ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶች
አይሁዳውያን፣ ኢሳይያስን ጨምሮ ሌሎች ነቢያት መሲሑን አስመልክተው የተናገሯቸውን ትንቢቶች ስለሚያውቁ የመሲሑን መምጣት ይጠብቁ ነበር። እንዲያውም በኢየሱስ ዘመን ብዙ አይሁዳውያን የመሲሑን መገለጥ ‘በጕጕት ይጠባበቁ’ ነበር። (ሉቃስ 3:15) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የመሲሑን ሕይወት አስመልክተው አስደናቂ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዙ መሆናቸው ትኩረት የሚስብ ነው። ማንም ሰው እነዚህን ዝርዝር ጉዳዮች አስቀድሞ መናገርም ሆነ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ እንዲፈጸሙ ሁኔታውን ማመቻቸት አይችልም።
ከመሲሑ መወለድ ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮች። ኢሳይያስ፣ መሲሑ ወይም ክርስቶስ ከድንግል እንደሚወለድ አስቀድሞ ተናግሯል። ሐዋርያው ማቴዎስ የኢየሱስን ተአምራዊ አወላለድ ከገለጸ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ጌታ በነቢዩ እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ፤ ‘እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች።’” (ማቴዎስ 1:22, 23፤ ኢሳይያስ 7:14) በተጨማሪም ኢሳይያስ፣ የዳዊት አባት የሆነውን እሴይን በስም በመጥቀስ ክርስቶስ በዳዊት የዘር ሐረግ እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሯል። በእርግጥም ኢየሱስ የመጣው ከዳዊት የዘር ሐረግ ነው። (ማቴዎስ 1:6, 16፤ ሉቃስ 3:23, 31, 32) በመሆኑም መልአኩ ገብርኤል፣ ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት የኢየሱስ እናት ለሆነችው ለማርያም “አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል” ብሏታል።—ሉቃስ 1:32, 33፤ ኢሳይያስ 11:1-5, 10፤ ሮሜ 15:12
ከመሲሑ ሕይወት ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮች። ኢየሱስ ካደገ በኋላ በናዝሬት በሚገኝ አንድ ምኩራብ ውስጥ በመግባት ድምፁን ከፍ አድርጎ ከኢሳይያስ ትንቢት ላይ የተወሰነ ክፍል አንብቦ ነበር። ኢየሱስ ካነበበው መካከል የሚከተለው ሐሳብ ይገኝበታል፦ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛል።” ኢየሱስ ትንቢቱ የሚናገረው ስለ እሱ መሆኑን ሲገልጽ “ይህ በጆሮአችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” ብሏል። (ሉቃስ 4:17-21፤ ኢሳይያስ 61:1, 2) በተጨማሪም ኢሳይያስ፣ ኢየሱስ ፈውስ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች በደግነት፣ በየዋህነትና በትሕትና እንደሚይዛቸው ትንቢት ተናግሯል። ማቴዎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ ሕመምተኞችን ሁሉ ፈወሰ፤ ማንነቱን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤ . . . ‘አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ . . . የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም።’”—ማቴዎስ 8:16, 17፤ 12:10-21፤ ኢሳይያስ 42:1-4፤ 53:4, 5
መሲሑ ከሚደርስበት ሥቃይ ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮች። ኢሳይያስ፣ አብዛኞቹ እስራኤላውያን መሲሑን እንደማይቀበሉት እንዲያውም ‘የሚያሰናክል ዐለት’ እንደሚሆንባቸው ትንቢት ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 2:6-8፤ ኢሳይያስ 8:14, 15) ኢየሱስ በርካታ ተአምራትን የፈጸመ ቢሆንም ሕዝቡ “አላመኑበትም፤ ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ምስክርነታችንን ማን አመነ? . . .’ ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው።” (ዮሐንስ 12:37, 38፤ ኢሳይያስ 53:1) አይሁዳውያን፣ የኢየሱስን መሲሕነት እንዳይቀበሉ አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ መሲሑ ወዲያውኑ ከሮም አገዛዝ ነፃ በማውጣት የዳዊትን ሥርወ መንግሥት በድጋሚ በምድር ላይ እንዲቋቋም ያደርጋል የሚል የተሳሳተ እምነት የነበራቸው መሆኑ ነው። ኢየሱስ ተሠቃይቶ በመሞቱ አብዛኞቹ አይሁዳውያን መሲሕ አድርገው አልተቀበሉትም። ይሁንና ኢሳይያስ፣ መሲሑ ንጉሥ ከመሆኑ በፊት መከራና ሥቃይ እንደሚደርስበት አስቀድሞ ተናግሯል።
