በአምላክ ቤተ መቅደስ ላይ “ልብህን አድርግ”!
“የሰው ልጅ ሆይ፣ . . . በማሳይህም ሁሉ ላይ ልብህን አድርግ፤ የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር።”—ሕዝቅኤል 40:4
1. የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች በ593 ከዘአበ በምን ሁኔታ ሥር ይገኙ ነበር?
ዓመቱ 593 ከዘአበ ሲሆን እስራኤላውያን በግዞት መኖር ከጀመሩ 14 ዓመት ሆኗል። በባቢሎን ይኖሩ ለነበሩት አይሁዶች ውዷ የትውልድ አገራቸው በጣም ሩቅ ሆና ታይታቸው መሆን አለበት። አብዛኞቻቸው ኢየሩሳሌምን ለመጨረሻ ጊዜ ያዩአት በእሳት ስትጋይና ትላልቅ ቅጥሮቿም ሆኑ የሚያኮሩ ሕንጻዎቿ የፍርስራሽ ክምር ሲሆኑ ነው። በአንድ ወቅት የከተማይቱ የክብር አክሊል እንዲሁም በመላው ምድር ብቸኛው የንጹሕ አምልኮ ማዕከል የነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ወድሟል። እስራኤላውያን ገና በርካታ የግዞት ዘመናት ከፊታቸው ይጠብቋቸዋል። በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት ነጻ ለመውጣት 56 ዓመት ይቀራቸዋል።—ኤርምያስ 29:10
2. በኢየሩሳሌም ይገኝ የነበረው የአምላክ ቤተ መቅደስ ትውስታዎች ሕዝቅኤልን ያሳዘኑት ለምን ነበር?
2 የአምላክ ቤተ መቅደስ በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ ሥፍራ የፍርስራሽ ክምርና የዱር አራዊት መፈንጫ መሆኑን ማሰብ ታማኙን ነቢይ ሕዝቅኤልን በጣም ሳያሳዝነው አልቀረም። (ኤርምያስ 9:11) የገዛ አባቱ ቡዝ በዚህ ቤተ መቅደስ በክህነት አገልግሎ ነበር። (ሕዝቅኤል 1:3) ሕዝቅኤል ገና በለጋ ዕድሜው በ617 ከዘአበ ከኢየሩሳሌም መኳንንት ጋር ወደ ግዞት ባይወሰድ ኖሮ የዚህ መብት ተካፋይ ይሆን ነበር። አሁን ግን 50 ዓመት የሚሆነው ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌምን ፈጽሞ ዳግመኛ እንደማያያትና በቤተ መቅደሱ ግንባታ ምንም የመካፈል አጋጣሚ እንደማይኖረው እንደሚገነዘብ ግልጽ ነው። ስለዚህ ሕዝቅኤል ታላቅ ግርማ ያለው ቤተ መቅደስ በራእይ ሲመለከት እንዴት እንደሚሰማው ልትገምቱ ትችላላችሁ!
3. (ሀ) ሕዝቅኤል የቤተ መቅደሱን ራእይ የተመለከተበት ዓላማ ምን ነበር? (ለ) የራእዩ አራት አበይት ክፍሎች ምንድን ናቸው?
3 ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘውና የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ዘጠኝ ምዕራፎች የሞላው ይህ ራእይ በግዞት ላይ ለነበሩት አይሁዳውያን እምነት የሚያጠነክር ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ንጹሕ አምልኮ በድጋሚ ይቋቋማል! ከዚያ ወዲህ ባሉት መቶ ዘመናት፣ እስከዚህ እስከ እኛ ዘመን ድረስ ይህ ራእይ ይሖዋን ለሚወዱ ሁሉ የመጽናኛ ምንጭ ሆኖ አገልግሏል። እንዴት? ሕዝቅኤል ያየው ይህ ትንቢታዊ ራእይ በግዞት ለነበሩት እስራኤላውያን ምን ትርጉም እንደነበረው እንመልከት። አራት አበይት ክፍሎች አሉት:- ቤተ መቅደሱ፣ ክህነቱ፣ አለቃውና ምድሪቱ ናቸው።
ቤተ መቅደሱ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ
4. በራእዩ መጀመሪያ ላይ ሕዝቅኤል የተወሰደው ወዴት ነው? በዚያስ ምን ተመለከተ? ቦታውን ያስጎበኘውስ ማን ነው?
