ከታላቁ ፈጣሪያችን ጋር መንጋው መጠበቅ
“ይሖዋ እረኛዬ ነው፣ የሚያሳጣኝም የለም። ነፍሴን ያድሳል፤ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ ይመራኛል።”—መዝሙር 23:1, 3 አዓት
1. ይሖዋ ምን ፍቅራዊ ማጽናኛ ይሰጣል?
‘ከዳዊት መዝሙሮች’ አንዱ የሆነው 23ኛው መዝሙር ብዙ የታከቱ ነፍሳትን አጽናንቶአል። በቁጥር 6 ላይ የተገለጸው ዓይነት ትምክህት እንዲኖራቸው አበረታቶአል። “ቸርነትህና [ጥሩነትህና አዓት] ምሕረትህ [ፍቅራዊ ደግነትህ አዓት] በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፣ በእግዚአብሔርም። [በይሖዋም አዓት] ቤት ለዘላለም እኖራለሁ።” የአንተም ምኞት ከሁሉም የምድር ብሔራት በመሰብሰብ ላይ ከሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች ጋር በአምልኮ ቤቱ ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ነውን? “የነፍስህ እረኛና ጠባቂ” የሆነው ታላቁ ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ይህን ግብህን አንድታሟላ ይረዳሃል።—1 ጴጥሮስ 2:25
2, 3. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቦቹን በፍቅራዊ እረኝነት የሚጠብቃቸው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ “መንጋ” በአስደናቂ ሁኔታ ያደገው እንዴት ነው?
2 “የአዲሱ ሰማይና የአዲሲቱ ምድር” ፈጣሪ በተጨማሪ “የእግዚአብሔር ቤት” የሆነው የክርስቲያን ጉባኤ አደራጅና የበላይ ጠባቂ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:15) ኢሳይያስ 40:10, 11 “እነሆ፣ ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፣ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙንም በፊቱ ነው። መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፣ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል” በማለት በግልጽ እንደሚናገረው ይሖዋ ሕዝቡን የመጠበቅ ጥልቅ ፍላጎት አለው።
3 የጥቅሱን ትርጉም ሠፋ አድርገን ስንመለከት ይህ “መንጋ” በክርስቲያናዊ እውነት ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የኖሩትንና አሁን በአፍሪካና በምሥራቅ አውሮፓ በከፍተኛ ቁጥር በመጠመቅ ላይ እንደሚገኙ ያሉትን በቅርብ ጊዜያት የተሰባሰቡ “ጠቦቶች” ያጠቃልላል። ጠንካራውና ከአደጋ የሚከላከለው የይሖዋ ክንድ ወደ እቅፉ ይሰበስባቸዋል። እንደተቅበዘበዙ በጎች የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን ከውድ አምላካቸውና እረኛቸው ጋር ወደተቀራረበ ዝምድና መጥተዋል።
የይሖዋ ተባባሪ እረኛ
4, 5. (ሀ) “መልካሙ እረኛ” ማን ነው? ትንቢቱስ ወደ እርሱ ያመለከተው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ በበላይነት እየተቆጣጠረ ያለው የትኛውን የመለየት ሥራ ነው? ምንስ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቶአል?
4 “መልካሙ እረኛ ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም በሰማይ በአባቱ ቀኝ ሆኖ በማገልገል ለ“በጎቹ” ርህራኄ የተሞላበት ትኩረት እየሰጣቸው ነው። በመጀመሪያ ቅቡዓን የሆኑት “ታናሽ መንጋ” ከዚያም በአሁኑ ጊዜ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑትን እጅግ ብዙ ሰዎች ለመጥቀም ሲል ሕይወቱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል። (ሉቃስ 12:32: ዮሐንስ 10:14, 16) ታላቁ እረኛ ይሖዋ አምላክ እነዚህን በጎች በሙሉ እንደሚከተለው በማለት ይናገራቸዋል:- “በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ። በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል፣ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፤ ያሰማራቸዋል እረኛም ይሆናቸዋል። እኔም እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላክ እሆናቸዋለሁ ባሪያዬም ዳዊት በመካከላቸው አለቃ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ተናግሬአለሁ።”—ሕዝቅኤል 34:20-24
5 “ባሪያዬ ዳዊት” የሚለው አጠራር በትንቢታዊ ሁኔታ የሚያመለክተው የዳዊትን ዙፋን የሚወርስ “ዘር” የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። (መዝሙር 89:35, 36) አሕዛብ የሚፈረዱበት በአሁኑ የፍርድ ቀን የይሖዋ ተባባሪ የበግ እረኛና ንጉሥ የሆነው የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “በጎች” የሆኑትን የሰው ልጆች “በጎች” ነን ከሚሉት “ፍየሎች” መለየቱን ቀጥሏል። (ማቴዎስ 25:31-33) ይህ “አንድ እረኛ” የተነሳው ‘በጎቹን ለመመገብ’ ጭምር ነው። በአሁኑ ጊዜ ይህ ትንቢት በአስደናቂ ሁኔታ ክብራማ ፍጻሜውን ሲያገኝ እያየን ነው። ፖለቲከኞች “በአዲሱ የዓለም ሥርዓት” አማካኝነት የሰው ልጆችን አንድ ስለማድረግ ቢያወሩም አንዱ እረኛ ግን በምድር ላይ ካለው የአምላክ ድርጅት በቀር ማንኛውም ሌላ ድርጅት ሊሞክረው እንኳን በማይቃጣው በብዙ ቋንቋዎች በሚሰጥ የምስክርነት ዘመቻ አማካኝነት ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡትን “በጎች” አንድ እያደረገ ነው።
6, 7. “ታማኝና ልባም ባሪያ” በጎቹ “በጊዜው ምግብ” እንዲያገኙ ሲያደርግ የቆየው እንዴት ነው?
6 የመንግሥቱ መልእክት ወደ አዳዲስ ክልሎች መሠራጨቱን ያለማቋረጥ በቀጠለ መጠን የቅቡዓን ክርስቲያኖች “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከአንዱ እረኛ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት “ምግቡ በጊዜው” እንዲደርስ የሚያስችለውን ማንኛውንም ዝግጅት ያደርጋል። (ማቴዎስ 24:45) በምድር ዙርያ ካሉት የሕትመት ሥራ የሚያከናውኑ 33 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፎች መካከል ብዙዎቹ እየጨመረ የሄደውን የተሻሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ መጻሕፍትና መጽሔቶች ፍላጎት ለማሟላት የሕትመት ምርታቸውን ከፍ በማድረግ ላይ ናቸው።
7 የይሖዋ ምስክሮች የአስተዳደር አካል መላውን የዓለም መስክ ለመሸፈን እንዲቻል 200 በሚሆኑ ቋንቋዎች የሚደረገውን የትርጉም ሥራ ጥራት ለማሻሻልና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎች የመተርጎም ሥራ ለማስጀመር የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው። ይህም ኢየሱስ በሥራ 1:8 ላይ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ . . . እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ተልእኮ የሚደግፍ ነው። ከዚህም በላይ ከአሁን በፊት በሙሉም ሆነ በከፊል በ14 ቋንቋዎች የተተረጎመው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በሩቅ ምሥራቅ አገሮች በሌሎች 16 ቋንቋዎች በመተርጎም ላይ ነው።
‘በአምላክ ሰላም’ መደሰት።
8. በጎቹ ይሖዋ ከእነርሱ ጋር በገባው የሰላም ቃል ኪዳን ሲባረኩ የቆዩት እንዴት ነው?
8 ይሖዋ በአንዱ እረኛ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በደንብ ከተቀለቡት በጎቹ ጋር “የሰላም ቃል ኪዳን” ያደርጋል። (ኢሳይያስ 54:10) በጎቹ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ እምነት በማሳየት በይሖዋ ብርሃን ለመመላለስ ችለዋል። (1 ዮሐንስ 1:7) ‘አሳብንም ሁሉ የሚያልፈውንና በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነትም ልባቸውንና የማሰብ ኃይላቸውን የሚጠብቀውን የአምላክ ሰላም’ አግኝተዋል። (ፊልጵስዩስ 4:7) ሕዝቅኤል 34:25-28 በመቀጠል እንደሚገልጸው ይሖዋ በጎቹን ወደ መንፈሳዊ ገነት ማለትም አስደሳች ወደሆነ የመረጋጋት ሁኔታ፣ መንፈስን ወደሚያድስ ብልጽግናና ፍሬያማነት ይመራቸዋል። ይህ አፍቃሪ እረኛ ስለበጎቹ “የቀንበራቸውንም ማነቆ በሰበርሁ ጊዜ ከሚገዙአቸውም እጅ ባዳንሁአቸው ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ ኣዓት] እንደሆንሁ ያውቃሉ። እንግዲህም ለአሕዛብ ንጥቂያ አይሆኑም . . . ተዘልለውም ይቀመጣሉ የሚያስፈራቸውም የለም” በማለት ይናገራል።
9. የአምላክ ሕዝቦች በላያቸው ላይ የነበረው ‘ቀንበር ስለተሰበረላቸው’ ምን አጋጣሚዎች ተከፍተውላቸዋል?
9 ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በብዙ አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምስክሮች ‘ቀንበራቸው ተሰብሮላቸዋል።’ የስብከት ሥራቸውን ለማከናወን ከማንኛውም ጊዜ የበለጠ ነፃነት አግኝተዋል። በማንኛውም አገር የምንኖር የይሖዋ አገልጋዮች ሥራው ወደሚፈጸምበት ጊዜ እየተቃረብን በሄድን መጠን ይሖዋ በሚሰጠን መረጋጋት በሚገባ የምንጠቀም እንሁን። የሰው ልጆች አይተውት ወደማያውቁት ታላቅ መከራ እየተቃረብን በሄድን መጠን ይሖዋ እንዴት ያለ ታላቅ ማጽናኛ ይሰጠናል!—ዳንኤል 12:1፤ ማቴዎስ 24:21, 22
10. ይሖዋ መልካሙን እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲረዱት ያዘጋጀው እነማንን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ከእነዚህ ለአንዳንዶች ምን ተናግሮ ነበር?
10 ይሖዋ ክፉዎችን ለሚበቀልበት ቀን ዝግጅት ለማድረግ ሲል መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመንጋው በሚያደርገው እንክብካቤ የሚረዱት የበታች እረኞች አዘጋጅቶአል። እነዚህ የበታች እረኞች በራእይ 1:16 ላይ በኢየሱስ ቀኝ እጅ ውስጥ እንዳሉ “ሰባት ከዋክብት” ተደርገው ተገልጸዋል። ሰባት ቁጥር ሰማያዊ ነገሮች ምልዓትን የሚያመለክት ቁጥር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የእነዚህ የበታች እረኞች ወኪል ለሆነው አካል “በገዛ ደሙ [ልጁ ደም አዓት] የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት [የበላይ ተመልካቶች አዓት] አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 20:28) በአሁኑ ግዜ በምድር ዙሪያ በሚገኙ 69,557 ጉባኤዎች ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የበታች እረኞች ያገለግላሉ።
የበታች እረኞች ቀዳሚ ሁኑ!
11. አንዳንድ እረኞች በተደጋጋሚ በሚሸፈኑ ክልሎች በተሳካ ሁኔታ መሪ በመሆን ያገለገሉት እንዴት ነው?
11 በብዙ ቦታዎች በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች በተደጋጋሚ በተሸፈኑ ከሌሎች በማገልገል በኩል እነዚህ የበታች እረኞች መሪዎች መሆን አለባቸው። የመንጋው የጋለ የአገልግሎት ስሜት ከፍ ባለ ደረጃ እንዲቆይ ለማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? እረኞቹ በጣም በሚያስመሰግን መንገድ ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን የተሳካ ውጤት ካስገኙባቸው መንገዶች አንዱ ለረዳትና ለዘወትር አቅኚነት ሥራ ወንድሞችን በመቀስቀስ ነው። ብዙ እረኞች ራሳቸውን በዚህ የአቅኚነት አገልግሎት ተካፍለዋል። አቅኚ ለመሆን ያልቻሉት አስፋፊዎችም የአቅኚነት መንፈስ አሳይተዋል። በደስታ በማገልገል በአገልግሎት ክልላቸው ያሉት ሰዎች የሚያሳዩትን ግድ የለሽነት ተቋቁመዋል። (መዝሙር 100:2፤ 104:33, 34፤ ፊልጵስዩስ 4:4, 5) ምንም እንኳ ዓለም በክፋትና በብጥብጥ እየተዋጠች ብትሄድም በግ መሰል ሰዎች ግን ስለ መንግሥቱ ተስፋ ግንዛቤ እንዲያገኙ እየተደረጉ ናቸው።—ማቴዎስ 12:18, 21፤ ሮሜ 15:12
12. በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉ ክልሎች ያለው አሳሳቢ ችግር ምንድነው? አንዳንድ ጊዜ ይህንን ችግር እንዴት መፍታት ተችሎአል?
12 ሌላው ችግር ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ መንጋውን የሚንከባከቡ ብቃት ያላቸው እረኞች በበቂ መጠን አለመገኘታቸው ነው። ፈጣን እድገት ባለባቸው የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች የተሾሙ ሽማግሌዎች ጨርሶ የሌሉባቸው ብዙ አዳዲስ ጉባኤዎች አሉ። ፈቃደኛ የሆኑ በጎች ኃላፊነቱን በመሸከም ላይ ያሉ ቢሆንም ተሞክሮ የሌላቸው ስለሆኑ ወደ ጉባኤዎች በመጉረፍ ላይ ያሉትን በጎች ለማሠልጠን እርዳታ ያስፈልጋል። ዕድገቱ ፈጣን በሆነባቸው እንደ ብራዚል፣ ሜክሲኮና ዛየር ባሉት አገሮች አገልግሎቱን ለማደራጀትና ሌሎች አዳዲሶችን ለማሠልጠን ወጣት ምስክሮችን መጠቀም አስፈላጊ ሆኖአል። አቅኚዎች በጣም ግሩም እርዳታ በመስጠት ላይ ያሉ ሲሆን በዚህ መስክ እህቶች ሌሎች አዳዲስ እህቶችን ማሠልጠን ይችላሉ። ይሖዋ በመንፈሱ ውጤቱን ባርኮታል። ጭማሪውም ሳያቋርጥ ይቀጥላል።—ኢሳይያስ 54:2, 3
13. (ሀ) መከሩ በጣም ብዙ በመሆኑ ሁሉም ምስክሮች መጸለይ የሚኖርባቸው ስለምን ነገር ነው? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች ጸሎት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊትና በኋላ መልስ ያገኘው እንዴት ነበር?
13 የስብከቱ ሥራ ተደላድሎ በተመሠረተባቸው አገሮችና አዲስ በተጀመረባቸው ክልሎች እንዲሁም በቅርብ ጊዜ እገዳ በተነሳላቸው አገሮች ኢየሱስ በማቴዎስ 9:37, 38 ላይ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” በማለት የተናገራቸው ቃላት አሁንም ይሠራሉ። ይሖዋ ተጨማሪ እረኞችን እንዲያስነሳ መጸለይም ያስፈልገናል። ይህን ለማድረግ እንደሚችልም አሳይቷል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊትና በኋላ አሶር መሰል ጨካኝ አምባገነን መንግሥታት የይሖዋ ምስክሮችን ለመደምሰስ ሞክረው ነበር። ይሖዋ ሕዝቦቹ ላቀረቡት ጸሎት መልስ በመስጠት ድርጅታቸው ሙሉ በሙሉ ቲኦክራቲካዊ እንዲሆን በማድረግ አጥርቶላቸዋል። የሚያስፈልጉትን እረኞችም ሰጥቷቸዋል።a ይህም “አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፣ ምድራችንም በረገጠ ጊዜ ሰባት እረኞችና ስምንት አለቆች [መሳፍንት አዓት] እናስነሳበታለን” ከሚለው ትንቢት ጋር የሚስማማ ሲሆን ይህም ከሚበቃው በላይ ብዛት ያላቸው ራሳቸውን የወሰኑና መሪዎች ሆነው የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች እንደሚኖሩ ያሳያል።—ሚክያስ 5:5
14. በድርጅቱ ውስጥ የሚያስፈልግ ምን ከፍተኛ ነገር አለ? ለወንድሞች ምን ማበረታቻ ሲሰጥ ቆይቷል?
14 የተጠመቁ ወንዶች ሁሉ ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶችን ለመቀበል የሚያስችለውን ብቃት ለማግኘት እንዲጣጣሩ አስፈልጎአል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1) ሁኔታው አጣዳፊ ነው። የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በፍጥነት እየቀረበ ነው። ዕንባቆም 2:3 “ራእዩ እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፤ . . . በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱም አይዘገይም” ብሏል። ወንድሞች ሆይ፣ ፍጻሜው ከመምጣቱ በፊት በዚህ የእረኝነት ሥራ ለመሳተፍና ለተጨማሪ መብቶች ለመብቃት ልትጣጣሩ ትችላላችሁን?—ቲቶ 1:6-9
ቲኦክራቲካዊ እረኝነት
15. የይሖዋ ሕዝቦች ቲኦክራሲያዊ የሆኑት በምን መንገድ ነው?
15 የአምላክ ሕዝቦች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በሚታየው ዕድገት ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ ከፈለጉ በአመለካከታቸው ቲኦክራቲካዊ መሆን ያስፈልጋቸዋል። ይህን ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው? “ቲኦክራቲክ” የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? የዌብስተር ኒው ትዌንቲዝ ሴንቸሪ መዝገበ ቃላት “ቲኦክራሲ” ለሚለው ቃል “በአምላክ የሚተዳደር መንግሥታዊ አገዛዝ” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። “ቅዱስ ብሔር” የሆነው የይሖዋ ሕዝብ ቲኦክራሲ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው። (1 ጴጥሮስ 2:9፤ ኢሳይያስ 33:22) እውነተኛ ክርስቲያኖች የዚህ ቲኦክራቲካዊ ብሔር አባሎች ወይም ተባባሪዎች በመሆናቸው የአምላክን ቃልና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በመታዘዝ መኖርና ማገልግል አለባቸው።
16. በመሠረቱ ቲኦክራቲካዊ መሆናችንን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?
16 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንዴት ቲኦክራቲካዊ መሆን እንዳለባቸው በግልጽ አስረድቷል። በመጀመሪያ “[በእውነተኛ] ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው መልበስ” እንዳለባቸው ተናግሯል። የአንድ ክርስቲያን ባሕርይ በአምላክ ቃል ውስጥ በሠፈረው መሠረት በአምላክ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት መቀረጽ አለበት። ለይሖዋና ለሕጎቹ ታማኝ መሆን አለበት። ጳውሎስ ይህ እንዴት ሊደረግ እንደሚችል በመግለጽ “እንደተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ [የምትመስሉ አዓት] ሁኑ” በማለት አጥብቆ አሳስቦአል። (ኤፌሶን 4:24 እስከ 5:1) እንደ ታዛዥ ልጆች አምላክን መምሰል አለብን። ይህም በእርግጥ በአምላክ እንደምንገዛ የሚያሳይ በሥራ ላይ የዋለ እውነተኛ ቲኦክራሲ ነው።—በተጨማሪ ቆላስይስ 3:10, 12-14 ተመልከት።
17, 18 (ሀ) ቲኦክራቲካዊ ክርስቲያኖች የሚኮርጁት የትኛውን የአምላክ የላቀ ባሕርይ ነው? (ለ) ይሖዋ ለሙሴ በተናገራቸው ቃላት ዋነኛ ባሕርያቱን አጥብቆ የገለጸው እንዴት ነው? ይሁን እንጂ ምን ማስጠንቀቂያ ጨምሮ ሰጥቷል?
17 አምላክን ልንመስልበት የሚገባን ዋነኛ ጠባይ ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ዮሐንስ 4:8 ላይ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት መልሱን ይሰጠናል። ዮሐንስ ስምንት ቁጥሮች ያህል ዝቅ ብሎ በቁጥር 16 ላይ ይህንኑ አስፈላጊ መሠረታዊ ሥርዓት “እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል” በማለት ደግሞታል። ታላቁ እረኛ ይሖዋ የፍቅር አብነት ነው። ቲኦክራቲካዊ እረኞችም ለይሖዋ በጎች ጥልቅ ፍቅር በማሳየት ይሖዋን ሊመስሉት ይችላሉ።—ከ1 ዮሐንስ 3:16, 18ና ከ4:7-11 ጋር አወዳድር።
18 ታላቁ ቲኦክራት ራሱን ለሙሴ “እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር [ይሖዋ፣ ይሖዋ አዓት] መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለብዙ ቸርነትና [ፍቅራዊ ደግነትና አዓት] እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን [ፍቅራዊ ደግነትን አዓት] የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፣ በደለኛውንም ከቶ የማያነፃ፣ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው” በማለት ገልጾለታል። (ዘጸአት 34:6, 7) ስለዚህ ይሖዋ ተገቢ ሆኖ ሲገኝና በደል ሲፈጸም እንደሚቀጣ ሲያስጠነቅቅ የላቀ ቲኦክራቲካዊ ባሕሪው የሆነውን የፍቅርን ልዩ ልዩ ገጽታዎች አጥብቆ ገልጿል።
19. ክርስቲያን እረኞች ከፈሪሳውያን በተለየ ሁኔታ ቲኦክራቲካዊ በሆነ መንገድ መሥራት የሚኖርባቸው እንዴት ነው?
19 በድርጅቱ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ላላቸው ሰዎች ቲኦክራቲካዊ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ኢየሱስ በዘመኑ ስለነበሩት ጻፎችና ፈሪሣውያን ሲናገር “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፣ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም” ብሏል። (ማቴዎስ 23:4) ምንኛ ጨቋኝና ፍቅር የጎደላቸው ነበሩ! እውነተኛ ቲኦክራሲ ወይም የአምላክ አገዛዝ በበጎቹ ላይ ማለቂያ የሌላቸው ሰው ሠራሽ ደንቦች መጫን ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስን የፍቅር መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ በማዋል መንጋውን መጠበቅን ይጠይቃል። (ከማቴዎስ 15:1-9 ጋር አወዳድር።) ከዚህም ጋር ቲኦክራቲካዊ እረኞች የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ በፍቅራቸው ላይ ጥብቅነትን በመጨመር አምላክን መምሰል አለባቸው።—ከሮሜ 2:11 ከ1 ጴጥሮስ 1:17 ጋር አወዳድር።
20. ቲኦክራቲካዊ እረኞች የሚገነዘቡት ምን ድርጅታዊ ዝግጅቶችን ነው።
20 በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ኢየሱስ ባለው ሁሉ ላይ ታማኝና ልባም ባሪያ እንደሾመና ይህ ባሪያም በጎቹን ለመጠበቅ ሽማግሌዎችን በሚሾምበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚመራ እውነተኛ እረኞች ይገነዘባሉ። (ማቴዎስ 24:3, 47፤ ሥራ 20:28) ስለዚህ ቲኦክራቲካዊ መሆን ለዚህ ባሪያ፣ ባሪያው ላቋቋማቸው ድርጅታዊ ዝግጅቶችና በጉባኤው ውስጥ ላለው የሽማግሌዎች ዝግጅት ጥልቅ አክብሮት ማሳደርን ያጠቃልላል።—ዕብራውያን 13:7, 17
21. ኢየሱስ ለበታች እረኞች ምን መልካም አርአያ ትቶላቸዋል?
21 ኢየሱስ መመሪያ ለማግኘት ያለማቋረጥ በይሖዋና በቃሉ ላይ ይተማመን ስለነበረ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፣ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና” ብሏል። (ዮሐንስ 5:30) የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የበታች እረኞች ተመሳሳይ የሆነ የትሕትና ጠባይ መኮትኮት ይኖርባቸዋል። አንድ ሽማግሌ መመሪያ ለማግኘት ኢየሱስ እንዳደረገው ሁልጊዜ ወደ አምላክ ቃል የሚመለከት ከሆነ በእርግጥም ቲኦክራቲካዊ ነው።—ማቴዎስ 4:1-11፤ ዮሐንስ 6:38
22. (ሀ) ሁላችንም ቲኦክራቲካዊ ለመሆን መጣር ያለብን በምን መንገድ ነው? (ለ) ኢየሱስ ለበጎቹ ያቀረበው የትኛውን የደግነት ጥሪ ነው?
22 የተጠመቃችሁ ወንዶች ከሆናችሁ በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነትን ለሚጠይቁ መብቶች ብቃት እንዲኖራችሁ ተጣጣሩ! እናንተ ሁላችሁም የተወደዳችሁ በጎች ሆይ፣ ፍቅርን በማሳየት ረገድ አምላክንና ክርስቶስን በመምሰል ቲኦክራቲካዊ መሆንን ግባችሁ አድርጉ! እረኞችና መንጋው ባንድነት “እናንተ ሽክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” ለሚለው የኢየሱስ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ደስ የሚላችሁ ሁኑ።—ማቴዎስ 11:28-30
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በሰኔ 1 እና 15 1938 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ድርጅት” የተሰኙትን ርዕሰ ትምህርቶች ተመልከቱ።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ የይሖዋ “መንጋ” ምንድን ነው? እነማንንስ ይጨምራል?
◻ ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመንና በአሁኑ ጊዜም “መልካሙ እረኛ” በመሆን የሠራው እንዴት ነው?
◻ የበታች እረኞች መንጋውን በመንከባከብ ምን ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ?
◻ “ቲኦክራሲ” የሚለው ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ ምንድን ነው?
◻ አንድ ክርስቲያን በተለይም ደግሞ አንድ የበታች እረኛ ቲኦክራቲካዊ ለመሆን መጣር የሚኖርበት ለምንድን ነው?