‘የአምላክን ቃል በድፍረት ተናገሩ’
“በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር ጀመሩ።”—ሥራ 4:31
1, 2. በአገልግሎታችን ውጤታማ ለመሆን መጣር ያለብን ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ከመሞቱ ከሦስት ቀናት በፊት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ ሊያርግ ሲል ‘ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት የማድረግና ያዘዛቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ የማስተማር’ ተልዕኮ ለተከታዮቹ ሰጥቷቸው ነበር። እንዲሁም “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል።—ማቴ. 24:14፤ 26:1, 2፤ 28:19, 20
2 የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተጀመረውን ሥራ በትጋት እናከናውናለን። ሕይወት አድን የሆነውን ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ያህል አስፈላጊ የሆነ ተልዕኮ የለም። በመሆኑም በአገልግሎታችን ውጤታማ ለመሆን መጣራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! በአገልግሎት በምንካፈልበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ መመራታችን በድፍረት እንድንናገር የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን። በቀጣዮቹ ሁለት ርዕሶች ላይ ደግሞ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድናስተምርና አዘውትረን እንድንሰብክ የይሖዋ መንፈስ የሚመራን እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
ድፍረት ያስፈልገናል
3. በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ለመካፈል ድፍረት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
3 አምላክ የሰጠን የመንግሥቱን ምሥራች የማወጅ ተልዕኮ ተወዳዳሪ የሌለው መብት ነው። ይሁን እንጂ ይህንን ተልዕኮ መፈጸም ተፈታታኝ የሚሆንበት ጊዜ አለ። አንዳንዶች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በደስታ የሚቀበሉ ቢሆንም ብዙዎች በኖኅ ዘመን እንደነበሩት ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች “የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴ. 24:38, 39) ከዚህም ሌላ የሚያፌዙብን ወይም የሚቃወሙን ሰዎች አሉ። (2 ጴጥ. 3:3) ከመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አብረውን ከሚማሩ ልጆች ወይም ከሥራ ባልደረቦቻችን ሌላው ቀርቶ ከቤተሰባችን አባላት እንኳ ተቃውሞ ሊያጋጥመን ይችላል። ከዚህም ባሻገር ከራሳችን ድክመት ጋር መታገል ያስፈልገናል፤ ለምሳሌ ዓይን አፋርነትንና በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት አጣለሁ የሚለውን ፍርሃት ማሸነፍ ያስፈልገን ይሆናል። “በነፃነት የመናገር ችሎታ” እንዳይኖረንና የአምላክን ቃል “በድፍረት” እንዳንናገር እንቅፋት የሚሆኑብን የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። (ኤፌ. 6:19, 20) በመሆኑም የአምላክን ቃል በጽናት ለመስበክ ድፍረት ያስፈልገናል። ታዲያ ድፍረት ለማግኘት ምን ሊረዳን ይችላል?
4. (ሀ) ድፍረት ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰሎንቄ ሰዎችን ለማነጋገር ድፍረት ያገኘው እንዴት ነው?
4 “ድፍረት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ያሰቡትን መናገር፣ ግልጽነት፣ ፊት ለፊት መናገር” የሚል ፍቺ አለው። ቃሉ “ቆራጥነት፣ ልበ ሙሉነት፣ . . . ፍርሃት የለሽ መሆን” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ደፋር ነው ሲባል አፉ እንዳመጣለት ወይም ጨዋነት በጎደለው መንገድ ይናገራል ማለት አይደለም። (ቆላ. 4:6) ድፍረት ለማዳበር ብንጥርም ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር እንፈልጋለን። (ሮም 12:18) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ስንሰብክ በድፍረት ብንናገርም ዘዴኞች መሆን አለብን፤ ምክንያቱም ሳናስበው ሰዎችን ቅር ማሰኘት አንፈልግም። በእርግጥም ተገቢ የሆነ ድፍረት እንዲኖረን ልናዳብራቸው የሚገቡ ሌሎች ባሕርያት አሉ። ይሁንና እንዲህ ያለውን ድፍረት የምናገኘው በራሳችን ጥንካሬ ወይም ችሎታ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ ‘በፊልጵስዩስ እንግልት ከደረሰባቸው’ በኋላ በተሰሎንቄ ያሉትን ለማነጋገር ‘ድፍረት ያገኙት’ እንዴት ነው? ጳውሎስ ‘በአምላክ እርዳታ’ እንደሆነ ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 2:2ን አንብብ።) ይሖዋ አምላክ ፍርሃታችንን ሊያስወግድልንና ጳውሎስና ባልደረቦቹ የነበራቸው ዓይነት ድፍረት ሊሰጠን ይችላል።
5. ይሖዋ ለጴጥሮስ፣ ለዮሐንስና ለሌሎች ደቀ መዛሙርት ድፍረት የሰጣቸው እንዴት ነበር?
