ምዕራፍ አሥራ አራት
ይሖዋ መሲሐዊ አገልጋዩን ከፍ ከፍ ያደርገዋል
1, 2. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መባቻ ላይ የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን የገጠማቸውን ሁኔታ በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ይሖዋ ታማኝ አይሁዳውያን መሲሑን ለይተው ማወቅ እንዲችሉ የሚረዳ ምን ዝግጅት አድርጓል?
ከአንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ልትገናኝ ቀጠሮ ይዘሃል እንበል። የምትገናኙበት ሰዓትና ቦታ ሁሉ ተወስኗል። ችግሩ ግን ይህን ሰው ከዚህ በፊት አይተኸው አታውቅም። ከዚህም በተጨማሪ ግለሰቡ የሚመጣው የማንንም ትኩረት በማይስብ ሁኔታ ያላንዳች አጀብና ሥነ ሥርዓት ነው። ታዲያ እንዴት አድርገህ ትለየዋለህ? የሰውየውን ማንነት የሚገልጽ ዝርዝር መረጃ ብታገኝ በእጅጉ እንደሚጠቅምህ ጥርጥር የለውም።
2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መባቻ ላይ ይኖሩ የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር። በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ታላቅ የሆነውን ሰው ማለትም መሲሑን እየተጠባበቁ ነበር። (ዳንኤል 9:24-27፤ ሉቃስ 3:15) ይሁን እንጂ ታማኝ አይሁዳውያን መሲሑን ሊለዩት የሚችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ አስተዋይ የሆኑ ሰዎች የመሲሑን ማንነት በትክክል ለይተው ማወቅ እንዲችሉ መሲሑ በሚገለጥበት ጊዜ የሚፈጸሙ ሁኔታዎችን የሚገልጽ ዝርዝር መግለጫ በዕብራውያን ነቢያት አማካኝነት ሰጥቷል።
3. በኢሳይያስ 52:13–53:12 ላይ መሲሑን በተመለከተ ምን መግለጫ ሰፍሮ ይገኛል?
3 በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መሲሑን አስመልክቶ ከተነገሩት ትንቢቶች መካከል በኢሳይያስ 52:13–53:12 ላይ ሰፍሮ የሚገኘውን ዘገባ ያህል በጣም ግልጽ የሆነ መረጃ የሚሰጥ ሌላ ትንቢት አለ ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። ኢሳይያስ 700 ዓመታት አስቀድሞ የመሲሑን አካላዊ ቁመና ሳይሆን ከዚያ ይበልጥ ትርጉም ያላቸውን ዝርዝር መረጃዎች ማለትም መከራ የሚቀበልበትን ምክንያትና ሁኔታ እንዲሁም የሚሞትበትን፣ የሚቀበርበትንና በኋላም ከፍ ከፍ የሚደረግበትን ሁኔታ በተመለከተ ሰፋ ያለ መግለጫ ሰጥቷል። ይህን ትንቢትና አፈጻጸሙን መመርመራችን ልባችን በደስታ ስሜት እንዲሞላ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ እምነታችንን ያጠነክርልናል።
“አገልጋዬ” የተባለው ማን ነው?
4. አንዳንድ የአይሁድ ምሁራን ‘የአገልጋዩን’ ማንነት በተመለከተ ምን አስተያየቶች ሰጥተዋል? እነዚህ አስተያየቶች ከኢሳይያስ ትንቢት ጋር የማይስማሙትስ ለምንድን ነው?
4 ኢሳይያስ አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ስለሚወጡበት ሁኔታ ከተናገረ በኋላ ብዙ ዘመናት አሻግሮ በመመልከት ከዚያ እጅግ የላቀ ግምት የሚሰጠውን ክንውን አስመልክቶ ይሖዋ የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት ዘገበ:- “እነሆ፣ ባሪያዬ [“አገልጋዬ፣” የ1980 ትርጉም ] በማስተዋል ያደርጋል፤ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል፣ እጅግ ታላቅም ይሆናል።” (ኢሳይያስ 52:13) ይህ ‘አገልጋይ’ ማን ነው? ባለፉት መቶ ዘመናት የአይሁድ ምሁራን የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል። አንዳንዶች ይህ አገልጋይ በባቢሎን በግዞት የነበረውን መላውን የእስራኤል ብሔር ያመለክታል የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ማብራሪያ ከትንቢቱ ጋር አይጣጣምም። እዚህ ላይ የተጠቀሰው የአምላክ አገልጋይ መከራ የሚደርስበት በራሱ ፈቃድ ነው። ምንም ጥፋት ያልሠራ ቢሆንም እንኳ ለሌሎች ኃጢአት ሲል መከራ ይቀበላል። ይህ በገዛ ራሱ ኃጢአት ለግዞት የተዳረገውን የአይሁድ ሕዝብ ሊያመለክት አይችልም። (2 ነገሥት 21:11-15፤ ኤርምያስ 25:8-11) ሌሎች ምሁራን ደግሞ ይህ አገልጋይ በእስራኤል ይኖሩ የነበሩትን ራሳቸውን ያመጻድቁ የነበሩ የከፍተኛ መደብ አባላት እንደሚያመለክትና እነዚህ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ኃጢአተኛ ለነበሩት እስራኤላውያን ሲሉ መከራ እንደተቀበሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በእስራኤል ላይ መከራና ሥቃይ በደረሰባቸው ጊዜያት ለሌላ ወገን ሲል መከራ የተቀበለ አንድ የተለየ የኅብረተሰብ ክፍል የለም።
5. (ሀ) አንዳንድ የአይሁድ ምሁራን የኢሳይያስ ትንቢት ማንን እንደሚያመለክት ተናግረዋል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) የሥራ መጽሐፍ የአገልጋዩን ማንነት በግልጽ የሚጠቁመው እንዴት ነው?
5 ክርስትና ከመቋቋሙ በፊትም ሆነ በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት እዘአ ጥቂት የአይሁድ ምሁራን ይህ ትንቢት መሲሑን እንደሚያመለክት ተናግረዋል።a በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያለው ዘገባ ይህ አባባል ትክክል እንደሆነ ይጠቁማል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደሚገልጸው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የተገለጸው አገልጋይ ማን እንደሆነ እንደማያውቅ በተናገረ ጊዜ ፊልጶስ “ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት።” (ሥራ 8:26-40፤ ኢሳይያስ 53:7, 8) ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትም በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የተጠቀሰው መሲሐዊ አገልጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ያመለክታሉ። ይህን ትንቢት እየመረመርን ስንሄድ ይሖዋ “አገልጋዬ” ሲል የጠራው ሰውና የናዝሬቱ ኢየሱስ ፍጹም ተመሳሳይ መሆናቸውን በግልጽ እንረዳለን።
6. የኢሳይያስ ትንቢት መሲሑ መለኮታዊውን ፈቃድ በተሳካ ሁኔታ እንደሚፈጽም የሚጠቁመው እንዴት ነው?
