የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 23—ኢሳይያስ
ጸሐፊው:- ኢሳይያስ
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ.ል.በፊት ከ732 በኋላ
የሚሸፍነው ጊዜ:-
ከክ.ል.በፊት ከ778 እስከ 732 በኋላ
ጨካኝ የሆነው የአሦር ንጉሠ ነገሥት ከሚሰነዝረው ጥቃት የተነሳ በመካከለኛው ምሥራቅ ይገኙ በነበሩት ታላላቅና ታናናሽ መንግሥታት ላይ የስጋት ደመና አንዣብቧል። በአካባቢው የሚወራው ወታደራዊ ቅንጅት ስለመፍጠርና ፖለቲካዊ ሴራ ስለመፈጸም ነበር። (ኢሳ. 8:9-13) በስተ ሰሜን ትገኝ የነበረችው ከሐዲዋ እስራኤል ብዙ ሳትቆይ በዚህ ብሔራት አቀፍ ውዥንብር ውስጥ ትገባለች። በስተ ደቡብ ያሉት የይሁዳ ነገሥታትም ቢሆኑ መንግሥታቸው አስተማማኝ አልነበረም። (2 ነገ. ከምዕራፍ 15 እስከ 21) አዳዲስ የጦር መሣሪያዎች ተፈልስፈው ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር። ይህ ደግሞ በወቅቱ የነበረውን ስጋት አባብሶታል። (2 ዜና 26:14, 15) ታዲያ ጥበቃና ደህንነት ከየት ሊገኝ ይችላል? የይሖዋ ስም በትንሿ የይሁዳ መንግሥት ይኖሩ ከነበሩት ካህናትና ሕዝቦች አፍ ያልተለየ ቢሆንም ልባቸው ግን በመጀመሪያ ወደ አሦር በኋላ ደግሞ ወደ ግብጽ ሸፍቶ ነበር። (2 ነገ. 16:7፤ 18:21) በይሖዋ ኃይል ላይ የነበራቸው እምነት በእጅጉ ተዳክሟል። ግልጽ የሆነ የጣዖት አምልኮ በማያካሂዱትም መካከል እውነተኛ በሆነ አምላካዊ ፍርሃት ሳይሆን በወግና በሥርዓት ላይ የተመሠረተ የግብዝነት አምልኮ ተስፋፍቶ ነበር።
2 ታዲያ ይሖዋን ወክሎ ማን ይናገር? የማዳን ኃይሉንስ ማን ያሳውቅ? አንድ ሰው “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” በማለት ዝግጁ መሆኑን የሚያሳይ መልስ ሰጠ። ይህን ምላሽ የሰጠው ከዚህ ቀደም ብሎም ትንቢት ይናገር የነበረው ኢሳይያስ ነው። ወቅቱ 778 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ሲሆን በለምጽ ደዌ የተመታው ንጉሥ ዖዝያን የሞተው በዚሁ ዓመት ነበር። (ኢሳ. 6:1, 8) ኢሳይያስ የሚለው ስም ትርጉም “የይሖዋ ማዳን” ማለት ሲሆን ኢየሱስ (“ይሖዋ ድነት ነው”) ከሚለው ስም ጋር አንድ ዓይነት ትርጉም አለው። የኢሳይያስ ትንቢት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ይህን ሐቅ፣ ማለትም ይሖዋ አዳኝ መሆኑን አጉልቶ ያሳያል።
3 ኢሳይያስ የአሞጽ ልጅ ነበር። (ይኼኛው አሞጽ የይሁዳ ነቢይ ከነበረው አሞጽ የተለየ ነው።) (1:1) ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ኢሳይያስ ልደትም ሆነ አማሟት የሚናገሩት ነገር የለም። የአይሁዳውያን አፈ ታሪክ ግን ክፉ የነበረው ንጉሥ ምናሴ በመጋዝ ተሰንጥቆ እንዲገደል እንዳደረገው ይተርካል። (ከዕብራውያን 11:37 ጋር አወዳድር።) ኢሳይያስ የጻፋቸው አንዳንድ ሐሳቦች ነቢይት ከነበረችው ሚስቱና ትንቢታዊ ስሞች ከነበሯቸው ወንዶች ልጆቹ ጋር በኢየሩሳሌም ይኖር እንደነበረ ያመለክታሉ፤ ኢሳይያስ ቢያንስ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት። (ኢሳ. 7:3፤ 8:1, 3) ኢሳይያስ ከ778 እስከ 732 ከክርስቶስ ልደት በፊት ይኸውም ዖዝያን ከሞተበት ዓመት ወይም ከዚያም በፊት ጀምሮ እስከ ሕዝቅያስ 14ኛ ዘመነ መንግሥት ድረስ ቢያንስ ለ46 ዓመታት፣ በአራት የይሁዳ ነገሥታት ዘመን (ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ) አገልግሏል። ትንቢቱን በጽሑፍ ያሰፈረው በዚህ የአገልግሎቱ ዘመን መገባደጃ ላይ እንደሆነ አያጠራጥርም። (1:1፤ 6:1፤ 36:1) በዘመኑ ይኖሩ የነበሩት ሌሎች ነቢያት በይሁዳ የነበረው ሚክያስ እንዲሁም በስተ ሰሜን ሆሴዕና ዖዴድ ናቸው።—ሚክ. 1:1፤ ሆሴዕ 1:1፤ 2 ዜና 28:6-9
