-
ተመልሶ የተቋቋመ ገነት!የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
-
-
ባድማ የሆነው ምድር ደስ ይለዋል
3. በኢሳይያስ ትንቢት መሠረት ምድሪቱ ምን ዓይነት ለውጥ ታደርጋለች?
3 ተመልሶ ስለተቋቋመው ገነት ኢሳይያስ በመንፈስ አነሳሽነት የተናገረው ትንቢት እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፣ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።”—ኢሳይያስ 35:1, 2
4. የአይሁዳውያኑ የትውልድ አገር ምድረ በዳ የሆነችው መቼና እንዴት ነው?
4 ኢሳይያስ እነዚህን ቃላት የጻፈው በ732 ከዘአበ ገደማ ነው። ከዚህ በኋላ 125 ዓመታት ቆይቶ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በማጥፋት የይሁዳን ሕዝብ በምርኮ አግዘዋል። ትውልድ አገራቸው ሰው አልባና ባድማ ሆና ቀርታለች። (2 ነገሥት 25:8-11, 21-26) የእስራኤል ሕዝብ የታመነ ሆኖ ሳይገኝ ከቀረ በምርኮ እንደሚወሰድ ይሖዋ አስቀድሞ የተናገረው ማስጠንቀቂያ በዚህ ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ዘዳግም 28:15, 36, 37፤ 1 ነገሥት 9:6-8) የዕብራውያኑ ብሔር በባዕድ አገር በምርኮ በቆየባቸው 70 ዓመታት ወቅት በመስኖ ለምተው የነበሩት ማሳዎቻቸውና የጓሮ አትክልቶቻቸው ተንከባካቢ አጥተው ምድረ በዳ ሆነው ነበር።—ኢሳይያስ 64:10፤ ኤርምያስ 4:23-27፤ 9:10-12
5. (ሀ) ምድሪቱ ወደ ገነታዊ ሁኔታ የተመለሰችው እንዴት ነው? (ለ) ሰዎች ‘የይሖዋን ክብር የሚያዩት’ በምን መንገድ ነው?
5 ይሁን እንጂ የኢሳይያስ ትንቢት ምድሪቱ ለዘላለም ባድማ ሆና እንደማትቀር ይተነብያል። ገነታዊ ሁኔታ ይኖራታል። ‘የሊባኖስን ክብር’ እና ‘የቀርሜሎስን ግርማ’ ትላበሳለች።a እንዴት? አይሁዳውያኑ ከምርኮ ሲመለሱ መሬታቸውን በእህል መሸፈንና በመስኖ ማልማት ስለሚችሉ ምድራቸው ቀደም ሲል ወደነበራት ፍሬያማነት ትመለሳለች። ለዚህ ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ ብቻ ነው። አይሁዳውያኑ እንዲህ ያለ ገነታዊ ሁኔታ ሊያገኙ የሚችሉት በእርሱ ፈቃድ፣ ድጋፍና በረከት ነው። አስገራሚ በሆነው የምድሪቱ ለውጥ የይሖዋ እጅ እንዳለበት የሚገነዘቡ ሰዎች ‘የይሖዋን ክብር የአምላካቸውንም ግርማ ያያሉ።’
6. የበለጠ ትርጉም ያለው የትኛው የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ እውን ሆኗል?
6 የሆነ ሆኖ ተመልሳ በምትቋቋመው በእስራኤል ምድር የኢሳይያስ ቃላት ከዚህ የበለጠ ትርጉም ያለው ፍጻሜም ይኖራቸዋል። እስራኤል በመንፈሳዊ ሁኔታ ሲታይ ለብዙ ዓመታት እንደ በረሃ ደረቅ ሆና ቆይታለች። ግዞተኞቹ በባቢሎን በቆዩባቸው ጊዜያት ንጹሕ አምልኮ በእጅጉ ተዳፍኖ ነበር። ቤተ መቅደስ፣ መሠዊያ ወይም የተደራጀ የክህነት አገልግሎት አልነበረም። በየዕለቱ የሚቀርበው መሥዋዕት ቀርቶ ነበር። አሁን ግን ኢሳይያስ ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ ሁኔታ እንደሚመጣ በትንቢት ተናግሯል። እንደ ዘሩባቤል፣ ዕዝራና ነህምያ በመሳሰሉት ሰዎች መሪነት ከ12ቱም የእስራኤል ነገዶች የተውጣጡ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱን በመገንባት ይሖዋን በነፃነት ያመልካሉ። (ዕዝራ 2:1, 2) ይህ በእርግጥም መንፈሳዊ ገነት ነው!
-
-
ተመልሶ የተቋቋመ ገነት!የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
-
-
a ቅዱሳን ጽሑፎች የጥንቷ ሊባኖስ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖችና ትላልቅ የዝግባ ዛፎች የነበሩባት ከኤድን ገነት ጋር የምትነጻጸር ለም ምድር እንደነበረች ይገልጻሉ። (መዝሙር 29:5፤ 72:16፤ ሕዝቅኤል 28:11-13) ሳሮን በውኃ ፈሳሾቿና የተለያዩ ዛፎች ባሉት ደኗ የምትታወቅ ሲሆን ቀርሜሎስ ደግሞ በወይን ቦታዎቿና በአትክልት ስፍራዎቿ እንዲሁም አበባ የተነጠፈባቸው በሚመስሉት ኮረብታዎቿ ትታወቃለች።
-