁ ሰውንም በእርስዋ ላይ ፈጥሬአለሁ፤ እኔ በእጄ ሰማያትን ዘርግቼአለሁ፣ ሠራዊታቸውንም ሁሉ አዝዣለሁ። እኔ በጽድቅ አስነሥቼዋለሁ መንገዱንም ሁሉ አቀናለሁ፤ እርሱ ከተማዬን ይሠራል፣ በዋጋም ወይም በደመወዝ ሳይሆን ምርኮኞቼን ያወጣል፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”—ኢሳይያስ 45:11-13
15 ይሖዋ “ቅዱስ” ተብሎ መጠራቱ ቅድስናውን ጠበቅ አድርጎ የሚገልጽ ሲሆን “ሠሪው” ተብሎ መጠራቱ ደግሞ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ወደፊት የሚከሰቱት ሁኔታዎች እሱ በፈለገው መንገድ እንዲፈጸሙ የማድረግ መብት ያለው መሆኑን ጎላ አድርጎ ያሳያል። ይሖዋ ወደፊት የሚፈጸሙትን ነገሮች ለእስራኤል ልጆች ማሳወቅና የእጁ ሥራ የሆኑትን ሕዝቡን መጠበቅ የሚችል አምላክ ነው። የፈለገውን ነገር የመፍጠር መብትና ሥልጣን እንዳለው ሁሉ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘውን ነገር አስቀድሞ የማሳወቅም ሥልጣን አለው። መላውን አጽናፈ ዓለም የፈጠረው ይሖዋ በመሆኑ እያንዳንዱ ነገር እሱ በፈለገው መንገድ እንዲፈጸም የማድረግ መብት አለው። (1 ዜና መዋዕል 29:11, 12) በዚያን ዘመን ሉዓላዊው ገዥ ይሖዋ ቂሮስ የተባለ አረማዊ ሰው በማስነሳት እስራኤልን ነፃ ለማውጣት ወሰነ። ቂሮስ የሚነሳው ትንቢቱ ከተነገረ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ቢሆንም እሱን አስመልክቶ የተነገረው ትንቢት የሰማይና የምድርን ሕልውና ያህል አስተማማኝ ነበር። ታዲያ ከእስራኤል ልጆች መካከል አባት የሆነውን ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋን’ ለመንቀፍ የሚደፍር ሊኖር ይችላል?
16. የይሖዋ አገልጋዮች ራሳቸውን ለእሱ ማስገዛት ያለባቸው ለምንድን ነው?
16 የአምላክ አገልጋዮች ራሳቸውን ለእርሱ ማስገዛት ያለባቸው ለምን እንደሆነ የሚጠቁም ሌላ ሐሳብም በእነዚሁ የኢሳይያስ መጽሐፍ ቁጥሮች ላይ ተጠቅሶ እናገኛለን። ይሖዋ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ምንጊዜም ለአገልጋዮቹ የሚበጁ ናቸው። (ኢዮብ 36:3) ለሕዝቡ ጥቅም ሲል የተለያዩ ሕግጋትን አውጥቷል። (ኢሳይያስ 48:17) በቂሮስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ የይሖዋን ሉዓላዊነት የተቀበሉ አይሁዳውያን የአምላክን ሕግጋት መጠበቃቸው በእጅጉ ጠቅሟቸዋል። ቂሮስ ከይሖዋ ጽድቅ ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ከባቢሎን ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ቤተ መቅደሱን ዳግመኛ እንዲገነቡ አድርጓል። (ዕዝራ 6:3-5) ዛሬም በተመሳሳይ የአምላክን ሕግጋት በዕለታዊ ሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉና ለይሖዋ ሉዓላዊነት ራሳቸውን የሚያስገዙ ሰዎች በእጅጉ ይባረካሉ።—መዝሙር 1:1-3፤ 19:7፤ 119:105፤ ዮሐንስ 8:31, 32
ሌሎች አሕዛብ የሚያገኙት በረከት
17. ይሖዋ የሚወስደው የማዳን እርምጃ ከእስራኤላውያን በተጨማሪ እነማንን ይጠቅማል? እንዴትስ?
