ምዕራፍ 8
“አንድ እረኛ . . . አስነሳለሁ”
ፍሬ ሐሳብ፦ ስለ መሲሑ የሚናገሩ አራት ትንቢቶች በክርስቶስ ላይ ፍጻሜያቸውን ያገኙበት መንገድ
1-3. ሕዝቅኤል ልቡ እጅግ ያዘነው ለምን ነበር? ይሖዋስ ምን ትንቢት እንዲናገር አነሳሳው?
ሕዝቅኤል በግዞት ከተወሰደ ስድስተኛ ዓመቱን ይዟል።a ነቢዩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው በሚወዳት የትውልድ አገሩ በይሁዳ ያለውን የአገዛዝ ሁኔታ ሲያስብ ልቡ እጅግ ያዝናል። ሕዝቅኤል የተለያዩ ነገሥታት ሥልጣን ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ተመልክቷል።
2 ሕዝቅኤል የተወለደው በታማኙ ንጉሥ ኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት አጋማሽ ላይ ነው። ሕዝቅኤል፣ ንጉሥ ኢዮስያስ የተቀረጹ ምስሎችን ለማጥፋትና በይሁዳ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንዲቋቋም ለማድረግ ያካሄደውን ዘመቻ ሲያውቅ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት። (2 ዜና 34:1-8) ይሁን እንጂ በኋላ የተነሱት አብዛኞቹ ነገሥታት ጣዖት አምላኪዎች ስለነበሩ ኢዮስያስ ያካሄደው ተሃድሶ ዘላቂ የሆነ ለውጥ አላመጣም። ብሔሩ እንደነዚህ ባሉት መጥፎ ገዢዎች ሥር በነበረበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባር ተበከለ። ታዲያ ሁኔታው ምንም ተስፋ የለውም ማለት ነው? በፍጹም!
3 ይሖዋ ታማኙን ነቢይ በመንፈሱ በመምራት ስለ መሲሑ ማለትም ንጹሕ አምልኮን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልሶ ስለሚያቋቁመው እንዲሁም የይሖዋን በጎች በርኅራኄ ስለሚንከባከበው እረኛና ገዢ ትንቢቶች እንዲናገር አድርጓል። የእነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜ ከዘላለም ሕይወት ተስፋችን ጋር ግንኙነት ያለው በመሆኑ እነዚህን ትንቢቶች በጥንቃቄ መመርመራችን ጠቃሚ ነው። እስቲ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ስለ መሲሑ የሚናገሩ አራት ትንቢቶች እንመርምር።
አንድ “ቀንበጥ” “የሚያምር አርዘ ሊባኖስ” ሆነ
4. ሕዝቅኤል የትኛውን ትንቢት ተናገረ? ሆኖም ይሖዋ ሕዝቅኤል ይህን ትንቢት ከመናገሩ በፊት ምን እንዲናገር አደረገ?
4 በ612 ዓ.ዓ. ገደማ “የይሖዋ ቃል” ወደ ሕዝቅኤል መጣ፤ ከዚያም ሕዝቅኤል የመሲሑን ግዛት ስፋትና በመሲሐዊው መንግሥት መታመን አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት የሚገልጽ ትንቢት ተናገረ። ሆኖም ይሖዋ፣ ሕዝቅኤል ይህን ትንቢት ከመናገሩ በፊት የይሁዳን ገዢዎች ከሃዲነት የሚያሳይና ጻድቅ የሆነ መሲሐዊ ገዢ መነሳቱ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት የሚያጎላ ትንቢታዊ እንቆቅልሽ በግዞት ላይ ላሉት ወገኖቹ እንዲናገር አደረገ።—ሕዝ. 17:1, 2
5. እንቆቅልሹ ምንድን ነው?
5 ሕዝቅኤል 17:3-10ን አንብብ። እንቆቅልሹ የሚከተለው ነው፦ አንድ “ታላቅ ንስር” በአንድ አርዘ ሊባኖስ ‘አናት ላይ ያለውን ቀንበጥ’ ቀጥፎ ‘በነጋዴዎች ከተማ ተከለው።’ ከዚያም ንስሩ “ከምድሪቱ ዘር የተወሰነውን ወስዶ” “ብዙ ውኃ ባለበት” ለም የሆነ መሬት ላይ ዘራው። ዘሩ በቀለና አድጎ ‘የተንሰራፋ የወይን ተክል’ ሆነ። ቀጥሎ ደግሞ ሌላ “ታላቅ ንስር” ብቅ አለ። የወይን ተክሉም ብዙ ውኃ ባለበት ሌላ መሬት ላይ መተከል ስለፈለገ “በታላቅ ጉጉት” ሥሮቹን ወደ ሁለተኛው ንስር ዘረጋ። ይሖዋ ሥሮቹ ተነቅለው እንደሚጣሉና ‘ሙሉ በሙሉ እንደሚደርቁ’ በመግለጽ የወይን ተክሉን ድርጊት አወገዘ።
6. የእንቆቅልሹን ፍቺ ተናገር።
6 የእንቆቅልሹ ፍቺ ምንድን ነው? (ሕዝቅኤል 17:11-15ን አንብብ።) በ617 ዓ.ዓ. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር (የመጀመሪያው “ታላቅ ንስር”) ኢየሩሳሌምን ከበበ። ከዚያም የይሁዳ ንጉሥ የነበረውን ንጉሥ ዮአኪንን (‘አናት ላይ ያለውን ቀንበጥ’) ከዙፋኑ አንስቶ ወደ ባቢሎን (‘የነጋዴዎች ከተማ’) ወሰደው። ናቡከደነጾር ሴዴቅያስን (ከምድሪቱ ንጉሣዊ ዘር አንዱን) ወስዶ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ዙፋን ላይ አስቀመጠው። አዲሱ የይሁዳ ንጉሥ ታማኝ ገባር ንጉሥ ለመሆን በአምላክ ስም እንዲምል ተደርጎ ነበር። (2 ዜና 36:13) ሴዴቅያስ ግን መሐላውን ንቆ በባቢሎን ንጉሥ ላይ በማመፅ የግብፁ ንጉሥ ፈርዖን (ሁለተኛው “ታላቅ ንስር”) ወታደራዊ እርዳታ እንዲሰጠው ጠየቀ፤ ሆኖም ያሰበው አልተሳካለትም። ይሖዋ ሴዴቅያስ መሐላውን በማፍረስ የፈጸመውን ክህደት አውግዟል። (ሕዝ. 17:16-21) በመጨረሻም ሴዴቅያስ ከዙፋኑ እንዲወርድ የተደረገ ሲሆን በባቢሎን እስር ቤት ውስጥ እያለ ሞተ።—ኤር. 52:6-11
7. ከትንቢታዊው እንቆቅልሽ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
7 ከዚህ ትንቢታዊ እንቆቅልሽ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ በንጹሕ አምልኮ የምንካፈል እንደመሆናችን መጠን ቃላችንን የማክበር ግዴታ አለብን። ኢየሱስ “ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን” ብሏል። (ማቴ. 5:37) በፍርድ ቤት ቆመን ስንመሠክርም ሆነ ሌላ ሁኔታ አጋጥሞን እውነቱን እንደምንናገር በአምላክ ስም መማል ካስፈለገን እንዲህ ያለውን ቃለ መሐላ አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እምነት የምንጥለው በማን ላይ እንደሆነ በጥንቃቄ ልናስብበት ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “በመኳንንትም ሆነ ማዳን በማይችሉ ሰዎች አትታመኑ” በማለት ይናገራል።—መዝ. 146:3
8-10. ይሖዋ መሲሐዊውን ገዢ የገለጸው እንዴት ነው? ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነው? (“ስለ መሲሑ የሚናገር ትንቢት—የሚያምር የአርዘ ሊባኖስ ዛፍ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
8 ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ ልንተማመንበትና ልንመካበት የምንችል አንድ ገዢ አለ። ይሖዋ ተቀንጥሶ ስለተተከለው ቀንበጥ የሚገልጸውን ትንቢታዊ እንቆቅልሽ ከተናገረ በኋላ ተመሳሳይ የሆነ ዘይቤያዊ አነጋገር በመጠቀም ወደፊት ስለሚነሳው መሲሐዊ ገዢ ገለጸ።
9 ትንቢቱ ምን ይላል? (ሕዝቅኤል 17:22-24ን አንብብ።) አሁን እርምጃ የሚወስዱት ታላላቆቹ ንስሮች ሳይሆኑ ይሖዋ ራሱ ነው። ይሖዋ “ከረጅሙ አርዘ ሊባኖስ ጫፍ ላይ” ቀንበጥ ቀጥፎ “ረጅምና ግዙፍ በሆነ ተራራ ላይ” ይተክለዋል። ይህ ቀንበጥ አድጎ በመንሰራፋት “የሚያምር አርዘ ሊባኖስ ይሆናል። በሥሩም የወፍ ዓይነቶች ሁሉ ይኖራሉ።” በዚያ ጊዜ “የዱር ዛፎች ሁሉ” ይህ የሚያምር ዛፍ እንዲንሰራፋ ያደረገው ይሖዋ ራሱ እንደሆነ ያውቃሉ።
10 ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ይሖዋ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ከዳዊት ንጉሣዊ ዘር (‘ከረጅሙ አርዘ ሊባኖስ’) ላይ ቀጥፎ በሰማያዊቷ የጽዮን ተራራ (‘ረጅምና ግዙፍ በሆነው ተራራ’) ላይ ተከለው። (መዝ. 2:6፤ ኤር. 23:5፤ ራእይ 14:1) በዚህ መንገድ ይሖዋ፣ በጠላቶቹ ዘንድ “ከሰዎች ሁሉ የተናቀ” ተደርጎ የተቆጠረውን ልጁን “የአባቱን የዳዊትን ዙፋን” በመስጠት ከፍ ከፍ አድርጎታል። (ዳን. 4:17፤ ሉቃስ 1:32, 33) መሲሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ታላቅ አርዘ ሊባኖስ በመላው ምድር ላይ በመንሰራፋት ለተገዢዎቹ በሙሉ የበረከት ምንጭ ይሆንላቸዋል። በእርግጥም ልንተማመንበት የሚገባው ገዢ እሱ ነው። በኢየሱስ ንጉሣዊ አገዛዝ ጥላ ሥር በመላው ምድር የሚኖሩ ታዛዥ የሰው ልጆች “መከራ ይደርስብኛል የሚል ስጋት” ሳያድርባቸው ‘ተረጋግተው ይኖራሉ።’—ምሳሌ 1:33
11. አድጎ “የሚያምር አርዘ ሊባኖስ” ስለሆነው “ቀንበጥ” ከሚናገረው ትንቢት ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?
11 ከዚህ ትንቢት ምን ትምህርት እናገኛለን? አድጎ “የሚያምር አርዘ ሊባኖስ” ስለሆነው “ቀንበጥ” የተነገረው ይህ ትንቢት ‘እምነታችንን መጣል ያለብን በማን ላይ ነው?’ ለሚለው በጣም አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ መልስ እንድናገኝ ያስችለናል። በሰብዓዊ መንግሥታትና በወታደራዊ ኃይላቸው መታመን ሞኝነት ነው። ያለምንም ስጋት መኖር የምንችለው፣ ሙሉ እምነታችንን በመሲሐዊው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ከጣልን ብቻ ነው። የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ ከፍተኛ ብቃት ባለው በኢየሱስ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ነው።—ራእይ 11:15
“ሕጋዊ መብት ያለው”
12. ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንዳላፈረሰ ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው?
12 ሕዝቅኤል ስለ ሁለቱ ንስሮች የሚገልጸውን ትንቢታዊ እንቆቅልሽ በተመለከተ የተሰጠው መለኮታዊ ማብራሪያ፣ ከዳዊት ንጉሣዊ ዘር የተገኘውና ከሃዲ የሆነው ሴዴቅያስ ከዙፋኑ እንዲወርድ ተደርጎ ወደ ባቢሎን በግዞት እንደሚወሰድ አስገንዝቦታል። በመሆኑም ነቢዩ ‘ታዲያ ከዳዊት ዘር የሆነ አንድ ንጉሥ ለዘላለም እንደሚገዛ የሚገልጸው አምላክ ለዳዊት የገባለት ቃል ኪዳን ምን ሊሆን ነው?’ ብሎ አስቦ ይሆናል። (2 ሳሙ. 7:12, 16) ሕዝቅኤል ይህ ጥያቄ አሳስቦት ከነበረ መልሱን ለማግኘት ብዙ መጠበቅ አላስፈለገውም። በሰባተኛው የግዞት ዓመት ማለትም በ611 ዓ.ዓ. ገደማ ሴዴቅያስ ገና በይሁዳ ላይ እየገዛ ሳለ ‘የይሖዋ ቃል ወደ ሕዝቅኤል መጣ።’ (ሕዝ. 20:2) ይሖዋ ሕዝቅኤልን፣ ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንዳልተወ ግልጽ የሚያደርግ ሌላ መሲሐዊ ትንቢት እንዲናገር አደረገው። ትንቢቱ ወደፊት የሚነሳው መሲሐዊ ገዢ የዳዊት ወራሽ ሆኖ የመግዛት ሕጋዊ መብት እንደሚኖረው የሚያመለክት ነው።
13, 14. በሕዝቅኤል 21:25-27 ላይ የተመዘገበው ትንቢት ምንድን ነው? ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነው?
13 ትንቢቱ ምን ይላል? (ሕዝቅኤል 21:25-27ን አንብብ።) ይሖዋ፣ የቅጣት ጊዜው ለደረሰበት “መጥፎው የእስራኤል አለቃ” በሕዝቅኤል በኩል የማያሻማ መልእክት አስተላለፈ። ይሖዋ ለዚህ ክፉ ገዢ “ጥምጥሙ” እና “አክሊሉ” ወይም ዘውዱ (ንጉሣዊ ሥልጣንን የሚወክሉ ምልክቶች) እንደሚወሰዱበት ነገረው። ከዚያ በኋላ፣ “ዝቅ” ብለው የነበሩ ገዢዎች ከፍ ይደረጋሉ፤ “ከፍ” ብለው የነበሩት ደግሞ ዝቅ ይደረጋሉ። ከፍ የተደረጉት ገዢዎች ሥልጣን ላይ የሚቆዩት “ሕጋዊ መብት ያለው” እስኪመጣ ድረስ ብቻ ነው፤ እሱ ከመጣ በኋላ ግን ይሖዋ መንግሥቱን ለእሱ ይሰጠዋል።
14 ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ኢየሩሳሌምን ማዕከሉ ያደረገው “ከፍ” ያለው የይሁዳ መንግሥት፣ በ607 ዓ.ዓ. ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን አውድመው ንጉሥ ሴዴቅያስን ከዙፋኑ ባወረዱበት ጊዜ ዝቅ ተደርጓል። ከዚያ በኋላ በኢየሩሳሌም ሆኖ የሚገዛ ከዳዊት ንጉሣዊ ዘር የመጣ ንጉሥ ስለሌለ “ዝቅ” ብለው የነበሩት የአሕዛብ መንግሥታት ከፍ ብለው መላዋን ምድር መቆጣጠር ጀመሩ፤ በዚህ መንገድ የሚገዙት ግን ለተወሰነ ጊዜ ያህል ብቻ ነው። ይሖዋ በ1914 ኢየሱስ ክርስቶስን ንጉሥ አድርጎ ሲሾመው “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” አበቁ። (ሉቃስ 21:24) ኢየሱስ የንጉሥ ዳዊት ዘር እንደመሆኑ መጠን መሲሐዊውን መንግሥት የመረከብ “ሕጋዊ መብት” አለው።b (ዘፍ. 49:10) በዚህ መንገድ ይሖዋ ዘላለማዊ በሆነው መንግሥት ላይ በዘላቂነት የሚገዛ ወራሽ እንደሚሰጠው ለዳዊት የገባውን ቃል በኢየሱስ አማካኝነት ፈጽሟል።—ሉቃስ 1:32, 33
15. በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሙሉ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው?
15 ከዚህ ትንቢት ምን ትምህርት እናገኛለን? በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሙሉ እምነት መጣል እንችላለን። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ በሰዎች ተመርጠው ወይም በጉልበታቸው ሥልጣን ከሚይዙ ሰብዓዊ ገዢዎች በተለየ መልኩ በይሖዋ በቀጥታ የተመረጠ ከመሆኑም ሌላ ይህን “መንግሥት” የመቀበል ሕጋዊ መብት አለው። (ዳን. 7:13, 14) በእርግጥም ኢየሱስ፣ ይሖዋ ራሱ የሾመልን ንጉሥ በመሆኑ ልንተማመንበት እንችላለን!
‘አገልጋዬ ዳዊት እረኛቸው ይሆናል’
16. ይሖዋ ስለ በጎቹ ምን ይሰማዋል? በሕዝቅኤል ዘመን የነበሩት “የእስራኤል እረኞች” መንጋውን የሚይዙት በምን መንገድ ነበር?
16 ታላቁ እረኛ ይሖዋ ለበጎቹ ማለትም በምድር ላይ ላሉ አምላኪዎቹ ከልቡ ያስባል። (መዝ. 100:3) በመሆኑም ሰዎችን የበታች እረኞች አድርጎ በመሾም በጎቹን ለእነሱ በአደራ በሚሰጥበት ጊዜ በጎቹን የሚይዙበትን መንገድ በቅርበት ይከታተላል። ስለዚህ ይሖዋ በሕዝቅኤል ዘመን የነበሩትን “የእስራኤል እረኞች” ሲያይ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ። እነዚህ ኀፍረተ ቢስ መሪዎች ሕዝቡን “በጭካኔና በግፍ” ይገዙ ነበር። በዚህም ምክንያት መንጋው የተሠቃየ ሲሆን ከሕዝቡ መካከል ብዙዎቹ ከንጹሕ አምልኮ ራቁ።—ሕዝ. 34:1-6
17. ይሖዋ በጎቹን ያስጣለው እንዴት ነው?
17 ታዲያ ይሖዋ ምን ያደርግ ይሆን? ጨካኞቹን የእስራኤል ገዢዎች ‘ስለ በጎቹ እንደሚጠይቃቸው’ ተናግሯል። በተጨማሪም “በጎቼን ከአፋቸው አስጥላለሁ” ሲል ቃል ገብቷል። (ሕዝ. 34:10) ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን ይጠብቃል። (ኢያሱ 21:45) በ607 ዓ.ዓ. ባቢሎናውያንን ተጠቅሞ የእነዚህን ራስ ወዳድ እረኞች ሥልጣን በመግፈፍ በጎቹን አስጥሏል። ከሰባ ዓመት በኋላ ደግሞ በግ መሰል አምላኪዎቹን ከባቢሎን በማውጣት እውነተኛውን አምልኮ መልሰው እንዲያቋቁሙ ወደ ትውልድ አገራቸው መልሷቸዋል። ይሁን እንጂ የይሖዋ በጎች አሁንም በአሕዛብ መንግሥታት ሥር ስለሚሆኑ ለጥቃት የተጋለጡ መሆናቸው አልቀረም። “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” ገና ለብዙ መቶ ዓመታት ይቀጥላሉ።—ሉቃስ 21:24
18, 19. ሕዝቅኤል በ606 ዓ.ዓ. የትኛውን ትንቢት ተናገረ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
18 ኢየሩሳሌም ከጠፋች ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላና እስራኤላውያን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ከመውጣታቸው ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት በ606 ዓ.ዓ. ታላቁ እረኛ ይሖዋ ስለ በጎቹ ዘላለማዊ ደህንነት ምን ያህል እንደሚያስብ የሚያሳይ ትንቢት እንዲናገር ሕዝቅኤልን በመንፈሱ አነሳሳው። ይህ ትንቢት መሲሐዊው ገዢ የይሖዋን በጎች እንዴት እንደሚንከባከብ ይገልጻል።
19 ትንቢቱ ምን ይላል? (ሕዝቅኤል 34:22-24ን አንብብ።) አምላክ “አገልጋዬ ዳዊት” ብሎ የሚጠራውን “አንድ እረኛ” ያስነሳል። “አንድ እረኛ” የሚለው አገላለጽ እንዲሁም “አገልጋዬ” የሚለው ቃል በነጠላ ቁጥር መቀመጡ፣ ይህ ገዢ የሚያመለክተው የዳዊት ዘር የሆኑ ነገሥታት የሚፈራረቁበትን ሥርወ መንግሥት ሳይሆን በዘላቂነት የዳዊት ወራሽ የሚሆንን አንድ ግለሰብ እንደሆነ ይጠቁማል። እረኛ የሆነው ገዢ የአምላክን በጎች ይመግባል፤ እንዲሁም “በመካከላቸው አለቃ ይሆናል።” ይሖዋ ከበጎቹ ጋር “የሰላም ቃል ኪዳን” ይገባል። በጎቹ “በረከት እንደ ዝናብ” ይወርድላቸዋል፤ ያለአንዳች ሥጋት በደስታ ይኖራሉ፤ ሕይወታቸውም ብልጽግና የሞላበት ይሆናል። በሰዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በሰዎችና በእንስሳት መካከልም ሰላም ይሰፍናል።—ሕዝ. 34:25-28
20, 21. (ሀ) “አገልጋዬ ዳዊት” ተብሎ ስለተጠራው ገዢ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) ስለ “ሰላም ቃል ኪዳን” የሚናገረው የሕዝቅኤል ትንቢት ወደፊት ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?
20 ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? አምላክ ይህን ገዢ “አገልጋዬ ዳዊት” ብሎ የጠራው፣ የዳዊት ዘር የሆነውንና የመግዛት መብት ያለውን ኢየሱስን ትንቢታዊ በሆነ መንገድ ለማመልከት ነው። (መዝ. 89:35, 36) ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ሕይወቱን ‘ለበጎቹ ሲል አሳልፎ በመስጠት’ “ጥሩ እረኛ” መሆኑን አሳይቷል። (ዮሐ. 10:14, 15) አሁን ደግሞ በሰማይ የሚገኝ እረኛ ነው። (ዕብ. 13:20) አምላክ በ1914 ኢየሱስን በማንገሥ በምድር ላይ ያሉትን የአምላክ በጎች የመጠበቅና የመመገብ ኃላፊነት ሰጥቶታል። አዲሱ ንጉሥ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በ1919 ‘ቤተሰቦቹን’ ማለትም ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የሚመግብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሾመ። (ማቴ. 24:45-47) በክርስቶስ አመራር ሥር ያለው ታማኝ ባሪያ የአምላክን በጎች ጥሩ አድርጎ መንፈሳዊ ምግብ ሲመግብ ቆይቷል። ይህ መንፈሳዊ ምግብ የአምላክ በጎች በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ በሚገኘው መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።
21 ሕዝቅኤል ስለ “ሰላም ቃል ኪዳን” እና እንደ ዝናብ ስለሚወርድ በረከት የተናገረው ሐሳብ ወደፊት ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? ምድር ላይ የሚኖሩ ንጹሕ አምልኮን የሚያራምዱ የይሖዋ አገልጋዮች በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ “የሰላም ቃል ኪዳን” የሚያስገኛቸውን በረከቶች ሙሉ በሙሉ ማጣጣም ይችላሉ። መላዋ ምድር ቃል በቃል ገነት በምትሆንበት ጊዜ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከጦርነት፣ ከወንጀል፣ ከረሃብ፣ ከበሽታ ወይም የአራዊት ጥቃት ይደርስብናል ከሚል ስጋት ሙሉ በሙሉ ነፃ ይሆናሉ። (ኢሳ. 11:6-9፤ 35:5, 6፤ 65:21-23) የአምላክ በጎች ‘ያለስጋት በሚኖሩበትና ምንም የሚያስፈራቸው ነገር በማይኖርበት’ ገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለህ ስታስብ ደስታ አይሰማህም?—ሕዝ. 34:28
22. ኢየሱስ ስለ አምላክ በጎች ምን ይሰማዋል? የበታች እረኞች የሆኑ ወንድሞችስ የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
22 ከዚህ ትንቢት ምን ትምህርት እናገኛለን? ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ የበጎቹ ደህንነት በጣም ያሳስበዋል። እረኛ የሆነው ንጉሡ ኢየሱስ የአባቱ በጎች ጥሩ መንፈሳዊ ምግብ መመገባቸውንና በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ሰላምና ደህንነት ማግኘታቸውን ይከታተላል። እንዲህ ባለው ገዢ እንክብካቤ ሥር መኖር እንዴት የሚያስደስት ነው! የበታች እረኞች ሆነው የሚያገለግሉ ሁሉ ልክ እንደ ኢየሱስ ለአምላክ በጎች ከልብ ማሰብ አለባቸው። ሽማግሌዎች የአምላክን መንጋ ‘በፈቃደኝነትና በጉጉት’ መጠበቅ እንዲሁም ለበጎቹ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል። (1 ጴጥ. 5:2, 3) የትኛውም ሽማግሌ የይሖዋን በጎች መበደል እንደማይፈልግ የታወቀ ነው! ይሖዋ በሕዝቅኤል ዘመን የነበሩትን ጨካኝ የእስራኤል እረኞች በተመለከተ የተናገረውን አስታውስ፤ “ስለ በጎቼ እጠይቃቸዋለሁ” ብሏል። (ሕዝ. 34:10) ታላቁ እረኛ ይሖዋ በጎቹ በምን መንገድ እንደተያዙ በቅርበት ይከታተላል፤ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስም ቢሆን ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል።
“አገልጋዬም ዳዊት ለዘላለም አለቃቸው ይሆናል”
23. ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር አንድ ስለማድረግ ምን ቃል ገባ? ይህን ቃሉን የፈጸመውስ እንዴት ነው?
23 ይሖዋ አምላኪዎቹ አንድ ሆነው በኅብረት እንዲያገለግሉት ይፈልጋል። አምላክ ስለ መልሶ መቋቋም በሚናገር አንድ ትንቢት ላይ ሁለት “በትሮች” በእጁ ውስጥ አንድ “በትር” እንደሚሆኑ ገልጿል፤ ይህም ሁለቱን ነገዶች ካቀፈው የይሁዳ መንግሥትም ሆነ አሥሩን ነገዶች ካቀፈው የእስራኤል መንግሥት የተውጣጡ ሕዝቦቹን ሰብስቦ “አንድ ብሔር” እንደሚያደርጋቸው ያመለክታል። (ሕዝ. 37:15-23) አምላክ “አንድ” የሆነውን የእስራኤል ብሔር በ537 ዓ.ዓ. በተስፋይቱ ምድር ውስጥ መልሶ በማቋቋም ይህ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል።c ይሁን እንጂ ይህ አንድነት ወደፊት ለሚመጣው ታላቅና ዘላቂ የሆነ አንድነት እንደ ቅምሻ ብቻ ነው። ይሖዋ እስራኤልን አንድ እንደሚያደርግ ቃል ከገባ በኋላ ወደፊት የሚነሳው ገዢ በመላው ምድር የሚገኙ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችን እንዴት ዘላለማዊ በሆነ የአንድነት ማሰሪያ አንድ እንደሚያደርጋቸው የሚገልጽ ትንቢት እንዲናገር ሕዝቅኤልን አዘዘው።
24. ይሖዋ መሲሐዊውን ገዢ የገለጸው እንዴት ነው? የዚህ ንጉሥ አገዛዝ ምን ይመስላል?
24 ትንቢቱ ምን ይላል? (ሕዝቅኤል 37:24-28ን አንብብ።) ይሖዋ በድጋሚ መሲሐዊውን ገዢ “አገልጋዬ ዳዊት”፣ “አንድ እረኛ” እና “አለቃ” ሲል ጠርቶታል፤ ሆኖም ይሖዋ በዚህ ትንቢት ላይ ይህን ገዢ ‘ንጉሥ’ በማለትም ጠርቶታል። (ሕዝ. 37:22) የዚህ ንጉሥ አገዛዝ ምን ይመስላል? አገዛዙ ዘላቂ ይሆናል። በትንቢቱ ውስጥ “ዘላለም” የሚለው ቃል በተደጋጋሚ መጠቀሱ የንጉሡ አገዛዝ የሚያስገኛቸው በረከቶች ማብቂያ እንደማይኖራቸው ያመለክታል።d በእሱ አገዛዝ ሥር አንድነት ይሰፍናል። ታማኝ ተገዢዎቹ ‘በአንድ ንጉሥ’ ሥር፣ አንድ ዓይነት ‘ድንጋጌዎችን’ አክብረው በተሰጣቸው “ምድር” ላይ በአንድነት ይኖራሉ። የንጉሡ አገዛዝ ተገዢዎቹን ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንዲቀርቡ ያደርጋቸዋል። ይሖዋ ከእነዚህ ተገዢዎች ጋር “የሰላም ቃል ኪዳን” ይገባል። ይሖዋ አምላካቸው ይሆናል፣ እነሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። ‘መቅደሱም ለዘላለም በመካከላቸው ይሆናል።’
25. ስለ መሲሐዊው ንጉሥ የሚናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
25 ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? በ1919 ታማኝ ቅቡዓን ‘በአንዱ እረኛቸው’ በመሲሐዊው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር አንድ ሆነዋል። ቆየት ብሎ ደግሞ “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ” “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ከቅቡዓን የእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር አንድ ሆኑ። (ራእይ 7:9) ሁለቱም ቡድኖች ‘በአንድ እረኛ’ የሚመራ “አንድ መንጋ” ሆነዋል። (ዮሐ. 10:16) ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ የይሖዋን ድንጋጌዎች አክብረው ይመላለሳሉ። በዚህም ምክንያት አንድነት ያለው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር አባል በመሆን በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ አብረው ይኖራሉ። ይሖዋ ሰላም በመስጠት የባረካቸው ከመሆኑም ሌላ ንጹሕ አምልኮን የሚወክለው መቅደሱ በመካከላቸው ነው። ይሖዋ አምላካቸው ነው፤ እነሱም አሁንም ሆነ ለዘላለም የእሱ አምላኪዎች በመሆናቸው ኩራት ይሰማቸዋል!
26. በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ላለው አንድነት የበኩልህን አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችለው እንዴት ነው?
26 ከዚህ ትንቢት ምን ትምህርት እናገኛለን? በይሖዋ ንጹሕ አምልኮ በሚካፈል ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ መታቀፋችን ትልቅ መብት ነው። ይህ መብት ግን ኃላፊነትም ያስከትላል፤ ለአንድነቱ አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅብናል። በመሆኑም ሁላችንም በእምነትም ሆነ በምግባር ያለን አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። (1 ቆሮ. 1:10) ለዚህም ሲባል አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ እንመገባለን፤ አንድ ዓይነት ቅዱስ ጽሑፋዊ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ጠብቀን እንኖራለን እንዲሁም አስፈላጊ በሆነው የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ በአንድነት እንካፈላለን። ይሁን እንጂ ለአንድነታችን አስተዋጽኦ የሚያደርገው ዋናው ቁልፍ ነገር ፍቅር ነው። የፍቅር ገጽታዎች የሆኑትን እንደ ርኅራኄ፣ ይቅር ባይነትና የሌላውን ስሜት መረዳት ያሉ ባሕርያት ስናዳብርና ስናንጸባርቅ ለአንድነታችን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው” ይላል።—ቆላ. 3:12-14፤ 1 ቆሮ. 13:4-7
27. (ሀ) በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኙት ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶች ምን ይሰማሃል? (ለ) በቀጣዮቹ ምዕራፎች ውስጥ ምን እንመረምራለን?
27 ይሖዋ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ስለ መሲሑ የሚናገሩ ትንቢቶች በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩልን ስላደረገ ምንኛ አመስጋኞች ነን! እነዚህን ትንቢቶች ማንበባችንና በእነዚህ ትንቢቶች ላይ ማሰላሰላችን ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት የሚጣልበት ገዢ እንደሆነ፣ የመግዛት ሕጋዊ መብት እንዳለው፣ በጎቹን በርኅራኄ የሚጠብቅ እረኛ እንደሆነ እንዲሁም ተገዢዎቹ ለዘላለም በአንድነት ተስማምተው እንዲኖሩ እንደሚያደርግ ያስገነዝበናል። የዚህ መሲሐዊ ንጉሥ ተገዢዎች መሆናችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ስለ መሲሑ የሚናገሩት እነዚህ ትንቢቶች ስለ መልሶ መቋቋም ከሚናገረው የሕዝቅኤል መጽሐፍ ዋነኛ ጭብጥ ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ ሕዝቡን የሚሰበስበውና ንጹሕ አምልኮን መልሶ የሚያቋቁመው በኢየሱስ አማካኝነት ነው። (ሕዝ. 20:41) የዚህ መጽሐፍ ቀጣዮቹ ምዕራፎች ስለ መልሶ መቋቋም የሚገልጸውን አስደሳች መልእክትና ይህ መልእክት በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ጎላ ተደርጎ የተገለጸው እንዴት እንደሆነ ያብራራሉ።
a የግዞቱ አንደኛ ዓመት የጀመረው የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን በግዞት ወደ ባቢሎን በተወሰዱበት በ617 ዓ.ዓ. ነው። ስለሆነም ስድስተኛው ዓመት የጀመረው በ612 ዓ.ዓ. ነው።
b ኢየሱስ ከዳዊት የትውልድ መስመር የመጣ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ በመንፈስ መሪነት በተጻፉት ወንጌሎች ውስጥ ይገኛል።—ማቴ. 1:1-16፤ ሉቃስ 3:23-31
d አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ “ዘላለም” ተብሎ የተተረጎመውን የዕብራይስጥ ቃል በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ቃል የጊዜ ርዝማኔን ብቻ ሳይሆን ቋሚነትን፣ ዘላቂነትን፣ አለመገሰስንና አለመቀልበስንም ሊያመለክት ይችላል።”