ምዕራፍ ሃያ ሰባት
ይሖዋ ንጹሕ አምልኮን ይባርካል
1. በኢሳይያስ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ጎላ ብለው የተጠቀሱት ጭብጦች የትኞቹ ናቸው? ለየትኞቹ ጥያቄዎችስ መልስ እናገኛለን?
በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ጭብጦች መካከል የተወሰኑት በመጽሐፉ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እጅግ ትኩረት በሚስብ መንገድ የተደመደሙ ሲሆን አንዳንድ አበይት ጥያቄዎችም መልስ አግኝተዋል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የይሖዋን ታላቅነት፣ ለግብዝነት ያለውን ጥላቻ፣ ክፉዎችን በመቅጣት ረገድ ያለውን ቁርጥ አቋም እንዲሁም ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያሳየውን ፍቅርና አሳቢነት የሚገልጹ ጭብጦች ጎላ ብለው ተጠቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ምዕራፍ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል:- እውነተኛውን አምልኮ ከሐሰት አምልኮ የሚለየው ነገር ምንድን ነው? ይሖዋ በሕዝቡ ላይ ግፍ እየፈጸሙ ቅዱስ መስለው ለመታየት የሚሞክሩትን ግብዞች እንደሚቀጣ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? በታማኝነት የሚጸኑ አገልጋዮቹን የሚባርካቸውስ እንዴት ነው?
ለንጹሕ አምልኮ ወሳኝ የሆነው ነገር
2. ይሖዋ ታላቅነቱን በተመለከተ ምን በማለት ተናገረ? ኢሳይያስ ይህን ቃል ያስተላለፈው ምን ለማለት ብሎ አልነበረም?
2 ትንቢቱ በመጀመሪያ የይሖዋን ታላቅነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል:- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ሰማይ ዙፋኔ ነው፣ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው?” (ኢሳይያስ 66:1) አንዳንዶች ነቢዩ ይህን የተናገረው አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ ቤተ መቅደሱን ዳግመኛ ለመገንባት እንዳይነሳሱ ለማሳነፍ ብሎ ነው ይላሉ። ይሁንና ይሖዋ ራሱ ቤተ መቅደሱን መልሰው እንዲገነቡ የሚያዝዛቸው በመሆኑ ኢሳይያስ ይህን ቃል የተናገረው አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን እንዳይገነቡ ለማድረግ ብሎ አይደለም። (ዕዝራ 1:1-6፤ ኢሳይያስ 60:13፤ ሐጌ 1:7, 8) ታዲያ ምን ለማለት ፈልጎ ነው?
3. ምድር የይሖዋ ‘የእግሩ መረገጫ’ ተደርጋ መገለጿ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
3 በመጀመሪያ ደረጃ ምድር የይሖዋ ‘የእግሩ መረገጫ’ ተደርጋ የተገለጸችው ለምን እንደሆነ እንመርምር። ይህ ምድርን ለማንኳሰስ ተብሎ የተነገረ ቃል አይደለም። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሚገኙት በቢልዮን የሚቆጠሩ የሰማይ አካላት መካከል እንዲህ ያለው ልዩ ስያሜ የተሰጣት ምድር ብቻ ነች። የይሖዋ አንድያ ልጅ ቤዛውን የከፈለውና ይሖዋም በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጠው በምድር ላይ መሆኑ ፕላኔታችንን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ካሉት ሰማያዊ አካላት ሁሉ ለዘላለም ልዩ ሆና እንድትኖር ያደርጋታል። ምድር የይሖዋ የእግሩ መረገጫ ተብላ መጠራቷ ምንኛ ተገቢ ነው! አንድ ንጉሥ እንዲህ ያለውን የእግር መረገጫ ከፍ ወዳለው ዙፋኑ ለመውጣትና በኋላም እግሩን ለማሳረፍ ሊጠቀምበት ይችላል።
4. (ሀ) በምድር ላይ የሚሠራ ማንኛውም ዓይነት ሕንፃ ለይሖዋ አምላክ የማረፊያ ሥፍራ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) ‘እነዚህ ሁሉ’ የሚለው ሐረግ ምን ያመለክታል? ለይሖዋ የሚቀርበውን አምልኮ በተመለከተ ምን ወደሚል መደምደሚያ እንደርሳለን?
4 እርግጥ አንድ ንጉሥ እግሩን በሚያሳርፍበት በርጩማ ላይ እንደማይኖር ሁሉ ይሖዋም በምድር ላይ አይኖርም። በጣም ግዙፍ የሆኑት ግዑዞቹ ሰማያት እንኳ ሊይዙት አይችሉም! ከዚህ አንጻር ሲታይ በምድር ላይ የሚሠራ የትኛውም ሕንፃ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ቃል በቃል ለይሖዋ መኖሪያ ሆኖ ሊያገለግል እንደማይችል የታወቀ ነው። (1 ነገሥት 8:27) የይሖዋ ዙፋንና የሚያርፍበት ሥፍራ የሚገኘው በመንፈሳዊው ዓለም ነው። በኢሳይያስ 66:1 ላይ የተጠቀሰው “ሰማይ” የሚለው ቃልም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው። የሚቀጥለው ቁጥር ለማስተላለፍ የተፈለገውን ሐሳብ ግልጽ ያደርግልናል:- “እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው፣ ይላል እግዚአብሔር።” (ኢሳይያስ 66:2ሀ) ይሖዋ ‘እነዚህ ሁሉ’ ብሎ በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች በሙሉ በእጁ ሲያመለክት በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። (ኢሳይያስ 40:26፤ ራእይ 10:6) መላውን አጽናፈ ዓለም የሠራ ታላቅ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን አንድን ሕንፃ ለእሱ አገልግሎት ከማዋል የበለጠ ሊደረግለት የሚገባ ነገር አለ። እንዲሁ ለታይታ ብቻ የሚደረግ የአምልኮ ሥርዓት በቂ አይደለም።
5. ‘ትሑቶች እንደሆንና መንፈሳችን እንደተሰበረ’ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5 የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ምን ዓይነት አምልኮ ሊቀርብለት ይገባል? እሱ ራሱ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፣ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፣ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።” (ኢሳይያስ 66:2ለ) አዎን፣ አንድ ሰው ንጹሕ አምልኮ ማቅረብ እንዲችል ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ሊኖረው ይገባል። (ራእይ 4:11) ይሖዋን የሚያመልክ ሰው ‘ትሑትና መንፈሱ የተሰበረ’ መሆን አለበት። ይህ ማለት ይሖዋ ደስታ እንድናጣ ይፈልጋል ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም፤ ይሖዋ ደስተኛ አምላክ በመሆኑ አምላኪዎቹም ደስተኞች እንዲሆኑ ይፈልጋል። (መዝሙር 104:31፤ ፊልጵስዩስ 4:4) ይሁን እንጂ ሁላችንም ብዙ ጊዜ ኃጢአት የምንሠራ በመሆኑ የምንሠራቸውን ኃጢአቶች አቅልለን እንዳንመለከት መጠንቀቅ ይገባናል። ‘ትሑቶች’ መሆንና የይሖዋን የጽድቅ መስፈርቶች ሳናሟላ በምንቀርበት ጊዜ ማዘን ይገባናል። (መዝሙር 51:17) ንስሐ በመግባት፣ የኃጢአት ዝንባሌዎቻችንን በመዋጋትና ይሖዋ ይቅር እንዲለን በጸሎት በመለመን ‘መንፈሳችን እንደተሰበረ’ ማሳየት አለብን።—ሉቃስ 11:4፤ 1 ዮሐንስ 1:8-10
6. እውነተኛ አምላኪዎች ‘በአምላክ ቃል መንቀጥቀጥ’ ያለባቸው ከምን አንጻር ነው?
6 በተጨማሪም ይሖዋ ‘በቃሉ ወደሚንቀጠቀጡ’ ሰዎች ይመለከታል። ይህ ሲባል ማሳሰቢያዎቹን ባነበብን ቁጥር በፍርሃት መሸበር አለብን ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ለሚናገረው ነገር ጥልቅ አክብሮት እንዲኖረን ይፈልጋል። ምክሩን ከልብ በመሻት በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች መመሪያ አድርገን እንጠቀምበታለን። (መዝሙር 119:105) በተጨማሪም በአምላክ ላይ ለማመፅ፣ የአምላክን እውነት በሰው ወጎች ለመበረዝ ወይም ይህን እውነት አቅልሎ ለመመልከት ማሰቡ ራሱ እንኳን በሚፈጥርብን ፍርሃት ‘ልንንቀጠቀጥ’ እንችላለን። እንዲህ ያለው የትሕትና ዝንባሌ ለንጹሕ አምልኮ ወሳኝ ሆኖ ሳለ በዛሬው ጊዜ ባለው ዓለም ውስጥ እምብዛም የማይታይ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል።
ይሖዋ በግብዝነት የሚቀርብን አምልኮ ይጠላል
7, 8. ይሖዋ ሃይማኖታዊ ግብዝነት ያለባቸው ሰዎች ለወጉ ያህል የሚያቀርቡትን አምልኮ እንዴት ይመለከተዋል?