17 የባቢሎን መውደቅ የሚጠቅመው እስራኤላውያንን ብቻ አልነበረም። ኢሳይያስ እንደሚከተለው ብሏል:- “እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል:- የግብጽ ድካምና [“የጉልበት ሠራተኞችና፣” NW ] የኢትዮጵያ ንግድ [“ነጋዴዎች፣” NW ] ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይሆናሉ እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፣ ለአንተም እየሰገዱ:- በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ፣ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል።” (ኢሳይያስ 45:14) በሙሴ ዘመን እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ እስራኤላውያን ያልሆኑ “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” አብረዋቸው ወጥተው ነበር። (ዘጸአት 12:37, 38) ልክ እንደዚሁም ከባቢሎን ወደ ትውልድ አገራቸው ከሚመለሱት አይሁዳውያን ምርኮኞች ጋር ተደባልቀው የሚወጡ የሌላ አገር ሰዎች ይኖራሉ። እነዚህ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ማንም ሳያስገድዳቸው ‘ራሳቸው ይመጣሉ።’ ይሖዋ ‘ለአንተ እየሰገዱ ይለምኑሃል’ ሲል እነዚህ የባዕድ አገር ሰዎች ራሳቸውን በፈቃደኝነት ለእስራኤል እንደሚያስገዙና ከጎናቸው እንደሚቆሙ ማመልከቱ ነበር። በሰንሰለት የሚታሰሩ ከሆነም ይህን የሚያደርጉት በራሳቸው ፍላጎት ይሆናል። ይህም “እግዚአብሔር በአንተ አለ” ብለው የአምላክን የቃል ኪዳን ሕዝብ ለማገልገል ራሳቸውን በፈቃደኝነት እንደሚያቀርቡ የሚያመለክት ነው። እነዚህ ሰዎች አምላክ ከእስራኤል ጋር በገባው ቃል ኪዳን በኩል ባዘጋጃቸው ዝግጅቶች በመጠቀም እምነታቸውን ለውጠው ይሖዋን ያመልካሉ።—ኢሳይያስ 56:6
18. ይሖዋ ‘የአምላክ እስራኤልን’ ነፃ በማውጣቱ ዛሬ እየተጠቀሙ ያሉት እነማን ናቸው? በምንስ መንገዶች?
18 ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ‘የአምላክ እስራኤል’ ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ ከወጣበት ከ1919 ጀምሮ በቂሮስ ዘመን ከነበረው ሁኔታ በላቀ መልኩ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በምድር ዙሪያ የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን ለማገልገል በፈቃደኝነት ራሳቸውን አቅርበዋል። (ገላትያ 6:16፤ ዘካርያስ 8:23) ኢሳይያስ እንደጠቀሳቸው ‘የጉልበት ሠራተኞችና ነጋዴዎች’ በራሳቸው ፍላጎት ተነሳስተው ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ለእውነተኛው አምልኮ ያውላሉ። (ማቴዎስ 25:34-40፤ ማርቆስ 12:30) በደስታ ራሳቸውን የአምላክ ባሪያዎች አድርገው በማቅረብ ሕይወታቸውን ለአምላክ ወስነው በመንገዱ ይሄዳሉ። (ሉቃስ 9:23) ከአምላክ ጋር ልዩ ቃል ኪዳን ከገባው ይሖዋ ከሚጠቀምበት ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ ጋር መተባበር የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እየተቋደሱ ይሖዋን ብቻ ያመልካሉ። (ማቴዎስ 24:45-47፤ 26:28፤ ዕብራውያን 8:8-13) እነዚህ ‘የጉልበት ሠራተኞችና ነጋዴዎች’ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የታቀፉ ባይሆኑም እንኳ ቃል ኪዳኑ ከሚያስገኛቸው በረከቶች ተካፋይ ይሆናሉ። በተጨማሪም “ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም” ብለው በድፍረት በማወጅ ከቃል ኪዳኑ ጋር ዝምድና ያላቸውን ሕግጋት ይጠብቃሉ። እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሄድ ማየቱ ምንኛ የሚያስደስት ነው!—ኢሳይያስ 60:22
19. በጣዖት አምልኳቸው የሚገፉ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል?
