“የአምላክ ሰላም” ልባችሁን ይጠብቅ
“ይሖዋ ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፤ ሰላምም ይስጥህ።”—ዘኁልቁ 6:26
1. ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ምን ብሎ ጻፈለት? ምንንስ በመግለጽ?
በ65 እዘአ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮማ እሥረኛ ነበር። በሮማ የሞት ፍርድ አስፈጻሚዎች እጅ በአሰቃቂ ሁኔታ ሊሞት የቀረበ ቢሆንም ጳውሎስ በውስጡ ሰላም ነበረው። ይህም እንደሚከተለው በማለት ለወጣት ጓደኛው ለጢሞቴዎስ በጻፈለት ቃላት ግልጽ ሆኗል፦ “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖት ጠብቄአለሁ፤ ወደፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል።”—2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8
2. በሥራ በተሞላ ሕይወቱ በሙሉና እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የጳውሎስን ልብ የጠበቀለት ምን ነበር?
2 ጳውሎስ ሞት ተደቅኖበት ሳለ ሊረጋጋ የቻለው እንዴት ነበር? “አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የአምላክ ሰላም” ልቡን ይጠብቅለት ስለነበረ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:7) ወደ ክርስትና ከተለወጠበት ጊዜ ጀምሮ ባሳለፋቸው በሥራ የተወጠሩ ዓመታት ሁሉ ይኸው ሰላም ጠብቆታል። የሕዝብ ረብሻዎች፣ እሥራቶች፣ ግርፋቶችና በድንጋይ መወገር ሲደርስበት ደግፎታል። ከክህደትና ወደ ይሁዲነት የመመለስ ተጽዕኖዎች ሁሉ ጋር ሲጋደል አበርትቶታል። እንዲሁም ከማይታዩ አጋንንታዊ ኃይሎች በሚያደርገው ውጊያ ረድቶታል። በግልጽ እንደሚታየው እስከ መጨረሻው አበርትቶታል።—2 ቆሮንቶስ 10:4, 5፤ 11:21-27፤ ኤፌሶን 6:11, 12
3. ስለ አምላክ ሰላም ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
3 ጳውሎስ ይህን ሰላም ምን ዓይነት ብርቱ ኃይል ሆኖ አግኝቶታል! እኛስ በአሁኑ ጊዜ ይህ ሰላም ምን እንደሆነ ልንማር እንችላለን? በእነዚህ አስቸጋሪና “አስጨናቂ ዘመናት” “መልካሙን ገድል” ስንጋደል ልባችንን ሊጠብቅልንና እኛን ሊያበረታን ይችላልን?—1 ጢሞቴዎስ 6:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1
ከአምላክ ጋር ሰላም የነበረው እንዴት እንደጠፋ
4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለ“ሰላም” የተሰጡት አንዳንድ ትርጉሞች ምንድን ናቸው?
4 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሰላም” የሚለው ቃል ብዙ ትርጉሞች አሉት። የአዲስ ኪዳን መንፈሳዊ ትምህርት አዲስ ኢንተርናሽናል መዝገበ ቃላት ውስጥ ተዘርዝረው ከሚገኙት የሰላም ትርጉሞች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦ “በብሉይ ኪዳን በሙሉ ሻሎም (ሰላም) የሚለው ቃል አጠቃላይ ስሜቱ ደህና መሆን የሚለውን ሐሳብ (መሳፍንት 19:20)፤ ብልጽግናን (መዝሙር 73:3)፣ ኃጢአተኞችን በሚመለከትና አካላዊ ጤንነትን ለማመልከት (ኢሳይያስ 57:18[- 20]፤ መዝ. 38:3)፤ በቃኝ ማለት ወይም እርካታን (ዘፍ. 15:15 ወዘተ)፤ በአሕዛብና በሰዎች መካከል መልካም ግንኙነት መኖሩን (መሳፍንት መሳ 4:17፤ 1 ዜና 1ዜና 12:17, 18)፤ ደህንነትን ( ኤርምያስ 29:11፤ 14:13) ለመግለጽ ተሠርቶበታል።” ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሚሆነው ግን ከይሖዋ ጋር ሊኖር የሚገባው ሰላማዊ ዝምድና ነው። ከእሱ ጋር ሰላማዊ ዝምድና ከሌለ ሊገኝ የሚችለው ግፋ ቢል ጊዜያዊና የተወሰነ ሰላም ብቻ ነው።—2 ቆሮንቶስ 13:11
5. የአምላክ ፍጥረት ሰላም በመጀመሪያ የተበጠበጠው እንዴት ነበር?
