ይሖዋን በደስታ ማገልገል
“ይሖዋን በደስታ አገልግሉ። በእልልታም ወደፊቱ ቅረቡ።”—መዝሙር 100:2
1, 2. (ሀ) በጀርመን አገር በበርሊን ከተማ የዘረኝነት መንፈስ የታየው እንዴት ነበር? ይሁን እንጂ “የሺህ ዓመቱ ራይክ” ተጋዳይ ምን ደረሰበት? (ለ) ሐምሌ 1936 በኦሎምፒያ ስታድየም ከታየው ሁኔታ የተለየ የሆነው እንዴት ነው? ከልዩ ልዩ ብሔራት የተውጣጣው የዚህ ሕዝብ ደስታ የተመሠረተው በምን ላይ ነበር?
ስፍራው በበርሊን የሚገኘው የኦሎምፒያ ስታድየም ነው። ይህ ስፍራ ከሃምሳ አራት ዓመት በፊት የናዚው አምባገነን አዶልፍ ሂትለር አራት የወርቅ ሜዳልያ የተሸለመውን ጥቁር አሜሪካዊ ሯጭ በተሳደበ ጊዜ ውዝግብ ተፈጥሮበት ነበር። በእውነትም ሂትለር ይሟገትለት የነበረውን “የአርያውያን ዘር የበላይነት!”a ከንቱ የሚያደርግ ድል ነበር። አሁን ግን በዚሁ ስታድየም ሐምሌ 26, 1990 ጥቁሮች፣ ነጮችና ብጫዎች በጠቅላላው ከ64 ብሔራት የተውጣጡ 44,532 ሰዎች “ንጹሕ ልሳን” ለተባለው የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ በአንድ ላይ ተሰብስበዋል። በዚህ የዕለተ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ታላቅ የደስታ መንፈስ ሰፍኖአል። 1,018 የጥምቀት እጩዎች የጥምቀት ንግግሩን ካዳመጡ በኋላ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሳቸውን መወሰናቸውን በማረጋገጥ ሁለት ጊዜ “ጃ!” (አዎ) በማለት ጮኸዋል።
2 እነዚህ አዳዲስ የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚጠመቁበት ስፍራ ሲሄዱ በቅደም ተከተል ከስታድየሙ ወጥተው እስኪያልቁ ድረስ 19 ደቂቃ ፈጅቷል። በዚህ ሁሉ ጊዜ በዚህ ሰፊ ሜዳ የጭብጨባ ድምጽ ከዳር እስከ ዳር ያስተጋባ ነበር። በኦሎምፒክ ጨዋታዎች አሸናፊ የሆኑ ስፖርተኞች ዓለምን ድል የሚነሳ ይህን እምነት ላሳዩት በመቶ የሚቆጠሩ ከአሕዛብ የተውጣጡ ሰዎች የተደረገላቸውን ጭብጨባ የሚያክል ተደርጎላቸው አያውቅም። (1 ዮሐንስ 5:3, 4) ደስታቸው በክርስቶስ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች በሙሉ የሺህ ዓመት የበረከት ዘመን እንደሚያመጣላቸው ባላቸው ትምክህት ላይ የተመሠረተ ነው።—ዕብራውያን 6:17, 18፤ ራእይ 20:6፤ 21:4, 5
3. ተሰብሳቢዎቹ ባሳዩት የትምክህት መንፈስ ጎልቶ የታየው የትኛው እውነት ነው? እንዴትስ?
3 በዚህ ቦታ ሁሉም የሚናገሩት የአምላክን ቃል ንጹሕ ልሳን ስለሆነ የዘር ወይም የብሔር ጥላቻ የለም። ይህም የጴጥሮስ ቃል እውነት መሆኑን በጉልህ ያሳያል፦ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።—ሥራ 10:34, 35፤ ሶፎንያስ 3:9
4. አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች አማኝ የሆኑት በምን ዓይነት ሁኔታ እየኖሩ ነው? ጸሎታቸውስ የተመለሰላቸው እንዴት ነው?
4 ከእነዚህ በበርሊኑ ስብሰባ ከተገኙት ሰዎች ብዙዎቹ አማኞች የሆኑት ከባድ ጭቆና በነበረበት በናዚ ዘመንና (1933-45) ከዚያ በኋላ በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ የተጣለው እገዳ እስከተነሳበት እስከ መጋቢት 14, 1990 ድረስ በምሥራቅ ጀርመን በነበረው የሶሻሊስት ዘመን ነበር። ስለዚህ ብዙዎቹ ‘ቃሉን የተቀበሉት በብዙ መከራና በመንፈስ ቅዱስ ደስታ ነበር።’ (1 ተሰሎንቄ 1:6) አሁን ግን ይሖዋን ለማገልገል የበለጠ ነፃነት ስላገኙ ከዚህ ተመለሰ የማይባል ደስታ አግኝተዋል።—ከኢሳይያስ 51:11 አወዳድር
የደስታ ጊዜያት
5. እሥራኤላውያን ይሖዋ ከጠላቶቻቸው ካዳናቸው በኋላ በቀይ ባህር በዓል ያከበሩት እንዴት ነበር?
5 በምሥራቅ አውሮፓና በቅርቡ ደግሞ በአንዳንድ የአፍሪካና የእስያ አገሮች የሚኖሩ ወንድሞቻችን ያገኙት ነፃነት ይሖዋ የጥንት ሕዝቦቹን ከጭቆና ነጻ ያወጣባቸውን ጊዜያት ያስታውሰናል። ይሖዋ በቀይ ባሕር ያደረገውን ኃያል ሥራና እሥራኤላውያን ስለዚህ ተአምራዊ ሥራ ያቀረቡትን የውዳሴ መዝሙር “አቤቱ፣ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፣ ድንቅንም የምታደርግ፣ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?” በሚሉ ቃላት እንደደመደሙ እናስተውላለን። (ዘፀአት 15:11) ዛሬም ይሖዋ ለሕዝቦቹ በሚያደርጋቸው አስደናቂ ሥራዎች አንደሰትምን? በእርግጥ እንደሰታለን።
6. እሥራኤላውያን በ537 እዘአ በፊት የእልልታ ጩኸት ከማሰማታቸው ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
6 የእሥራኤል ሕዝብ በባቢሎን ምርኮ ቆይቶ በ537 ከዘአበ ወደ ምድሩ በተመለሰ ጊዜ ደስታ በደስታ ሆኖ ነበር። በዚህ ጊዜ የይሖዋ ብሔር ኢሳይያስ በትንቢት እንደተናገረው “እነሆ፣ አምላክ መድኃኒቴ ነው፤ ጌታ (ይሖዋ) ኃይሌና ዝማሬዬ ነውና፣ መድኃኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም”ለማለት ችሎ ነበር። እንዴት ያለ ታላቅ ደስታ ነበር! ይህ ሕዝብ ያገኘውን ይህን ደስታ እንዴት ባሉ ቃላት ይገልጽ ይሆን? ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ:- [ይሖዋን] አመስግኑ፣ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናገሩ። ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና [ለይሖዋ] ተቀኙ።” በዘመናችን ነፃነት ያገኙ የይሖዋ አገልጋዮች እንደሚያደርጉት ኃያል ሥራውን በምድር በሙሉ በማሳወቅ እልል ብለዋል።—ኢሳይያስ 12:1-6
በይሖዋ ሥራ መደሰት
7. በ1919 እልል ያሰኘው የትኛው የማዳን እርምጃ ነበር?
7 በዘመናችን የይሖዋ አገልጋዮች በ1919 በአስደናቂ ሁኔታ ነፃነት ባገኙ ጊዜ እልል ማለት ጀምረው ነበር። በዚህ ዓመት መጋቢት 26 ቀን የአስተዳደር ክፍል አባሎች ሁከት አስነስተዋል በሚል የሐሰት ክስ ለዘጠኝ ወራት ታስረው ከቆዩበት የዩናይትድ ስቴትስ ወህኒ ቤት ተፈቱ። ወደ ቤቴል በተመለሱ ጊዜ ትልቅ የአቀባበል በዓል ተደረገላቸው። ከዚህም በላይ ቅቡዓን ቀሪዎች በሙሉ ሠይጣን መላውን ዓለም አስሮ ከያዘበት የሃይማኖት ሥርዓት ማለትም ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ በመውጣታቸው ሊደሰት ችለዋል።—ራእይ 17:3-6፤ 18:2-5
8. በ1919 በሴዳር ፖይንት በተደረገው ስብሰባ ምን አዲስ ጽሑፍ ወጣ? ምንስ ዓይነት የሥራ ጥሪ ቀረበ?
8 በ1919 የተፈጸሙት ታሪካዊ ክንውኖች የተደመደሙት ከመስከረም 1-8 በሴዳር ፖይንት ኦሃዩ ዩ ኤስ ኤ በተደረገው የአምላክ ሕዝቦች ስብሰባ ነበር። “የተባባሪ ሠራተኞች ቀን” በተባለው የዚህ ስብሰባ አምስተኛ ቀን የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ፕሬዘዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ “መንግሥቱን አውጁ” በሚል ርዕስ ቀስቃሽ ንግግር አደረገ። ራእይ 15:2ና ኢሳይያስ 52:7ን ካብራራ በኋላ ወርቃማው ዘመን የተባለ አዲስ መጽሔት (አሁን ንቁ! ይባላል) በየሁለት ሣምንት ታትሞ እየወጣ በተለይ ለመስክ ሥርጭት እንደሚውል አስታወቀ። በንግግሩ መደምደሚያ ላይ እንዲህ አለ፦ “ሙሉ በሙሉ ለጌታ ያደሩ ሁሉ፣ ደፋሮች የሆኑ ሁሉ፣ ልበ ንጹሐን የሆኑ ሁሉ፣ በሙሉ አእምሮአቸው፣ በሙሉ ኃይላቸውና በሙሉ ነፍሳቸው አምላክንና ጌታን ኢየሱስን የሚወዱ ሁሉ አጋጣሚያቸው በፈቀደላቸው መጠን በዚህ ሥራ በደስታ ይሳተፋሉ። እውነተኛ፣ ታማኝና ጥሩ አምባሳደሮች ለመሆን እንድትችሉ ጌታ አመራርና ዘዴ እንዲሰጣችሁ ጠይቁት። ከዚያም የደስታ ዝማሬ በልባችሁ እየዘመራችሁ አገልግሉት።”
9, 10. ይሖዋ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁን መጽሔቶች የማተምና መጽሔቶች ሥራ ያበለጸገው እንዴት ነው?
9 ይህ “የደስታ ዝማሬ” በዓለም በሙሉ ተሰምቶአል። ንቁ! መጽሔት አሁን ባለበት ደረጃ በየእትሙ 12,980,000 ቅጂዎች በ64 ቋንቋዎች እንዲሠራጭ በማስቻል ሥራ ብዙዎቹ አንባቢዎቻችን እንደተካፈሉ አያጠራጥርም። የንቁ! መጽሔት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ወደ እውነት በመምራት የመጠበቂያ ግንብ ባልደረባ ሆኖ አገልግሎአል። በአንድ የሩቅ ምሥራቅ አገር አንዲት አቅኚ እህት አዳዲስ የወጡ መጽሔቶችን ለመጽሔት ደንበኞቿ ለማድረስ በሄደች ቁጥር አንድ ሰው ለዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ እርዳታ እንዲሆን 20 ብር የሚያክል ገንዘብ ይሰጣት ነበር። በእውነትም ለመንግሥቱ ሥራ ያለውን አድናቆት የሚገልጽ መልካም ተግባር ነው።
10 112ኛ ዓመቱን የጀመረው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በአሁኑ ጊዜ በ111 ቋንቋዎች በ15,290,000 ቅጂዎች ይታተማል። ከእነዚህ መካከል በ59 ቋንቋዎች የሚታተሙት መጽሔቶች አንድ ዓይነት ትምህርት ይዘው የሚወጡ ናቸው። የቅቡዓን ቀሪዎች ክፍል ታማኝ መጋቢ እንደመሆኑ መጠን በአድናቆት ለሚጠባበቁት አንባቢዎች ‘መንፈሳዊ ምግባቸውን በተገቢው ጊዜ’ በመስጠት ላይ ነው።(ሉቃስ 12:42) በ1990 የይሖዋ ምሥክሮች ለሁለቱ መጽሔቶች 2,968,309 አዳዲስ ኮንትራት እንዳስገቡ ሪፖርት አድርገዋል። ይህም በ1989 ላይ 22.7 በመቶ ጭማሪ ነው።
ደስታ ተትረፍርፏል
11. (ሀ) በ1922 በሴዳር ፖይንት ለአምላክ ሕዝቦች ምን ዓይነት ጥሪ ቀረበ? (ለ) የእልልታው ድምጽ የተስፋፋው እንዴት ነው?
11 በተጨማሪም በዚያ ጊዜ በቁጥር 10,000 የደረሱት የአምላክ ሕዝቦች በመስከረም ወር 1922 በሴዳር ፖይንት ኦሃዩ ለሁለተኛ ጊዜ በተሰበሰቡና 361 ሰዎች በተጠመቁ ጊዜ ደስታ ተትረፍርፎ ነበር። ወንድም ራዘርፎርድ በማቴዎስ 4:17 “መንግሥተ ሰማያት እነሆ!” የተባለውን ንግግር እንዲህ በማለት ደመደመ፦ “ዓለም በሙሉ ይሖዋ አምላክ መሆኑንና ኢየሱስ ክርስቶስ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል። ይህ ከቀናት ሁሉ የበለጠ ቀን ነው። እነሆ፣ ንጉሥ ነግሦአል። እናንተም የማስታወቂያ ወኪሎቹ ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ።” በዚያ ስብሰባ ላይ በአንድ ድምጽ የእልልታ ጩኸት ያሰሙት ሰዎች ቁጥር በጣም ስለጨመረ በ1989 በዓለም በሙሉ በተደረጉት 1,210 የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ 6,600,000 ሰዎች ተገኝተዋል። 123,688 ሰዎችም ተጠምቀዋል።
12. (ሀ) ዛሬ የአምላክ ሕዝቦች በየትኛው ከግምት ሁሉ በላይ በሆነ ደስታ ይካፈላሉ? (ለ) ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት ለበላይ ባለሥልጣኖች ከምናሳየው መገዛት ጋር የምናመዛዝነው እንዴት ነው?
12 የይሖዋ ምሥክሮች ነፃነታቸውን በአክብሮትና በጥንቃቄ ይንከባከቡታል። ከሁሉም በላይ “እውነትን ታውቃላችሁ፣ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” በሚለው ቃል ዘመናዊ ፍጻሜ በጣም ይደሰታሉ። ከሐሰት ሃይማኖት ምሥጢሮችና አጉል እምነቶች ነፃ መውጣት ምን ያህል የሚያስደስት ነገር ነው! ይሖዋንና ልጁን ማወቅና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይዞ ከይሖዋና ከልጁ ጋር የሥራ ባልደረባ መሆን በቁጥር ሊተመን የማይችል ታላቅ ደስታ ነው። (ዮሐንስ 8:32፤ 17:3፤ 1 ቆሮንቶስ 3:9-11) በተጨማሪም የአምላክ አገልጋዮች የሚያስተዳድሯቸው ዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች በክርስቶስ የሚተዳደረውን የይሖዋ መንግሥት የማወጅ ነፃነታቸውን ሲያከብሩላቸው በጣም ይደሰታሉ። “የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” እየሰጡ “የቄሣርን ለቄሣር” በፈቃደኝነት ይሰጣሉ።—ሮሜ 13:1-7፤ ሉቃስ 20:25
13. የይሖዋ ምሥክሮች ከጭቆና ነፃ ሲወጡ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት እንዴት ነው?
13 ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ የሚፈልግባቸውን ግዴታ እንዳይፈጽሙ ሰብዓዊ ባለሥልጣኖች ሲከለክሏቸው እንደ ሐዋርያት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ይላሉ። በዚህ ጊዜ ሐዋርያት ገዥዎች ፈትተው በለቀቁአቸው ጊዜ “ደስ እያላቸው ወጡ።” ታዲያ ይህን ደስታቸውን የገለጡት እንዴት ነበር? “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።” (ሥራ 5:27-32, 41, 42) የዘመኑ የይሖዋ ምሥክሮችም አገልግሎታቸውን ለመፈጸም የበለጠ ነፃነት ሲያገኙ በጣም ይደሰታሉ። ይሖዋ መንገዳቸውን በከፈተላቸው ብዙ አገሮች ለይሖዋ ስምና ስለ መጪው የክርስቶስ ኢየሱስ መንግሥት ሰፊ ምሥክርነት በመስጠት ጥልቅ ደስታቸውን ይገልጻሉ።—ከሥራ 20:20, 21, 24፤ 23:11፤ 28:16, 23 ጋር አወዳድር።
በደስታ መጽናት
14. ይህ የመንፈስ ፍሬ የሆነው ደስታ በመዝገበ ቃላት ከሚገለጸው ደስታ የጠለቀ የሆነው እንዴት ነው?
14 እውነተኛ ክርስቲያኖች ያገኙት የጠለቀ ደስታ ምንድን ነው? የኦሎምፒክ ውድድር አሸናፊ ከሚያገኘው አላፊና ጊዜያዊ ደስታ በጣም የጠለቀና ዘላቂነት ያለው ደስታ ነው። አምላክ ‘ለሚገዙለት ሁሉ’ የሚሰጠው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው። (ሥራ 5:32) የዌብስተር መዝገበ ቃላት ለደስታ “ከመፈንጠዝ የጠለቀ፣ ከውጪያዊ ተድላ የበለጠ ግልጽ ሆኖ የሚታይ ስሜት” የሚል ፍቺ ይሰጣል። ደስታ ለክርስቲያን ከዚህም የበለጠ ጥልቅ ትርጉም አለው። በእምነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ጠንካራ የመከላከል ኃይል ያለው ባሕርይ ነው። “የይሖዋ ደስታ አምባቸው ነው።” (ነህምያ 8:10 አዓት) የአምላክ ሕዝቦች የሚኮተኩቱት ደስታ ሰዎች ከሥጋዊና ከዓለማዊ ፈንጠዝያዎች ከሚያገኙት ውጪያዊ ተድላ በጣም የላቀ ነው።—ገላትያ 5:19-23
15. (ሀ) በታማኝ ክርስቲያኖች ተሞክሮ ጽናት በደስታ ላይ የታከለው እንዴት ነው? (ለ) ደስተኛ ሆኖ በመኖር ረገድ ዋስትና የሚሰጡ አንዳንድ ጥቅሶችን ጥቀስ።
15 በዩክሬይን የሚኖሩትን ወንድሞቻችን እንውሰድ። የበላይ ባለ ሥልጣኖች በ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ እነዚህን በሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን ወደ ሳይቤሪያ ባጋዙአቸው ጊዜ ብዙ መከራ ደርሶባቸው ነበር። በኋላ ግን ባለሥልጣኖቹ ምሕረት አድርገንላችኋል ብለው በለቀቁአቸው ጊዜ ስላገኙት ነፃነት አመስጋኞች ቢሆኑም ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው የተመለሱት ሁሉም አይደሉም። ለምን ይሆን? ምክንያቱም በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የሠሩት ሥራ ያዕቆብ 1:2-4ን አስታውሶአቸዋል። “ወንድሞቼ ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቊጠሩት።” በሚያስደስተው የመከር ሥራ ጸንተው ለመቆየት ፈለጉ። በቅርቡ በፖላንድ አገር በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እነዚህን ከሩቅ ምሥራቅ ጠረፎች የመጡትን የይሖዋ ምሥክሮች ለመቀበል መቻሉ ታላቅ ደስታ ነበር። ይህን ፍሬ ለማግኘት ጽናትና ደስታ አስፈልጎ ነበር። በእርግጥ በይሖዋ አገልግሎት በደስታ የምንጸና ሁሉ የሚከተለውን ለማለት እንችላለን፦ “እኔ ግን [በይሖዋ] ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። ጌታ [ይሖዋ] ኃይሌ ነው።”—ዕንባቆም 3:18, 19፤ ማቴዎስ 5:11, 12
16. የኤርምያስና የኢዮብ ጥሩ ምሳሌ በመስክ አገልግሎታችን ሊያጽናናን የሚገባው እንዴት ነው?
16 ይሁን እንጂ ልበ ደንዳና የሆኑ ተቃዋሚዎች ባሉበት መሐል በምንመሰክርበት ጊዜ ደስታችንን ጠብቀን ልንኖር የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ነቢያት ይህን የመሰለ ሁኔታ እያጋጠማቸው ደስተኛ ሆነው ለመኖር እንደቻሉ አስታውስ። ኤርምያስ በተፈተነ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ፤ አቤቱ፣ የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ።” (ኤርምያስ 15:16) በይሖዋ ስም መጠራትና ስለዚህ ስም መመስከር እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! በግል ጥናታችን መትጋትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ሙሉ በሙሉ መካፈላችን በእውነት ተደስተን እንድንኖር ያንጸናል። ደስታችን በመስክ አገልግሎት ስንሰማራና በተለያዩ ጊዜያት በፊታችን ላይ በሚታየው ፈገግታ ይገለጻል። ኢዮብ ከባድ ፈተና በደረሰበት ጊዜ እንኳን ስለ ጠላቶቹ “እነርሱ ባልታመኑ ጊዜ ሳቅሁላቸው፤ የፊቴንም ብርሃን አላወረዱም”ለማለት ችሎ ነበር። (ኢዮብ 29:24) እኛም እንደታማኙ ኢዮብ መሆን አለብን እንጂ ተቃዋሚዎች ሲዘብቱብን ማዘን አይገባንም። ሁልጊዜ ፈገግታ ይኑራችሁ። በፊታችን ላይ የሚታየው ፈገግታ ደስታችንን ሊያንጸባርቅና አድማጭ ጆሮ ሊያተርፍልን ይችላል።
17. በደስታ መጽናት ፍሬ ሊያስገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
17 ክልላችንን ደጋግመን በምንሸነፍበት ጊዜ የሚታይብን ደስታና ጽናት የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ልብ ሊነካና ታላቁን ተስፋችንን እንዲመረምሩ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ቋሚ ፕሮግራም አውጥቶ እንደነዚህ ላሉት ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት በጣም የሚያስደስት ሥራ ነው። ውድ የሆነው የአምላክ ቃል እውነት ወደ ልባቸው ጠልቆ ሲገባና በይሖዋ አገልግሎት ባልደረቦቻችን ሲሆኑ እንዴት ያስደስታል! በዚህ ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩት አዳዲስ አማኞች ያለውን ለማለት እንችላለን። “ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።”(1 ተሰሎንቄ 2:19, 20) በእውነትም አዳዲስ ሰዎችን ወደ አምላክ ቃል እውነት ከመምራትና ራሳቸውን የወሰኑ የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሆኑ ከመርዳት የሚያረካ ደስታ ይገኛል።
አጽንቶ የሚያኖር ደስታ
18. በዘመናችን የሚያጋጥሙንን የተለያዩ ፈተናዎች እንድንቋቋም የሚረዳን ምንድን ነው?
18 በዕለታዊ ኑሮአችን ጽናት የሚጠይቅብን የተለያየ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል አካላዊ በሽታ፣ የመንፈስ ጭንቀትና የኢኮኖሚ ችግር ያጋጥማል። ታዲያ አንድ ክርስቲያን እንደነዚህ ያሉትን ሁኔታዎች ለመቋቋምና ደስታውን ጠብቆ ለመኖር እንዴት ይችላል? ይህን ለማድረግ የሚቻለው ማጽናኛና መመሪያ ለማግኘት ወደ አምላክ ቃል በመሄድ ነው። የመዝሙርን መጽሐፍ ማንበብ ወይም በቴፕ የተቀረጸውን መስማት ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥም በጣም ያጽናናል። ዳዊት የሰጠውን የጥበብ ምክር ልብ በል። “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል። እርሱም ይደግፍሃል። እርሱ ጻድቅ እንዲናወጥ አይፈቅድም።” (መዝሙር 55:22 አዓት) ይሖዋ በእርግጥ ‘ጸሎት ሰሚ’ ነው።—መዝሙር 65:2
19. እንደ ዳዊትና ጳውሎስ ምን ትምክህት ሊኖረን ይችላል?
19 የይሖዋ ድርጅትም በተለያዩ ጽሑፎች በጉባኤ ሽማግሌዎች አማካኝነት እኛ ደካሞች የሆንነው በሚያጋጥመን ችግር ሁሉ ለመርዳት ዝግጁ ሆኖ ይጠባበቃል። ዳዊት “መንገድህን (ለይሖዋ) አደራ ስጥ፣ በእርሱም ታመን፣ እርሱም ያደርግልሃል” በማለት ሞቅ ባለ መንፈስ ይጋብዘናል። በተጨማሪም “ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” ለማለት ችሎአል። ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ተባብረን ስንኖር “የጻድቃን መድኃኒታቸው(ከይሖዋ) ዘንድ ነው፤ በመከራቸውም ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው” የሚለውን ቃል እውነተኝነት እንገነዘባለን። (መዝሙር 37:5, 25, 39) “በማንኛውም ጊዜ የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር እንከተል፦ ስለዚህም አንታክትም . . . የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፣ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፣ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። ”—2 ቆሮንቶስ 4:16-18
20. በእምነት ዓይናችን ምን እንመለከታለን? ይህስ እንዴት ይገፋፋናል?
20 በእምነት ዓይናችን ከፊታችን የይሖዋን አዲስ ሥርዓት ለማየት እንችላለን። በዚያ ሥርዓት ውስጥ ወደር የማይገኝለት ደስታና በረከት ይኖራል። (መዝሙር 37:34፤ 72:1, 7፤ 145:16) ለዚህ ታላቅ ዘመን ስንዘጋጅ የመዝሙር 100:2 ቃላት እንፈጽም። “ይሖዋን በደስታ አገልግሉት። በእልልታም ወደፊቱ ቅረቡ።”
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ስለ አርያውያን የበላይነት”ጉዳይ በየካቲት 17, 1940 ኒውዮርክ ታይምስ አንድ የጆርጅ ታውን ዩኒቨርስቲ ካቶሊክ ባለ ሥልጣን “አዶልፍ ሂትለር የጀርመን መንግሥት የሆነችው ቅድስቲቱ የሮማ መንግሥት ተመልሳ መቋቋም ይኖርበታል” ብሎ ሲናገር እንደሰሙ መናገራቸውን ገልጾአል። ይሁን እንጂ ታሪክ ጸሐፊው ዊልያም ኤል ሺረር ያስከተለውን ውጤት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ለሺህ ዓመት ይኖራል ብሎ ሂትለር የፎከረለትንና በናዚ ተከታዮች ‘የሺህ ዓመቱ ራይክ’ ተብሎ ይጠራ የነበረው ጥር 30 ቀን 1933 የተወለደው ሦስተኛ ራይክ የቆየው አሥራ ሁለት ዓመት ከአራት ወር ብቻ ነበር።”
ለመከለስ ያህል
◻ ዛሬ በዘረኝነት ላይ ምን አስደሳች ድል ተገኝቷል?
◻ የጥንት የአምላክ ሕዝቦች እልል እንዲሉና በደስታ እንዲዘምሩ ያደረጋቸው ምን ነበር?
◻ በዘመናችን እውነተኛ ደስታ የበዛው እንዴት ነው?
◻ ጽናትና ደስታ ጎን ለጎን የሚሄዱና የማይነጣጠሉ የሆኑት እንዴት ነው?
◻ ደስታችንን ጠብቀን ለመኖር የምንችለው በምን መንገድ ነው?