‘አሁን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ’
“እናንተ በአንድ ወቅት አንድ ሕዝብ አልነበራችሁም፣ አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ።”—1 ጴጥ. 2:10
1, 2. በ33 ዓ.ም. ምን ለውጥ ተከሰተ? የይሖዋ አዲስ ሕዝብ አባላት የሆኑትስ እነማን ናቸው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ በምድር ባሉ የይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ጉልህ የሆነ ክንውን ተፈጸመ። በዚህ ቀን ሥር ነቀል ለውጥ ተደረገ። ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት አንድ አዲስ ብሔር ማለትም መንፈሳዊ እስራኤልን ወይም ‘የአምላክ እስራኤልን’ አቋቋመ። (ገላ. 6:16) ከአብርሃም ዘመን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ለውጥ ተደረገ፤ ይኸውም የአምላክ ሕዝቦች መለያ የወንዶች ግርዘት መሆኑ ቀረ። በዚያ ፋንታ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው እያንዳንዱ የዚህ አዲስ ብሔር አባል “በመንፈስ የሆነ የልብ ግርዘት” ያስፈልገዋል።—ሮም 2:29
2 የአምላክ አዲስ ብሔር የመጀመሪያ አባላት ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም በደርብ ላይ ባለ ክፍል ውስጥ ተሰብስበው የነበሩት ከመቶ የሚበልጡ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ናቸው። (ሥራ 1:12-15) መንፈስ ቅዱስ በእነዚህ ደቀ መዛሙርት ላይ የፈሰሰ ሲሆን ይህም የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። (ሮም 8:15, 16፤ 2 ቆሮ. 1:21) መንፈስ ቅዱስ መውረዱ ክርስቶስ መካከለኛ የሆነለትና በደሙ የጸናው አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራ ላይ መዋል መጀመሩን ያረጋግጣል። (ሉቃስ 22:20፤ ዕብራውያን 9:15ን አንብብ።) በመሆኑም እነዚህ ደቀ መዛሙርት የይሖዋ አዲስ ብሔር ወይም የእሱ አዲስ ሕዝብ አባል ሆኑ። ደቀ መዛሙርቱ፣ የአይሁዳውያንን የሳምንታት በዓል ወይም ጴንጤቆስጤን ለማክበር ከመላው የሮም ግዛት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች በሚናገሯቸው የተለያዩ ቋንቋዎች መስበክ እንዲችሉ መንፈስ ቅዱስ ረድቷቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” ሲሰብኩ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መስማትና መረዳት ችለዋል።—ሥራ 2:1-11
አዲሱ የአምላክ ሕዝብ
3-5. (ሀ) ጴጥሮስ በጴንጤቆስጤ ዕለት ለአይሁዳውያን ምን ነገራቸው? (ለ) የይሖዋ አዲስ ብሔር በተቋቋመባቸው የመጀመሪያ ዓመታት እድገት እንዲያደርግ የረዱት ደረጃ በደረጃ የተከናወኑ ነገሮች ምንድን ናቸው?
3 ይሖዋ፣ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች የዚህ አዲስ ብሔር ይኸውም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንዲሆኑ መንገድ ለመክፈት በሐዋርያው ጴጥሮስ ተጠቅሟል። በጴንጤቆስጤ ዕለት ጴጥሮስ፣ አይሁዳውያን ‘በእንጨት ላይ ሰቅለው የገደሉትን’ ኢየሱስን “አምላክ ጌታም ክርስቶስም [ስላደረገው]” እሱን መቀበል እንዳለባቸው በድፍረት ተናግሯል። ከዚያም ሕዝቡ ምን ቢያደርጉ እንደሚሻል ላቀረቡት ጥያቄ ጴጥሮስ እንዲህ የሚል መልስ ሰጠ፦ “ንስሐ ግቡ፤ እያንዳንዳችሁም ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ነፃ ስጦታ ትቀበላላችሁ።” (ሥራ 2:22, 23, 36-38) በዚያን ዕለት 3,000 የሚያህሉ ሰዎች አዲስ በተቋቋመው የመንፈሳዊ እስራኤል ብሔር ላይ ተጨመሩ። (ሥራ 2:41) በኋላም ሐዋርያት ምሥራቹን በቅንዓት በመስበካቸው ብዙ ፍሬ ተገኘ። (ሥራ 6:7) በእርግጥም አዲሱ ብሔር እያደገ ነበር።
4 በመቀጠል ምሥራቹ ለሳምራውያን የተሰበከ ሲሆን እነሱም ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። ወንጌላዊው ፊልጶስ ብዙ ሳምራውያንን አጠመቀ፤ ያም ቢሆን እነዚህ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት ወዲያውኑ አይደለም። በኢየሩሳሌም የነበረው የበላይ አካል፣ ሐዋርያው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ክርስትናን ወደተቀበሉት ወደ እነዚህ ሳምራውያን ላካቸው፤ ሐዋርያቱ “እጃቸውን ጫኑባቸው፤ እነሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።” (ሥራ 8:5, 6, 14-17) እነዚህ ሳምራውያንም በመንፈስ የተቀቡ የመንፈሳዊው እስራኤል አባላት ሆኑ።
5 በ36 ዓ.ም. ሌሎችም አዲስ የተቋቋመው የመንፈሳዊ እስራኤል ብሔር አባላት እንዲሆኑ አጋጣሚ ለመክፈት ይሖዋ እንደገና በጴጥሮስ ተጠቅሟል። ይህ የሆነው ጴጥሮስ፣ ቆርኔሌዎስ ለተባለ መቶ አለቃ እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቹ በሰበከ ጊዜ ነው። (ሥራ 10:22, 24, 34, 35) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ጴጥሮስ . . . ገና እየተናገረ ሳለ ቃሉን እየሰሙ በነበሩት [አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች] ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስ ጋር የመጡት ከተገረዙት ወገን የሆኑ ታማኝ አገልጋዮች የመንፈስ ቅዱስ ነፃ ስጦታ ከአሕዛብ ወገን በሆኑ ሰዎችም ላይ በመፍሰሱ ተገረሙ።” (ሥራ 10:44, 45) በመሆኑም አማኝ የሆኑ ያልተገረዙ አሕዛብም አዲስ የተቋቋመው የመንፈሳዊ እስራኤል ብሔር አባላት የመሆን መብት ተከፈተላቸው።
“ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች”
6, 7. የአዲሱ ብሔር አባላት “[ለይሖዋ ስም] የሚሆኑ ሰዎች” መሆናቸውን ያሳዩት በየትኞቹ መንገዶች ነበር? ምን ያህልስ ተሳክቶላቸዋል?
6 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የበላይ አካል በ49 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ላይ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ትኩረቱን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ወደ እነሱ እንዳዞረ ስምዖን [ጴጥሮስ] በሚገባ ተርኳል።” (ሥራ 15:14) የይሖዋን ስም የሚሸከመው ይህ አዲስ ሕዝብ አይሁዳውያንና አይሁዳውያን ያልሆኑ አማኞችን ይጨምራል። (ሮም 11:25, 26ሀ) ከጊዜ በኋላ ጴጥሮስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች “እናንተ በአንድ ወቅት አንድ ሕዝብ አልነበራችሁም፣ አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ” በማለት ጽፎላቸዋል። ጴጥሮስ እነዚህ ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን ተልእኮ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ . . . ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእሱን ‘ድንቅ ባሕርያት በስፋት እንድታስታውቁ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ’ ናችሁ።” (1 ጴጥ. 2:9, 10) እነዚህ ክርስቲያኖች፣ የሚወክሉትን አምላክ ማወደስ እንዲሁም ስሙን በሕዝብ ፊት ከፍ ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢ የሆነው የይሖዋ ደፋር ምሥክሮች መሆን ነበረባቸው።
7 ይሖዋ ሥጋዊ እስራኤላውያንን አስመልክቶ እንደተናገረው ሁሉ የመንፈሳዊ እስራኤል አባላትንም ‘ምስጋናዬን የሚያውጅ ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ’ በማለት ጠርቷቸዋል። (ኢሳ. 43:21) እነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች በዚያን ጊዜ ይመለኩ የነበሩት አማልክት ሐሰተኛ መሆናቸውን በመግለጽ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ እንደሆነ በድፍረት አውጀዋል። (1 ተሰ. 1:9) ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ “በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ” ምሥክሮች ሆነዋል።—ሥራ 1:8፤ ቆላ. 1:23
8. ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ የአምላክ ሕዝቦች ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር?