7 ኢሳይያስ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ይሖዋ ከአምላኪዎቹ የሚፈልገው ዓይነት ዝንባሌ እንደሌላቸው ተገንዝቧል። በመሆኑም በከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ላይ ያንዣበበው የጥፋት ፍርድ አግባብነት ያለው ነው። ይሖዋ በኢየሩሳሌም ውስጥ የሚካሄደውን የአምልኮ ሥርዓት በተመለከተ ምን እንደተሰማው ተመልከት:- “በሬን የሚያርድልኝ ሰውን እንደሚገድል ነው፤ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደሚሰብር ነው፤ የእህልን ቁርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው፤ ዕጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኩሰታቸው ደስ ይላታል።”—ኢሳይያስ 66:3
8 እነዚህ ቃላት በኢሳይያስ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ሰፍረው የሚገኙትን የይሖዋ ቃላት ያስታውሱናል። እዚያ ላይ ይሖዋ አልታዘዝ ያሉትን ሕዝቦቹን ለወጉ ያህል የሚፈጽሙት የአምልኮ ሥርዓት እንዳላስደሰተው ብቻ ሳይሆን ግብዝነታቸው የጽድቅ ቁጣው እንዲገነፍል እንዳደረገው ጭምር ገልጾላቸዋል። (ኢሳይያስ 1:11-17) አሁንም በተመሳሳይ ይሖዋ መሥዋዕታቸውን ዘግናኝ ከሆኑ የወንጀል ድርጊቶች ጋር አመሳስሎታል። ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣውን የበሬ መሥዋዕታቸውን ሰውን የመግደል ያህል ተጸይፎታል። ሌሎቹን መሥዋዕቶች ደግሞ የውሻ ወይም የእሪያ መሥዋዕት ከማቅረብ ጋር ያመሳሰላቸው ሲሆን እነዚህ እንስሳት በሙሴ ሕግ መሠረት ርኩስ በመሆናቸው መሥዋዕት ሆነው ሊቀርቡ የሚችሉ አልነበሩም። (ዘሌዋውያን 11:7, 27) ይሖዋ እንዲህ ያለውን ሃይማኖታዊ ግብዝነት በቸልታ ያልፈዋልን?
9. አብዛኞቹ አይሁዶች ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል ለሰጣቸው ማሳሰቢያዎች ምን ምላሽ ሰጥተዋል? መጨረሻቸውስ ምን ይሆናል?
9 ይሖዋ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን [“እነሱን የምቀጣበትን መንገድ፣” NW] እመርጣለሁ፣ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ፤ በፊቴ ክፉ ነገርን አደረጉ፣ ያልወደድሁትንም መረጡ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሱልኝምና፣ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝምና።” (ኢሳይያስ 66:4) ኢሳይያስ እነዚህን ቃላት ፍጹም እርግጠኛ ሆኖ ተናግሯቸው ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ለብዙ ዓመታት ሕዝቡን ‘በመጥራት’ እና ለሕዝቡ ‘በመናገር’ የይሖዋ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ነቢዩ በጥቅሉ ሲታይ ሕዝቡ ጆሮውን ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ በሚገባ ያውቃል። ክፉ ድርጊታቸውን ለመተው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ቅጣት መቀበላቸው የማይቀር ነው። በእርግጥም ይሖዋ እነርሱን የሚቀጣበትን መንገድ የሚመርጥ ከመሆኑም ሌላ ከሃዲ በሆኑ ሕዝቦቹ ላይ አስፈሪ ነገሮችን ያመጣል።
10. ይሖዋ ይሁዳን በተመለከተ የወሰደው እርምጃ ለሕዝበ ክርስትና ያለውን አመለካከት የሚጠቁመን እንዴት ነው?
10 ዘመናዊቷ ሕዝበ ክርስትናም ይሖዋ የማይደሰትባቸውን ድርጊቶች ፈጽማለች። በቤተ ክርስቲያኖቿ ውስጥ የጣዖት አምልኮ በእጅጉ የተስፋፋ ከመሆኑም በላይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ፍልስፍናዎችንና ወጎችን ታስተምራለች። እንዲሁም ፖለቲካዊ ሥልጣን ለማግኘት ያላት ከፍተኛ ፍላጎት ከዓለም ብሔራት ጋር በመወዳጀት ከምንጊዜውም በከፋ መንፈሳዊ ምንዝር ውስጥ እንድትዘፈቅ አድርጓታል። (ማርቆስ 7:13፤ ራእይ 18:4, 5, 9) በጥንቷ ኢየሩሳሌም ላይ እንደደረሰው ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም ከሚደርስባት ፍትሐዊ የሆነ የቅጣት እርምጃ ማለትም ‘አስፈሪ ነገር’ አታመልጥም። ከቅጣት እንዳታመልጥ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ በአምላክ ሕዝቦች ላይ የፈጸመችው በደል ነው።
11. (ሀ) በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት ከሃዲዎች የሠሩትን ኃጢአት ይበልጥ ያከበደው ነገር ምንድን ነው? (ለ) በዘመኑ የነበሩት አይሁዳውያን ታማኝ ሰዎችን ‘በአምላክ ስም የተነሳ’ ያባርሯቸው ነበር የምንለው ከምን አንጻር ነው?