6 ትንቢቱ ዘገባውን የሚጀምረው መሲሑ መለኮታዊውን ፈቃድ በመፈጸም መጨረሻ ላይ የሚያገኘውን ስኬት በመግለጽ ነው። ‘አገልጋይ’ የሚለው ቃል አንድ አገልጋይ ለጌታው እንደሚገዛ ሁሉ እሱም ለአምላክ ፈቃድ የሚገዛ መሆኑን ያመለክታል። ይህንንም “በማስተዋል ያደርጋል።” ማስተዋል አንድን ሁኔታ ጠለቅ ብሎ የመረዳት ችሎታ ነው። በማስተዋል ማድረግ ማለት በሚገባ አመዛዝኖ መሥራት ማለት ነው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እዚህ ላይ የገባውን የዕብራይስጥ ግስ በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “ቃሉ በሚገባ አመዛዝኖ ጥበብ በተሞላበት መንገድ መሥራት የሚል መልእክት ያዘለ ነው። በጥበብ የሚሠራ ሰው ይከናወንለታል።” ትንቢቱ “ከፍ ከፍም ይላል፣ እጅግ ታላቅም ይሆናል” ሲል መናገሩ መሲሑ በእርግጥ እንደሚሳካለት ይጠቁማል።
7. ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በማስተዋል ያደረገው’ እንዴት ነው? ‘ከፍ ከፍ ያለውና እጅግ ታላቅ የሆነውስ’ እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ስለ እሱ የተነገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በመረዳትና በእነዚህ ትንቢቶች ተመርቶ የአባቱን ፈቃድ በማድረግ ተልዕኮውን ‘በማስተዋል ፈጽሟል።’ (ዮሐንስ 17:4፤ 19:30) ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል? ኢየሱስ ከሞት ከተነሳና ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ “እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው።” (ፊልጵስዩስ 2:9፤ ሥራ 2:34-36) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ክብር የተጎናጸፈውን ልጁን በ1914 በመሲሐዊው መንግሥት ዙፋን ላይ በማስቀመጥ ይበልጥ ከፍ ከፍ አደረገው። (ራእይ 12:1-5) በእርግጥም ‘ከፍ ከፍ ብሏል፣ እጅግ ታላቅም ሆኗል።’
‘በመደነቅ ያዩታል’
8, 9. ከፍ ከፍ የተደረገው ኢየሱስ ፍርድ ለማስፈጸም በሚመጣበት ጊዜ የምድር ገዥዎች ምን ስሜት ያድርባቸዋል? ለምንስ?
8 ብሔራትና ገዥዎቻቸው ከፍ ከፍ የተደረገውን መሲሕ በተመለከተ ምን ስሜት ያድርባቸዋል? በቁጥር 14 መግቢያ ላይ ያለውን ሐሳብ ለጊዜው ትተን ቀሪውን ክፍል ብንመለከት ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- “ብዙ ሰዎች ስለ አንተ እንደ ተደነቁ፣ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን ያስደንቃል፤ ያልተነገረላቸውንም ያያሉና፣ ያልሰሙትንም ያስተውላሉና ነገሥታት ስለ እርሱ አፋቸውን ይዘጋሉ።” (ኢሳይያስ 52:14ለ, 15) ኢሳይያስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት መሲሑ መጀመሪያ ላይ ሲገለጥ የሚኖረውን ሁኔታ ሳይሆን ከምድራዊ ገዥዎች ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የሚፋጠጥበትን ሁኔታ የሚገልጹ ናቸው።
9 ከፍ ከፍ የተደረገው ኢየሱስ አምላክን በማይታዘዘው በዚህ ዓመፀኛ ዓለም ላይ ፍርድ ለማስፈጸም በሚመጣበት ጊዜ ምድራዊ ገዥዎች ‘በመደነቅ ያዩታል።’ ሰብዓዊ ገዥዎች ክብር የተጎናጸፈውን ኢየሱስን ቃል በቃል በዓይናቸው እንደማያዩት የታወቀ ነው። ሆኖም የይሖዋ ሰማያዊ ተዋጊ ሆኖ በሚገለጥበት ጊዜ ኃይሉን በግልጽ የሚያንጸባርቁትን የሚታዩ ማስረጃዎች ይመለከታሉ። (ማቴዎስ 24:30) ከሃይማኖት መሪዎች ያልሰሙትን ነገር ማለትም ኢየሱስ የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ መሆኑን ለማስተዋል ይገደዳሉ! በድንገት የሚገናኙት ከፍ ከፍ የተደረገው አገልጋይ ባላሰቡት መንገድ እርምጃ ይወስዳል።
10, 11. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ መልክ ተጎሳቁሎ ነበር ማለት የሚቻለው በምን መንገድ ነው? በዘመናችንስ?
10 ኢሳይያስ በቁጥር 14 መግቢያ ላይ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ፊቱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ፣ መልኩም ከሰዎች ልጆች ይልቅ ተጐሳቁሎአልና።” (ኢሳይያስ 52:14ሀ) ኢየሱስ አንድ ዓይነት አካላዊ እንከን ነበረበትን? በፍጹም። ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ምን ዓይነት መልክ እንደነበረው ዝርዝር መግለጫ ባይሰጥም ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ የሚያምር መልክና ቁመና እንደነበረው መገመት አያዳግትም። ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው እነዚህ የኢሳይያስ ቃላት የሚያመለክቱት በኢየሱስ ላይ የደረሰውን ውርደት ነው። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ግብዞች፣ ውሸታሞችና ነፍሰ ገዳዮች መሆናቸውን በድፍረት በማጋለጡ ሰድበውታል። (1 ጴጥሮስ 2:22, 23) ሕግ ይጥሳል፣ አምላክን ይሳደባል፣ ያታልላል እንዲሁም በሮም መንግሥት ላይ ዓመፅ ያነሳሳል በማለት ከሰውታል። በዚህ መንገድ እነዚህ የሐሰት ከሳሾች ጨርሶ የሌለውን መልክ ሰጥተውታል።
11 ዛሬም ቢሆን ሰዎች ኢየሱስን በተሳሳተ መንገድ ይገልጹታል። አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ሲያስቡ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው በግርግም የተኛ ሕፃን ወይም ደግሞ በደረሰበት ከባድ መከራ የተነሳ ፊቱ እጅግ የተጎሳቆለና የእሾህ አክሊል ደፍቶ በመስቀል ላይ የተቸነከረ ምስኪን ሰው ነው። በሰዎች አእምሮ ውስጥ እንዲህ ያለ አስተሳሰብ እንዲቀረጽ ያደረጉት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ናቸው። ኢየሱስ ብሔራትን የመጠየቅ ሥልጣን ያለው ኃያል ሰማያዊ ንጉሥ እንደሆነ አላስተማሯቸውም። በቅርቡ ሰብዓዊ ገዥዎች የሚፋጠጡት ከፍ ከፍ ከተደረገውና ‘ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ከተሰጠው’ መሲሕ ጋር ነው።—ማቴዎስ 28:18
ይህን ምሥራች የሚያምነው ማን ነው?
