የይሖዋ ክብር በሕዝቡ ላይ አበራ
‘ይሖዋ የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናል።’—ኢሳይያስ 60:20 NW
1. ይሖዋ ታማኝ ሕዝቡን የሚባርከው እንዴት ነው?
“እግዚአብሔር በሕዝቡ ደስ ይለዋልና፤ የዋሃንንም በማዳኑ ውበት ያጐናጽፋል።” (መዝሙር 149:4 አ.መ.ት ) ይህን የተናገረው በጥንት ዘመን የኖረው መዝሙራዊው ሲሆን ታሪክ የዚህን አባባል እውነተኝነት ያረጋግጣል። ይሖዋ ሕዝቦቹ ታማኝ ሲሆኑ ይንከባከባቸዋል፣ ያበዛቸዋል እንዲሁም ይጠብቃቸዋል። በጥንት ዘመን ጠላቶቻቸውን ድል እንዲነሱ አስችሏቸዋል። በዛሬው ጊዜ በመንፈሳዊ ያጠነከራቸው ከመሆኑም በላይ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት መዳን እንደሚያገኙ ዋስትና ሰጥቷቸዋል። (ሮሜ 5:9) እንዲህ የሚያደርግላቸው በፊቱ ውብ በመሆናቸው ነው።
2. የአምላክ ሕዝቦች ተቃውሞ ቢደርስባቸውም እንኳ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችላሉ?
2 በጨለማ በተዋጠ ዓለም ውስጥ ‘እግዚአብሔርን እየመሰሉ የሚኖሩ’ ሰዎች ተቃውሞ እንደሚያጋጥማቸው የታወቀ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ይሁን እንጂ ይሖዋ የተቃዋሚዎችን አድራጎት የሚመለከት ከመሆኑም በላይ እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃቸዋል:- “ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፣ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ።” (ኢሳይያስ 60:12) በዛሬው ጊዜ ተቃውሞ የሚሰነዘረው በተለያየ መንገድ ነው። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ተቃዋሚዎች እውነተኛ ክርስቲያኖች ለይሖዋ የሚያቀርቡት አምልኮ በሕግ እንዲታገድ ለማድረግ ይሞክራሉ። በሌሎች አገሮች ደግሞ ሃይማኖታዊ አክራሪዎች የይሖዋን ሕዝቦች ይደበድባሉ እንዲሁም መኖሪያቸውን በእሳት ያቃጥላሉ። ሆኖም ይሖዋ ፈቃዱ እንዳይፈጸም ለማድረግ የሚሰነዘር ማንኛውም ተቃውሞ ምን ውጤት እንደሚኖረው አስቀድሞ ተናግሯል። ተቃዋሚዎች አይሳካላቸውም። በዚህ ምድር ላይ በልጆችዋ የተወከለችውን ጽዮንን የሚዋጉ ሰዎች ማሸነፍ አይችሉም። ይህ ታላቁ አምላካችን ይሖዋ የሰጠን የሚያበረታታ ዋስትና አይደለም?
ከጠበቁት በላይ በረከት አገኙ
3. የይሖዋ ሕዝቦች ውበትና ፍሬያማነት በምሳሌያዊ ሁኔታ የተገለጸው እንዴት ነው?
3 በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ይሖዋ ሕዝቦቹን ከጠበቁት በላይ እንደባረካቸው በተጨባጭ ታይቷል። በተለይ የአምልኮቱን ቦታና በዚያ የታቀፉትን ስሙን የሚሸከሙ ሰዎች ደረጃ በደረጃ አስጊጧቸዋል። የኢሳይያስ ትንቢት እንደሚያሳየው ጽዮንን እንዲህ ይላታል:- “የመቅደሴንም ስፍራ ያስጌጡ ዘንድ የሊባኖስ ክብር፣ ጥዱና አስታው ባርሰነቱም፣ ወደ አንቺ ይመጣሉ፣ የእግሬንም ስፍራ አከብራለሁ።” (ኢሳይያስ 60:13) ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈኑ ተራሮች ዓይን ይማርካሉ። በመሆኑም ግርማ ሞገስ ያላቸው ዛፎች የይሖዋ ሕዝቦች ለተላበሱት ውበትና ላገኙት የተትረፈረፈ ፍሬ ተስማሚ ምሳሌ ናቸው።—ኢሳይያስ 41:19, 20፤ 55:13
4. ‘መቅደሱ’ እና ‘የይሖዋ የእግሩ ስፍራ’ ምንድን ናቸው? እነዚህ ነገሮች የተዋቡትስ እንዴት ነው?
