ምዕራፍ 16
‘ፍትሕን በማድረግ’ ከአምላክ ጋር መሄድ
1-3. (ሀ) ይሖዋ ባለውለታችን ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ሕይወታችንን የታደገው አፍቃሪ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ነገር ምንድን ነው?
እየሰመጠች ባለች መርከብ ላይ እንዳለህ አድርገህ አስብ። በሕይወት የመትረፍ ተስፋህ ተሟጥጦ ባለበት ሰዓት አንድ የነፍስ አድን ሠራተኛ ደርሶ አዳነህ እንበል። ከመርከቧ አውጥቶ ወደ ባሕሩ ዳርቻ እየወሰደህ ሳለ “አይዞህ፣ ተርፈሃል” ሲልህ ምን ያህል እንደምትደሰት ልትገምት ትችላለህ። ይህ ሰው ትልቅ ውለታ እንደዋለልህ አይሰማህም? እሱ ባይደርስልህ ኖሮ በሕይወት አትተርፍም ነበር።
2 ይህ ምሳሌ ይሖዋ ያደረገልንን ነገር በመጠኑም ቢሆን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ይሖዋ ትልቅ ባለውለታችን እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ቤዛ በመክፈል ከኃጢአትና ከሞት መዳፍ እንድንላቀቅ ያደረገን እሱ ነው። በዚህ ውድ መሥዋዕት እስካመንን ድረስ ኃጢአታችን ይቅር እንደሚባልልንና የወደፊት ሕይወታችን ዋስትና እንደሚኖረው ስለምናውቅ ምንም ዓይነት ስጋት አያድርብንም። (1 ዮሐንስ 1:7፤ 4:9) ምዕራፍ 14 ላይ እንዳየነው ይሖዋ ፍቅሩንና ፍትሑን ከሁሉ በላቀ መንገድ የገለጸው በዚህ የቤዛ ዝግጅት ነው። ታዲያ እኛ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?
3 ሕይወታችንን የታደገው አፍቃሪ አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ መመርመራችን ተገቢ ነው። ይሖዋ በነቢዩ ሚክያስ በኩል እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሰው ሆይ፣ መልካም የሆነውን ነግሮሃል። ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን እንድታደርግ፣ ታማኝነትን እንድትወድና ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ ብቻ ነው!” (ሚክያስ 6:8) ይሖዋ ‘ፍትሕን እንድናደርግ’ እንደሚፈልግ ልብ በል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
‘እውነተኛውን ጽድቅ’ መከታተል
4. ይሖዋ በጽድቅ መሥፈርቶቹ እንድንመራ እንደሚፈልግ እንዴት እናውቃለን?
4 ይሖዋ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ እሱ ያወጣቸውን መሥፈርቶች እንድንከተል ይፈልጋል። ፍትሐዊና ጻድቅ በሆኑት በእነዚህ መሥፈርቶች የምንመራ ከሆነ ፍትሕንና ጽድቅን እየተከታተልን ነው ማለት ነው። ኢሳይያስ 1:17 “መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን ፈልጉ” ይላል። የአምላክ ቃል “ጽድቅን ፈልጉ” ሲል ያሳስበናል። (ሶፎንያስ 2:3) በተጨማሪም “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅ . . . ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል” በማለት አጥብቆ ይመክረናል። (ኤፌሶን 4:24 ) ዓመፅ፣ ርኩሰትና የፆታ ብልግና ቅድስናን የሚጻረሩ ስለሆኑ እውነተኛ ጽድቅ ወይም እውነተኛ ፍትሕ እንዲህ ካሉት ነገሮች ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ አይኖረውም።—መዝሙር 11:5፤ ኤፌሶን 5:3-5
5, 6. (ሀ) ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መከተል ሸክም የማይሆንብን ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅን መከታተል ቀጣይ ሂደት እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?
5 ይሖዋ ያወጣቸውን የጽድቅ መሥፈርቶች መከተል ሸክም ነው? በፍጹም። ከልባችን ይሖዋን የምንወድ ከሆነ መሥፈርቶቹን መከተል ሸክም አይሆንብንም። ግሩም ባሕርያት ያሉትን አምላካችንን ስለምንወደው እሱን በሚያስደስት መንገድ ለመመላለስ እንጥራለን። (1 ዮሐንስ 5:3) ይሖዋ “የጽድቅ ሥራዎችን ይወዳል።” (መዝሙር 11:7) ስለዚህ መለኮታዊውን ፍትሕ ወይም ጽድቅ መከተል የምንፈልግ ከሆነ ይሖዋ የሚወደውን መውደድ፣ የሚጠላውን ደግሞ መጥላት ይኖርብናል።—መዝሙር 97:10
6 ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ጽድቅን መከታተል ሊከብዳቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። በኃጢአት ልማዶች የተተበተበውን አሮጌውን ስብዕና ገፈን መጣልና አዲሱን ስብዕና መልበስ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ ስብዕና በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት ‘እየታደሰ እንደሚሄድ’ ይገልጻል። (ቆላስይስ 3:9, 10) እዚህ ላይ የገባው “እየታደሰ የሚሄደው” የሚለው አገላለጽ አዲሱን ስብዕና የመልበሱ ሂደት ቀጣይነት እንዳለውና ትጋት የተሞላበት ጥረት እንደሚጠይቅ ያመለክታል። ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የቱንም ያህል ብንጥር በወረስነው ኃጢአት ምክንያት በሐሳብ፣ በቃል ወይም በድርጊት የምንሰናከልባቸው ጊዜያት አሉ።—ሮም 7:14-20፤ ያዕቆብ 3:2
7. ጽድቅን ለመከታተል በምናደርገው ጥረት የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?
7 ጽድቅን ለመከታተል በምናደርገው ጥረት የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል? እርግጥ ነው፣ ኃጢአትን አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። በሌላ በኩል ግን በምንሠራቸው ስህተቶች የተነሳ ይሖዋን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆንን ተሰምቶን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ሩኅሩኅ የሆነው አምላካችን ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ሰዎች ሞገሱን መልሰው ማግኘት የሚችሉበትን ዝግጅት አድርጓል። ሐዋርያው ዮሐንስ “እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ኃጢአት እንዳትሠሩ ነው” ካለ በኋላ የተናገረው ሐሳብ ያጽናናናል። “[በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት] ማንም ኃጢአት ቢሠራ ግን በአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብሏል። (1 ዮሐንስ 2:1) አዎን፣ ኃጢአት የወረስን ብንሆንም እንኳ ይሖዋ በፊቱ ሞገስ አግኝተን እንድናገለግለው ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። ይህ እሱን ለማስደሰት የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ አይገፋፋንም?
ምሥራቹና መለኮታዊ ፍትሕ
8, 9. የምሥራቹ መታወጅ የይሖዋን ፍትሕ የሚያሳየው እንዴት ነው?
8 የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች በመስበኩ ሥራ በትጋት በመካፈል ፍትሕን ማድረግ አልፎ ተርፎም መለኮታዊውን ፍትሕ መኮረጅ እንችላለን። በይሖዋ ፍትሕና በምሥራቹ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?
9 ይሖዋ በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ይህን ክፉ ሥርዓት አያጠፋም። ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን የሚፈጸመውን ሁኔታ አስመልክቶ ትንቢት ሲናገር “አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት” ብሏል። (ማርቆስ 13:10፤ ማቴዎስ 24:3) “አስቀድሞ” የሚለው አነጋገር ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ ከተሰበከ በኋላ የሚከናወኑ ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ያመለክታል። በትንቢት የተነገረው ታላቁ መከራ ከእነዚህ ክንውኖች አንዱ ሲሆን ይህም በክፉዎች ላይ ጥፋት የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ ጽድቅ ለሚሰፍንበት አዲስ ዓለም መንገድ የሚጠርግ ይሆናል። (ማቴዎስ 24:14, 21, 22) ይሖዋ በክፉዎች ላይ እርምጃ መውሰዱ ፍትሐዊ አይደለም ብሎ ሊከራከር የሚችል አይኖርም። አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ እንዲነገር በማድረግ እነዚህ ሰዎች ከክፉ መንገዳቸው ተመልሰው ከጥፋት መትረፍ እንዲችሉ በቂ ዕድል ሰጥቷቸዋል።—ዮናስ 3:1-10
10, 11. ምሥራቹን መስበካችን መለኮታዊ ፍትሕን የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?
10 ምሥራቹን መስበካችን መለኮታዊ ፍትሕን የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሌሎች እንዲድኑ ለመርዳት የተቻለንን ጥረት ማድረጋችን ትክክለኛው እርምጃ ነው። እየሰመጠች ካለች መርከብ ላይ በሕይወት ስለመትረፍ የሚናገረውን ምሳሌ መለስ ብለን እንመልከት። ሕይወት አድን ጀልባ ላይ ከወጣህ በኋላ ገና ከውኃ ውስጥ ያልወጡትን ሌሎች ሰዎች ለመርዳት ጥረት እንደምታደርግ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም በዚህ ክፉ ዓለም “ባሕር” ውስጥ ላለመስመጥ እየተፍጨረጨሩ ያሉትን ሰዎች የመርዳት ግዴታ አለብን። እርግጥ ነው፣ ብዙዎች የምንነግራቸውን መልእክት አይቀበሉም። ይሁን እንጂ ይሖዋ እስከታገሠ ድረስ ‘ለንስሐ እንዲበቁ’ እና መዳን እንዲችሉ አጋጣሚ የመስጠት ኃላፊነት አለብን።—2 ጴጥሮስ 3:9
11 ምንም ሳናዳላ ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን መስበካችን ፍትሕ የምናሳይበት ሌላው መንገድ ነው። “አምላክ እንደማያዳላ . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት [እንዳለው]” አስታውስ። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ መኮረጅ ከፈለግን በሰዎች ላይ ለመፍረድ መቸኮል የለብንም። ከዚህ ይልቅ ዘራቸው፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ ወይም የኑሮ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ለሁሉም ምሥራቹን መስበክ ይኖርብናል። በዚህ መንገድ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን ሰምተው እርምጃ እንዲወስዱ አጋጣሚ እንከፍትላቸዋለን።—ሮም 10:11-13
ሌሎችን የምንይዝበት መንገድ
12, 13. (ሀ) በሌሎች ላይ ለመፍረድ መቸኮል የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ “መፍረዳችሁን ተዉ” እና “አትኮንኑ” ሲል የሰጠው ምክር ምን ትርጉም አለው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
12 በተጨማሪም ይሖዋ እኛን በሚይዝበት መንገድ ሌሎችን በመያዝ ፍትሕን ማንጸባረቅ እንችላለን። ይሁንና ብዙውን ጊዜ ሰዎችን በጥርጣሬ ዓይን በማየትና ስህተቶቻቸውን በመለቃቀም በእነሱ ላይ መፍረድ ይቀናናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ እያንዳንዱን ዝንባሌያችንን በጥርጣሬ ዓይን የሚመለከትና ስህተቶቻችንን የማያልፍ ቢሆን ምን ይሰማን ነበር? ደግነቱ ይሖዋ እንዲህ አያደርግም። መዝሙራዊው “ያህ ሆይ፣ አንተ ስህተትን የምትከታተል ቢሆን ኖሮ፣ ይሖዋ ሆይ፣ ማን ሊቆም ይችል ነበር?” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 130:3) ፍትሐዊና መሐሪ የሆነው አምላካችን አንድ በአንድ ስህተታችንን የማይከታተል በመሆኑ አመስጋኞች ልንሆን አይገባንም? (መዝሙር 103:8-10) ታዲያ እኛስ ሌሎችን እንዴት ልንይዝ ይገባል?
13 የአምላክ ፍትሕ ምሕረት የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ከተገነዘብን በረባ ባልረባው ሰውን ለመተቸት ወይም በማይመለከቱን ጉዳዮች ገብተን በሌሎች ላይ ለመፍረድ አንቸኩልም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ መፍረዳችሁን ተዉ” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 7:1 የግርጌ ማስታወሻ) ሉቃስ እንደዘገበው ደግሞ ኢየሱስ “ሌሎችን አትኮንኑ፤ እናንተም ፈጽሞ አትኮነኑም” ሲል አክሎ ተናግሯል።a (ሉቃስ 6:37) ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መናገሩ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በሌሎች ላይ መፍረድ እንደሚቀናቸው መገንዘቡን ያሳያል። የኢየሱስ አድማጮች በሌሎች ላይ የመፍረድ ልማድ ከነበራቸው ይህን ልማዳቸውን እርግፍ አድርገው መተው ይጠበቅባቸው ነበር።
14. በሌሎች ላይ ‘መፍረዳችንን መተው’ ያለብን ለምንድን ነው?
14 በሌሎች ላይ ‘መፍረዳችንን መተው’ ያለብን ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ እኛ እንዲህ የማድረግ ሥልጣን የለንም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሕግ የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ [ይሖዋ] ብቻ ነው” ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። በመሆኑም “በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?” የሚል ቀጥተኛ ጥያቄ አቅርቧል። (ያዕቆብ 4:12፤ ሮም 14:1-4) በተጨማሪም በወረስነው ኃጢአት ሳቢያ የተዛባ ፍርድ ወደ መስጠት ልናደላ እንችላለን። መሠረተ ቢስ ጥላቻ፣ ቅናት፣ ራስን ከፍ አድርጎ መመልከትና እነዚህን የመሳሰሉ ዝንባሌዎች ለሌሎች ሰዎች ያለንን አመለካከት ሊያዛቡብን ይችላሉ። ሌሎች ጉድለቶችም እንዳሉብን ማሰባችን የሰዎችን ስህተት ከመለቃቀም እንድንታቀብ ሊያደርገን ይገባል። የሰዎችን ልብ ማንበብም ሆነ ያሉበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። እንግዲያው የእምነት አጋሮቻችን የሚያደርጉትን ነገር በመጥፎ የምንተረጉም ወይም አምላክን ለማገልገል የሚያደርጉትን ጥረት የምንተች እኛ ማን ነን? የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ጉድለት ሳይሆን መልካም ጎናቸውን በመመልከት ይሖዋን ለመኮረጅ ጥረት ማድረጋችን ምንኛ የተሻለ ነው!
15. በአምላክ ሕዝቦች መካከል ምን ነገሮች ቦታ የላቸውም? ለምንስ?
15 የቤተሰባችንን አባላት ስለምንይዝበት መንገድስ ምን ማለት ይቻላል? በዛሬው ጊዜ፣ ቤት ሰላም የሰፈነበት ሊሆን ሲገባው አንዳንዴ ከሁሉ የከፋ ትችትና ነቀፋ የሚሰነዘርበት ቦታ መሆኑ ያሳዝናል። በቤተሰባቸው አባላት ላይ የስድብ ወይም የዱላ ናዳ የሚያወርዱ ባሎች፣ ሚስቶች ወይም ወላጆች ማየት የተለመደ ነው። ሆኖም ስድብ፣ አሽሙር እንዲሁም ሌላ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ቦታ የላቸውም። (ኤፌሶን 4:29, 31፤ 5:33፤ 6:4) ኢየሱስ “መፍረዳችሁን ተዉ” እና “አትኮንኑ” ሲል የሰጠው ምክር በቤተሰብ ውስጥም እንደሚሠራ መዘንጋት አይኖርብንም። ፍትሕን ማንጸባረቅ ይሖዋ እኛን በሚይዘን መንገድ ሌሎችን መያዝንም እንደሚጨምር አስታውስ። ይሖዋ ጨካኝና ምሕረት የለሽ አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለሚወዱት ሰዎች “ከአንጀት የሚራራ” አምላክ ነው። (ያዕቆብ 5:11 የግርጌ ማስታወሻ) ልንኮርጀው የሚገባ ግሩም ምሳሌያችን ነው!
“ፍትሕ ለማስፈን” የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች
16, 17. (ሀ) ይሖዋ ሽማግሌዎች ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል? (ለ) ኃጢአት የሠራ ሰው ከልቡ ንስሐ ካልገባ ምን መደረግ ይኖርበታል? ለምንስ?
16 ሁላችንም ፍትሕን የማንጸባረቅ ኃላፊነት ያለብን ቢሆንም በተለይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ከሁሉ የላቀ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ኢሳይያስ ‘መኳንንትን’ ወይም ሽማግሌዎችን በተመለከተ የተናገረውን ትንቢት ተመልከት፦ “እነሆ፣ ንጉሥ ለጽድቅ ይነግሣል፤ መኳንንትም ፍትሕ ለማስፈን ይገዛሉ።” (ኢሳይያስ 32:1) አዎን፣ ይሖዋ ሽማግሌዎች በፍትሕ እንዲያገለግሉ ይፈልጋል። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
17 እነዚህ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች ፍትሕ ወይም ጽድቅ እንዲሰፍን የጉባኤውን ንጽሕና መጠበቅ እንዳለባቸው በሚገባ ያውቃሉ። ሽማግሌዎች አንዳንድ ከባድ ኃጢአቶችን በመመርመር ፍርድ የሚሰጡባቸው ጊዜያት አሉ። በዚህ ጊዜ፣ መለኮታዊ ፍትሕ በተቻለ መጠን ምሕረት እንዲያሳዩ እንደሚጠይቅባቸው ይገነዘባሉ። በመሆኑም ኃጢአት የሠራው ሰው ንስሐ እንዲገባ ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። ሆኖም ግለሰቡ እርዳታ ተደርጎለትም ከልቡ ንስሐ ሳይገባ ቢቀርስ? የይሖዋ ቃል “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት” በማለት ፍጹም ፍትሐዊ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድበት ያዛል። በመሆኑም ሽማግሌዎች፣ ግለሰቡ ከጉባኤው እንዲወገድ ይወስናሉ። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13፤ 2 ዮሐንስ 9-11) ሽማግሌዎች እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ሲወስዱ የሚያዝኑ ቢሆንም የጉባኤውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕና ለመጠበቅ ይህን ማድረጉ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። በዚህ ጊዜም እንኳ ቢሆን ግለሰቡ አንድ ቀን ወደ ልቡ ተመልሶ ከጉባኤው ጋር እንደሚቀላቀል ተስፋ ያደርጋሉ።—ሉቃስ 15:17, 18
18. ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር በሚሰጡበት ጊዜ ምን ማስታወስ አለባቸው?
18 ፍትሕ ለማስፈን የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር መስጠትም ይጠበቅባቸዋል። እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች የሌሎችን ስህተት አይለቃቅሙም። በተጨማሪም በትንሹም በትልቁም እርማት ለመስጠት አይሞክሩም። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን “ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና [ሊከተል]” ይችላል። ሽማግሌዎች፣ መለኮታዊ ፍትሕ ጨካኝ ወይም ርኅራኄ የጎደለው እንዳልሆነ ማስታወሳቸው ግለሰቡን “በገርነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት [እንዲያደርጉ]” ይገፋፋቸዋል። (ገላትያ 6:1) በመሆኑም ሽማግሌዎች ስህተት የሠራውን ሰው ከመዝለፍ ወይም ሻካራ ቃል ከመናገር ይቆጠባሉ። ከዚህ ይልቅ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የሚሰጥ ምክር ግለሰቡን ሊያበረታታው ይችላል። ሽማግሌዎች ስህተት የሠራው ሰው እያደረገ ያለው ነገር የሚያስከትለውን ውጤት በግልጽ በማስቀመጥ ተግሣጽ በሚሰጡበት ጊዜ እንኳ ግለሰቡ የይሖዋ መንጋ አባል እንደሆነ አይዘነጉም።b (ሉቃስ 15:7) አብዛኛውን ጊዜ፣ ከፍቅር የመነጨና በደግነት የሚሰጥ ምክር ወይም ተግሣጽ ስህተት የሠራውን ሰው እንዲታረም ሊረዳው ይችላል።
19. ሽማግሌዎች ምን ውሳኔዎችን ያደርጋሉ? እነዚህ ውሳኔዎችስ በምን ላይ የተመረኮዙ መሆን አለባቸው?
19 ሽማግሌዎች የእምነት አጋሮቻቸውን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን የሚያደርጉባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንድሞች በሽማግሌነት ወይም በጉባኤ አገልጋይነት ለማገልገል ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለመወሰን ተሰብስበው የሚወያዩበት ጊዜ ይኖራል። በዚህ ጊዜ ምንም ዓይነት አድልዎ ማድረግ እንደሌለባቸው ያውቃሉ። በራሳቸው የግል ስሜት ሳይሆን አምላክ ባወጣቸው መሥፈርቶች ላይ ተመርኩዘው “መሠረተ ቢስ ከሆነ ጥላቻና ከአድልዎ በራቀ መንገድ” ትክክለኛ ውሳኔ ያደርጋሉ።—1 ጢሞቴዎስ 5:21
20, 21. (ሀ) ሽማግሌዎች ምን ጥረት ያደርጋሉ? ለምንስ? (ለ) ሽማግሌዎች “የተጨነቁትን” ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
20 ሽማግሌዎች መለኮታዊ ፍትሕን የሚያንጸባርቁባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ኢሳይያስ ሽማግሌዎች “ፍትሕ ለማስፈን” እንደሚያገለግሉ ከተነበየ በኋላ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “እያንዳንዱም ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ፣ ውኃ በሌለበት ምድር እንደ ጅረት፣ በደረቅ ምድርም እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 32:1, 2) ስለሆነም ሽማግሌዎች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው የእረፍትና የመጽናኛ ምንጭ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ።
21 በዛሬው ጊዜ ተስፋ የሚያስቆርጡ በርካታ ችግሮች ስላሉ ብዙዎች ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ሽማግሌዎች፣ “የተጨነቁትን” ለማጽናናት ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? (1 ተሰሎንቄ 5:14) ችግራቸውን እንደ ራሳችሁ ችግር አድርጋችሁ በመመልከት በርኅራኄ አዳምጧቸው። (ያዕቆብ 1:19) በልባቸው ያለውን ጭንቀት የሚያካፍሉት የሚያምኑት ሰው ይፈልጉ ይሆናል። (ምሳሌ 12:25) ይሖዋም ሆነ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እንደሚወዷቸውና ከፍ አድርገው እንደሚመለከቷቸው እንዲገነዘቡ እርዷቸው። (1 ጴጥሮስ 1:22፤ 5:6, 7) ከዚህም በተጨማሪ አብራችኋቸው ጸልዩ፤ በግላችሁም ልትጸልዩላቸው ትችላላችሁ። አንድ ሽማግሌ አብሯቸው መጸለዩ በእጅጉ ሊያጽናናቸው ይችላል። (ያዕቆብ 5:14, 15) የተጨነቁትን ለመርዳት ከልብ የምታደርጉትን ጥረት የፍትሕ አምላክ የሆነው ይሖዋ እንደሚመለከተው አትዘንጉ።
ሽማግሌዎች ያዘኑትንና የተከዙትን በማበረታታት የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ ያንጸባርቃሉ
22. የይሖዋን ፍትሕ ልንኮርጅ የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ይህስ ምን ውጤት አለው?
22 በእርግጥም የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ በመኮረጅ ወደ እሱ ይበልጥ መቅረብ እንችላለን! የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች በመከተል፣ ሕይወት አድን የሆነውን ምሥራች ለሌሎች በመንገርና የሰዎችን ስህተት ከመለቃቀም ይልቅ መልካም ጎናቸውን በማየት መለኮታዊውን ፍትሕ እናንጸባርቃለን። ሽማግሌዎች ደግሞ የጉባኤውን መንፈሳዊ ንጽሕና በመጠበቅ፣ ገንቢ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመስጠት፣ ከአድልዎ ነፃ የሆነ ውሳኔ በመወሰን እንዲሁም ያዘኑትንና የተከዙትን በማጽናናት መለኮታዊውን ፍትሕ ያንጸባርቃሉ። ይሖዋ ሕዝቡ ‘ፍትሕን በማድረግ’ ከእሱ ጋር ለመሄድ የሚያደርጉትን ጥረት ከሰማይ ሆኖ ሲመለከት ምንኛ ይደሰታል!
a በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኘው አገላለጽ በሂደት ላይ ያለንና መቆም ያለበትን ድርጊት የሚያመለክት ነው። በመሆኑም ኢየሱስ አድማጮቹ እያደረጉ ያሉትን ነገር እንዲተዉ ይኸውም በሌሎች ላይ መፍረዳቸውን ወይም ሌሎችን መኮነናቸውን እንዲያቆሙ መምከሩ ነበር።
b መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ጢሞቴዎስ 4:2 ላይ ሽማግሌዎች አልፎ አልፎ ‘መውቀስ፣ መገሠጽ እንዲሁም አጥብቀው መምከር’ እንዳለባቸው ይናገራል። ‘አጥብቆ መምከር’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ፓራካሌኦ) “ማበረታታት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው ፓራክሊቶስ የሚለው የግሪክኛ ቃል፣ ሕግ ነክ ለሆኑ ጉዳዮች ለአንድ ግለሰብ ጥብቅና የሚቆምን ሰው ሊያመለክት ይችላል። በመሆኑም ሽማግሌዎች ጠንከር ያለ ወቀሳ በሚሰጡበት ጊዜም እንኳ ግባቸው ግለሰቡን በመንፈሳዊ መርዳት ነው።