ውኃ የማይዙ ጉድጓዶች
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ጉድጓዶች በዋነኝነት ውኃ ለማጠራቀም የሚያገለግሉ ከመሬት በታች ያሉ ሰው ሠራሽ ጎድጓዳ ቦታዎች ነበሩ። ይህ በአንዳንድ ወቅቶች በተስፋይቱ ምድር የሚጠጣ ውኃ እንዳይጠፋ ማድረግ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ነበር።
ነቢዩ ኤርምያስ አምላክ ያስተላለፈውን መልእክት ሲጽፍ ጉድጓድ የሚለውን ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም እንዲህ ብሏል:- “ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና፤ እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፣ የተቀደዱትንም ጉድጓዶች፣ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጉድጓዶች፣ ለራሳቸው ቆፍረዋል።”—ኤርምያስ 2:13
እስራኤላውያን ‘የሕያው ውኃ ምንጭ’ የሆነውን አምላካቸውን ይሖዋን ትተው ከአረማዊ ብሔራት ጋር አስተማማኝ ያልሆነ ወታደራዊ ኅብረት ፈጥረውና ከንቱ የሆኑ የሐሰት አማልክትን ማምለክ ጀምረው ነበር። እነዚህ ተስፋ የተደረገባቸው መሸሸጊያዎች ኤርምያስ በተጠቀመበት ምሳሌያዊ አነጋገር መሠረት ምንም የመከላከል ወይም የማዳን ኃይል የሌላቸው ከተቀደዱ ጉድጓዶች የማይሻሉ መሆናቸው ታይቷል።—ዘዳግም 28:20
በዛሬው ጊዜ ከዚህ ታሪካዊ ምሳሌ የምናገኘው ትምህርት አለ? በኤርምያስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዘላለማዊው አምላክ ይሖዋ ዛሬም ብቸኛው የሕይወት ውኃ ምንጭ ነው። (መዝሙር 36:9፤ ራእይ 4:11) የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከእርሱ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 4:14፤ 17:3) ሆኖም በኤርምያስ ዘመን እንደነበሩት ሰዎች ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የአምላክ ቃል ላለመቀበል ብሎም ለማጥላላት መርጠዋል። እንዲያውም ትምክህታቸውን ጊዜያዊ በሆኑ ፖለቲካዊ መፍትሔዎች፣ ከንቱ በሆኑ ሰብዓዊ አስተሳሰቦችና ለአምላክ ክብር በማይሰጡ ፋይዳ ቢስ መርሆችና ፍልስፍናዎች ላይ ጥለዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:18-20፤ ቆላስይስ 2:8) ከፊታችን የተደቀነው ምርጫ አሻሚ አይደለም። ትምክህታችሁን የምትጥሉት በማን ላይ ነው? ‘የሕያው ውኃ ምንጭ’ በሆነው በይሖዋ ወይስ ‘ውኃውን ይይዙ ዘንድ በማይችሉ የተቀደዱ ጉድጓዶች’?
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአንድ እስራኤላዊ መቃብር ላይ የተገኘ ከሸክላ የተሠራ የእናት አምላክ ምስል
[ምንጭ]
Photograph taken by courtesy of the British Museum