ይሖዋ ልዩ መብት ያደላት ሴት ነበረች
“ደስ ይበልሽ፣ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው።” እንዴት ያለ ሰላምታ ነው! ተናጋሪው መልአኩ ገብርኤል ነው። ገብርኤል ኤሊ የሚባል ሰው ሴት ልጅ የሆነችውን ማርያም የምትባል ትሑት ልብ ያላት አንዲት ወጣት ሴት እያነጋገረ ነበር። ዓመቱ 3 ከዘአበ ሲሆን ቦታው የናዝሬት ከተማ ነበር።—ሉቃስ 1:26–28
ማርያም ለአናፂው ለዮሴፍ የታጨች ነበረች። በአይሁድ ሕግና ልማድ መሠረት እንዳገባት ሚስቱ ተደርጋ ትታይ ነበር። (ማቴዎስ 1:18) እሱም እንደ እሷ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለው ነበር። ታዲያ መልአኩ ልዩ መብት እንደተሰጣት አድርጎ ሰላም ያላት ለምንድን ነው?
ያገኘችው አስደናቂ መብት
ገብርኤል እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ማርያም ሆይ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።”—ሉቃስ 1:29–33
ማርያም በመገረምና ግራ በመጋባት “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” ስትል ጠየቀች። ገብርኤልም “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” ሲል መለሰ። መልአኩም ጥርጣሬዋን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ “እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፣ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፣ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና” በማለት ቀጠለ።—ሉቃስ 1:34–37
ማርያም ይህን አስደናቂ የአገልግሎት መብት ወዲያኑ ተቀበለች። በፈቃደኝነትና በትሕትና “እነሆኝ የጌታ ባሪያ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” ስትል መለሰች። ገብርኤልም ወዲያው ተለይቷት ሄደ። ማርያምም ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ሄደች። ካህኑ ዘካርያስና ሚስቱ ኤልሳቤጥ ወደሚኖሩበት ቤት ስትደርስ ሁኔታዎቹ ሁሉ በትክክል መልአኩ እንደነገራት ሆነው አገኘቻቸው። የማርያም ልብ እንዴት በደስታ ይሞላ! ከንፈሮቿ ለይሖዋ የውዳሴ ቃላት ማፍለቅ ጀመሩ።—ሉቃስ 1:38–55
የዮሴፍ ሚስት ሆነች
አንዲት ድንግል የኢየሱስን ሰብዓዊ አካል ልታስገኝ ነው። አስቀድሞ የተነገረውም በዚህ መንገድ እንደሚወለድ ነበር። (ኢሳይያስ 7:14፤ ማቴዎስ 1:22, 23) ነገር ግን የታጨች ድንግል የተፈለገችው ለምንድን ነው? ሕፃኑ የንጉሥ ዳዊትን ዙፋን የመውረስ ሕጋዊ መብት እንዲያገኝ የሚያስችለው አሳዳጊ አባት እንዲኖረው ለማድረግ ሲባል ነው። ዮሴፍና ማርያም፣ ሁለቱም ከይሁዳ ነገድ ሲሆኑ የንጉሥ ዳዊት ዝርያዎች ናቸው። ስለዚህ የኢየሱስ የመውረስ መብት በሁለቱም በኩል አስተማማኝ ነው። (ማቴዎስ 1:2–16፤ ሉቃስ 3:23–33) ምንም እንኳን የፀነሰች ብትሆንም ዮሴፍም ሕጋዊ ሚስቱ አድርጎ ከመውሰድ እንዳያመነታ በኋላ መልአኩ ማረጋገጫ የሰጠው በዚህ ምክንያት ነው።—ማቴዎስ 1:19–25a
አውግስጦስ ቄሣር ያወጣው የቀረጥ አዋጅ ዮሴፍና ማርያም ወደ ቤተ ልሔም ሄደው እንዲመዘገቡ አስገደዳቸው። እዚያ እያሉ ማርያም የበኩር ልጅዋን ወለደች። እረኞች ሕፃኑን ለማየት መጡና ለአባቱ ለይሖዋ ምስጋና አቀረቡ። የሙሴ ሕግ በሚያዘው መሠረት ከ40 የመንጻት ቀናት በኋላ ማርያም ለኃጢአትዋ ማስተሰርያ መሥዋዕት ለማቅረብ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ሄደች። (ዘሌዋውያን 12:1–8፤ ሉቃስ 2:22–24) ማርያም ንጽሕት ሆና ስላልተጸነሰችና ኃጢአት ከሚያመጣው እድፍ ነፃ ስላልሆነች የወረሰችው አለፍጽምና በማስተሰርያ መሥዋዕት መሸፈን ነበረበት።—መዝሙር 51:5
ማርያምና ዮሴፍ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሳሉ አረጋዊው ስምዖንና በዕድሜ ገፍታ የነበረችው ነቢይቷ ሐና የአምላክን ልጅ ለማየት መብት አግኝተዋል። የሰዎችን ትኩረት ስባ የነበረችው ማርያም አልነበረችም። (ሉቃስ 2:25–38) በኋላም ሰብአ ሰገል መጥተው የሰገዱት ለማርያም ሳይሆን ለኢየሱስ ነው።—ማቴዎስ 2:1–12
የኢየሱስ ወላጆች ክፉ የነበረው ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ወደ ግብፅ ሸሽተው በዚያው ከቆዩ በኋላ ወደ ናዝሬት ተመልሰው በአንዲት አነስተኛ መንደር ውስጥ መኖር ጀመሩ። (ማቴዎስ 2:13–23፤ ሉቃስ 2:39) ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን በአምላካዊ ቤተሰብ ውስጥ ያሳደጉት በዚሁ መንደር ነበር።
ማርያም ሌሎች ልጆች ነበሯት
ከጊዜ በኋላ ማርያምና ዮሴፍ ለኢየሱስ ሥጋዊ ወንድሞችና እኅቶች ወለዱለት። ኢየሱስ በአገልግሎቱ ምክንያት ወዳደገባት ከተማ ወደ ናዝሬት ሲመጣ በልጅነቱ ያውቁት የነበሩት ሰዎች ማን መሆኑን ለይተውታል። “ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን?” ሲሉ ጠይቀዋል። (ማቴዎስ 13:55, 56) የናዝሬት ነዋሪዎች የኢየሱስ ሥጋዊ ወንድሞችና እኅቶች እንደሆኑ የሚያውቋቸውን የዮሴፍንና የማርያምን ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጨምሮ ጠቅላላ ሰብዓዊ ቤተሰቡን መጥቀሳቸው ነበር።
እነዚህ የኢየሱስ ወንድሞችና እኅቶች የአጎቱ ልጆች አይደሉም። ዮሐንስ 2:12 “ከዚህ በኋላ [ኢየሱስ] ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ” በማለት ሥጋዊ ወንድሞቹንና ደቀ መዛሙርቱን በግልጽ ለይቶ ስለሚናገር ደቀ መዛሙርቱ ወይም መንፈሳዊ ወንድሞቹና እኅቶቹም አይደሉም። ከዓመታት በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ኬፋን ወይም ጴጥሮስን እንዳገኘው ከገለጸ በኋላ አክሎም “ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም” ሲል ገልጿል። (ገላትያ 1:19) ከዚህም በላይ ዮሴፍም “[ማርያም] የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም” የሚለው አነጋገር የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ከዚያ በኋላ ከእርሷ ጋር የጾታ ግንኙነት እንዳደረገና ሌሎች ልጆችን እንደወለደችለት ይጠቁማል። (ማቴዎስ 1:25) ለዚህም ነው ሉቃስ 2:7 ኢየሱስን ‘የበኩር ልጅዋ’ በማለት የሚጠራው።
አምላክን የምትፈራ እናት
ማርያም አምላክን የምትፈራ እናት ስለነበረች ልጆችዋን በጽድቅ መንገድ በማሠልጠን ረገድ ከዮሴፍ ጋር ትተባበር ነበር። (ምሳሌ 22:6) ማርያም ኤልሳቤጥን ሰላም ባለችበት ጊዜ የተጠቀመችበት በመንፈሳዊ የዳበረ አነጋገር ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ታጠና እንደነበረ የሚያሳይ ነው። የኢየሱስ እናት በዚህ ጊዜ ሐና የዘመረቻቸውን ስሜት የሚነኩ መዝሙሮች ደግማለች፤ በዚህም መዝሙራትን፣ ታሪካዊና ትንቢታዊ መጻሕፍትን እንዲሁም የሙሴን መጻሕፍት በሚገባ እንደምታውቅ አሳይታለች። (ዘፍጥረት 30:13፤ 1 ሳሙኤል 2:1–10፤ ምሳሌ 31:28፤ ሚልክያስ 3:12፤ ሉቃስ 1:46–55) ማርያም ትንቢታዊ ክስተቶችንና አባባሎችን በቃሏ እስክትይዛቸው ድረስ በደንብ ተምራቸው ነበር፤ እንደ ውድ ነገር በማየት በልቧ ውስጥ ቀርጻቸው ነበር፤ እንዲሁም በአእምሮዋ ውስጥ ታሰላስልባቸው ነበር። ሁኔታዎችንና አነጋገሮችን ለማስታወስ የቻለችው ቀደም ሲል በልቧ ውስጥ ከያዘችውና በአእምሮዋ ውስጥ ታሰላስልበት ከነበረው ሐሳብ ነው። ስለዚህ ሕፃን ለነበረው ኢየሱስ በወላጅነቷ የሚጠበቅባትን ትምህርት ለማካፈል በሚገባ የታጠቀች ነበረች።—ሉቃስ 2:19, 33