4 በመጀመሪያ ሕዝቅኤል “እጅግ በረዘመ ተራራ ላይ” እንዲወጣ ተደረገ። ከተራራው በስተ ደቡብ የታጠረች ከተማ የሚመስል አንድ ግዙፍ ቤተ መቅደስ አለ። “መልኩ እንደ ናስ መልክ የመሰለ” አንድ መልአክ ሕንጻዎቹን ለነቢዩ አንድ በአንድ ያስጎበኘዋል። (ሕዝቅኤል 40:2, 3) ራእዩ እየቀጠለ ሲሄድ መልአኩ ሦስቱን ጥንድ ተካፋች በሮች ከነዘበኞቹ ጓዳ፣ የውጩን አደባባይ፣ የውስጠኛውን አደባባይ፣ የዕቃ ቤቶቹን፣ መሠዊያውን፣ ቤተ መቅደሱን ከቅድስቱና ከቅድስተ ቅዱሳኑ ጋር በጥንቃቄ ሲለካ ሕዝቅኤል ተመለከተ።
5. (ሀ) ይሖዋ ለሕዝቅኤል ምን የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶታል? (ለ) ከቤተ መቅደሱ መወገድ የነበረባቸው ‘የነገሥታቶቻቸው ሬሳ’ የተባሉት ነገሮች ምንድን ነበሩ? ይህስ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?
5 ከዚያ በኋላ ይሖዋ ራሱ በራእዩ ታየ። ወደ ቤተ መቅደሱ በመግባት በዚያ እንደሚኖር ለሕዝቅኤል አረጋገጠለት። ይሁን እንጂ ይሖዋ በቅድሚያ ቤቱ እንዲጸዳ እንዲህ ሲል ጠየቀ:- “አሁንም ግልሙትናቸውንና የነገሥታቶቻቸውን ሬሳ ከእኔ ዘንድ ያርቁ፣ እኔም ለዘላለም በመካከላቸው አድራለሁ።” (ሕዝቅኤል 43:2-4, 7, 9) ‘የነገሥታቶቻቸው ሬሳ’ የተባሉት ጣዖቶቻቸው እንደሆኑ ግልጽ ነው። ዓመፀኛ የነበሩት የኢየሩሳሌም ገዥዎችና ሕዝቡ የአምላክን መቅደስ በጣዖቶች አርክሰውት ነበር፤ ጣዖቶቹን ነገሥታት አድርገዋቸው ነበር። (ከአሞጽ 5:26 ጋር አወዳድር።) እነዚህ ጣዖቶች ሕያዋን አማልክት ወይም ነገሥታት እንዳልሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ዓይን አስጸያፊ የሆኑ በድን ነገሮች ናቸው። መወገድ ይኖርባቸዋል።—ዘሌዋውያን 26:30፤ ኤርምያስ 16:18
6. የቤተ መቅደሱ መለካት ምን የሚያመለክት ነበር?
6 የዚህኛው የራእይ ክፍል ዋና መልእክት ምንድን ነው? ንጹሕ አምልኮ በአምላክ ቤተ መቅደስ ሙሉ በሙሉ ተመልሶ እንደሚቋቋም ለግዞተኞቹ አረጋግጦላቸዋል። ከዚህም በላይ የቤተ መቅደሱ መለካት ራእዩ ሙሉ በሙሉ መፈጸሙ የማይቀር ስለመሆኑ መለኮታዊ ዋስትና የሚሰጥ ነበር። (ከኤርምያስ 31:39, 40፤ ዘካርያስ 2:2-8 ጋር አወዳድር።) ማንኛውም የጣዖት አምልኮ ርዝራዥ ተጠራርጎ ይወገዳል። ይሖዋ ቤቱን ዳግመኛ ይባርካል።
ክህነቱና አለቃው
7. ሌዋውያኑንና ካህናቱን በተመለከተ ምን መረጃ ተሰጥቷል?
