የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የሕዝቅኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2
ጊዜው ታኅሣሥ 609 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። የባቢሎን ንጉሥ ኢየሩሳሌምን ለመጨረሻ ጊዜ ከቧታል። እስካሁን ድረስ ሕዝቅኤል፣ በባቢሎን ለሚገኙት ግዞተኞች የነገራቸው መልእክት ያተኮረው በተወደደችው ከተማ ማለትም በኢየሩሳሌም መውደቅና መጥፋት ላይ ነው። አሁን ግን የሕዝቅኤል ትንቢት ጭብጥ ተለውጦ የአምላክ ሕዝቦች ሲጠፉ በሚደሰቱ አረማውያን ብሔራት ላይ ጥፋት እንደሚመጣ እየተናገረ ነው። ኢየሩሳሌም ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ስትወድቅ ደግሞ የሕዝቅኤል መልእክት እንደገና ተለውጦ ስለ እውነተኛው አምልኮ መልሶ መቋቋም የሚናገር ይሆናል።
ከሕዝቅኤል 25:1 እስከ 48:35 ያሉት ዘገባዎች ስለ አምላክ ሕዝቦች ነፃ መውጣት እንዲሁም በእስራኤል ዙሪያ ስላሉት ብሔራት የሚናገሩ ትንቢቶችን ይዘዋል።a በሕዝቅኤል 29:17-20 ላይ ካለው ዘገባ በስተቀር ሌሎቹ የተቀመጡት በተፈጸሙበት የጊዜ ቅደም ተከተልና በርዕሰ ጉዳይ ነው። እነዚህ አራት ቁጥሮች ግን የተፈጸሙበትን የጊዜ ቅደም ተከተል ሳይጠብቁ በርዕሰ ጉዳይ ብቻ የተቀመጡ ናቸው። የሕዝቅኤል መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል እንደመሆኑ መጠን መልእክቱ “ሕያውና የሚሠራ ነው።”—ዕብራውያን 4:12
‘ይህ ምድር እንደ ዔድን ገነት ይመስላል’
ኢየሩሳሌም ስትወድቅ አሞን፣ ሞዓብ፣ ኤዶም፣ ፍልስጥኤም፣ ጢሮስና ሲዶና በሰጡት ምላሽ ምክንያት ይሖዋ በእነዚህ ብሔራት ላይ የጥፋት ትንቢት እንዲናገር ሕዝቅኤልን አዘዘው። ግብጽ ትበዘበዛለች። ‘የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንና ስፍር ቊጥር የሌለው ሕዝቡ’ ‘በባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ’ በሚቆረጠው የዝግባ ዛፍ ተመስለዋል።—ሕዝቅኤል 31:2, 3, 12፤ 32:11, 12
በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌም ከጠፋች ከስድስት ወር በኋላ ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ ሕዝቅኤል መጥቶ “ከተማዪቱ ወደቀች!” አለው። ነቢዩ በምርኮ ላሉት ሰዎች ‘ከዚያ በኋላ ዝም አላለም።’ (ሕዝቅኤል 33:21, 22) ሕዝቅኤል፣ ስለ መልሶ መቋቋም የሚናገር ትንቢት ያውጃል። ይሖዋ ‘በእነርሱ ላይ አንድ እረኛ ማለትም ባሪያውን ዳዊትን ያቆማል።’ (ሕዝቅኤል 34:23) ኤዶም ባድማ ስትሆን ከእሷ ባሻገር ያለችው ምድር ማለትም ይሁዳ “እንደ ዔድን ገነት” ትሆናለች። (ሕዝቅኤል 36:35) ይሖዋ ተመልሰው የሚቋቋሙትን ሕዝቦቹን ‘ከጎግ’ ጥቃት እንደሚጠብቃቸው ቃል ገባ።—ሕዝቅኤል 38:2
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
29:8-12—ግብጽ ለ40 ዓመታት ባድማ የሆነችው መቼ ነበር? ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከጠፋች በኋላ ከጥፋቱ የተረፉ አይሁዳውያን የነቢዩ ኤርምያስን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለው ወደ ግብጽ ሸሽተው ነበር። (ኤርምያስ 24:1, 8-10፤ 42:7-22) ሆኖም ናቡከደነፆር በግብጽ ላይ ዘምቶ ድል ስላደረጋት ከባቢሎናውያን አላመለጡም። ግብጽ ለ40 ዓመታት ባድማ የሆነችው ከዚህ ወረራ በኋላ ሊሆን ይችላል። የዓለም ታሪክ ይህን ጥፋት በተመለከተ ምንም ማስረጃ ባይሰጠንም ይሖዋ የተናገረውን ትንቢት የሚፈጽም በመሆኑ ይህ ሁኔታ እንደተከሰተ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ኢሳይያስ 55:11