በሚገባ የተማረው የ12 ዓመቱ ኢየሱስ ያለው ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን የተማሩ ሰዎች አስደንቋል። በዚያ የፋሲካ ወቅት ኢየሱስ ከወላጆቹ ስለተለየ እናቱ “ልጄ ሆይ፣ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፣ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን” አለችው። ኢየሱስም “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” ሲል መለሰ። ማርያምም ይህ መልስ ምን ማለት እንደሆነ ለማስተዋል ስላልቻለች በልብዋ ይዛ ትጠብቀው ነበር። ወደ ናዝሬት ተመልሰው መጡ። ኢየሱስም “በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት” ያድግ ነበር።—ሉቃስ 2:42–52
ማርያም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሆናለች
በመጨረሻም ማርያም ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ለእሱ ከሰጡት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዷ መሆኗ ምንኛ ተገቢ ነው! ማርያም ምንም እንኳን አምላክ አንድ ልዩ ሥራ ሰጥቷት የነበረ ቢሆንም ገርና ከሌሎች ልቆ የመታየት ፍላጎት የሌላት ሴት ነበረች። ማርያም ቅዱሳን ጽሑፎችን ታውቃለች። ራሳችሁ ቅዱሳን ጽሑፎችን ብትመረምሩ በራሷ ላይ የብርሃን አክሊል ያላት “እመቤታችን” ተብላ የክርስቶስ ክብር በላይዋ ላይ ፈንጥቆ በዙፋን ላይ እንደተቀመጠች የሚገልጽ አንድም ሐሳብ አታገኙም። እንዲያውም ያሳለፈችውን ኑሮ መለስ ብላችሁ ስትመረምሩ ሰዎች ብዙም ትኩረት ያልሰጧት መሆኑን ትረዳላችሁ።—ማቴዎስ 13:53–56፤ ዮሐንስ 2:12
ኢየሱስ በተከታዮቹ መካከል እንደ ማርያም አምልኮ የመሳሰለው ማንኛውም ነገር እንዳይኖር በእንጭጩ ቀጭቶት ነበር። አንድ ጊዜ እየተናገረ ሳለ “ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፦ የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው።” “እርሱ ግን፦ . . . ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው” ሲል መለሰ። (ሉቃስ 11:27, 28) በአንድ የሠርግ ግብዣ ላይ ኢየሱስ ለማርያም “አንቺ ሴት፣ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” ብሏት ነበር። (ዮሐንስ 2:4) ሌሎች ትርጉሞች ደግሞ እንደሚከተለው ይነበባሉ፦ “ጉዳዩን ለእኔ ተይው” (ዊይማውዝ) “መመሪያ ልትሰጪኝ አትሞክሪ።” (አን አሜሪካን ትራንስሌሽን) እው ነት ነው፣ ኢየሱስ እናቱን ያከብር ነበር። ነገር ግን አምልኮታዊ አክብሮት ፈጽሞ አላሳያትም።
ዘላለማዊ መብቶች
ማርያም ልዩ መብቶችን አግኝታለች! ኢየሱስን ወልዳለች። ከዚያም ሕፃኑን በእናትነት ተንከባክባና አሠልጥና አሳድጋለች። በመጨረሻም እምነት በማሳየት የክርስቶስ ደቀ መዝሙርና መንፈሳዊ እኅት ሆናለች። ስለ ማርያም የተሰጠው የመጨረሻው ቅዱስ ጽሑፋዊ ፍንጭ በኢየሩሳሌም በሰገነት ላይ እንደነበረች ይጠቅሳል። እዚያም ከኢየሱስ ሐዋርያት፣ ከቀሩት ልጆቿና ከአንዳንድ ታማኝ ሴቶች ጋር ነበረች። ሁሉም የይሖዋ አምላኪዎች ናቸው።—ሥራ 1:13, 14
በመጨረሻም ማርያም ሞተችና አስከሬኗ ወደ አፈር ተመለሰ። ጥንት እንደነበሩት ቅቡዓን የውድ ልጅዋ ተከታዮች ሁሉ አምላክ መንፈሳዊ ፍጥረት አድርጎ ለማይሞት ሰማያዊ ሕይወት እርሷን ለማስነሣት የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በሞት አንቀላፍታ ቆይታለች። (1 ቆሮንቶስ 15:44, 50፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:8) ይህች ‘ልዩ መብት በማግኘት የታደለች’ ሴት በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኙበት ቦታ በመሆኗ ምንኛ ተደስታ ይሆን!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ማርያም ድንግል ባትሆን ኖሮ ማን ሊያገባት ይፈልግ ነበር? አይሁዶች አንዲት ልጃገረድ ድንግል መሆን አለባት የሚል የጠበቀ አቋም ነበራቸው።—ዘዳግም 22:13–19፤ ከዘፍጥረት 38:24–26 ጋር አወዳድር።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማርያም የኢየሱስ እናት የመሆን ልዩ መብት ታድሏታል