ይሖዋ ሕዝቡን በብርሃን ያስጌጣል
“ብርሃንሽ መጥቶአልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፣ አብሪ።”—ኢሳይያስ 60:1
1, 2. (ሀ) የሰው ልጅ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል? (ለ) ይህን ዓለም ከዋጠው ጨለማ በስተጀርባ ያለው ማን ነው?
“የኢሳይያስ ያለህ፣ የቅዱስ ጳውሎስ ያለህ!” ይህ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ሃሪ ትሩማን በ1940ዎቹ ያሰሙት እሮሮ ነበር። እንዲህ እንዲሉ ያደረጋቸው ምን ነበር? እሳቸው በኖሩበት ዘመን ከፍተኛ የሞራል ጥንካሬ ያላቸው መሪዎች እንደሚያስፈልጉ ስለተሰማቸው ነው። የሰው ልጅ ከ20ኛው መቶ ዘመን አስከፊ የጨለማ ወቅት ማለትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገና መውጣቱ ነበር። ጦርነቱ ያብቃ እንጂ ዓለም ሰላምን እንደተጠማች ነበር። ጨለማው ጸንቶባታል። በእርግጥም፣ ጦርነቱ ካበቃ ከ57 ዓመታት በኋላ ዓለም ከዋጣት ጨለማ ገና አልተላቀቀችም። ፕሬዚዳንት ትሩማን ዛሬም በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ የኢሳይያስ ወይም የጳውሎስ ዓይነት የሞራል ጥንካሬ ያላቸው መሪዎች እንደሚያስፈልጉ መናገራቸው አይቀርም ነበር።
2 ፕሬዚዳንት ትሩማን በወቅቱ ተረዱትም አልተረዱት ሐዋርያው ጳውሎስ የሰው ልጅ ጨለማ እንደዋጠው የተናገረ ከመሆኑም በላይ በጻፈው ጽሑፍ ላይ ይህን ጉዳይ ጠቅሶ አስጠንቅቋል። ለምሳሌ ያህል የእምነት ባልንጀሮቹን “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ” ሲል አስጠንቅቋቸዋል። (ኤፌሶን 6:12፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እዚህ ላይ ጳውሎስ ዓለምን የሸፈነ መንፈሳዊ ጨለማ መኖሩን መገንዘብ ብቻ ሳይሆን የጨለማው ትክክለኛ ምንጭ ‘የዓለም ገዦች’ ተብለው የተገለጹት አጋንንታዊ ኃይሎች መሆናቸውን እንደሚያውቅም ገልጿል። ይህን ዓለም ከዋጠው ጨለማ በስተጀርባ ያሉት ብርቱ አጋንንታዊ ኃይሎች ከሆኑ ሥጋ ለባሽ ሰዎች ጨለማውን ለማስወገድ ምን ማድረግ ይችላሉ?
3. የሰው ልጅ በጨለማ የተዋጠ ቢሆንም ኢሳይያስ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ምን እንደሚያገኙ ትንቢት ተናግሯል?
3 በተመሳሳይ ኢሳይያስ በሰው ልጅ ላይ መከራ ስላስከተለው ጨለማ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 8:22፤ 59:9) ይሁን እንጂ እኛ ያለንበትን ጊዜ አሻግሮ በመመልከት በዚህ የጨለማ ዘመን እንኳ ይሖዋ ብርሃንን ለሚወድዱ ሰዎች ብሩህ ዕይታ እንደሚያጎናጽፋቸው በመንፈስ አነሳሽነት ትንቢት ተናግሯል። አዎን፣ ጳውሎስና ኢሳይያስ ከእኛ ጋር በአካል ባይገኙም በመንፈስ አነሳሽነት የጻፏቸው መጻሕፍት መመሪያ ሆነው ያገለግሉናል። እነዚህ መጻሕፍት ይሖዋን ለሚወድዱ ሰዎች ምን በረከት እንዳስገኙላቸው ለማስተዋል ኢሳይያስ የተናገራቸውን በ60ኛው የመጽሐፉ ምዕራፍ ላይ የሚገኙትን ትንቢታዊ ቃላት እንመርምር።
በትንቢቱ ውስጥ የተገለጸችው ሴት ብርሃን አበራች
4, 5. (ሀ) ይሖዋ ለአንዲት ሴት ምን ትእዛዝ ሰጣት? ምን ብሎስ ቃል ገባላት? (ለ) ኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ምን ስሜት ቀስቃሽ ትንቢት ይዟል?
