በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ሁሉ ይከሽፋል
“በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል።”—ኢሳይያስ 54:17
1, 2. በአልባኒያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ያጋጠማቸው ሁኔታ የኢሳይያስ 54:17ን እውነተኝነት የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
ከአሥርተ ዓመታት በፊት በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ በምትገኝ አንዲት ትንሽ አገር ውስጥ ጥቂት ክርስቲያኖች ይኖሩ ነበር። በአምላክ መኖር የማያምነው የኮሚኒስት ሥርዓት እነዚህን ደፋር ክርስቲያኖች ለማጥፋት ያላደረገው ጥረት አልነበረም። መንግሥት ሥቃይ ቢያደርስባቸውም፣ የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ካምፖች ቢልካቸውም እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ቢነዛባቸውም እነዚህን ክርስቲያኖች ማጥፋት አልቻለም። ይህ ሁሉ የደረሰባቸው በአልባኒያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ለእነዚህ ክርስቲያኖች መሰብሰብም ሆነ መስበክ በጣም አስቸጋሪ ቢሆንባቸውም ለአሥርተ ዓመታት መጽናታቸው ክርስትናን ያስከበረ ከመሆኑም በላይ ለይሖዋ ስም ውዳሴ አምጥቷል። ባለፈው ዓመት አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሯቸው ለአምላክ አገልግሎት በተወሰነበት ወቅት ለረጅም ጊዜ በታማኝነት ያገለገሉ አንድ ወንድም “ሰይጣን የቱንም ያህል ቢፍጨረጨር አንዴም አልተሳካለትም፤ ሁሌም ድሉ የይሖዋ ነው” በማለት ተናግረዋል።
2 ይህ ሁሉ አምላክ በኢሳይያስ 54:17 ላይ “በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ” በማለት ለሕዝቦቹ የገባው ቃል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሕያው ማስረጃ ነው። የሰይጣን ዓለም የሚያደርገው ማንኛውም ነገር የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ ሊያስተጓጉል እንደማይችል ታሪክ ያረጋግጥልናል።
ሰይጣን ያደረጋቸው ያልተሳኩ ሙከራዎች
3, 4. (ሀ) ሰይጣን የሚጠቀምባቸው አንዳንድ መሣሪያዎች ምንድን ናቸው? (ለ) የዲያብሎስ መሣሪያዎች እንደከሸፉ የታየው እንዴት ነው?
3 በእውነተኛ አምላኪዎች ላይ ከሚደገኑት መሣሪያዎች መካከል እገዳ መጣል፣ ሕዝብ እንዲያምጽባቸው ማድረግ፣ እስር እንዲሁም ‘ሕግን ተንተርሶ ክፋት መሸረብ’ ይገኙበታል። (መዝሙር 94:20 NW) እንዲያውም የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ርዕስ እያጠኑ ባለበት በዚህ ሰዓትም እንኳ በአንዳንድ አገሮች የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለአምላክ ያላቸውን ጽኑ አቋም በመጠበቃቸው ‘ፈተና እየደረሰባቸው’ ይሆናል።—ራእይ 2:10
4 ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ የአምላክ ሕዝቦች አገልግሎት ላይ እያሉ የተደበደቡባቸው 32 አጋጣሚዎች እንደነበሩ ሪፖርት አድርጓል። በተጨማሪም ፖሊስ ወጣት አረጋዊ፣ ወንድ ሴት ሳይል በስብከቱ ሥራ ላይ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ያሰረባቸው 59 አጋጣሚዎች ነበሩ። ከእነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዳንዶቹ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው አሻራ እንዲሰጡና ፎቶግራፍ እንዲነሱ ተደርገዋል እንዲሁም ታስረዋል። ሌሎች ደግሞ ተደብድበዋል። በሌላም አገር የይሖዋ ምሥክሮች ከመታሠራቸው፣ መቀጫ እንዲከፍሉ ከመደረጋቸው ወይም ከመደብደባቸው ጋር በተያያዘ በመታየት ላይ የሚገኙ ከ1,100 በላይ የፍርድ ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህም መካከል ከ200 በላይ የሚሆኑት ጉዳዮች ወንድሞች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር በተሰበሰቡበት ዕለት የተፈጸሙ ናቸው! ይሁንና ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት በእነዚህም ሆነ በሌሎች አገሮች ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦቹ የሚደርሱባቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲቋቋሙ አስችሏቸዋል። (ዘካርያስ 4:6) ጠላት በከፍተኛ ቁጣ ተነሳስቶ ምንም ቢያደርግ ይሖዋን የሚያወድሱ ሰዎችን አንደበት ዝም ማሰኘት አይችልም። የትኛውም መሣሪያ የአምላክን ዓላማ ሊያጨናግፍ እንደማይችል እርግጠኞች ነን!
የሐሰት አንደበቶች ይረታሉ
5. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች ምን የሐሰት ክስ ተሰንዝሮባቸዋል?
5 ኢሳይያስ የአምላክ ሕዝቦች የሚከሳቸውን አንደበት ሁሉ እንደሚረቱ ትንቢት ተናግሯል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መጥፎ ሰዎች እንደሆኑ ተደርገው ስለሚታዩ ብዙውን ጊዜ ያለስማቸው ስም ይሰጣቸው ነበር። በሐዋርያት ሥራ 16:20, 21 ላይ የሚገኙት ቃላት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆኑናል። ጥቅሱ “እነዚህ ሰዎች . . . ከተማችንን አውከዋል፤ ደግሞም እኛ ሮማውያን መቀበል ወይም መፈጸም የማይገባንን ልማድ በሕዝቡ መካከል ይነዛሉ” ይላል። በሌላ ወቅት ደግሞ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች ‘እነዚህ ሰዎች ዓለሙን ሁሉ ሲያውኩ ቈይተው አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል፤ የቄሣርንም ሕግ ይጥሳሉ’ ብለው የክርስቶስን ተከታዮች በመወንጀል የከተማው ባለ ሥልጣናት እርምጃ እንዲወስዱባቸው ለማነሳሳት ሞክረዋል። (የሐዋርያት ሥራ 17:6, 7) ሐዋርያው ጳውሎስም “በሽታ” ተብሎ ተጠርቷል፤ እንዲሁም ‘በዓለም ሁሉ’ ሁከት የሚያስነሳ ኑፋቄ መሪ ነው የሚል ስም ተሰጥቶታል።—የሐዋርያት ሥራ 24:2-5
6, 7. እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚሰነዘርባቸውን ውንጀላ ውድቅ የሚያደርጉበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?
6 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የሚገኙት እውነተኛ ክርስቲያኖች ያለስማቸው ስም ቢሰጣቸው፣ መጥፎ ወሬ ቢወራባቸውና የስም ማጥፋት ዘመቻ ቢካሄድባቸው የሚያስገርም አይደለም። ታዲያ ይህ ሁሉ ጥቃት እየደረሰባቸው ረትተዋል ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?—ኢሳይያስ 54:17
7 የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሳዩት መልካም ምግባር እንዲህ ያሉት ውንጀላዎችና ፕሮፓጋንዳዎች ውድቅ መሆናቸውን ያረጋግጣል። (1 ጴጥሮስ 2:12) ክርስቲያኖች ስለ ሌሎች ደኅንነት ከልብ የሚያስቡ፣ ሕግ አክባሪና በሥነ ምግባር የታነጹ ዜጎች መሆናቸውን በተግባር ሲያሳዩ በእነሱ ላይ የሚሰነዘረው ክስ ሐሰት መሆኑ ይረጋገጣል። መልካም ባሕርያችን ምን ዓይነት ሰዎች ለመሆናችን ምሥክር ነው። ሰዎች ሁልጊዜ ጥሩ ለማድረግ እንደምንጥር ሲመለከቱ በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ክብር ለመስጠት ብሎም የአገልጋዮቹ አኗኗር ከሁሉ የተሻለ መሆኑን ለመቀበል ይገፋፋሉ።—ኢሳይያስ 60:14፤ ማቴዎስ 5:14-16
8. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አቋማችንን ለማሳወቅ አንዳንድ ጊዜ ምን ማድረግ ያስፈልገናል? (ለ) የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ተቃዋሚዎቻችንን መርታት የምንችለው እንዴት ነው?
8 ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ከማንጸባረቅ በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው አቋማችን በድፍረት መናገር አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜም ይኖራል። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ ከሚደርስብን ጥቃት ጥበቃ ለማግኘት ለመንግሥታትና ለፍርድ ቤቶች አቤቱታ ማቅረብ ነው። (አስቴር 8:3፤ የሐዋርያት ሥራ 22:25-29፤ 25:10-12) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የሚሰነዘርበትን የሐሰት ውንጀላ በመቃወም ይተቹት የነበሩትን ሰዎች ፊት ለፊት ያወገዘበት ጊዜ ነበር። (ማቴዎስ 12:34-37፤ 15:1-11) እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ከልብ ስለምናምንባቸው ነገሮች ግልጽ ማብራሪያ ለመስጠት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በሚገባ እንጠቀምባቸዋለን። (1 ጴጥሮስ 3:15) በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም ከማያምኑ ዘመዶቻችን የሚደርስብን ነቀፋ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለሌሎች ከማሳወቅ እንዲያግደን አንፍቀድ።—2 ጴጥሮስ 3:3, 4
ኢየሩሳሌም—‘የማትነቃነቅ ዐለት’
9. በዘካርያስ 12:3 ላይ ‘የማትነቃነቅ ዐለት’ ተብላ የተጠቀሰችው ኢየሩሳሌም የምታመለክተው ማንን ነው? በምድር ላይ የምትወከለውስ በማን ነው?
9 የዘካርያስ ትንቢት ብሔራት እውነተኛ ክርስቲያኖችን የሚቃወሙበትን ምክንያት ይገልጽልናል። ዘካርያስ 12:3 ምን እንደሚል ልብ በሉ:- “በዚያ ቀን፣ ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ የማይነቃነቅ ዐለት አደርጋታለሁ።” ይህ ትንቢት የሚናገረው ስለ የትኛዋ ኢየሩሳሌም ነው? ዘካርያስ ኢየሩሳሌምን በተመለከተ የተናገረው ትንቢት ‘ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌም’ ማለትም ቅቡዓን ክርስቲያኖች አባላት የሆኑበትን በሰማይ ያለውን መንግሥት የሚያመለክት ነው። (ዕብራውያን 12:22) ከዚህ መሲሐዊ መንግሥት ወራሾች መካከል የተወሰኑት አሁንም ምድር ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ቅቡዓን፣ አጋሮቻቸው ከሆኑት “ሌሎች በጎች” ጋር በመሆን ጊዜው ከማለቁ በፊት ሰዎች ለአምላክ መንግሥት ራሳቸውን እንዲያስገዙ ያበረታታሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 11:15) ታዲያ ብሔራት ለዚህ ማበረታቻ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው? ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ላሉት እውነተኛ አምላኪዎቹ ምን ድጋፍ ይሰጣል? ዘካርያስ ምዕራፍ 12ን ይበልጥ ስንመረምር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የምናገኝ ከመሆኑም በላይ በቅቡዓኑም ሆነ ራሳቸውን በወሰኑት አጋሮቻቸው ላይ ‘እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ’ ሁሉ እንደሚከሽፍ ማረጋገጫ ማግኘት እንችላለን።
10. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ጥቃት የሚሰነዘርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ‘የማይነቃነቀውን ዐለት’ ለማስወገድ የሞከሩ ሰዎች ምን ደርሶባቸዋል?
10 ዘካርያስ 12:3 አሕዛብ ወይም ብሔራት ‘ራሳቸውን እንደሚጎዱ’ ይናገራል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? አምላክ የመንግሥቱ ምሥራች እንዲሰበክ አዟል። የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በቁም ነገር ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ እንደሆነ መታወጁ ለብሔራት “የማይነቃነቅ ዐለት” ሆኖባቸዋል። በመሆኑም ብሔራት የመንግሥቱን ሰባኪዎች በመቃወም ይህን ዓለት ለማስወገድ ሞክረዋል። እነዚህ ብሔራት ይህን ለማድረግ ሲሞክሩ በመቆሳሰላቸው በከፍተኛ ሁኔታ ‘ራሳቸውን ጎድተዋል።’ እንዲያውም በጣም አሳፋሪ ውድቀት ስለደረሰባቸው ስማቸው ጎድፏል። ብሔራት የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት ስለ አምላክ መሲሐዊ መንግሥት የሚናገረውን “የዘላለም ወንጌል” የማወጅ መብታቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱትን እውነተኛ አምላኪዎች ዝም ማሰኘት አልቻሉም። (ራእይ 14:6) በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ የሚገኝ የአንድ እስር ቤት ጠባቂ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ከተመለከተ በኋላ ‘እነዚህን ሰዎች በማሠቃየት በከንቱ እየደከማችሁ ነው። እነሱ እንደሆነ ከአቋማቸው ፍንክች አይሉም። እንዲያውም በቁጥር እየጨመሩ ይሄዳሉ’ በማለት ተናግሯል።
11. አምላክ በዘካርያስ 12:4 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ቃሉን የጠበቀው እንዴት ነው?
11 ዘካርያስ 12:4ን (የ1954 ትርጉም) አንብብ። ይሖዋ ደፋር የሆኑትን የመንግሥቱን ሰባኪዎች የሚቃወሙትን ብሔራት ‘እንደሚያስደነግጥና’ በምሳሌያዊ መንገድ እንደሚያሳውራቸው ቃል ገብቷል። ይሖዋ ይህን ቃሉን ጠብቋል። እውነተኛው አምልኮ ታግዶ በነበረበት አንድ አገር ውስጥ ተቃዋሚዎች የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ምግብ እንዳይደርሳቸው ማድረግ አለመቻላቸው ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። እንዲያውም አንድ ጋዜጣ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ አገሪቱ ለማስገባት ፊኛዎችን ሳይቀር ይጠቀሙ እንደነበር ዘግቧል! አምላክ “ዓይኖቼንም . . . እከፍታለሁ፤ የአሕዛብንም ፈረሶች ሁሉ በዕውርነት እመታለሁ” በማለት ለታማኝ አገልጋዮቹ የገባውን ቃል ፈጽሟል። የአምላክ መንግሥት ጠላቶች ቁጣ ስላሳወራቸው ወዴት እንደሚሄዱ ግራ ገብቷቸዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሕዝቡን በቡድን ደረጃ እንደሚጠብቅና ስለ ደኅንነታቸውም በጥልቅ እንደሚያስብ እናምናለን።—2 ነገሥት 6:15-19
12. (ሀ) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት እሳት የለኮሰው በምን መንገድ ነው? (ለ) ቅቡዓን ቀሪዎች በምሳሌያዊ ሁኔታ እሳት የለኮሱት እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?
12 ዘካርያስ 12:5, 6ን አንብብ። “የይሁዳ መሪዎች” የሚለው አገላለጽ በአምላክ ሕዝቦች መካከል በአመራር ቦታ ላይ ያሉትን ያመለክታል። ይሖዋ እነዚህ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ላይ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ነገሮችን እንዲያከናውኑ እንደ እሳት ነበልባል ያለ ቅንዓት እንዲኖራቸው ያደርጋል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እኔ የመጣሁት በምድር ላይ እሳት ለመለኰስ ነው” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 12:49) በእርግጥም ኢየሱስ በምሳሌያዊ ሁኔታ እሳት ለኩሶ ነበር። ኢየሱስ ቅንዓት በተሞላበት መንገድ በመስበክ የአምላክ መንግሥት ትልቁ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ እንዲሆን አድርጓል። ይህም በአይሁድ ብሔር ውስጥ የጦፈ ክርክር አስነስቷል። (ማቴዎስ 4:17, 25፤ 10:5-7, 17-20) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ፈለግ በመከተል ‘በዕንጨት ክምር ውስጥ እንዳለ የእሳት ምድጃና በነዶ መካከል እንዳለ የፋና ነበልባል’ የመሰለ እሳት ለኩሰዋል። በ1917 የወጣው ያለቀለት ምስጢርa (እንግሊዝኛ) የተባለ መጽሐፍ የሕዝበ ክርስትናን ግብዝነት አጋልጧል። ይህ ሁኔታ ቀሳውስቱን ክፉኛ አስቆጥቷቸዋል። በቅርቡ ያሰራጨነው “የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!” የሚል ርዕስ ያለው የመንግሥት ዜና ቁጥር 37 ደግሞ በርካታ ሰዎች የአምላክን መንግሥት በመደገፍ አሊያም በመቃወም ሚናቸውን እንዲለዩ አድርጓቸዋል።
“የይሁዳን ድንኳኖች” ያድናል
13. ‘የይሁዳ ድንኳኖች’ የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? ይሖዋ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን የሚያድነውስ ለምንድን ነው?
13 ዘካርያስ 12:7, 8ን (የ1954 ትርጉም) አንብብ። በጥንቷ እስራኤል የነበሩ አንዳንድ እረኞችና በግብርና ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች በድንኳን ይኖሩ ስለነበር በየቦታው ድንኳኖችን ማየት የተለመደ ነበር። የጠላት ብሔር ኢየሩሳሌምን ለማጥቃት ከመጣ የመጀመሪያዎቹ ሰለባዎች የሚሆኑት በድንኳኖቹ ውስጥ የሚኖሩት እነዚህ ሰዎች ስለሆኑ ጥበቃ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ‘የይሁዳ ድንኳኖች’ የሚለው አገላለጽ በዘመናችን ያሉት ቅቡዓን ቀሪዎች በገላጣ ሜዳ ላይ ማለትም በምሳሌያዊ አነጋገር ምንም ከለላ በሌላቸው ከተሞች ውስጥ እንደሚኖሩ የሚያመለክት ነው። ቅቡዓኑ ለጥቃት በተጋለጠ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለመሲሐዊው መንግሥት ጉዳዮች በድፍረት ጥብቅና ይቆማሉ። ሰይጣን “የይሁዳን ድንኳኖች” ዋነኛ የጥቃት ዒላማው ስለሚያደርግ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እነሱን “አስቀድሞ” ያድናል።
14. ይሖዋ ‘በይሁዳ ድንኳኖች’ ውስጥ የሚገኙትን የሚጠብቃቸውና እንዳይደክሙ የሚያደርጋቸው እንዴት ነው?
14 በእርግጥም ይሖዋ ሜዳ ላይ ‘ድንኳናቸው’ ውስጥ የሚገኙትን በመንፈስ የተቀቡ የመንግሥቱን አምባሳደሮች እየጠበቃቸው እንዳለ ታሪክ ያረጋግጥልናል።b ይሖዋ እነዚህ ቅቡዓን ‘እንዳይደክሙ’ ማለትም ተዋጊ ንጉሥ እንደነበረው እንደ ዳዊት ብርቱና ደፋር እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
15. ይሖዋ ‘በአሕዛብ ላይ የሚወጣው’ ለምንድን ነው? ይህን የሚያደርገውስ ምን ጊዜ ነው?