7 ክህነቱ ጭምር መጣራት ወይም መጽዳት ነበረበት። ሌዋውያን ለጣዖት አምልኮ በመሸነፋቸው ሊገሰጹ ሲሆን የክህነቱ ክፍል የነበሩት የሳዶቅ ልጆች ደግሞ ንጽሕናቸውን ጠብቀው በመኖራቸው ሊመሰገኑና ወሮታ ሊቀበሉ ነው።a ካህናትም ሆኑ ሌዋውያን በየግላቸው ባሳዩት ታማኝነት እየተመዘኑ እንደገና በተገነባው የአምላክ ቤት ውስጥ የአገልግሎት ምድብ ይኖራቸዋል። በተጨማሪም ይሖዋ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷል:- “በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ይለዩ ዘንድ ሕዝቤን ያስተምሩ፣ ንጹሕና ንጹሕ ባልሆነው መካከል ይለዩ ዘንድ ያሳዩአቸው።” (ሕዝቅኤል 44:10-16, 23) ስለዚህ ክህነቱ ተመልሶ ይቋቋማል፤ ካህናቱም በታማኝነት ያሳዩት ጽናት የሚገባውን ወሮታ ያገኛል።
8. (ሀ) የጥንቷ እስራኤል አለቆች እነማን ነበሩ? (ለ) በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የተገለጸው አለቃ በንጹህ አምልኮ ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርግ የነበረው በምን መንገዶች ነው?
8 በተጨማሪም ራእዩ አለቃ የሚባል ግለሰብ መኖሩን ይገልጻል። የእስራኤል ብሔር ከሙሴ ዘመን ጀምሮ አለቆች ነበሩት። አለቃ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ናሲ ሲሆን የአባቶች ቤት አለቃን፣ የአንድን ነገድ ወይም የአንድን ብሔር አለቃ ያመለክታል። በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የእስራኤል ገዥዎች ሕዝቡን በመጨቆናቸው በጅምላ ከተገሰጹ በኋላ ቅኖችና ፍትሐዊ እንዲሆኑ ተመክረዋል። አለቃው ከካህናት ክፍል ባይሆንም ንጹሕ አምልኮን በማስፋፋት ሥራ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፏል። ካህናት ካልሆኑ ነገዶች ጋር በአደባባዩ በሮች ይገባል፣ ይወጣል፤ እንዲሁም በምሥራቅ በር ደጀ ሰላም ተቀምጦም ሕዝቡ የሚያቀርቧቸውን መሥዋዕቶች ይሰጣቸዋል። (ሕዝቅኤል 44:2, 3፤ 45:8-12, 17) ራእዩ በዚህ መንገድ፣ ተመልሶ የሚቋቋመው ብሔር በምሳሌነት የሚጠቀሱ፣ የአምላክን ሕዝብ በማደራጀት ረገድ ካህናቱን የሚረዱና በመንፈሳዊ ጉዳዮች ጥሩ አርዓያ የሚሆኑ መሪዎች በማግኘት እንደሚባረክ ለሕዝቅኤል ሕዝቦች አረጋግጧል።
ምድሪቱ
9. (ሀ) ምድሪቱ መከፋፈል የነበረባት እንዴት ነው? ሆኖም እነማን ርስት አይኖራቸውም? (ለ) የተቀደሰ መባ የተባለው ምን ነበር? ምንስ ይዟል?