5 “የሕዝቡ ገዥዎችና ሽማግሌዎች እንዲሁም ጸሐፍት” እንዳይሰብኩ ሐዋርያትን ባዘዟቸው ጊዜ ጴጥሮስና ዮሐንስ እንዲህ አሏቸው፦ “አምላክን ከመስማት ይልቅ እናንተን መስማት በአምላክ ፊት ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ እናንተ ለራሳችሁ ፍረዱ። በእኛ በኩል ግን ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ልንል አንችልም።” ሐዋርያት ስደቱ እንዲቆም ወደ አምላክ ከመጸለይ ይልቅ “ይሖዋ ሆይ፣ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው” በማለት ከሌሎች የእምነት ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው ምልጃ አቀረቡ። (ሥራ 4:5, 19, 20, 29) ይሖዋ ለጸሎታቸው ምን ምላሽ ሰጠ? (የሐዋርያት ሥራ 4:31ን አንብብ።) ይሖዋ ድፍረት እንዲያገኙ በመንፈሱ አማካኝነት ረድቷቸዋል። የአምላክ መንፈስ ለእኛም እንዲሁ ሊያደርግልን ይችላል። ታዲያ የአምላክን መንፈስ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ይህ መንፈስ በአገልግሎታችን ሊመራን የሚችለውስ እንዴት ነው?
ድፍረት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
6, 7. የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት ቀላሉ መንገድ ምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።
6 የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት ቀላሉ መንገድ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን መጠየቅ ነው። ኢየሱስ ያዳምጡት ለነበሩት ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!” (ሉቃስ 11:13) በእርግጥም መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት አዘውትረን መጸለይ አለብን። በአንዳንድ የአገልግሎቱ ዘርፎች ስለ መካፈል፣ ለምሳሌ ከመንገድ ወደ መንገድ ስለ ማገልገል እንዲሁም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወይም በንግድ አካባቢዎች ስለ መስበክ ስናስብ ፍርሃት ፍርሃት የሚለን ከሆነ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን በመጸለይ የሚያስፈልገንን ድፍረት ለማግኘት እንዲረዳን መጠየቅ እንችላለን።—1 ተሰ. 5:17
7 ሮሳ የተባለች ክርስቲያን ሴት ያደረገችው ይህንኑ ነው።a አንድ ቀን ሮሳ በሥራ ቦታዋ ሳለች አብራት የምትሠራ አንዲት መምህርት በልጆች ላይ ስለሚፈጸም በደል የሚገልጽ ከሌላ ትምህርት ቤት የመጣ ሪፖርት ታነብ ነበር። መምህርቷም ያነበበችው ነገር በጣም ስለረበሻት “ኧረ እንደው ይህ ዓለም መጨረሻው ምን ይሆን?” በማለት በምሬት ተናገረች። ሮሳ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችላትን ይህን አጋጣሚ ለማለፍ አልፈለገችም። ታዲያ ለመናገር የሚያስችላትን ድፍረት ለማግኘት ምን አደረገች? “ወደ ይሖዋ በመጸለይ መንፈሱን እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት” ብላለች። በውጤቱም ግሩም ምሥክርነት መስጠት የቻለች ከመሆኑም በላይ ሌላ ጊዜ ለመወያየት ቀጠሮ ያዙ። በኒው ዮርክ ሲቲ የምትኖረውን ሚላኒ የተባለች የአምስት ዓመት ልጅም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሚላኒ “ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዴ በፊት እኔና እናቴ ሁልጊዜ ወደ ይሖዋ እንጸልያለን” በማለት ተናግራለች። የሚጸልዩት ምን ለማግኘት ነው? ሚላኒ ጠንካራ አቋም ለመያዝና ስለ አምላኳ ለመናገር የሚያስችል ድፍረት እንድታገኝ ነው። የሚላኒ እናት እንደሚከተለው ብላለች፦ “እንዲህ ማድረጋችን ሚላኒ ልደትና ሌሎች በዓላትን በተመለከተ አቋሟን ለማስረዳት እንድትችልና እነዚህ በዓላት ሲከበሩ በሚደረጉት ዝግጅቶች ላይ ከመካፈል እንድትቆጠብ ረድቷታል።” ድፍረት ለማግኘት ጸሎት እንደሚረዳ ከእነዚህ ምሳሌዎች መመልከት አንችልም?
8. ድፍረት ከማግኘት ጋር በተያያዘ ከነቢዩ ኤርምያስ ምን እንማራለን?
8 ነቢዩ ኤርምያስ ድፍረት ለማግኘት ምን እንደረዳውም እንመልከት። ይሖዋ ኤርምያስን ለሕዝቦች ነቢይ እንዲሆን በሾመው ጊዜ ኤርምያስ “እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና” በማለት መልሶለት ነበር። (ኤር. 1:4-6) ከጊዜ በኋላ ግን ኤርምያስ የስብከቱን ሥራ በጽናትና በድፍረት ከማከናወኑ የተነሳ ብዙ ሰዎች መዓት እንደሚያውጅ አድርገው ተመልክተውት ነበር። (ኤር. 38:4) የይሖዋን የፍርድ መልእክት ከ65 ለሚበልጡ ዓመታት በድፍረት አውጇል። ኤርምያስ ያለ ምንም ፍርሃት በድፍረት በመስበኩ በእስራኤል ውስጥ በጣም ታውቆ ስለነበር ከ600 ዓመት ገደማ በኋላ ኢየሱስ በድፍረት ሲሰብክ አንዳንዶች ኤርምያስ ዳግም ሕያው የሆነ መስሏቸው ነበር። (ማቴ. 16:13, 14) መጀመሪያ ላይ ይህን ሥራ ለመጀመር አመንትቶ የነበረው ነቢዩ ኤርምያስ ዓይን አፋርነቱን ለማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው? “ቃሉ በልቤ እንደ እሳት፣ በዐጥንቴም ውስጥ እንደ ረመጥ ሆነብኝ፤ ዐፍኜ መያዝ አቃተኝ” በማለት ተናግሯል። (ኤር. 20:9) አዎን፣ የይሖዋ ቃል ለኤርምያስ ኃይል የሰጠው ከመሆኑም ሌላ እንዲናገር ገፋፍቶታል።
9. የአምላክ ቃል ልክ እንደ ኤርምያስ ለእኛም ድፍረት ሊሰጠን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?
9 ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን እንዲሁም መገጣጠሚያንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።” (ዕብ. 4:12) የአምላክ ቃል ወይም መልእክት ልክ እንደ ኤርምያስ ለእኛም ድፍረት ሊሰጠን ይችላል። አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው በሰዎች ተጠቅሞ ቢሆንም ይህ መጽሐፍ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ እንጂ ሰብዓዊ ጥበብ የያዙ መጻሕፍት ስብስብ እንዳልሆነ አስታውስ። ሁለተኛ ጴጥሮስ 1:21 እንዲህ ይላል፦ “መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ።” ጊዜ ወስደን ትርጉም ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስናደርግ አእምሯችን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተጻፈው መልእክት ይሞላል። (1 ቆሮንቶስ 2:10ን አንብብ።) ይህ መልእክት በውስጣችን “እንደ እሳት” ስለሚሆንብን አፍነን መያዝ ያቅተናል።
10, 11. (ሀ) ለመስበክ ድፍረት እንዲኖረን ምን ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልማድ ማዳበር ይኖርብናል? (ለ) የግል ጥናትህን ጥራት ለማሻሻል ልትወስዳቸው ካሰብካቸው እርምጃዎች ቢያንስ አንዱን ተናገር።
10 በግላችን የምናደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለሥራ እንዲያንቀሳቅሰን ከተፈለገ መልእክቱ ልባችንን እና ውስጣዊ ማንነታችንን እንዲነካው በሚያደርግ መንገድ ማጥናት ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል በተመለከተው ራእይ ላይ ልበ ደንዳና ለሆኑ ሰዎች የሚናገረውን ኃይለኛ መልእክት የያዘ አንድ ጥቅልል መጽሐፍ እንዲበላ ተነግሮት ነበር። ሕዝቅኤል ሙሉውን መልእክት በመብላት ከሰውነቱ ጋር እንዲዋሃድ ማድረግ ነበረበት። እንዲህ ማድረጉ መልእክቱን እንዲያደርስ የተሰጠው ተልዕኮ ልክ እንደ ማር ጣፋጭ እንዲሆንለት ይረዳዋል።—ከሕዝቅኤል 2:8 እስከ 3:4, 7-9ን አንብብ።
11 የእኛም ሁኔታ ከሕዝቅኤል ጋር ተመሳሳይ ነው። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በፍጹም መስማት አይፈልጉም። የአምላክን ቃል በመስበኩ ሥራ በጽናት መካፈል ከፈለግን ቅዱሳን መጻሕፍትን ሙሉ በሙሉ ለመረዳትና ትምህርቱን ለማመን በሚያስችለን መንገድ ማጥናታችን አስፈላጊ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራማችን ያዝ ለቀቅ ዓይነት ሳይሆን ቋሚ መሆን ይኖርበታል። የእኛም ፍላጎት “መጠጊያዬና አዳኜ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፌ ቃልና የልቤ ሐሳብ፣ በፊትህ ያማረ ይሁን” ብሎ እንደዘመረው መዝሙራዊ ሊሆን ይገባል። (መዝ. 19:14) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ወደ ልባችን ጠልቆ እንዲገባ ጊዜ ወስደን ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰላችን እንዴት አስፈላጊ ነው! እንግዲያው የግል ጥናታችንን ጥራት ለማሻሻል ጥረት ማድረግ እንደሚኖርብን ምንም ጥርጥር የለውም።b
12. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመንፈስ ቅዱስ ለመመራት የሚረዱን እንዴት ነው?
12 ከይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ጥቅም ማግኘት የምንችልበት ሌላው መንገድ ‘እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት ለመስጠት አንድ ላይ መሰብሰብ’ ነው። (ዕብ. 10:24, 25) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ለመገኘት ጥረት ማድረጋችን እንዲሁም ትምህርቱን በጥሞና ማዳመጣችንና የተማርነውን ነገር በሥራ ላይ ማዋላችን በመንፈስ ለመመራት የሚያስችለን ግሩም መንገድ ነው። ደግሞስ የይሖዋ መንፈስ መመሪያ የሚሰጠው በጉባኤ አማካኝነት አይደለም?—ራእይ 3:6ን አንብብ።
ድፍረት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
13. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ካከናወኑት የስብከት ሥራ ምን ትምህርት እናገኛለን?
13 መንፈስ ቅዱስ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ኃይል ሲሆን ሰዎች የይሖዋን ፈቃድ እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ታላቅ የስብከት ሥራ ማከናወን ችለዋል። ምሥራቹን “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ መካከል” ሰብከዋል። (ቆላ. 1:23) አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርት “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” መሆናቸውን ስንመለከት አንድ ታላቅ ኃይል እርዳታ እንዳደረገላቸው ግልጽ ይሆንልናል።—ሥራ 4:13
14. ‘በመንፈስ የምንቃጠል’ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
14 ከመንፈስ ቅዱስ አመራር ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታችንን መምራታችንም አገልግሎታችንን በድፍረት እንድናከናውን ያነሳሳናል። መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት አዘውትረን መጸለያችን፣ በትጋትና ትርጉም ባለው መንገድ የግል ጥናት ማድረጋችን፣ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰላችንና ስለ ጉዳዩ መጸለያችን እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን አንድ ላይ ተዳምረው የሚያስገኙት ጥቅም ‘በመንፈስ የጋልን’ እንድንሆን ይረዳናል። (ሮም 12:11) መጽሐፍ ቅዱስ “የእስክንድርያ ተወላጅ [ስለሆነ] አጵሎስ የሚባል ጥሩ የመናገር ተሰጥኦ ያለው አንድ አይሁዳዊ” ሲገልጽ “በመንፈስ እየተቃጠለ ኢየሱስን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች በትክክል ይናገርና ያስተምር ነበር” ይላል። (ሥራ 18:24, 25) እኛም ‘በመንፈስ የምንቃጠል’ ከሆነ ከቤት ወደ ቤትም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በምናከናውነው አገልግሎት የበለጠ ድፍረት ማሳየት እንችላለን።—ሮም 12:11 የ1954 ትርጉም
15. በምንመሠክርበት ጊዜ የበለጠ ድፍረት ማሳየታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
15 በምንመሠክርበት ጊዜ የበለጠ ድፍረት ማሳየታችን በእኛም ላይ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል። አገልግሎታችን ምን ያህል አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ የበለጠ ስለምንገነዘብ ለስብከቱ ሥራ አዎንታዊ አመለካከት እያዳበርን እንሄዳለን። በአገልግሎታችን ውጤታማ ስንሆን ደስታችንም ስለሚጨምር የበለጠ ግለት ይኖረናል። የስብከቱ ሥራ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ይበልጥ ስለምንረዳ ቅንዓታችን ይቀጣጠላል።
16. ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት እየቀዘቀዘ ከመጣ ምን ማድረግ አለብን?
16 ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት ቀዝቅዞ ቢሆንስ? ወይም ቀድሞ የነበረን ዓይነት ቅንዓት ባይኖረንስ? ሁኔታችን እንዲህ ከሆነ ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ይገባናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በእምነት ውስጥ እየተመላለሳችሁ መሆናችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ ራሳችሁን ዘወትር ፈትኑ።” (2 ቆሮ. 13:5) ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘አሁንም እንደ ቀድሞው በመንፈስ የጋልኩ ነኝ? ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠኝ እጸልያለሁ? ጸሎቴ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በእሱ እንደምታመን ያሳያል? በአደራ የተሰጠንን የአገልግሎት መብት እንደማደንቅ በጸሎቴ ላይ እገልጻለሁ? የግል ጥናት ልማዴ ምን ይመስላል? በማነባቸውና በምሰማቸው ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ምን ያህል ጊዜ እመድባለሁ? በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ምን ያህል ተሳትፎ አደርጋለሁ?’ እንደነዚህ ባሉ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰልህ ያሉብህን ድክመቶች ለይተህ እንድታውቅና አስፈላጊውን ማስተካከያ እንድታደርግ ይረዳሃል።
የአምላክ መንፈስ ድፍረት እንድታገኝ ይርዳህ
17, 18. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የስብከቱ ሥራ ምን ያህል እየተከናወነ ነው? (ለ) የአምላክን መንግሥት ምሥራች “በታላቅ የመናገር ነፃነት” ማወጅ የምንችለው እንዴት ነው?
17 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) በዚያን ጊዜ የተጀመረው ሥራ ከአሁን በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዛሬው ጊዜ በስፋት እየተከናወነ ነው። ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮች የመንግሥቱን መልእክት እየሰበኩ ሲሆን በዓመት ወደ 1.5 ቢሊዮን የሚጠጋ ሰዓት በአገልግሎት ያሳልፋሉ። ፈጽሞ በማይደገመው በዚህ ሥራ በቅንዓት መካፈል እጅግ የሚያስደስት ነው!
18 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜም ዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ የሚከናወነው በአምላክ መንፈስ መሪነት ነው። መንፈሱ የሚሰጠንን አመራር የምንቀበል ከሆነ “በታላቅ የመናገር ነፃነት” ማገልገል እንችላለን። (ሥራ 28:31) እንግዲያው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በምናውጅበት ጊዜ የአምላክ መንፈስ እንዲመራን እንፍቀድ!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስሞቹ ተቀይረዋል።
b ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህና ከግል ጥናትህ የላቀ ጥቅም ለማግኘት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 21-32 ላይ የሚገኙትን “ለማንበብ ትጋ” እና “ጥናት በረከት ያስገኛል” የሚሉትን ምዕራፎች ተመልከት።
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• የአምላክን ቃል ስንሰብክ ድፍረት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
• የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት በድፍረት እንዲናገሩ የረዳቸው ምንድን ነው?
• ድፍረት ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን?
• ድፍረት ማግኘታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች ልጆቻቸው ድፍረት እንዲያገኙ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አጭር ጸሎት ማቅረብህ በአገልግሎት ድፍረት እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል