ምዕራፍ አሥራ ሁለት
አሦራውያንን አትፍሯቸው
1, 2. (ሀ) በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ ዮናስ ለአሦራውያን እንዲሰብክ የተሰጠውን ተልእኮ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ የማያስገርመው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) የነነዌ ሰዎች ለዮናስ መልእክት የሰጡት ምላሽ ምን ነበር?
በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አጋማሽ ላይ የአማቴ ልጅ የሆነው ዕብራዊው ነቢይ ዮናስ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ወደ አሦር ዋና ከተማ ወደ ነነዌ ተጉዞ ነበር። እንዲያደርስ የተሰጠው መልእክት ከባድ ነበር። ይሖዋ እንደሚከተለው ብሎታል:- “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፣ ክፋታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ።”—ዮናስ 1:2, 3
2 ዮናስ መጀመሪያ ይህ ተልእኮ ሲሰጠው በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ ተርሴስ ሸሽቶ ነበር። በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ ዮናስ እምቢተኛ የሆነበት ምክንያት ነበረው። አሦራውያን ጨካኝ ሕዝብ ነበሩ። አንድ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ጠላቶቹን ምን እንዳደረጋቸው ተመልከት:- “የመኮንኖቹን እጅና እግር ቆርጫለሁ . . . ከምርኮኞቹ መካከል ብዙዎቹን በእሳት አቃጥያለሁ። ብዙዎችንም ከነሕይወታቸው ይዤአለሁ። የአንዳንዶቹንም እጃቸውንና ጣታቸውን የሌሎቹን ደግሞ አፍንጫቸውን ቆርጫለሁ።” ያም ሆኖ ግን በመጨረሻ ዮናስ የይሖዋን መልእክት ሲያደርስ የነነዌ ሰዎች ከኃጢአታቸው ንስሐ በመግባታቸው ይሖዋ ሳያጠፋቸው ቀርቷል።—ዮናስ 3:3-10፤ ማቴዎስ 12:41
ይሖዋ ‘በትሩን’ አነሣ
3. እስራኤላውያን በይሖዋ ነቢያት አማካኝነት ለደረሳቸው ማስጠንቀቂያ የሰጡት ምላሽ የነነዌ ሰዎች ከሰጡት ምላሽ የሚለየው እንዴት ነው?
3 ዮናስ የሰበከላቸው እስራኤላውያንስ ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋልን? (2 ነገሥት 14:25) በፍጹም። ለንጹሕ አምልኮ ጀርባቸውን ሰጥተው ነበር። በእርግጥም ‘ለሰማይ ሠራዊት እስከ መስገድና በኣልን እስከ ማምለክ’ ደርሰው ነበር። ይህ አልበቃ ብሏቸው “ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አሳለፉአቸው፣ ምዋርተኞችና አስማተኞችም ሆኑ፣ ያስቆጡትም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ።” (2 ነገሥት 17:16, 17) ከነነዌ ሰዎች በተቃራኒ እስራኤላውያን ይሖዋ እነርሱን ለማስጠንቀቅ የላካቸውን ነቢያት አልሰሙም። በመሆኑም ይሖዋ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ ወስኗል።
4, 5. (ሀ) ‘አሦራውያን’ እንዴት ተደርገው ተገልጸዋል? ይሖዋ እንደ “በትር” የሚጠቀምባቸው እንዴት ነው? (ለ) ሰማርያ የወደቀችው መቼ ነው?
4 ዮናስ ወደ ነነዌ ከተላከ በኋላ የአሦር ጠብ አጫሪነት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ጋብ ብሎ ነበር።a ይሁን እንጂ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጀመሪያ ላይ አሦር ዳግም ወታደራዊ ኃይል ሆኖ ብቅ ያለ ሲሆን ይሖዋም አስገራሚ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። ነቢዩ ኢሳይያስ ከይሖዋ የተላከውን ማስጠንቀቂያ ለሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ሲያሰማ እንዲህ ብሏል:- “ለቁጣዬ በትር ለሆነ፣ የመዓቴም ጨንገር በእጁ ላለ ለአሦር ወዮለት! እርሱንም በዝንጉ ሕዝብ ላይ እልካለሁ፣ ምርኮውንና ብዝበዛውንም ይወስድ ዘንድ እንደ አደባባይም ጭቃ የተረገጡ ያደርጋቸው ዘንድ በምቈጣቸው ሰዎች ላይ አዝዘዋለሁ።”—ኢሳይያስ 10:5, 6
5 ይህ ለእስራኤላውያን እንዴት ያለ ውርደት ነው! አምላክ አንድን አረማዊ ብሔር ማለትም ‘አሦርን’ እንደ ‘በትር’ ተጠቅሞ ሊቀጣቸው ነው። በ742 ከዘአበ የአሦራውያኑ ንጉሥ ስልምናሶር አምስተኛ ከሃዲ የሆነውን የእስራኤል ብሔር ዋና ከተማ ሰማርያን ከብቦ ነበር። ሰማርያ የምትገኘው 90 ሜትር ከፍ ብሎ በሚገኝ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው ጉብታ ላይ በመሆኑ ጠላቷን ለሦስት ዓመታት ያህል ስትከላከል ቆይታለች። ይሁን እንጂ የአምላክ ዓላማ እንዳይፈጸም ሊያግድ የሚችል ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ስትራቴጂ ሊኖር አይችልም። በ740 ከዘአበ ሰማርያ ወድቃ በአሦራውያን እግር ተረግጣለች።—2 ነገሥት 18:10
6.አሦር ይሖዋ ካሰበለት አልፎ የሄደው በምን መንገድ ነበር?
6 ምንም እንኳ ይሖዋ ለሕዝቡ ትምህርት ለመስጠት አሦራውያንን ቢጠቀምባቸውም እነርሱ ራሳቸውም ይሖዋን አላወቁትም። ከዚህም የተነሣ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “እርሱ [አሦር] እንዲሁ አያስብም፣ በልቡም እንዲህ አይመስለውም፤ ነገር ግን ማጥፋት፣ ጥቂት ያይደሉትንም አሕዛብን መቁረጥ በልቡ አለ።” (ኢሳይያስ 10:7) ይሖዋ ያሰበው አሦራውያን በመለኮታዊ እጅ እንደ መሣሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ ነው። ይሁን እንጂ የአሦራውያኑ ሕልም ሌላ ነበር። የልባቸው ምኞት በጊዜው የነበረውን ዓለም በቁጥጥራቸው ሥር በማስገባት ከዚህ የበለጠ ነገር ማከናወን ነበር!
7. (ሀ) “መሳፍንቴ ሁሉ ነገሥታት አይደሉምን?” የሚለው አነጋገር ምን ትርጉም እንዳለው ግለጽ። (ለ) ዛሬ ይሖዋን የሚተዉ ሰዎች ልብ ሊሉት የሚገባ ነገር ምንድን ነው?
7 እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች መኖሪያ የነበሩት ብዙ ከተሞች በአሦራውያን ከመያዛቸው በፊት የሚተዳደሩት በነገሥታት ነበር። እነዚህ የቀድሞ ነገሥታት አሁን በአሦር ሥር ያለ እንደራሴ መሳፍንት በመሆናቸው “መሳፍንቴ ሁሉ ነገሥታት አይደሉምን?” በማለት በጉራ መናገር ችሎ ነበር። (ኢሳይያስ 10:8) በታላላቅ የአሕዛብ ከተሞች ውስጥ የነበሩት የሐሰት አማልክት አምላኪዎቻቸውን ከጥፋት ሊያድኗቸው አልቻሉም። የሰማርያ ነዋሪዎች ያመልኳቸው የነበሩት እንደ በኣል፣ ሞሎክና የወርቅ ጥጃ ያሉት አማልክት ከተማዋን ሊጠብቋት አይችሉም። ሰማርያ ይሖዋን ትታ ስለነበር እርሱ ይጠብቀኛል ብላ የምታስብበት ምንም ምክንያት አልነበረም። ዛሬም ይሖዋን የሚተዉ ሁሉ ሰማርያ የገጠማትን ዕጣ ሊያስታውሱ ይገባል! አሦር ሰማርያንም ሆነ ድል ያደረጋቸውን ሌሎቹን ከተሞች በሚመለከት እንደሚከተለው በማለት በጉራ መናገር ይችል ነበር:- “ካልኖ እንደ ከርከሚሽ አይደለችምን? ሐማትስ እንደ አርፋድ አይደለችምን? ሰማርያስ እንደ ደማስቆ አይደለችምን?” (ኢሳይያስ 10:9) በአሦር ዓይን ሁሉም አንድ ነበሩ። ሁሉም ለእርሱ እንደተዘጋጁ ምርኮዎች ሆነውለት ነበር።
8, 9. አሦር ዓይኑን በኢየሩሳሌም ላይ መጣሉ ከገደብ ማለፍ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
8 ይሁን እንጂ የአሦር ጉራ ከልኩ አልፏል። እንዲህ ብሏል:- “የተቀረጹ ምስሎቻቸው ከኢየሩሳሌምና ከሰማርያ ምስሎች የበለጡትን የጣዖቶችን መንግሥታት እጄ እንዳገኘች፣ በሰማርያና በጣዖቶችዋም እንዳደረግሁ፣ እንዲሁስ በኢየሩሳሌምና በጣዖቶችዋ አላደርግምን?” (ኢሳይያስ 10:10, 11) ከዚህ ቀደም ድል የተደረጉት መንግሥታት በኢየሩሳሌም አልፎ ተርፎም በሰማርያ ከነበሩት የበለጠ ቁጥር ያላቸው ጣዖታት ያሏቸው ነበሩ። ‘በሰማርያ ያደረግሁትን በኢየሩሳሌም ላይ እንዳልደግም የሚከለክለኝ ምንድን ነው?’ ብሎ አስቧል።