9 በመጨረሻም የሕዝቅኤል ራእይ የእስራኤልን ምድር አጠቃላይ ገጽታ ያመለክተናል። ምድሪቱ ለእያንዳንዱ ነገድ ተከፋፍላ በርስትነት ትሰጣለች። አለቃውም ጭምር የራሱ ርስት ይኖረዋል። ካህናቱ ግን ይሖዋ “እኔ ርስታቸው ነኝ” ስላለ ርስት አይኖራቸውም። (ሕዝቅኤል 44:10, 28፤ ዘኁልቁ 18:20) ራእዩ የአለቃው የመሬት ድርሻ የተቀደሰ መባ ከሚባለው ልዩ አካባቢ ግራና ቀኝ እንደሚሆን ያመለክታል። ይህ የተቀደሰ መባ በሦስት ክፍል የተከፈለ እኩል ወርድና ስፋት ያለው አራት ማዕዘን መሬት ሲሆን ላይኛው ክፍል ንሥሐ ለገቡ ሌዋውያን፣ መካከለኛው ክፍል ለካህናት፣ የመጨረሻው ታችኛ ክፍል ደግሞ ለከተማውና በከተማው ዙሪያ ላለው ለም መሬት ተመድቧል። የይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚቆመው ለካህናት በተመደበው መሬት ማለትም በባለ አራት ማዕዘኑ መባ እምብርት ላይ ይሆናል።—ሕዝቅኤል 45:1-7
10. በግዞት ለሚገኙት ታማኝ አይሁዳውያን ስለ ምድሪቱ መከፋፈል የሚናገረው ትንቢት ምን ትርጉም ነበረው?
10 ይህ ሁሉ ገለጻ የግዞተኞቹን ልብ ምን ያህል አነሳስቶ ይሆን! እያንዳንዱ ቤተሰብ የየራሱ ርስት እንደሚኖረው ተረጋግጦለታል። (ከሚክያስ 4:4 ጋር አወዳድር።) በዚህች ምድር ንጹሕ አምልኮ ከፍተኛና ማዕከላዊ የሆነ ቦታ ይኖረዋል። በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ አለቃው ልክ እንደ ካህናቱ ሕዝቡ አዋጥቶ በሚሰጠው መሬት ላይ እንደሚኖር መገለጹን ልብ በሉ። (ሕዝቅኤል 45:16) ስለዚህ በድጋሚ በምትቋቋመው ምድር ሕዝቡ ሥራውን በግንባር ቀደምትነት እንዲመሩ ይሖዋ ለሾማቸው ሰዎች አስፈላጊውን አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ በታዛዥነትም ይተባበራል ማለት ነው። በአጠቃላይ ይህች ምድር የድርጅት፣ የትብብርና የተደላደለ ኑሮ ነጸብራቅ ነበረች።
11, 12. (ሀ) ይሖዋ ዳግመኛ የምትቋቋመውን ምድራቸው እንደሚባርክ ለሕዝቡ በትንቢታዊ ሁኔታ ያረጋገጠው እንዴት ነው? (ለ) በወንዙ ዳርቻዎች የበቀሉት ዛፎች የምን ነገር ሥዕላዊ መግለጫዎች ነበሩ?
11 ይሖዋ ምድራቸውን ይባርክ ይሆን? ትንቢቱ አስደሳች በሆነ ሥዕላዊ መግለጫ መልሱን ይሰጣል። ውኃ ከቤተ መቅደሱ ይወጣና እየሰፋ ሄዶ ሙት ባሕር ሲደርስ ትልቅ ወንዝ ይሆናል። በዚያም ሕይወት የማይኖርበትን ባሕር ፈውሶ በባሕሩ ዳርቻዎች የዓሣ ማጥመድ ኢንዱስትሪ ይስፋፋል። በወንዙ ዳርቻዎች ከዓመት እስከ ዓመት ለምግብነትና ለመድኃኒትነት የሚያገለግል ፍሬ የሚሰጡ ዛፎች ይበቅላሉ።—ሕዝቅኤል 47:1-12
12 ይህ የተስፋ ቃል ለግዞተኞቹ ቀደም ብለው የሰሟቸውንና በታላቅ ናፍቆት የሚጠብቋቸውን ትንቢቶች የሚያረጋግጥና የሚያስተጋባ ነው። የይሖዋ መንፈስ ያለባቸው ነቢያት ከአንድ ጊዜ በላይ እስራኤል እንደገና ተቋቁማ ሰው የሚኖርባት ገነታዊ ምድር እንደምትሆን ገልጸዋል። በድን የነበሩ አካባቢዎች ነፍስ እንደሚዘሩ የሚገልጹ ትንቢቶች በርካታ ናቸው። (ኢሳይያስ 35:1, 6, 7፤ 51:3፤ ሕዝቅኤል 36:35፤ 37:1-14) በመሆኑም ሕዝቡ ሕይወት ሰጪ የሆኑት የይሖዋ በረከቶች ዳግመኛ ከሚሠራው ቤተ መቅደስ እንደ ወንዝ እንደሚፈስሱ ሊጠባበቁ ይችሉ ነበር። በዚህ መንገድ በመንፈሳዊ በድን የነበረው ብሔር ሕይወት ዘርቶ መንቀሳቀስ ይጀምራል። ዳግመኛ የሚቋቋመው ሕዝብ የወደመውን ምድር መልሶ በመገንባት ረገድ በግንባር ቀደምትነት የሚሰለፉ መንፈሳዊ ወንዶች፣ በሌላ አባባል በዚህ ራእይ ውስጥ በታዩት በወንዙ ዳርቻዎች እንደበቀሉት ዛፎች ጻድቃንና ጽኑ የሆኑ ወንዶች በማግኘት ይባረካል። ኢሳይያስም “ከጥንት ጀምሮ ባድማ የነበሩትን” ቦታዎች ስለሚገነቡ “የጽድቅ ዛፎች” ጽፏል።—ኢሳይያስ 61:3, 4
ራእዩ የሚፈጸመው መቼ ነው?
13. (ሀ) ይሖዋ ዳግመኛ የተቋቋመውን ሕዝቡን ‘በጽድቅ ዛፎች’ የባረከው በምን መንገድ ነው? (ለ) ስለ ሙት ባሕር የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?
13 ከግዞት የተመለሱት አይሁድ እነዚህ ተስፋዎች ሳይፈጸሙላቸው በመቅረታቸው ተበሳጭተው ይሆን? በፍጹም! ዳግመኛ የተቋቋሙ ቀሪዎች በ537 ከዘአበ ውድ ወደሆነችው ምድራቸው ተመልሰዋል። ከጊዜ በኋላ እንደ ጸሐፊው ዕዝራ፣ እንደ ነቢዩ ሐጌና ዘካርያስ እንዲሁም እንደ ሊቀ ካህናቱ ኢያሱ ባሉ “የጽድቅ ዛፎች” አመራር ለብዙ ዘመናት ባድማ ሆነው የኖሩት ቦታዎች ዳግመኛ ተገንብተዋል። እንደ ነህምያና ዘሩባቤል ያሉት አለቆች ምድሪቱን በሥርዓትና በፍትሕ አስተዳድረዋል። የይሖዋ ቤተ መቅደስ ዳግመኛ ተገንብቶ የሕይወት ዝግጅቶቹ፣ ማለትም ቃል ኪዳኑን ጠብቆ ከመኖር የሚገኙት በረከቶች ዳግመኛ መፍሰስ ጀምረዋል። (ዘዳግም 30:19፤ ኢሳይያስ 48:17-20) ካገኟቸው በረከቶች አንዱ እውቀት ነበር። ሥርዓተ ክህነቱ ወደ መደበኛ ተግባሩ ተመልሶ ካህናት ሕጉን ለሕዝቡ ማስተማር ጀምረዋል። (ሚልክያስ 2:7) በዚህም ምክንያት ፈውስ አግኝቶ ዓሣዎችን ማፍራት በቻለው ሙት ባሕር እንደታየው ሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት ዘርቶ ፍሬያማ የሆነ የይሖዋ አገልጋይ ለመሆን በቅቷል።
14. የሕዝቅኤል ትንቢት አይሁዶች ከባቢሎን ግዞት በተመለሱ ጊዜ ከተከሰተው የሚልቅ ፍጻሜ የሚኖረው ለምንድን ነው?
14 ታዲያ የሕዝቅኤል ራእይ ፍጻሜ በእነዚህ ክንውኖች ብቻ ተወስኖ ይቀራል? የለም፣ ራእዩ ከዚህ በጣም የሚልቅ ነገር የሚያመለክት ነው። የሚከተሉትን ሁኔታዎች ልብ በሉ። ሕዝቅኤል ያየው ቤተ መቅደስ በተገለጸው ሥፍር መሠረት ሊገነባ የሚችል አይደለም። እርግጥ ነው፣ አይሁዶች ራእዩን በቁም ነገር ተመልክተውት የነበረ ሲሆን አንዳንድ ነገሮችን ቃል በቃል ተግባራዊ አድርገዋል።b ይሁን እንጂ የቀድሞው ቤተ መቅደስ ቆሞበት የነበረው የሞሪያ ተራራ እንኳን በራእይ ለታየው ለዚህ ቤተ መቅደስ አይበቃውም። በተጨማሪም የሕዝቅኤል ቤተ መቅደስ የታየው በከተማዋ ውስጥ ሳይሆን ከዚህች ከተማ ርቆ በሚገኝ ሌላ መሬት ላይ ሲሆን ሁለተኛው ቤተ መቅደስ የተሠራው ግን ከእርሱ በፊት የነበረው ቤተ መቅደስ በነበረባት በኢየሩሳሌም ከተማ ነው። (ዕዝራ 1:1, 2) ከዚህም በላይ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ቃል በቃል ወንዝ ፈልቆ አያውቅም። ስለዚህ የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ የተመለከተው የሕዝቅኤል ትንቢት ፍጻሜ የቅምሻ ያህል ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ ራእዩ በጣም ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ፍጻሜ እንደሚኖረው ያመለክታል።
15. (ሀ) የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሥራውን የጀመረው መቼ ነበር? (ለ) የሕዝቅኤል ራእይ በክርስቶስ ምድራዊ የሕይወት ዘመን አለመፈጸሙን የሚያሳየው ምንድን ነው?
15 የሕዝቅኤል ራእይ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ውስጥ በስፋት በገለጸው የይሖዋ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ላይ ዋነኛ ፍጻሜውን ማግኘት ይኖርበታል ብለን የምንጠብቅበት ጥሩ ምክንያት አለን። ይህ ቤተ መቅደስ ሥራውን የጀመረው ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሆኖ በተቀባበት በ29 እዘአ ነው። ታዲያ የሕዝቅኤል ራእይ በኢየሱስ ዘመን ፍጻሜውን አግኝቷልን? እንዳላገኘ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ሊቀ ካህናት እንደመሆኑ መጠን በመጠመቅ፣ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞትና ወደ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ማለትም ወደ ሰማይ በመግባት የሥርየት ቀን የሚያስተላልፈውን ትንቢታዊ ትርጉም ፈጽሟል። (ዕብራውያን 9:24) ይሁን እንጂ የሕዝቅኤል ራእይ ሊቀ ካህናቱንም ሆነ የሥርየት ቀንን አንድ ጊዜ እንኳን አይጠቅስም። ስለዚህ ራእዩ የመጀመሪያውን መቶ ዘመን እዘአ የሚያመለክት አይመስልም። ታዲያ የሚያመለክተው የትኛውን ዘመን ነው?
16. የሕዝቅኤል ራእይ የታየበት ሥፍራ የትኛውን ሌላ ራእይ ያስታውሰናል? ይህስ የሕዝቅኤል ራእይ አበይት ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ጊዜ ለማወቅ የሚረዳን እንዴት ነው?
16 የዚህን መልስ ለማግኘት ወደ ራእዩ እንመለስ። ሕዝቅኤል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፣ በዚያም ላይ በደቡብ ወገን እንደ ከተማ ሆኖ የተሠራ ነገር ነበረ።” (ሕዝቅኤል 40:2) ይህ ራእይ የታየበት ሥፍራ፣ ማለትም ‘እጅግ የረዘመው ተራራ’ “በመጨረሻውም ዘመን በእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጎርፋሉ” የሚለውን ሚክያስ 4:1ን ያስታውሰናል። ይህ ትንቢት የሚፈጸመው መቼ ነው? ሚክያስ 4:5 ብሔራት የሐሰት አማልክትን በማምለክ ላይ ባሉበት ጊዜ እንደሚጀምር ያመለክታል። እንዲያውም ንጹሕ አምልኮ ከፍ ከፍ ያለውና በአምላክ አገልጋዮች ሕይወት ውስጥ ሊይዝ የሚገባውን ተገቢ ቦታ ያገኘው በዚህ በዘመናችን ማለትም ‘በዘመኑ ፍጻሜ’ ነው።
17. በሚልክያስ 3:1-5 ላይ የሚገኘው ትንቢት በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የታየው ቤተ መቅደስ የጸዳበትን ጊዜ ለማወቅ የሚያስችለን እንዴት ነው?
17 ለዚህ ተሐድሶ ምክንያት የሆነው ነገር ምን ነበር? በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ ከተገለጹት ዋነኛ ክንውኖች አንዱ ይሖዋ ወደ ቤተ መቅደሱ መምጣቱና ቤቱ ከማንኛውም ጣዖት አምልኮ እንዲጸዳ መናገሩ እንደሆነ አስታውሱ። የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ እንዲጸዳ የተደረገው መቼ ነበር? በሚልክያስ 3:1-5 ላይ ይሖዋ ‘ከቃል ኪዳኑ መልእክተኛ’ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር “ወደ መቅደሱ” ስለሚመጣበት ጊዜ ተናግሯል። የሚመጣበት ዓላማ ምን ነበር? “እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና” ይሆናል። ይህ የማጥራት ሥራ የጀመረው በአንደኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ነበር። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ይሖዋ በቤቱ መኖር ከመጀመሩም በላይ ከ1919 ጀምሮ የሕዝቡን መንፈሳዊ ምድር ባረከ። (ኢሳይያስ 66:8 NW) ስለዚህ ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደስ የተናገረው ትንቢት በመጨረሻው ቀን ትልቅ ፍጻሜ ይኖረዋል ብለን ለመደምደም እንችላለን።
18. የቤተ መቅደሱ ራእይ የመጨረሻውን ፍጻሜ የሚያገኘው መቼ ነው?
18 የሕዝቅኤል ራእይ፣ እንደ ሌሎቹ የተሐድሶ ትንቢቶች ሁሉ፣ ሌላ ተጨማሪና የመጨረሻ ፍጻሜ በገነት ውስጥ ይኖረዋል። ቅን ልብ ያላቸው የሰው ልጆች ከአምላክ የቤተ መቅደስ ዝግጅት ሙሉ ጥቅም የሚያገኙት በዚያ ጊዜ ብቻ ነው። በዚያ ጊዜ ክርስቶስ ከ144,000ዎቹ ሰማያዊ ካህናቱ ጋር ሆኖ የቤዛዊ መሥዋዕቱን ጥቅሞች ለሰው ልጆች ያዳርሳል። የክርስቶስን አገዛዝ በታዛዥነት የሚቀበሉ የሰው ልጆች በሙሉ ወደ ፍጽምና ከፍ ከፍ ይደረጋሉ። (ራእይ 20:5, 6) ይሁን እንጂ የሕዝቅኤል ራእይ ዋነኛ ፍጻሜውን የሚያገኘው በገነት ሊሆን አይችልም። ለምን?
ራእዩ በዚህ በእኛ ዘመን ላይ ያነጣጠረ ነው
19, 20. የራእዩ አቢይ ፍጻሜ በገነት ውስጥ ሳይሆን በዚህ በጊዜያችን መሆን ያለበት ለምንድን ነው?
19 ሕዝቅኤል ከጣዖት አምልኮና ከመንፈሳዊ ምንዝር መጽዳት የሚያስፈልገው ቤተ መቅደስ ተመልክቷል። (ሕዝቅኤል 43:7-9) በገነት ውስጥ በሚኖረው የይሖዋ አምልኮ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንደማይኖር የተረጋገጠ ነው። ከዚህም በላይ በራእዩ ውስጥ የታዩት ካህናት የሚያመለክቱት ገና በምድር ላይ ያሉትን ቅቡዓን የካህናት ክፍል እንጂ ሰማያዊ ትንሣኤ ያገኙትን ወይም በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት ያሉትን አይደለም። ለምን? ካህናቱ በውስጠኛው አደባባይ በማገልገል ላይ እንደሆኑ መገለጹን ልብ በሉ። ይህ አደባባይ የክርስቶስ የበታች ካህናት በምድር ላይ ሳሉ የሚገኙበትን በዓይነቱ ልዩ የሆነ መንፈሳዊ አቋም እንደሚያመለክት ቀደም ያሉ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች አመልክተዋል።c በተጨማሪም ራእዩ የካህናቱን ፍጹም አለመሆን ጎላ አድርጎ እንደሚገልጽ አስተውሉ። ለገዛ ራሳቸው ኃጢአት መሥዋዕት እንደሚያቀርቡ ተነግሯቸዋል። በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባር ሊረክሱ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ “መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ” ያለላቸውን ከሙታን የተነሡ ቅቡዓን አያመለክቱም። (1 ቆሮንቶስ 15:52 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ ሕዝቅኤል 44:21, 22, 25, 27) በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የታዩት ካህናት ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው ሕዝቡን በቀጥታ የሚያገለግሉ ናቸው። በዚያን ጊዜ የካህናቱ ክፍል በሰማይ ስለሚሆን በገነት ውስጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ራእዩ ቅቡዓኑ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ከሚኖሩት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ጋር እንዴት በቅርብ ተባብረው እንደሚያገለግሉ በጥሩ ሁኔታ ያሳያል።—ራእይ 7:9፤ ሕዝቅኤል 42:14
20 ስለዚህ ሕዝቅኤል የተመለከተው የቤተ መቅደስ ራእይ በአሁኑ ጊዜ በመካሄድ ላይ ያለው መንፈሳዊ የማጥራት ሥራ ያስገኛቸውን መልካም ውጤቶች ያመላከተ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ይህ አእምሮን ለማመራመር ተብሎ ብቻ የቀረበ ሃይማኖታዊ እንቆቅልሽ አይደለም። ለብቸኛው እውነተኛ አምላክ ለይሖዋ ከምታቀርበው የዕለት ተዕለት አምልኮ ጋር ትልቅ ተዛምዶ ያለው ራእይ ነው። በሚቀጥለው ርዕሳችን ላይ ይህ የሆነበትን ምክንያት እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሕዝቅኤል ራሱ የሳዶቅ የክህነት ቤተሰብ ክፍል እንደሆነ ስለሚነገር ይህ እሱንም የሚመለከት ሳይሆን አልቀረም።
b ለምሳሌ ያህል ዳግመኛ የተገነባው መሠዊያ፣ የቤተ መቅደሱ ጥንድ ተካፋች በሮችና የዕቃ ቤቱ አካባቢዎች የተገነቡት ከሕዝቅኤል ራእይ ጋር እንዲስማሙ ተደርገው እንደነበረ የጥንቱ ሚሽና ይናገራል።
[ታስታውሳለህን?]
◻ ስለ ቤተ መቅደሱና ሥርዓተ ክህነቱ የሚናገረው የሕዝቅኤል ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜ ምን ነበር?
◻ ስለ ርስት ክፍፍል የሚናገረው የሕዝቅኤል ራእይ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?
◻ በጥንቷ እስራኤል ዳግመኛ ግንባታ ወቅት ታማኝ አለቃዎች የነበሩት እነማን ናቸው? “የጽድቅ ዛፎች” ሆነው ያገለገሉትስ እነማን ነበሩ?
◻ የሕዝቅኤል የቤተ መቅደስ ራእይ አቢይ ፍጻሜ በመጨረሻ ቀናት ውስጥ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?