4 ኢሳይያስ 60:13 ላይ የተጠቀሰው ‘መቅደስ’ እና ‘[የይሖዋ] የእግር ስፍራ’ ምንድን ነው? እነዚህ መግለጫዎች የታላቁን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አደባባይ ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ለአምልኮ ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚቻልበትን ዝግጅት የሚያመለክቱ ናቸው። (ዕብራውያን 8:1-5፤ 9:2-10, 23) ይሖዋ ከብሔራት ሁሉ ሰዎችን በመሰብሰብና ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ መጥተው እንዲያመልኩት በማድረግ ቦታውን የማስዋብ ዓላማ እንዳለው ተናግሯል። (ሐጌ 2:7) ቀደም ሲል ኢሳይያስ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ብዙ ሰዎች ከፍ ወዳለው ይሖዋ የሚመለክበት ተራራ ሲጎርፉ ተመልክቷል። (ኢሳይያስ 2:1-4) ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ “አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” በራእይ ተመልክቷል። እነዚህ ሰዎች ‘በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሌሊትና ቀን በመቅደሱ ያመልኩታል።’ (ራእይ 7:9, 15) እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እያገኙ ባሉበት በዚህ ዘመን የይሖዋ ቤት ውበት ለመላበሱ የዓይን ምስክሮች ነን።
5. የጽዮን ልጆች ያገኙት ከፍተኛ መሻሻል ምንድን ነው?
5 ይህ ሁሉ ለጽዮን ከፍተኛ መሻሻል ነው! ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “ከሰውም ማንም እስከማያልፍብሽ ድረስ የተተውሽና የተጠላሽ ነበርሽ፤ ነገር ግን የዘላለም ትምክሕትና የልጅ ልጅ ደስታ አደርግሻለሁ።” (ኢሳይያስ 60:15) በእርግጥም በአንደኛው የዓለም ጦርነት መደምደሚያ አካባቢ ‘የአምላክ እስራኤል’ የተተወ ያህል ሆኖ ነበር። (ገላትያ 6:16) በምድር ላይ ያሉት የጽዮን ልጆች አምላክ ለእነሱ ያለውን ፈቃድ በግልጽ ስላላስተዋሉ ‘እንደተተዉ’ ተሰምቷቸው ነበር። በ1919 ግን ይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮቹን እንደ አዲስ ለሥራ በማንቀሳቀስ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ድንቅ በሆነ መንፈሳዊ ብልጽግና ባርኳቸዋል። ይህ ጥቅስ የያዘው ተስፋ የሚያነቃቃ አይደለምን? ይሖዋ ጽዮንን ‘ትምክሕት’ የሚጣልባት እንደሆነች አድርጎ ይመለከታታል። አዎን፣ የጽዮን ልጆችም ሆኑ ይሖዋ ራሱ በጽዮን ላይ ትምክሕት ይጥላሉ። የከፍተኛ “ደስታ” ምንጭ ትሆናለች። ደግሞም ደስታው ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ አይደለም። በምድራዊ ልጆቿ የተወከለችው ጽዮን የምትገኝበት የላቀ ሁኔታ ‘ለልጅ ልጅ’ የሚቀጥል ስለሆነ ማቆሚያ የለውም።
6. እውነተኛ ክርስቲያኖች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የተጠቀሙት እንዴት ነው?
6 ሌላም መለኮታዊ ተስፋ ተሰጥቷል። ይሖዋ ጽዮንን እንዲህ ብሏታል:- “የአሕዛብንም ወተት ትጠጫለሽ የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ እኔም እግዚአብሔር የያዕቆብ ኃያል፣ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ።” (ኢሳይያስ 60:16) ጽዮን ‘የአሕዛብን ወተት’ የጠጣችውና ‘የነገሥታትን ጡት’ የጠባችው እንዴት ነው? ቅቡዓን ክርስቲያኖችና አጋሮቻቸው የሆኑት “ሌሎች በጎች” ንጹሑን አምልኮ ለማስፋፋት አንዳንድ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀማቸው ነው። (ዮሐንስ 10:16) በፈቃደኝነት የሚሰጠው የገንዘብ መዋጮ ዓለም አቀፋዊ የሆነ ታላቅ የስብከትና የማስተማር ሥራ እንዲካሄድ አስችሏል። በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሚገባ በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ማተም ተችሏል። በዛሬው ጊዜ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ደርሷቸዋል። የበርካታ ብሔራት ዜጎች ይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮቹን ከመንፈሳዊ ምርኮ የታደገ እውነተኛ አዳኝ መሆኑን በመማር ላይ ናቸው።
ድርጅታዊ መሻሻል
7. የጽዮን ልጆች ምን ከፍተኛ መሻሻል አድርገዋል?
