የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የሕዝቅኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
ወቅቱ 613 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። ነቢዩ ኤርምያስ፣ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋና ይሁዳ ባድማ እንደምትሆን በይሁዳ ሆኖ በድፍረት እየተናገረ ነው። የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር በርካታ አይሁዳውያንን በግዞት ወስዷል። ከእነዚህም መካከል በከለዳውያን ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚያገለግሉት ወጣቱ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ይገኙበታል። አብዛኞቹ የአይሁድ ምርኮኞች “በባቢሎናውያን ምድር” በኮቦር ወንዝ አጠገብ ሰፍረዋል። (ሕዝቅኤል 1:1-3) ይሖዋ ለእነዚህ ምርኮኞች፣ ሕዝቅኤል የተባለውን የ30 ዓመት ጎልማሳ መልእክተኛ አድርጎ ላከው።
የሕዝቅኤል መጽሐፍ የተጠናቀቀው በ591 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን የ22 ዓመታት ታሪክ ይሸፍናል። ሕዝቅኤል መጽሐፉን ያሰፈረው በጥንቃቄና በዝርዝር ነው። ትንቢት የተናገረበትን ዓመት ብቻ ሳይሆን ወሩንና ቀኑን ጭምር መዝግቧል። የሕዝቅኤል መልእክት የመጀመሪያ ክፍል ያተኮረው በኢየሩሳሌም መውደቅና መጥፋት ላይ ነው። ሁለተኛው ክፍል በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉት ብሔራት ላይ የተነገሩ የፍርድ መልእክቶችን የያዘ ሲሆን የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ስለ ይሖዋ አምልኮ መልሶ መቋቋም ይገልጻል። ይህ ርዕስ ኢየሩሳሌም ከሚደርስባት ነገር ጋር የተያያዙ ራእዮችን፣ ትንቢቶችን እንዲሁም ትዕይንቶችን በያዙት ከሕዝቅኤል 1:1 እስከ 24:27 ላይ ባሉት ምዕራፎች ውስጥ የሚገኙትን ጎላ ያሉ ነጥቦች ያብራራል።
“ጠባቂ አድርጌሃለሁ”
ሕዝቅኤል ስለ ይሖዋ ዙፋን የሚገልጽ አስደናቂ ራእይ ከተመለከተ በኋላ የሚከተለው ተልዕኮ ተሰጠው። ይሖዋ እንዲህ አለው:- “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ ቃሌን ስማ፤ የምነግርህንም ማስጠንቀቂያ አስተላልፍላቸው።” (ሕዝቅኤል 3:17) ሕዝቅኤል፣ ሁለት ትዕይንቶችን በማሳየት ስለ ኢየሩሳሌም ከበባና ከበባው ስለሚያስከትለው ውጤት እንዲተነብይ ታዘዘ። ይሖዋ “ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፤ የማምለኪያ ኰረብቶቻችሁን አጠፋለሁ” በማለት የይሁዳን ምድር በተመለከተ በሕዝቅኤል በኩል ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 6:3) ለምድሪቱ ነዋሪዎች ደግሞ “የጥፋት ፍርድ መጥቶባችኋል” ብሏቸዋል።—ሕዝቅኤል 7:7
በ612 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሕዝቅኤል በራእይ ወደ ኢየሩሳሌም የተወሰደ ሲሆን በዚያም በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚፈጸመውን ጸያፍ ተግባር ተመለከተ። ይሖዋ በከሃዲዎቹ ላይ ቁጣውን ለመግለጽ፣ ‘በስድስት ሰዎች’ የተመሰሉትን በሰማይ የሚገኙ ፍርድ አስፈጻሚ ኃይሎች ሲልክ ከጥፋቱ የሚተርፉት ‘በግምባራቸው ላይ ምልክት የተደረገባቸው’ ሰዎች ብቻ ይሆናሉ። (ሕዝቅኤል 9:2-6) ይህ ከመሆኑ በፊት ግን “የእሳት ፍም” ማለትም የአምላክን ቁጣ የሚገልጽ የጥፋት መልእክት በከተማይቱ ላይ መበተን አለበት። (ሕዝቅኤል 10:2) ይሖዋ ክፉዎችን ‘እንደ ሥራቸው ሲከፍላቸው’ የተበተኑትን እስራኤላውያን ግን እንደገና እንደሚሰበስባቸው ቃል ገብቷል።—ሕዝቅኤል 11:17-21
የአምላክ መንፈስ ሕዝቅኤልን ወደ ከለዳውያን አገር መለሰው። ንጉሥ ሴዴቅያስና ሕዝቡ ከኢየሩሳሌም እንደሚሸሹ የሚያመለክት ትዕይንት ሕዝቅኤል አሳየ። ወንዶችና ሴቶች የሐሰት ነቢያትም ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች ተወግዘዋል። ይሁዳም ለምንም ነገር ከማይረባ ወይን ጋር ተመሳስላለች። ስለ ንስርና ወይን የሚገልጸው እንቆቅልሽ ኢየሩሳሌም ለእርዳታ ወደ ግብጽ ፊቷን ማዞሯ የሚያስከትልባትን ከባድ መዘዝ ያሳያል። እንቆቅልሹ፣ ይሖዋ ‘ከቀንበጦቹ ጫፍ አንዱን ቀንጥሶ ከሁሉ ከፍ ባለው ተራራ ላይ እንደሚተክለው’ በሚገልጽ ተስፋ ይደመደማል። (ሕዝቅኤል 17:22) ይሁን እንጂ በይሁዳ “በትረ መንግሥት የሚሆን . . . አልተረፈም።”—ሕዝቅኤል 19:14
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:4-28—በሰማይ የታየው ሠረገላ ምን ያመለክታል? ሠረገላው ታማኝ መንፈሳዊ ፍጡራንን ያቀፈውን የይሖዋን ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ያመለክታል። የሠረገላው ኃይል ምንጭ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ነው። የሠረገላው ነጂ ይሖዋን የሚወክል ሲሆን የእሱን የላቀ ክብር በቃላት ለመግለጽ ያስቸግራል። እርጋታውም በሚያምር ቀስተ ደመና ተመስሏል።
1:5-11—አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት እነማን ናቸው? ሕዝቅኤል ስለ ሠረገላው በተመለከተው ሁለተኛ ራእይ ላይ አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት ኪሩቤል እንደሆኑ ገልጿል። (ሕዝቅኤል 10:1-11፤ 11:22) በዚህኛው ራእይ ላይ የበሬውን ፊት ‘የኪሩብ ፊት’ በማለት ጠርቶታል። (ሕዝቅኤል 10:14) በሬ የኃይልና የጥንካሬ አምሳያ ሲሆን ኪሩቤል ደግሞ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡራን በመሆናቸው ሕዝቅኤል እንዲህ ማለቱ ተገቢ ነው።
2:6—ሕዝቅኤል በተደጋጋሚ “የሰው ልጅ” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? ይሖዋ፣ ሕዝቅኤልን በዚህ መንገድ የጠራው ነቢዩ ሰው መሆኑን እንዲያስታውስ ለማድረግ እንዲሁም በሰብዓዊው መልእክተኛና የመልእክቱ ምንጭ በሆነው መለኮታዊ አካል መካከል ያለውን ታላቅ ልዩነት ለማጉላት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሎች ውስጥ 80 ጊዜ ያህል በዚህ መንገድ የተጠራ ሲሆን ይህም የአምላክ ልጅ ወደ ምድር ሲመጣ፣ ሰው እንጂ ሥጋ የለበሰ መንፈሳዊ አካል እንዳልነበረ በግልጽ ያሳያል።
2:9 እስከ 3:3—ሕዝቅኤል፣ ሰቆቃና ልቅሶ የተጻፈበትን ጥቅልል ሲበላ የጣፈጠው ለምንድን ነው? ጥቅልሉ ለሕዝቅኤል ጣፋጭ እንዲሆንለት ያደረገው ለተሰጠው ተልዕኮ የነበረው አመለካከት ነው። ሕዝቅኤል ነቢይ ሆኖ ይሖዋን በማገልገሉ አመስጋኝ ነበር።
4:1-17—ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌም እንደምትከበብ የሚያመለክተውን ትዕይንት ቃል በቃል አሳይቶታል? ሕዝቅኤል ምግቡን በሰው ዓይነ ምድር ሳይሆን በኩበት ለማብሰል መጠየቁና ይሖዋም እንዲህ እንዲያደርግ መፍቀዱ ነቢዩ ትዕይንቱን ቃል ቃል እንዳሳየው ያመለክታል። ሕዝቅኤል በግራ ጎኑ የተኛው የአሥሩ ነገድ መንግሥት፣ ከተቋቋመበት ከ997 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ ኢየሩሳሌም እስከጠፋችበት እስከ 607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድረስ ለ390 ዓመታት የፈጸመውን ኃጢአት ለመሸከም ነበር። ነቢዩ በቀኝ ጎኑ የተኛው ደግሞ ኤርምያስ ነቢይ ሆኖ ከተሾመበት ከ647 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ እስከ 607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሉት 40 ዓመታት ውስጥ የይሁዳ መንግሥት ለፈጸመው ኃጢአት ነበር። ሕዝቅኤል የሁለቱን መንግሥታት ኃጢአት በተሸከመባቸው 430 ቀናት ውስጥ በቂ ምግብና ውኃ አልነበረውም፤ ይህም በኢየሩሳሌም ከበባ ወቅት ረሃብ እንደሚኖር የሚያሳይ ትንቢት ነበር።
5:1-3—ሕዝቅኤል ለነፋስ ከሚበትነው ጸጉር ጥቂት ወስዶ በመጐናጸፊያው ጫፍ መቋጠሩ ምን ትርጉም አለው? እንዲህ ማድረጉ፣ ይሁዳ ለ70 ዓመታት ባድማ ሆና ከቆየች በኋላ ቀሪዎቹ ወደ ይሁዳ ተመልሰው እውነተኛውን አምልኮ እንደገና እንደሚያቋቁሙ ያመለክታል።—ሕዝቅኤል 11:17-20
17:1-24—ሁለቱ ታላላቅ ንስሮች እነማን ናቸው? የዝግባው ዛፍ ቀንበጥ የተቀነጠበው እንዴት ነው? ይሖዋ የተከለው ‘ለምለም ቀንበጥ’ [የ1980 ትርጉም] ማን ነው? ሁለቱ ንስሮች የባቢሎንንና የግብጽን ገዢዎች ያመለክታሉ። የመጀመሪያው ንስር ወደ ዝግባው ጫፍ ማለትም የዳዊትን የንግሥና መስመር ተከትሎ ወደሚገዛው ንጉሥ መጣ። ይህ ንስር የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን ዮአኪንን በሴዴቅያስ በመተካት ከዛፉ ጫፍ ላይ የላይኛውን ቀንበጥ ቀነጠበ። ሴዴቅያስ ለዚህኛው ንስር ታማኝ ለመሆን መሐላ ቢፈጽምም የሌላውን ንስር ማለትም የግብጽን ንጉሥ እርዳታ ጠየቀ፤ ሆኖም አልተሳካለትም። በምርኮ ወደ ባቢሎን ተወስዶ በዚያው ይሞታል። ይሖዋም “ለምለሙን ቀንበጥ” ማለትም መሲሐዊውን ንጉሥ ይቀነጥሰዋል። ከዚያም ቀንበጡ “ከሁሉ ከፍ ባለው ተራራ ላይ” ይኸውም በሰማይ ባለው የጽዮን ተራራ ላይ ይተከልና ለምድር በረከት የሚያስገኝ ‘ያማረ ዝግባ’ ይሆናል።—ራእይ 14:1
ምን ትምህርት እናገኛለን?
2:6-8፤ 3:8, 9, 18-21፦ ክፉዎችን መፍራትም ሆነ እነርሱን ማስጠንቀቅን የሚጨምረውን የአምላክን መልእክት ከማወጅ ወደ ኋላ ማለት የለብንም። ሰዎች ለምናውጀው መልእክት ቸልተኞች በሚሆኑበት ወይም ተቃውሞ በሚያጋጥመን ወቅት እንደ አልማዝ መጠንከር አለብን። ይሁን እንጂ ልበ ደንዳኖች፣ ለሰዎች የማናስብ ወይም ጨካኞች እንዳንሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ ይሰብክላቸው ለነበሩት ሰዎች ያዝን ነበር፤ እኛም በርኅራኄ ስሜት ተገፋፍተን ለሰዎች መስበክ ይገባናል።—ማቴዎስ 9:36
3:15፦ ሕዝቅኤል ተልዕኮውን ከተቀበለ በኋላ እንዲያውጀው የተነገረውን መልእክት እያብላላ ‘በድንጋጤ ፈዝዞ ለሰባት ቀናት’ በቴል አቢብ ተቀምጦ ነበር። እኛስ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ለመረዳት እንድንችል ለማጥናትና ለማሰላሰል ጊዜ መዋጀት አይኖርብንም?
4:1 እስከ 5:4፦ ሕዝቅኤል ሁለቱን ትንቢታዊ ትዕይንቶች ለማሳየት ትሕትናና ድፍረት ጠይቆበታል። እኛም አምላክ የሰጠንን ማንኛውንም ሥራ በትሕትናና በድፍረት ማከናወን ይኖርብናል።
7:4, 9፤ 8:18፤ 9:5, 10፦ በአምላክ የቅጣት ፍርድ የሚጠፉትን ሰዎች በርኅራኄ ዓይን መመልከት ወይም ማዘን አይኖርብንም።
7:19፦ ይሖዋ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ጊዜ ገንዘብ ምንም ዋጋ አይኖረውም።
8:5-18፦ ክሕደት አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ያለው ዝምድና እንዲበላሽ ያደርጋል። “ከሐዲዎች በንግግራቸው ሰውን ያጠፋሉ።” (ምሳሌ 11:9 የ1980 ትርጉም) ለከሐዲዎች ጆሯችንን ለመስጠት ማሰብ እንኳ አይኖርብንም።
9:3-6፦ ‘ከታላቁ መከራ’ ለመትረፍ፣ ራሳችንን ወስነን የተጠመቅን የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንንና ክርስቲያናዊውን ባሕርይ መላበሳችንን የሚያሳየውን ምልክት ማግኘታችን አስፈላጊ ነው። (ማቴዎስ 24:21) የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር ባነገበው ሰው የተመሰሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምልክት በማድረጉ ማለትም ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው እየተካፈሉ ናቸው። እኛም ምልክታችን እንዳይጠፋብን ከፈለግን በዚህ ሥራ በቅንዓት በመካፈል ልናግዛቸው ይገባል።
12:26-28፦ ሕዝቅኤል በመልእክቱ ለሚያሾፉ ሰዎችም እንኳ “ከተናገርሁት [የይሖዋ] ቃል ከእንግዲህ የሚዘገይ የለም” እንዲላቸው ታዝዞ ነበር። ይሖዋ ይህንን ሥርዓት ከማጥፋቱ በፊት ሰዎች በእሱ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን።
14:12-23፦ መዳን ለማግኘት ኃላፊነታችንን መወጣት ያለብን እኛው ራሳችን ነን። ማንም ሰው እንዲህ ሊያደርግልን አይችልም።—ሮሜ 14:12
18:1-29፦ የምናደርጋቸው ነገሮች ለሚያስከትሉት መዘዝ ተጠያቂዎቹ እኛው ራሳችን ነን።
“ባድማ! ባድማ! ባድማ አደርጋታለሁ”
በ611 ከክርስቶስ ልደት በፊት ማለትም አይሁዳውያን በግዞት በተወሰዱ በሰባተኛው ዓመት የእስራኤል ሽማግሌዎች “የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊጠይቁ” ወደ ሕዝቅኤል መጡ። ሕዝቅኤልም የእስራኤልን ዓመጽ የሚመለከት ረዥም ታሪክ እንዲሁም ይሖዋ ‘ሰይፉን እንደሚመዝዝ’ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ነገራቸው። (ሕዝቅኤል 20:1፤ 21:3) ይሖዋ ለእስራኤል መስፍን (ለሴዴቅያስ) እንዲህ ብሎታል:- “ጥምጥምህን አውልቅ፤ ዘውድህን ጣል፤ እንደ ከዚህ በፊቱ አይሆንም፤ ዝቅ ያለው ከፍ ይላል፤ ከፍ ያለውም ዝቅ ይላል። ባድማ! ባድማ! ባድማ አደርጋታለሁ፤ የሚገባው ባለ መብት [ኢየሱስ ክርስቶስ] እስከሚመጣ ድረስ እንደ ቀድሞው አትሆንም፤ ለእርሱም ደግሞ እሰጣታለሁ።”—ሕዝቅኤል 21:26, 27
ኢየሩሳሌም መጥፎ ድርጊት እንደፈጸመች የሚገልጽ ክስ ቀርቦባታል። የኦሖላ (እስራኤል) እና የኦሖሊባ (ይሁዳ) ኃጢአት ተጋለጠ። ኦሖላ “አብራቸው ላመነዘረች ለአሦራውያን ውሽሞቿ” ተሰጥታለች። (ሕዝቅኤል 23:9) ኦሖሊባም በቅርቡ ባድማ ትሆናለች። በ609 ከክርስቶስ ልደት በፊት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የዘለቀው የኢየሩሳሌም ከበባ ጀመረ። በመጨረሻ ከተማዋ ስትወድቅ አይሁዳውያን በጣም ከመደንገጣቸው የተነሳ ሐዘናቸውን መግለጽ እንኳ ያቅታቸዋል። ሕዝቅኤል፣ ኢየሩሳሌም ስትጠፋ “ያመለጠ ሰው” መጥቶ የከተማዋን መጥፋት እስኪነግረው ድረስ በባቢሎን ለሚገኙት ምርኮኞች የአምላክን መልእክት መናገር የለበትም።—ሕዝቅኤል 24:26, 27
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
21:3—ይሖዋ ከሰገባው የሚመዝዘው ‘ሰይፍ’ ምንድን ነው? ይሖዋ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ፍርዱን ለማስፈጸም የተጠቀመበት ‘ሰይፍ’ የባቢሎን ንጉሥ የሆነው ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ናቸው። ይህ ሰይፍ የአምላክ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል የሆኑትን ኃያላን መንፈሳዊ ፍጥረታትንም ሊጨምር ይችላል።
24:6-14—የብረት ድስቱ መዛግ ምን ያመለክታል? ኢየሩሳሌም በከበባው ወቅት በብረት ድስት ተመስላለች። ብረት ድስቱ መዛጉ በከተማዋ ውስጥ የሚታየውን የሥነ ምግባር ውድቀት ይኸውም ከተማዋ ያፈሰሰችውን ደም እንዲሁም የፈጸመችውን ርኩሰትና ብልግና ያመለክታል። ከተማዋ በጣም ከመርከሷ የተነሳ ድስቱ ባዶውን ከሰል ላይ ተጥዶ በጣም ቢግልም እንኳ ዝገቱ ሊለቅ አልቻለም።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
20:1, 49፦ የእስራኤል ሽማግሌዎች የሰጡት ምላሽ ሕዝቅኤል የተናገረውን እንዳላመኑት ያሳያል። መለኮታዊ ማስጠንቀቂያዎች ሲሰጡን የመጠራጠር ዝንባሌ እንዳይኖረን እንጠንቀቅ።
21:18-22፦ ናቡከደነፆር በጥንቆላ ቢጠቀምም እንኳ ይህ አረማዊ ገዢ ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት እንዲመጣ ያደረገው ይሖዋ ነበር። ይህም አጋንንት እንኳ ይሖዋ የቅጣት ፍርዱን ለማስፈጸም የሚጠቀምባቸው ሰዎች ዓላማውን እንዳይፈጽሙ ማድረግ እንደማይችሉ ያሳያል።
22:6-16፦ ይሖዋ ወሬ ማቀበልን፣ ዝሙትን፣ ኃይልን አላግባብ መጠቀምን እንዲሁም ጉቦ መቀበልን ይጠላል። እንደነዚህ ከመሳሰሉት መጥፎ ድርጊቶች ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ ልናደርግ ይገባል።
23:5-49፦ እስራኤልና ይሁዳ ከሌሎች ብሔራት ጋር ፖለቲካዊ ጥምረት መፍጠራቸው የእነርሱን የሐሰት አምልኮ እንዲከተሉ አድርጓቸዋል። ከዓለም ጋር ወዳጅነት መመሥረት እምነታችንን ሊያጠፋብን ስለሚችል እንዲህ ከማድረግ እንቆጠብ።—ያዕቆብ 4:4
ሕያው የሆነና የሚሠራ መልእክት
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው የሕዝቅኤል መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ 24 ምዕራፎች እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት አግኝተናል! በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች የአምላክን ሞገስ የሚያሳጣን ምን እንደሆነ፣ ምሕረቱን እንዴት ማግኘት እንደምንችልና ክፉዎችን የምናስጠነቅቅበትን ምክንያት ይጠቁማሉ። ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት የተነገረው ትንቢት ይሖዋ ‘አዲስ ነገር ከመብቀሉ በፊት ለሕዝቡ የሚያስታውቅ’ አምላክ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል።—ኢሳይያስ 42:9
በሕዝቅኤል 17:22-24 እና 21:26, 27 ላይ ተመዝግበው እንደሚገኙት ያሉት ትንቢቶች መሲሐዊው መንግሥት በሰማይ እንደሚቋቋም ጠቁመዋል። በቅርቡ ይህ አገዛዝ የአምላክ ፈቃድ በምድር እንዲሆን ያደርጋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ጠንካራ እምነት በመያዝ የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች በጉጉት መጠበቅ እንችላለን። አዎን “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው።”—ዕብራውያን 4:12
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰማይ የታየው ሠረገላ ምን ያመለክታል?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል “ምልክቱ” እንዳይጠፋብን ይረዳናል