4 የኢሳይያስ 60 የመጀመሪያዎቹ ቃላት አንጀት በሚበላ ሁኔታ ውስጥ ለምትገኝ አንዲት ሴት የተነገሩ ናቸው። ሴቲቱ ጨለማ ውስጥ መሬት ላይ ድፍት ብላለች። ድንገት ብርሃን ጨለማውን ሰንጥቆ ይወጣና ይሖዋ “ብርሃንሽ መጥቶአልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፣ አብሪ” ሲል ይናገራል። (ኢሳይያስ 60:1) ሴቲቱ ተነስታ የምትቆምበትና የአምላክን ብርሃን ማለትም ክብሩን የምታንጸባርቅበት ጊዜ ደርሷል። እንዴት? ቀጥሎ ባለው ቁጥር መልሱን እናገኛለን:- “እነሆ፣ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል።” (ኢሳይያስ 60:2) ሴቲቱ ይሖዋ እንዳዘዛት ስታደርግ አስደናቂ ውጤት እንደምታገኝ ተነግሯታል። ይሖዋ “አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ” ብሏታል።—ኢሳይያስ 60:3
5 በእነዚህ ሦስት ቁጥሮች ላይ የሚገኙት ስሜት ቀስቃሽ ቃላት የኢሳይያስ ምዕራፍ 60 መግቢያ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ቀሪው ክፍል ምን እንደያዘ ጠቅለል አድርገው ይገልጻሉ። ይህ ምዕራፍ በትንቢቱ ውስጥ የተገለጸችው ሴት ያጋጠማትን ሁኔታ እንዲሁም የሰው ዘር በጨለማ ቢዋጥም በይሖዋ ብርሃን እንዴት መኖር እንደምንችል ይጠቁመናል። ይሁንና በእነዚህ ሦስት ቁጥሮች ውስጥ የተሰጠው ትንቢታዊ መግለጫ ትክክለኛ ትርጉም ምንድን ነው?
6. በኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ላይ የተጠቀሰችው ሴት ማን ናት? በምድር ላይ የምትወከለውስ በማን ነው?
6 በኢሳይያስ 60:1-3 ላይ የተጠቀሰችው ሴት መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈችው የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት ጽዮን ናት። በዛሬው ጊዜ ጽዮን በምድር ላይ የምትወከለው ‘በአምላክ እስራኤል’ ቀሪዎች ማለትም ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት መብት ያላቸውን በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ባቀፈው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ነው። (ገላትያ 6:16) ይህ መንፈሳዊ ብሔር በአጠቃላይ 144, 000 አባላት ያሉት ሲሆን የኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ዘመናዊ ፍጻሜ “በመጨረሻው ቀን” በምድር ላይ በሚኖሩት የዚህ ብሔር አባላት ላይ ያተኩራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ራእይ 14:1) ትንቢቱ የእነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ተባባሪዎችና “የሌሎች በጎች” ክፍል ስለሆኑት ስለ ‘እጅግ ብዙ ሰዎችም’ ብዙ ሐሳብ ይዟል።—ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16
7. በ1918 ጽዮን የነበረችበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ይህስ በትንቢት የተገለጸው እንዴት ነው?