11 ኢሳይያስ በመቀጠል እንዲህ ሲል ገለጸ:- “በቃሉ የምትንቀጠቀጡ ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ:- የጠሉአችሁ ስለ ስሜም ያባረሩአችሁ ወንድሞቻችሁ:- ደስታችሁን እናይ ዘንድ እግዚአብሔር ይክበር ብለዋል፤ ነገር ግን ያፍራሉ።” (ኢሳይያስ 66:5) የኢሳይያስ ‘ወንድሞች’ ማለትም የአገሩ ሰዎች ይሖዋ አምላክን የመወከልና ለሉዓላዊነቱ የመገዛት ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። ይህን ኃላፊነት አለመወጣታቸው በእርግጥም ከባድ ኃጢአት ነበር። ይሁንና ኃጢአታቸውን ይበልጥ ያከበደው እንደ ኢሳይያስ ላሉ ታማኝና ትሑት ሰዎች ያደረባቸው ጥላቻ ነው። እነዚህ ታማኝ ሰዎች ይሖዋ አምላክን በትክክል ይወክሉ ስለነበር ከሃዲዎቹ አይሁዳውያን ይጠሏቸውና ያባርሯቸው ነበር። ከዚህ አንጻር ሲታይ ያባርሯቸው የነበረው ‘በአምላክ ስም የተነሳ’ ነው ሊባል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚሁ የሐሰት አገልጋዮች በግብዝነት “እግዚአብሔር ይክበር” እንደሚሉት ያሉ ሃይማኖተኛ እንደሆኑ የሚያስመስሉ ሐረጎችን በመጠቀም ይሖዋን እንደሚወክሉ አድርገው ይናገራሉ!a
12. ሃይማኖታዊ ግብዝነት ያለባቸው ሰዎች በይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ላይ የሚያደርሱትን ስደት የሚያሳዩት አንዳንዶቹ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
12 የሐሰት ሃይማኖት ለንጹሕ አምልኮ ተከታዮች ያለው ጥላቻ እንግዳ ነገር አይደለም። ይህ ሁኔታ በሰይጣን ዘርና በአምላክ ሴት ዘር መካከል ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ጠላትነት እንደሚኖር የሚናገረው የዘፍጥረት 3:15 ትንቢት አንዱ ፍጻሜ ነው። ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ቅቡዓን ተከታዮቹ በገዛ አገራቸው ሰዎች እጅ መከራ እንደሚደርስባቸው ይኸውም ከምኩራብ እንደሚያስወጧቸውና እስከ ሞት የሚያደርስ ስደት እንደሚያመጡባቸው ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 16:2) በዘመናችን ስላለው ሁኔታስ ምን ለማለት ይቻላል? “በመጨረሻው ቀን” መጀመሪያ ላይ የአምላክ ሕዝቦች ተመሳሳይ የሆነ ስደት እንደሚጠብቃቸው ተገንዝበው ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በ1914 መጠበቂያ ግንብ ኢሳይያስ 66:5ን በመጥቀስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚደርሰው ስደት በሙሉ ማለት ይቻላል፣ ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች የሚፈጸም ነው።” ይኸው ጽሑፍ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “በዘመናችን የሚመጣው ስደት ከኅብረተሰቡ እንድንገለል እስከ ማድረግ፣ የድርጅታችንን ሥራ እስከ ማስተጓጎልና ምናልባትም ቃል በቃል እስከ መግደል ደረጃ ይደርስ እንደሆነና እንዳልሆነ የምናውቀው ነገር የለም።” በእርግጥም እነዚህ ቃላት እውነት ሆነው ተገኝተዋል! ይህ ጽሑፍ ከታተመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በቀሳውስት ቆስቋሽነት የተነሳው ስደት በከፍተኛ ደረጃ ተፋፋመ። ይሁንና አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ሕዝበ ክርስትና የኀፍረት ማቅ የምትከናነብበት ጊዜ ደርሶ ነበር። እንዴት?
ፈጣንና ድንገተኛ የሆነ ተሃድሶ
13. በትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ መሠረት ‘ከከተማዋ የተሰማው የጩኸት ድምፅ’ ምን ያመለክታል?
13 ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተነበየ:- “የጩኸት ድምፅ ከከተማ፣ ድምፅም ከመቅደስ፣ በጠላቶቹ ላይ ፍዳን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ድምፅ ተሰምቶአል።” (ኢሳይያስ 66:6) በትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ መሠረት ‘ከተማዋ’ የይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚገኝባት ኢየሩሳሌም ነች። “የጩኸት ድምፅ” የሚለው ሐረግ በ607 ከዘአበ ወራሪው የባቢሎናውያን ጦር ሠራዊት በከተማይቱ ላይ ጥቃት በከፈተበት ወቅት በከተማዋ ውስጥ የተሰማውን ሁካታና ሽብር ያመለክታል። ይሁን እንጂ ስለ ዘመናዊው ፍጻሜስ ምን ለማለት ይቻላል?