12. ኢሳይያስ 53:1 ላይ የተጠቀሱት ቃላት የትኞቹን ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎች ያስነሳሉ?
12 ኢሳይያስ “ተጎሳቁሎ” የነበረው መሲሕ በሚያስደንቅ ሁኔታ “እጅግ ታላቅ” እንደሆነ ከገለጸ በኋላ የሚከተለውን ጥያቄ አቀረበ:- “የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል?” (ኢሳይያስ 53:1) እነዚህ የኢሳይያስ ቃላት የሚከተሉትን ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎች ያስነሳሉ:- ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኝ ይሆን? ኃይሉን የመጠቀም ችሎታውን የሚወክለው ‘የአምላክ ክንድ’ ተገልጦ እነዚህን ቃላት ያስፈጽም ይሆን?
13. ጳውሎስ የኢሳይያስ ትንቢት በኢየሱስ ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ ያመለከተው እንዴት ነው? በዚያ ዘመን የነበሩት ሰዎችስ ምን ዓይነት ምላሽ ሰጥተዋል?
13 መልሱ እንዴታ! የሚል ነው። ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኢሳይያስ የሰማውና የመዘገበው ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ ለማመልከት እነዚህን የኢሳይያስ ቃላት ጠቅሷል። ኢየሱስ ምድር ላይ የተለያዩ መከራዎችን ሲቀበል ከቆየ በኋላ ክብር መጎናጸፉ ምሥራች ነበር። ጳውሎስ ያላመኑ አይሁዶችን አስመልክቶ ሲናገር “ነገር ግን ኢሳይያስ ‘ጌታ ሆይ! የተናገርነውን ቃል ማንም አልተቀበለም’ ብሎ እንደተናገረ ሁሉም የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም። ስለዚህ እምነት የሚገኘው የምሥራቹን ቃል ከመስማት ነው፤ የምሥራቹም ቃል ስለ ክርስቶስ የሚነገረው ትምህርት ነው።” (ሮሜ 10:16, 17 የ1980 ትርጉም ) የሚያሳዝነው ግን በጳውሎስ ዘመን ስለ አምላክ አገልጋይ በሚናገረው ምሥራች ያመኑት ሰዎች ጥቂት መሆናቸው ነው። ለምን?
14, 15. መሲሑ ወደ ዓለም መድረክ ብቅ የሚለው እንዴት ነው?
14 ትንቢቱ በመቀጠል ቁጥር 1 ላይ የተጠቀሱት ጥያቄዎች የተነሱበትን ምክንያት ለእስራኤላውያን በመግለጽ ብዙዎች መሲሑን ሳይቀበሉ የሚቀሩት ለምን እንደሆነ ይጠቁማል:- “[በተመልካች ፊት ] እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፤ መልክና ውበት የለውም፣ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም።” (ኢሳይያስ 53:2) መሲሑ ወደ ዓለም መድረክ ብቅ የሚልበት ሁኔታ ይህን ይመስላል። ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካለው ቤተሰብ የሚወለድ ሲሆን የሚመለከቱት ሰዎች ለምንም ነገር ሊበቃ እንደማይችል ሆኖ ይሰማቸዋል። በተጨማሪም በዛፍ ግንድ ወይም ቅርንጫፍ ላይ እንደሚያድግ ቡቃያ ወይም ቀምበጥ ተደርጎ ይታያል። ከዚህም ሌላ በደረቅና ምቹ ባልሆነ አፈር ላይ እንደበቀለና ውኃ ካላገኘ እንደሚጠወልግ ሥር ተደርጎ ይታያል። ወደ ምድር የሚመጣውም ካባ ለብሶና የሚያብረቀርቅ ዘውድ ደፍቶ በደመቀ ንጉሣዊ ሥነ ሥርዓት በመታጀብ ሳይሆን እንደማንኛውም ተራ ሰው ሆኖ ነው።
15 ይህ ከተራ ቤተሰብ የተወለደውን የኢየሱስን ሰብዓዊ ሕይወት አጀማመር ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ዘገባ ነው! ኢየሱስ ቤተ ልሔም በመባል በምትታወቅ አንዲት አነስተኛ ከተማ በግርግም ውስጥ ከአይሁዳዊቷ ድንግል ማርያም ተወለደ።b (ሉቃስ 2:7፤ ዮሐንስ 7:42) ማርያምና ባሏ ዮሴፍ ድሆች ነበሩ። ኢየሱስ ከተወለደ ከ40 ቀናት ገደማ በኋላ ለድሆች የተፈቀደውን የኃጢአት መሥዋዕት ይኸውም ‘ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች’ አቀረቡ። (ሉቃስ 2:24፤ ዘሌዋውያን 12:6-8) ከጊዜ በኋላ ማርያምና ዮሴፍ ወደ ናዝሬት የተዛወሩ ሲሆን በዚያም ኢየሱስ መጠነኛ ገቢ ባለው ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ አደገ።—ማቴዎስ 13:55, 56
16. ኢየሱስ “መልክ” ወይም “ውበት” ያልነበረው ከምን አንጻር ነው?
16 ኢየሱስ ሰው ሆኖ በተወለደበት ጊዜ በተገቢው መሬት ላይ እንዳልበቀለ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። (ዮሐንስ 1:47፤ 7:41, 52) ምንም እንኳ ኢየሱስ ፍጹም ሰውና የንጉሥ ዳዊት ዘር የነበረ ቢሆንም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካለው የኅብረተሰብ ክፍል በመብቀሉ ቢያንስ ቢያንስ መሲሑ ከትልቅ ቤተሰብ ይወለዳል ብለው ይጠብቁ በነበሩት ሰዎች ዓይን “መልክ” ወይም “ውበት” ሊኖረው አልቻለም። ብዙ ሰዎች በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ገፋፊነት ኢየሱስን እስከ መጥላትና እስከ መናቅ ደረጃ ደርሰዋል። በመጨረሻም ሕዝቡ ፍጹሙን የአምላክ ልጅ ምንም የሚወደድ ነገር አላገኙበትም።—ማቴዎስ 27:11-26
“የተናቀ ከሰውም የተጠላ”
17. (ሀ) ኢሳይያስ መግለጽ የጀመረው ነገር ምንድን ነው? ልክ እንደተፈጸመ አድርጎ የጻፈውስ ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስን ‘የናቁትና የጠሉት’ እነማን ናቸው? ይህንንስ ያሳዩት እንዴት ነው?
