ምዕራፍ 42
አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር
1. መልአኩ ዮሐንስን ወደ ሺው ዓመት መጀመሪያ በመለሰው ጊዜ ምን ነገር እንደተመለከተ ገለጸ?
ዮሐንስ ይህን ታላቅ ራእይ ማየቱን ቀጠለ። መልአኩ ወደ ሺው ዓመት ግዛት መጀመሪያ መለሰው። የተመለከተውን ነገር እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፣ ባሕርም ወደ ፊት የለም።” (ራእይ 21:1) ልብ የሚመስጥ ትዕይንት መታየት ጀመረ!
2. (ሀ) ኢሳይያስ ስለ አዲስ ሰማይና ስለ አዲስ ምድር የተናገረው ትንቢት በ537 ከዘአበ በአይሁዳውያን ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) የኢሳይያስ ትንቢት ሌላ ተጨማሪ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው እንዴት እናውቃለን? ይህስ ተስፋ የሚፈጸመው እንዴት ነው?
2 ዮሐንስ ዘመን በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ይሖዋ ለኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እነሆ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም።” (ኢሳይያስ 65:17፤ 66:22) ይህ ትንቢት ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመው ታማኝ አይሁዳውያን ከ70 ዓመታት የባቢሎን ግዞት በኋላ በ537 ከዘአበ ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱ ጊዜ ነበር። በዚህ የተሐድሶ ዘመን በ“አዲስ ሰማይ” ማለትም በአዲስ የአገዛዝ ሥርዓት ሥር “አዲስ ምድር” ወይም የጸዳ ማኅበረሰብ አቋቁመው ነበር። ይሁን እንጂ ትንቢቱ ሌላ ተጨማሪ ፍጻሜ እንደሚኖረው ሐዋርያው ጴጥሮስ አመልክቶአል። “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:13) አሁን ደግሞ ዮሐንስ ይህ የተስፋ ቃል በጌታ ቀን ውስጥ እንደሚፈጸም አመለከተ። “የቀደመው ሰማይና የቀደመው ምድር” ማለትም የተደራጀው የሰይጣን ሥርዓት በሰይጣንና በአጋንንቱ ከሚመራው መንግሥታዊ መዋቅር ጋር ያልፋል። የክፉዎችና የዓመፀኞች ሰዎች ተነዋዋጭ “ባሕር” ፈጽሞ አይኖርም። በእርሱ ቦታ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ማለትም በአዲሱ የአምላክ መንግሥት ሥር የሚተዳደር አዲስ ሰብዓዊ ማኅበረሰብ ይቋቋማል።—ከራእይ 20:11 ጋር አወዳድር።
3. (ሀ) ዮሐንስ ምን ነገር ይገልጽልናል? አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ምንድን ነች? (ለ) አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ‘ከሰማይ የወረደችው’ እንዴት ነው?
3 ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣ ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፣ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።” (ራእይ 21:2) አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የክርስቶስ ሙሽራ ስትሆን እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ሆነው ከፍ ያለ ክብር ከተቀዳጀው ኢየሱስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ለመሆን በሚነሱት ቅቡዓን ክርስቲያኖች አባልነት የተገነባች ነች። (ራእይ 3:12፤ 20:6) ምድራዊቱ ኢየሩሳሌም በጥንትዋ የእስራኤል ምድር የመንግሥት መቀመጫ እንደነበረች ሁሉ በጣም የተዋበችው አዲሲቱ ኢየሩሳሌምና ሙሽራው የአዲሱን ሥርዓት መንግሥት ይመሠርታሉ። አዲሱ ሰማይ የተባለው ይህ ነው። ሙሽራይቱ ከሰማይ የምትመጣው ቃል በቃል ሳይሆን ትኩረቷን ወደ ምድር በማዞር ነው። በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የሚገዛውን የጽድቅ መንግሥት በሚያስተዳድርበት ጊዜ የበጉ ሙሽራ ረዳቱ ሆና ትሠራለች። በእውነትም ለአዲሱ ምድር ትልቅ በረከት ነው።
4. አምላክ ለእስራኤል ሕዝብ የሰጠውን የመሰለ ምን ተስፋ ሰጥቶአል?
4 ዮሐንስ በመቀጠል እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ታላቅም ድምፅ ከሰማይ:- እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል።” (ራእይ 21:3) ይሖዋ በዚያ ጊዜ ከተወለደው አዲስ ብሔር ጋር የሕግ ቃል ኪዳን በገባበት ጊዜ የሚከተለውን እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። “ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፣ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁም እሄዳለሁ፣ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ።” (ዘሌዋውያን 26:11, 12) አሁን ደግሞ ይሖዋ ለታማኝ ሰዎች ተመሳሳይ ቃል ገብቶላቸዋል። በሺህ ዓመቱ የፍርድ ቀን ልዩ ሕዝቦች ይሆኑለታል።
5. (ሀ) አምላክ በሺው ዓመት ዘመን ከሰው ልጆች ጋር የሚያድረው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ ከሺው ዓመት በኋላ ከሰው ልጆች ጋር የሚኖረው እንዴት ነው?
5 በሺው ዓመት ግዛት ዘመን ይሖዋ በሚኖረው ጊዜያዊ ዝግጅት አማካኝነት በንጉሣዊ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ተወክሎ ከሰው ልጆች ጋር “ያድራል።” ይሁን እንጂ የሺው ዓመት ግዛት በሚፈጸምበት ጊዜ ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ ካስረከበ በኋላ ንጉሣዊ ወኪል ወይም አማላጅ አስፈላጊ አይሆንም። ይሖዋ ‘ከሕዝቦቹ ጋር’ ለዘለቄታው ቀጥተኛ በሆነ መንገድ በመንፈስ ይኖራል። (ከዮሐንስ 4:23, 24 ጋር አወዳድር።) ይህም ተሐድሶ ላገኘው የሰው ልጅ እንዴት ያለ ከፍተኛ መብት ይሆናል!
6, 7. (ሀ) ዮሐንስ የትኛውን ታላቅ ተስፋ ገልጾልናል? ከእነዚህስ በረከቶች የሚካፈሉት እነማን ናቸው? (ለ) ኢሳይያስ መንፈሳዊና አካላዊ ስለሆነ ገነት የገለጸው እንዴት ነው?
6 ዮሐንስ አሁንም በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኃዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” (ራእይ 21:4) አሁንም እንደገና ቀደም ሲል በመንፈስ የተነገረ የተስፋ ቃል እንድናስታውስ ተደርገናል። ኢሳይያስም ሞትና ሐዘን ጠፍቶ ልቅሶ በሐሴት የሚተካበትን ጊዜ በተስፋ ተጠባብቆ ነበር። (ኢሳይያስ 25:8፤ 35:10፤ 51:11፤ 65:19) እነዚህ ተስፋዎች በሺው ዓመት የፍርድ ቀን በአስደናቂ ሁኔታ እንደሚፈጸሙ ዮሐንስ አረጋግጦልናል። በረከቶቹን ለማግኘት የመጀመሪያ የሚሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ናቸው። “በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው” ሆኖ “ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” (ራእይ 7:9, 17) ቀስ በቀስ ግን ከሙታን የተነሱትና በይሖዋ ዝግጅት የሚታመኑ ሁሉ ከእነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ጋር እየኖሩ በመንፈሣዊም ሆነ በሥጋዊ ገነት ውስጥ ይደሰታሉ።
7 “በዚያን ጊዜም” ይላል ኢሳይያስ “የዕውሮች ዓይን ይገለጣል፣ የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል።” አዎ፣ “በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።” (ኢሳይያስ 35:5, 6) በተጨማሪም በዚያን ጊዜ “ቤቶችንም ይሠራሉ፣ ይቀመጡባቸውማል። ወይኑንም ይተክላሉ፣ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም። የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፣ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።” (ኢሳይያስ 65:21, 22) ስለዚህ ከምድር ላይ ጨርሰው አይነቀሉም።
8. ይሖዋ ስለ እነዚህ ተስፋዎች አስተማማኝነት ምን ተናግሮአል?
8 እነዚህን ተስፋዎች በምናሰላስልበት ጊዜ ልባችን በጣም አስደናቂ በሆነ የወደፊት ሁኔታ ትዕይንት ይሞላል። ታማኝ የሆነው የሰው ልጅ በፍቅር ላይ በተመሰረተው የሰማይ መንግሥት ሥር አስደናቂ ዝግጅቶች ይጠብቁታል። እነዚህ ተስፋዎች በጣም ጥሩ ስለሆኑ ይፈጸማሉ ብሎ ለማመን ያስቸግራልን? በጳጥሞስ ደሴት ታስሮ የነበረው ሽማግሌ የተመለከተው ነገር ሁሉ ተራ ቅዠት ነውን? ይሖዋ ራሱ መልሱን ይሰጠናል:- “በዙፋንም የተቀመጠው:- እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም:- እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ። አለኝም:- ተፈጽሞአል። አልፋና ዖሜጋ፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።”— ራእይ 21: 5, 6ሀ
9. እነዚህ በረከቶች እንደሚመጡ እርግጠኛ ለመሆን የሚቻለው ለምንድን ነው?
9 እነዚህ የወደፊት በረከቶች መፈጸማቸው እንደማይቀር ይሖዋ ራሱ የማረጋገጫ ፊርማ እንደፈረመ ወይም ዋስትና እንደሰጠ ያህል ነው። እንዲህ ያለው አምላክ የሰጠውን ዋስትና ሊጠራጠር የሚደፍር ማን ነው? እነዚህ ተስፋዎች በጣም እርግጠኞች ስለሆኑ ቀደም ብለው እንደተፈጸሙ አድርጎ ተናግሮአል። “ተፈጽሞአል!” አለ። ይሖዋ “ያለውና የነበረው፣ የሚመጣውም፣ ሁሉንም የሚገዛ . . . አልፋና ዖሜጋ” አይደለምን? (ራእይ 1:8) እርግጥ ነው። እርሱ ራሱ “እኔ ፊተኛ ነኝ፣ እኔም ኋለኛ ነኝ። ከእኔ ሌላም አምላክ የለም” ብሎአል። (ኢሳይያስ 44:6) እንዲህ ያለ አምላክ በመሆኑም ትንቢት ሊያስነግርና ያስነገራቸውም ትንቢቶች በዝርዝር መፈጸማቸውን ሊከታተል ይችላል። በጣም እምነት የሚያጠነክር ነገር ነው። በዚህም ምክንያት “እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” በማለት ቃል ገብቶልናል። እነዚህ አስደናቂ ተስፋዎች እውነት ይፈጸሙ ይሆንን እያልን ከመጠራጠር ይልቅ ‘እንደዚህ ያለውን በረከት ለመውረስ እኔ በግሌ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ ብለን ብንጠይቅ ይበጀናል።
“ውኃ” ለተጠሙ ሰዎች
10. ይሖዋ ምን ዓይነት “ውኃ” ሰጥቶአል? እርሱስ የምን ምሳሌ ነው?
10 “ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ” ያለው ይሖዋ ራሱ ነው። (ራእይ 21:6ለ) አንድ ሰው ይህን ጥማት ለማርካት ከፈለገ ስለሚያስፈልጉት መንፈሳዊ ነገሮች የሚያስብና ይሖዋ የሚሰጠውን “ውኃ” ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል። (ኢሳይያስ 55:1፤ ማቴዎስ 5:3) ይህ “ውኃ” ምንድን ነው? ኢየሱስ ራሱ በሰማርያ በነበረ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሴት በመሰከረላት ጊዜ የዚህን ጥያቄ መልስ ሰጥቶአል። እንዲህ አላት:- “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም። እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ።” ይህ “የሕይወት ውኃ ምንጭ” በክርስቶስ በኩል ከአምላክ የሚፈስና ሰውን ወደ ፍጹም ሕይወት የሚያደርስ የሕይወት ዝግጅት ነው። እንደ ሳምራዊቷ ሴት ከዚህ ምንጭ ለመጠጣት ትልቅ ጉጉት ሊኖረን ይገባል። እንደዚህች ሴት ጊዜያዊ የሆኑ ሰብዓዊ ጉዳዮችን ትተን ለሌሎች ምሥራቹን ለመናገር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።—ዮሐንስ 4:14, 15, 28, 29
ድል ነሺዎቹ
11. ይሖዋ ምን ዓይነት ተስፋ ሰጥቶአል? ይህስ የመጀመሪያ ተፈጻሚነቱን ያገኘው በማን ላይ ነው?
11 ከዚህ አርኪ “ውኃ” የሚጠጡ ሁሉ ድል መንሳት ይኖርባቸዋል። ይህንንም ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል:- “ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል፣ አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል።” (ራእይ 21:7) ይህ ተስፋ ለሰባቱ ጉባኤዎች በተላኩት መልእክቶች ከተገለጹት ተስፋዎች ጋር ይመሳሰላል። በዚህም ምክንያት እነዚህ ቃላት በአንደኛ ደረጃ የሚፈጸሙት ለቅቡዓን ደቀ መዛሙርት ነው። (ራእይ 2:7, 11, 17, 26-28፤ 3:5, 12, 21) የክርስቶስ መንፈሣዊ ወንድሞች ባለፉት ዘመናት ሁሉ የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ክፍል የመሆንን መብት በጉጉትና በናፍቆት ሲጠባበቁ ኖረዋል። እንደ ኢየሱስ ድል ከነሱ ተስፋቸው ይረጋገጥላቸዋል።—ዮሐንስ 16:33
12. በራእይ 21:7 ላይ የተጠቀሰው የይሖዋ ተስፋ ለእጅግ ብዙ ሰዎች የሚፈጸመው እንዴት ነው?
12 ከብሔራት የተውጣጡት እጅግ ብዙ ሰዎችም ይህን ተስፋ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። እነርሱም ቢሆኑ ታላቁን መከራ በሕይወት እስኪያልፉ ድረስ አምላክን በታማኝነት በማገልገል ድል መንሳት ይኖርባቸዋል። ይህን ካደረጉ ወደ ምድራዊ ውርሻቸው ማለትም ‘ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ወደ ተዘጋጀላቸው መንግሥት’ ይገባሉ። (ማቴዎስ 25:34) እነዚህም ሆኑ ሌሎቹ በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ የሚሰጠውን ፈተና የሚያልፉ የጌታ ምድራዊ በጎች ክፍሎች “ቅዱሳን” ተብለው ተጠርተዋል። (ራእይ 20:9) የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ክፍል እንደመሆናቸው መጠን ከፈጣሪያቸው ጋር ቅዱስ የሆነና የአባትና የልጅነት ዝምድና ይኖራቸዋል።—ኢሳይያስ 66:22፤ ዮሐንስ 20:31፤ ሮሜ 8:21
13, 14. የአምላክን ታላቅ ተስፋ ለመውረስ ከፈለግን እንዴት ያሉ ድርጊቶችን በቆራጥነት ማስወገድ ይኖርብናል? ለምንስ?
13 የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ይህን ታላቅ ተስፋ በሚጠባበቁበት ጊዜ ከሰይጣን ዓለም እድፈት ሁሉ ንጹሕ ሆነው መኖራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ዲያብሎስ አስገድዶም ሆነ አታልሎ ይሖዋ ቀጥሎ ከገለጻቸው ሰዎች ጋር እንድንቆጠር እንዳያደርገን ጠንካሮች፣ ቆራጦችና ብርቱዎች መሆን ያስፈልገናል:- “ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኩሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛ ሞት ነው።” (ራእይ 21:8) አዎ፣ በረከቶቹን ለመውረስ የሚፈልግ ሁሉ ይህን አሮጌ ሥርዓት ካቆሸሹትና ካረከሱት ድርጊቶች መራቅ ይኖርበታል። ማንኛውንም ተጽዕኖና ፈተና ተቋቁሞ በታማኝነት በመጽናት ድል መንሳት ይኖርበታል።—ሮሜ 8:35-39
14 ሕዝበ ክርስትና የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ ብትልም ዮሐንስ እዚህ ላይ በገለጻቸው አስነዋሪ ድርጊቶች ሁሉ የጐደፈች ነች። በዚህም ምክንያት ከቀሩት የታላቂቱ ባቢሎን ክፍሎች ጋር ወደ ዘላለም ጥፋት ትወርዳለች። (ራእይ 18:8, 21) በተመሳሳይም ከቅቡዓን ወይም ከእጅግ ብዙ ሰዎች መካከል እነዚህን ክፉ ድርጊቶች ቢፈጽም ወይም ሌሎች እንዲፈጽሙ ማበረታታት ቢጀምር የዘላለም ጥፋት ያገኘዋል። በእነዚህ ድርጊቶች የጸኑ ሰዎች ሁሉ ተስፋዎቹን አይወርሱም። በአዲሱ ምድር ውስጥም ቢሆን እነዚህን አስነዋሪ ድርጊቶች ለማስለመድ የሚሞክር ሰው ቢኖር ፈጥኖ ይጠፋል። የትንሣኤ ተስፋ ወደሌለው ሁለተኛ ሞት ይጣላል።—ኢሳይያስ 65:20
15. ግንባር ቀደም ድል አድራጊዎች የሚሆኑት እነማን ናቸው? የራእይ መጽሐፍ የሚደመደመው በየትኛው ውብ ራእይ ነው?
15 ግንባር ቀደሞቹ ድል አድራጊዎች በጉ ኢየሱስ ክርስቶስና የሙሽራይቱ ወይም የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ክፍል የሆኑት 144,000ዎች ናቸው። ስለዚህ የራእይ መጽሐፍ አንጸባራቂ የሆነውን የአዲሲቱ ኢየሩሳሌምን ትዕይንት በማሳየት ወደ መደምደሚያው መድረሱ በጣም ተገቢ ነው! አሁን ዮሐንስ የመጨረሻውን ራእይ ይገልጽልናል።
[በገጽ 302 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በአዲሱ የምድር ኅብረተሰብ ውስጥ ሰው ሁሉ አስደሳች ሥራና ጥሩ ወዳጆች ይኖሩታል