29:18—‘የሁሉም ራስ የተመለጠውና የሁሉም ትከሻ የተላጠው’ እንዴት ነበር? የጢሮስን መሃል ከተማ መያዝ ከባድና አድካሚ ነበር፤ በመሆኑም የናቡከደነፆር ሠራዊት ጭንቅላታቸው በራስ ቁራቸው በመፈግፈጉ ምክንያት ተመልጠው የነበረ ሲሆን ግንብና ምሽግ ለመሥራት የሚያገለግሉ የግንባታ መሣሪያዎችን በመሸከማቸው ደግሞ ትከሻቸው ተልጦ ነበር።—ሕዝቅኤል 26:7-12
ምን ትምህርት እናገኛለን፦
29:19, 20፦ የጢሮስ ሕዝቦች ንብረታቸውን ይዘው ወደ ደሴታቸው በመሸሻቸው ንጉሥ ናቡከደነፆር ከጢሮስ የወሰደው ምርኮ በጣም ጥቂት ነበር። ናቡከደነፆር ኩሩና ራስ ወዳድ የሆነ አረማዊ ገዥ ቢሆንም ለለፋበት ዋጋ ይሖዋ፣ ግብጽን ‘እንደ ሰራዊቱ ደመወዝ’ አድርጎ ሰጥቶታል። እኛም መንግሥታት ለሚሰጡን አገልግሎት ግብር በመክፈል እውነተኛውን አምላክ መምሰል አይገባንም? የሰብዓዊ ባለ ሥልጣናቱ ምግባርም ይሁን ግብሩን የሚጠቀሙበት መንገድ ይህን ግዴታችንን እንዳንፈጽም ሰበብ ሊሆነን አይገባም።—ሮሜ 13:4-7
33:7-9፦ ዘመናዊ ጉበኛ የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎችና አጋሮቻቸው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከመስበክና ስለሚመጣው “ታላቅ መከራ” ሰዎችን ከማስጠንቀቅ ፈጽሞ ወደኋላ ማለት የለባቸውም።—ማቴዎስ 24:21
33:10-20፦ መዳናችን፣ ከመጥፎ አካሄድ ተመልሰን አምላክን በመታዘዝ ላይ የተመካ ነው። በእርግጥም የይሖዋ መንገድ “ቀና” ነው።
36:20, 21፦ ‘የይሖዋ ሕዝብ’ ተብለው የሚጠሩት እስራኤላውያን ከዚህ ስም ጋር በሚስማማ መልኩ ባለመኖራቸው የአምላክን ስም በብሔራት መካከል አርክሰውታል። እኛም በስም ብቻ የይሖዋ አገልጋዮች መሆን የለብንም።
36:25, 37, 38 የ1954 ትርጉም:- በዛሬው ጊዜ ያለን መንፈሳዊ ገነት ‘በተቀደሱ በጎች’ ወይም በተቀደሱ ሰዎች የተሞላ ነው። እኛም የዚህ ቡድን አባላት እንደመሆናችን መጠን ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመኖር ጥረት ማድረግ አለብን።
38:1-23፦ ይሖዋ ሕዝቡን በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ ከሚሰነዘርባቸው ጥቃት እንደሚታደጋቸው ማወቁ እንዴት ያበረታታል! ጎግ “የዚህም ዓለም ገዥ” ለሆነው ለሰይጣን ዲያብሎስ የተሰጠው ስም ሲሆን በዚህ መንገድ መጠራት የጀመረው ከሰማይ ከተባረረ በኋላ ነው። የማጎግ አገር ደግሞ ምድርን የሚያመለክት ሲሆን ሰይጣንና አጋንንቱ በምድር ተወስነው እንዲቆዩ ተደርገዋል።—ዮሐንስ 12:31፤ ራእይ 12:7-12
“የማሳይህንም ሁሉ ልብ ብለህ አስተውል”
የኢየሩሳሌም ከተማ ከወደቀች 14 ዓመታት አልፈዋል። (ሕዝቅኤል 40:1) ሕዝቡ በግዞት የሚቆዩባቸው ተጨማሪ ሃምሳ ስድስት ዓመታት ይቀራሉ። (ኤርምያስ 29:10) ሕዝቅኤል አሁን ወደ 50 ዓመት ይሆነዋል። በራእይ ወደ እስራኤል ምድር ከተወሰደ በኋላ እንዲህ ተባለ:- “የሰው ልጅ ሆይ፤ በዐይንህ እይ፤ በጆሮህ ስማ፤ የማሳይህንም ሁሉ ልብ ብለህ አስተውል።” (ሕዝቅኤል 40:2-4) ሕዝቅኤል፣ በራእይ አዲስ ቤተ መቅደስ ሲመለከት ምን ያህል ተደስቶ ይሆን?