7 በዚህች ትንቢታዊ ትርጉም ባላት ሴት ሁኔታ እንደተገለጸው ‘የአምላክ እስራኤል’ ጨለማ ውጦት የነበረበት ጊዜ አለን? አዎን፣ ከ80 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ይህ ሁኔታ ተፈጽሞ ነበር። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምሥክርነቱ ሥራ ለመቀጠል ከባድ ትግል ጠይቆባቸው ነበር። ሆኖም ጦርነቱ ባበቃበት በ1918 በተደራጀ መልክ የሚከናወነው የስብከት ሥራ ጭራሽ የቆመ ያህል ሆኖ ነበር። ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ አመራር ይሰጥ የነበረው ወንድም ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊነት የነበራቸው ክርስቲያኖች በሐሰት ተከስሰው የረጅም ዓመት እስራት ተበየነባቸው። የራእይ መጽሐፍ በወቅቱ በምድር ላይ ስለነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ትንቢት ሲናገር ‘በመንፈሳዊ ዓይን ሰዶምና ግብፅ ተብላ በተጠራች በታላቂቱ ከተማ አደባባይ’ ላይ እንደተኙ በድኖች አድርጎ ይገልጻቸዋል። (ራእይ 11:8) ይህ ምድር ባሉት ቅቡዓን ልጆቿ ለምትወከለው ጽዮን በእርግጥም የጨለማ ወቅት ነበር!
8. በ1919 የተከናወነው አስገራሚ ለውጥ ምንድን ነው? ምንስ ውጤት አስገኝቷል?
8 ይሁን እንጂ በ1919 አንድ አስገራሚ ለውጥ ተከናወነ። ይሖዋ በጽዮን ላይ ብርሃን አበራ! በሕይወት የነበሩት የአምላክ እስራኤል አባላት የምሥራቹን ዳግም ያለ ፍርሃት በማወጅ የአምላክን ብርሃን ለማንጸባረቅ ተንቀሳቀሱ። (ማቴዎስ 5:14-16) የእነዚህ ክርስቲያኖች ቅንዓት ዳግመኛ በመቀጣጠሉ ምክንያት ሌሎችም ወደ ይሖዋ ብርሃን ሊሳቡ ችለዋል። በመጀመሪያ ወደ ብርሃኑ ተስበው የመጡት የአምላክ እስራኤል ተጨማሪ አባላት በመሆን በመንፈስ ተቀብተዋል። እነዚህ ቅቡዓን ከክርስቶስ ጋር በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ተባባሪ ገዥዎች ስለሚሆኑ ኢሳይያስ 60:3 ላይ ነገሥታት ተብለው ተጠርተዋል። (ራእይ 20:6) ከጊዜ በኋላ ደግሞ የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ ብርሃን ተስበዋል። በትንቢቱ ውስጥ የተጠቀሱት “አሕዛብ” እነርሱ ናቸው።
የሴቲቱ ልጆች ወደ ቤት መጡ!
9, 10. (ሀ) ሴቲቱ ያየችው አስደናቂ ነገር ምንድን ነው? ይህስ ምንን ያመለክታል? (ለ) ጽዮን እንድትደሰት ያስቻላት ነገር ምንድን ነው?
9 አሁን ይሖዋ በኢሳይያስ 60:1-3 ላይ ጠቅለል ብሎ ለተቀመጠው ትንቢታዊ መልእክት ተጨማሪ ማብራሪያ ሊሰጥ ነው። ለሴቲቱ ተጨማሪ ትእዛዝ ሰጣት። ምን እንደሚላት ልብ በል:- “ዓይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ።” ሴቲቱ በተሰጣት ትእዛዝ መሠረት ዓይኖቿን አቅንታ ስትመለከት የምታየው ነገር ምንኛ የሚያስደስት ነው! ልጆቿ ወደ ቤት እየመጡላት ነው። ጥቅሱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፣ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል።” (ኢሳይያስ 60:4) ከ1919 ጀምሮ የተከናወነው የመንግሥቱን መልእክት በዓለም ዙሪያ የማወጅ ሥራ በሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ ሰዎች በይሖዋ አገልግሎት እንዲሳተፉ አድርጓል። እነዚህም የጽዮን ‘ወንዶችና ሴቶች ልጆች’ ማለትም ቅቡዓን የአምላክ እስራኤል አባላት ሆነዋል። ይህም በመሆኑ ይሖዋ የመጨረሻዎቹን የ144, 000 አባላት ወደ ብርሃን በማምጣት ጽዮንን አስጊጧታል።
10 ጽዮን ልጆቿን በማግኘቷ ምን ያህል እንደምትደሰት መገመት ትችላለህ? ይሖዋ ጽዮንን የሚያስደስት ተጨማሪ ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፣ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፣ አይተሽ ደስ ይልሻል፣ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል።” (ኢሳይያስ 60:5) ከእነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ እጅግ ብዙ ክርስቲያኖች ከ1930ዎቹ ዓመታት አንስቶ ወደ ጽዮን ጎርፈዋል። ከአምላክ ከተቆራረጠው የሰው ዘር “ባሕር” ተለይተው እንደመጡና የአሕዛብ ብልጥግና እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል። ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡ ዕቃዎች’ ናቸው። (ሐጌ 2:7፤ ኢሳይያስ 57:20) እነዚህ ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ ይሖዋን የሚያገለግሉት በየፊናቸው እንዳልሆነም ልብ በል። ከቅቡዓን ወንድሞቻቸው ጋር ‘በአንድ እረኛ’ ሥር እንደ ‘አንድ መንጋ’ ሆነው ለአምልኮ በመሰባሰብ ለጽዮን ውበት ድምቀት ይሰጣሉ።—ዮሐንስ 10:16
ነጋዴዎችና እረኞች ወደ ጽዮን መጡ
11, 12. ወደ ጽዮን የሚተምሙት ሰዎች ሁኔታ ምን እንደሚመስል ግለጽ።
11 በትንቢት በተነገረው መሠረት እነዚህ ሰዎች መሰብሰባቸው ይሖዋን የሚያወድሱት ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እንዲጨምር አድርጓል። ይህ ቀጥሎ ባለው ትንቢት ላይ አስቀድሞ ተነግሯል። በትንቢቱ ውስጥ ከተጠቀሰችው ሴት ጋር በጽዮን ተራራ እንደቆምህ አድርገህ አስብ። እስቲ ዓይንህን ወደ ምሥራቅ አቅንተህ ተመልከት፤ ምን ይታይሃል? “የግመሎች ብዛት፣ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፣ ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፣ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ።” (ኢሳይያስ 60:6) ብዙ ቁጥር ያላቸው ነጋዴዎች የግመል ቅፍለቶቻቸውን እየመሩ ወደ ኢየሩሳሌም ይተምማሉ። ግመሎቹ ምድሪቱን እንደ ጎርፍ አጥለቅልቀዋታል! ነጋዴዎቹ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች፣ ይህም ‘ወርቅና ዕጣን’ ጭነዋል። እንዲሁም እነዚህ ነጋዴዎች ‘የይሖዋን ምስጋና ለማውራት’ ማለትም ይሖዋን በይፋ ለማወደስ ወደ ብርሃኑ መጥተዋል።
12 እየተመሙ የሚመጡት ነጋዴዎች ብቻ አይደሉም። እረኞችም ወደ ጽዮን እየጎረፉ ነው። ትንቢቱ በመቀጠል “የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል” ይላል። (ኢሳይያስ 60:7ሀ) ከብት አርቢ ነገዶችም ከመንጋቸው መካከል ለይሖዋ ምርጡን ለመስጠት ወደ ቅድስቲቱ ከተማ እየነጎዱ ነው። ከዚህም በላይ ጽዮንን ለማገልገል ራሳቸውን አቅርበዋል! ይሖዋ እነዚህን የባዕድ አገር ሰዎች የሚቀበላቸው እንዴት ይሆን? አምላክ ራሱ እንዲህ በማለት ይመልሳል:- “እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፣ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ [“አስጌጣለሁ፣” NW ]።” (ኢሳይያስ 60:7ለ) ይሖዋ እነዚህ የባዕድ አገር ሰዎች የሚያቀርቡትን ስጦታና አገልግሎት በአክብሮት ይቀበላል። የሚያቀርቡት ስጦታ የእሱን ቤተ መቅደስ ያስጌጣል።
13, 14. ከምዕራብ አቅጣጫ ሲመጣ የታየው ምንድን ነው?
13 አሁን ደግሞ ዓይንህን አቅንተህ ወደ ምዕራብ ተመልከት። ምን ይታይሃል? ከሩቅ ነጭ ደመና የሚመስል ነገር በባሕሩ ላይ ይታያል። ይሖዋ “ርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፣ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው?” በማለት በአንተም አእምሮ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን ጥያቄ ይጠይቃል። (ኢሳይያስ 60:8) ይሖዋ ለራሱ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ይላል:- “እርሱ አክብሮሻልና [“አስጊጦሻልና፣” NW ] ለአምላክሽ ለእግዚአብሔር ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ልጆችሽን ከሩቅ ከእነርሱ ጋርም ብራቸውንና ወርቃቸውን ያመጡ ዘንድ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል።”—ኢሳይያስ 60:9
14 ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ? ነጩ ደመና ከምዕራብ አቅጣጫ እየቀረበ ሲመጣ እጅብ ያሉ ጥቃቅን ነገሮች ወይም ሞገዱን ሰንጥቆ የሚያልፍ የአእዋፍ መንጋ ይመስላል። ይበልጥ እየተጠጉ ሲመጡ ግን በነፋስ እየታገዙ የሚሄዱ ሸራቸውን የዘረጉ መርከቦች መሆናቸው ይታወቃል። ወደ ኢየሩሳሌም የሚተምሙት መርከቦች ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ የእርግብ መንጋ ይመስላሉ። እነዚህ በከፍተኛ ፍጥነት የሚነጉዱ መርከቦች ይሖዋን ለማምለክ ወደ ኢየሩሳሌም የሚያቀኑ አማኞችን አሳፍረው ከሩቅ አገር የተነሡ ናቸው።
የይሖዋ ድርጅት እያደገ ሄደ
15. (ሀ) ኢሳይያስ 60:4-9 ምን ዓይነት ጭማሪ እንደሚኖር ይተነብያል? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት መንፈስ ያሳያሉ?
15 ከ4 እስከ 9 ባሉት ቁጥሮች ላይ የሰፈረው ሐሳብ ከ1919 ወዲህ የታየውን ዓለም አቀፍ እድገት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ እንዴት ያለ ሕያው ትንቢታዊ መግለጫ ነው! ይሖዋ ጽዮንን እንዲህ ባለ ጭማሪ የባረካት ለምንድን ነው? ከ1919 አንስቶ የአምላክ እስራኤል በታዛዥነትና በጽናት ብርሃኑን በማብራቱ ነው። ይሁንና ቁጥር 7 ላይ እንደተገለጸው አዲስ መጪዎቹ ‘በአምላክ መሠዊያ ላይ እንደሚወጡ’ አስተውላችኋል? መሠዊያ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ ሲሆን ይህ የትንቢቱ ገጽታ የይሖዋ አገልግሎት መሥዋዕት ማቅረብ እንደሚጠይቅ ያስታውሰናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ . . . እለምናችኋለሁ፣ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው።” (ሮሜ 12:1) ጳውሎስ ከተናገራቸው ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ እውነተኛ ክርስቲያኖች በሳምንት አንዴ በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ በመገኘታቸው ብቻ አይረኩም። ንጹሕ የሆነውን አምልኮ ለማራመድ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን ይሰጣሉ። እንዲህ ዓይነት ለአምላክ ያደሩ ሰዎች መገኘታቸው የይሖዋን ቤት የሚያስጌጥ አይደለምን? ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ቤቱን እንደሚያስጌጠው ያሳያል። እንደዚህ ያሉ ቀናተኛ አምላኪዎች ደግሞ በይሖዋ ዓይን ውብ እንደሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
16. በጥንት ዘመን ለመልሶ ግንባታው ሥራ ድጋፍ የሰጡት እነማን ናቸው? በዘመናችንስ?