14. (ሀ) ሚልክያስ፣ ይሖዋ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚመጣበትን ሁኔታ አስመልክቶ ምን ትንቢት ተናግሯል? (ለ) በሕዝቅኤል ትንቢት መሠረት ይሖዋ ወደ ቤተ መቅደሱ በመጣ ጊዜ ምን አድርጓል? (ሐ) ይሖዋና ኢየሱስ መንፈሳዊውን ቤተ መቅደስ የመረመሩት መቼ ነው? ይህ ምርመራ ንጹሑን አምልኮ እንወክላለን በሚሉ ሰዎች ላይ ምን አስከትሏል?
14 በኢሳይያስ ላይ የተጠቀሱት እነዚህ ቃላት ከሌሎች ሁለት ትንቢታዊ ቃላት ጋር ይስማማሉ። አንደኛው በሕዝቅኤል 43:4, 6-9 ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በሚልክያስ 3:1-5 ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ሕዝቅኤልም ሆነ ሚልክያስ፣ ይሖዋ አምላክ ወደ ቤተ መቅደሱ ስለሚመጣበት ጊዜ ተንብየዋል። የሚልክያስ ትንቢት ይሖዋ የንጹሕ አምልኮ ቤቱን ለመመርመርና ለማጥራት እንደሚመጣ እንዲሁም እሱን በአግባቡ የማይወክሉትን ሰዎች እንደማይቀበል ያመለክታል። ሕዝቅኤል ባየው ራእይ ላይ ደግሞ ይሖዋ ወደ ቤተ መቅደሱ በመግባት ማንኛውም የፆታ ብልግናና የጣዖት አምልኮ ርዝራዥ ከቤቱ እንዲወገድ እንዳዘዘ ተደርጎ ተገልጿል።b በእነዚህ ትንቢቶች ዘመናዊ ፍጻሜ መሠረት በ1918 ከይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዘ በመንፈሳዊው ዓለም ታላቅ ክንውን ተከናውኖ ነበር። ይሖዋና ኢየሱስ ንጹሑን አምልኮ እንወክላለን በሚሉ ሰዎች ላይ ምርመራ እንዳካሄዱ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ይህ ምርመራ ብልሹ የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንድትጣል ምክንያት ሆኗል። በዚህ ምርመራ አማካኝነት በክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች ላይ ለአጭር ጊዜ የቆየ የማጥራት ሥራ የተካሄደ ሲሆን ከዚያ ተከትሎ በ1919 ፈጣን የሆነ መንፈሳዊ ተሃድሶ ተካሂዷል።—1 ጴጥሮስ 4:17
15. ልጅ ከመውለድ ጋር በተያያዘ ምን ትንቢት ተነግሮ ነበር? ይህ ትንቢት በ537 ከዘአበ ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነው?
15 ይህ ተሃድሶ በተከታዮቹ የኢሳይያስ ምዕራፍ 66 ቁጥሮች ላይ ተስማሚ በሆነ መንገድ ቁልጭ ብሎ ተገልጿል:- “ሳታምጥ ወለደች፤ ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጅን ወለደች። ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር በአንድ ቀን ታምጣለችን [“ይፈጠራልን፣” አ.መ.ት]? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና።” (ኢሳይያስ 66:7, 8) እነዚህ ቃላት በባቢሎን በግዞት በነበሩት አይሁዳውያን ላይ አስደሳች በሆነ መንገድ የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ጽዮን ወይም ኢየሩሳሌም ልጅ እንደወለደች ሴት ተደርጋ በድጋሚ ተገልጻለች። ይሁንና ልጅ የወለደችው በጣም እንግዳ በሆነ መንገድ ነው! አወላለዷ በጣም ፈጣንና ድንገተኛ ከመሆኑ የተነሳ ምጥ እንኳ አልያዛትም! ይህ ተስማሚ የሆነ ሕያው መግለጫ ነው። የአምላክ ሕዝብ በ537 ከዘአበ ራሱን የቻለ ብሔር ሆኖ ዳግመኛ የተወለደበት ሁኔታ በጣም ፈጣንና ድንገተኛ ከመሆኑ የተነሳ ልክ እንደ ተአምር የሚቆጠር ነበር። ቂሮስ አይሁዳውያንን ከግዞት ነፃ ካወጣበት ጊዜ አንስቶ ታማኝ ቀሪዎች ወደ ትውልድ አገራቸው እስኪመለሱ ድረስ የፈጀው ጊዜ በወራት ብቻ የሚቆጠር ነው! ይህ ሁኔታ የእስራኤል ሕዝብ መጀመሪያ ላይ በተወለደበት ጊዜ ከተፈጸሙት ሁኔታዎች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት አለው! በ537 ከዘአበ እምቢተኛ የሆነን መሪ ሕዝቡን እንዲለቅቅ መለመን፣ ከጠላት ጦር ሠራዊት ሸሽቶ ማምለጥም ሆነ ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ መቆየት አላስፈለገም።
16. በኢሳይያስ 66:7, 8 ዘመናዊ ፍጻሜ መሠረት ጽዮን ማንን ትወክላለች? ዘሮቿ ዳግመኛ የተወለዱትስ እንዴት ነው?
