ከሽመላ የሚገኝ ትምህርት
ነቢዩ ኤርምያስ አምላካቸውን ይሖዋን ትተው ሌሎች ባዕድ አማልክትን ባመለኩት ከሃዲ የይሁዳ ሕዝቦች ላይ ይሖዋ የበየነውን ፍርድ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሽመላ በሰማይ ጊዜዋን አውቃለች፤ . . . ሕዝቤ ግን የእግዚአብሔርን ፍርድ አላወቁም።” (ኤርምያስ 8:7፤ 7:18, 31) ኤርምያስ ታማኝ ያልነበሩትን እስራኤላውያን ለማስተማር ሽመላን እንደ ምሳሌ አድርጎ የተጠቀመው ለምን ነበር?
ሽመላ በተለይም ነጩ ሽመላ ወቅቱን ጠብቆ ሲፈልስ ማየት ለእስራኤላውያን የተለመደ ነገር ነበር። ይህ ትልቅ፣ ረዣዥም እግሮች ያሉትና በወንዝ ዳር የሚኖር ወፍ በዕብራይስጥ አንስታይ ጾታን በሚያመለክት ስም የሚጠራ ሲሆን የቃሉ ትርጉም “ታማኝ፣ ፍቅራዊ ደግነት ያለው” ማለት ነው። ከሌሎች ወፎች በተለየ መልኩ ወንድና ሴት ነጭ ሽመላዎች ሕይወታቸውን ሙሉ ተጣምረው ስለሚቆዩ ይህ ስም ተስማሚያቸው ነው። አብዛኞቹ ሽመላዎች በየዓመቱ የክረምቱን ወራት በሞቃት አካባቢዎች ካሳለፉ በኋላ ቀደም ሲል ወደ ነበሩበት ጎጆ ይመለሳሉ።
ሽመላዎች የታማኝነት ባሕርይን የሚያንጸባርቁ ሌሎች ነገሮችንም በደመ ነፍስ ሲያከናውኑ ይታያል። ወንዱም ሆነ ሴቷ እንቁላሎቻቸውን በመፈልፈሉና ጫጩቶቹን በመመገቡ ሥራ በጋራ ይካፈላሉ። አወር ማግኒፊሰንት ዋይልድ ላይፍ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ጫጩት የፈለፈሉ ሽመላዎች አንዳቸው ለሌላው በጣም ታማኝ ናቸው። በጀርመን አንድ ወንድ ሽመላ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ካለው ገመድ ጋር ይጋጭና ይሞታል። እንስቷ ሽመላ ለ3 ቀናት እንቁላሎቹን ለብቻዋ ታቀፈቻቸው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለአጭር ጊዜ ያህል ምግብ ለመፈለግ ከመነሳትዋ በቀር ወዴትም አልሄደችም። . . . በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ሴቷ ሽመላ ስትገደል አባትየው ጫጩቶቹን አሳድጓል።”
በእርግጥም ሽመላ ከዕድሜ ልክ አጋሩ ባለመለየትና ልጆቹንም በእንክብካቤ በመያዝ ረገድ እንደ ስሙ “ታማኝ” ነው። በመሆኑም ሽመላዎች ታማኝነት ለጎደላቸውና ለእምቢተኞቹ እስራኤላውያን ጥሩ ትምህርት የሚሆኑ ናቸው።
ዛሬ ያሉ ብዙ ሰዎች ታማኝነትን የሚደነቅ ሆኖም ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ጊዜ ያለፈበት ባሕርይ አድርገው ይመለከቱታል። ፍቺ፣ ቤተሰብን ጥሎ መሄድ፣ ማጭበርበር እንዲሁም ሌሎች የማታለል ተግባራት መስፋፋታቸው ታማኝነት የቀድሞውን ያህል ከፍ ተደርጎ የሚታይ ባሕርይ እንዳልሆነ ያሳየናል። ከዚህ በተቃራኒው መጽሐፍ ቅዱስ በፍቅርና በደግነት ላይ ለተመሠረተ ታማኝነት ከፍተኛ ቦታ ይሰጣል። ክርስቲያኖችን “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” በማለት ያበረታታል። (ኤፌሶን 4:24) አዎን፣ አዲሱ ሰውነት ታማኝ እንድንሆን ይረዳናል፤ ሆኖም ታማኝነትን በተመለከተ ከሽመላም ትምህርት መውሰድ እንችላለን።