8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሖዋ ስም ከሚጠራው ሕዝብ መካከል ደፋር የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ ይገኝበታል። ጳውሎስ ‘ዓለምንና በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ የፈጠረውን አምላክ እንዲሁም የሰማይና የምድር ጌታ የሆነውን’ የይሖዋን ሉዓላዊነት አረማዊ በሆኑ ፈላስፎች ፊት በድፍረት ደግፎ ተናግሯል። (ሥራ 17:18, 23-25) ጳውሎስ ሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን ሊያጠናቅቅ አካባቢ በአምላክ ስም ለሚጠራው ሕዝብ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “እኔ ከሄድኩ በኋላ ጨካኝ ተኩላዎች በመካከላችሁ እንደሚገቡና መንጋውን በርኅራኄ እንደማይዙ አውቃለሁ፤ ከእናንተ ከራሳችሁ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ።” (ሥራ 20:29, 30) አስቀድሞ የተነገረለት ይህ ክህደት በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በግልጽ ታይቷል።—1 ዮሐ. 2:18, 19
9. ከሐዋርያት ሞት በኋላ ‘ለይሖዋ ስም ከሚሆኑት ሰዎች’ ጋር በተያያዘ ምን ተከሰተ?
9 ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ይህ ክህደት ይበልጥ የተስፋፋ ሲሆን የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እንዲቋቋሙም መንገድ ከፈተ። ከሃዲ ክርስቲያኖች “[ለይሖዋ ስም] የሚሆኑ ሰዎች” ከመሆን ይልቅ መለኮታዊውን ስም ከበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው አውጥተውታል። የአረማውያንን የአምልኮ ሥርዓቶች ወደ ክርስትና አስገብተዋል፤ እንዲሁም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ትምህርቶቻቸው፣ በአምላክ ስም በሚያካሂዷቸው ጦርነቶችና በመጥፎ ሥነ ምግባራቸው አምላክን አቃልለዋል። በመሆኑም ለበርካታ ዘመናት ይሖዋ በምድር ላይ ተበታትነው የሚገኙ ታማኝ አገልጋዮች እንጂ ‘ለስሙ የሚሆን’ የተደራጀ ሕዝብ አልነበረውም።
የአምላክ ሕዝብ እንደገና መወለድ
10, 11. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ በሚገልጸው ምሳሌ ላይ ምን ትንቢት ተናግሯል? (ለ) የኢየሱስ ምሳሌ ከ1914 በኋላ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?
10 ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ በተናገረው ምሳሌ ላይ በክህደቱ የተነሳ መንፈሳዊ ጨለማ የሚሆንበት ጊዜ እንደሚመጣ ገልጿል። ኢየሱስ፣ የሰው ልጅ በእርሻው ላይ የስንዴ ዘር ቢዘራም “ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ” ዲያብሎስ እርሻው ላይ እንክርዳድ እንደዘራበት ተናግሯል። ስንዴውና እንክርዳዱ እስከዚህ “ሥርዓት መደምደሚያ” ድረስ አብረው ያድጋሉ። ኢየሱስ “ጥሩው ዘር” የሚያመለክተው ‘የመንግሥቱን ልጆች’ “እንክርዳዱ” ደግሞ ‘የክፉውን ልጆች’ እንደሆነ አብራርቷል። በፍጻሜው ዘመን የሰው ልጅ ምሳሌያዊውን ስንዴ ከእንክርዳዱ ለመለየት “አጫጆቹን” ወይም መላእክትን ይልካል። የመንግሥቱ ልጆችም ይሰበሰባሉ። (ማቴ. 13:24-30, 36-43) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ትንቢቱ ይሖዋ በምድር ላይ ሕዝብ ያለው ከመሆኑ ጋር የሚያያዘውስ እንዴት ነው?