15 ዘካርያስ 12:9ን አንብብ። ይሖዋ ‘በአሕዛብ ላይ የሚወጣው’ ለምንድን ነው? መሲሐዊውን መንግሥት ያለማቋረጥ ስለሚቃወሙ ነው። የአምላክን ሕዝቦች ስለሚያሠቃዩአቸውና ስለሚያሳድዷቸው ይፈረድባቸዋል። በቅርቡ የሰይጣን ምድራዊ ወኪሎች በአምላክ እውነተኛ አምላኪዎች ላይ የመጨረሻ ጥቃት ይሰነዝራሉ፤ ይህም ዓለምን መጽሐፍ ቅዱስ አርማጌዶን ብሎ ወደሚጠራው ሁኔታ ይመራዋል። (ራእይ 16:13-16) በዚህ ጊዜ ታላቁ ፈራጅ ይሖዋ አገልጋዮቹን ይታደጋል ብሎም በአሕዛብ መካከል ስሙን ያስቀድሳል።—ሕዝቅኤል 38:14-18, 22, 23
16, 17. (ሀ) ‘የይሖዋ ባሪያዎች ርስት’ ምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን የሚሰነዝራቸውን ጥቃቶች በጽናት መቋቋማችን ምን ያረጋግጣል?
16 ሰይጣን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦችን እምነት ለማዳከም ወይም ቅንዓታቸውን ለማቀዝቀዝ የሚያስችል መሣሪያ የለውም። ይሖዋ የማዳን ኃይሉን ተጠቅሞ እንደሚደግፈን በማወቃችን ያገኘነው መንፈሳዊ ሰላም ‘ርስታችን ነው።’ (ኢሳይያስ 54:17) ሰላማችንንና መንፈሳዊ ብልጽግናችንን ማንም ሊነጥቀን አይችልም። (መዝሙር 118:6) ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ተቃውሞ ማስነሳቱንና መከራ ማምጣቱን አያቆምም። ነቀፋ እየተሰነዘረብንም እንኳ ታማኝነታችንን ጠብቀን መጽናታችን የአምላክ መንፈስ እንዳለን የሚያሳይ ነው። (1 ጴጥሮስ 4:14) በመግዛት ላይ ስለሚገኘው ስለ ይሖዋ መንግሥት የሚናገረው ምሥራች በዓለም ዙሪያ እየታወጀ ነው። ተቃዋሚዎች በአምላክ ሕዝቦች ላይ ምሳሌያዊ ‘ድንጋይ’ ይወነጭፋሉ። ሆኖም የይሖዋ አገልጋዮች ከእሱ በሚያገኙት ብርታት እንዲህ ያሉትን ድንጋዮች በማምከን ጉዳት እንዳያደርሱ ያደርጓቸዋል። (ዘካርያስ 9:15) ቅቡዓን ቀሪዎችና ታማኝ አጋሮቻቸው ሥራቸውን እንዲያቆሙ ሊያደርጋቸው የሚችል ምንም መሣሪያ የለም!
17 ዲያብሎስ ከሚሰነዝረው ጥቃት ሙሉ በሙሉ ነጻ የምንሆንበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን። ‘በእኛ ላይ እንዲደገን የተበጀ ማንኛውም መሣሪያ እንደሚከሽፍና የሚከሰንንም አንደበት ሁሉ እንደምንረታ’ የተሰጠን ዋስትና በእጅጉ ያጽናናናል!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።
b ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የሚለውን መጽሐፍ ገጽ 675-676 ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የሰይጣን መሣሪያዎች እንደከሸፉ የሚያሳየው ምንድን ነው?
• ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ‘የማትነቃነቅ ዐለት’ የሆነችው እንዴት ነው?
• ይሖዋ “የይሁዳን ድንኳኖች” የሚያድነው እንዴት ነው?
• አርማጌዶን የሚጀምርበት ጊዜ እየተቃረበ ሲሄድ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአልባኒያ የሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች ሰይጣን ጥቃት ቢሰነዝርባቸውም በታማኝነት ጸንተዋል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የተሰነዘረበትን የሐሰት ውንጀላ ውድቅ አድርጓል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምሥራቹን በሚያውጁ ሰዎች ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ሁሉ ይከሽፋል