5 በመጀመሪያ ፍጥረት በሙሉ ከይሖዋ ጋር ፍጹም ሰላም ነበረው። የፍጥረት ሥራው በሙሉ እጅግ መልካም ነበረ ብሎ አምላክ የተናገረው በበቂ ምክንያት ነበር። የሰማይ መላእክት የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች ሲያዩ በእርግጥ በእልልታ አጨብጭበዋል። (ዘፍጥረት 1:31፤ ኢዮብ 38:4-7) የሚያሳዝነው ግን ያ ጽንፈ ዓለማዊ ሰላም አልዘለቀም። አሁን ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው መንፈሳዊ ፍጡር ከአምላክ አስተዋይ ፍጥረቶች ሁሉ አዲስ የነበረችውን ሄዋንን አምላክን ከመታዘዝ ባሳታት ጊዜ ያ ሰላም ተናጋ። የሔዋን ባል አዳምም ተከተላትና በጠቅላላው ሦስት አመጸኞች ስለሆኑ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ብጥብጥ ተነሣ።—ዘፍጥረት 3:1-6
6. ከአምላክ ጋር ሰላም ማጣት ለሰው ዘር ምን አስከተለ?
6 አዳምና ሔዋን ከአምላክ ጋር ሰላም ማጣታቸው አጥፊ ሆነባቸው። ቀስ በቀስ አካላቸው እየተበላሸ ሄደና በሞት አከተመ። በገነት ውስጥ ሰላምን በማግኘት ፋንታ አዳም ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄደውን ቤተሰቡን ለመመገብ ከኤደን ውጭ ካለው ያልለማ መሬት ጋር መታገል ነበረበት። ሔዋንም ደስ ብሎአት የፍጹም ልጆች እናት በመሆን ፋንታ ፍጹም ያልሆኑ ልጆችን በጭንቀትና በስቃይ ወለደች። ከአምላክ ጋር ሰላምን ማጣቱ በሰዎች መካከል ወደ ቅንዓትና ዓመጽ አመራ። ቃየን ወንድሙን አቤልን ገደለ። በጥፋት ውሃ ዘመን መላዋ ምድር በዓመጽ ተሞልታ ነበር። (ዘፍጥረት 3:7 እስከ 4:16፤ 5:5፤ 6:11, 12) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ሲሞቱ ከዚያ በኋላ ብዙ መቶ ዓመታት ቆይቶ እንደሞተው እንደ አብርሃም ወደ መቃብራቸው የሄዱት በሕይወታቸው ረክተውና “በሰላም” አልነበረም።—ዘፍጥረት 15:15
7. (ሀ) አምላክ ፍጹም ሰላም እንደሚመለስ የሚጠቁም ምን ትንቢት ተናግሯል? (ለ) የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ሌሎችን በመለወጥ በኩል ምን ያህል ኃያል ሆኖአል?
7 አዳምና ሔዋን ሰላም ካጡ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠላትነት ተጠቅሶ እናገኛለን። አምላክ ለሰይጣን እንዲህ በማለት ተናገረው፦ “በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:15) ጊዜ እያለፈ በሄደ መጠን ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል” ብሎ ለመናገር እስኪበቃ ድረስ የሰይጣን ግፊት ተስፋፍቶ ነበር። (1 ዮሐንስ 5:19) በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለ ዓለም ያላንዳች ጥርጥር ከአምላክ ጋር ሰላም የለውም። ይህም በመሆኑ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ክርስቲያኖችን “ዓለምን መውደድ ከእግዚአብሔር ጋር ጥል እንዲሆን አታውቁምን?” በማለት በትክክል አስጠንቅቋል።—ያዕቆብ 4:4
ጠላት በሆነ ዓለም ውስጥ ሰላም ማግኘት
8, 9. አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ሰዎች ከአምላክ ጋር ሰላም ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነበር?
8 አምላክ በኤደን “ጠላትነት” የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በጠቀሰ ጊዜ ለፍጥረት ፍጹም ሰላም እንዴት እንደሚመለስለትም በቅድሚያ ተናግሮአል። ተስፋ የተሰጠበት የአምላክ ሴት ዘር የመጀመሪያውን ሰላም አደፍራሽ ጭንቅላት ይቀጠቅጣል። ከዚያ በኋላ በዚያ ተስፋ እምነት ያሳደሩ ሰዎች ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ዝምድና አግኝተዋል። በአብርሃም ረገድ ይህ ሰላማዊ ዝምድና ወደ ወዳጅነት ሊያድግ በቅቷል።—2 ዜና 20:7፤ ያዕቆብ 2:23
9 በሙሴ ዘመን ይሖዋ የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነውን የእሥራኤልን ልጆች ራሱን የቻለ አሕዛብ አደረጋቸው። ሊቀ ካህኑ አሮን እሥራኤላውያንን ሲመርቃቸው “[ይሖዋ (አዓት)] ይባርክህ፤ ይጠብቅህም፤ [ይሖዋ (አዓት)] ፊቱን ያብራልህ፤ ይራራልህም፤ [ይሖዋ (አዓት)] ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፤ ሰላምንም ይስጥህ” ብሎ በተናገረው ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ለዚህ ሕዝብ ሰላሙን ሰጣቸው። (ዘኁልቁ 6:24-26) የይሖዋ ሰላም በአጸፋው መልካም ውጤቶችን አምጥቷል። ይሁን እንጂ ይህን ሰላም ለማግኘት መሟላት ያለባቸው ብቃቶች ነበሩ።
10, 11. እሥራኤላውያን ከአምላክ ጋር የሚኖራቸው ሰላም በምን ላይ የተመሠረተ ነበር? ምንስ ያመጣላቸው ነበር?
10 ይሖዋ ለሕዝቡ እንዲህ ብሎ ነግሮት ነበር፦ “በሥርዓቴ ብትሄዱ ትዕዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፤ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ። ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ። ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ። ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። በመካከላችሁም እሄዳለሁ፣ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ።” (ዘሌዋውያን 26:3, 4, 6, 12) እሥራኤላውያን ከጠላቶቻቸው ጥበቃ ስለሚያገኙ በሚያስፈልጋቸው ሥጋዊ ነገሮች ረገድም መትረፍረፍና ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና ስለሚኖራቸው ሰላምን ሊያገኙ ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ከይሖዋ ሕግ ጋር በመጣበቃቸው ላይ የተመካ ነበር።—መዝሙር 119:165
11 በሕዝቡ ታሪክ በሙሉ የይሖዋን ሥርዓት በታማኝነት ለመጠበቅ የጣሩ ሁሉ ከእርሱ ጋር ሰላም አግኝተዋል፤ ያም አብዛኛውን ጊዜ ሌሎች ብዙ በረከቶችም አምጥቶላቸዋል። በንጉሥ ሰለሞን ግዛት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ወቅት ከአምላክ ጋር የነበራቸው ሰላም ሥጋዊ መትረፍረፍንና ከእሥራኤል ጎረቤቶች ጋር ከመዋጋትም እረፍትን አምጥቷል። ያንን ጊዜ በመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በሰለሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እሥራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።” (1 ነገሥት 4:25) ከጐረቤት አገሮች ጋር ጦርነት በሚነሳበትም ጊዜ እንኳን ታማኝ እሥራኤላውያን አስፈላጊው ሰላም ማለትም ከአምላክ ጋር ሰላም ነበራቸው። ስለሆነም የታወቀ ጦረኛ የነበረው ንጉሥ ዳዊት እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ አንተ ብቻህን በሰላም አሳድረኸኛልና።”—መዝሙር 4:8
ለሰላም የሚረዳ የተሻለ መሠረት
12. እሥራኤላውያን በመጨረሻ ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ሰላም ያጡት እንዴት ነው?
12 በመጨረሻም ፍጹም ሰላምን የሚመልሰው ዘር ኢየሱስ በመባል ሰው ሆኖ መጣ። በልደቱ ዕለትም መላእክት “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር በበጎ ፈቃድ ሰዎች መካከል” በማለት ዘምረዋል። (ሉቃስ 2:14) ኢየሱስ የተገለጠው በእሥራኤል ምድር ነው። ይሁን እንጂ ያ ሕዝብ በአምላክ ቃል ኪዳን ሥር የነበረ ቢሆንም ብሔሩ ባጠቃላይ አልተቀበለውም። እንዲያውም ሮማውያን እንዲገድሉት አሳልፈው ሰጡት። ከመሞቱ ጥቂት ጊዜ አስቀድሞ ኢየሱስ እንዲህ በማለት ለኢየሩሳሌም አለቀሰላት፦ “ለሰላምሽ የሚሆነውን አንቺስ እንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሯል።” (ሉቃስ 19:42፤ ዮሐንስ 1:11) ኢየሱስን ባለመቀበሉ ምክንያት የእሥራኤል ሕዝብ ከአምላክ ጋር የነበረውን ሰላም ጨርሶ አጣ።
13. ይሖዋ ሰዎች ከእሱ ጋር ሰላም የሚያገኙበትን ምን አዲስ መንገድ አቋቋመ?
13 ቢሆንም የአምላክ ዓላማዎች አልተጨናገፉም። ኢየሱስ ከሙታን ተነሣና ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ቤዛ የሚሆን የፍጹም ሕይወቱን ዋጋ ለይሖዋ አቀረበ። (ዕብራውያን 9:11-14) ሰዎች በጠቅላላው (ሥጋዊ እሥራኤላውያንም ሆኑ አሕዛብ) ከአምላክ ጋር ሰላም እንዲያገኙ የኢየሱስ መሥዋዕት አዲስና የበለጠ መንገድ ሆነላቸው። ጳውሎስ በሮም ለነበሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ታረቅን” ብሏል። (ሮሜ 5:10) በመጀመሪያ መቶ ዘመን በዚህ መንገድ የታረቁት ሰዎች የአምላክ ልጆችና “የእግዚአብሔር እሥራኤል” የተባለ አዲስ መንፈሳዊ ሕዝብ አባሎች እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተው ነበር።—ገላትያ 6:16፤ ዮሐንስ 1:12, 13፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21, 22፤ 1 ጴጥሮስ 2:9
14, 15. የአምላክን ሰላም ግለጽ። እንዲሁም ክርስቲያኖች የሰይጣን ጠላትነት ዒላማ በሚሆኑበት ጊዜ እንዴት እንደሚጠብቃቸው አብራራ።
14 እነዚህ አዲስ መንፈሳውያን እሥራኤላውያን የሰይጣንና እርሱ የሚገዛው ዓለም የጥላቻ ዒላማዎች ሆኑ። (ዮሐንስ 17:14) ይሁን እንጂ “ከእግዚአብሔር አብና ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ሰላም” ነበሯቸው። (2 ጢሞቴዎስ 1:2) ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”—ዮሐንስ 16:33
15 ጳውሎስና መሰል ክርስቲያኖች ባጋጠማቸው መከራ ሁሉ እንዲጸኑ የረዳቸው ይህ ሰላም ነበር። ይህ ሰላም በኢየሱስ መስዋዕት አማካኝነት የተገኘውን ከአምላክ ጋር የተረጋጋና ስምም የሆነ ዝምድናን ያንጸባርቃል። ይህ ሰላም ባለቤቱን እርጋታ የሠፈነበት የአእምሮ ሰላም ይሰጠዋል። የአምላክን አሳቢነት ስለሚገነዘብ በአፍቃሪ አባቱ እቅፍ የተኛ ልጅም ተመሳሳይ የሆነ ሰላምና በሚያስብለት ሰው እየተጠበቀ ያለ ስለመሆኑ የማያጠያይቅ እርግጠኝነት ይሰማዋል። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” በማለት አበረታቷቸዋል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
16. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከአምላክ ጋር የነበራቸው ሰላም እርስ በርሳቸው የነበራቸውን ግንኙነት የነካው እንዴት ነው?
16 ሰው ከአምላክ ጋር ሰላም የማጣቱ አንድ ውጤት ጥላቻና ብጥብጥ ነው። ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ግን ከአምላክ ጋር ሰላም ማግኘት ተቃራኒ ውጤት ይኸውም ጳውሎስ “የሰላም ማሠሪያ፣ የመንፈስ አንድነት” ብሎ የጠቀሰው በመካከላቸው ሰላምና አንድነት አምጥቷል። (ኤፌሶን 4:3) ‘በአንድ ልብ (አሳብ) ነበሩ፤ በሰላምም ኖረዋል፤ የፍቅርና የሰላም አምላክም ከእነርሱ ጋር ነበረ።’ ከዚህም ሌላ ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ለሚሰጡት “የሰላም ልጆች” ለሆኑ ሰዎች የመዳን የምሥራች የሆነውን “የሰላም ወንጌል” ሰብከዋል።—2 ቆሮንቶስ 13:11፤ ሥራ 10:36፤ ሉቃስ 10:5, 6
የሰላም ቃል ኪዳን
17. አምላክ በዘመናችን ከሕዝቡ ጋር ምን አድርጓል?
17 ዛሬ እንዲህ ዓይነቱ ሰላም ሊገኝ ይችላልን? አዎ፤ ይችላል። ከፍ ያለ ክብር በተሰጠው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተቋቋመችበት ጊዜ ጀምሮ የአምላክ እሥራኤል ቀሪዎችን ይሖዋ ሰብስቦ ከእነሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን አድርጓል። በዚህም በነቢዩ ሕዝቅኤል በኩል የተናገረውን የሚከተለውን ትንቢት ፈጽሟል፦ “የሰላምም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ። የዘላለም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል። እኔም እባርካቸዋለሁ። አበዛቸውማለሁ። መቅደሴንም ለዘላለም በመካከላቸው እኖራለሁ።” (ሕዝቅኤል 37:26) ይሖዋ ይህን ቃል ኪዳን የገባው እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ወንድሞቻቸውን በኢየሱስ መሥዋዕት ካመኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ነው። ከመንፈሳዊ መበከል ነጽተው ሕይወታቸውን ለሰማያዊ አባታቸው ወስነዋል፤ የተቋቋመችውን መንግሥት ወንጌል በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስበክም በኩል በጣም ግልጽ በሆነ መንገድ ግንባር ቀደም በመሆን ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ ይጥራሉ።—ማቴዎስ 24:14
18. ከአሕዛብ መካከል አንዳንዶች የይሖዋ ስም በአምላክ እሥራኤል ላይ መሆኑን ሲገነዘቡ ምን አደረጉ?
18 ትንቢቱ በመቀጠልም እንዲህ ይላል፦ “ማደሪያዬም በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እስራኤልን የምቀድሰው እኔ [ይሖዋ (አዓት)] እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ።” (ሕዝቅኤል 37:27, 28) ከዚህ ጋር በመስማማት “ከአሕዛብ” የመጡ በብዙ መቶ ሺህ፤ አዎ፤ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ስም በአምላክ እሥራኤል ላይ መሆኑን ተገንዝበዋል። (ዘካርያስ 8:23) ከአሕዛብ ተውጣጥተው በዮሐንስ ራእይ አስቀድሞ የታየው “ታላቅ መንጋ” በመሆን ከዚያ መንፈሳዊ ሕዝብ ጋር ይሖዋን ለማገልገል እየጐረፉ በመምጣት ላይ ናቸው። ልብሳቸውን “በበጉ ደም አጥበው ስላነጹ” ከታላቁ መከራ በሕይወት ተርፈው ወደ ሰላማዊው አዲስ ሥርዓት ይገባሉ።—ራእይ 7:9, 14
19. በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ምን ሰላም አግኝተው ይደሰታሉ?
19 የአምላክ እሥራኤልና ታላቁ መንጋ በአንድነት በንጉሥ ሰለሞን ሥር የእሥራኤል ሕዝብ ካገኙት ሰላም ጋር የሚወዳደር መንፈሳዊ ሰላም እያገኙ ነው። እነሱን በሚመለከት ሚክያስ “ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፣ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሳም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም። ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፤ የሚያስፈራውም የለም”በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ሚክያስ 4:3, 4፤ ኢሳይያስ 2:2-4) ከዚህም ጋር በመስማማት በምሳሌያዊ ሁኔታ ሰይፋቸውን ማረሻ ጦራቸውን ማጭድ ለማድረግ በመቀጥቀጥ ለጦርነትና ለጠብ ጀርባቸውን ሰጥተዋል። ስለሆነም ምንም ዓይነት ዜግነት፣ ቋንቋ፣ ዘር ወይም ማህበራዊ መደብ ቢኖራቸውም በዓለም አቀፍ ማህበረሰባቸው ሰላማዊ ወንድማማችነት አግኝተዋል። ይሖዋ በእነሱ ላይ በሚያደርገው ከለላ የሚሆን እንክብካቤ የተሞላበት ጥበቃው እርግጠኝነት ደስ ይላቸዋል። “የሚያስፈራቸውም የለም።” “[ይሖዋ (አዓት)] እውነትም ለሕዝቡ ኃይል ሰጥቷል። [ይሖዋ (አዓት)] ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።”—መዝሙር 29:11
20, 21. (ሀ) ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ለመጠበቅ መጣር ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች ሰላም ለማናጋት ስለሚያደርገው ጥረት ምን ለማለት እንችላለን?
20 ይሁን እንጂ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም የአምላክ አገልጋዮች ያላቸው ሰላም የሰይጣንን ጠላትነት አነሳስቷል። የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተቋቋመች በኋላ ከሰማይ ወደ ውጭ ሲጣል ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰይጣን “በሴቲቱ ዘር” ቀሪዎች ላይ ጦርነት ከፍቷል። (ራእይ 12:17) ጳውሎስም እንኳ በዘመኑ “ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን . . . በሰማያዊ ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳዊ ሠራዊት ጋር ትግል (ተጋድሎ) አለን” በማለት አስጠንቅቋል። (ኤፌሶን 6:12) አሁን ሰይጣን በምድር አካባቢ ብቻ ስለተወሰነ ያ ማስጠንቀቂያ አስቸኳይ ነው።
21 ሰይጣን የአምላክን ሕዝብ ሰላም ለማጥፋት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በብልሃት ተጠቅሟል፤ ግን አልተሳካለትም። በ1919 አምላክን በታማኝነት ለማገልገል የሚጥሩ 10,000 የሚሞሉ እንኳ አልነበሩም። ዛሬ ዓለምን በእምነታቸው አማካኝነት ያሸነፉ ከአራት ሚልዮን በላይ አሉ። (1 ዮሐንስ 5:4) እነዚህ የሰይጣንንና የዘሮቹን ጠላትነት መቋቋም ቢኖርባቸውም ከአምላክ ጋርና እርስ በርሳቸው ያላቸው ሰላም እውን ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ ጠላትነት አንጻርና የራሳችንን አለፍጽምናና የምንኖርበትን “አስጨናቂ ጊዜ” ከግምት በማስገባት ሰላማችንን ለመጠበቅ በትጋት መሥራት ይኖርብናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በሚቀጥለው ርዕስ ይህ ምን ምን እንደሚያጠቃልል እንመለከታለን።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ሰው መጀመሪያ ከአምላክ ጋር የነበረውን ሰላም ያጣው ለምንድን ነው?
◻ የእሥራኤል ሕዝብ ከአምላክ ጋር የሚኖራቸው ሰላም በምን ላይ የተመሠረተ ነበር?
◻ በአሁኑ ጊዜ ከአምላክ ጋር ሰላም መሆን በምን ላይ የተመሠረተ ነው?
◻ ልባችንን የሚጠብቀው “የአምላክ ሰላም” ምንድን ነው?
◻ ከአምላክ ጋር ሰላም ካለን ምን ተጨማሪ በረከቶች እናገኛለን?