ሕዝቅኤል የተመለከተው አስደናቂ ቤተ መቅደስ 6 የመግቢያ በሮች፣ 30 ዕቃ ቤቶች፣ ቅድስት፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ የእንጨት መሠዊያና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆን መሠዊያ አለው። ከቤተ መቅደሱ ‘የሚወጣው ውሃ’ ቀስ በቀስ ወንዝ ይሆናል። (ሕዝቅኤል 47:1) ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቅኤል ምድሪቱ ለየነገዱ ስትከፋፈል በራእይ ተመለከተ፤ የእያንዳንዱ ነገድ ድርሻ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የሚዘልቅ ሲሆን በይሁዳና በብንያም ነገዶች ድርሻ መካከል ያለው ቦታ ለገዢው ይሆናል። ‘የይሖዋ መቅደስ’ እና ያህዌ ሻማ ተብላ የተጠራችው ‘ከተማ’ የሚገኙት በዚህ ቦታ ላይ ነው።—ሕዝቅኤል 48:9, 10, 15, 35 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፍ ጋር የግርጌ ማስታወሻ
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
40:3 እስከ 47:12—ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ቤተ መቅደስ ምን ያመለክታል? ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ይህ ግዙፍ ቤተ መቅደስ ፈጽሞ አልተገነባም። ይህ ቤተ መቅደስ፣ የአምላክን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ማለትም ይሖዋ በዘመናችን ለንጹሕ አምልኮ ያደረገውን እንደ ቤተ መቅደስ ያለ ዝግጅት ያመለክታል። (ሕዝቅኤል 40:2፤ ሚክያስ 4:1፤ ዕብራውያን 8:2፤ 9:23, 24) ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ የተመለከተው ራእይ ፍጻሜውን ያገኘው “በመጨረሻው ዘመን” ሲሆን በዚህ ወቅት ካህናቱ ተጣርተዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ሕዝቅኤል 44:10-16፤ ሚልክያስ 3:1-3) ይሁን እንጂ ይህ ራእይ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው በገነት ነው። ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ የተመለከተው ራእይ፣ ለአይሁዳውያኑ ግዞተኞች ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋምና እያንዳንዱ አይሁዳዊ ቤተሰብ በምድሪቱ ውስጥ ርስት እንደሚኖረው ተስፋ ሰጥቷቸዋል።
40:3 እስከ 43:17—ቤተ መቅደሱ መለካቱ ምን ትርጉም አለው? የቤተ መቅደሱ መለካት ይሖዋ ንጹሕ አምልኮን በተመለከተ ያለው ዓላማ እንደሚፈጸም የሚያረጋግጥ ምልክት ነው።
43:2-4, 7, 9 የ1954 ትርጉም—ከቤተ መቅደሱ መራቅ የነበረባቸው ‘የነገሥታቶቻቸው ሬሳ’ የተባሉት ምን ነበሩ? ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ሬሳዎቹ ጣዖታትን ያመለክታሉ። የኢየሩሳሌም ገዢዎችና ሕዝቦቿ የአምላክን ቤተ መቅደስ በጣዖታት በማርከስ እነዚህን ጣዖታት ነገሥታቶቻቸው አድርገዋቸው ነበር ማለት ይቻላል።
43:13-20—ሕዝቅኤል በራእይ ያየው መሠዊያ ምን ያመለክታል? ምሳሌያዊው መሠዊያ ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጋር በተያያዘ የአምላክን ፈቃድ ያመለክታል። በቤዛዊው መሥዋዕት ምክንያት ቅቡዓኑ ጻድቃን ሆነው የተቆጠሩ ሲሆን ‘እጅግ ብዙ ሕዝብም’ በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም አላቸው። (ራእይ 7:9-14፤ ሮሜ 5:1, 2) በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውና ‘ከቀለጠ ብረት የተሠራው ገንዳ’ ማለትም ካህናቱ የሚታጠቡበት ትልቅ የውኃ ማጠራቀሚያ ሕዝቅኤል በተመለከተው ራእይ ላይ ያልታየው ለዚህ ሊሆን ይችላል።—1 ነገሥት 7:23-26