7 በተጨማሪም ይሖዋ ድርጅታዊ መሻሻል እንዲያደርጉ በመባረክ ሕዝቡን አስጊጧል። በኢሳይያስ 60:17 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “በናስ ፋንታ ወርቅን፣ በብረትም ፋንታ ብርን፣ በእንጨትም ፋንታ ናስን፣ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፣ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ።” በናስ ፋንታ ወርቅ መተካት ትልቅ መሻሻል ነው። በሌሎቹም ማዕድናት እንዲሁ። ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ የአምላክ እስራኤል በመጨረሻዎቹ ቀናት ያለማቋረጥ ድርጅታዊ መሻሻል አድርጓል። ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት።
8-10. ከ1919 አንስቶ የተደረጉትን አንዳንድ ድርጅታዊ ማሻሻያዎች ግለጽ።
8 ከ1919 በፊት የአምላክ ሕዝብ ጉባኤዎች የሚተዳደሩት የጉባኤው አባላት በዲሞክራሲያዊ መንገድ በመረጧቸው ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ነበር። ከዚያ ዓመት አንስቶ ግን “ታማኝና ልባም ባሪያ” በየጉባኤው የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴውን የሚከታተል የአገልግሎት ዲሬክተር ይሾም ጀመር። (ማቴዎስ 24:45-47) ይሁን እንጂ በምርጫ የተሾሙ አንዳንድ ሽማግሌዎች ለወንጌላዊነቱ ሥራ የተሟላ ድጋፍ ባለመስጠታቸው ይህ ዝግጅት በበርካታ ጉባኤዎች ውስጥ እምብዛም ውጤታማ አልሆነም። ከዚህ የተነሣ በ1932 ጉባኤዎች ሽማግሌዎችንና ዲያቆናትን መምረጣቸው ቀረና ከአገልግሎት ዲሬክተሩ ጋር በመሆን በአገልግሎት ኮሚቴው ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞችን እንዲመርጡ ተደረገ። ይህ ‘በእንጨት ፋንታ ናስ’ እንደተባለው ትልቅ መሻሻል ነው!
9 በ1938 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጉባኤዎች ከቅዱስ ጽሑፋዊው አሠራር ጋር ይበልጥ ስምም የሆነ የተሻለ ዝግጅት መከተል ጀመሩ። የየጉባኤው አስተዳደር ለአንድ የቡድን አገልጋይ ተሰጥቶ ሌሎች አገልጋዮች እንዲያግዙት ተደረገ። ሁሉም የሚሾሙት ግን በታማኝና ልባም ባሪያ የበላይ ክትትል ነበር። በምርጫ የሚደረግ ሹመት አከተመ! በዚህ መንገድ በጉባኤ ውስጥ ሹመት የሚሰጠው በቲኦክራሲያዊ መንገድ ሆነ። ይህም ‘በድንጋይ ፋንታ ብረት’ ወይም ‘በናስ ፋንታ ወርቅ’ ሊባል ይችላል።
10 ከዚያ ጊዜ ወዲህም መሻሻል መታየቱ ቀጥሏል። ለምሳሌ ያህል በ1972 የበላይ ሆኖ የሚያገለግል አንድ ሽማግሌ በመሾም ፋንታ በቲኦክራሲያዊ መንገድ የተሾሙ በአንድነት የሚያገለግሉ ሽማግሌዎችን ያቀፈ አካል በየጉባኤው እንዲቋቋም ተደረገ። ይህ አሠራር የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤዎች ይከተሉት ከነበረው አሠራር ጋር ይበልጥ የሚመሳሰል ነው። የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ደግሞ ሌላ ማሻሻያ ተደርጎ ነበር። በአንዳንድ ሕጋዊ ኮርፖሬሽኖች የአስተዳደር መዋቅር ላይ ማስተካከያ የተደረገ ሲሆን ይህም የአስተዳደር አካሉ በየጊዜው በሚነሱ ሕግ ነክ ጉዳዮች ከመጠመድ ይልቅ ይበልጥ በተሟላ መልኩ በአምላክ ሕዝብ መንፈሳዊ ፍላጎት ላይ እንዲያተኩር አስችሎታል።
11. የይሖዋ ሕዝቦች እነዚህን ድርጅታዊ ለውጦች እንዲያደርጉ የረዳቸው ማን ነው? ለውጦቹስ ምን ውጤት አስገኝተዋል?
11 የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን የማሻሻያ ለውጦች እንዲያደርጉ የረዳቸው ማን ነው? ከይሖዋ አምላክ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ‘ወርቅ አመጣለሁ’ ሲል የተናገረው እሱ ነው። ደግሞም “አለቆችሽንም ሰላም፣ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ” ብሎ የተናገረው እሱ ነው። አዎን፣ ለሕዝቡ የበላይ ጥበቃ የሚያደርገው ይሖዋ ነው። በትንቢት የተነገረው ድርጅታዊ መሻሻል ይሖዋ ሕዝቡን እያስጌጠ እንዳለ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ከዚህም የተነሣ የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ መንገዶች ተባርከዋል። ኢሳይያስ 60:18:- “ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፣ በዳርቻሽም ውስጥ ጉስቁልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥርሽን መዳን በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያለሽ” ይላል። ይህ እንዴት ያለ ድንቅ ነገር ነው! ሆኖም ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
12. እውነተኛ ክርስቲያኖች የላቀ ሰላም ሊያገኙ የቻሉት እንዴት ነው?
12 እውነተኛ ክርስቲያኖች ትምህርትና መመሪያ ለማግኘት ይሖዋን ይጠባበቃሉ። እንዲህ ማድረጋቸው የሚያስገኘውን ውጤት ኢሳይያስ “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” ሲል በትንቢት ገልጾታል። (ኢሳይያስ 54:13) በተጨማሪም የይሖዋ መንፈስ በሕዝቡ ላይ የሚሠራ ሲሆን ይህ መንፈስ ከሚያፈራቸው ፍሬዎች አንዱ ሰላም ነው። (ገላትያ 5:22, 23) የይሖዋ ሕዝቦች ሰላማዊ መሆናቸው ሁከት በነገሠበት ዓለም ውስጥ መንፈስ የሚያድስ የበረሃ ገነት አድርጓቸዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርስ የሚፋቀሩ በመሆናቸው ምክንያት ያገኙት ሰላም በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖረውን ሕይወት የሚያመላክት ቅምሻ ነው። (ዮሐንስ 15:17፤ ቆላስይስ 3:14) ለአምላካችን ውዳሴና ክብር የሚያመጣውን እንዲሁም የመንፈሳዊ ገነታችን ጉልህ ገጽታ የሆነውን ይህንን ሰላም በማግኘታችንና ለዚህ ሰላም የበኩላችንን አስተዋጽኦ በማበርከታችን ሁላችንም ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል!—ኢሳይያስ 11:9
የይሖዋ ብርሃን አይቋረጥም
13. ይሖዋ ብርሃኑን በሕዝቡ ላይ ማብራቱን እንደማያቋርጥ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
13 ይሖዋ ብርሃኑን በሕዝቡ ላይ ማብራቱን ይቀጥል ይሆን? አዎን፣ ይቀጥላል! ኢሳይያስ 60:19, 20 እንዲህ ይላል:- “ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ፣ አምላክሽም ክብርሽ [“ጌጥሽ፣” NW ] ይሆናልና ፀሐይ በቀን ብርሃን አይሆንልሽም፣ የጨረቃም ብርሃን በሌሊት አያበራልሽም። እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናልና፣ የልቅሶሽም ወራት ታልቃለችና ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም ጨረቃሽም አይቋረጥም።” በ1919 በመንፈሳዊ ሁኔታ በግዞት የተወሰዱት ሰዎች ‘ለቅሶ’ ካበቃ በኋላ ይሖዋ ብርሃኑን ያበራላቸው ጀመር። ከ80 ዓመታት በላይ ካለፈ በኋላም የይሖዋ ብርሃን ስላልተቋረጠባቸው ሞገሱን ማግኘታቸውን ቀጥለዋል። ብርሃኑ ወደፊትም አይቋረጥባቸውም። ከአገልጋዮቹ ጋር በተያያዘ አምላካችን እንደ ፀሐይ ‘አይጠልቅም’ ወይም እንደ ጨረቃ ‘አይቋረጥም።’ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ብርሃኑን ለዘላለም ያበራላቸዋል። ጨለማ በዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ስንኖር ይህ ለእኛ እንዴት ግሩም ዋስትና ነው!
14, 15. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች በአጠቃላይ ‘ጻድቃን’ የሆኑት በምን መንገድ ነው? (ለ) ኢሳይያስ 60:21ን በተመለከተ ሌሎች በጎች በተስፋ የሚጠባበቁት ምንድን ነው?
14 አሁን ደግሞ ይሖዋ የጽዮን ምድራዊ ወኪል ስለሆነው ስለ አምላክ እስራኤል የሚናገረውን ተጨማሪ የተስፋ ቃል አዳምጥ። ኢሳይያስ 60:21 “ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ እኔም እከብር ዘንድ የአታክልቴን ቡቃያ፣ የእጄ ሥራ የምትሆን ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ” ይላል። በ1919 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ ሥራው እንቅስቃሴ ሲመለሱ ለየት ያሉ ሕዝቦች ነበሩ። እጅግ ኃጢአተኛ በሆነ ዓለም ውስጥ በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባላቸው ጽኑ እምነት ‘ጸድቀዋል።’ (ሮሜ 3:24፤ 5:1) ከዚያም ከባቢሎን ምርኮ እንደተለቀቁት እስራኤላውያን ሁሉ መንፈሳዊ ገነት የሰፈነበትን ምሳሌያዊ ‘ምድር’ ወይም የእንቅስቃሴ ቀጣና ወርሰዋል። (ኢሳይያስ 66:8) ከጥንቱ የእስራኤል ብሔር በተለየ መልኩ የአምላክ እስራኤል በብሔር ደረጃ ታማኝነቱን ስለማያጓድል ምድሪቱ ያላት እንደ ገነት ያለ ውበት ፈጽሞ አይጠወልግም። የሚያሳዩት እምነት፣ ጽናትና ቅንዓት የአምላክን ስም ማስከበሩን ይቀጥላል።
15 የዚህ መንፈሳዊ ብሔር አባላት በሙሉ በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር ናቸው። በሁሉም ልብ ላይ የይሖዋ ሕግ የተጻፈ ሲሆን በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይሖዋ ኃጢአታቸውን ይቅር ብሏቸዋል። (ኤርምያስ 31:31-34) ይሖዋ እንደ ‘ልጆቹ’ በማየት ጻድቃን አድርጎ ይቆጥራቸዋል፤ እንዲሁም ፍጹማን አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ሮሜ 8:15, 16, 29, 30) የእምነት አጋሮቻቸው የሆኑት ሌሎች በጎችም በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ በማመናቸው የኃጢአት ይቅርታ አግኝተው እንደ አብርሃም የአምላክ ወዳጆች በመሆን እንደ ጻድቃን ተቆጥረዋል። ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል።’ እንዲሁም እነዚህ ሌሎች በጎች በተስፋ የሚጠባበቁት ሌላ የላቀ በረከት አለ። ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት ካለፉ ወይም ትንሣኤ ካገኙ በኋላ የኢሳይያስ 60:21 ቃላት ቃል በቃል ፍጻሜያቸውን አግኝተው መላዋ ምድር ገነት ስትሆን ይመለከታሉ። (ራእይ 7:14፤ ሮሜ 4:1-3) በዚያን ጊዜ “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11, 29
እድገቱ ይቀጥላል
16. ይሖዋ የሰጠው አስደናቂ የተስፋ ቃል ምንድን ነው? ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነው?
16 በኢሳይያስ 60 የመጨረሻ ቁጥር ላይ ይሖዋ በምዕራፉ ውስጥ የተናገረውን የመጨረሻ የተስፋ ቃል እናገኛለን። ጽዮንን እንዲህ ይላታል:- “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ።” (ኢሳይያስ 60:22) በዚህ ባለንበት ዘመን ይሖዋ ቃሉን ጠብቋል። ቅቡዓኑ በ1919 ወደ ሥራው እንቅስቃሴ ሲመለሱ በቁጥር ጥቂት ወይም ‘ታናሽ’ ነበሩ። ተጨማሪ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ሲሰበሰቡ ቁጥራቸው ጨምሮ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሌሎች በጎች በከፍተኛ ቁጥር መጉረፍ ጀመሩ። የአምላክ ሕዝብ ሰላም ማለትም ‘በምድራቸው’ ላይ የሰፈነው መንፈሳዊ ገነት ቅን ልብ ያላቸው በጣም ብዙ ሰዎች ተስበው እንዲመጡ ስላደረገ በእርግጥም ‘የሁሉም ታናሽ ለብርቱ ሕዝብ’ ሆኗል። በዛሬው ጊዜ የአምላክ እስራኤልንና ከስድስት ሚልዮን የሚበልጡ ‘መጻተኞችን’ ያካተተው ይህ “ሕዝብ” በዓለም ላይ ከሚገኙ ብዙ ሉዓላዊ መንግሥታት የበለጠ ቁጥር ያለው ብሔር ሆኗል። (ኢሳይያስ 60:10) ዜጎቹ በአጠቃላይ የይሖዋን ብርሃን በማንጸባረቁ ሥራ ይካፈላሉ። ይህ ደግሞ በእሱ ዓይን ሁሉም ውብ ሆነው እንዲታዩ ያደርጋል።
17. ኢሳይያስ ምዕራፍ 60ን መመርመርህ ምን ጥቅም አስገኝቶልሃል?
17 በእርግጥም፣ በኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ላይ የሚገኙትን ጎላ ያሉ ነጥቦች መመርመሩ እምነት የሚያጠነክር ነው። ይሖዋ ሕዝቦቹ በመንፈሳዊ ሁኔታ ምርኮኞች ሆነው እንደሚወሰዱና ከዚያም ተመልሰው እንደሚቋቋሙ ከረጅም ዘመናት በፊት ማወቁ የሚያስደስት ነው። ይሖዋ በዘመናችን የእውነተኛ አምላኪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ከረጅም ጊዜ በፊት ማየቱ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ እንደማይተወን ማወቁ ምንኛ ያጽናናል! ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ’ ሰዎች እንዲገቡ ‘የከተማይቱ’ በሮች ምንጊዜም ክፍት ሆነው እንደሚቆዩ መገለጹ እንዴት ያለ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው! (ሥራ 13:48) ይሖዋ በሕዝቡ ላይ ብርሃኑን ማብራቱን አያቆምም። የጽዮን ልጆች ብርሃናቸውን ይበልጥ ቦግ አድርገው ያበራሉ። ይህም ጽዮን ትምክሕት የሚጣልባት ሆና እንድትቀጥል ያስችላታል። (ማቴዎስ 5:16) በእርግጥም ከአምላክ እስራኤል ጎን ለመቆምና የይሖዋን ብርሃን የማንጸባረቅ መብታችንን ከፍ አድርገን ለመመልከት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጠናል!
ልታብራራ ትችላለህን?
• ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
• የጽዮን ልጆች ‘የአሕዛብን ወተት የጠጡት’ እንዴት ነው?
• ይሖዋ ‘በእንጨት ፋንታ ነሐስን ያመጣው’ እንዴት ነው?
• በኢሳይያስ 60:17, 21 ላይ ጎላ ብለው የተገለጹት የይሖዋ ሕዝቦች የሚያሳዩት ሁለት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
• ‘ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ’ የሆነው እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን
በእነዚህ የጥናት ርዕሶች ላይ የወጣው ትምህርት በ2001/02 በተደረገው “የአምላክ ቃል አስተማሪዎች” የአውራጃ ስብሰባ ላይ በንግግር ቀርቦ ነበር። ስብሰባው በተካሄደባቸው በአብዛኞቹ ቦታዎች ተናጋሪው በንግግሩ መደምደሚያ ላይ የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን (የእንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ሁለተኛ ጥራዝ መውጣቱን አሳውቆ ነበር። ቀደም ባለው ዓመት የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ጥራዝ ወጥቶ ነበር። ይህ አዲስ ጽሑፍ የኢሳይያስ መጽሐፍ በያዘው በእያንዳንዱ ጥቅስ ላይ ወቅታዊ የሆነ ማብራሪያ ይሰጣል። እነዚህ ጥራዞች እምነት ቀስቃሽ ለሆነው የኢሳይያስ ትንቢታዊ መጽሐፍ ያለንን ግንዛቤና አድናቆት ለማሳደግ ይረዱናል።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባድ ተቃውሞ ቢደርስባቸውም ‘ይሖዋ ሕዝቡን በማዳኑ ውበት ያጎናጽፋቸዋል’
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ሕዝቦች ንጹሑን አምልኮ ለማራመድ በአሕዛብ ዋጋማ እሴቶች ተጠቅመዋል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ድርጅታዊ መሻሻልና ሰላም እንዲኖር በማድረግ ሕዝቡን ባርኳል