17 ኢሳይያስ በመቀጠል ሰዎች ለመሲሑ ምን ዓይነት አመለካከት እንደሚያድርባቸውና ምን እንደሚደርስበት በዝርዝር መግለጽ ጀመረ:- “የተናቀ ከሰውም የተጠላ፣ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፣ እኛም አላከበርነውም።” (ኢሳይያስ 53:3) ኢሳይያስ እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ እርግጠኛ ከመሆኑ የተነሳ ድርጊቱ ልክ እንደተፈጸመ አድርጎ ጽፏል። በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰዎች የተናቀና የተጠላ ነበርን? አዎን፣ የተናቀ ነበር! ራሳቸውን በሚያመጻድቁት የሃይማኖት መሪዎችም ሆነ በተከታዮቻቸው ፊት ከሰው ሁሉ ይልቅ የተናቀ ነበር። የቀራጮችና የጋለሞቶች ወዳጅ ብለውታል። (ሉቃስ 7:34, 37-39) ፊቱ ላይ ተፍተውበታል። ጎስመውታል እንዲሁም ሰድበውታል። አፊዘውበታል እንዲሁም አላግጠውበታል። (ማቴዎስ 26:67) እነዚህ የእውነት ጠላቶች ባሳደሩባቸው ተጽዕኖ ሳቢያ “የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።”—ዮሐንስ 1:10, 11
18. ኢየሱስ ታሞ የማያውቅ ሰው ሆኖ እያለ “የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን አልታመመም። ሆኖም “የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው።” ይህ የራሱ ሕመምና ደዌ አይደለም። ኢየሱስ የመጣው በበሽታ ወደተሞላ ዓለም ነው። በመከራና በሕመም በተጠቃ ኅብረተሰብ መካከል ሲኖር በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ የታመሙትን ሰዎች አላገለላቸውም። ልክ እንደ አንድ አሳቢ ሐኪም በአካባቢው ያሉት ሰዎች ያለባቸውን ችግር ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ከዚህም በላይ አንድ ተራ ሰብዓዊ ሐኪም ሊያደርገው የማይችለውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ነበረው።—ሉቃስ 5:27-32
19. ‘የተሰወረው’ የማን ፊት ነው? የኢየሱስ ጠላቶች ‘እንዳላከበሩት’ ያሳዩት እንዴት ነው?
19 ይሁን እንጂ የኢየሱስ ጠላቶች እንደ በሽተኛ አድርገው ይመለከቱት የነበረ ከመሆኑም በላይ በሞገስ ዓይን ሊቀበሉት አልወደዱም። ፊቱ ከእይታ ‘የተሰወረ’ ነበር። ይህ የሆነው ግን እሱ ራሱ ፊቱን ከሰዎች ሰውሮ አይደለም። አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢሳይያስ 53:3ን ሲተረጉም “ሰዎች ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት ዐይነት” የሚል ሐረግ ተጠቅሟል። የኢየሱስ ተቃዋሚዎች ኢየሱስን ለማየት እንደሚቀፍ ነገር በመጸየፍ ፊታቸውን ያዞሩበት ያህል ነበር። ከአንድ ባሪያ የተሻለ ዋጋ እንዳለው እንኳ አድርገው አልቆጠሩትም። (ዘጸአት 21:32፤ ማቴዎስ 26:14-16) ለኢየሱስ የነበራቸው አመለካከት በርባን ለተባለው ነፍሰ ገዳይ ከነበራቸው አመለካከት እንኳ የከፋ ነበር። (ሉቃስ 23:18-25) ለኢየሱስ ያላቸውን ንቀት ከዚህ የበለጠ እንዴት ሊገልጹ ይችላሉ?
20. የኢየሱስ ቃላት በዘመናችን ላሉት የይሖዋ ሕዝቦች ምን ማጽናኛ ይሰጣሉ?
20 ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት በዘመናችን ላሉት የአምላክ አገልጋዮች ከፍተኛ ማጽናኛ ሊሆኗቸው ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ተቃዋሚዎች የአምላክ ታማኝ አምላኪዎችን ሊንቋቸው ወይም ምንም ዋጋ እንደሌላቸው አድርገው ሊመለከቷቸው ይችላሉ። ይሁን እንጂ በኢየሱስ ላይ እንደታየው ዋናው ነገር ይሖዋ አምላክ ለእኛ ያለው አመለካከት ነው። ሰዎች ‘ኢየሱስን አለማክበራቸው’ በአምላክ ፊት ያለውን ትልቅ ዋጋ ፈጽሞ አልቀነሰውም!
“ስለ መተላለፋችን ተወጋ”
21, 22. (ሀ) መሲሑ ለሌሎች ሲል የተሸከመው ሸክም ምንድን ነው? (ለ) ብዙዎች መሲሑን በተመለከተ ምን አመለካከት አድሮባቸዋል? በመሲሑ ላይ የደረሰው መከራ የተደመደመው እንዴት ነው?
21 መሲሑ መሰቃየትና መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ [“ተወጋ፣” አ.መ.ት ]፣ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።”—ኢሳይያስ 53:4-6
22 መሲሑ የሌሎችን ደዌ ከመቀበሉም በላይ ሕመማቸውን ተሸክሟል። የእነሱን ሸክም ከላያቸው አውርዶ በራሱ ትከሻ ላይ የተሸከመ ያህል ነበር። ደዌና ሕመም ደግሞ በሰው ልጅ ኃጢአት ምክንያት የመጡ ነገሮች በመሆናቸው መሲሑ የሌሎችን ኃጢአት ተሸክሟል። ብዙዎች በኢየሱስ ላይ መከራ የደረሰበትን ምክንያት ስላልተገነዘቡ አምላክ ዘግናኝ በሆነ ደዌ በመምታት እየቀጣው እንዳለ ሆኖ ተሰምቷቸዋል።c በመሲሑ ላይ የደረሰው መከራ እየተባባሰ ሄዶ የተወጋ፣ የደቀቀና የቆሰለ ሲሆን እነዚህ ቃላት መሲሑ ከፍተኛ ሥቃይ በተሞላበት ሁኔታ መሞቱን የሚያመለክቱ ኃይለኛ መግለጫዎች ናቸው። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ሞት ኃጢአት የማስተሰረይ ኃይል አለው። በበደላቸውና በኃጢአታቸው ጠፍተው በመቅበዝበዝ ላይ ያሉትን እንደገና በመመለስ ከአምላክ ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ ለመርዳት የሚያስችል መሠረት ይጥላል።
23. ኢየሱስ የሌሎችን መከራ የተሸከመው በምን መንገድ ነው?