11 ‘የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ የጀመረው በ1914 ነው። በዚያ ዓመት በፈነዳው ጦርነት ወቅት በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወይም “የመንግሥቱ ልጆች” በመንፈሳዊ ሁኔታ ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ አልወጡም ነበር። ይሖዋ በ1919 በእነሱና ‘በእንክርዳዶቹ’ ወይም በአስመሳይ ክርስቲያኖች መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት እንዲኖር በማድረግ ከምርኮ ነፃ አውጥቷቸዋል። ‘የመንግሥቱን ልጆች’ በመሰብሰብ እንደ አንድ ሕዝብ ያደራጃቸው ሲሆን ይህም የሚከተለው የኢሳይያስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል፦ “አገር በአንድ ጀምበር ይፈጠራልን? ወይስ ሕዝብ በቅጽበት ይገኛል? ጽዮንን ምጥ ገና ሲጀምራት፣ ልጆቿን ወዲያውኑ ትወልዳለች።” (ኢሳ. 66:8) የይሖዋን መንፈሳዊ ፍጥረታት ያቀፈችው ጽዮን፣ በመንፈስ የተቀቡ ልጆቿን ወልዳለች፤ እነሱም በብሔር ደረጃ ተደራጅተዋል።
12. ቅቡዓኑ በዛሬው ጊዜ “[ለይሖዋ ስም] የሚሆኑ ሰዎች” እንደሆኑ ያሳዩት እንዴት ነው?
12 ልክ እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ የተቀቡት ‘የመንግሥቱ ልጆችም’ የይሖዋ ምሥክሮች የመሆን መብት አግኝተዋል። (ኢሳይያስ 43:1, 10, 11ን አንብብ።) እነሱም በክርስቲያናዊ ምግባራቸውና “ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን” የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራቸው ተለይተው ይታወቃሉ። (ማቴ. 24:14፤ ፊልጵ. 2:15) በዚህ ሥራ አማካኝነት ብዙዎች እንዲያውም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲኖራቸው ረድተዋል።—ዳንኤል 12:3ን አንብብ።
“አብረን እንሂድ”
13, 14. መንፈሳዊ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክና ለማገልገል ምን ማድረግ አለባቸው? ይህስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀድሞ የተነገረው እንዴት ነው?
13 በጥንቷ እስራኤል መጻተኞች ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ እንደሚችሉ ሆኖም ይህን ለማድረግ እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝብ ጋር መተባበር እንደነበረባቸው ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ተመልክተናል። (1 ነገ. 8:41-43) በተመሳሳይ ዛሬም መንፈሳዊ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች ከይሖዋ ሕዝብ ማለትም “የመንግሥቱ ልጆች” ከተባሉት የይሖዋ ቅቡዓን ምሥክሮች ጋር መተባበር አለባቸው።
14 በዚህ የመጨረሻ ዘመን ከሕዝቦቹ ጋር ይሖዋን ለማምለክ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ወደ ንጹሕ አምልኮ እንደሚጎርፉ በጥንት ጊዜ የኖሩ ሁለት ነቢያት ትንቢት ተናግረዋል። ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ሕዝቦችም መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ ‘ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱ መንገዱን ያስተምረናል፤ በጐዳናውም እንሄዳለን።’ ሕግ ከጽዮን፣ የእግዚአብሔር ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።” (ኢሳ. 2:2, 3) በተመሳሳይም ነቢዩ ዘካርያስ “ብዙ ሕዝብና ኀያላን መንግሥታትም እግዚአብሔር ጸባኦትን ለመፈለግና ለመለመን ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ” የሚል ትንቢት ተናግሯል። እነዚህን ሰዎች “ከየወገኑና ከየቋንቋው [በተውጣጡ] ዐሥር ሰዎች” የመሰላቸው ሲሆን እነሱም በምሳሌያዊ ሁኔታ የመንፈሳዊ እስራኤልን ልብስ ዘርፍ በመያዝ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ” ይላሉ።—ዘካ. 8:20-23
15. “ሌሎች በጎች” ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ጋር ‘አብረው የሚሄዱት’ በየትኛው ሥራ በመካፈል ነው?
15 “ሌሎች በጎች” የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ በመሳተፍ ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ጋር ‘አብረው ይሄዳሉ።’ (ማር. 13:10) እነዚህ ሰዎች ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ይቀላቀላሉ፤ ይኸውም “ጥሩ እረኛ” በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ አመራር ሥር ሆነው ከቅቡዓኑ ጋር “አንድ መንጋ” ይሆናሉ።—ዮሐንስ 10:14-16ን አንብብ።
ከይሖዋ ሕዝብ ጋር በመሆን ጥበቃ አግኙ
16. ይሖዋ ‘የታላቁን መከራ’ የመደምደሚያ ምዕራፍ የሚያስጀምረው እንዴት ነው?
16 ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ይሰነዘራል፤ በመሆኑም በዚያ ጊዜ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ከሚያዘጋጀው ጥበቃ መጠቀም አለብን። ይህ ጥቃት ‘የታላቁ መከራ’ የመደምደሚያ ምዕራፍ እንዲጀምር ስለሚያደርግ ፍልሚያው የሚካሄድበትን መድረክና ጊዜ የሚወስነው ይሖዋ ራሱ ይሆናል። (ማቴ. 24:21፤ ሕዝ. 38:2-4) በዚያን ጊዜ ጎግ “ከአሕዛብ ተሰባስቦ እንደ ገና በሰፈረው” የይሖዋ ሕዝብ ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። (ሕዝ. 38:10-12) ይህ ጥቃት ይሖዋ በጎግና በግብረ አበሮቹ ላይ የፍርድ እርምጃ እንዲወስድ ያደርገዋል። ይሖዋ “በብዙ ሕዝቦች ፊት ራሴን አሳውቃለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” በማለት ስለተናገረ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑ እንዲታወቅና ስሙ እንዲቀደስ ያደርጋል።—ሕዝ. 38:18-23
17, 18. (ሀ) ጎግ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት ምን መመሪያ ይሰጠናል? (ለ) የይሖዋን ጥበቃ ማግኘት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
17 ጎግ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምር ይሖዋ “ሕዝቤ ሆይ፤ ሂድ ወደ ቤትህ ግባ፤ በርህን ከኋላህ ዝጋ፤ ቍጣው እስኪያልፍ ድረስ፣ ለጥቂት ቀን ተሸሸግ” በማለት ለአገልጋዮቹ መመሪያ ይሰጣቸዋል። (ኢሳ. 26:20) በዚያ ወሳኝ ጊዜ ይሖዋ ሕይወታችንን ለማዳን የሚያስችል መመሪያ ይሰጠናል፤ በኢሳይያስ ትንቢት ላይ “ቤት” የሚለው አገላለጽ ከጉባኤያችን ጋር የተያያዙ ዝግጅቶችን ሊያመለክት ይችላል።
18 እንግዲያው በታላቁ መከራ ወቅት ይሖዋ ካዘጋጀው ጥበቃ ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን ይሖዋ በምድር ላይ ሕዝብ እንዳለውና እነሱንም በጉባኤዎች እንዳደራጃቸው መገንዘብ አለብን። ከይሖዋ ሕዝብ ጋር መተባበራችንን መቀጠል ይኖርብናል፤ እንዲሁም ከጉባኤያችን መራቅ የለብንም። እኛም እንደ መዝሙራዊው “ማዳን የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ነው፤ በረከትህ በሕዝብህ ላይ ይሁን” በማለት በሙሉ ልባችን እናውጅ።—መዝ. 3:8