9 እንዴት ጉረኛ ነው! ኢየሩሳሌምን እንዲወስድ ይሖዋ አይፈቅድለትም። ይሁዳ እውነተኛውን አምልኮ በመደገፍ ረገድ ምንም የማያስነቅፍ አካሄድ ነበራት ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። (2 ነገሥት 16:7-9፤ 2 ዜና መዋዕል 28:24) ይሁዳ ታማኝ ሳትሆን በመቅረቷ ምክንያት አሦራውያን በሚያካሄዱባት ወረራ ወቅት ብዙ መከራ እንደሚደርስባት ይሖዋ አስጠንቅቋል። ይሁን እንጂ ኢየሩሳሌም አትነካም። (ኢሳይያስ 1:7, 8) በአሦራውያን ወረራ ወቅት የኢየሩሳሌም ንጉሥ የነበረው ሕዝቅያስ ነው። ሕዝቅያስ እንደ አባቱ እንደ አካዝ አልነበረም። እንዲያውም በነገሠ በመጀመሪያው ወር የቤተ መቅደሱ በሮች እንደገና እንዲከፈቱና ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንዲቋቋም አድርጓል!—2 ዜና መዋዕል 29:3-5
10. አሦራውያንን በተመለከተ ይሖዋ ምን ቃል ገብቷል?
10 በመሆኑም አሦር በኢየሩሳሌም ላይ ሊሰነዝር ያሰበው ጥቃት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ይሖዋ ይህን ኩራተኛ የዓለም ኃይል በኃላፊነት እንደሚጠይቀው ቃል ገብቷል:- “ስለዚህ እንዲህ ይሆናል፤ ጌታ ሥራውን ሁሉ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ በፈጸመ ጊዜ የአሦርን ንጉሥ የኩሩ ልብ ፍሬን የዓይኑንም ከፍታ ትምክሕት ይጐበኛል።”—ኢሳይያስ 10:12
ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም!
11. አሦራውያን ኢየሩሳሌምን በቀላሉ በቁጥጥራቸው ሥር እንደሚያውሏት ያሰቡት ለምንድን ነው?
11 በአሦር የነገሠው ሰናክሬም የሚባል አዲስ ንጉሠ ነገሥት ሰሜናዊው መንግሥት በ740 ከዘአበ ከወደቀ ከስምንት ዓመት በኋላ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። ኢሳይያስ የሰናክሬምን የትዕቢት ዕቅድ እንዲህ በማለት ዘይቤያዊ በሆነ አገላለጽ አስፍሮታል:- “እርሱ እንዲህ ብሎአልና:- አስተዋይ ነኝና በእጄ ኃይልና በጥበቤ አደረግሁት፤ የአሕዛብን ድንበሮች አራቅሁ፣ ሀብታቸውንም ዘረፍሁ፣ እንደ ጀግናም ሆኜ በምድር የተቀመጡትን አዋረድሁ፤ እጄም የአሕዛብን ኃይል እንደ ወፍ ቤት አገኘች፤ የተተወም እንቁላል እንደሚሰበሰብ እንዲሁ እኔ ምድርን ሁሉ ሰበሰብሁ፤ ክንፉን የሚያራግብ አፉንም የሚከፍት የሚጮኽም የለም።” (ኢሳይያስ 10:13, 14) ሰናክሬም ሌሎቹ ከተሞች በእጄ ወድቀዋል፤ ሰማርያም ብትሆን አሁን የለችም። ስለዚህ ኢየሩሳሌምን መያዝ ቀላል ነው ብሎ ያስባል! የከተማዋ ሰዎች በግማሽ ልብ ይዋጉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይፍጨረጨሩ በቀላሉ እጃቸውን ይሰጣሉ። በተተወ የወፍ ጎጆ ውስጥ እንደተገኘ እንቁላል ንብረታቸውን ያስረክባሉ።
12. ይሖዋ የአሦራውያንን ኩራት አስመልክቶ ሲናገር ትክክለኛው አስተሳሰብ ምን መሆኑን ገልጿል?
12 ይሁን እንጂ ሰናክሬም አንድ ነገር ረስቷል። ከሃዲዋ ሰማርያ የደረሰባት ቅጣት የሚገባት ነበር። ኢየሩሳሌም ግን በንጉሥ ሕዝቅያስ አመራር እንደገና ንጹሕ አምልኮ የሚካሄድባት አምባ ሆናለች። ኢየሩሳሌምን ለመንካት የሚቃጣ ካለ ጠቡ ከይሖዋ ጋር ይሆናል! ኢሳይያስ እንዲህ በማለት በቁጣ ይጠይቃል:- “በውኑ መጥረቢያ በሚቈርጥበት ሰው ላይ ይመካልን? ወይስ መጋዝ በሚስበው ላይ ይጓደዳልን? ይህስ፣ በትር የሚያነሣውን እንደ መነቅነቅ ዘንግም እንጨት ያይደለውን እንደ ማንሣት ያህል ነው።” (ኢሳይያስ 10:15) የአሦራውያን ግዛት በአንድ የእንጨት ሥራ ባለሙያ፣ ዛፍ ቆራጭ ወይም እረኛ እጅ እንዳለ መጥረቢያ፣ መጋዝ፣ ዘንግ ወይም በትር በይሖዋ እጅ ያለ መሣሪያ ብቻ ነው። ታዲያ በትሩ በሚጠቀምበት ሰው ላይ እንዴት ሊጓደድ ይችላል!
13. (ሀ) ‘ወፍራሞቹ’ (ለ) ‘እሾህና ኩርንችቶቹ’ (ሐ) ‘የእርሻው ክብር’ የተባሉት እነማን እንደሆኑና ምን እንደሚደርስባቸው ግለጽ።
13 የአሦራውያን መጨረሻ ምን ይሆን? “ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በወፍራሞች ላይ ክሳትን ይልካል፤ ከክብሩም በታች ቃጠሎው እንደ እሳት መቃጠል ይነድዳል። የእስራኤልም ብርሃን እንደ እሳት ቅዱሱም እንደ ነበልባል ይሆናል፤ እሾሁንና ኩርንችቱን በአንድ ቀን ያቃጥላል ይበላውማል። ከነፍስም እስከ ሥጋ ድረስ የዱሩንና የሚያፈራውን እርሻ ክብር ይበላል፤ ይህም የታመመ ሰው እንደሚሰለስል ይሆናል። የቀሩትም የዱር ዛፎች በቁጥር ጥቂት ይሆናሉ፣ ታናሽ ብላቴናም ይጽፋቸው ዘንድ ይችላል።” (ኢሳይያስ 10:16-19) አዎን፣ ይሖዋ የአሦራውያንን “በትር” ያሰልለዋል! ‘የወፈረው’ የአሦራውያን ሠራዊትና ብርቱ የሆኑት ወታደሮቹ ‘በክሳት በሽታ’ ይመታሉ። ስለዚህ ልፍስፍስ ሆነው ይታያሉ! እንደ ብዙ እሾህና ኩርንችት ያለው እግረኛው ሠራዊት በእስራኤል ብርሃን ማለትም በይሖዋ አምላክ ይቃጠላል። ‘የዱሩ ክብር’ ማለትም የጦር መኮንኖቹ መጨረሻቸው ይሆናል። ይሖዋ ከአሦራውያን ጋር ከጨረሰ በኋላ የሚቀሩት መኮንኖች አንድ ብላቴና በእጁ ጣቶች ሊቆጥራቸው የሚችል ያህል በጣም ጥቂት ብቻ ይሆናሉ!—በተጨማሪም ኢሳይያስ 10:33, 34ን ተመልከት።
14. በ732 ከዘአበ አሦራውያን በይሁዳ ምድር ያደረጉት ግስጋሴ ምን እንደሚመስል ግለጽ።
14 ያም ሆኖ እንኳ በ732 ከዘአበ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን አሦራውያን ይሸነፋሉ ብሎ ማመን አስቸጋሪ ሆኖባቸው መሆን አለበት። ግዙፍ የሆነው የአሦራውያን ሠራዊት ያለ ፋታ ወደ ፊት በመገስገስ ላይ ነበር። በይሁዳ ያሉትን በእጁ የወደቁ ከተሞች ዝርዝር ልብ በል:- “አንጋይ . . . መጌዶን . . . ማክማስ . . . ጌባ . . . ራማ . . . የሳኦል ጊብዓ . . . ጋሊም . . . ላይሳ . . . ዓናቶት . . . መደቤና . . . ግቤር . . . ኖብ።” (ኢሳይያስ 10:28-32ሀ)b በመጨረሻ ወራሪዎቹ ከኢየሩሳሌም 50 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ለኪሶ ደረሱ። ብዙም ሳይቆይ ግዙፍ የሆነው የአሦራውያን ሠራዊት ከተማዋን ስጋት ላይ ጣላት። “በጽዮን ሴት ልጅ ተራራ በኢየሩሳሌም ኮረብታ ላይ እጁን ያንቀሳቅሳል።” (ኢሳይያስ 10:32ለ) አሦራውያንን ሊገታቸው የሚችለው ምንድን ነው?
15, 16. (ሀ) ንጉሥ ሕዝቅያስ ጠንካራ እምነት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? (ለ) ሕዝቅያስ ይሖዋ እንደሚረዳው እንዲያምን የሚያስችል ምን መሠረት ነበረው?
15 ከተማው ውስጥ በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ያለው ንጉሥ ሕዝቅያስ ተጨንቋል። ልብሱን ቀድዶ ማቅ ለበሰ። (ኢሳይያስ 37:1) ስለ ይሁዳ ይሖዋን ይጠይቁ ዘንድ ሰዎችን ወደ ነቢዩ አሳይያስ ላከ። ወዲያውም የይሖዋን መልስ ይዘው መጡ:- “አትፍራ . . . ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ።” (ኢሳይያስ 37:6, 35) ያም ሆኖ ግን አሦራውያን እጅግ የሚያስፈሩና ፍጹም የእርግጠኝነት ስሜት የነበራቸው ናቸው።
16 ንጉሥ ሕዝቅያስን ከገጠመው ቀውስ የሚያወጣው እምነት ነበር። እምነት “የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” (ዕብራውያን 11:1) በዓይን ከሚታየው ነገር ባሻገር መመልከትን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ እምነት በእውቀት ላይ የተመሠረተ ነው። ይሖዋ ቀደም ብሎ የሚከተሉትን የሚያጽናኑ ቃላት እንደተናገረ ሕዝቅያስ ሳያስታውስ አይቀርም:- “በጽዮን የምትኖር ሕዝቤ ሆይ፣ አሦር[ን] . . . አትፍራው። ቁጣዬ እስኪፈጸም መዓቴም እስኪያጠፋቸው ድረስ ጥቂት ጊዜ ቀርቶአልና። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ምድያምን በሔሬብ ዓለት በኩል እንደ መታው ጅራፍ ያነሣበታል፤ በትሩም በባሕር ላይ ይሆናል፣ በግብጽም እንዳደረገ ያነሣዋል።” (ኢሳይያስ 10:24-26)c አዎን፣ የአምላክ ሕዝቦች ከዚህ ቀደምም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥመዋቸው ነበር። የሕዝቅያስ ወገኖች የሆኑት የቀድሞዎቹ እስራኤላውያን በቀይ ባሕር እጅግ ብርቱ ከነበረው የግብጻውያን ሠራዊት ጋር ተፋጥጠው ነበር። ከዚህ ብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ጌዴዎንም እስራኤልን ከወረሩትና በቁጥር እጅግ ከሚበልጡት የምድያማውያንና የአማሌቃውያን ሠራዊት ጋር ተፋጥጦ ነበር። ይሁን እንጂ በእነዚህ ሁለት አጋጣሚዎች ይሖዋ ሕዝቡን አድኗል።—ዘጸአት 14:7-9, 13, 28፤ መሳፍንት 6:33፤ 7:21, 22
17. የአሦራውያን ቀንበር ‘የተሰበረው’ እንዴት ነው? ለምንስ?
17 ይሖዋ ቀደም ባሉት በእነዚያ ጊዜያት ያደረገውን ዓይነት ነገር ደግሞ ያደርግ ይሆን? አዎን። ይሖዋ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “በዚያም ቀን ሸክሙ ከጫንቃህ ቀንበሩም ከአንገትህ ላይ ይወርዳል፤ ቀንበሩም ከውፍረት [ከዘይቱ፣” NW] የተነሣ ይሰበራል።” (ኢሳይያስ 10:27) የአሦራውያን ቀንበር ከአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ጫንቃና አንገት ላይ ይወርዳል። በእርግጥም ደግሞ ቀንበሩ “ይሰበራል” እንክትክቱ ይወጣል! የይሖዋ መልአክ 185,000 የአሦራውያን ወታደሮችን በአንድ ሌሊት ገደለ። የስጋት ደመናው ተገፈፈ፤ አሦራውያንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የይሁዳን ምድር ለቅቀው ወጡ። (2 ነገሥት 19:35, 36) ለምን? ‘ከዘይቱ የተነሣ’ ነው። ይህም አባባል ንጉሥ ሕዝቅያስ በዳዊት መስመር ንጉሥ ሆኖ የተቀባበትን ዘይት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ይሖዋ “ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አጸናት ዘንድ እጋርዳታለሁ” ሲል የገባውን ቃል ፈጽሟል።—2 ነገሥት 19:34
18. (ሀ) የኢሳይያስ ትንቢት ከአንድ በላይ ፍጻሜ አለውን? አብራራ። (ለ) ከጥንቷ ሰማርያ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ዛሬ ያለው ድርጅት የትኛው ነው?
18 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኘው የኢሳይያስ ዘገባ ከ2,700 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በይሁዳ ውስጥ ስለተፈጸሙት ነገሮች የሚተርክ ነው። ይሁን እንጂ እነዚያ ክንውኖች ዛሬ ከፍተኛ ትርጉም አላቸው። (ሮሜ 15:4) ታዲያ ይህ ማለት በዚህ ልብ የሚያንጠለጥል ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ የነበራቸው የሰማርያ እና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲሁም አሦራውያን ዘመናዊ አምሳያ አላቸው ማለት ነውን? አዎን፣ አላቸው። ጣዖት አምላኪ እንደነበረችው ሰማርያ ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም ይሖዋን አመልካለሁ ትበል እንጂ የለየላት ከሃዲ ነች። የሮማ ካቶሊኩ ጆን ሄንሪ ካርዲናል ኒውማን አን ኢሴይ ኦን ዘ ዴቨሎፕመንት ኦቭ ክርስቺያን ዶክትሪን በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ ሕዝበ ክርስትና ለዘመናት ስትጠቀምባቸው የኖሩት እንደ ዕጣን፣ ጧፍ፣ ጠበል፣ ልብሰ ተክህኖ እና ምስሎች ያሉት ነገሮች “ሁሉ ምንጫቸው አረማዊ” ነው ሲሉ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ይሖዋ በሰማርያ ጣዖት አምልኮ እንዳልተደሰተ ሁሉ አረማዊ አምልኮን በቀላቀለችው ሕዝበ ክርስትናም ቢሆን አይደሰትም።
19. ሕዝበ ክርስትና ስለ ምን ነገር ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷታል? ማስጠንቀቂያውን የሚናገሩትስ እነማን ናቸው?
19 የይሖዋ ምሥክሮች ለብዙ ዓመታት ይሖዋ በሕዝበ ክርስትና እንደማይደሰት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። ለምሳሌ ያህል በ1955 “‘የዓለም ብርሃን’ ሕዝበ ክርስትና ናት ወይስ ክርስትና?” የሚል ርዕስ ያለው የሕዝብ ንግግር በዓለም ዙሪያ ተሰጥቷል። ንግግሩ ሕዝበ ክርስትና ከእውነተኛ የክርስትና ትምህርቶችና ልማዶች እንዴት እንደራቀች ቁልጭ አድርጎ የሚያስረዳ ነበር። ከዚያም ጠንካራ መልእክት ያለው የዚህ ንግግር ቅጂዎች በብዙ አገሮች ለሚገኙ ቀሳውስት ተልከዋል። በድርጅት ደረጃ ሕዝበ ክርስትና ማስጠንቀቂያውን ሳትቀበል ቀርታለች። ይሖዋ የቀረው አማራጭ አንድ ብቻ ይኸውም እርስዋን ‘በበትር’ መቅጣት ነው።
20. (ሀ) ዘመናዊ አሦር በመሆን ሚና የሚጫወተው ማን ነው? እንደ በትር ሆኖ የሚያገለግለውስ እንዴት ነው? (ለ) ሕዝበ ክርስትና የሚደርስባት ቅጣት ምን ይመስላል?
20 ይሖዋ ዓመፀኛ የሆነችውን ሕዝበ ክርስትና ለመቅጣት የሚጠቀመው በማን ይሆናል? መልሱን በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ እናገኘዋለን። እዚያ ምዕራፍ ውስጥ ሕዝበ ክርስትናን ጨምሮ መላውን የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅት የምትወክል “ታላቂቱ ባቢሎን” የተባለች አንዲት ጋለሞታ እንዳለች ይገልጻል። ይህች ጋለሞታ ሰባት ራስና አሥር ቀንድ ያለውን ቀይ አውሬ ትጋልባለች። (ራእይ 17:3, 5, 7-12) አውሬው የሚያመለክተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ነው።d የጥንቱ አሦር ሰማርያን እንዳጠፋ ሁሉ ቀዩ አውሬም ‘ጋለሞታይቱን ይጣላና ባዶዋንና ራቁትዋን ያደርጋታል፣ ሥጋዋንም ይበላል፣ በእሳትም ያቃጥላታል።’ (ራእይ 17:16) በዚህ መንገድ ዘመናዊው አሦር (በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የታቀፉት መንግሥታት) በሕዝበ ክርስትና ላይ ኃያል ክንዱን በማሳረፍ ከሕልውና ውጭ ያደርጋታል።
21, 22. አውሬው በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር የሚያነሳሳው ማን ነው?
21 የታመኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር አብረው ይጠፉ ይሆን? በፍጹም። አምላክ በእነርሱ አልተከፋም። ንጹሕ አምልኮ ይቀጥላል። ይሁን እንጂ ታላቂቱ ባቢሎንን የሚያጠፋው አውሬ በይሖዋ ሕዝቦችም ላይ የስስት ዓይኑን ይጥላል። አውሬው ይህን ሲያደርግ የሚያስፈጽመው የአምላክን ሐሳብ አይደለም። ታዲያ የማንን ሐሳብ ነው? የሰይጣን ዲያብሎስን ነው።
22 ይሖዋ የሰይጣንን ትዕቢት የሞላበት ሴራ እንዲህ በማለት ያጋልጣል:- “በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ [ወደ ሰይጣን ልብ] ይገባል፤ ክፉ አሳብንም ታስባለህ፣ እንዲህም ትላለህ:- . . . ተዘልለው ወደሚኖሩ፣ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ [መከላከያ] ቅጥር . . . ወደሚቀመጡ እገባለሁ፤ ምርኮን ትማርክ ዘንድ ብዝበዛንም ትበዘብዝ ዘንድ።” (ሕዝቅኤል 38:10-12) ሰይጣን እንዲህ ብሎ ያስባል:- ‘ብሔራት የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲያጠቁ ለምን አላነሳሳቸውም? የሚኖሩት ተዘልለው ነው፣ መከላከያም ሆነ ፖለቲካዊ ኃይል የላቸውም። ምንም መቋቋም አይችሉም። እነርሱን መበዝበዝ ከተተወ የወፍ ጎጆ ውስጥ እንቁላል የመሰብሰብን ያህል ቀላል ይሆናል!’
23. ዘመናዊው አሦር በሕዝበ ክርስትና ላይ እንዳደረገው በአምላክ ሕዝቦች ማድረግ ሳይችል የሚቀረው ለምንድን ነው?
23 ይሁን እንጂ ብሔራት ተጠንቀቁ! የይሖዋን ሕዝብ ብትነኩ የምትጣሉት ከራሱ ከአምላክ ጋር መሆኑን እወቁ! ይሖዋ ሕዝቡን ይወድዳል። በሕዝቅያስ ዘመን ለኢየሩሳሌም እንደተዋጋ ሁሉ ዛሬም ለሕዝቦቹ እንደሚዋጋላቸው ጥርጥር የለውም። የዘመናችን አሦር የይሖዋን አገልጋዮች ለማጥፋት ሲሞክር ከይሖዋ አምላክና ከበጉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መዋጋቱ ይሆናል። ይህ ደግሞ በድል የማይወጣው ጦርነት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል” ይላል። (ራእይ 17:14፤ ከማቴዎስ 25:40 ጋር አወዳድር።) እንደ ጥንቱ አሦር ሁሉ ቀዩ አውሬም ‘ወደ ጥፋት ይሄዳል።’ ከዚያ በኋላ የሚፈራው አይኖርም።—ራእይ 17:11
24. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ለወደፊቱ ጊዜ ለመዘጋጀት ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል? (ለ) ኢሳይያስ የወደፊቱን ጊዜ አሻግሮ የተመለከተው እንዴት ነው? (በገጽ 155 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)
24 እውነተኛ ክርስቲያኖች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና አጠንክረው እንደያዙ ከቀጠሉና የእርሱን ፈቃድ መፈጸምን በሕይወታቸው ውስጥ አንደኛ ቦታ ከሰጡት የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት ሊጠባበቁ ይችላሉ። (ማቴዎስ 6:33) ‘የሚያስፈራቸው ክፉ ነገር’ አይኖርም። (መዝሙር 23:4) የአምላክ ኃያል ክንድ እነርሱን ለመቅጣት ሳይሆን ከጠላቶቻቸው ለመታደግ ከፍ ብላ እንደተነሳች በእምነት ዓይናቸው ያያሉ። ጆሮአቸውም ‘አትፍሩ’ የሚለውን መንፈስ የሚያረጋጋ ቃል ይሰማል።—ኢሳይያስ 10:24
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 203ን ተመልከት።
b ሐሳቡን ግልጽ ለማድረግ ሲባል ኢሳይያስ 10:28-32 ከኢሳይያስ 10:20-27 ቀድሞ ተብራርቷል።
c ስለ ኢሳይያስ 10:20-23 የተሰጠውን ማብራሪያ ለማግኘት በገጽ 155 ላይ የሚገኘውን “ኢሳይያስ የወደፊቱን ጊዜ አሻግሮ ይመለከታል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በተዘጋጀው ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 34 እና 35 ላይ ስለ ጋለሞታዋና ስለ ቀዩ አውሬ ማንነት ተጨማሪ መረጃ ይገኛል።
[በገጽ 155, 156 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ኢሳይያስ የወደፊቱን ጊዜ አሻግሮ ይመለከታል
አሥረኛው የኢሳይያስ ምዕራፍ በዋነኛነት ያተኮረው ይሖዋ የአሦራውያንን ወረራ በመጠቀም በእስራኤል ላይ የቅጣት ፍርዱን በማስፈጸሙና ኢየሩሳሌምን ለመጠበቅ በገባው ቃል ላይ ነው። ከኢሳይያስ 10 ቁጥር 20 እስከ 23 ያሉት ቁጥሮች በትንቢቱ መሐል የሚገኙ በመሆናቸው በተመሳሳይ ወቅት ላይ አጠቃላይ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ። (ከኢሳይያስ 1:7-9 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ከቃላቱ አቀማመጥ መረዳት እንደሚቻለው እነዚህ ቁጥሮች በትክክል የሚያመለክቱት ኢየሩሳሌምም ጭምር ለነዋሪዎቿ ኃጢአት መልስ ስለምትሰጥበት የኋለኛው ጊዜ ነው።
ንጉሥ አካዝ ለደኅንነቱ ዋስትና እንዲሆነው የአሦርን እርዳታ ለማግኘት ሞክሯል። ነቢዩ ኢሳይያስ ወደፊት ከእስራኤል ቤት የተረፉት ሰዎች በፍጹም እንዲህ ያለ ከንቱ ጎዳና እንደማይከተሉ አስቀድሞ ተናግሯል። ኢሳይያስ 10:20 “በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ በእውነት” እንደሚታመኑ ይናገራል። ይሁን እንጂ ኢሳይያስ 10 ቁጥር 21 ይህንን የሚያደርጉት ‘ጥቂት ቀሪዎች’ ብቻ እንደሆኑ ይገልጻል። ይህም እንደ ምልክት የሆነውንና ‘ጥቂት ቀሪዎች ብቻ ይመለሳሉ’ የሚል ትርጉም ያዘለ ስም ያለውን የኢሳይያስ ልጅ ያሱብን ያስታውሰናል። (ኢሳይያስ 7:3) ኢሳይያስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 22 የተቀጠረ “ጥፋት” እንዳለ ያስጠነቅቃል። በዓመፀኛ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው እንዲህ ያለው ጥፋት ተገቢ ቅጣት በመሆኑ የጽድቅ እርምጃ ነው። ከዚህ የተነሣ “እንደ ባሕር አሸዋ” ካለው ትልቅ ብሔር መካከል የሚመለሱት ጥቂት ቀሪዎች ብቻ ይሆናሉ። ኢሳይያስ 10 ቁጥር 23 ደግሞ መጪው ጥፋት ምድሪቱን በሙሉ የሚጠቀልል እንደሚሆን ያስጠነቅቃል። በዚህ ጊዜ ኢየሩሳሌምም ብትሆን አትተርፍም።
እነዚህ ቁጥሮች በ607 ከዘአበ ይሖዋ የባቢሎናውያንን ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት እንደ “በትር” በተጠቀመበት ጊዜ ምን ነገር እንደተከናወነ በሚገባ የሚገልጹ ናቸው። ኢየሩሳሌምን ጨምሮ መላው ምድር በወራሪዎች እጅ ወድቆ ነበር። አይሁዳውያን ለ70 ዓመታት ያህል በባቢሎን ምርኮ ተወስደው ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ‘ጥቂት ብቻ’ ቢሆኑም አንዳንድ ‘ቀሪዎች’ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው እውነተኛውን አምልኮ ለማቋቋም በቅተዋል።
ከሮሜ 9:27, 28 መረዳት እንደሚቻለው በኢሳይያስ 10:20-23 ላይ የሚገኘው ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ተጨማሪ ፍጻሜ ነበረው። (ከኢሳይያስ 1:9፤ ሮሜ 9:29 ጋር አወዳድር።) ጥቂት ቁጥር ያላቸው የታመኑ አይሁዳውያን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በመሆን ይሖዋን “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ በመጀመራቸው ጳውሎስ በመንፈሳዊ ሁኔታ አይሁዳውያን ‘ቀሪዎች’ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ወደ ይሖዋ ‘እንደተመለሱ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:24) ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ ሌላ ያመኑ አሕዛብም ተጨምረው ‘የአምላክ እስራኤል’ መንፈሳዊ ብሔር ሆነዋል። (ገላትያ 6:16) በዚህ ጊዜ “ከእንግዲህ ወዲህ” ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ብሔር ከእርሱ ዘወር በማለት በሰብዓዊ ኃይሎች እንደማይታመን የሚናገሩት የኢሳይያስ 10:20 ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል።
[በገጽ 147 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]
ሰናክሬም ብሔራትን መሰብሰብ ከወፍ ጎጆ ውስጥ እንቁላል የመሰብሰብን ያህል ቀላል እንደሆነ አድርጎ አስቧል