4 ይሖዋ፣ ትንቢታዊ ፍርዶቹን በጽሑፍ እንዲያሰፍር ኢሳይያስን እንዳዘዘው ኢሳይያስ 30:8 ያረጋግጥልናል:- “አሁንም ሂድ፤ በሰሌዳ ላይ ጻፍላቸው፤ በጥቅልል መጽሐፍ ላይ ክተብላቸው፤ ለሚመጡትም ዘመናት፣ ለዘላለም ምስክር ይሆናል።” የጥንቶቹ አይሁዳውያን ረቢዎች የመጽሐፉ ጸሐፊ ኢሳይያስ መሆኑን የተቀበሉ ከመሆኑም በላይ ይህን የትንቢት መጽሐፍ ከዋነኞቹ የነቢያት መጻሕፍት (ኢሳይያስ፣ ኤርምያስና ሕዝቅኤል) የመጀመሪያው አድርገውታል።
5 አንዳንዶች ከምዕራፍ 40 በኋላ የመጽሐፉ የአጻጻፍ ዘይቤ ለየት ያለ መሆኑን በማመልከት ከዚያ በኋላ ያለው በሌላ ሰው ወይም “በሁለተኛ ኢሳይያስ” እንደተጻፈ ይናገራሉ፤ ሆኖም አጻጻፉ የተለወጠው የርዕሰ ጉዳይ ለውጥ በመኖሩ ነው። በስሙ የሚጠራውን መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ የጻፈው ኢሳይያስ ራሱ መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ‘የእስራኤል ቅዱስ’ የሚለው ሐረግ ከኢሳይያስ ምዕራፍ 1 እስከ 39 ድረስ 12 ጊዜ፣ ከምዕራፍ 40 እስከ 66 ደግሞ 13 ጊዜ በጠቅላላው 25 ጊዜ የሚገኝ ሲሆን በቀሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ግን ይህ አባባል የተጠቀሰው 6 ጊዜ ብቻ መሆኑ የመጽሐፉን አንድነት ያመለክታል። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ከሁሉም የትንቢቱ ክፍሎች በመጥቀስና ሁሉም የተጻፉት በኢሳይያስ መሆኑን በመግለጽ መጽሐፉ አንድ መሆኑን መስክሯል።—ሮሜ 10:16, 20፤ 15:12ን ከኢሳይያስ 53:1፤ 65:1፤ 11:1 ጋር አወዳድር።
6 ከ1947 ጀምሮ ባሉት ዓመታት በሙት ባሕር ሰሜናዊ ምዕራብ ዳርቻ አቅራቢያ ከሚገኘው ከኪርበት ኩምራን አጠገብ አንዳንድ የጥንት ሰነዶች ከነበሩበት የጨለማ ዋሻ ወጥተዋል። እነዚህ ሰነዶች የሙት ባሕር ጥቅልሎች ተብለው የሚጠሩ ሲሆን የኢሳይያስ ትንቢትም ይገኝባቸዋል። የኢሳይያስ ጥቅልል በጥሩ ሁኔታ ተጠብቆ በቆየው የቅድመ ማሶሪታውያን ዕብራይስጥ በሚያምር እጅ ጽሑፍ የተጻፈ ሲሆን የ2,000 ዓመት ዕድሜ አለው፤ ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ የተዘጋጀ መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም ይህ ጥቅልል፣ ለዘመናዊዎቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉሞች መሠረት ከሆኑትና በዘመናችን በእጅ ከሚገኙት ጥንታዊ የሚባሉ የማሶሪታውያን ጽሑፎች አንድ ሺህ ዓመት ያህል ቀድሞ የተጻፈ ነው። ከማሶሪታውያን ጽሑፍ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ የሆነ የፊደላትና የሰዋሰው ልዩነቶች ቢገኝበትም በመሠረተ ትምህርት ረገድ ግን ምንም ዓይነት ልዩነት የለውም። ይህም በአሁኑ ጊዜ በእጃችን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የመጀመሪያውን የኢሳይያስ መልእክት እንዳለ የያዘ ለመሆኑ አሳማኝ ማስረጃ ነው። ከዚህም በላይ እነዚህ ጥንታውያን ጥቅልሎች “ኢሳይያስ” የሚባሉ ሁለት ጸሐፊዎች እንደነበሩ የሚናገሩት ሐያሲያን ሐሳብ የተሳሳተ መሆኑን ያሳያሉ። ኢሳይያስ ምዕራፍ 40 የሚጀምረው ምዕራፍ 39 በሚገኝበት አምድ የመጨረሻ መስመር ላይ ሲሆን የመክፈቻው ዓረፍተ ነገር የሚያልቀው በሚቀጥለው አምድ ላይ ነው። ስለዚህ የመጽሐፉ ገልባጭ በዚህ ቦታ ላይ የጸሐፊ ለውጥ ተደርጓል ወይም መጽሐፉ እዚህ ቦታ ላይ ተከፍሏል ስለሚባለው ጉዳይ የሚያውቀው ነገር አልነበረም ማለት ነው።a
7 የኢሳይያስ ትንቢት በመንፈስ የተጻፈና ትክክለኛ መጽሐፍ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። ከሙሴ ሌላ የኢሳይያስን ያህል በክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ብዙ ጊዜ የተጠቀሰ ነቢይ የለም። በተጨማሪም የኢሳይያስ መጽሐፍ እውነተኛ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ታሪካዊና አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የአሦር ነገሥታት ታሪካዊ መዛግብት የሚገኙ ሲሆን የሰናክሬም ባለ ስድስት ጎን ጽላት በሚባለው በአንደኛው ላይ በኢየሩሳሌም ላይ ያደረገውን ከበባ ራሱ ሰናክሬብ ተርኳል።b (ኢሳ. ምዕ. 36, 37) በአንድ ወቅት የባቢሎን ከተማ በነበረችበት ቦታ የሚታየው የፍርስራሽ ክምር ኢሳይያስ 13:17-22 በትክክል መፈጸሙን አሁንም ድረስ ይመሠክራል።c ኢሳይያስ ከ200 ዓመታት ገደማ በፊት ስሙን ጠቅሶ የጻፈለት ንጉሥ ቂሮስ ነጻ አውጥቷቸው ከባቢሎን ምርኮ የተመለሱት በሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያንም ሕያው ምሥክሮች ናቸው። ቂሮስ ራሱ አይሁዳውያን ቀሪዎችን ነጻ ካወጣ በኋላ ይህን እንዲያደርግ ያዘዘው ይሖዋ መሆኑን ስለተናገረ የኢሳይያስን ትንቢታዊ ጽሑፍ ሳያሳዩት አልቀሩም።—ኢሳ. 44:28፤ 45:1፤ ዕዝራ 1:1-3
8 በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች ጎላ ብለው ይታያሉ። ኢሳይያስ ከተናገራቸው ትንቢቶች መካከል በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተፈጸሙት በጣም በርካታ በመሆናቸው “ወንጌላዊው ነቢይ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ላይ ለተጠቀሰው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአይሁድ ሕዝብ ለረዥም ዘመናት “ምሥጢራዊ ምዕራፍ” ሆኖ የኖረው ምዕራፍ 53 በኢየሱስ ላይ የደረሱትን ነገሮች በዝርዝር የሚተነብይ በመሆኑ የዓይን ምሥክር የሆነ ሰው የጻፈው ታሪክ ይመስላል። ከሚቀጥለው ንጽጽር መረዳት እንደሚቻለው የክርስቲያን ግሪክኛ ጽሑፎች የዚህን አስደናቂ ምዕራፍ ፍጻሜ መዝግበዋል:- ቁ. 1—ዮሐንስ 12:37, 38፤ ቁ. 2—ዮሐንስ 19:5-7፤ ቁ. 3—ማርቆስ 9:12፤ ቁ. 4—ማቴዎስ 8:16, 17፤ ቁ. 5—1 ጴጥሮስ 2:24፤ ቁ. 6—1 ጴጥሮስ 2:25፤ ቁ. 7—የሐዋርያት ሥራ 8:32, 35፤ ቁ. 8—የሐዋርያት ሥራ 8:33፤ ቁ. 9—ማቴዎስ 27:57-60፤ ቁ. 10—ዕብራውያን 7:27፤ ቁ. 11—ሮሜ 5:18፤ ቁ. 12—ሉቃስ 22:37። እንደዚህ ያለው ትክክለኛ ትንቢት ምንጭ ከአምላክ በቀር ሌላ ማን ሊሆን ይችላል?
