በቅርቡ ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ይመጣል
በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ “ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደገና ተመልከት። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ሰይፋቸውን ማረሻ ለማድረግ የሚቀጠቅጡት በአምላክ መንገድ የሚሄዱ ‘ብዙ ሰዎች’ መሆናቸውን እንደሚገልጽ አስተውል። (ኢሳይያስ 2:2-4) ይህም እነዚህ ሰዎች ይሖዋ አምላክን የሚያመልኩና ትእዛዛቱን የሚያከብሩ ሰዎች ናቸው ማለት ነው። ታዲያ እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?
የጦር መሣሪያዎችን መጠቀም ከማቆማቸውም በላይ ወደ ግጭትና ውጊያ የሚመሩ ዝንባሌዎችንና አስተሳሰቦችን ከአእምሮአቸውና ከልባቸው ነቅለው ያስወገዱ ከብዙ ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች መሆን ይኖርባቸዋል። (ሮሜ 12:2) ሰው አይገድሉም፤ ከዚህ ይልቅ ፍቅር ያሳያሉ። (ማቴዎስ 22:36-39) እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ስላላቸው ሰዎች ሰምተህ ታውቃለህን?
የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት እንዳላቸውና የጦር መሣሪያ አንሥተው ሌሎች ሰዎችን እንደማይገድሉ ሰምተህ ሊሆን ይችላል። እስቲ አስበው:- በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ የእነርሱ ዓይነት አመለካከት ቢኖራቸው ኖሮ ይህች ፕላኔት ሰላምና ደኅንነት የሰፈነባት ቦታ አትሆንም ነበርን?
እርግጥ እንደነሱ ዓይነት አመለካከት ያለው ሁሉም ሰው አይደለም። ሁኔታው ንጉሥ ሰሎሞን ከ3,000 ዓመታት በፊት እንደሚከተለው በማለት እንደተናገረው ነው:- “እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፣ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፏቸውም እጅ ኃይል ነበረ።”— መክብብ 4:1
ሰላም ወዳድ ለሆኑ ሰዎች የቀረበ ጥሪ
ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ይመጣልን? አዎን፣ ይመጣል። እንዲህ ያለው ዓለም የሚመጣው በሰዎች ጥረት ነውን? በፍጹም አይደለም። ሰላም የሚመጣው ሰዎች በጅምላ ወደ እውነተኛ ሃይማኖት ሲለወጡ ነውን? አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የመዝሙር መጽሐፍ “የእግዚአብሔርን (“የይሖዋን፣” አዓት) ሥራ፣ . . . እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል” በማለት መልሱን ይሰጣል።— መዝሙር 46:8, 9
ይሖዋ አምላክ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? የምሳሌ መጽሐፍ እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣል:- “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥኣን [የአምላክን ሕግጋት የማያከብሩ ሰዎች] ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”— ምሳሌ 2:21, 22
አምላክ ከአሁን በፊት እርምጃ ያልወሰደበት ዋነኛ ምክንያት የሚከተለው ነው:- ሰዎች መንገዶቹን ተምረው በጎዳናዎቹ ለመመላለስ እንዲችሉ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል” በማለት ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:9) በመሆኑም የአምላክ ሕዝቦች ከራስ ወዳድነት ውጭ በሆነ ስሜት ተገፋፍተው ስለ ይሖዋ እንዲማሩ ሰዎችን በመርዳት ላይ ናቸው። ኢሳይያስ እንደገለጸው “ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ . . . እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል” የሚል ጥሪ ያቀርባሉ።— ኢሳይያስ 2:3
‘የፍጻሜው ዘመን’
በተጨማሪም በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ጥቅስ ሰዎች የሰላም መንገድ የሚማሩት ‘በፍጻሜው ዘመን’ እንደሆነ ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 2:2) በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው በዚህ ዘመን ውስጥ ነው። እንዲያውም በዚህ መቶ ዘመን ውስጥ የተፈጸሙት ጦርነቶች በፍጻሜው ዘመን ውስጥ እየኖርን እንዳለን በግልጽ ያሳያሉ።
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ምልክት ምን እንደሆነ ኢየሱስን ሲጠይቁት “ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል” በማለት ተንብዮአል። (ሉቃስ 21:11፤ ማቴዎስ 24:3) በተጨማሪም “ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፣ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም። በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው:- ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል” ብሏል።— ሉቃስ 21:9, 10
ምንም እንኳ ጦርነቶች ለብዙ ሺህ ዓመታት የነበሩ ቢሆንም ሁለት የዓለም ጦርነቶችና በአንዳንዶች ስሌት መሠረት ሌሎች በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ትናንሽ ጦርነቶች የተካሄዱት በዚህ መቶ ዘመን ብቻ ነው። በዚህ መቶ ዘመን በተደረጉ ጦርነቶች በአሥር ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው በጣም አስደንጋጭ ነው። ወርልድ ዎች የተባለው መጽሔት በዘገበው መሠረት ከ20ኛው መቶ ዘመን በፊት በነበሩት 2,000 ዓመታት ውስጥ አንድ ሚልዮን ሰዎች በጦርነት የሞቱት በአማካይ በ50 ዓመት ጊዜ ውስጥ ነበር። በዚህ መቶ ዘመን አንድ ሚልዮን ሰዎች በጦርነት የሚሞቱበት አማካይ የጊዜ ርዝመት አንድ ዓመት ነው።
ጦርነት የማይኖርበት ዓለም
በእኛ መቶ ዘመን የተፈጸሙት ከባድ ጦርነቶችና በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ውስጥ የተነገሩት ሌሎች ክንውኖች አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ደፍ ላይ መሆናችንን ያሳያሉ። የአሮጌው ዓለም ሥርዓት አልበኝነት ይወገድና ሰላምና ጽድቅ የሰፈነበት “አዲስ ምድር” ይተካል። (2 ጴጥሮስ 3:13) የአምላክ ቃል “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል” ይላል።— መዝሙር 37:9, 11
ዛሬ በመላው ዓለም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጦርነት በማይኖርበት ዓለም ውስጥ ለመኖር ይጓጓሉ። አምላክ እንዲህ ዓይነቱን ዓለም እንደሚያመጣ የገባው ቃል በእርግጥ እንደሚፈጸም በማሳየት አንድ የአምላክ ነቢይ ከረጅም ጊዜ በፊት እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር:- “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።”— ዕንባቆም 2:3
ስለዚህ በአምላክ በመተማመን የሚከተለው ተስፋ ሲፈጸም ማየት ትችላለህ:- “እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ [ከሕዝቡ ጋር ይሆናል፤] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”— ራእይ 21:3, 4
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አዲስ ዓለም በተመለከተ የሚሰጣቸው ተስፋዎች:-
ወንጀል፣ ዓመፅና ክፋት አይኖርም:-
“[አምላክ] እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል።”— መዝሙር 46:9
“ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ . . . ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም።”— መዝሙር 37:9, 10
ሁሉም የሰው ዘሮች በሰላም ይኖራሉ
“ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም . . . የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። . . . በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።”— ኢሳይያስ 9:6, 7
መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች
ኢየሱስ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሏል።— ሉቃስ 23:43
“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”— መዝሙር 37:29
ዓለም አቀፍ ፍቅራዊ ወንድማማችነት
‘እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላም፤ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ ነው።’— ሥራ 10:34, 35
በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ይነሣሉ
‘በመታሰቢያው መቃብር ያሉቱ ሁሉ [የኢየሱስን] ድምፅ ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት ይመጣል።’— ዮሐንስ 5:28, 29
በሽታ፣ እርጅና ወይም ሞት አይኖርም
“እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”— ራእይ 21:4