19 ነቢዩ የሌሎች ብሔራት ሕዝቦች ይሖዋን በማምለክ ከእስራኤላውያን ጎን እንደሚሰለፉ ከገለጸ በኋላ እንዲህ አለ:- “የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ፣ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ።” (ኢሳይያስ 45:15) ምንም እንኳ ይሖዋ ለጊዜው ኃይሉን ከመግለጥ ቢታቀብም የኋላ ኋላ ራሱን መግለጡ አይቀርም። የእስራኤል አምላክና የሕዝቡ አዳኝ መሆኑን ያሳያል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በጣዖታት የሚታመኑትን ሰዎች አያድንም። ኢሳይያስ እነዚህን ሰዎች በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “ሁሉም ያፍራሉ ይዋረዱማል፣ ጣዖታትንም የሚሠሩ በአንድነት ወደ ውርደት ይሄዳሉ።” (ኢሳይያስ 45:16) የሚደርስባቸው ውርደት እንዲሁ ጊዜያዊ የሆነ ኃፍረት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ቀጥሎ ለእስራኤል ከሰጠው ተስፋ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መንገድ ጥፋት ይደርስባቸዋል።
20. እስራኤል ‘ለዘላለም የሚድነው’ በምን መንገድ ነው?
20 “እግዚአብሔር ግን እስራኤልን በዘላለማዊ መድኃኒት ያድነዋል፣ እናንተም ለዘላለም አታፍሩምና አትዋረዱም።” (ኢሳይያስ 45:17) ይሖዋ እስራኤልን ለዘላለም እንደሚያድን ቃል ገብቷል። ሆኖም ይህ በእነሱ ሁኔታ ላይ የተመካ ነው። መዳን የሚያገኙት ከይሖዋ ጋር እስከተባበሩ ድረስ ብቻ ነው። እስራኤላውያን ኢየሱስን መሲሕ አድርገው ለመቀበል አሻፈረን በማለት ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ሲያፈርሱ ‘ለዘላለም የመዳን’ ተስፋቸውን ያጣሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ እስራኤላውያን በኢየሱስ ስለሚያምኑ በሥጋዊ እስራኤል ምትክ የሚቋቋመው የአምላክ እስራኤል መሠረት ይሆናሉ። (ማቴዎስ 21:43፤ ገላትያ 3:28, 29፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) መንፈሳዊው እስራኤል ፈጽሞ ውርደት አይደርስበትም። ከዚህ ይልቅ ‘በዘላለም ቃል ኪዳን’ ይታቀፋል።—ዕብራውያን 13:20
የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎችም ሆኑ ራእዮቹ አስተማማኝ ናቸው
21. ይሖዋ በፍጥረት ሥራዎቹም ሆነ በራእዮቹ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት መሆኑን የገለጸው እንዴት ነው?
21 አይሁዳውያን ይሖዋ እስራኤልን ለዘላለም እንደሚያድን በገባው ቃል ላይ መታመን ይችላሉ? ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል:- “ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፣ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፣ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፣ እንዲህ ይላል:- እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም። በስውር ወይም በጨለማ ምድር ስፍራ አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር:- በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም፤ እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ ቅንንም አወራለሁ።” (ኢሳይያስ 45:18, 19) ኢሳይያስ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ለአራተኛና ለመጨረሻ ጊዜ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” የሚለውን ሐረግ በመጠቀም ጠንከር ያለ ትንቢታዊ መልእክት አስተላልፏል። (ኢሳይያስ 45:1, 11, 14) እዚህ ላይ ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹም ሆኑ ራእዮቹ እምነት የሚጣልባቸው መሆኑን ገልጿል። ምድርን የፈጠረው እንዲሁ “ለከንቱ” አይደለም። ሕዝቡን እስራኤልንም ‘ፈልጉኝ ያለው በከንቱ’ አይደለም። አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ዳር እንደሚደርስ ሁሉ ለተመረጠው ሕዝቡ ያለው ዓላማም ፍጻሜውን ያገኛል። ስውር ቃል ከሚናገሩት የሐሰት አማልክት አገልጋዮች በተለየ መልኩ የይሖዋ ቃሎች በግልጽ የተነገሩ ናቸው። የሚናገረው ቃል ትክክለኛ ከመሆኑም በላይ መሬት ጠብ አይልም። ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎች አገልግሎታቸው ከንቱ አይሆንም።
22. (ሀ) በባቢሎን ምድር በግዞት የነበሩት አይሁዶች ስለምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችሉ ነበር? (ለ) ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖች ምን ዋስትና ተሰጥቷቸዋል?
22 እነዚህ ቃላት በባቢሎን በግዞት ለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ተስፋይቱ ምድር ባድማ ሆና እንደማትቀር ከዚህ ይልቅ ዳግም እንደምትቆረቆር ማረጋገጫ ሆነውላቸው ነበር። ይሖዋም ቃል የገባላቸውን ሁሉ ፈጽሞላቸዋል። ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ዛሬ ላሉት የአምላክ ሕዝቦችም ምድር አንዳንዶች እንደሚሉት በእሳት ጋይታ እንደማትጠፋ ወይም አንዳንድ ሰዎች እንደሚሰጉት በኑክሊየር ቦምብ እንደማትወድም ዋስትና ይሆኑላቸዋል። የአምላክ ዓላማ መላዋ ምድር ውብ ገነት እንድትሆንና ጻድቅ በሆኑ ሰዎች ተሞልታ ለዘላለም እንድትኖር ነው። (መዝሙር 37:11, 29፤ 115:16፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:3, 4) አዎን፣ በእስራኤል ታሪክ እንደታየው ይሖዋ የተናገረው ቃል ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ጥርጥር የለውም።
ይሖዋ የምሕረት እጁን ይዘረጋል
23. ጣዖታትን የሚያመልኩ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆናል? ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎችስ?
23 ይሖዋ ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት እስራኤላውያን የሚያገኙትን መዳን ጠበቅ አድርገው የሚገልጹ ናቸው:- “እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፣ ተሰብስባችሁ ኑ በአንድነትም ቅረቡ፤ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ እውቀት የላቸውም። ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ፤ ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፣ ከእኔም በቀር ማንም የለም።” (ኢሳይያስ 45:20, 21) ይሖዋ ‘ያመለጡት ሰዎች’ ያገኙትን መዳን ጣዖት የሚያመልኩት ሰዎች ከደረሰባቸው ሁኔታ ጋር እንዲያነጻጽሩ ይሰበስባቸዋል። (ዘዳግም 30:3፤ ኤርምያስ 29:14፤ 50:28) ጣዖት አምላኪዎች የሚለምኑትም ሆነ የሚያገለግሉት ሊያድኗቸው የማይችሉ ከንቱ አማልክትን ስለሆነ “እውቀት የላቸውም።” አምልኳቸው ከንቱ ነው፤ አንዳች እርባና የለውም። ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ግን በባቢሎን የሚማረኩ ሕዝቦቹን እንደሚያድን የተናገረውን ትንቢት ጨምሮ ‘ከረጅም ጊዜ በፊት’ የተነበያቸውን ነገሮች የመፈጸም ችሎታ እንዳለው ይገነዘባሉ። ይሖዋ እንዲህ ያለ ኃይልና የመተንበይ ችሎታ ያለው መሆኑ ከሌሎች አማልክት ሁሉ ልዩ ያደርገዋል። በእርግጥም ‘ጻድቅ አምላክና አዳኝ ነው።’
‘ማዳን የአምላካችን ነው’
24, 25. (ሀ) ይሖዋ ምን ጥሪ አቅርቧል? የገባው ቃል ፍጻሜውን ማግኘቱ የማይቀረው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ምን መጠየቁ ተገቢ ነው?
24 የይሖዋ ምሕረት የሚከተለውን ጥሪ እንዲያቀርብ ገፋፍቶታል:- “እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፣ እኔ አምላክ ነኝና፣ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፣ አትመለስም:- ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፣ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ። ስለ እኔም:- በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ጽድቅና ኃይል አለ፣ ወደ እርሱም ሰዎች ይመጣሉ፣ በእርሱም ላይ የተቈጡ ሁሉ ያፍራሉ። የእስራኤልም ዘር ሁሉ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፣ ይመካሉም ይባላል።” —ኢሳይያስ 45:22-25
25 ይሖዋ በባቢሎን ከሚማረኩት ሰዎች መካከል ወደ እሱ ዞር የሚሉትን ሁሉ እንደሚያድን ለእስራኤል ቃል ገብቷል። ሕዝቡን የማዳን ፍላጎትም ሆነ ችሎታ ያለው በመሆኑ ትንቢቱ ሳይፈጸም ይቀራል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። (ኢሳይያስ 55:11) ይሖዋ የሚናገረው ቃል በራሱ እምነት የሚጣልበት ቢሆንም እንኳ መሐላውን ሲጨምርበት ደግሞ ይበልጥ የተረጋገጠ ይሆናል። (ዕብራውያን 6:13) ሞገሱን ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ እንዲገዙለት (“ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል”) እና ቃል እንዲገቡለት (“ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል”) መጠየቁ የተገባ ነው። ይሖዋን በማምለክ የሚጸኑ እስራኤላውያን ይድናሉ። በተጨማሪም ይሖዋ ባደረገላቸው ነገር መመካት ይችላሉ።—2 ቆሮንቶስ 10:17
26.ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ይሖዋ ወደ እሱ ዘወር እንዲሉ ላቀረበው ጥሪ ምላሽ እየሰጡ ያሉት እንዴት ነው?
26 ይሁንና አምላክ ወደ እሱ ዘወር እንዲሉ ጥሪ ያቀረበው በጥንቷ ባቢሎን ለነበሩት ምርኮኞች ብቻ አይደለም። (ሥራ 14:14, 15፤ 15:19፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ይህ ጥሪ አሁንም እየቀረበ ሲሆን ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ጥሪውን በመቀበል “ለአምላካችንና ለበጉ [ለኢየሱስ] ማዳን ነው” ሲሉ አውጀዋል። (ራእይ 7:9, 10፤ 15:4) በየዓመቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ሰዎች የአምላክን ሉዓላዊነት ሙሉ በሙሉ በመቀበልና ከእሱ ጎን የተሰለፉ መሆናቸውን በይፋ በማሳወቅ ወደ ይሖዋ ዘወር እያሉ በመሆኑ የእጅግ ብዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው። እነዚህ ሰዎች “የአብርሃም ዘር” ለሆኑት መንፈሳዊ እስራኤላውያን በታማኝነት ድጋፍ ያደርጋሉ። (ገላትያ 3:29) በዓለም ዙሪያ “በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ጽድቅና ኃይል አለ” ብለው በማወጅ ለይሖዋ የጽድቅ አገዛዝ ከፍተኛ ፍቅር እንዳላቸው ያሳያሉ።a ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ኢሳይያስ 45:23ን ከሰፕቱጀንት ትርጉም ላይ በመጥቀስ ሕይወት ያለው ሁሉ በመጨረሻ የአምላክን ሉዓላዊነት አምኖ እንደሚቀበልና ስሙን ለዘላለም እንደሚያመሰግን አመልክቷል።—ሮሜ 14:11፤ ፊልጵስዩስ 2:9-11፤ ራእይ 21:22-27
27. ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖች ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ሙሉ በሙሉ ሊተማመኑ የሚችሉት ለምንድን ነው?
27 እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ ዞር ማለታቸው ሕይወት እንደሚያስገኝላቸው እርግጠኞች መሆን የሚችሉት ለምንድን ነው? በኢሳይያስ ምዕራፍ 45 ላይ የሚገኙት ትንቢታዊ ቃላት በግልጽ እንደሚያሳዩት የይሖዋ ተስፋዎች አስተማማኝ ናቸው። ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ጥበቡና ኃይሉ የፈጠረው ይሖዋ ትንቢቶቹ እንዲፈጸሙ ማድረግ አይሳነውም። ቂሮስን በተመለከተ የተናገረውን ትንቢት እንደፈጸመ ሁሉ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ያደርጋል። በመሆኑም የይሖዋ አምላኪዎች በቅርቡ ይሖዋ ‘ጻድቅ አምላክና አዳኝ’ መሆኑን በድጋሚ እንደሚያረጋግጥ ሙሉ በሙሉ ሊተማመኑ ይችላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የዕብራይስጡ ጽሑፍ እዚህ ላይ የገባውን “ጽድቅ” የሚለውን ቃል የገለጸው በብዙ ቁጥር ነው። ይህ ቃል በብዙ ቁጥር መገለጹ የይሖዋ ጽድቅ ማለቂያ የሌለው መሆኑን ያመለክታል።
[በገጽ 80, 81 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ብርሃንንም ሆነ ጨለማን የፈጠረው ይሖዋ ሰላም ሊያሰፍን እንዲሁም ጥፋት ሊያመጣ ይችላል
[በገጽ 83 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ “ሰማያት” በረከት እንዲያዘንቡ “ምድርም” መዳንን እንድታበቅል ያደርጋል
[በገጽ 84 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተጣሉ የሸክላ ዕቃ ስብርባሪዎች የሠሪያቸውን ጥበብ አጠያያቂ ለማድረግ መሞከር ይኖርባቸዋልን?
[በገጽ 89 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ምድርን የፈጠረው ለከንቱ አይደለም