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
34 የኢሳይያስ ትንቢታዊ መጽሐፍ ከየትኛውም አቅጣጫ ሲታይ እጅግ ጠቃሚ የሆነ የይሖዋ አምላክ ስጦታ ነው። ከፍተኛ የሆኑትን የአምላክ ሐሳቦች ያንጸባርቃል። (ኢሳ. 55:8-11) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በተመለከተ የሕዝብ ንግግር የሚያቀርቡ ወንድሞች፣ እንደ ኢየሱስ ምሳሌዎች ያሉ ለማስገንዘብ የተፈለገውን ነጥብ በትክክል የሚያስጨብጡ ጥሩ ምሳሌዎችን ከኢሳይያስ መጽሐፍ ሊያገኙ ይችላሉ። ኢሳይያስ አንድ ዛፍ ቆርጦ ገሚሱን ለማገዶ ገሚሱን ደግሞ ለአምልኮ የሚሆን ጣዖት ለመሥራት የሚያውል ሰው ምን ያህል ሞኝ እንደሆነ ያስገነዝበናል። ለቁመቱ በማይበቃ አጭር አልጋ ላይ ሙሉ ሰውነቱን ሊሸፍን የማይችል ጠባብ ብርድ ልብስ ለብሶ የተኛ ሰው ምን ያህል እንደሚቸገር እንዲሰማን ያደርጋል። ነቢያቱን ለመጮኽ እንኳ ከሰነፉ ድምፅ የለሽ ውሾች ጋር በማመሳሰል ምን ያህል ከባድ እንቅልፍ ጥሏቸው እንደነበረ እንድናስተውል ያስችለናል። ኢሳይያስ እንደሚመክረው እኛ ራሳችን ‘የእግዚአብሔርን ቃል ብንመለከትና ብናነብ’ ስለ አሁኑ ዘመን የተናገረውን ጠንካራ መልእክት መረዳት እንችላለን።—44:14-20፤ 28:20፤ 56:10-12፤ 34:16
35 ትንቢቱ በይበልጥ የሚያተኩረው በመሲሑ በሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ላይ ነው። ከሁሉ በላይ የሆነው ንጉሥ ይሖዋ ሲሆን የሚያድነንም እርሱ ነው። (33:22) የመሲሑ ቦታስ ምንድን ነው? መልአኩ የሚወለደውን ሕፃን አስመልክቶ ለማርያም የተናገረው መልእክት፣ የኢሳይያስ 9:6, 7 ትንቢት የሚፈጸመው ሕፃኑ የዳዊትን ዙፋን ሲቀበልና “በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም” የሚለው ቃል ሲፈጸም እንደሆነ ያመለክታል። (ሉቃስ 1:32, 33) ማቴዎስ 1:22, 23፣ ኢየሱስ ከድንግል መወለዱ የኢሳይያስ 7:14 ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነና “አማኑኤል” ተብሎ እንደሚጠራም ያመለክታል። ይህ ከሆነ 30 ከሚያክሉ ዓመታት በኋላ አጥማቂው ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” እያለ መስበክ ጀመረ። አራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች ዮሐንስ “በበረሓ የሚጮኽ ድምፅ” የተባለው ሰው መሆኑን ለማሳየት ኢሳይያስ 40:3ን ጠቅሰዋል። (ማቴ. 3:1-3፤ ማር. 1:2-4፤ ሉቃስ 3:3-6፤ ዮሐ. 1:23) ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ መሲሕ፣ ማለትም የይሖዋ ቅቡዕ እንዲሁም አሕዛብን የሚገዛ የእሴይ ቁጥቋጥ ወይም ሥር ሆነ። በኢሳይያስ 11:1, 10 ፍጻሜ መሠረት አሕዛብ ሁሉ ተስፋ ማድረግ የሚኖርባቸው ይህንን መሲሕ ነው።—ሮሜ 15:8, 12
36 ኢሳይያስ በመቀጠል ንጉሥ የሚሆነውን መሲሕ እንዴት እንደገለጸ ተመልከት! ኢየሱስ፣ የይሖዋ ቅቡዕ መሆኑን ለማሳየት ስለተሰጠው ተልዕኮ የሚገልጸውን ክፍል ከኢሳይያስ ጥቅልል ላይ ካነበበ በኋላ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል” መስበኩን ቀጠለ፤ ይህን ያደረገበትንም ምክንያት ሲገልጽ “የተላክሁት ለዚሁ ዐላማ ነው” ብሏል። (ሉቃስ 4:17-19, 43፤ ኢሳ. 61:1, 2) አራቱ ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት እንዲሁም በኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ላይ ስለተተነበየው የአሟሟቱ ሁኔታ በርካታ ዘገባዎችን በዝርዝር አስፍረዋል። አይሁዳውያን የመንግሥቱን ምሥራች ቢሰሙና የኢየሱስን ድንቅ ተአምራት ቢመለከቱም ልባቸው ደንዳና ስለነበር ትርጉሙ አልገባቸውም። ይህም የሆነው በኢሳይያስ 6:9, 10፤ 29:13 እና 53:1 ፍጻሜ መሠረት ነው። (ማቴ. 13:14, 15፤ ዮሐ. 12:38-40፤ ሥራ 28:24-27፤ ሮሜ 10:16፤ ማቴ. 15:7-9፤ ማር. 7:6, 7) በኢሳይያስ 8:14 እና 28:16 ፍጻሜ መሠረት ኢየሱስ ለእነርሱ የማሰናከያ ድንጋይ ቢሆንም ይሖዋ በጽዮን የተከለው መሠረትና መንፈሳዊ ቤቱን የሚገነባበት የማዕዘን ድንጋይ ሆኗል።—ሉቃስ 20:17፤ ሮሜ 9:32, 33፤ 10:11፤ 1 ጴጥ. 2:4-10
37 የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት የኢሳይያስን ትንቢት በአገልግሎታቸው ላይ ጥሩ አድርገው ተጠቅመውበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ እምነት ለመገንባት ሰባኪዎች እንደሚያስፈልጉ ለማመልከት ከኢሳይያስ ትንቢት ጠቅሶ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ብሏል። (ሮሜ 10:15፤ ኢሳ. 52:7፤ በተጨማሪም ሮሜ 10:11, 16, 20, 21ን ተመልከት።) ጴጥሮስም የምሥራቹን ዘላለማዊነት ለማሳየት ከኢሳይያስ ትንቢት በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “መጽሐፍ እንደሚል፣ ‘ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው። ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።’ የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይህ ነው።”—1 ጴጥ. 1:24, 25፤ ኢሳ. 40:6-8
38 ኢሳይያስ መጪውን የአምላክ መንግሥት ተስፋ በጣም ውብ በሆነ ሁኔታ ገልጾታል! ‘ንጉሥ በጽድቅ የሚነግሥበት፣’ መሳፍንትም በፍትሕ የሚገዙበት ‘አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ይመጣል። ምንኛ የሚያስደስትና የሚያስፈነድቅ ተስፋ ነው! (65:17, 18፤ 32:1, 2) ጴጥሮስ አስደሳች የሆነውን የኢሳይያስን መልእክት በድጋሚ በመጥቀስ “እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር [በአምላክ] ተስፋ [ቃል] መሠረት እንጠባበቃለን” ብሏል። (2 ጴጥ. 3:13) ይህ አስደናቂ የሆነ የአምላክ መንግሥት ጭብጥ በራእይ መጽሐፍ የመደምደሚያ ምዕራፎች ላይ በጣም ውብ በሆነ አገላለጽ ተጠቃሏል።—ኢሳ. 66:22, 23፤ 25:8፤ ራእይ 21:1-5
39 የኢሳይያስ መጽሐፍ የይሖዋን ጠላቶችና በግብዝነት አገልጋዮቹ ነን የሚሉትን ሰዎች የሚያወግዝ ከባድ መልእክት የያዘ ቢሆንም ታላቅ የሆነው የይሖዋ ስም ስለሚቀደስበት የመሲሐዊ መንግሥት ተስፋ ውብ በሆኑ ቃላት ይናገራል። የይሖዋን መንግሥት አስደናቂ እውነቶች ከመግለጹም በላይ ‘ማዳኑን’ በደስታ እንድንጠባበቅ ልባችንን ያነሳሳል።—ኢሳ. 25:9፤ 40:28-31
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1 ገጽ 1221-1223
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1 ገጽ 957፤ ጥራዝ 2 ገጽ 894-895
c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 2 ገጽ 324