44:10-16—ካህናቱ እነማንን ያመለክታሉ? ካህናቱ በዛሬው ጊዜ የሚገኘውን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን ያመለክታሉ። ይሖዋ በ1918 ‘ለማንጠርና ለማንጻት’ በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ሲቀመጥ እነዚህን ቅቡዓን ክርስቲያኖች አጥርቷቸዋል። (ሚልክያስ 3:1-5) ንጹሐን ሆነው የተገኙት ወይም ንስሐ የገቡት በአገልግሎት መብታቸው መቀጠል ችለዋል። ከዚያ በኋላም እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ከዓለም ርኵሰት ራሳቸውን ለመጠበቅ’ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው፤ በዚህ መንገድ ካህናት ያልሆኑትን ነገዶች ለሚያመለክቱት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ምሳሌ ይሆናሉ።—ያዕቆብ 1:27፤ ራእይ 7:9, 10
45:1፤ 47:13 እስከ 48:29—‘ምድሪቱ’ ምን ታመለክታለች? የምድሪቱ መከፋፈልስ? ምድሪቱ የአምላክ ሕዝቦች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ታመለክታለች። አንድ የይሖዋ አምላኪ የሚኖረው የትም ይሁን የት፣ እውነተኛውን አምልኮ እስከደገፈ ድረስ ይህ ሰው ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ በተመለሰችው ምድር ላይ ነው። የምድሪቱ መከፋፈል የተሟላ ፍጻሜውን የሚያገኘው በአዲሱ ዓለም ውስጥ እያንዳንዱ ታማኝ ግለሰብ የራሱ ቦታ ሲኖረው ነው።—ኢሳይያስ 65:17, 21
45:7, 16—ሕዝቡ ለካህናቱና ለገዥው የሚሰጡት መባ ምን ያመለክታል? በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ ይህ መባ፣ በዋነኝነት የሚያመለክተው መንፈሳዊ ድጋፍ መስጠትን ይኸውም እገዛ ማድረግንና የትብብር መንፈስ ማሳየትን ነው።
47:1-5—ሕዝቅኤል ስለ ወንዙ በተመለከተው ራእይ ላይ ውኃው ምን ያመለክታል? ውኃው፣ ይሖዋ ሕይወት እንድናገኝ ያደረጋቸውን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ያመለክታል፤ ከእነዚህም መካከል የክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ እውቀት ይገኙበታል። (ኤርምያስ 2:13፤ ዮሐንስ 4:7-26፤ ኤፌሶን 5:25-27) ወንዙ ደረጃ በደረጃ ጥልቅ እየሆነ የሚሄድ ሲሆን ይህም እውነተኛውን አምልኮ እየተከተሉ ያሉትን አዲሶች ለመቀበል ያስችላል። (ኢሳይያስ 60:22) በሺው ዓመት ግዛት ወቅት ከወንዙ የሚፈሰው የሕይወት ውኃ በጣም የሚጨምር ሲሆን ውኃውም በዚያን ጊዜ በሚከፈቱት “መጻሕፍት” ውስጥ የሚገኘውን ተጨማሪ እውቀት ያካተተ ይሆናል።—ራእይ 20:12፤ 22:1, 2
47:12—ፍሬ የሚያፈሩት ዛፎች ምን ያመለክታሉ? እነዚህ ምሳሌያዊ ዛፎች አምላክ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ለመመለስ ያደረጋቸውን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ያመለክታሉ።
48:15-19, 30-35 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፍ ጋር የግርጌ ማስታወሻ—ሕዝቅኤል በራእይ ያያት ከተማ ምን ታመለክታለች? “ያህዌ ሻማ” የተባለችው ከተማ የምትገኘው ‘የተቀደሰ ባልሆነ’ [የ1980 ትርጉም] ስፍራ መሆኑ ከተማዋ ምድራዊ ነገርን እንደምታመለክት ይጠቁማል። ከተማዋ፣ ጽድቅ ለሚኖርበት “አዲስ ምድር” አባላት ጠቃሚ የሆነውን ምድራዊ አስተዳደር የምታመለክት ይመስላል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህች ከተማ በእያንዳንዱ አቅጣጫ በሮች ያሏት መሆኑ ወደ ከተማዋ በቀላሉ መግባት እንደሚቻል ያመለክታል። በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያሉት የበላይ ተመልካቾችም በቀላሉ የሚቀረቡ መሆን አለባቸው።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
40:14, 16, 22, 26፦ በቤተ መቅደሱ መተላለፊያ ግድግዳ ላይ የዘንባባ ዛፍ መቀረጹ፣ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው ንጹሕ ሥነ ምግባር ያላቸው ብቻ እንደሆኑ ያሳያል። (መዝሙር 92:12) ይህ ደግሞ አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው ምግባራችን ንጹሕ ከሆነ ብቻ መሆኑን ያስተምረናል።
44:23፦ በዘመናችን ያለው የካህናት ክፍል ለሚያቀርበው አገልግሎት አመስጋኞች ልንሆን ይገባል! “ታማኝና ልባም ባሪያ” በይሖዋ ዓይን ንጹሕ የሆነውንና ንጹሕ ያልሆነውን ለመለየት የሚረዳንን መንፈሳዊ ምግብ በወቅቱ ያቀርባል።—ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም
47:9, 11፦ የምሳሌያዊው ውኃ ዋና ገጽታ የሆነው እውቀት በዘመናችንም አስደናቂ ፈውስ እያከናወነ ነው። ሰዎች ይህንን ውኃ የትም ቦታ ሆነው ቢጠጡት በመንፈሳዊ ሕያው ይሆናሉ። (ዮሐንስ 17:3) በሌላ በኩል ግን የሕይወትን ውኃ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ‘ጨው ሆነው ይቀራሉ’ ማለትም ለዘላለም ይጠፋሉ። ‘የእውነትን ቃል በትክክል ለማስረዳት መትጋታችን’ ምንኛ አስፈላጊ ነው!—2 ጢሞቴዎስ 2:15
“የታላቁን ስሜን ቅድስና አሳያለሁ”
በዳዊት የዘር ሐረግ የመጣው የመጨረሻው ንጉሥ ከሥልጣኑ ከወረደ በኋላ እውነተኛው አምላክ፣ ንጉሥ ለመሆን “ባለ መብት” የሆነው እስኪመጣ ድረስ ረዘም ያለ ጊዜ እንዲያልፍ ፈቅዷል። ይሁን እንጂ አምላክ ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አልረሳውም። (ሕዝቅኤል 21:27፤ 2 ሳሙኤል 7:11-16) ይሖዋ፣ “ባሪያዬ ዳዊት” ብሎ የጠራው ግለሰብ “እረኛ” እንዲሁም “ንጉሥ” እንደሚሆን የሕዝቅኤል ትንቢት ያሳያል። (ሕዝቅኤል 34:23, 24፤ 37:22, 24, 25) ይህ ግለሰብ በአምላክ መንግሥት ላይ እየገዛ ካለው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። (ራእይ 11:15) ይሖዋ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ‘የታላቁን ስሙን ቅድስና ያሳያል።’—ሕዝቅኤል 36:23
የአምላክን ቅዱስ ስም የሚያረክሱ ሁሉ በቅርቡ ይጠፋሉ። ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ በማምለክ ስሙን በአኗኗራቸው የሚቀድሱ ግን የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። እንግዲያው በዘመናችን በብዛት እየፈሰሰ ካለው የሕይወት ውኃ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንሁን፤ እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ ለእውነተኛው አምልኮ ዋነኛ ቦታ እንስጥ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ከሕዝቅኤል 1:1 እስከ 24:27 ስላሉት ምዕራፎች ማብራሪያ ለማግኘት በሐምሌ 1, 2007 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን ““የይሖዋ ቃል ሕያው ነው—የሕዝቅኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው አስደናቂ ቤተ መቅደስ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የተጠቀሰው የሕይወት ወንዝ ምን ያመለክታል?
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.