23 ኢየሱስ የሌሎችን መከራ የተሸከመው እንዴት ነው? የማቴዎስ ወንጌል ኢሳይያስ 53:4ን በመጥቀስ እንዲህ ይላል:- “አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ:- እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፣ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፣ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።” (ማቴዎስ 8:16, 17) ኢየሱስ ወደ እሱ የመጡትን የተለያዩ በሽታዎች ያሉባቸውን ሰዎች በመፈወስ የእነሱን መከራ ተሸክሟል። እንዲህ ያለውን ፈውስ ለመፈጸም ኃይሉን መጠቀም አስፈልጎታል። (ሉቃስ 8:43-48) ሁሉንም ዓይነት አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ በሽታዎች መፈወስ መቻሉ የሰው ልጆችን ከኃጢአት የማንጻት ሥልጣን እንደተሰጠው የሚያረጋግጥ ነበር።—ማቴዎስ 9:2-8
24. (ሀ) ብዙዎች ኢየሱስ በአምላክ “እንደ ተመታ” ሆኖ የተሰማቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ መከራ የደረሰበትና የሞተው ለምንድን ነው?
24 ይሁን እንጂ ብዙዎች ኢየሱስ በአምላክ “እንደ ተመታ” ሆኖ ተሰምቷቸዋል። ምክንያቱም መከራው የደረሰበት ትልቅ ቦታ ባላቸው የሃይማኖት መሪዎች ቆስቋሽነት ነው። ይሁንና ይህ መከራ የደረሰበት እሱ በሠራው ኃጢአት ሳቢያ እንዳልሆነ አስታውስ። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፣ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፣ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ።” (1 ጴጥሮስ 2:21, 22, 24) በአንድ ወቅት ሁላችንም በኃጢአት ምክንያት ጠፍተን ‘እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ነበር።’ (1 ጴጥሮስ 2:25) ሆኖም ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ከኃጢአት ልንቤዥ የምንችልበትን ዝግጅት አድርጓል። በደላችንን በኢየሱስ ላይ ‘አኑሯል።’ ምንም ዓይነት ኃጢአት ያልሠራው ኢየሱስ የእኛ ኃጢአት ያስከተለውን ቅጣት በፈቃደኝነት ተቀብሏል። ባልሠራው ጥፋት እጅግ በሚያዋርድ ሁኔታ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ በመሞት ከአምላክ ጋር መታረቅ እንድንችል በር ከፍቷል።
“መከራን ታግሦ ተቀበለ”
25. ኢየሱስ መከራ የተቀበለውና የሞተው በፈቃደኝነት መሆኑን እንዴት እናውቃለን?
25 መሲሑ መከራ ለመቀበልና ለመሞት ፈቃደኛ ነበርን? ኢሳይያስ እንዲህ ይላል:- “ተጨነቀ ተሣቀየም [“መከራን ታግሦ ተቀበለ፣” የ1980 ትርጉም ] አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።” (ኢሳይያስ 53:7) ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ሌሊት “ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት” መጥተው እንዲረዱት ማድረግ ይችል ነበር። ሆኖም “እንዲህ ከሆነስ:- እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 26:53, 54) በመሆኑም “የእግዚአብሔር በግ” ምንም ዓይነት የአጸፋ እርምጃ አልወሰደም። (ዮሐንስ 1:29) የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በጲላጦስ ፊት በሐሰት ሲከሱት “ምንም አልመለሰም።” (ማቴዎስ 27:11-14) የአምላክን ፈቃድ ሊያስተጓጉል የሚችል ነገር መናገር አልፈለገም። ኢየሱስ የእሱ ሞት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ከኃጢአት፣ ከበሽታና ከሞት ሊቤዥ እንደሚችል በሚገባ በመገንዘቡ የመሥዋዕት በግ ሆኖ ለመሞት ፈቃደኛ ነበር።
26. የኢየሱስ ተቃዋሚዎች “ማዕቀብ” ያደረጉት በምን መንገድ ነው?
26 ኢሳይያስ በመቀጠል በመሲሑ ላይ የሚደርሰውን መከራና ውርደት በተመለከተ ይበልጥ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመስጠት እንዲህ ሲል ጻፈ:- “በማስጨነቅና [“በማዕቀብና፣” NW ] በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?” (ኢሳይያስ 53:8) ኢየሱስ በመጨረሻ በጠላቶቹ ሲወሰድ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹ “ማዕቀብ” አድርገዋል። እንዲህ ሲባል ግን በኢየሱስ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ከመግለጽ ታቅበዋል ማለት አይደለም። ማዕቀብ ያደረጉት በፍትሕ ላይ ነው። የግሪክኛው የሰፕቱጀንት ትርጉም ኢሳይያስ 53:8 ላይ “ማዕቀብ” በሚለው ቃል ፋንታ “ውርደት” የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። የኢየሱስ ጠላቶች አንድ ተራ ወንጀለኛ እንኳ ሊያገኘው የሚገባውን መብት በመንፈግ አዋርደውታል። የኢየሱስን ጉዳይ ያየው ችሎት ለይስሙላ የተቀመጠ ነበር። እንዴት?
27. የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች በኢየሱስ ላይ የተመሠረተውን ክስ በመረመሩበት ጊዜ የትኞቹን ደንቦች ጥሰዋል? የአምላክን ሕግ የጣሱትስ በምን መንገዶች ነው?