16 አዲስ መጪዎቹ የመሥራት ፍላጎት አላቸው። ትንቢቱ በመቀጠል “መጻተኞች ቅጥርሽን ይሠራሉ፣ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል” ይላል። (ኢሳይያስ 60:10) እነዚህ ቃላት ከባቢሎን ምርኮ መልስ የመጀመሪያ ፍጻሜአቸውን ባገኙበት ወቅት ከሌሎች ብሔራት የመጡ ነገሥታትና ሌሎች ሰዎች ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ መልሶ ለመገንባቱ ሥራ ድጋፍ ሰጥተዋል። (ዕዝራ 3:7፤ ነህምያ 3:26) በዘመናዊ ፍጻሜው መሠረት ደግሞ እጅግ ብዙ ሰዎች እውነተኛውን አምልኮ በመገንባት ረገድ ከቅቡዓኑ ጋር ይተባበራሉ። ክርስቲያን ጉባኤን በመገንባቱ ሥራ በመተባበር በከተማ የተመሰለውን የይሖዋ ድርጅት ‘ቅጥር’ ያጠናክራሉ። እንዲሁም በመንግሥት አዳራሽ፣ በትላልቅ መሰብሰቢያ አዳራሾችና በቤቴል ቤቶች ግንባታ ሥራ ይካፈላሉ። እያደገ የሚሄደውን የይሖዋን ድርጅት ፍላጎት ለማሟላት በእነዚህ ሁሉ መንገዶች ከቅቡዓን ወንድሞቻቸው ጋር ይተባበራሉ!
17. ይሖዋ ሕዝቡን የሚያስጌጥበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?
17 የኢሳይያስ 60:10 የመጨረሻ ቃላት ከፍተኛ ማጽናኛ ይዘዋል! ይሖዋ “በቁጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁ” ይላል። አዎን፣ ይሖዋ በ1918/19 ሕዝቡን ቀጥቶ ነበር። ሆኖም ይህ ከተፈጸመ ረጅም ጊዜ አልፏል። አሁን ይሖዋ በመንፈስ ለተቀቡ አገልጋዮቹና አጋሮቻቸው ለሆኑት ሌሎች በጎች ምሕረት የሚያሳይበት ጊዜ ነው። ከፍተኛ ጭማሪ እንዲያገኙ በመባረክ በምሳሌያዊ አነጋገር ‘እነርሱን ማስጌጡ’ ምሕረት እንዳሳያቸው ያረጋግጣል።
18, 19. (ሀ) ይሖዋ ወደ ድርጅቱ የሚመጡትን አዲሶች በተመለከተ የገባው ቃል ምንድን ነው? (ለ) የኢሳይያስ ምዕራፍ 60 የቀሩት ቁጥሮች ምን ያሳውቁናል?
18 በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አዲስ “መጻተኞች” ከይሖዋ ድርጅት ጋር ይተባበራሉ። ደግሞም ተጨማሪ ሰዎች ይገቡ ዘንድ በሩ ክፍት ነው። ይሖዋ ጽዮንን እንዲህ ይላታል:- “በሮችሽም ሁልጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጥግና የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ያመጡ ዘንድ ሌሊትና ቀን አይዘጉም።” (ኢሳይያስ 60:11) አንዳንድ ተቃዋሚዎች እነዚህን ‘በሮች’ ለመዝጋት ሙከራ አድርገዋል፤ ሆኖም እንደማይሳካላቸው እናውቃለን። በዚያም ሆነ በዚህ በሮቹ ክፍት ሆነው እንደሚቆዩ የተናገረው ይሖዋ ራሱ ነው። ጭማሪው አያቆምም።
19 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ ሕዝቡን በማስጌጥ በረከቱን ያወረደባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። የኢሳይያስ ምዕራፍ 60 የቀሩት ቁጥሮች እነዚህ መንገዶች ምን እንደሆኑ በትንቢታዊ መንገድ ይገልጻሉ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ሴቲቱ ማን ናት? በምድር ላይ የምትወከለውስ በማን ነው?
• የጽዮን ልጆች መሬት ላይ ተደፍተው የነበረው መቼ ነው? ‘የተነሱትስ’ መቼና እንዴት ነበር?
• ይሖዋ የተለያዩ መግለጫዎችን በመጠቀም በዛሬው ጊዜ የሚታየውን የመንግሥቱን ሰባኪዎች እድገት የተነበየው እንዴት ነበር?
• ይሖዋ ለሕዝቦቹ ብርሃኑን ያበራላቸው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ሴቲቱ” እንድትነሳ ትእዛዝ ተሰጥቷታል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መርከቦቹ ከርቀት ሲታዩ ርግቦችን ይመስላሉ