የአምላክ የበቀል ቀን
ባለፈው ርዕስ ትምህርት ላይ እንደተመለከትነው ለመበቀል መሻታችን ስሕተት የሆነበት አያሌ ምክንያት አለ። ስሕተት የሆነበት ምክንያት ለዘለቄታው ለምንም ነገር የማይፈይድ በመሆኑ ነው። ስሕተት የሆነው የወዳጅነት ድልድይ በመገንባት ፈንታ ጠላትነትን ስለሚያጠነክር ነው። ስሕተት የሆነው የበቀል ሐሳብ ለሚያሳድረው ሰው ጎጂ ስለሆነ ነው።
ይሁን እንጂ የሰው በቀል ስሕተት የሆነበት ዋናው ምክንያት ሙሴ ለእሥራኤል፦ “አምላክህ ይሖዋ መሐሪ አምላክ ነው” ሲል የተናገረው ቃል ነው። (ዘዳግም 4:31) አምላክ መሐሪ ስለሆነ እኛም እንደ እሱ መሐሪዎች መሆን አለብን። ኢየሱስ ለተከታዮቹ፦ “አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ መሐሪ በመሆን ቀጥሉ” ብሏቸዋል።—ሉቃስ 6:36
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “የበቀል አምላክ ነው” በማለት ይገልጸዋል። (መዝሙር 94:1) ነቢዩ ኢሳይያስ “ስለተወደደችው የይሖዋ ዓመት” እና “አምላካችን ስለሚበቀልበት ቀን” ይናገራል። (ኢሳይያስ 61:2) አምላክ መሐሪም ተበቃይም ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? የአምላክን መሐሪነት መምሰል ካለብን ተበቃይነቱንስ መምሰል የሌለብን ለምንድን ነው?
የመጀመሪያውን ጥያቄ ለመመለስ አምላክ መሐሪ የሆነበት ምክንያት የሰው ልጆችን ስለሚወድና ሰዎች መንገዳቸውን ለማስተካከል ይችሉ ዘንድ አጋጣሚ ለመስጠት ሲል የተቻለውን ያህል ለረዥም ጊዜ ይቅር ይላል። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉ ብዙ ሰዎች በምሕረቱ ተጠቅመዋል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ምሕረት ሊቀጥል የሚችለው ፍትሕ እስከሚበየን ድረስ ብቻ ስለሆነ አምላክ ተበቃይ አምላክ ነው። ሰዎች መንገዳቸውን ፈጽሞ እንደማይለውጡ ሲያሳዩ የበቀሉ ቀን በተወሰነው ጊዜ ፍርዱን ያስፈጽማል።
ሁለተኛውን ጥያቄ ለመመለስ እኛ ተበቃዮች መሆናችን ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም በቀል መመለስ ያለበት አምላክ ስለሆነ ነው። ይሖዋ በፍርድ ፍጹም ነው። ሰዎች ግን አይደሉም። አምላክ አንድን ጉዳይ ከሁሉም አቅጣጫዎች ስለሚመለከት ሁልጊዜ ጻድቅ ውሣኔ ያደርጋል። እኛ ግን እንዲህ እንድናደርግ እምነት ሊጣልብን አይችልም። ጳውሎስ “ወዳጆች ሆይ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ለቁጣው ፈንታ ስጡት እንጂ ‘በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ’ ተብሎ ተጽፎአልና” በማለት የመከረን በዚህ ምክንያት ነው። (ሮሜ 12:19) ለእኛው ለራሳችን ብለን በቀልን በይሖዋ እጅ መተው አለብን።
የበቀል ቀን ለምን አስፈለገ?
የሆነ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ንስሐ ለማይገቡ ክፉ አድራጊዎች ፍርድ መስጠት እንደሚያስፈልግ በብዙ ቦታዎች ላይ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል “እግዚአብሔርን የማያውቁትን ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል” በማለት ተንብዮአል። (2 ተሰሎንቄ 1:8) እነዚህን ቃላት በጥሞና ለመመልከት ጥሩ ምክንያቶች አሉን። ለምን?
መጀመሪያ ነገር ዛሬ አብዛኞቹ ሰዎች የፈጣሪን ልዕልና በመቃወም ስለሚቀጥሉና ጻድቅ ሕጎቹንም ስለሚንቁ ነው። በአምላክ እንደሚያምኑ ይናገሩም አይናገሩ ጠባያቸው በግልጽ የሚያሳየው በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች እንደሆኑ የማይሰማቸው መሆኑን ነው። የመዝሙራዊው ቃላት እንዲህ ለመሰሉት ሁሉ ይሠራል፦ “ኃጢአተኛ ሰው እግዚአብሔርን ስለምን ይንቃል? በአሳቡስ ‘እግዚአብሔር አይቀጣኝም’ ለምን ይላል?” (መዝሙር 10:13 1980 ትርጉም) በእርግጥ ይሖዋ በዚህ ዓይነት ለዘላለም መሳለቂያ ሆኖ እንዲኖሩ አይፈቅድም። የፍቅር አምላክ ቢሆንም የፍትሕ አምላክም ነው። “አቤቱ ይሖዋ ሆይ ተነስ። እጅህም ከፍ ከፍ ይበል። የተጠቁትን አትርሳ” ስለሚል የፍትሕ ጉዳይ በእውነት የሚያሳስባቸውን ሰዎች ጩኸት ይሰማል።—መዝሙር 10:12
ከዚህም በላይ ሕግ አፍራሽ ሰዎች የምንኖርበትን መሬትም እያጠፉአት ነው። አየሩን፣ ምድሩንና ውሃውን እየመረዙት ነው። ምድርንም በፍትሕ መጓደልና በጭካኔ ሞልተዋታል። የሰው ዘሮችን ሕልውና በአስጊ ሁኔታ ላይ ለመጣል የሚችሉ ኬሚካል፣ ኑክሊየርና ሌሎች ገዳይ መሣሪያዎችን ያከማቻሉ። ለታዛዥ የሰው ልጆች አስተማማኝ መጪ ጊዜ ለማረጋገጥ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው። (ራእይ 11:18) ኢሳይያስ የበቀል ቀን በማለት የጠቀሰው ይህን ጣልቃ ገብነት ነው።
የአምላክ የበቀል ቀን ምን ያከናውናል?
በቫይን የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቃላት ማብራሪያ መዝገበ ቃላት መሠረት በግሪክኛ ቅዱስን ጽሑፎች በቀል የሚለው ቃል ከአምላክ ጋር ተያይዞ ሲሠራበት ቃል በቃል “‘ከፍትሕ የሚመነጭ’ ነው እንጂ ከመጎዳት ስሜት የሚመነጭ ወይም ከቁጣ ስሜት የሚመነጭ ሰው የሚፈጽመው በቀል አይደለም።” በመሆኑም አምላክ በጠላቶቹ ላይ የሚያመጣው በቀል የግል ቂም ለመወጣት የሚደረግ ገደብ የለሽ ደም አፍሳሽነት አይደለም። “ይሖዋ የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን በደለኞችንም . . . ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።—2 ጴጥሮስ 2:9
የአምላክ አገልጋዮች የበቀል ቀን ትክክለኛ ጠባይ ወይም አኗኗር የሚያረጋግጥበትና ጻድቁን ከክፉው ጭቆና የሚያድንበት ቀን በመሆኑ በተስፋ ይጠባበቁታል። ይህ ማለት ግን ሰው የሚጠሉና ቂመኞች ናቸው ማለት አይደለም። “(በሌላው) ሰው ጥፋት (መከራ) ደስ የሚለው ሳይቀጣ አይቀርም” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 17:5) በተቃራኒው ስለ በቀል ማንኛውንም ውሣኔ ለአምላክ በመተው መሐሪነትንና ርኅራሄን ይከተላሉ።
እውነት ነው ለተቆጡ ግለሰቦች መሐሪና ርኅሩኅ መሆን ቀላል አይሆንም። ቢሆንም ይቻላል፣ ብዙዎችም አድርገውታል። ለምሳሌ ያህል ፔድሮ የሚያሳዝን የልጅነት ዘመን ያሳለፈና አዘውትሮም ታላቅ ወንድሙ ይደበድበው የነበረ ሰው ነው። ስለዚህ ዓመፀኛ ሆኖ አደገ። ብዙ ጊዜም ከፖሊሶች ጋር ይጣላና ችግር ያጋጥመው ነበር። በወንድሙ ላይ የነበረውን ቂም በሚስቱና በልጆቹ ላይ ይወጣ ነበር። በመጨረሻ ከይሖዋ ምስክሮች አንዱን አዳመጠና ቆይቶም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ። “በይሖዋ እርዳታ ተለውጫለሁ። አሁን ከሰዎች ጋር በመጣላት ፋንታ ክርስቲያን ሽማግሌ በመሆን እየረዳኋቸው ነው” ይላል። በተመሳሳይ በመጽሐፍ ቅዱስና በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሌሎች ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎች እልከኛና ተበቃይ ከመሆን ለሌሎች ፍቅርና ትዕግሥት የሚያሳዩ ወደመሆን ተለውጠዋል።
አንተስ ምን ታደርጋለህ?
የአምላክን የበቀል ቀን መምጣት በአእምሮአችን መያዝ የይሖዋን ትዕግሥት እንድንጠቀምበት ይረዳናል። ነገር ግን ይህ የሚደረግበት ጊዜ ገደብ የሌለው አይደለም። ያ ቀን በቅርቡ ይደርሳል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ያ ቀን ከዚህ በፊት ለምን እንዳልመጣ “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ይሖዋ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም። ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል” በማለት ገልጾታል።—2 ጴጥሮስ 3:9
እንግዲያውስ ቅዱሳን ጽሑፎችን በማጥናትና ምክራቸውን በሥራ ላይ በማዋል ለአምላክ የበቀል ቀን መዘጋጀት አጣዳፊ ጉዳይ ነው። ይህም የመዝሙራዊውን “ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው። እንዳትበድል አትቅና (አትናደድ) ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ” የሚሉትን ቃላት ለመከተል ይረዳናል።—መዝሙር 37:8, 9
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአምላክ የበቀል ቀን በኋላ ‘ይሖዋን ተስፋ ያደረጉት ሰዎች ምድርን ይወርሳሉ’