27 የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስን ለማጥፋት ቆርጠው ተነስተው ስለነበረ የራሳቸውን ደንብ እንኳ ሳይቀር ጥሰዋል። ሲወርድ ሲዋረድ የኖረው ወግና ሥርዓት እንደሚለው የሳንሄድሪን ሸንጎ በሞት ሊያስቀጣ የሚችል ከባድ ወንጀልን መመርመር የሚችለው በሊቀ ካህናቱ ቤት ሳይሆን በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ በሚገኘው በተጠረቡ ድንጋዮች በተሠራው አዳራሽ ውስጥ ብቻ ነው። እንዲህ ያለው የፍርድ ሂደት ቀን ላይ ካልሆነ በስተቀር ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ መካሄድ አይችልም ነበር። በሞት ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል ተከስሶ ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘ ሰው ላይ የሚተላለፈው ብያኔ የሚገለጸው ችሎቱ ወንጀሉን በመረመረበት ዕለት ሳይሆን በማግስቱ ነው። በመሆኑም በሰንበት ወይም በበዓል ዋዜማ ምንም ዓይነት የፍርድ ጉዳይ ማየት አይቻልም ነበር። በኢየሱስ ላይ የተመሠረተው ክስ በታየበት ጊዜ ግን እነዚህ ሁሉ ደንቦች ተጥሰዋል። (ማቴዎስ 26:57-68) ከሁሉ የከፋው ደግሞ የሃይማኖት መሪዎቹ የአምላክን ሕግ በግልጽ መጣሳቸው ነው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስን ለመያዝ ሲሉ ጉቦ ሰጥተዋል። (ዘዳግም 16:19፤ ሉቃስ 22:2-6) የሐሰት ምሥክሮችን ቃል ተቀብለዋል። (ዘጸአት 20:16፤ ማርቆስ 14:55, 56) ከዚህም በተጨማሪ ነፍሰ ገዳይ የሆነን ሰው ለማስለቀቅ በማሴር ራሳቸውንም ሆነ ምድሪቱን የደም ባለዕዳ አድርገዋል። (ዘኍልቁ 35:31-34፤ ዘዳግም 19:11-13፤ ሉቃስ 23:16-25) በመሆኑም ትክክለኛና ከአድልዎ ነፃ የሆነ ብያኔ ለመስጠት የሚያስችል “ፍርድ” ወይም ፍትሐዊ የሆነ የምርመራ ሂደት አልነበረም።
28. የኢየሱስ ጠላቶች ሳያስተውሉት የቀሩት ነገር ምንድን ነው?
28 የኢየሱስ ጠላቶች ችሎት ፊት የቀረበውን ሰው ትክክለኛ ማንነት ለማጣራት ሞክረዋል? ኢሳይያስም “ከትውልዱ ማን አስተዋለ?” በማለት ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቧል። ‘ትውልድ’ የሚለው ቃል የአንድን ሰው የዘር ሃረግ ወይም ያለፈ ታሪክ ሊያመለክት ይችላል። ኢየሱስ ተከስሶ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረበ ጊዜ የሸንጎው አባላት ያለፈ ታሪኩን ማለትም አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ ሊያሟላቸው የሚገቡትን ብቃቶች ሁሉ እንዳሟላ ሳያስተውሉ ቀርተዋል። ከዚህ ይልቅ አምላክን ሰድቧል ብለው በመወንጀል ሞት ፈረዱበት። (ማርቆስ 14:64 የ1980 ትርጉም ) በመጨረሻም የሮማው ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ሕዝቡ ባሳደረበት ተጽዕኖ ተገፋፍቶ ኢየሱስ እንዲሰቀል ፈረደበት። (ሉቃስ 23:13-25) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ገና በ33 ዓመት ተኩል ዕድሜው በሕይወቱ አጋማሽ ላይ “ተወገደ” ወይም ተቀጨ።
29. የኢየሱስ መቃብር ‘ከክፉዎችና ከባለጠጎች ጋር’ የሆነው እንዴት ነው?
29 ኢሳይያስ በመቀጠል የመሲሑን ሞትና መቃብር በተመለከተ እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፣ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ፤ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፣ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም ነበር።” (ኢሳይያስ 53:9) ኢየሱስ አሟሟቱም ሆነ መቃብሩ ከክፉዎችና ከባለጠጎች ጋር የሆነው እንዴት ነው? ኒሳን 14, 33 እዘአ ላይ ከኢየሩሳሌም ቅጥር ውጪ በተተከለ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሞተ። በሁለት ክፉ አድራጊዎች መካከል የተሰቀለ በመሆኑ መቃብሩ ከክፉዎች ጋር ነበረ ሊባል ይችላል። (ሉቃስ 23:33) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ባለጠጋ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ ራሱን በማደፋፈር የኢየሱስን አስከሬን አውርዶ ለመቅበር እንዲፈቀድለት ጲላጦስን ጠየቀው። ከኒቆዲሞስ ጋር ሆነው አስከሬኑን ከገነዙ በኋላ ዮሴፍ ለራሱ ባስወቀረው አዲስ መቃብር ውስጥ ቀበሩት። (ማቴዎስ 27:57-60፤ ዮሐንስ 19:38-42) በመሆኑም የኢየሱስ መቃብር ከባለጠጎች ጋርም ሊሆን ችሏል።
‘ይሖዋ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ’
30. ይሖዋ ኢየሱስን ማድቀቁ ያስደሰተው ከምን አንጻር ነው?
30 ኢሳይያስ በመቀጠል አንድ ግር የሚያሰኝ ነገር ተናገረ:- “እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፣ ዕድሜውም ይረዝማል፣ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፣ ኃጢአታቸውንም ይሸከማል።” (ኢሳይያስ 53:10, 11) ይሖዋ ይህ ታማኝ አገልጋይ እንዲደቅቅ እንዴት ይፈቅዳል? እጅግ በሚወድደው ልጁ ላይ መከራውን ያመጣው ይሖዋ ራሱ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። በኢየሱስ ላይ ለደረሰው መከራ ሁሉ ተጠያቂዎቹ ጠላቶቹ ናቸው። ይሁን እንጂ ይሖዋ እነዚህ ሰዎች በልጁ ላይ የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙ ፈቅዷል። (ዮሐንስ 19:11) ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ርኅሩኅና አዛኝ የሆነው አምላክ ልጁ ባልሠራው ጥፋት ሲሰቃይ ሲያይ ምን ያህል ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። (ኢሳይያስ 63:9፤ ሉቃስ 1:77, 78) ኢየሱስ ይሖዋን ሊያሳዝን የሚችል አንዳች ነገር አልሠራም። ሆኖም ኢየሱስ በኋላ ለሚመጡት በረከቶች ሲል መከራውን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑ ይሖዋን እጅግ አስደስቶታል።
31. (ሀ) ይሖዋ የኢየሱስን ነፍስ “ስለ ኃጢአት መሥዋዕት” ያደረገው በምን መንገድ ነው? (ለ) ኢየሱስ ሰው ሆኖ ብዙ መከራዎች ከደረሱበት በኋላ ምን ነገር እጅግ አስደስቶት መሆን አለበት?