16 በትንቢቱ ዘመናዊ ፍጻሜ መሠረት ጽዮን የይሖዋን ሰማያዊት “ሴት” ማለትም መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈችውን ሰማያዊት ድርጅት ትወክላለች። ይህች “ሴት” በ1919 በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ልጆቿ የተደራጀ አንድ “ሕዝብ” ሆነው ሲወለዱ በማየቷ እጅግ ተደስታለች። ይህ ሕዝብ ዳግመኛ የተወለደበት ሁኔታ በጣም ፈጣንና ድንገተኛ ነበር።c በድን የሆኑ ያህል ሥራቸውን አቋርጠው የነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በቡድን ደረጃ በጥቂት ወራት ውስጥ አንሰራርተው ‘በምድራቸው’ ማለትም አምላክ በሰጣቸው መንፈሳዊ የሥራ መስክ በሙሉ ኃይል መንቀሳቀስ ጀመሩ። (ራእይ 11:8-12) እንዲያውም በ1919 የመከር ወራት ከመጠበቂያ ግንብ ጎን ለጎን ሌላ አዲስ መጽሔት እንደሚታተም አስታወቁ። ወርቃማው ዘመን (አሁን ንቁ!) በመባል የሚታወቀው ይህ አዲስ ጽሑፍ የአምላክ ሕዝቦች ዳግመኛ ሕያው እንደሆኑና ለአገልግሎት እንደተደራጁ የሚያሳይ ጥሩ ማስረጃ ነበር።
17. ይሖዋ መንፈሳዊ እስራኤልን በተመለከተ ያለውን ዓላማ ከመፈጸም ምንም ነገር ሊያግደው እንደማይችል ለሕዝቡ ማረጋገጫ የሰጠው እንዴት ነው?
17 የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ሁኔታ ዳግም እንዳይወለዱ ማገድ የሚችል አንድም ኃይል በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የለም። የሚቀጥለው ቁጥር ይህን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል:- “በውኑ ወደ መውለድ የማደርስ እኔ አላስወልድምን? ይላል እግዚአብሔር፤ የማስወልድስ ማኅፀንን እኔ እዘጋለሁን? ይላል አምላክሽ።” (ኢሳይያስ 66:9) ምጥ የጀመራት ሴት እንዳትወልድ ሂደቱን መግታት እንደማይቻል ሁሉ መንፈሳዊው እስራኤልም ዳግመኛ መወለድ ከጀመረ በኋላ ሂደቱን ማስቆም የማይቻል ነገር ነው። እርግጥ በወቅቱ ተቃውሞ እንደነበረ አይካድም። ወደፊትም ተቃውሞ መኖሩ አይቀርም። ይሁን እንጂ ራሱ የጀመረውን ነገር ሊያስቆም የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። እሱ ደግሞ እንዲህ እንደማያደርግ የታወቀ ነው። ይሁንና ይሖዋ ዳግም ሕያው የሆኑትን ሕዝቦቹን የሚይዛቸው እንዴት ነው?
የይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ
18, 19. (ሀ) ይሖዋ ምን ልብ የሚነካ ምሳሌ ተጠቅሟል? ምሳሌው በግዞት በነበሩት ሕዝቦቹ ላይ የሚሠራውስ እንዴት ነው? (ለ) በዘመናችን ያሉት ቅቡዓን ቀሪዎች ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ከሚቀርብላቸው ምግብና ከሚደረግላቸው እንክብካቤ የተጠቀሙት እንዴት ነው?