የኢሳይያስ መጽሐፍ መሲሑን አስመልክቶ ትንቢት ሲናገር “ለሚገርፉኝ ጀርባዬን፣ . . . ፊቴን ከውርደት፣ ከትፋትም አልሰወርሁም” ብሏል። ማቴዎስ፣ ኢየሱስ ለፍርድ በቀረበ ጊዜ የሆነውን ሲዘግብ “ፊቱ ላይ እየተፉ በጡጫ መቱት፤ ሌሎቹም በጥፊ [መቱት]” ብሏል። (ኢሳይያስ 50:6፤ ማቴዎስ 26:67) ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ “ተሠቃየም፤ ነገር ግን አፉን አልከፈተም” በማለት ጽፏል። በመሆኑም ጲላጦስ፣ አይሁዳውያን ላቀረቡበት ክስ መልስ እንዲሰጥ ኢየሱስን በጠየቀው ጊዜ “አገረ ገዥው እስኪገረም ድረስ ለቀረበበት ክስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰም።”—ኢሳይያስ 53:7፤ ማቴዎስ 27:12-14፤ የሐዋርያት ሥራ 8:28, 32-35
ከመሲሑ ሞት ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮች። ኢሳይያስ የተናገራቸው ትንቢቶች፣ ኢየሱስ በሞተበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውን ቀጥለዋል። ኢሳይያስ “አሟሟቱ ከክፉዎች፣ መቃብሩም ከባለጠጎች ጋር ሆነ” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 53:9) እርስ በርሱ የሚቃረን የሚመስለው ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ኢየሱስ የተሰቀለው ከሁለት ወንበዴዎች ጋር ነበር። (ማቴዎስ 27:38) በኋላ ላይ ግን ባለጠጋ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ ኢየሱስን ከዐለት አስፈልፍሎ ለራሱ ባሠራው አዲስ መቃብር ውስጥ እንዲቀበር አድርጓል። (ማቴዎስ 27:57-60) በመጨረሻም ኢሳይያስ ከተናገራቸው ዋነኛ ትንቢቶች መካከል አንዱ ኢየሱስ በሞተ ጊዜ ተፈጽሟል። ኢሳይያስ መሲሑን አስመልክቶ “ጻድቅ ባሪያዬ በዕውቀቱ ብዙዎቹን ያጸድቃል፤ መተላለፋቸውንም ይሸከማል” ብሏል። በእርግጥም የኢየሱስ ሞት ታማኝ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ከኃጢአት ቀንበር ነፃ እንዲወጡ ቤዛ ሆኖላቸዋል።—ኢሳይያስ 53:8, 11፤ ሮሜ 4:25
መፈጸማቸው የማይቀሩ ትንቢቶች
ኢየሱስና ሐዋርያት፣ የመሲሑን ማንነት ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ለማቅረብ ሲሉ ከሌሎች ቅዱሳን መጻሕፍት ይበልጥ ከኢሳይያስ ትንቢት ጠቅሰዋል። ያም ሆኖ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚናገሩ ትንቢቶችን የያዘው የኢሳይያስ መጽሐፍ ብቻ ነው ማለት አይደለም። በሌሎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የሚገኙት ስለ ኢየሱስና ስለ መንግሥቱ እንዲሁም ይህ መንግሥት ስለሚያከናውናቸው መልካም ነገሮች የሚናገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውን ይቀጥላሉ።a (የሐዋርያት ሥራ 28:23፤ ራእይ 19:10 NW) እነዚህ ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ ምን ያህል እርግጠኛ መሆን ይቻል ነበር? ኢየሱስ ለአይሁዳውያን አድማጮቹ እንደሚከተለው ብሏቸዋል፦ “ሕግንና የነቢያትን ቃል [ማለትም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን] ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳ አትሻርም።”—ማቴዎስ 5:17, 18
ኢየሱስ ስለ እሱ የተነገሩትን ጨምሮ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንዴት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ገልጿል። (ዳንኤል 9:27፤ ማቴዎስ 15:7-9፤ 24:15) በተጨማሪም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በዛሬው ጊዜ በዓለማችን ላይ የምናያቸውን ነገሮች ጨምሮ ከእነሱ ዘመን በኋላ ስለሚከናወኑት ነገሮች አስቀድመው ተናግረዋል። የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህንና ወደፊት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን ስላገኙ ትንቢቶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 200 ተመልከት።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ድንግል ወንድ ልጅ ትወልዳለች’
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ፊቴን ከውርደት . . . አልሰወርሁም”