“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው”
በእነዚህ ሁለት የጥናት ርዕሶች ውስጥ የተብራራው ሐሳብ በ2002/03 በዓለም ዙሪያ በተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በወጣው ወደ ይሖዋ ቅረቡ በተባለው መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ነው።—በገጽ 20 ላይ የሚገኘውን “የነበረብኝን የባዶነት ስሜት አስወግዶልኛል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፣ ያድነንማል፤ ይሖዋ ይህ ነው።”—ኢሳይያስ 25:9 NW
1, 2. (ሀ) ይሖዋ አብርሃምን ምን ብሎ ጠርቶታል? ይህስ ምን ብለን እንድንጠይቅ ሊያነሳሳን ይችላል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት እንደምንችል የሚያሳየው እንዴት ነው?
የሰማይና የምድር ፈጣሪ አብርሃምን ‘ወዳጄ’ በማለት ጠርቶታል። (ኢሳይያስ 41:8) እስቲ አስበው፣ አንድ ተራ የሆነ ሰው የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ወዳጅ መሆን ችሏል! ‘እኔስ ከአምላክ ጋር ይህንን ያህል የቀረበ ዝምድና መመሥረት እችል ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።
2 መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት እንደሚቻል ያረጋግጥልናል። አብርሃም ከአምላክ ጋር እንዲህ ያለ የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት የቻለው ‘በይሖዋ ስላመነ’ ነበር። (ያዕቆብ 2:23) ዛሬም ይሖዋ ‘ወዳጅነቱ ከቅኖች ጋር ነው።’ (ምሳሌ 3:32) መጽሐፍ ቅዱስ በያዕቆብ 4:8 ላይ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በማለት ያሳስበናል። ከዚህ መመልከት እንደሚቻለው እኛ ከእርሱ ጋር ለመወዳጀት የሚያስችሉንን እርምጃዎች ከወሰድን እርሱም ወደ እኛ በመቅረብ የበኩሉን ያደርጋል። ታዲያ ይህ ጥቅስ ኃጢአተኛና ፍጽምና የጎደለን የሰው ልጆች ቅድሚያውን መውሰድ እንዳለብን ይጠቁማልን? በፍጹም። ከይሖዋ ጋር የመወዳጀት መብት ልናገኝ የቻልነው እርሱ አስቀድሞ ሁለት ወሳኝ እርምጃዎችን በመውሰዱ ነው።—መዝሙር 25:14 አ.መ.ት
3. ይሖዋ ከእርሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንድንችል ምን ሁለት እርምጃዎችን ወስዷል?
3 በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ፣ ኢየሱስ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ እንዲሰጥ’ ወደዚህ ምድር ልኮታል። (ማቴዎስ 20:28) ይህ ቤዛዊ መሥዋዕት ወደ አምላክ መቅረብ የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 4:19) አዎን፣ ‘አስቀድሞ የወደደን’ አምላክ እንደመሆኑ ከእርሱ ጋር መወዳጀት የምንችልበትን መሠረት የጣለው እርሱ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ይሖዋ ራሱን ገልጦልናል። ማንኛውም ወዳጅነት ግለሰቡን በትክክል በማወቅ፣ ልዩ የሚያደርጉትን ባሕርያት በማድነቅና ከፍ አድርጎ በመመልከት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ምን ማለት ነው? ይሖዋ የተሰወረና ሊታወቅ የማይችል አምላክ ቢሆን ኖሮ ወደ እርሱ መቅረብ አንችልም ነበር። ሆኖም ይሖዋ ራሱን ከመሸሸግ ይልቅ እንድናውቀው ይጋብዘናል። (ኢሳይያስ 45:19) በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀላሉ ልንረዳው በምንችለው መንገድ ራሱን መግለጡ እርሱ እንደሚወድደን ብቻ ሳይሆን እንድናውቀውና እንደ ሰማያዊ አባታችን አድርገን እንድንወድደው የሚፈልግ አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል።
4. ስለ ይሖዋ ባሕርያት ይበልጥ ባወቅን መጠን ስለ እርሱ ምን ይሰማናል?
4 አንድ ትንሽ ልጅ ወደ አባቱ እየጠቆመ በኩራት ‘አባዬ ያውና’ ብሎ በደስታ እየተፍለቀለቀ ለጓደኞቹ ሲናገር ሰምተህ ታውቃለህ? የአምላክ አገልጋዮችም ስለ ይሖዋ እንደዚህ ብለው ለመናገር በቂ ምክንያት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ሰዎች “እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው” ብለው እንደሚናገሩ አስቀድሞ ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 25:8, 9) ስለ ይሖዋ ባሕርያት ይበልጥ ባወቅን መጠን ወደር የማይገኝለት አባት እንዳለንና ከእርሱ የቀረበ ወዳጅ ማግኘት እንደማንችል ይሰማናል። በእርግጥም፣ የይሖዋን ባሕርያት ማወቃችን ወደ እርሱ እንድንቀርብ የሚገፋፉ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉን እንድንገነዘብ ይረዳናል። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት ስለሆኑት ስለ ኃይሉ፣ ስለ ፍትሑ፣ ስለ ጥበቡና ስለ ፍቅሩ የሚናገረውን እንመልከት። በዚህ ርዕስ ሥር ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ሦስቱን እንመረምራለን።
‘ኃይሉ ታላቅ ነው’
5. “ሁሉን ቻይ” ተብሎ የተጠራው ይሖዋ ብቻ መሆኑ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? እጅግ ታላቅ የሆነ ኃይሉን ምን ለማድረግ ይጠቀምበታል?
5 ይሖዋ “በኃይል ታላቅ ነው።” (ኢዮብ 37:23) ኤርምያስ 10:6 “አቤቱ፣ እንደ አንተ ያለ የለም፤ አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው” በማለት ይናገራል። ይሖዋ ከማንም ፍጥረት ጋር ሊወዳደር የማይችል ገደብ የለሽ ኃይል አለው። በዚህም የተነሳ “ሁሉን ቻይ” ተብሎ የተጠራው እርሱ ብቻ ነው። (ራእይ 15:3 አ.መ.ት ) ይሖዋ እጅግ ታላቅ የሆነ ኃይሉን ለመፍጠር፣ ለማጥፋት፣ ሕዝቦቹን ለመጠበቅ እና ነገሮችን ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ ይጠቀምበታል። ከእነዚህ መካከል ኃይሉን ለመፍጠርና አገልጋዮቹን ለመጠበቅ እንዴት እንደተጠቀመበት እንመልከት።
6, 7. ፀሐይ ምን ያህል ኃይል አላት? ፀሐይ ያላት ኃይል ምን ያስተምረናል?
6 ብዙውን ጊዜ በበጋ ወራት ወደ ውጭ ስትወጣ የፀሐይዋ ሙቀት እንደሚሰማህ የታወቀ ነው። በተዘዋዋሪ መንገድ እየተሰማህ ያለው ይሖዋ ለመፍጠር የተጠቀመበት ኃይል ነው። ፀሐይ ምን ያህል ኃይል አላት? መካከለኛው የፀሐይ ክፍል 15 ሚልዮን ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚያክል ሙቀት አለው። ከፀሐይ መካከለኛ ክፍል ላይ ከምስር የሚያንስ ቅራፊ ወስደን ወደ ምድራችን ማምጣት ብንችል ወደዚች ቅንጣት 140 ኪሎ ሜትር ከሚያህል ርቀት በላይ መቅረብ አይቻልም! ፀሐይ በየሴኮንዱ ከብዙ መቶ ሚልዮን የኑክሌር ቦምብ ፍንዳታ ጋር የሚመጣጠን ኃይል ታመነጫለች። ያም ሆኖ ምድራችን ከፍተኛ ኃይል ከምታመነጨው ከዚህች የኑክሌር ምድጃ በትክክለኛው ርቀት ላይ ትገኛለች። ፀሐይ ወደ ምድር በጣም ብትቀርብ ኖሮ በምድር ላይ ያለው ውኃ ተንኖ ያልቅ ነበር፤ በአንጻሩ ደግሞ በጣም ብትርቅ ውኃው ወደ በረዶነት ይቀየር ነበር። ሁለቱም ክስተቶች ምድርን ሕይወት አልባ ያደርጓታል።
7 ሰዎች ሕልውናቸው በፀሐይ ላይ የተመካ ቢሆንም ፀሐይ ስለምትሰጠው ጥቅም የሚያስቡት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። በመሆኑም ከፀሐይ ሊያገኙ የሚችሉትን ትምህርት ሳያገኙ ይቀራሉ። መዝሙር 74:16 “አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ” በማለት ስለ ይሖዋ ይናገራል። አዎን፣ ፀሐይ “ሰማይንና ምድርን” የፈጠረውን የይሖዋን ክብር ትናገራለች። (መዝሙር 146:6) ሆኖም ይሖዋ እጅግ ከፍተኛ ኃይል እንዳለው ትምህርት ሊሰጡን ከሚችሉት በርካታ ፍጥረታት መካከል ፀሐይ አንዷ ብቻ ናት። ይሖዋ ለመፍጠር ስለሚጠቀምበት ኃይል ይበልጥ እያወቅን በሄድን መጠን ለእርሱ ያለን አክብሮትም የዚያኑ ያህል እያደገ ይሄዳል።
8, 9. (ሀ) ይሖዋ አምላኪዎቹን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ፈቃደኛ መሆኑን የሚያሳየን የትኛው ምሳሌያዊ መግለጫ ነው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት እረኞች በጎቻቸውን የሚጠብቁት እንዴት ነበር? ይህስ ስለ ታላቁ እረኛችን ምን ያስተምረናል?
8 በተጨማሪም ይሖዋ አገልጋዮቹን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ከፍተኛ ኃይሉን ይጠቀማል። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሚያደርገውን ጥበቃ መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው በሆኑና ልብን በሚነኩ ምሳሌዎች ይገልጻል። ኢሳይያስ 40:11ን እንደ ምሳሌ እንመልከት። እዚህ ጥቅስ ላይ ይሖዋ ራሱን እንደ አንድ እረኛ ሕዝቡን ደግሞ እንደ በጎች አድርጎ ገልጿል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፣ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።” በዚህ ጥቅስ ላይ የሰፈረውን ምሳሌያዊ መግለጫ በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ?
9 የበጎችን ያህል እንክብካቤ የሚያሻቸው እንስሶች የሉም ብሎ መናገር ይቻላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ እረኞች በጎቻቸውን ከተኩላዎች፣ ከድቦችና ከአንበሶች በድፍረት መጠበቅ ነበረባቸው። (1 ሳሙኤል 17:34-36፤ ዮሐንስ 10:10-13) ሆኖም በጎች በርኅራኄ መያዝ የሚያስፈልጋቸውም ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት በግ ከመንጋው ተነጥላ በምትወልድበት ጊዜ እረኛው ለግልገሏ እንክብካቤ የሚያደርገው እንዴት ነው? ግልገሏን በሸማው ሸፍኖ ምናልባትም ለብዙ ቀናት “በብብቱ” ይሸከማታል። ጠቦቷ ወይም ትንሿ ግልገል እረኛው እንዲያቅፋት የምታደርገው እንዴት ነው? ግልገሏ ወደ እረኛው ተጠግታ እግሩን ትታከከዋለች። ሆኖም ጎንበስ ብሎ ግልገሏን በማንሳት በብብቱ ውስጥ ማቀፍ ያለበት እረኛው ነው። ታላቁ እረኛችን አገልጋዮቹን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ፈቃደኛ መሆኑን የሚገልጽ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌያዊ መግለጫ ነው!
10. በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ምን ዓይነት ጥበቃ ያደርግልናል? እንደዚህ ያለው ጥበቃ በተለይ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
10 ይሖዋ እኛን እንደሚጠብቀን ቃል በመግባት ብቻ አልተወሰነም። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋ ‘የሚያመልኩትን ከፈተና የማዳን’ ችሎታ እንዳለው ተአምራዊ በሆነ መንገድ አሳይቷል። (2 ጴጥሮስ 2:9) ዛሬስ? ይሖዋ ምንም ዓይነት መከራ እንዳይደርስብን ለማድረግ ኃይሉን ይጠቀማል ብለን አንጠብቅም። ሆኖም ከዚያ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል። አፍቃሪው አምላካችን መከራዎችን መቋቋም እንድንችልና ከእርሱ ጋር የመሠረትነው ዝምድና እንዳይበላሽ ድጋፍ በመስጠት መንፈሳዊ አደጋ ላይ እንዳንወድቅ ይጠብቀናል። ለምሳሌ ያህል ሉቃስ 11:13 እንዲህ ይላል:- “እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” ይህ ኃይል የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና ወይም ችግር ለመቋቋም የሚያስፈልጉንን ባሕርያት እንድናዳብር ይረዳናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ይሖዋ ለጥቂት ዓመታት ሳይሆን ለዘላለም ለመኖር የሚያስፈልጉንን ዝግጅቶች አድርጎልናል። ይህንን ተስፋ በአእምሯችን በመያዝ በዚህ ሥርዓት የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ችግር ‘ቀላልና ጊዜያዊ’ አድርገን እንመለከተዋለን። (2 ቆሮንቶስ 4:17) ለእኛ ጥቅም ሲል ኃይሉን እንዲህ በመሰለ ፍቅራዊ መንገድ ወደሚጠቀም አምላክ ለመቅረብ አንገፋፋም?
‘ይሖዋ ፍትሕን ይወድዳል’
11, 12. (ሀ) የይሖዋ ፍትሕ ወደ እርሱ እንድንቀርብ የሚገፋፋ ባሕርይ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ዳዊት የይሖዋን ፍትሕ በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሷል? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት እነዚህ ቃላት የሚያጽናኑን እንዴት ነው?
11 ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በጽድቅና በትክክል እንዲሁም ያለ አድልዎ ነው። መለኮታዊ ፍትሕ ከአምላክ እንድንርቅ የሚያደርግ ጨካኝና ርኅራኄ የጐደለው ባሕርይ ሳይሆን ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚያደርግ ማራኪ ባሕርይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አስደሳች ስለሆነው ስለዚህ ባሕርይ በግልጽ ይናገራል። ይሖዋ ፍትሑን ያሳየባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።
12 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ፍትሑ ለአገልጋዮቹ ታማኝ እንዲሆን ይገፋፋዋል። መዝሙራዊው ዳዊት ይህንን የይሖዋ ፍትሕ ገጽታ በራሱ ሕይወት ተመልክቷል። ዳዊት ከራሱ ተሞክሮ በመነሳትና አምላክ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ በመመልከት ምን መደምደሚያ ላይ ደረሰ? እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እግዚአብሔር ፍርድን [“ፍትሕን፣” አ.መ.ት ] ይወድዳልና፣ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና፤ ለዘላለም ይጠብቃቸዋል።” (መዝሙር 37:28) ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው! አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን ለአንዲት ሴኮንድ እንኳን አይጥላቸውም። በዚህም የተነሳ በእርሱ ወዳጅነትና ፍቅራዊ እንክብካቤ ላይ ልንታመን እንችላለን። ፍትሑ ለዚህ ዋስትና ይሰጠናል!—ምሳሌ 2:7, 8 አ.መ.ት
13. ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ ለተቸገሩ ሰዎች እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው?
13 በሁለተኛ ደረጃ፣ ይሖዋ ፍትሐዊ በመሆኑ በመከራ ሥር የሚገኙ ሰዎች ያለባቸውን ችግር ይረዳል። አምላክ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች እንደሚያስብ ለእስራኤላውያን ከሰጣቸው ሕግ ማየት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆችና ባል የሞተባቸው ሴቶች ጥበቃ እንዲያገኙ የሚያስችል ዝግጅት በሕጉ ውስጥ ተካትቷል። (ዘዳግም 24:17-21) ይሖዋ እነዚህ ቤተሰቦች ሊገጥማቸው የሚችለውን የኑሮ ችግር ስለሚያውቅ እርሱ ራሱ ፈራጃቸውና ጠባቂያቸው ሆኗል። (ዘዳግም 10:17, 18) እነዚህ ረዳት የሌላቸው ሴቶችና ልጆች ግፍ ተፈጽሞባቸው ወደ ይሖዋ ቢጮሁ ጩኸታቸውን ሰምቶ እርምጃ እንደሚወስድ እስራኤላውያንን አስጠንቅቋቸዋል። በዘጸአት 22:22-24 ላይ “ቁጣዬም ይጸናባችኋል” ብሏል። ቁጣ ከአምላክ ዋነኛ ባሕርያት አንዱ ባይሆንም በተለይ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ ግፍ ሲፈጸም ይሖዋ የጽድቅ ቁጣ ይቆጣል።—መዝሙር 103:6
14. ይሖዋ የማያዳላ አምላክ መሆኑን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
14 በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስ በዘዳግም 10:17 ላይ ይሖዋ “በፍርድ የማያደላ፣ መማለጃም የማይቀበል” አምላክ እንደሆነ ይናገራል። ይሖዋ ሥልጣን ወይም ተሰሚነት እንዳላቸው በርካታ ሰዎች በቁሳዊ ሃብት ወይም በውጫዊ መልክ አይደለልም። በስሜት ተገፋፍቶ ለአንዱ ወገን አያደላም ወይም አንዱን ከሌላው አስበልጦ አያይም። ይሖዋ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ በማድረግ የእርሱ እውነተኛ አምላኪ የመሆንን መብት የሰጠው ለጥቂት የተመረጡ ሰዎች ብቻ አለመሆኑ እንደማያዳላ የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። ከዚህ ይልቅ ሥራ 10:34, 35 እንደሚናገረው ‘እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያደላም፤ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ ነው።’ አንድ ሰው በኅብረተሰቡ ውስጥ ምንም ዓይነት ቦታ ወይም የቆዳ ቀለም ይኑረው አሊያም የየትኛውም አገር ዜጋ ይሁን ይህ ተስፋ ለሁሉም ሰው ተዘርግቷል። ከዚህ የሚበልጥ የፍትሕ መግለጫ ሊኖር ይችላል? በእርግጥም ስለ ይሖዋ ፍትሕ የተሻለ ግንዛቤ ማዳበር ወደ እርሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ያደርገናል!
‘የእግዚአብሔር ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’
15. ጥበብ ምንድን ነው? ይሖዋ ይህንን ባህርይ የሚያሳየውስ እንዴት ነው?
15 ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 11:33 ላይ “የእግዚአብሔር . . . ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው” በማለት ተናግሯል። ጥልቅ ስለሆነው የይሖዋ ጥበብ ስናስብ በአድናቆት መሞላታችን የማይቀር ነው። ይሁን እንጂ ጥበብ ሲባል ምን ማለት ነው? ጥበብ አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ እውቀትንና ማስተዋልን በአንድ ላይ የመጠቀም ችሎታ ነው። ይሖዋ ሰፊ የእውቀት ክምችቱና ጥልቅ ማስተዋሉ ምንጊዜም ከሁሉ የተሻለውን ውሳኔ ለማድረግ እንዲሁም ውሳኔዎቹን በተሻለ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ያስችለዋል።
16, 17. የይሖዋ ፍጥረታት ጥበቡ ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳዩት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
16 የይሖዋ ጥበብ ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎች የትኞቹ ናቸው? መዝሙር 104:24 “አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፣ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች” በማለት ይናገራል። የይሖዋን የእጅ ሥራዎች ይበልጥ እያወቅን በሄድን መጠን ስለ ጥበቡ ያለን አድናቆትም የዚያኑ ያህል እያደገ ይሄዳል። ሳይንቲስቶች እንኳን ሳይቀሩ የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በማጥናት ይህ ነው የማይባል እውቀት አካብተዋል! ሌላው ቀርቶ ባዮሚሜቲክስ የሚባል የምህንድስና ዘርፍ ያለ ሲሆን በዚህ ሞያ የተሰማሩ ሰዎች የተፈጥሮ ንድፎችን አስመስለው ለመሥራት ይሞክራሉ።
17 ለምሳሌ ያህል፣ የሸረሪት ድር ስትመለከት በአሠራሩ ትደነቅ ይሆናል። በእርግጥም ንድፉ የሚያስደንቅ ነው። በቀላሉ የሚበጠሱ የሚመስሉ አንዳንድ የሸረሪት ድሮች ተመጣጣኝ መጠን ካለው ብረትና ጥይት የማይበሳው ልብስ ለመሥራት ከሚያገለግል ክር የበለጠ ጥንካሬ አላቸው። ይህ ምን ማለት ነው? የሸረሪት ድር ተገምዶ ዓሣ ለማጥመድ የሚያገለግል መረብ የሚያህል መጠን እንዲኖረው አደረግን እንበል። ይህን ያህል መጠን ያለው ድር በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ በከፍተኛ ፍጥነት እየበረረ ያለን አንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውሮፕላን ሊያቆም ይችላል! በእርግጥም ይሖዋ ሁሉን ነገር “በጥበብ” አዘጋጅቷል።
18. ይሖዋ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ በሰዎች መጠቀሙ ጥበቡን የሚያሳየው እንዴት ነው?
18 ከሁሉም የሚበልጠውን የይሖዋን ጥበብ የምናገኘው ግን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያለበት ምክር የተሻለ ሕይወት የምንመራበትን መንገድ ያስተምረናል። (ኢሳይያስ 48:17) ሆኖም አቻ የማይገኝለት የይሖዋ ጥበብ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ በተጠቀመበት መንገድ ላይም ታይቷል። እንዴት? ጥበበኛ የሆነው ይሖዋ ቃሉን በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ ለማድረግ ሰዎችን ተጠቅሟል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቃሉን ለማስጻፍ በመላእክት ተጠቅሞ ቢሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ የአሁኑን ያህል ማራኪ ይሆን ነበር? እርግጥ ነው፣ መላእክት ይሖዋን እነርሱ ካላቸው ከፍተኛ የማገናዘብ ችሎታ አንጻር ሊገልጹትና ለእርሱ ያላቸውን ስሜት ሊጽፉ ይችሉ ነበር። ሆኖም ከእኛ የበለጠ እውቀት፣ ተሞክሮና ጥንካሬ ያላቸው ፍጹም መንፈሳዊ ፍጥረታት ያሰፈሩትን ሐሳብ መረዳት እንችል ነበር?—ዕብራውያን 2:6, 7
19. መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መጻፉ ሰብዓዊ ስሜት የተንጸባረቀበትና ማራኪ እንዲሆን እንዳደረገው የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው?
19 መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መጻፉ ሰብዓዊ ስሜት የተንጸባረቀበትና ማራኪ እንዲሆን አድርጎታል። ጸሐፊዎቹ የእኛው ዓይነት ስሜት ያላቸው ሰዎች ነበሩ። ፍጹማን ባለመሆናቸው እንደኛው የተለያዩ መከራዎችንና ተጽዕኖዎችን አሳልፈዋል። እንዲያውም ስለ ራሳቸው ስሜትና ከገጠሟቸው ችግሮች ጋር ስላደረጉት ትግል የጻፉበትም ጊዜ አለ። (2 ቆሮንቶስ 12:7-10) በመሆኑም መላእክት ቢሆኑ ኖሮ ሊገልጿቸው የማይችሏቸውን ስሜቶች አስፍረዋል። ለምሳሌ ያህል በመዝሙር 51 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የዳዊት ቃላት እንመልከት። በመዝሙሩ አናት ላይ የሰፈረው ሐሳብ ዳዊት ይህን መዝሙር ያቀናበረው ከባድ ኃጢአት ከሠራ በኋላ እንደሆነ ይገልጻል። የተሰማውን ጥልቅ የሐዘን ስሜት በመግለጽና አምላክ ይቅር እንዲለው በመማጸን የልቡን ግልጽልጽ አድርጎ ተናግሯል። ቁጥር 2 እና 3 እንዲህ ይላል:- “ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፣ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፣ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና።” ቁጥር 5 ላይ “እነሆ፣ በዓመፃ ተፀነስሁ፣ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ” እንዳለ ልብ በል። በተጨማሪም ቁጥር 17 “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፣ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” ይላል። ይህን ስታነብ ጸሐፊው ምን ያህል እንዳዘነ አልተሰማህም? ፍጽምና ከጎደላቸው ሰዎች ሌላ እንዲህ ያለውን ስሜት ማን ሊገልጸው ይችላል?
20, 21. (ሀ) አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ የተጠቀመው በሰዎች ቢሆንም መጽሐፉ የይሖዋን ጥበብ ይዟል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን ይብራራል?
20 ይሖዋ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን በመጠቀም ‘በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ’ ሆኖም ሰብዓዊ ስሜት የተንጸባረቀበት መጽሐፍ ሰጥቶናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እርግጥ ነው፣ እነዚህ ጸሐፊዎች የጻፉት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ነው። በዚህም የተነሳ የጻፉት የራሳቸውን ሳይሆን የይሖዋን ጥበብ ነው። ይህ ጥበብ ደግሞ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት ነው። ይሖዋ ከእኛ የላቀ ጥበብ እንዳለው ስለሚያውቅ የሚከተለውን ፍቅራዊ ማሳሰቢያ ሰጥቶናል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።” (ምሳሌ 3:5, 6) ይህን ጥበብ የተሞላበት ምክር በመከተል ከፍተኛ ጥበብ ወዳለው አምላክ ልንቀርብ እንችላለን።
21 ከይሖዋ ባሕርያት መካከል ይበልጥ ተወዳጅና ማራኪ የሆነው ፍቅር ነው። ይሖዋ ፍቅሩን እንዴት እንዳሳየ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይብራራል።
ታስታውሳለህን?
• ይሖዋ ከእርሱ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት እንድንችል ምን እርምጃዎች ወስዷል?
• ይሖዋ ኃይሉን ነገሮችን ለመፍጠርና ሕዝቦቹን ለመጠበቅ እንደተጠቀመበት የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
• የይሖዋ ፍትሕ የታየው በምን መንገዶች ነው?
• የይሖዋ ጥበብ በፍጥረት ሥራዎቹና መጽሐፍ ቅዱስን ባስጻፈበት መንገድ የተንጸባረቀው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጠቦቱን በብብቱ ሥር አስገብቶ እንደሚያቅፍ እረኛ ይሖዋም በጎቹን በርኅራኄ ይይዛቸዋል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት መንገድ የይሖዋን ጥበብ በግልጽ ያሳያል