18 የሚቀጥሉት አራት ቁጥሮች ይሖዋ የሚያደርገውን ፍቅራዊ እንክብካቤ ልብ በሚነካ መንገድ ቁልጭ አድርገው ይገልጻሉ። በመጀመሪያ ኢሳይያስ እንዲህ አለ:- “እናንተ የምትወድዱአት ሁሉ፣ ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሤትን አድርጉ፣ ስለ እርስዋም ደስ ይበላችሁ፤ እናንተም የምታለቅሱላት ሁሉ፣ ከእርስዋ ጋር በደስታ ሐሤትን አድርጉ፣ ትጠቡ ዘንድ ከማጽናናትዋም ጡት ትጠግቡ ዘንድ፤ እጅግ ጠጥታችሁ በክብርዋ ሙላት ደስ ይላችሁ ዘንድ።” (ኢሳይያስ 66:10, 11) እዚህ ላይ ይሖዋ ልጅዋን የምታጠባ እናትን ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል። አንድ ሕፃን ሲርበው ያለማቋረጥ ያለቅሳል። ይሁን እንጂ እናቱ ወደ ጡቷ አስጠግታ ልታጠባው ስትል ማልቀሱን ትቶ በደስታ ፍንድቅድቅ ይላል። በተመሳሳይም በባቢሎን የሚኖሩት ታማኝ አይሁዳውያን ቀሪዎች ነፃ የሚወጡበትና ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ የሚመለሱበት ጊዜ ሲደርስ ሐዘናቸው ወዲያውኑ በደስታና በፍስሃ ተተክቶ እጅግ ሐሴት ያደርጋሉ። ኢየሩሳሌም ዳግመኛ ተገንብታ ነዋሪዎች ሲሰፍሩባት እንደገና በክብር ትሞላለች። ከተማዋ የምትላበሰው ክብር ደግሞ በአጸፋው ታማኝ ነዋሪዎቿን ያስደስታቸዋል። ብቃት ባለው የክህነት አገልግሎት አማካኝነት እንደ ቀድሞው ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ይመገባሉ።—ሕዝቅኤል 44:15, 23
19 መንፈሳዊው እስራኤልም በ1919 ከተካሄደው ተሃድሶ በኋላ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አግኝቷል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል የሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ አልተቋረጠም። (ማቴዎስ 24:45-47) ይህ ወቅት በእርግጥም ለቅቡዓን ቀሪዎች የመጽናኛና የደስታ ዘመን ሆኖላቸዋል። ይሁን እንጂ በረከቱ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም።
20. ኢየሩሳሌም በጥንት ዘመንም ሆነ በዘመናችን ‘በሚጎርፍ ፈሳሽ’ የተባረከችው እንዴት ነው?
20 ትንቢቱ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና:- እነሆ፣ ሰላምን እንደ ወንዝ፣ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ከዚያም ትጠባላችሁ፣ በጫንቃ ላይ ይሸከሙአችኋል በጉልበትም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሉአችኋል።” (ኢሳይያስ 66:12) እዚህ ላይ ጡት ማጥባት “እንደ ወንዝ” እና “እንደሚጐርፍ ፈሳሽ” ከተትረፈረፈ በረከት ጋር አንድ ላይ ተያይዞ ተገልጿል። ኢየሩሳሌም የምትባረከው ከይሖዋ በምታገኘው ሰላም ብቻ ሳይሆን በአምላክ ሕዝቦች ላይ በሚፈስሰው ‘የአሕዛብ ክብር’ ጭምር ነው። ይህም ከአሕዛብ የተውጣጡ ሰዎች ወደ ይሖዋ ሕዝብ እንደሚጎርፉ ያመለክታል። (ሐጌ 2:7) በጥንቱ ፍጻሜ መሠረት ከተለያዩ ብሔራት የተውጣጡ በርካታ ሰዎች ወደ ይሁዲነት በመለወጥ ከእስራኤል ጋር ተወዳጅተዋል። ይሁን እንጂ በዘመናችን እንደ ጎርፍ ፈሳሽ ያሉ “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ከመንፈሳዊ አይሁዳውያን ቀሪዎች ጋር በተወዳጁ ጊዜ ትንቢቱ በላቀ መንገድ ፍጻሜውን አግኝቷል።—ራእይ 7:9፤ ዘካርያስ 8:23
21. ይሖዋ ትኩረትን የሚስብ ሕያው መግለጫ በመጠቀም ምን ዓይነት ማጽናኛ እንደሚሰጥ ተንብዮአል?
21 ከዚህም በተጨማሪ በኢሳይያስ 66:12 ላይ ልጅን በጉልበት ላይ አስቀምጦ እንደማቀማጠልና በጫንቃ እንደመሸከም ያሉ የእናትነትን ፍቅር የሚያሳዩ መግለጫዎች ተጠቅሰዋል። በሚቀጥለው ቁጥር ላይ ይኸው ሐሳብ ለየት ባለ መንገድ ተገልጿል። “እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፣ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ትጽናናላችሁ።” (ኢሳይያስ 66:13) በኩረ ጽሑፉ እንደሚገልጸው ልጁ በዚህ ጊዜ አድጎ ትልቅ ሰው ሆኗል። ያም ሆኖ እናትየው በመከራ ጊዜ ልጅዋን ለማጽናናት ያላት ፍላጎት አልቀነሰም።
22. ይሖዋ ፍቅሩ ምን ያህል ጠንካራና ጥልቀት ያለው እንደሆነ ያመለከተው እንዴት ነው?
22 ይሖዋ ይህን ልብ የሚነካ ምሳሌ በመጠቀም ለሕዝቡ ምን ያህል ጠንካራና ጥልቅ የሆነ ፍቅር እንዳለው ገልጿል። ለሕዝቦቹ ያለው ፍቅር በጣም ጠንካራ ከሚባለው የእናት ፍቅር እንኳ እጅግ የላቀ ነው። (ኢሳይያስ 49:15) ሁሉም ክርስቲያኖች ይህን የሰማያዊ አባታቸውን ባሕርይ ማንጸባረቃቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ባሕርይ በማንጸባረቅ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ ትቷል። (1 ተሰሎንቄ 2:7) ኢየሱስ ተከታዮቹ በዋነኝነት ተለይተው የሚታወቁት በመካከላቸው በሚኖረው የወንድማማችነት ፍቅር እንደሆነ ገልጿል።—ዮሐንስ 13:34, 35
23. ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱት የይሖዋ ሕዝቦች የሚገጥማቸውን አስደሳች ሁኔታ ግለጽ።
23 ይሖዋ ፍቅሩን በተግባር የሚገልጥ በመሆኑ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “ታያላችሁ፣ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፣ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፤ የእግዚአብሔርም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፣ በጠላቶቹም ላይ ይቈጣል።” (ኢሳይያስ 66:14) አንድ የዕብራይስጥ ቋንቋ ሰዋስው ምሁር እንዳሉት “ታያላችሁ” የሚለው መግለጫ ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱት ግዞተኞች ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ በተመለሰችው አገራቸው “የሚያዩት ነገር ሁሉ እንደሚያስደስታቸው” ያመለክታል። በእርግጥም ወደሚወዷት ትውልድ አገራቸው በመመለሳቸው እጅግ በመደሰት ሐሴት ያደርጋሉ። በጸደይ ወቅት እንደሚለመልም ሣር አጥንታቸው ዳግመኛ ጠንክሮ ሰውነታቸው ሙሉ በሙሉ እንደታደሰ ሆኖ ይሰማቸዋል። ይህ በረከት የተገኘው በሰው ጥረት ሳይሆን ‘በእግዚአብሔር እጅ’ እንደሆነ ሁሉም ይገነዘባሉ።
24. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር በተያያዘ የተከናወኑትን ክንውኖች ስትመረምር ወደ ምን መደምደሚያ ትደርሳለህ? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?
24 በዛሬው ጊዜ የይሖዋ እጅ በሕዝቦቹ መካከል እየሠራ እንዳለ ትገነዘባለህን? ንጹሑን አምልኮ ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ሊመልስ የሚችል ሰብዓዊ ፍጡር እንደማይኖር የታወቀ ነው። የትኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ተወዳጅ ሰዎች ወደ መንፈሳዊው ምድር በመጉረፍ ከታማኞቹ ቀሪዎች ጋር እንዲቀላቀሉ ሊያደርግ አይችልም። እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማድረግ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ይሖዋ ፍቅሩን በዚህ መንገድ መግለጹ በጣም እንድንደሰት ያደርገናል። እንግዲያው ይሖዋ ያሳየንን ፍቅር አቅልለን እንዳንመለከት ልንጠነቀቅ ይገባናል። ምንጊዜም ‘በቃሉ የምንንቀጠቀጥ’ እንሁን። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመመራትና ይሖዋን በማገልገል ለመደሰት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዛሬው ጊዜ በርካታ የሕዝበ ክርስትና አባላት የይሖዋን የግል ስም ለመጠቀም አሻፈረን ከማለታቸውም በላይ ከብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ አውጥተውታል። የአምላክ ሕዝቦች በግል ስሙ በመጠቀማቸው አንዳንድ ሰዎች ያላግጡባቸዋል። ሆኖም ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል ብዙዎቹ “ያህን አመስግኑ” የሚል ትርጉም ያለውን “ሃሌ ሉያ” የሚለውን ቃል በመጠቀም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው መስለው ለመታየት ይሞክራሉ።
b በሕዝቅኤል 43:7, 9 ላይ የተጠቀሰው ‘የነገሥታቶቻቸው ሬሳ’ የሚለው መግለጫ ጣዖታትን የሚያመለክት ነው። ዓመፀኞቹ የኢየሩሳሌም መሪዎችና ነዋሪዎች የአምላክን ቤተ መቅደስ በጣዖታት በማርከስ ጣዖታቱን በላያቸው ላይ አንግሠዋል።
c የዚህን ሕዝብ መወለድ አስመልክቶ የተነገረው ትንቢት በራእይ 12:1, 2, 5 ላይ ከተገለጸው ትንቢት የተለየ ነው። በራእይ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው “ወንድ ልጅ” በ1914 መግዛት የጀመረውን መሲሐዊ መንግሥት የሚያመለክት ነው። ይሁን እንጂ በሁለቱም ትንቢቶች ላይ የተጠቀሰችው “ሴት” አንድ ናት።
[በገጽ 395 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለች”
[በገጽ 402 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ለጽዮን ‘የአሕዛብን ክብር’ ይሰጣታል