ራሳችሁን ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ጠብቁ
“የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው?” —2 ቆሮንቶስ 6:16
1. የእስራኤላውያን የመገናኛ ድንኳንና ቤተ መቅደሱ የምን ጥላ ነበሩ?
ይሖዋ ጣዖታት እንዲኖሩ ያልፈቀደበት ቤተ መቅደስ አለው። ለዚህ ቤተ መቅደስ ሙሴ የሠራው የመገናኛ ድንኳንና በኋላም በኢየሩሳሌም የተሠራው ቤተ መቅደስ ጥላ ሆኖለታል። እነዚህ ሕንፃዎች ‘ለእውነተኛው ድንኳን’ ማለትም ለታላቁ የይሖዋ ቤተ መቅደስ ምሳሌ ነበሩ። (ዕብራውያን 8:1-5) ይህ ቤተ መቅደስ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መስዋዕት አማካኝነት ወደ አምላክ ቀርቦ እርሱን ለማምለክ የተደረገው ዝግጅት ነው።—ዕብራውያን 9:2-10, 23
2. በታላቁ የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንደ ዓምድ የሆኑት እነማን ናቸው? እጅግ ብዙ ሰዎችስ ምን ዓይነት ቦታ አላቸው?
2 እያንዳንዱ የተቀባ ክርስቲያን በሰማይ ቦታ አግኝቶ በአምላክ መቅደስ ውስጥ አንድ “ዓምድ” ይሆናል። “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉት የይሖዋ ሌሎች አምላኪዎች ደግሞ ሄሮድስ እንደገና በሠራው ቤተ መቅደስ ይገኝ በነበረው የአሕዛብ አደባባይ በተወከለው ሥፍራ ላይ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ። እነዚህ ሰዎች በኢየሱስ መስዋዕት በማመናቸው ምክንያት “ከታላቁ መከራ” የሚያሳልፋቸውን የጽድቅ አቋም አግኝተዋል።—ራእይ 3:12፤ 7:9-15
3, 4. በምድር ላይ ያሉትን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ያሰባሰበው ጉባኤ በምን ተመስሏል? ከምን ዓይነት እድፈትስ ራሱን ንጹሕ ማድረግ ይኖርበታል?
3 በምድር ላይ የሚገኙትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያሰባሰበው ጉባኤ ከጣዖት አምልኮ ከጸዳ ቤተ መቅደስ ጋር ተመሳስሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለእነዚህ በመንፈስ ቅዱስ የታተሙ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፣ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።” (ኤፌሶን 1:13፤ 2:20-22) እነዚህ 144,000 የታተሙ ሰዎች ለቅዱስ ክህነት የሚታነጸው መንፈሳዊ ቤት ሕያዋን ዓለቶች ናቸው—1 ጴጥሮስ 2:5፤ ራእይ 7:4፤ 14:1
4 እነዚህ የበታች ካህናት “የአምላክ ሕንፃ” ስለሆኑ ይሖዋ ይህ መቅደሱ እንዲረክስበት አይፈልግም። (1 ቆሮንቶስ 3:9, 16, 17) ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቋል:- “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው?” ሁሉን የሚችለው አምላክ የይሖዋ ንብረት የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከጣዖት የጸዱ መሆን ይኖርባቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:14-18) እጅግ ብዙ ሰዎች የተባሉትም ቢሆኑ ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ መራቅ ይኖርባቸዋል።
5. እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋ እርሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ እንደሆነ በመገንዘብ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
5 ግልጽና ስውር የሆነ ሁለት የጣዖት አምልኮ ዓይነት አለ። የጣዖት አምልኮ ወንድና ሴት የጣዖት አማልክትን ብቻ በማምለክ የተወሰነ አይደለም። ከይሖዋ ሌላ ማንንም ወይም ምንንም ነገር ማምለክ የጣዖት አምልኮ ነው። ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ እንደመሆኑ መጠን ለሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ መጠየቁ ተገቢ ነው። (ዘዳግም 4:24) እውነተኛ ክርስቲያኖችም ይህን ስለሚገነዘቡ ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ እንዲርቁ የሚያስጠነቅቋቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ይከተላሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:7) የይሖዋ አገልጋዮች ሊያስወግዱአቸው የሚገቡትን አንዳንድ የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች እንመልከት።
ለሕዝበ ክርስትና የጣዖት አምልኮ ጥላ የሆነ ድርጊት
6. ሕዝቅኤል በራእይ ምን ዓይነት አስጸያፊ ነገሮችን አየ?
6 ነቢዩ ሕዝቅኤል በባቢሎን ግዞተኛ ሆኖ በሚኖርበት ጊዜ በ612 ከዘአበ ከሃዲ አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም በሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ይፈጽሙአቸው ስለ ነበሩት አስጸያፊ ነገሮች ራእይ አይቶ ነበር። ሕዝቅኤል “ቅንዓት የሚያነሳሳ” ምስል ተመልክቶ ነበር። ሰባ ሽማግሌዎች በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያጥኑ ታይተዋል። ሴቶችም ለሐሰት አምላክ ሲያለቅሱ ታይተዋል። 25 ሰዎች ደግሞ ፀሐይን ሲያመልኩ ነበር። እነዚህ የክሕደት ድርጊቶች ምን ትርጉም ነበራቸው?
7, 8. “ቅንዓት የሚያነሳሳው” ምስል ምን ሊሆን ይችላል? እርሱስ ይሖዋን ለቅንዓት የሚያነሳሳው ለምንድን ነው?
7 ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው አስጸያፊ ነገር ለሕዝበ ክርስትና የጣዖት አምልኮ ጥላ ነው። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ብሏል:- “እነሆም፣ በመሰዊያው በር በሰሜን በኩል በመግቢያው ይህ የቅንዓት ጣዖት ነበረ። እርሱም [ይሖዋ አምላክም አዓት]:- የሰው ልጅ ሆይ፣ የሚያደርጉትን፣ ከመቅደሴም ያርቁኝ ዘንድ የእስራኤል ቤት በዚህ የሚያደርጉትን ታላቁን ርኩሰት ታያለህን? . . . አለኝ።”—ሕዝቅኤል 8:1-6
8 ይህ ቅንዓት የሚያነሳሳው የጣዖት ምስል ከነዓናውያን የአምላካቸው የባአል ሚስት ነች ብለው የሚያመልኩአት የሐሰት አምላክ ምሳሌ የሆነ ዓምድ ሊሆን ይችላል። ምስሉ ምንም ይሁን ምን እስራኤላውያን ለይሖዋ ብቻ ወስነው ማቅረብ የነበረባቸውን አምልኮ የሚከፋፍልባቸው ስለሆነ ይሖዋን ለቅንዓት አነሳስቶት ነበር፤ ምክንያቱም የሚከተለውንም ትእዛዝ እንዲጥሱ አድርጓቸዋል:- “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት ] አምላክህ እኔ ነኝ . . . ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም . . . እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት ] አምላክ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።”—ዘጸአት 20:2-5
9. ሕዝበ ክርስትና የአምላክን ቅንዓት ያነሳሳችው እንዴት ነው?
9 ቅንዓት የሚያነሳሳውን ምስል በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ አቁሞ ማምለክ ከሃዲዎቹ እስራኤላውያን ይፈጽሙአቸው ከነበሩት እጅግ በጣም አስጸያፊ ድርጊቶች አንዱ ነበር። በተመሳሳይም የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እናገለግለዋለን ለሚሉት አምላክ እናቀርባለን የሚሉትን ፍጹም አምልኮ በሚከፋፍሉና አምላክን በሚያዋርዱ ምስሎች ረክሰዋል። በተጨማሪም ቀሳውስቱ የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን ክደው “በቅዱሱ ስፍራ የቆመውን የጥፋት ርኩሰት” ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ስለሚያመልኩ ቅንዓቱን አነሳስተዋል።—ማቴዎስ 24:15, 16፤ ማርቆስ 13:14[4]
10. ሕዝቅኤል በቤተ መቅደስ ውስጥ ምን ተመለከተ? ይህስ በሕዝበ ክርስትና ከሚታየው ሆኔታ ጋር እንዴት ይመሳሰላል?
10 ሕዝቅኤል ወደ ቤተ መቅደሱ ከገባ በኋላ የሚከተለውን ሪፖርት አድርጓል:- “እነሆ፣ በግንቡ ዙሪያ ላይ የተንቀሳቃሾችና የርኩሳን አራዊት ምሳሌ የእስራኤልንም ቤት ጣዖታት ሁሉ ተስለው አየሁ። በፊታቸውም ከእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች ሰባ ሰዎች ቆመው ነበር፣ ሰውም ሁሉ እያንዳንዱ በእጁ ጥናውን ይዞ ነበር፣ የዕጣኑም ጢስ ሽቱ ይወጣ ነበር።” እስቲ ገምቱት! የእስራኤላውያን ሽማግሌዎች በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሆነው አስጸያፊ ለሆኑ በግድግዳ ላይ ለተሳሉ የሐሰት አማልክት ቅርጾች ዕጣን ሲያጥኑ ነበር። (ሕዝቅኤል 8:10–12) የሕዝበ ክርስትና አገሮችም ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የአዕዋፍና የአራዊቶችን ምስል ሠርተው ሕዝቦቻቸውን እንዲሰግዱ ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ ብዙ ቄሶች ፍጥረት ከይሖዋ አምላክ የተገኘ ነው የሚለውን እውነተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ከመደገፍ ይልቅ ሰው ከሰው በታች ከሆኑ የእንስሳት ሕይወት ተገኘ የሚለውን ስህተት የሆነውን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ በመደገፍ ብዙኃኑን የማሳሳት ወንጀል ሰርተዋል።—ሥራ 17:24-28
11. ከሐዲ እስራኤላውያን ሴቶች ለተሙዝ የሚያለቅሱት ለምን ነበር?
11 ሕዝቅኤል በይሖዋ ቤት መግቢያ ላይ ከሃዲ እስራኤላውያን ሴቶች ለተሙዝ ሲያለቅሱ ተመለከተ። (ሕዝቅኤል 8:13, 14) ባቢሎናውያንና ሶሪያውያን ተሙዝ በዝናብ ወራት በቅሎ በበጋ ወራት የሚሞት የዕጽዋት አምላክ እንደሆነ ያምኑ ነበር። የእጽዋቱ መሞት የተሙዝ አምላኪዎች በየዓመቱ ከፍተኛ የፀሐይ ትኩሳት ሲመጣ እያለቀሱ የሚያከብሩት የራሱን የተሙዝን ሞት ያመለክታል ብለው ያምኑ ነበር። የዝናቡ ወራት ገብቶ እጽዋት ሲያቆጠቁጡ ተሙዝ ከነበረበት ከታችኛው ዓለም ማለትም ከመቃብር መጣ ተብሎ ይታሰባል። የተሙዝ ምስል በግሪክኛ የስሙ የመጀመሪያ ፊደል የሆነው ታው (T) ነበረ። ይህም ፊደል መስቀል የሚመስል ቅርጽ ያለው ነው። ይህ ደግሞ ሕዝበ ክርስትና ለመስቀል የምትሰጠውን የቅድስና አምልኮ ያስታውሰናል።[6]
12. ሕዝቅኤል 25 ከሃዲ እስራኤላውያን ወንዶች ምን ሲያደርጉ ተመለከተ? በሕዝበ ክርስትና ውስጥስ ይህን የሚመስል ምን ድርጊት ይፈጸማል?
12 ሕዝቅኤል ቀጥሎ በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ አደባባይ ውስጥ 25 ከሃዲ እስራኤላውያን ወንዶች ፀሐይን ሲያመልኩ ተመለከተ። ይህም ይሖዋ ስለ ጣዖት አምልኮ የሰጠውን ትእዛዝ የሚጥስ ነበር። (ዘዳግም 4:15-19) በተጨማሪም እነዚህ ጣዖት አምላኪዎች አስነዋሪውን ቅርንጫፍ በእጃቸው ይዘው ወደ ይሖዋ ዘርግተው ነበር። ይህ አስነዋሪ ቅርንጫፍ የወንድን የመራቢያ ብልት የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። አምላክ ጸሎታቸውን አልሰማም ማለቱ አያስደንቅም። ሕዝበ ክርስትናም ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት አምላክ እንዲረዳት ብትጮህ በተመሳሳይ አይሰማትም። (ማቴዎስ 24:21) እነዚህ እስራኤላውያን ጀርባቸውን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ አዙረው ብርሃን ሰጪ የሆነችውን ፀሐይ እንዳመለኩ ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም ከአምላክ ለሚገኘው ብርሃን ጀርባዋን ሰጥታ የሐሰት ትምህርቶችን ታስተምራለች፤ ዓለማዊ ጥበቦችን ታመልካለች፤ የፆታ ብልግናንም እንዳላየች ሆና ታልፈዋለች።—ሕዝቅኤል 8:15-18
13. የይሖዋ ምስክሮች በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የታዩትን የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች የሚያስወግዱት በምን መንገዶች ነው?
13 የይሖዋ ምስክሮች ሕዝቅኤል አስቀድሞ የተመለከተውን በሕዝበ ክርስትና ወይም በምሳሌያዊቱ እስራኤል የሚፈጸመውን የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች ያስወግዳሉ። አምላክን የሚያዋርዱ ምስሎችን አናመልክም። ለመንግሥታዊ “የበላይ ባለሥልጣኖች” አክብሮት ብናሳይም እንኳ የምንገዛላቸው በገደብ ነው። (ሮሜ 13:1-7፤ ማርቆስ 12:17፤ ሥራ 5:29) ሙሉው ልባችን የተወሰነው ለአምላክና ለመንግሥቱ ነው። የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ ተቀብለን ፈጣሪንና ፍጥረቱን አንክድም። (ራእይ 4:11) መስቀልን፣ ወይም የከፍተኛ ትምህርትን፣ ፍልስፍናዎችን፣ ወይም ሌላ ዓይነት ዓለማዊ ጥበብን አናመልክም። (1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21) በተጨማሪም ከሌሎቹ የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች ሁሉ ራሳችንን እንጠብቃለን። እነዚህ ሌሎች የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች ምንድን ናቸው?
ሌሎች የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች
14. የይሖዋ አገልጋዮች በራእይ 13:1 የተጠቀሰውን “አውሬ” በተመለከተ ምን አቋም ይወስዳሉ?
14 ክርስቲያኖች ምሳሌያዊውን “አውሬ” በማምለክ ከቀረው የሰው ልጅ ጋር አይተባበሩም። ሐዋርያው ዮሐንስ:- “አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፣ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች . . . በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል” ብሏል። (ራእይ 13:1, 8) አራዊት “የነገሥታት” ወይም የፖለቲካ ባለሥልጣኖች ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። (ዳንኤል 7:17፤ 8:3-8, 20-25) ስለዚህ የምሳሌያዊው አውሬ ሰባት ራሶች የዓለምን ኃያል መንግሥታት ማለትም ግብጽን፣ አሦርን፣ ባቢሎንን፣ ሜዶ–ፋርስን፣ ግሪክን፣ ሮምንና የብሪታንያና የዩናይትድ ስቴትስ ጥምር የሆነውን የአንግሎ–አሜሪካ መንግሥት ያመለክታል። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የሰው ልጅ “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነውን የሰይጣንን ፖለቲካዊ ሥርዓት እንዲያመልክ በማድረጋቸው ለአምላክና ለክርስቶስ በከፍተኛ ሁኔታ ንቀት አሳይተዋል። (ዮሐንስ 12:31) የይሖዋ አገልጋዮች ግን ገለልተኛና የመንግሥቱ ጠበቆች እንደመሆናቸው መጠን እንዲህ ያለውን የጣዖት አምልኮ አይቀበሉም።—ያዕቆብ 1:27[8]
15. የይሖዋ ሕዝቦች ዓለማዊ የመዝናኛና የስፖርት ኮከቦችን እንዴት ይመለከታሉ? ይህን በተመለከተ አንድ ምስክር ምን አለ?
15 በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች የዓለም የመዝናኛና የስፖርት ኮከቦችን ከማምለክ ይርቃሉ። አንድ ሙዚቀኛ የይሖዋ ምስክር ከሆነ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ለመዝናኛና ለዳንስ የሚሰማ ሙዚቃ የተሳሳቱ ፍላጎቶችን ሊቀሰቅስ ይችላል። ዘፋኙ ብዙ አድማጮች የራሳቸው የትዳር ጓደኛ ይጎለዋል ብለው ስለሚያስቡት የደስታና የርኅራሄ ስሜት ይዘፍናል። አርቲስቱ አብዛኛውን ጊዜ በሚጫወተው ወይም በሚዘፍነው ሙዚቃ የተገለጸው ባሕርይ ያለው ዓይነት ሰው እንደሆነ ተደርጐ ይታሰባል። እኔ የማውቃቸው አንዳንድ የሙዚቃና የዘፈን ባለሞያዎች በዚህ የተነሳ በሴቶች ዘንድ ከፍ ያለ ተወዳጅነት አትርፈዋል። አንድ ሰው በዚህ የቅዠት ዓለም ከተዋጠ ዘፋኙን ወይም ሙዚቀኛውን ወደ ማምለክ ሊያደርሰው ይችላል። ይህ አምልኮ የሚጀምረው ምንም ጉዳት የሌለው በሚመስል ሁኔታ ነው። ግለሰቡ አንድ ሙዚቀኛ ስሙን ወይም ፊርማውን ለማስታወሻ ያህል እንዲጽፍለት ብቻ ሊጠይቀው ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች አርቲስቱን ሊከተሉት የሚገባ ምሳሌያቸው አድርገው ይመለከቱታል። ስለዚህ በከፍተኛ ደረጃ ላይ በማስቀመጥ እንደ ጣዖት ማክበር ይጀምራሉ። የዝነኛውን ሙዚቀኛ ፎቶግራፍ በግድግዳቸው ላይ መስቀል ወይም በአለባበስና በጸጉር አያያዝ እርሱን መምሰል ይጀምራሉ። ክርስቲያኖች ግን በላቀ ሁኔታ መከበርና መመለክ የሚገባው አምላክ ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ይገባቸዋል።”[9]
16. ጻድቅ የሆኑ መላእክት የጣዖት አምልኮን እንደማይቀበሉ የሚያመለክት ምን ማስረጃ አለ?
16 አዎ፣ የላቀ አክብሮትና አምልኮ የሚገባው አምላክ ብቻ ነው። ዮሐንስ አስደናቂ ነገሮችን ባሳየው መልአክ እግር ፊት ወድቆ ሊሰግድለት በጀመረ ጊዜ ይህ መንፈሳዊ ፍጡር በምንም ዓይነት እንደ ጣዖት እንዲመለክ ፈቃደኛ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ አለ:- “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ።” (ራእይ 22:8, 9) ይሖዋን ብቻ እንድናመልክ የሚገፋፋን ለእርሱ ያለን ፍርሐት ወይም የጠለቀ አክብሮት ነው። (ራእይ 14:7) ስለዚህ እውነተኛ የሆነ ለአምላክ የማደር አካሄድ ከጣዖት አምልኮ ይጠብቀናል። — 1 ጢሞቴዎስ 4:8
17. የጣዖት አምልኮን ያህል ከሆነ የፆታ ብልግና ራሳችንን ልንጠብቅ የምንችለው እንዴት ነው?
17 ሌላው የይሖዋ አገልጋዮች የሚርቁት የጣዖት አምልኮ ዓይነት የፆታ ብልግና ነው። የይሖዋ አገልጋዮች “አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኩስ ወይም የሚመኝ [ስግብግብ] እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት” እንደሌለው ያውቃሉ። (ኤፌሶን 5:5) ያልተፈቀደውን ዓይነት የፆታ ደስታን የሚፈልግ ሰው ለዚህ ፍላጎቱ ተገዥ ስለሚሆን የፆታ ርኩሰት የጣዖት አምልኮ ይሆንበታል። ተገቢ ያልሆኑ የፆታ ፍላጎቶች አምላካዊ ባሕሪያትን የማበላሸት አደጋ አላቸው። ዓይኖቹና ጆሮዎቹ ወደ ብልግና ስዕሎችና ፊልሞች እንዲያዘነብል በማድረጉ አንድ ሰው ቅዱስ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ጋር ሊኖረው የሚችለውን ዝምድና ሁሉ በአደጋ ላይ ይጥላል። (ኢሳይያስ 6:3) እንግዲያው የአምላክ አገልጋዮች ራሳቸውን እንዲህ ካለው የጣዖት አምልኮ ራሳቸውን ለመጠበቅ ከብልግና ጽሑፎችና ፊልሞች እንዲሁም ምግባረ ብልሹ ከሆኑ ሙዚቃዎች መራቅ አለባቸው። በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሰረተ ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ይዘው መጽናት ይኖርባቸዋል። “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና [ታማኝ ሆኖ መቆም አዓት] እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” መልበስ ይገባቸዋል።—ኤፌሶን 4:22-24[10]
ከስግብግብነትና ከመጐምጀት ራቁ
18, 19. (ሀ) ስግብግብነትና መጐምጀት ምንድን ናቸው? (ለ) የጣዖት አምልኮ ከሆኑት ስግብግብነትና መጐምጀት ራሳችንን ልንጠብቅ የምንችለው እንዴት ነው?
18 በተጨማሪም ክርስቲያኖች እርስ በእርስ የተሳሰሩ የጣዖት አምልኮ ዘርፍ ከሆኑት ከስግብግብነትና ከመጐምጀት ይርቃሉ። ስግብግብነት ተገቢ ያልሆነና ከመጠን ያለፈ ወይም በቃኝ ማለትን የማያውቅ ፍላጐት ሲሆን መጐምጀት ደግሞ የሌላ ሰው ንብረት የሆነውን ነገር መፈለግ ማለት ነው። ኢየሱስ ከመጐምጀት እንድንጠበቅ አስጠንቅቋል። ከፍተኛ የመጐምጀት ስሜት ስለነበረው ‘በአምላክ ዘንድ ባለጠጋ’ ያልነበረው ሰው በሞተ ጊዜ ሐብቱ ምንም ሊጠቅመው ስላልቻለው ሐብታም ተናግሯል። (ሉቃስ 12:15-21) ጳውሎስም የእምነት ባልደረቦቹን እንደሚከተለው ሲል መምከሩ ተገቢ ነበር:- “እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ . . . ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀትም ነው።”—ቆላስይስ 3:5[11]
19 ገንዘብን፣ ምግብን እና መጠጥ ወይም ስልጣንን በከፍተኛ ፍቅርና ምኞት የሚፈልጉ ሰዎች ይህን ምኞታቸውን እንደ ጣዖት ያመልካሉ። ጳውሎስ እንደገለጸው ስግብግብ የሆነ ሰው ጣዖት አምላኪ ስለሆነ የአምላክን መንግሥት አይወርስም። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ኤፌሶን 5:5) ስለዚህ ስግብግብ በመሆን ጣዖትን የሚያመልኩ የተጠመቁ ግለሰቦች ሁሉ ከክርስቲያን ጉባኤ ሊወገዱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚናገሩትን በሥራ ላይ በማዋልና ከልብ በመጸለይ የስግብግብነትን ዝንባሌ ልናስወግድ እንችላለን። ምሳሌ 30:7–9 “ሁለትን ነገር ከአንተ [ከይሖዋ አምላክ] እሻለሁ፣ ሳልሞትም አትከልክለኝ፤ ከንቱነትና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፤ ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፤ እንዳልጠግብ አንዳልክድህም:- እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ማን ነው? እንዳልል ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፣ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል” ይላል። እንዲህ ያለው መንፈስ የጣዖት አምልኮን ያህል ከሆነው ከስግብግብነትና ከመጐምጀት ሊጠብቀን ይችላል።
ራሳችሁን ከማምለክ ራቁ
20, 21. የይሖዋ ሕዝቦች ራሳቸውን ከማምለክ የሚጠበቁት እንዴት ነው?
20 በተጨማሪም የይሖዋ ሕዝቦች ራሳቸውን ከማምለክ ይርቃሉ። በዚህ ዓለም ውስጥ ራስንና የራስን ፈቃድ እንደ ጣዖት ማምለክ የተለመደ ነገር ነው። ለዝናና ለክብር ያላቻው ምኞት ብዙ ሰዎችን ጠማማ ድርጊት እንዲፈጽሙ ምክንያት ሆኖአቸዋል። የአምላክ ሳይሆን የራሳቸው ፈቃድ እንዲደረግ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ የራሳችንን ፈቃድ ለማስፈጸም ወይም ሌሎችን ለመግዛት በመፈለግ የተንኮል ድርጊት ብንፈጽም እና ራሳችንን እንደ ጣዖት አድርገን ማምለክ ብንጀምር ከአምላክ ጋር ዝምድና ሊኖረን አይችልም። (ምሳሌ 3:32፤ ማቴዎስ 20:20-28፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3) የኢየሱስ ተከታዮች እንደ መሆናችን መጠን የዓለምን የሸርና የተንኮል መንገድ ትተናል።—2 ቆሮንቶስ 4:1, 2
21 የአምላክ ሕዝቦች ስምና ዝና ከመፈለግ ይልቅ “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” የሚለውን የጳውሎስ ምክር ይከተላሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:31) የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን የታማኝና ልባም ባሪያ አመራር እየተቀበልንና ከይሖዋ ድርጅት ጋር ሙሉ በሙሉ እየተባበርን በደስታ መለኮታዊውን ፈቃድ እንፈጽማለን እንጂ ራሳችንን እንደ ጣዖት በማድረግ ሁልጊዜ የራሳችን መንገድ ብቻ ይፈጸም አንልም።—ማቴዎስ 24:45-47
ሁልጊዜ ራሳችሁን ጠብቁ!
22, 23. ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ራሳችንን ለመጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
22 የይሖዋ ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን በግዑዛን ጣዖታት ፊት ተንበርክከን አንሰግድም። በተጨማሪም በግልጽ ከማይታዩ ስውር የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች ራሳችንን እንጠብቃለን። ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ እንደራቅን መኖር አለብን። በዚህ መንገድ “ራሳችሁን ከጣዖታት ጠብቁ” ከሚለው የዮሐንስ ምክር ጋር ተስማምተን እንኖራለን።—1 ዮሐንስ 5:21
23 ከይሖዋ አገልጋዮች አንዱ ከሆንክ በማንኛውም ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነውን ሕሊናህንና የማስተዋል ኃይልህን አሠራው። (ዕብራውያን 5:14) እንዲህ ካደረግህ በዚህ ዓለም የጣዖት አምልኮ መንፈስ አትበከልም። እንደ ሦስቱ ታማኝ ዕብራውያንና እንደ መጀመሪያዎቹ ታማኝ ክርስቲያኖች ትሆናለህ። ለይሖዋ የተወሰነውን አምልኮ ለእርሱ ብቻ ትሰጣለህ። እርሱም ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ርቀህ እንድትኖር ይረዳሃል።
ምን ሐሳብ ትሰጣለህ?
◻ የይሖዋ ምስክሮች በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ ከታዩት የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች የሚርቁት እንዴት ነው?
◻ በራእይ 13:1 የተጠቀሰው “አውሬ” ምንድን ነው? አውሬውን በተመለከተስ የይሖዋ አገልጋዮች ምን አቋም ይወስዳሉ?
◻ የመዝናኛንና የስፖርት ኮከቦችን እንደ ጣዖት ከማምለክ መጠበቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
◻ ራስን እንደ ጣዖት ከማምለክ ልንጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ እንደራቅን መቀጠል የሚገባን ለምንድን ነው?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የታዩት አስጸያፊ ነገሮች ለሕዝበ ክርስትና የጣዖት አምልኮ እንዴት ጥላ እንደሆኑ ታውቃለህን?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Artwork (upper left) based on photo by Ralph Crane/Bardo Museum