‘በምድራችን’ ላይ የወረደው የይሖዋ በረከት
“ወንዙም በሚመጣበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል።”—ሕዝቅኤል 47:9
1, 2. (ሀ) ውኃ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? (ለ) ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ወንዝ ውኃ ምን ያመለክታል?
ውኃ አስደናቂ የሆነ ፈሳሽ ነው። ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ያለ ውኃ ሊኖር አይችልም። ማናችንም ብንሆን ያለ ውኃ ብዙ ልንቆይ አንችልም። በተጨማሪም ውኃ ቆሻሻን አጥቦ የማስወገድ ችሎታ ስላለው ንጽሕናችንን ለመጠበቅ የምንችለው በውኃ ነው። ስለዚህም ገላችንን፣ ልብሳችንን፣ ምግባችንን ሳይቀር በውኃ እናጥባለን። ይህን ማድረጋችን ከሞት ሊጠብቀን ይችላል።
2 መጽሐፍ ቅዱስ ውኃን ይሖዋ ለሕይወት ያደረገውን ዝግጅቶች ለመግለጽ እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀምበታል። (ኤርምያስ 2:13፤ ዮሐንስ 4:7-15) እነዚህ ዝግጅቶች በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን የአምላክ እውቀትና ሕዝቦቹ በክርስቶስ መሥዋዕታዊ ቤዛ አማካኝነት የሚያገኙትን መንጻት ያካትታሉ። (ኤፌሶን 5:25-27) ሕዝቅኤል በተመለከተው የቤተ መቅደስ ራእይ ውስጥ ከቤተ መቅደሱ የሚፈሰው ተአምራዊ ውኃ እንዲህ ያሉትን ሕይወት ሰጪ በረከቶች ያመለክታል። ይሁን እንጂ ይህ ወንዝ የሚፈስሰው መቼ ነው? ዛሬ ለምንኖረው ለእኛስ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ዳግመኛ በተቋቋመው ምድር የሚፈስስ ወንዝ
3. በሕዝቅኤል 47:2-12 ላይ በተዘገበው መሠረት ሕዝቅኤል ምን ተመልክቷል?
3 የሕዝቅኤል ወገኖች በባቢሎን ግዞተኛ ሆነው የሚኖሩ በመሆናቸው የይሖዋን በረከቶች ለማግኘት ከመጠን በላይ ይጓጉ ነበር። ስለዚህ ሕዝቅኤል ከራእያዊው ቤተ መቅደስ የመነጨ ውኃ ሲፈስ ማየቱ ምንኛ አጽናንቶታል! አንድ መልአክ ወንዙን በ1,000 ክንድ ልዩነት ይለካል። ጥልቀቱ ከቁርጭምጭሚት ወደ ጉልበት፣ ከጉልበት ወደ ወገብ፣ በመጨረሻም በዋና ካልሆነ በስተቀር ለመሻገር የሚያስቸግር ትልቅ ወራጅ ሆነ። ወንዙ ሕይወትና ልምላሜ የሚያመጣ ነው። (ሕዝቅኤል 47:2-12) ሕዝቅኤል እንደሚከተለው ተብሏል:- “በወንዙም አጠገብ በዳሩ ላይ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል።” (ሕዝቅኤል 47:12) ወንዙ ምንም ዓይነት ሕይወት ወደማይኖርበት የሙት ባሕር ሲገባ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት መታየት ጀመሩ! ዓሦች የሚርመሰመሱበት ባሕር ሆነ። ዓሣ የማጥመድ ኢንዱስትሪ ተደራጀ።
4, 5. በኢዩኤል ትንቢት ላይ የተገለጸው ወንዝ በሕዝቅኤል ላይ ከተገለጸው ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
4 ይህ አስደሳች ትንቢት ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት የተነገረ ሌላ ትንቢት እንዲያስታውሱ ሳያደርጋቸው አልቀረም። “ከእግዚአብሔርም ቤት ምንጭ ትፈልቃለች፣ የሰጢምንም ሸለቆ ታጠጣለች።”a (ኢዩኤል 3:18) የኢዩኤል ትንቢትም እንደ ሕዝቅኤል ትንቢት ከቤተ መቅደሱ ማለትም ከአምላክ ቤት ወንዝ እንደሚመነጭና በረሐ የሆነ አካባቢ እንደሚያለመልም ይተነብያል።
5 የኢዩኤል ትንቢት በዚህ በዘመናችን በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ መጠበቂያ ግንብ ሲገልጽ ቆይቷል።b ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው የሕዝቅኤል ትንቢትም የተለየ አይሆንም። ዛሬም ዳግመኛ በተቋቋመው የአምላክ ሕዝቦች ምድር እንደ ጥንቱ የእስራኤል ምድር የይሖዋ በረከቶች ፈስሰዋል።
የተትረፈረፈ በረከት
6. በራእያዊው መሠዊያ ላይ ደም መረጨቱ አይሁዳውያን ምን እንዲያስታውሱ አድርጓቸው መሆን አለበት?
6 ዳግመኛ በተቋቋሙት የአምላክ ሕዝቦች ላይ የፈሰሰው የአምላክ በረከት ከየት የመነጨ ነው? ወንዙ የሚፈስሰው ከአምላክ ቤተ መቅደስ መሆኑን ልብ በሉ። ዛሬም በተመሳሳይ ከይሖዋ የሚመነጩት በረከቶች በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ማለትም ለንጹሕ አምልኮ ባደረገው ዝግጅት በኩል ለሕዝቦቹ ይደርሳሉ። የሕዝቅኤል ትንቢት ሌላ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ይነግረናል። በውስጠኛው አደባባይ ወንዙ ከመሠዊያው በስተ ደቡብ በኩል ያልፋል። (ሕዝቅኤል 47:1) መሠዊያው የሚገኘው በራእያዊው ቤተ መቅደስ መሐል ላይ ነው። ይሖዋ ስለ መሠዊያው አንድ በአንድ ለሕዝቅኤል ሲገልጽለትና የመሥዋዕቶቹ ደም እንዲረጭበት ትእዛዝ ሲሰጠው እናነባለን። (ሕዝቅኤል 43:13-18, 20) ይህ መሠዊያ ለእስራኤላውያን በሙሉ ትልቅ ትርጉም ነበረው። ከብዙ ዘመናት በፊት ከይሖዋ ጋር የገቡት ቃል ኪዳን የጸደቀው ሙሴ በሲና ተራራ ግርጌ በተሠራ መሠዊያ ላይ ደም በረጨ ጊዜ ነበር። (ዘጸአት 24:4-8) ስለዚህ በራእያዊው መሠዊያ ላይ ደም መረጨቱ ዳግመኛ ወደሚታደሰው አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከእርሱ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ጠብቀው እስከኖሩ ድረስ የይሖዋ በረከቶች መፍሰሳቸውን እንደማያቆሙ ሊያስገነዝባቸው ይገባ ነበር።—ዘዳግም 28:1-14
7. ምሳሌያዊው መሠዊያ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ምን ትርጉም ይኖረዋል?
7 ዛሬም በተመሳሳይ የአምላክ ሕዝቦች በሚበልጠው አዲስ ቃል ኪዳን አማካኝነት በረከት አግኝተዋል። (ኤርምያስ 31:31-34) ይኸኛውም ቃል ኪዳን የጸደቀው ከብዙ ዓመታት በፊት በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው። (ዕብራውያን 9:15-20) ዛሬ፣ የዚህ ቃል ኪዳን ተጋቢዎች ከሆኑት ቅቡዓን መካከልም ሆንን የቃል ኪዳኑ ተጠቃሚዎች ከሆኑት “ሌሎች በጎች” ምሳሌያዊው መሠዊያ ለሁላችንም ትልቅ ትርጉም አለው። አምላክ የክርስቶስን መሥዋዕት በሚመለከት ያለውን ፈቃድ የሚያመለክት ምሳሌ ነው። (ዮሐንስ 10:16፤ ዕብራውያን 10:10) ምሳሌያዊው መሠዊያ የቆመው በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ መሐል እንደሆነ ሁሉ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕትም ለንጹሕ አምልኮ እምብርት ነው። ለኃጢአታችን ሥርየትና በዚህም ምክንያት ለወደፊት ተስፋችን ሁሉ መሠረት ነው። (1 ዮሐንስ 2:2) በመሆኑም ከአዲሱ ኪዳን ጋር በሚዛመደው ሕግ፣ ማለትም ‘በክርስቶስ ሕግ’ ለመመላለስ እንጣጣራለን። (ገላትያ 6:2) ይህን እስካደረግን ድረስ ከይሖዋ የሕይወት ዝግጅቶች ተጠቃሚዎች እንሆናለን።
8. (ሀ) በራእያዊው ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ ላይ ምን ነገር አልነበረም? (ለ) በራእያዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚገኙ ካህናት ራሳቸውን የሚያነጹት በምን ታጥበው ነበር?
8 ከእነዚህ ጥቅሞች አንዱ በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም ማግኘት ነው። የራእያዊው ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ፣ በመገናኛው ድንኳንም ሆነ ሰሎሞን በሠራው ቤተ መቅደስ ዋነኛ ቦታ ይታይ የነበረ አንድ ነገር ይጎድለዋል። ካህናቱ ይታጠቡበት የነበረው ትልቅ ኩሬ ወይም ገንዳ የለም። (ዘጸአት 30:18-21፤ 2 ዜና መዋዕል 4:2-6) ታዲያ የሕዝቅኤል ራእያዊ ቤተ መቅደስ ካህናት በምን ታጥበው ሊነጹ ነው? በውስጠኛው አደባባይ በኩል የሚያልፈው ተአምራዊ ወንዝ አለላቸው! አዎን፣ ይሖዋ ንጹሕና ቅዱስ አቋም ሊያገኙ በሚያስችላቸው ዝግጅት ይባርካቸዋል።
9. በዛሬው ጊዜ የቅቡዓኑም ሆነ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ንጹሕ አቋም ሊኖራቸው የሚችለው እንዴት ነው?
9 ዛሬም በተመሳሳይ ቅቡዓኑ በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም በማግኘት ተባርከዋል። ይሖዋ ጻድቃን እንደሆኑ ስለቆጠራቸው ቅዱሳን አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ሮሜ 5:1, 2) ካህናት ባልሆኑት ነገዶች ስለተመሰሉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ምን ለማለት ይቻላል? ይኸው ተአምራዊ ወንዝ እነርሱ በሚያመልኩበት የራእያዊው ቤተ መቅደስ ውጨኛ አደባባይ በኩልም ያልፋል። ስለዚህ ሐዋርያው ዮሐንስ እጅግ ብዙ ሰዎች ነጭና ንጹሕ ልብስ ለብሰው በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ አደባባይ ሲያመልኩ መመልከቱ ምንኛ ተገቢ ነው! (ራእይ 7:9-14) ይህ ወራዳ ዓለም ምንም ዓይነት በደል ቢፈጽምባቸው በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት እስካመኑ ድረስ በይሖዋ ፊት ንጹሐን ሆነው እንደሚታዩ እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ። እምነታቸውን የሚያሳዩት እንዴት ነው? የክርስቶስን ፈለግ በመከተልና በቤዛዊው መሥዋዕቱ ላይ ሙሉ በሙሉ በመታመን ነው።—1 ጴጥሮስ 2:21
10, 11. የምሳሌያዊው ውኃ አንዱ አስፈላጊ ገጽታ ምንድን ነው? ይህስ ከወንዙ መስፋፋት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
10 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ይህ ምሳሌያዊ ውኃ ሌላ አስፈላጊ የሆነ ገጽታ አለው። እርሱም እውቀት ነው። ዳግመኛ በተቋቋመችው የእስራኤል ምድር ይሖዋ ሕዝቡን በካህናቱ አማካኝነት በሚሰጥ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ባርኮ ነበር። (ሕዝቅኤል 44:23) ዛሬም ይሖዋ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ሕዝቡን ‘በንጉሣውያን ካህናት’ በኩል በሚሰጥ የእውነት ቃል ትምህርት አብዝቶ ባርኳል። (1 ጴጥሮስ 2:9) በዚህ በመጨረሻው ቀን ስለ ይሖዋ አምላክና እርሱ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ፣ በተለይም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ መሲሐዊው መንግሥቱ ብዙ እውቀት ሲፈስስ ቆይቷል። ይህንን ጥልቀቱ እየጨመረ የሄደውን የመንፈሳዊ ምግብ ጎርፍ ማግኘታችን እንዴት ድንቅ ነገር ነው!—ዳንኤል 12:4
11 መልአኩ የለካው ወንዝ እያደር ጥልቀቱ እየጨመረ እንደሄደ ሁሉ ከይሖዋ የሚመጡት ሕይወት ሰጪ በረከቶችም ወደተባረከው መንፈሳዊ ምድራችን እየጎረፉ ላሉት በርካታ ሰዎች ሊበቃ በሚችል መጠን በብዛት ፈስሰዋል። ሌላ የተሐድሶ ትንቢት እንዲህ ይላል:- “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ።” (ኢሳይያስ 60:22) እነዚህ ቃላት በትክክል ተፈጽመዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከእኛ ጋር በንጹሕ አምልኮ ለመተባበር ጎርፈዋል! ይሖዋ ወደ እርሱ ለሚመጡ ሁሉ የሚበቃ “ውኃ” አትረፍርፎ ሰጥቷል። (ራእይ 22:17) ምድራዊ ድርጅቱ መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመላው ምድር በመቶ በሚቆጠሩ ቋንቋዎች እንዲያሰራጭ አስችሏል። በተጨማሪም እንደ ብርሌ የጠራ የእውነት ውኃ ለሰው ሁሉ እንዲዳረስ ክርስቲያናዊ የጉባኤና የአውራጃ ስብሰባዎች ተዘጋጅተዋል። እንደነዚህ ያሉት ዝግጅቶች በሰዎች ላይ ምን ዓይነት ለውጥ አስከትለዋል?
ውኃው ሕይወት ይዘራል!
12. (ሀ) በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የተገለጹት ዛፎች ያን ያህል ሊያፈሩ የቻሉት ለምንድን ነው? (ለ) በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ በእነዚህ ፍሬያማ ዛፎች የተወከለው ምንድን ነው?
12 በሕዝቅኤል ራእይ የታየው ወንዝ ሕይወትና ጤና አስገኝቷል። ሕዝቅኤል በወንዙ ዳርና ዳር ስለሚበቅሉት ዛፎች ሲነገረው “ቅጠሉም አይረግፍም፣ ፍሬውም አይጎድልም፤ . . . ፍሬውም ለመብል ቅጠሉም ለመድኃኒት ይሆናል” ተብሎ ነበር። እነዚህ ዛፎች እንዲህ ባለ አስደናቂ መንገድ ፍሬ የሚያፈሩት ለምንድን ነው? ‘ውኃው ከመቅደስ ስለሚወጣ ነው።’ (ሕዝቅኤል 47:12) እነዚህ ምሳሌያዊ ዛፎች የሰው ልጅ ወደ ፍጽምና እንዲመለስ አምላክ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ያደረጋቸውን ዝግጅቶች በሙሉ ያመለክታሉ። በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ቅቡዓን ቀሪዎች መንፈሳዊ ምግብና ፈውስ በመስጠት ሥራ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈዋል። እነዚህ 144,000ዎች ሁሉም ሰማያዊ ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ የክርስቶስ ተባባሪ ገዥዎች በመሆን ከሚያከናውኑት ክህነታዊ አገልግሎት የሚመነጩት ጥቅሞች ወደፊት ይዘረጋሉ፤ በመጨረሻም አዳማዊው ሞት ሙሉ በሙሉ ድል ይነሣል።—ራእይ 5:9, 10፤ 21:2-4
13. በዘመናችን ምን ፈውስ ተከናውኗል?
13 ራእያዊው ወንዝ በድን ወደ ሆነው ሙት ባሕር ገብቶ በዚያ የሚያገኘውን ሁሉ ይፈውሳል። ይህ ባሕር በመንፈሳዊ በድን የሆነን አካባቢ ያመለክታል። ይሁን እንጂ “ወንዙም በመጣበት ስፍራ ሁሉ” ሕይወት ይርመሰመሳል። (ሕዝቅኤል 47:9) በመጨረሻውም ቀን የሕይወት ውኃ ሊደርስ በቻለባቸው ሥፍራዎች የሚኖሩ ሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት አግኝተዋል። በዚህ መንገድ ነፍስ ለመዝራት የመጀመሪያ የሆኑት በ1919 የነበሩት ቅቡዓን ቀሪዎች ናቸው። እንቅስቃሴ አልባ ከሆነው የበድንነት ሁኔታቸው ነቅተው መንፈሳዊ ሕይወት አግኝተዋል። (ሕዝቅኤል 37:1-14፤ ራእይ 11:3, 7-12) ይህ ወሳኝ የሆነ ውኃ ከዚያ ወዲህ በመንፈሳዊ በድን ወደሆኑ ሌሎች ሰዎች ተዳርሶ ሕይወት ሊዘሩ ስለቻሉ ቁጥራቸው በጣም እየጨመረ የመጣ ይሖዋን የሚወዱና የሚያገለግሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ሊገኙ ችለዋል። በቅርቡ ደግሞ ይህ ዝግጅት ከሙታን ለሚነሱ ብዙ ሰዎች ይዘረጋል።
14. በሙት ባሕር ዳርቻ የዓሣ ማጥመድ ሥራ መስፋፋቱ ምን ነገርን በሚገባ ይገልጻል?
14 መንፈሳዊ ሕያውነትና ብርታት ምርታማነትን ያስገኛል። በአንድ ወቅት በድን በነበረው ባሕር ዳርቻዎች ዓሣ የማጥመድ ሥራ መስፋፋቱ ይህንኑ የሚያመለክት ነው። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 4:19) ዓሣ የማጥመዱ ሥራ በመጨረሻው ቀን የጀመረው ከቅቡዓኑ የቀሩትን በመሰብሰብ ቢሆንም በዚያ አላቆመም። የትክክለኛ እውቀትን በረከት የሚጨምረው ከይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የሚወጣው ሕይወት ሰጪ ውኃ በሁሉም ብሔራት የሚገኙ ሰዎችን ሕይወት ይነካል። ይህ ወንዝ በደረሰበት ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወት አስገኝቷል።
15. የአምላክን የሕይወት ዝግጅቶች የሚቀበለው ሁሉም ሰው አለመሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው? የእነዚህ ሰዎች መጨረሻስ ምንድን ነው?
15 እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ ሁሉ ሰው የሕይወትን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናል ወይም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን ከሙታን የሚነሱትም ሁሉም ተቀባዮች ይሆናሉ ማለት አይደለም። (ኢሳይያስ 65:20፤ ራእይ 21:8) መልአኩ የባሕሩ አንዳንድ ክፍሎች እንደማይፈወሱ ተናግሯል። እነዚህ በድን የሆኑ ረግረጋማ ቦታዎች “ጨው እንደሆኑ” ይኖራሉ። (ሕዝቅኤል 47:11) የይሖዋ ሕይወት ሰጪ ውኃ ከሚደርሳቸው የዘመናችን ሰዎችም መካከል ለመቀበል አሻፈረኝ የሚሉ አሉ። (ኢሳይያስ 6:10) በመንፈሳዊ በድንነታቸውና በበሽተኝነታቸው ለመኖር የመረጡ ሁሉ በአርማጌዶን ‘ጨው እንደሆኑ ይኖራሉ’ ማለትም ለዘላለም ይጠፋሉ። (ራእይ 19:11-21) ይህን ውኃ በታማኝነት ሲጠጡ የቆዩት ግን ከጥፋቱ ለመዳንና የዚህን ትንቢት የመጨረሻ ፍጻሜ ለመመልከት ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ።
በገነት የሚፈሰው ወንዝ
16. የሕዝቅኤል የቤተ መቅደስ ራእይ የመጨረሻውን ፍጻሜ የሚያገኘው መቼና እንዴት ነው?
16 ሕዝቅኤል የተመለከተው የቤተ መቅደስ ራእይ እንደ ሌሎቹ የተሐድሶ ትንቢቶች ሁሉ የመጨረሻ ፍጻሜውን የሚያገኘው በሺህ ዓመቱ ግዛት ነው። በዚያ ጊዜ የካህናቱ ክፍል በዚህች ምድር ላይ አይኖርም። “የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት [በሰማይ] ይነግሣሉ” ይላል። (ራእይ 20:6) እነዚህ ሰማያዊ ካህናት ከክርስቶስ ጋር ተባብረው የቤዛዊ መሥዋዕቱን ሙሉ ጥቅሞች ለሰው ልጆች ያዳርሳሉ። በዚህ መንገድ ጻድቃን የሆኑ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ፣ ይድናሉ!—ዮሐንስ 3:17
17, 18. (ሀ) በራእይ 22:1, 2 ላይ ሕይወት ሰጪ የሆነው ወንዝ የተገለጸው እንዴት ነው? ትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው? (ለ) በገነት ውስጥ የሕይወት ውኃ ወንዝ በስፋት መሰራጨት ያለበት ለምንድን ነው?
17 በዚያ ጊዜ ሕዝቅኤል የተመለከተው ወንዝ በጣም ከፍተኛ በሆነ የፈዋሽነት ኃይል የሚፈስስ ያህል ይሆናል። በራእይ 22:1, 2 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዋነኛነት የሚፈጸመው በዚህ ጊዜ ነው:- “በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸበርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ። በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፣ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ።”
18 በሺህ ዓመቱ ግዛት ማንኛውም አካላዊ፣ አእምሮአዊና ስሜታዊ ሕመም ይፈወሳል። አሕዛብ በምሳሌያዊው ዛፍ መፈወሳቸው የሚያመለክተው ይህንን ነው። በክርስቶስና በ144,000ዎቹ በኩል ላገኘናቸው ዝግጅቶች ምሥጋና ይድረስና “በዚያ የሚቀመጥ:- ታምሜያለሁ አይልም።” (ኢሳይያስ 33:24) ይህ ወንዙ ከፍተኛ መስፋፋት የሚያደርግበት ወቅት ይሆናል። ከዚህ ንጹሕ የሕይወት ውኃ ለሚጠጡት በሚልዮን፣ ምናልባትም በቢልዮን የሚቆጠሩ ከሙታን የሚነሱ ሰዎች በቂ እንዲሆን የበለጠ ጥልቀትና ስፋት ማግኘት ይኖርበታል። በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ ወንዙ ሙት ባሕርን ሲፈውስ ውኃው የደረሰበት አካባቢ ሁሉ ነፍስ ዘርቷል። ስለዚህ በገነት ውስጥ የሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች በሙሉ በተዘረጋላቸው ቤዛዊ ጥቅሞች ካመኑ ከወረሱት አዳማዊ ሞት ተፈውሰው ሙሉ በሙሉ ሕያዋን ይሆናሉ። ራእይ 20:12 በዚያ ዘመን ከሙታን ለሚነሱት ጭምር የሚጠቅም ተጨማሪ እውቀትና ማስተዋል የሚሰጡ “ጥቅልሎች” እንደሚከፈቱ ይተነብያል። የሚያሳዝነው ግን በዚህ በገነት እንኳን ለመፈወስ እምቢተኛ የሚሆኑ አንዳንድ ሰዎች ይኖራሉ። ‘ጨው ሆነው እንዲቀሩ’ የሚደረጉት ማለትም ለዘላለም ጥፋት የሚዳረጉት እነዚህ ዓመፀኞች ናቸው።—ራእይ 20:15
19. (ሀ) ስለ መሬት መከፋፈል የሚናገረው ራእይ በገነት ውስጥ የሚፈጸመው እንዴት ይሆናል? (ለ) ከተማው በገነት ውስጥ የሚኖረውን የትኛውን ሁኔታ ያመለክታል? (ሐ) ከተማው ከቤተ መቅደሱ በተወሰነ ርቀት ላይ መገኘቱ ምን ቁም ነገር ያስተላልፋል?
19 በተጨማሪም በዚያ ጊዜ በሕዝቅኤል ራእይ የታየው የርስት ክፍፍል የመጨረሻ ፍጻሜውን ያገኛል። ሕዝቅኤል በራእዩ ውስጥ ምድሪቱ በትክክል ስትከፋፈል ተመልክቷል። እያንዳንዱ ታማኝ ክርስቲያንም በተመሳሳይ በገነት ውስጥ የራሱ የሆነ የርስት ቦታ እንደሚያገኝ እርግጠኛ ሊሆን ይችላል። በራስ ቤት የመኖርና የራስን ቤት የመንከባከብ ፍላጎት ሥርዓት ባለው መንገድ እውን ይሆናል። (ኢሳይያስ 65:21፤ 1 ቆሮንቶስ 14:33) ሕዝቅኤል የተመለከተው ከተማ ይሖዋ ለአዲሱ ምድር ያዘጋጀውን አስተዳደር ማመልከቱ ተገቢ ነው። በዚያ ጊዜ የቅቡዓኑ የካህናት ክፍል በሰው ልጆች መካከል በአካል አይገኝም። ራእዩ ከተማው የሚገኘው ከቤተ መቅደሱ ርቆ በሚገኝ ‘ቅዱስ ያልሆነ’ ሥፍራ እንደሆነ መግለጹ የሚያመለክተው ይህንኑ ነው። (ሕዝቅኤል 48:15 የ1980 ትርጉም) ይሁን እንጂ 144,000ዎቹ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙ ቢሆንም ንጉሡ በምድር ላይ ወኪሎች ይኖሩታል። ምድራዊ ተገዥዎቹ ኢየሱስ ለጽድቅ መሣፍንት ሆነው እንዲገዙ የሚመርጣቸው የአለቃው ክፍል አባሎች ከሚሰጡት ፍቅራዊ አመራር ብዙ ጥቅም ያገኛሉ። ይሁን እንጂ የመንግሥቱ መቀመጫ በምድር ሳይሆን በሰማይ ነው። የአለቃውን ክፍል ጨምሮ በምድር ላይ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ለመሲሐዊው መንግሥት ይገዛል።—ዳንኤል 2:44፤ 7:14, 18, 22
20, 21. (ሀ) የከተማዋ ስም ተስማሚ የሆነው በምን መንገድ ነው? (ለ) የሕዝቅኤልን ትንቢት መገንዘባችን የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን እንድንጠይቅ ሊያደርገን ይገባል?
20 የሕዝቅኤልን ትንቢት የመጨረሻ ቃላት ልብ በሉ። “ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም:- እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] በዚያ አለ ተብሎ ይጠራል።” (ሕዝቅኤል 48:35) ከተማው የሚኖረው ለሰዎች ኃይል ወይም ሥልጣን ለመስጠት ወይም የማንኛውንም ሰው ፈቃድ ለማስፈጸም አይሆንም። ይህች ከተማ የይሖዋን አስተሳሰብ፣ ፍቅራዊና ምክንያታዊ አሠራሩን የምታንጸባርቅ የይሖዋ ከተማ ናት። (ያዕቆብ 3:17) እንዲህ መሆኑ ይሖዋ የተደራጀውን “የአዲስ ምድር” የሰው ልጆች ማኅበረሰብ ለዘላለም እንደሚባርክ ዋስትና ይሰጠናል።—2 ጴጥሮስ 3:13
21 ከፊታችን የሚጠብቀን ተስፋ በጣም አያስፈነድቀንም? ከሆነ ሁላችንም እንዲህ እያልን ራሳችንን ብንጠይቅ ጥሩ ይሆናል:- ‘በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ ለተገለጹት አስደናቂ በረከቶች ምን ምላሽ እሰጣለሁ? ቅቡዓን ቀሪዎችን ጨምሮ ወደፊት የአለቃው ክፍል አባሎች የሚሆኑት አፍቃሪ የበላይ ተመልካቾች የሚያከናውኑትን ሥራ በታማኝነት እደግፋለሁ? ንጹሕ አምልኮን የሕይወቴ ዋነኛ ትኩረት አድርጌአለሁን? በዛሬው ጊዜ በጣም ተትረፍርፎ በመፍሰስ ላይ በሚገኘው የሕይወት ውኃ ሙሉ በሙሉ እጠቀማለሁ?’ ሁላችንም አሁንም ሆነ ለዘላለም በአምላክ የሕይወት መንገድ መደሰታችንን እንቀጥል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህ የሰጢም ሸለቆ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምሥራቅ ተነስቶ ወደ ሙት ባሕር የሚገባውን የቄድሮን ሸለቆ ሳያመለክት አይቀርም። በተለይ ዝቅተኛ ቦታው ውኃ አልባና ዓመቱን ሙሉ ደረቅ ነው።
b የግንቦት 1, 1881 እና ሰኔ 1, 1981 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ እትሞችን ተመልከት።
[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]
◻ ከቤተ መቅደሱ የሚፈሰው ውኃ ምን ያመለክታል?
◻ ይሖዋ በምሳሌያዊው ወንዝ አማካኝነት ምን ፈውስ አከናውኗል? ወንዙ ጥልቀቱ እየጨመረ የሄደው ለምንድን ነው?
◻ በወንዙ ዳርቻ የሚገኙት ዛፎች ምን ያመለክታሉ?
◻ ከተማይቱ በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት ምን ታመለክታለች? የከተማዋ ስም ተስማሚ የሆነው በምን መንገድ ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሕይወት ሰጪ የሆነው ወንዝ የአምላክን የመዳን ዝግጅት ያመለክታል