የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—መጋቢት 2017
ከመጋቢት 6-12
jr-E 88 አን. 14-15
“የዛለውን አድሳለሁና”
የደከሙትን ታበረታላችሁ?
14 ኤርምያስ የተበረታታውና ‘የደከሙትን ማበረታታት’ የቻለው እንዴት እንደሆነ መመርመራችን ጠቃሚ ነው። (ኤር. 31:25) ነቢዩ በቀጥታ ከይሖዋ ማበረታቻ አግኝቷል። ይሖዋ አንተን በቀጥታ እንደሚከተለው ቢልህ ምን ሊሰማህ እንደሚችል ገምት፦ “ዛሬ አንተን የተመሸገ ከተማ . . . አድርጌሃለሁ። እነሱም በእርግጥ ይዋጉሃል፤ ሆኖም አያሸንፉህም፤ ‘አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና’ ይላል ይሖዋ።” (ኤር. 1:18, 19) በእርግጥም ኤርምያስ ይሖዋን “ብርታቴና መጠጊያዬ፣ በጭንቀት ጊዜ መሸሸጊያዬ” ብሎ መጥራቱ የሚያስገርም አይደለም።—ኤር. 16:19
15 ይሖዋ ለኤርምያስ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝ” ያለው መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ይህ ሐሳብ አንድን ሰው ለማበረታታት ምን ማድረግ እንደምንችል ይጠቁመናል። ክርስቲያን ወንድማችን ወይም እህታችን አሊያም ዘመዳችን ማበረታቻ እንደሚያስፈልገው ማወቃችን አስፈላጊ ቢሆንም ዋናው ነገር ግለሰቡን ማበረታታታችን ነው። አብዛኛውን ጊዜ ይህን ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው መንገድ አምላክ ለኤርምያስ ያደረገለትን ነገር ማድረግ ይኸውም ችግር ከደረሰበት ሰው ጋር አብሮ መሆን ነው። ከዚያም አስፈላጊ ሲሆን የሚያበረታታ ነገር መናገራችን ተገቢ ነው፤ ሆኖም ብዙ እንዳናወራ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ጥቂት ቢሆኑም በሚገባ የታሰበባቸው አበረታችና ገንቢ ቃላት መናገር የበለጠ ኃይል አለው። የተራቀቁ ቃላትን መጠቀም አያስፈልጋችሁም። ለግለሰቡ ያላችሁን አሳቢነትና ክርስቲያናዊ ፍቅር የሚያንጸባርቁ ያልተወሳሰቡ ቃላትን ተጠቀሙ። እንዲህ ያሉ ቃላት ትልቅ ኃይል አላቸው።—ምሳሌ 25:11ን አንብብ።
ከመጋቢት 13-19
w88-E 4/1 11-12 አን. 7-8
ኤርምያስ—የአምላክን የፍርድ መልእክት የሚያውጅ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘ ነቢይ
7 ይሖዋ ኤርምያስን “እነሱም በእርግጥ ይዋጉሃል” በማለት ካስጠነቀቀው በኋላ “ሆኖም አያሸንፉህም” ብሎታል። (ኤርምያስ 1:19) ለመሆኑ አይሁዳውያንና ገዢዎቻቸው ከዚህ ነቢይ ጋር የሚዋጉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም የሚያውጀው መልእክት ግድየለሽነታቸውንና በዘልማድ የሚያደርጉትን አምልኮ የሚያወግዝ ነበር። ኤርምያስም ቢሆን መልእክቱን ለማለሳለስ አልሞከረም፤ እንዲህ ብሏል፦ “እነሆ፣ ጆሮዎቻቸው ስለተዘጉ ማዳመጥ አይችሉም። እነሆ፣ የይሖዋን ቃል መሳለቂያ አድርገውታል፤ ቃሉም ደስ አያሰኛቸውም። ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ እያንዳንዱ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ይሯሯጣል፤ ከነቢዩ አንስቶ እስከ ካህኑ ድረስ [ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ እሴቶችን የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው ሰዎች] ሁሉም ያጭበረብራል።”—ኤርምያስ 6:10, 13
8 እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች መሥዋዕት በማቅረብ ረገድ በብሔሩ ውስጥ ግንባር ቀደም ነበሩ። ከእውነተኛው አምልኮ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ቢያከናውኑም ይህን የሚያደርጉት ከልባቸው አልነበረም። ትክክለኛውን ምግባር ከማሳየት የበለጠ ትኩረት የሚሰጡት የአምልኮ ሥርዓቶችን ለመፈጸም ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹም ቢሆኑ ሰላም ሳይኖር “ሰላም ነው! ሰላም ነው!” በማለት ሕዝቡን ያታልሉ ነበር። (ኤርምያስ 6:14፤ 8:11) በዚህ መንገድ ሕዝቡ ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዳለው እንዲሰማው አድርገዋል። ይሖዋ ጥበቃ የሚያደርግለት ሕዝብ ስለሆኑ እንዲሁም የሚኖሩት ቤተ መቅደሱ ባለበት በቅድስቲቱ ከተማ ስለሆነ ምንም የሚያሳስባቸው ነገር እንደሌለ ተሰምቷቸዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ስለ ጉዳዩ የእነሱ ዓይነት አመለካከት ነበረው?
w88-E 4/1 12 አን. 9-10
ኤርምያስ—የአምላክን የፍርድ መልእክት የሚያውጅ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘ ነቢይ
9 ኤርምያስ በቤተ መቅደሱ በር ላይ ሁሉም ሰው በሚያየው ቦታ ቆሞ አምልኮ ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደሱ ለሚገቡ ሰዎች መልእክቱን እንዲያውጅ ይሖዋ አዞት ነበር። መልእክቱ እንዲህ የሚል ነበር፦ “‘ይህ የይሖዋ ቤተ መቅደስ፣ የይሖዋ ቤተ መቅደስ፣ የይሖዋ ቤተ መቅደስ ነው!’ እያላችሁ በአሳሳች ቃል አትታመኑ። . . . ይህ ደግሞ ፈጽሞ አይጠቅማችሁም።” አይሁዳውያኑ በቤተ መቅደሳቸው በመመካት በእምነት ሳይሆን በማየት እየተመላለሱ ነበር። ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት የተናገራቸውን የማስጠንቀቂያ ቃላት ዘንግተው ነበር፦ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድር ደግሞ የእግሬ ማሳረፊያ ናት። ታዲያ እናንተ ምን ዓይነት ቤት ልትሠሩልኝ ትችላላችሁ? ደግሞስ የማርፍበት ቦታ የት ነው?” ቤተ መቅደሳቸው ምንም ያህል የሚያምር ቢሆን የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እነሱ በሠሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ ተወስኖ አይኖርም!—ኤርምያስ 7:1-8፤ ኢሳይያስ 66:1
10 ኤርምያስ ለሕዝቡ የሚናገረውን ኃይለኛ መልእክት ሲቀጥል እንዲህ ብሏል፦ “እየሰረቃችሁ፣ እየገደላችሁ፣ እያመነዘራችሁ፣ በሐሰት እየማላችሁ፣ ለባአል መሥዋዕት እያቀረባችሁና የማታውቋቸውን አማልክት እየተከተላችሁ . . . ‘ምንም ችግር አይደርስብንም’ ማለት ትችላላችሁ?” የአምላክ ‘የተመረጠ ሕዝብ’ የሆኑት አይሁዳውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ መሥዋዕት እስካቀረቡ ድረስ አምላክ የሚያደርጉትን ማንኛውንም ነገር በቸልታ እንደሚያልፍ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋን ይመለከቱት የነበረው አንድያ ልጁን እንደሚያሞላቅቅ ስሜታዊ አባት አድርገው ነበር። እውነታውን የሚገነዘቡት ጊዜው ካለፈ በኋላ ነው።—ኤርምያስ 7:9, 10፤ ዘፀአት 19:5, 6
jr-E 21 አን. 12
“በዘመኑ መጨረሻ” ይሖዋን ማገልገል
12 ኢዮዓቄም መግዛት በጀመረበት ጊዜ አካባቢ ኤርምያስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ አይሁዳውያንን ለፈጸሙት ክፉ ድርጊት ፊት ለፊት እንዲያወግዛቸው ይሖዋ ነግሮት ነበር። አይሁዳውያኑ የይሖዋ ቤተ መቅደስ ምትሃታዊ በሆነ መንገድ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ይሰማቸው ነበር። ሆኖም ‘መስረቃቸውን፣ መግደላቸውን፣ በሐሰት መማላቸውን፣ ለባአል መሥዋዕት ማቅረባቸውንና የማያውቋቸውን አማልክት መከተላቸውን’ እስካላቆሙ ድረስ ይሖዋ ቤተ መቅደሱን እንደሚተወው ነግሯቸዋል። በሊቀ ካህናቱ በኤሊ ዘመን በሴሎ የነበረውን የማደሪያ ድንኳን እንደተወው ሁሉ በቤተ መቅደሱ የሚያመልኩትን ግብዝ የሆኑ አይሁዳውያንንም ይተዋቸዋል። የይሁዳ ምድር “የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች።” (ኤር. 7:1-15, 34፤ 26:1-6) ኤርምያስ ይህን መልእክት ለማወጅ ምን ያህል ድፍረት እንደጠየቀበት ለማሰብ ሞክር! መልእክቱን የሚያውጀው በሕዝቡ ዘንድ በተከበሩና ተሰሚነት ባላቸው ሰዎች ፊት ሳይሆን አይቀርም። በዛሬው ጊዜም አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች መንገድ ላይ ለመመሥከር አሊያም ከፍተኛ ሥልጣን ወይም የኑሮ ደረጃ ላላቸው ሰዎች ለመስበክ ፈራ ተባ ሊሉ ይችላሉ። ይሁንና ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ አምላክ ኤርምያስን እንደረዳው ሁሉ እኛንም ይረዳናል።—ኤር. 7:1-15, 34፤ 26:1-6
w88-E 4/1 13 አን. 15
ኤርምያስ—የአምላክን የፍርድ መልእክት የሚያውጅ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘ ነቢይ
ይሁዳ የእጇን አግኝታለች
15 በ632 ዓ.ዓ. አሦር በከለዳውያንና በሜዶናውያን እጅ ወድቃ ነበር፤ ግብፅም ኃይሏ ተመናምኖ ግዛቷ የሚሸፍነው ከይሁዳ በስተ ደቡብ ያለውን አካባቢ ብቻ ሆኖ ነበር። ይሁዳን ለስጋት የሚዳርግ ሁኔታ ሊመጣ የሚችለው ከሰሜን አቅጣጫ ብቻ ነበር። በመሆኑም ኤርምያስ ለአይሁዳውያን መርዶ ማርዳት ነበረበት! “እነሆ፣ ከሰሜን ምድር አንድ ሕዝብ እየመጣ ነው፤ . . . [እነሱም] ጨካኝና ምሕረት የለሽ ናቸው። . . . የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ ልክ እንደ ተዋጊ በአንቺ ላይ ይሰለፋሉ።” በዚህ ወቅት የዓለም ኃያል በመሆን ላይ የነበረችው ባቢሎን ነበረች። አምላክ እምነት የለሽ የሆነችውን ይሁዳን ለመቅጣት በባቢሎን ይጠቀማል።—ኤር. 6:22, 23፤ 25:8, 9
ከመጋቢት 20-26
it-1-E 555
ኪያር
ሰዎች፣ እንስሳት ሰብልን እንዳያጠፉ ለማስፈራራት እንጨት ወይም ሌሎች ነገሮችን ሰብሉ መሃል ያቆሙ ነበር። ነቢዩ ኤርምያስ ጣዖት አምላኪ የሆኑት ብሔራት የሠሯቸውን ምስሎች ‘በኪያር እርሻ ውስጥ ለማስፈራሪያነት ከሚተከል ማስፈራርቾ’ ጋር አመሳስሏቸዋል።—ኤር. 10:5
ከመጋቢት 27–ሚያዝያ 2
jr-E 51 አን. 17
ከዳተኛ ልባችሁ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ
17 ኤርምያስ የተሰጠው ተልእኮ የአምላክን አመራር መከተልን የሚጠይቅ ነበር። አንተ ኤርምያስን ብትሆን ኖሮ የሚሰጡህን መመሪያዎች ሁሉ በፈቃደኝነት ትቀበል ነበር? በአንድ ወቅት ይሖዋ ኤርምያስን ከተልባ እግር የተሠራ ቀበቶ ገዝቶ እንዲታጠቅ አዞት ነበር። ከዚያም ወደ ኤፍራጥስ እንዲሄድ አዘዘው። ካርታ አውጥተህ ብትመለከት ይህ ጉዞ 500 ኪ.ሜ. (300 ማይል) የሚሸፍን እንደሆነ ትረዳለህ። ኤርምያስ እዚያ ሲደርስ ቀበቶውን በቋጥኝ ስንጥቅ ውስጥ ከደበቀ በኋላ እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ነበረበት። የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ አምላክ ኤርምያስን ቀበቶውን ሄዶ እንዲያመጣ አዘዘው። (ኤርምያስ 13:1-9ን አንብብ።) ኤርምያስ በድምሩ 1,900 ኪ.ሜ. (1,200 ማይል) ተጉዟል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች፣ ኤርምያስ ወራት ሊፈጅ የሚችለውን ይህን ጉዞ እንዳደረገ ማመን ይከብዳቸዋል። (ዕዝራ 7:9) ያም ሆነ ይህ፣ አምላክ የሰጠው ትእዛዝም ሆነ ኤርምያስ ያደረገው ነገር ይህንኑ ነው።
jr-E 52 አን. 18
ከዳተኛ ልባችሁ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ
18 ይህ ነቢይ የይሁዳን ተራሮች ካቋረጠ በኋላ በምድረ በዳው በኩል አድርጎ ወደ ኤፍራጥስ ሲሄድ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ይህን አድካሚ ጉዞ የሚያደርገው ቀበቶውን ለመደበቅ ነበር! ኤርምያስ ለረጅም ጊዜ ከሰፈሩ መጥፋቱ የአካባቢውን ሰዎች ሳያነጋግር አልቀረም። ሲመለስ ከተልባ እግር የተሠራውን ቀበቶ አልያዘም ነበር። ከብዙ ቀናት በኋላ አምላክ ኤርምያስን በድጋሚ ያንን ረጅም ጉዞ እንዲያደርግና በወቅቱ “ተበላሽቶና ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆኖ” የሚገኘውን ቀበቶ እንዲያመጣ አዘዘው። ኤርምያስ ‘እንዴ፣ አሁንስ አልበዛም? እንዲህ ማድረግ ለምን አስፈለገ?’ ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር። ኤርምያስ ግን አምላክ ጥሩ አድርጎ እንዲቀርጸው ስለፈቀደ እንዲህ ያለ ምላሽ አልሰጠም። በአምላክ ላይ ከማጉረምረም ይልቅ የታዘዘውን ፈጽሟል!
jr-E 52 አን. 19-20
ከዳተኛ ልባችሁ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ
19 አምላክ ጉዳዩን ለኤርምያስ ያብራራለት ኤርምያስ ሁለተኛውን ጉዞ ካደረገ በኋላ ነበር። ኤርምያስ ያደረገው ነገር የሚከተለውን ጠንካራ መልእክት የሚያውጅበትን ሁኔታ አመቻችቶለታል፦ “ቃሌን ለመታዘዝ አሻፈረኝ ያለው፣ ግትር ሆኖ የገዛ ልቡን የሚከተለው እንዲሁም ሌሎች አማልክትን የሚከተለው፣ የሚያገለግለውና ለእነሱ የሚሰግደው ይህ ክፉ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ እንደሆነው እንደዚህ ቀበቶ ይሆናል።” (ኤር. 13:10) ይሖዋ ሕዝቡን ያስተማረው እንዴት ባለ አስገራሚ መንገድ ነው! ኤርምያስ ምንም ጥቅም የሌለው ሊመስል በሚችል ጉዳይም እንኳ ታዛዥ መሆኑ ይሖዋ የሕዝቡን ልብ ለመንካት ባደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ ለማበርከት አስችሎታል።—ኤር. 13:10
20 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለሌሎች ትምህርት ለመስጠት ሲል ክርስቲያኖችን በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች እንዲጓዙ አይጠይቃቸውም። ይሁንና የምትከተሉት ክርስቲያናዊ ጎዳና ጎረቤቶቻችሁ ወይም የሚያውቋችሁ ሰዎች ግራ እንዲጋቡ አልፎ ተርፎም እንዲተቿችሁ ያደርግ ይሆን? ሰዎች በአለባበሳችሁና በአጋጌጣችሁ፣ ከምትከታተሉት ትምህርት ጋር በተያያዘ በምታደርጉት ውሳኔ፣ በሥራ ምርጫችሁ ሌላው ቀርቶ የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ባላችሁ አቋም ይተቿችሁ ይሆናል። ታዲያ ልክ እንደ ኤርምያስ የአምላክን አመራር ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ ታደርጋላችሁ? ልባችሁ በአምላክ እንዲቀረጽ በመፍቀድ የምታደርጉት ምርጫ ለሰዎች ጥሩ ምሥክርነት ይሰጣል። አምላክ በቃሉ እንዲሁም በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት የሚሰጠውን መመሪያ መታዘዛችሁ ዘላቂ ጥቅም ያስገኝላችኋል። ከዳተኛ የሆነው ልባችሁ እንዲመራችሁ ከመፍቀድ ይልቅ ኤርምያስ የተወውን ምሳሌ ተከተሉ። እንግዲያው ምንጊዜም በአምላክ ለመቀረጽ ፈቃደኞች ሁኑ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ አምላክ ለዘለቄታው ክብር ላለው ዓላማ የሚጠቀምበት ዕቃ መሆን ትችላላችሁ።
it-1-E 1121 አን. 2
ወገብ
ይሖዋ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት በወገቡ ላይ እንደተጣበቀ ቀበቶ አድርጎ ገልጿቸዋል፤ እነዚህን ሕዝቦች ውዳሴውና ውበቱ እንዲሆኑ ከራሱ ጋር ልክ እንደ ቀበቶ አጣብቋቸው ነበር። (ኤር. 13:11) ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገዛበት ጊዜ ጽድቅ የወገቡ መታጠቂያ፣ ታማኝነት ደግሞ የጎኑ መታጠቂያ እንደሚሆን በትንቢት ተነግሯል። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወስደው እርምጃ ከጽድቅና ከታማኝነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። ቀበቶ ወገብን እንደሚደግፍ ሁሉ ኢየሱስ በይሖዋ የተሾመ ዳኛ ሆኖ በሚያገለግልበት ጊዜም ጽድቅ ድጋፍ ይሆነዋል።—ኢሳ. 11:5
jr-E 118 አን. 11
በየዕለቱ “ይሖዋ የት አለ?” ብለህ ትጠይቃለህ?
11 ኤርምያስ ክፉዎች ሲሳካላቸው ሲያይ በውስጡ ጥያቄ ተፈጥሮበት ነበር። (ኤርምያስ 12:1, 3ን አንብብ።) ይህ ነቢይ የይሖዋን ጽድቅ በተመለከተ ጥያቄ ባያነሳም ‘ለአቤቱታው’ መልስ ማግኘት ፈልጎ ነበር። ኤርምያስ ይሖዋን እንዲህ በግልጽ ማናገሩ፣ አንድ ልጅ ከአባቱ ጋር እንደሚቀራረብ ሁሉ እሱም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንደነበረው ያሳያል። ኤርምያስ ይህን ጥያቄ ያነሳው፣ በርካታ አይሁዳውያን ክፉዎች ሆነው ሳለ ኑሯቸው የተሳካላቸው ለምን እንደሆነ ማወቅ ስለፈለገ ነበር። ታዲያ ኤርምያስ አጥጋቢ መልስ አግኝቶ ይሆን? ይሖዋ ክፉዎችን እንደሚነቅላቸው አረጋገጠለት። (ኤር. 12:14) ኤርምያስ ጥያቄ ፈጥሮበትና ለአምላክ በጸሎት አቅርቦት የነበረው ጉዳይ እንዴት ደረጃ በደረጃ መፍትሔ እንዳገኘ ሲመለከት በመለኮታዊ ፍትሕ ላይ ያለው እምነት በጣም ተጠናክሮ መሆን አለበት። በተጨማሪም ይበልጥ ወደ አምላክ እንዲጸልይና ስሜቱን አውጥቶ እንዲናገር አነሳስቶት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።