31 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ መከራውን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑ ይሖዋ የኢየሱስን ነፍስ “ስለ ኃጢአት መሥዋዕት” ለማድረግ አስችሎታል። በመሆኑም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ባረገበት ጊዜ የኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ የሠዋውን የሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ በይሖዋ ፊት ያቀረበ ሲሆን ይሖዋም ለመላው የሰው ዘር ቤዛ አድርጎ በደስታ ተቀብሎታል። (ዕብራውያን 9:24፤ 10:5-14) ኢየሱስ ባቀረበው የኃጢአት መሥዋዕት አማካኝነት ‘ዘር’ አግኝቷል። “የዘላለም አባት” እንደመሆኑ መጠን በፈሰሰው ደሙ ለሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት መስጠት ይችላል። (ኢሳይያስ 9:6) ኢየሱስ ሰው ሆኖ ያን ሁሉ መከራ በማሳለፍ የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት የሚያስችል መሠረት በመጣሉ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት! በአቋሙ መጽናቱ ሰማያዊ አባቱ ቀንደኛ ባላጋራው ለሆነው ለሰይጣን ዲያብሎስ ስድብ መልስ ለመስጠት እንዳስቻለው ማወቁ ደግሞ ይበልጥ እንደሚያስደስተው ጥርጥር የለውም።—ምሳሌ 27:11
32. ኢየሱስ ‘ብዙ ሰዎችን የሚያጸድቀው’ በየትኛው ‘እውቀት’ አማካኝነት ነው? ይህን የጽድቅ አቋም የሚያገኙትስ እነማን ናቸው?
32 ኢየሱስ መሞቱ ያስገኘው ሌላው በረከት በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሳይቀር ‘ብዙ ሰዎችን ማጽደቅ’ መቻሉ ነው። ኢየሱስ ይህን የሚያደርገው “በእውቀቱ” እንደሆነ ኢሳይያስ ተናግሯል። ይህ እውቀት ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመጣበትና አምላክን በመታዘዙ ምክንያት አላግባብ መከራ በደረሰበት ጊዜ ያገኘው እውቀት መሆን አለበት። (ዕብራውያን 4:15) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ መከራን በመቀበል ሌሎች የጽድቅ አቋም እንዲያገኙ የሚረዳ መሥዋዕት ማቅረብ ችሏል። ይህን የጽድቅ አቋም የሚያገኙት እነማን ናቸው? በመጀመሪያ ቅቡዓን ተከታዮቹ ናቸው። በኢየሱስ መሥዋዕት ስለሚያምኑ ይሖዋ ጻድቃን ብሎ በመጥራት ልጆቹ አድርጎ የሚቀበላቸው ከመሆኑም በላይ ከኢየሱስ ጋር አብረው ወራሾች እንዲሆኑ ያደርጋል። (ሮሜ 5:19፤ 8:16, 17) ከዚህም ሌላ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም የሚያምኑ ‘የሌሎች በጎች’ አባላት የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” የጽድቅ አቋም የሚያገኙ ሲሆን ይህም የአምላክ ወዳጆች የመሆንና ከአርማጌዶን የመትረፍ መብት ያስገኝላቸዋል።—ራእይ 7:9፤ 16:14, 16፤ ዮሐንስ 10:16፤ ያዕቆብ 2:23, 25
33, 34. (ሀ) ይሖዋን በተመለከተ ምን አስደሳች ነገር እንማራለን? (ለ) ከመሲሐዊው አገልጋይ ጋር ‘ድርሻቸውን’ የሚካፈሉት “ብዙዎች” እነማን ናቸው?
33 በመጨረሻም ኢሳይያስ መሲሑ የሚጎናጸፈውን ድል እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል [“ድርሻውን ከታላላቆች ጋር እሰጠዋለሁ፣” አ.መ.ት ]፣ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፣ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፣ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።”—ኢሳይያስ 53:12
34 በዚህኛው የኢሳይያስ ትንቢት ክፍል ላይ የሚገኙት የመደምደሚያ ቃላት ይሖዋን በተመለከተ አንድ እጅግ አስደሳች የሆነ እውነታ እንድንገነዘብ ያደርጉናል። ይሖዋ ለእሱ ታማኝ የሆኑትን ሁሉ ከፍ አድርጎ ይመለከታል። “ድርሻውን ከታላላቆች ጋር እሰጠዋለሁ” ሲል ለመሲሐዊ አገልጋዩ የገባው ቃል ይህን የሚጠቁም ነው። ይህ አነጋገር በጦርነት የተገኘ ምርኮን ከመከፋፈል ልማድ ጋር በተያያዘ የመጣ ይመስላል። ይሖዋ ኖኅን፣ አብርሃምንና ኢዮብን ጨምሮ በጥንት ዘመን የነበሩ “ብዙ” የእምነት ሰዎች ያሳዩትን ታማኝነት የሚያደንቅ ከመሆኑም በላይ በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ‘ድርሻቸውን’ ይሰጣቸዋል። (ዕብራውያን 11:13-16) ለመሲሐዊ አገልጋዩም ልክ እንደዚሁ ድርሻውን ይሰጠዋል። በእርግጥም ይሖዋ፣ ኢየሱስ ላሳየው ጽኑ አቋም ወሮታውን መክፈሉ የማይቀር ነው። እኛም ይሖዋ ‘ያደረግነውን ሥራ ለስሙም ያሳየነውን ፍቅር እንደማይረሳ’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዕብራውያን 6:10
35. ከኢየሱስ ጋር ምርኮ የሚካፈሉት “ኃያላን” እነማን ናቸው? ምርኮውስ ምንድን ነው?
35 በተጨማሪም የአምላክ አገልጋይ በጠላቶቹ ላይ ድል በመቀዳጀት የጦርነት ምርኮ ያገኛል። ይህን ምርኮ ደግሞ “ከኃያላን” ጋር ይከፋፈላል። እነዚህ “ኃያላን” እነማንን ያመለክታሉ? እንደ ኢየሱስ ዓለምን ድል ያደረጉት የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ማለትም 144, 000ዎቹ ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ናቸው። (ገላትያ 6:16፤ ዮሐንስ 16:33፤ ራእይ 3:21፤ 14:1) ምርኮውስ እነማንን ያመለክታል? ይህ ምርኮ ኢየሱስ ከሰይጣን መዳፍ አላቅቆ ለክርስቲያን ጉባኤ የሚሰጣቸውን ‘የወንዶች ሥጦታዎች’ እንደሚጨምር ግልጽ ነው። (ኤፌሶን 4:8-12) ከዚህም በተጨማሪ 144, 000ዎቹ “ኃያላን” ሌላ ምርኮም ይካፈላሉ። በዓለም ላይ የሚቀዳጁት ድል ሰይጣን፣ አምላክን ለመስደብ ሰበብ አድርጎ የሚጠቀምበትን ነገር ሁሉ እንዲያጣ ያደርገዋል። ለይሖዋ ያላቸው የጸና አቋም አምላካቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ልቡን ደስ ያሰኘዋል።
36. ኢየሱስ ስለ አምላክ አገልጋይ የተነገረውን ትንቢት እየፈጸመ መሆኑን ተገንዝቦ ነበርን? አብራራ።
36 ኢየሱስ ስለ አምላክ አገልጋይ የተነገረውን ትንቢት እየፈጸመ እንዳለ ተገንዝቦ ነበር። በተያዘበት ሌሊት በኢሳይያስ 53:12 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ቃላት በመጥቀስ በእሱ ላይ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ተናግሯል:- “እላችኋለሁና፣ ይህ:- ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፣ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው።” (ሉቃስ 22:36, 37) በእርግጥም ኢየሱስ እንደ ዓመፀኛ ተደርጎ ተቆጥሯል። ሕግ ይጥሳል በሚል ክስ ተወንጅሎ በሁለት ዘራፊዎች መካከል ተሰቀለ። (ማርቆስ 15:27) ሆኖም ይህን ውርደት በፈቃደኝነት የተሸከመው ለእኛ እየማለደ መሆኑን በሚገባ በመገንዘብ ነው። በኃጢአተኞችና በሞት ቅጣት መካከል የቆመ ያህል የነበረ ሲሆን ቅጣቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኗል።
37. (ሀ) ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ሞት የሚናገረው ታሪካዊ ዘገባ ምን ነገር ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል? (ለ) ለይሖዋ አምላክና ከፍ ከፍ ለተደረገው አገልጋዩ ለኢየሱስ ክርስቶስ አመስጋኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
37 ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ሞት የሚናገረው ታሪካዊ ዘገባ በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የተጠቀሰው መሲሐዊ አገልጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በትክክል ለይተን እንድናውቅ ያስችለናል። ይሖዋ እኛ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ መውጣት እንድንችል ውድ ልጁ በመሠቃየትና በመሞት ለአገልጋዩ የተሰጠውን ትንቢታዊ ተልዕኮ እንዲፈጽም በመፍቀዱ ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይገባናል! ይሖዋ ይህን በማድረግ ለእኛ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። ሮሜ 5:8 “ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” ይላል። በፈቃደኝነት ነፍሱን ለሞት የሰጠውና ከፍ ከፍ የተደረገው አገልጋይ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ላሳየን ፍቅርም እጅግ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በጄ ኤፍ ስቴኒንግ የተተረጎመው የጆናታን ቤን ኡዝኤል የአረማይክ ጽሑፍ (መጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ) ኢሳይያስ 52:13ን እንዲህ ሲል ፈትቶታል:- “እነሆ፣ የተቀባው አገልጋዬ (ወይም መሲሑ ) ይከናወንለታል።” በተመሳሳይም የባቢሎናውያን ታልሙድ (ሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ገደማ) እንዲህ ይላል:- “መሲሑ ስሙ ማን ነው? . . . ‘ሕመማችንን ተሸከመ’ ተብሎ እንደተነገረ ከረቢዎች ወገን የሆኑት [ሰዎች ሕመምተኛው ይሉታል]።”—ሳንሄድሪን 98ለ፤ ኢሳይያስ 53:4
b ነቢዩ ሚክያስ ቤተ ልሔምን “በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ” ሲል ገልጿት ነበር። (ሚክያስ 5:2) ይሁን እንጂ መሲሑ በዚህች አነስተኛ ከተማ ውስጥ በመወለዱ ቤተ ልሔም የማይገኝ ልዩ ክብር ልትጎናጸፍ ችላለች።
c “ተመታ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ከሥጋ ደዌ ጋር በተያያዘም ይሠራበታል። (2 ነገሥት 15:5 አ.መ.ት ) ምሁራን እንደሚሉት አንዳንድ አይሁዳውያን መሲሑ በሥጋ ደዌ ይመታል የሚለውን አስተሳሰብ ያመነጩት በኢሳይያስ 53:4 ላይ ተመርኩዘው ነው። የባቢሎናውያን ታልሙድ ይህን ጥቅስ መሲሑን ለማመልከት የተጠቀመበት ሲሆን “በሥጋ ደዌ የተያዘው ምሁር” ሲል ጠርቶታል። ዱዌይ ቨርሽን የተባለው የካቶሊክ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በላቲኑ ቩልጌት ላይ የሰፈረውን ሐሳብ በማንጸባረቅ ይህን ጥቅስ “በሥጋ ደዌ እንደተያዘ አድርገን ቆጠርነው” ሲል ተርጉሞታል።
[በገጽ 212 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የይሖዋ አገልጋይ
ኢየሱስ ተልዕኮውን የፈጸመበት መንገድ
ትንቢት
ክንውን
ፍጻሜ
ከፍ ከፍ አለ፣ ታላቅም ሆነ
ሥራ 2:34-36፤ ፊልጵ. 2:8-11፤ 1 ጴጥ. 3:22
ስሙን አላግባብ አጥፍተዋል፣ አዋርደውታል
ማቴ. 11:19፤ 27:39-44, 63, 64፤ ዮሐ. 8:48፤ 10:20
ብዙ አሕዛብን ያስደንቃል
ማቴ. 24:30፤ 2 ተሰ. 1:6-10፤ ራእይ 1:7
አላመኑበትም
ዮሐ. 12:37, 38፤ ሮሜ 10:11, 16, 17
ዝቅተኛና ተራ ከሆነ ቤተሰብ ተወለደ
ናቁት፣ ጠሉት
ማቴ. 26:67፤ ሉቃስ 23:18-25፤ ዮሐ. 1:10, 11
ደዌያችንን ተሸከመ
ተወጋ
ሌሎች ለፈጸሙት በደል መከራ ተቀበለ
በከሳሾቹ ፊት አፉን አልከፈተም አቤቱታም አላሰማም
ማቴ. 27:11-14፤ ማር. 14:60, 61፤ ሥራ 8:32, 35
አግባብ ባልሆነ መንገድ ተወንጅሎ ተፈረደበት
ማቴ. 26:57-68፤ 27:1, 2, 11-26፤ ዮሐ. 18:12-14, 19-24, 28-40
ከባለጠጎች ጋር ተቀበረ
ነፍሱ ለኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ቀረበ
ብዙዎች የጽድቅ አቋም እንዲያገኙ በሩን ከፈተ
ሮሜ 5:18, 19፤ 1 ጴጥ. 2:24፤ ራእይ 7:14
ከኃጢአተኞች ጋር ተቆጠረ
ማቴ. 26:55, 56፤ 27:38፤ ሉቃስ 22:36, 37
[በገጽ 203 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘በሰዎች የተናቀ ነበር’
[በገጽ 206 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“አፉን አልከፈተም”
[ምንጭ]
በአንቶኒዮ ቺሴሪ ከተዘጋጀው “ኤከ ሆሞ” የተወሰደ
[በገጽ 211 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአል”