ምዕራፍ ሰባት
ዓለምን የለወጡ አራት ቃላት
1. ከረጅም ዘመናት በፊት በግድግዳ ላይ የተጻፉት አራት ቃላት ምን ያህል ሰፊ ትርጉም ነበራቸው?
በተለሰነ ግድግዳ ላይ የተጻፉ አራት ተራ ቃላት ናቸው። ይሁንና እነዚህ አራት ቃላት አንድን ኃያል ገዥ ነፍሱን እስኪስት ድረስ በፍርሃት እንዲርድ አድርገውታል። የሁለት ነገሥታትን ከሥልጣን መውረድና የአንዱን መገደል እንዲሁም የአንድን ታላቅ የዓለም ኃይል ፍጻሜ አስታውቀዋል። እነዚሁ ቃላት ትልቅ ግምት ይሰጠው የነበረ ሃይማኖታዊ ቡድን የውርደት ጽዋ እንዲጎነጭ አድርገዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አብዛኞቹ ሰዎች ለይሖዋ ንጹህ አምልኮም ሆነ ለሉዓላዊነቱ ደንታ ቢስ ሆነው በነበረበት ወቅት የይሖዋ ንጹህ አምልኮ ከፍ እንዲልና ሉዓላዊነቱ እንዲረጋገጥ አድርገዋል። እነዚሁ ቃላት ዛሬ በዓለም ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች ሳይቀር እንድናስተውል ይረዱናል! አራት ቃላት ይህን ሁሉ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው? እስቲ ቀጥለን እንመልከት።
2. (ሀ) ከናቡከደነፆር ሞት በኋላ በባቢሎን የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? (ለ) ከዚያ በኋላ ሥልጣን የያዘው ገዥ ማን ነው?
2 በዳንኤል ምዕራፍ አራት ውስጥ የተገለጹት ሁኔታዎች ከተከናወኑ ብዙ አሥርተ ዓመታት አልፈው ነበር። ለ43 ዓመት በባቢሎን የዘለቀው የኩሩው ንጉሥ የናቡከደነፆር ግዛት እርሱ በሞተበት ዓመት በ582 ከዘአበ አብቅቷል። ከዚያ በኋላ ከቤተሰቡ መካከል በተከታታይ የተነሡ ነገሥታት ቢኖሩም በድንገተኛ ሞት ወይም በተፈጸመባቸው ግድያ ሳቢያ ሁሉም በአጭሩ ተቀጭተዋል። በመጨረሻም ናቦኒደስ የተባለ ሰው አብዮት በማካሄድ ሥልጣን ላይ ወጣ። ሲን ለተባለው የጨረቃ አምላክ ሊቀ ካህናት ሆና ከምታገለግለው ሴት የተወለደው ናቦኒደስ ከባቢሎን ንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር የደም ትስስር የነበረው አይመስልም። አንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት የንግሥናውን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ ሲል የናቡከደነፆርን ሴት ልጅ ያገባ ሲሆን ወንድ ልጃቸውን ብልጣሶርን ተባባሪ ገዥው አድርጎት ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ለዓመታት ያህል በባቢሎን የማስተዳደር ኃላፊነት ሰጥቶት ነበር። እንደዚያ ከሆነ ብልጣሶር የናቡከደነፆር የልጅ ልጅ ነው ማለት ነው። ታዲያ ይሖዋ ማንኛውንም ንጉሥ ሊያዋርድ የሚችል ታላቅ አምላክ መሆኑን ከአያቱ ተሞክሮ ተምሮ ይሆን? በፍጹም!—ዳንኤል 4:37
መረን የለቀቀ ግብዣ
3. የብልጣሶር ግብዣ ምን ይመስል ነበር?
3 የዳንኤል መጽሐፍ አምስተኛ ምዕራፍ የሚጀምረው ስለ አንድ ትልቅ ድግስ በመናገር ነው። “ንጉሡ ብልጣሶር ለሺህ መኳንንቶቹ ትልቅ ግብዣ አደረገ፣ በሺሁም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር።” (ዳንኤል 5:1) የንጉሡን ሚስቶችና ቁባቶች ጨምሮ እነዚህን ሁሉ ሰዎች ማስተናገድ ምን ያህል ትልቅ አዳራሽ እንደሚጠይቅ አስበው! አንድ ምሁር እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “የባቢሎናውያኑ ትላልቅ ግብዣዎች ብዙውን ጊዜ የሚደመደሙት በስካር ቢሆንም እጅግ ድንቅ ናቸው። ጠረጴዛው ላይ ከውጭ አገር የሚመጣ ወይንና የተለያዩ ዓይነት የቅንጦት ምግቦች ይደረደራሉ። አዳራሹ በሽቶ መዓዛ ይሞላል፤ ድምፃውያንና የመሣሪያ ተጫዋቾች ታዳሚዎቹን እንግዶች ያዝናናሉ።” ብልጣሶር ሁሉም እርሱን ሊያዩት በሚችሉበት ቦታ ተቀምጦ ወይኑን ማንደቅደቁን ተያይዞታል።
4. (ሀ) ባቢሎናውያን በጥቅምት 5/6, 539 ከዘአበ ምሽት ፈንጠዝያ ላይ መሆናቸው የሚያስገርመው ለምንድን ነው? (ለ) ባቢሎናውያን በወራሪው ሠራዊት ፊት እንዲተማመኑ ያደረጋቸው ምን ሊሆን ይችላል?
4 በጥቅምት 5/6, 539 ከዘአበ ምሽት ባቢሎናውያን ይህን በመሰለ አስረሽ ምችው ላይ መሆናቸው ያስገርማል። አገራቸው በውጊያ ላይ የነበረች ከመሆኑም ሌላ እነርሱ ድል ርቋቸው ነበር። ከዚህ ትንሽ ቀደም ብሎ ናቦኒደስ በወራሪው የሜዶ ፋርስ ኃይል ድል ተነሥቶ ከባቢሎን ደቡብ ምዕራብ በምትገኘው በቦርሲፕ ጥገኝነት ጠይቋል። አሁን ደግሞ የቂሮስ ሠራዊት ከባቢሎን ውጭ ሠፍሯል። ይሁንና ብልጣሶርና መኳንንቱ ብዙም የተጨነቁ አይመስልም። ደግሞስ ከተማቸው ባቢሎን መች የምትደፈር ሆነችና! ከፍ ያለው ቅጥሯ ወደ ከተማዋ በሚፈስሰው የኤፍራጥስ ውኃ ከተሞላው የመከላከያ ቦይ በላይ ጉብ ብሎ ይታያል። ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ዓመታት በወታደራዊ ዘመቻ ባቢሎንን ድል አድርጎ የያዘ አንድም ሠራዊት አልነበረም። ታዲያ ምን የሚጨነቁበት ምክንያት ይኖራል? ምናልባትም ብልጣሶር በውጭ ያሉ ጠላቶቻቸው ጭፈራውንና ሆታውን ሲሰሙ የባቢሎናውያኑን ትምክህት ተረድተው ወኔ ይከዳቸዋል ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል።
5, 6. ብልጣሶር በወይን ጠጅ ግፊት ምን አደረገ? ይህስ ለይሖዋ ትልቅ ስድብ የነበረው ለምንድን ነው?
5 ብዙም ሳይቆይ ብልጣሶር ያለልክ የወሰደው መጠጥ ሥራውን ጀመረ። ምሳሌ 20:1 “ወይን ጠጅ ፌዘኛ ያደርጋል” ይላል። በዚህ ጊዜ ግን ንጉሡ አስከፊ መዘዝ ያለው ስህተት እንዲፈጽም አድርጎታል። ከይሖዋ ቤተ መቅደስ የተወሰዱት ንዋየ ቅድሳቱ ወደ ግብዣው ቦታ እንዲመጡ አዘዘ። ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ድል ባደረገበት ጊዜ በምርኮ የተወሰዱት እነዚህ ዕቃዎች ለንጹሕ አምልኮ አገልግሎት ብቻ የሚውሉ ነበሩ። ድሮ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ በእነዚህ ዕቃዎች የመጠቀም ሥልጣን የነበራቸው ካህናት እንኳ ንጹሕ እንዲሆኑ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸው ነበር።—ዳንኤል 5:2፤ ከኢሳይያስ 52:11 ጋር አወዳድር።
6 ይሁን እንጂ ብልጣሶር ገና ከዚህም የባሰ ነገር በማድረግ ሊሳለቅ ነው። “ንጉሡና መኳንንቶቹም ሚስቶቹና ቁባቶቹም . . . የወይን ጠጅ እየጠጡ ከወርቅና ከብር ከናስና ከብረት ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገኑ።” (ዳንኤል 5:3, 4) ብልጣሶር የሐሰት አማልክቱን ከይሖዋ በላይ ከፍ ከፍ ማድረጉ ነበር! እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ ደግሞ በባቢሎናውያን ዘንድ የተለመደ ነገር ይመስላል። በምርኮ የነበሩትን አይሁዳውያን ያንጓጥጧቸውና በአምልኳቸው ላይ ያላግጡ የነበረ ሲሆን ወደሚወዷት አገራቸው የመመለስ ምንም ተስፋ እንደሌላቸውም ይነግሯቸው ነበር። (መዝሙር 137:1-3፤ ኢሳይያስ 14:16, 17) ምናልባትም ይህ በመጠጥ የናወዘ ንጉሥ እነዚህን ምርኮኞች ማቃለሉና አምላካቸውን መሳደቡ ሴቶቹና ባለ ሥልጣኖቹ እንዲደነቁለት ሲል እንዲሁም በእነርሱ ፊት ኃያል መስሎ ለመታየት ያደረገው ሊሆን ይችላል።a ይሁን እንጂ ብልጣሶር ከፍ ያለ ሥልጣን እንዳለው ተሰምቶት ቢጀነንም እንኳ ይህ ስሜቱ ብዙም አልዘለቀም።
የግድግዳው ላይ ጽሕፈት
7, 8. የብልጣሶርን ግብዣ የሚያቋርጥ ምን ነገር ተከሰተ? ይህስ በንጉሡ ላይ ምን ውጤት ነበረው?
7 በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “በዚያም ሰዓት የሰው እጅ ጣቶች ወጥተው በንጉሡ ቤት በተለሰነው ግንብ ላይ በመቅረዙ አንጻር ጻፉ፤ ንጉሡም የሚጽፉትን ጣቶች አየ።” (ዳንኤል 5:5) እንዴት የሚያስፈራ ነገር ነው! ከየት መጣ ሳይባል አንድ እጅ ብቅ ብሎ ጥሩ ብርሃን በሚያገኘው ግድግዳ በኩል በአየር ላይ መንቀሳቀስ ጀመረ። ታዳሚዎቹ አፋቸውን ከፍተው ይህን እጅ ሲመለከቱ ድግሱ በምን ዓይነት ፀጥታ እንደሚዋጥ ገምት። እጁም በተለሰነው ግድግዳ ላይ አንድ ምሥጢራዊ መልእክት መጻፍ ጀመረ።b ይህ እጅግ ወሳኝና ፈጽሞ የማይረሳ ክስተት ነበር። ከዚህ የተነሣ እስከ ዛሬም ድረስ ሰዎች ፈጥኖ የሚመጣን ጥፋት ለማመልከት “የግድግዳው ላይ ጽሕፈት” የሚለውን መግለጫ ይጠቀማሉ።
8 ራሱንና አማልክቱን ከይሖዋ በላይ ከፍ ከፍ ለማድረግ የሞከረው ይህ ኩራተኛ ንጉሥ ምን አድርጎ ይሆን? “የዚያን ጊዜም የንጉሡ ፊት ተለወጠበት፣ አሳቡም አስቸገረው፣ የወገቡም ጅማቶች ተፈቱ፣ ጉልበቶቹም ተብረከረኩ።” (ዳንኤል 5:6) ብልጣሶር በተገዥዎቹ ፊት ገናና እና ባለ ግርማ ሆኖ መታየት ፈልጎ ነበር። ነገር ግን ፍርሃት እንዲህ ያደርጋል ወይ እስኪያሰኝ ድረስ ተርበተበተ፣ ፊቱ ተለዋወጠ፣ ወገቡ ተንቀጠቀጠ፣ ሰውነቱ በሙሉ ከመራዱ የተነሣ ጉልበቶቹ ተብረከረኩ። ዳዊት ለይሖዋ ባቀረበው መዝሙር ውስጥ “የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ” ሲል የተናገራቸው ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው።—2 ሳሙኤል 22:1, 28፤ ከምሳሌ 18:12 ጋር አወዳድር።
9. (ሀ) ብልጣሶር ያደረበት ፍርሃት ከአምላካዊ ፍርሃት የተለየ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ንጉሡ ለባቢሎን ጠቢባን ምን ለመስጠት ቃል ገባ?
9 የብልጣሶር ፍርሃት ለይሖዋ ጥልቅ አክብሮት ከማሳደር የመነጨ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ የሆነው አምላካዊ ፍርሃት እንዳልነበር ልብ ማለት ይገባናል። (ምሳሌ 9:10) የንጉሡ ፍርሃት ከጥበብ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ሽብር ነበር።c ሲሰድበው የቆየውን አምላክ ይቅርታ ከመለመን ይልቅ “አስማተኞቹንና ከለዳውያኑን ቃላተኞቹን” ጮኾ ተጣራ። እንዲያውም እንዲህ ሲል አዋጅ አስነገረ:- “ይህን ጽሕፈት ያነበበ ፍቺውንም ያሳየኝ ሐምራዊ ግምጃ ይለብሳል፣ የወርቅም ማርዳ በአንገቱ ዙሪያ ይሆንለታል፣ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ ይሆናል።” (ዳንኤል 5:7) በመንግሥቱ ላይ ሦስተኛ ቦታ መያዝ ማለት በወቅቱ ይገዙ ከነበሩት ከናቦኒደስና ከብልጣሶር ቀጥሎ ያለውን ቦታ መያዝ ማለት ስለነበር ትልቅ ሥልጣን ነበር። ለወትሮው እንዲህ ያለው ሥልጣን ክፍት ይሆን የነበረው ለብልጣሶር ታላቅ ልጅ ነበር። ንጉሡ ግን የዚህን ተዓምራዊ መልእክት ፍቺ ለማወቅ ያን ያህል ጓጉቶ ነበር!
10. ጠቢባኑ በግድግዳው ላይ ያለውን ጽሕፈት ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ውጤት ምን ሆነ?
10 ጠቢባኑ ሰፊው አዳራሽ ውስጥ ገብተው ተኮለኮሉ። ባቢሎን የሐሰት ሃይማኖቶች የሞሉባትና ብዙ ቤተ መቅደሶች የነበሯት ከተማ እንደመሆኗ መጠን እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሞልተዋል። ልዩ ልዩ የድግምት ጽሑፎችን ትርጉም እንፈታለን የሚሉት እጅግ በርካታ እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ጠቢባን ከፊታቸው በተዘረጋው አጋጣሚ እጅግ ፈንጥዘው መሆን አለበት። በታወቁ ሰዎች ፊት ችሎታቸውን የሚያሳዩበት፣ የንጉሡን ሞገስ የሚያተርፉበትና ከፍተኛ ሥልጣን መጨበጥ የሚችሉበት አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል። ይሁን እንጂ እንዴት የሚያሳፍር ነው! “ጽሕፈቱንም ያነብቡ፣ ፍቺውንም ለንጉሡ ያስታውቁ ዘንድ አልቻሉም።”d—ዳንኤል 5:8
11. የባቢሎን ጠቢባን ጽሕፈቱን ሊያነቡት ያልቻሉት ለምን ሊሆን ይችላል?
11 የባቢሎን ጠቢባን ለመረዳት የተቸገሩት ጽሕፈቱን ራሱን ማለትም ፊደላቱን ስለመሆኑ በእርግጠኛነት መናገር አይቻልም። ፊደላቱ የማይታወቁ ሆነው አግኝተዋቸው ቢሆን ኖሮ እነዚህ ይሉኝታ የሌላቸው ሰዎች ንጉሡን ለመደለል የራሳቸውን ታሪክ ፈጥረው ሊናገሩ የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራቸው ነበር። ሌላው አማራጭ ደግሞ ፊደላቱ በቀላሉ የሚነበቡ ሆነው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንደ አረማይክና ዕብራይስጥ ያሉት ቋንቋዎች የሚጻፉት ካለ አናባቢ ስለነበር እያንዳንዱ ቃል የተለያየ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። እንደዚያ ከሆነ እነዚህ ጠቢባን የትኛውን ቃል ለማለት እንደተፈለገ ለመወሰን ተቸግረው መሆን አለበት። የትኛውን ቃል ለማለት እንደተፈለገ ማወቅ ቢችሉ እንኳ ፍችውን ለመናገር የቃሎቹን ትርጉም መረዳት ተስኗቸው ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ አንድ ነገር ተረጋግጧል። የባቢሎን ጠቢባን ምንም አልፈየዱም!
12. ጠቢባኑ ለማንበብ ሳይችሉ መቅረታቸው ምን ነገር አረጋግጧል?
12 በዚህ መንገድ ጠቢባኑ አጭበርባሪዎች መሆናቸው እንዲሁም ትልቅ ግምት ይሰጠው የነበረው ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውም ሐሰት መሆኑ ተረጋገጠ። እንዴት የሚያሳፍሩ ናቸው! ብልጣሶር በእነዚህ ሃይማኖተኞች ላይ የነበረው ትምክህት መና እንደቀረ ሲመለከት እጅግ ደነገጠ፣ ፊቱም ተለወጠበት፣ መኳንንቶቹም “ተደናገጡ።”e—ዳንኤል 5:9
ጥልቅ ማስተዋል ያለው ሰው ተጠራ
13. (ሀ) ንግሥቲቱ ዳንኤል እንዲጠራ ሐሳብ ያቀረበችው ለምንድን ነው? (ለ) ዳንኤል ምን ዓይነት ሕይወት በመምራት ላይ ነበር?
13 በዚህ የጭንቅ ወቅት ንግሥቲቷ ራሷ (የንጉሡ እናት ሳትሆን አትቀርም) ወደ ግብዣው አዳራሽ ገባች። በግብዣው ቦታ የነበረውን ሁከት የሰማችው ይህች ንግሥት በግድግዳው ላይ ያለውን ጽሕፈት ሊፈታ እንደሚችል የምታውቀው ሰው አለ። ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት አባቷ ናቡከደነፆር ዳንኤልን የጠቢባኑ ሁሉ አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር። ንግሥቲቱ “መልካም [“የላቀ፣” NW] መንፈስ፣ እውቀትም፣ ማስተዋልም” ያለው ሰው መሆኑን ታስታውሳለች። ብልጣሶር ዳንኤልን አለማወቁ ነቢዩ ናቡከደነፆር ከሞተ በኋላ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣኑን ሳያጣ እንዳልቀረ ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ዳንኤል ከፍተኛ ሥልጣን ለማግኘት የሚጓጓ ሰው አልነበረም። በዚህ ጊዜ ዕድሜው ወደ ዘጠናዎቹ ውስጥ ሳይገባ አይቀርም። አሁንም የታመነ ሆኖ ይሖዋን በማገልገል ላይ ነው። ባቢሎን ውስጥ ለስምንት አሥርተ ዓመታት ያህል በግዞት ቢቆይም አሁንም የሚታወቀው በዕብራዊ ስሙ ነው። ንግሥቲቷም ጭምር የጠራችው ዳንኤል ብላ ሲሆን ባቢሎናዊ ስሙን እንደ ራሱ ስም አድርጋ አልተጠቀመችበትም። “አሁንም ዳንኤል ይጠራ፣ እርሱም ፍቺውን ያሳያል” ስትል ለንጉሡ አጥብቃ ተናገረች።—ዳንኤል 1:7፤ 5:10-12
14. ዳንኤል የግድግዳውን ጽሕፈት ካየ በኋላ ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ይጠብቀው ነበር?
14 ዳንኤል ተጠርቶ ብልጣሶር ፊት ቀረበ። ንጉሡ ከጥቂት ጊዜ በፊት የዚህን ዕብራዊ አምላክ ሲሳደብ ቆይቶ አሁን ከእርሱ ውለታ መለመኑ እጅግ የሚያሳፍር ነበር። ያም ሆኖ ግን ብልጣሶር ለሌሎቹ እንዳለው ሁሉ ምሥጢራዊዎቹን ቃላት ሊፈታለት ከቻለ የመንግሥቱን ሦስተኛ ቦታ እንደሚሰጠው በመናገር ዳንኤልን ሊያባብለው ሞከረ። (ዳንኤል 5:13-16) ዳንኤልም ዓይኑን ቀና አድርጎ በግድግዳው ላይ ያለውን ጽሕፈት ሲመለከት መንፈስ ቅዱስ ትርጉሙን እንዲያስተውል ረዳው። ከይሖዋ አምላክ የመጣ የጥፋት መልእክት ነበር! ዳንኤል ስለዚህ ከንቱ ንጉሥ የተነገረውን ይህን ከባድ ፍርድ በራሱ በንጉሡ እንዲሁም በሚስቶቹና በመኳንንቶቹ ሁሉ ፊት እንዴት ሊናገር ይችላል? ዳንኤል ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደገባ አስበው! በንጉሡ የማባበያ ቃላትና ባቀረበለት የሀብትና የክብር መደለያ ይሳብ ይሆን? ነቢዩ የይሖዋን መልእክት ቀለል አድርጎ ይነግረው ይሆን?
15, 16. ብልጣሶር ከታሪክ ምን ትልቅ ትምህርት ሳያገኝ ቀርቷል? ዛሬስ ተመሳሳይ ስህተት መሥራት ምን ያህል የተለመደ ነው?
15 ዳንኤል በድፍረት እንዲህ ሲል ተናገረ:- “ስጦታህ ለአንተ ይሁን፣ በረከትህንም ለሌላ ስጥ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነብባለሁ ፍቺውንም አስታውቃለሁ።” (ዳንኤል 5:17) ወዲያውም ዳንኤል፣ ናቡከደነፆር ኃያል ንጉሥ እንደነበረና የፈቀደውን ሊገድል፣ የፈቀደውን ሊመታ፣ የፈቀደውንም ከፍ ከፍ ሊያደርግ ወይም ሊያዋርድ የሚችል እንደነበር ተናገረ። ይሁን እንጂ ናቡከደነፆርን ታላቅ ያደረገው “ልዑሉ አምላክ” መሆኑን ለብልጣሶር ሳያስታውሰው አላለፈም። ንጉሡ በታበየ ጊዜም ያንን ኃያል ንጉሥ ያዋረደው ይሖዋ ነበር። አዎን፣ ናቡከደነፆር “ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፣ የሚወድደውንም እንዲሾምበት” አምኖ ለመቀበል ተገድዶ ነበር።—ዳንኤል 5:18-21
16 ብልጣሶር ‘ይህን ሁሉ ያውቅ’ ነበር። ይሁን እንጂ ከታሪክ ሳይማር ቀረ። እንዲያውም ናቡከደነፆር ባደረበት የተሳሳተ ኩራት ከሠራውም ኃጢአት የባሰ ብልጣሶር በቀጥታ በይሖዋ ላይ የመሳለቅ ድርጊት ፈጽሟል። ዳንኤል የንጉሡን ኃጢአት ፍርጥርጥ አድርጎ ተናገረ። በተጨማሪም በተሰበሰበው የአረማውያን ማኅበር ፊት የሐሰት አማልክት ‘ምንም የማያዩ፣ የማይሰሙና፣ የማያውቁ’ መሆናቸውን በድፍረት ለብልጣሶር ነገረው። ደፋሩ የአምላክ ነቢይ ንግግሩን በመቀጠል ከእነዚህ ምንም የማይፈይዱ አማልክት በተቃራኒ የይሖዋን ታላቅነት ሲናገር ‘ትንፋሽህ በእጁ ነው’ ብሎታል። እስከዛሬም ድረስ ሰዎች ከግዑዛን ነገሮች የተሠሩ አማልክት አሏቸው፤ ገንዘብን፣ ሙያቸውን፣ ክብርንና አልፎ ተርፎም ተድላን እንደ ጣዖት ያመልካሉ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል ማናቸውም ሕይወትን አይሰጡንም። የእያንዳንዳችን ሕልውና የተመካው የምንተነፍሰው አየር ባለቤት በሆነው በይሖዋ ላይ ነው።—ዳንኤል 5:22, 23፤ ሥራ 17:24, 25
እንቆቅልሹ ተፈታ!
17, 18. በግድግዳው ላይ የተጻፉት አራት ቃላት ምንድን ናቸው? ጥሬ ፍቺያቸውስ ምንድን ነው?
17 በዕድሜ የገፋው ነቢይ የባቢሎን ጠቢባን በሙሉ ሊያደርጉት ወዳቃታቸው ነገር መለስ አለ። በግድግዳው ላይ ያለውን የእጅ ጽሕፈት አንብቦ ትርጉሙን አብራራ። ቃላቱ “ሜኔ፣ ሜኔ፣ ቴኬል እና ፓርሲን” የሚሉ ናቸው። (ዳንኤል 5:24, 25 NW) ትርጉማቸው ምንድን ነው?
18 እነዚህ ቃላት ቃል በቃል ከተወሰዱ “አንድ ምናን፣ አንድ ምናን፣ አንድ ሰቅል እና ግማሽ ሰቅል” የሚል ትርጉም አላቸው። እያንዳንዳቸው የገንዘብ ክብደት መለኪያ ሲሆኑ ከትልቅ ወደ ትንሽ በቅደም ተከተል ተመዝግበዋል። እንዴት ያለ እንቆቅልሽ ነው! የባቢሎን ጠቢባን ፊደላቱን እንኳ ማወቅ ቢችሉ ትርጓሜውን መረዳት አለመቻላቸው ምንም አያስገርምም።
19. “ሜኔ” የሚለው ቃል ትርጓሜ ምንድን ነበር?
19 ዳንኤል በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል አስረድቷል:- “የነገሩ ፍቺ ይህ ነው ማኔ [“ሜኔ፣” NW] ማለት፣ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቆጠረው ፈጸመውም ማለት ነው።” (ዳንኤል 5:26) የመጀመሪያው ቃል ተናባቢ ፊደላት አንባቢው እንደሚጨምረው አናባቢ ፊደል “ምናን” ማለትም ሊሆኑ ይችላሉ ወይም በአረማይክ “ተቆጠረ” የሚል ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል። ዳንኤል የአይሁዳውያኑ የግዞት ዘመን ሊያበቃ እንደተቃረበ አሳምሮ ያውቅ ነበር። በትንቢት ከተነገረው 70 ዓመት ውስጥ 68 ዓመታት አልፈው ነበር። (ኤርምያስ 29:10) ታላቁ የጊዜ ጠባቂ ይሖዋ ባቢሎን የዓለም ኃያል መሆኗ የሚያበቃበትን ዘመን ቆርጦ የነበረ ሲሆን ይህ ፍጻሜ በብልጣሶር ታላቅ ግብዣ ላይ ከተገኙት ሰዎች መካከል ማናቸውም ከሚገምቱት በላይ እጅግ ቀርቦ ነበር። ጊዜው ያለቀበት ብልጣሶር ብቻ ሳይሆን አባቱ ናቦኒደስም ጭምር ነበር። “ሜኔ” የሚለው ቃል ሁለት ጊዜ የተጻፈውም የሁለቱም ንግሥና ማክተሙን ለማስታወቅ ሳይሆን አይቀርም።
20. “ቴኬል” ለሚለው ቃል የተሰጠው ማብራሪያ ምን ነበር? ይህስ በብልጣሶር ላይ የሚሠራው እንዴት ነው?
20 በሌላ በኩል ደግሞ “ቴኬል” የተጻፈው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን እሱም በነጠላ ቁጥር ነበር። ይህም በቀጥታ ለብልጣሶር ብቻ የተነገረ መሆኑን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ብልጣሶር ራሱ በተናጠል ለይሖዋ ከፍተኛ ንቀት አሳይቶ ስለነበረ ይህ መሆኑ ተገቢ ነበር። ቃሉ “ሰቅል” ማለት ሲሆን የሚጨመሩት አናባቢዎች ግን “ተመዘነ” የሚል ትርጉም እንዲሰጥ ሊያደርጉትም ይችላሉ። በመሆኑም ዳንኤል ብልጣሶርን እንዲህ አለው:- “ቴቄል [“ቴኬል፣” NW] ማለት፣ በሚዛን ተመዘንህ፣ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው።” (ዳንኤል 5:27) ብሔራት በጠቅላላ በይሖዋ ፊት በሚዛን እንዳለ ትንሽ ትቢያ ያህል ከቁብም የሚቆጠሩ አይደሉም። (ኢሳይያስ 40:15) ዓላማውን ለማጨናገፍ ምንም ኃይል የላቸውም። ታዲያ አንድ ትዕቢተኛ ንጉሥ ብቻውን ምን ሊያደርግ ይችላል? ብልጣሶር ራሱን ከጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ በላይ ከፍ ከፍ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ይህ አፈር የሆነ ደካማ ሰው ይሖዋን እስከመሳደብና በንጹሕ አምልኮ እስከ መሳለቅ ድረስ እጅግ ተዳፍሮ ነበር። ይሁን እንጂ ‘ቀልሎ ተገኝቷል።’ አዎን፣ ብልጣሶር በፍጥነት እየገሰገሰ የነበረውን ፍርድ ሊቀበል ይገባው ነበር!
21. “ፓርሲን” ሦስት ድርብ ትርጉም ያለው ቃል የሆነው እንዴት ነው? ይህስ ቃል ባቢሎን በዓለም ኃያልነቷ ረገድ ወደፊት ምን እንደሚጠብቃት የሚጠቁም ነበር?
21 በግድግዳው ላይ የነበረው የመጨረሻው ቃል “ፓርሲን” የሚል ነው። ዳንኤል በነጠላ ቁጥር “ፔሬስ” ብሎ አንብቦታል። ምናልባትም ይህን ያደረገው አንደኛው ንጉሥ ስለሌለና የሚናገረው ለአንዱ ብቻ ስለነበር ይሆናል። ይህ ሦስት ድርብ ትርጉም ያለው ቃል የይሖዋ ታላቅ እንቆቅልሽ መደምደሚያ ነበር። ቃል በቃል ከተወሰደ ‘ፓርሲን’ ማለት “ግማሽ ሰቅል” ማለት ነው። ይሁን እንጂ ፊደላቱ “መከፋፈል” እና “የፋርስ ሰዎች” የሚሉ ሌሎች ሁለት ትርጉሞችም ሊኖሯቸው ይችላሉ። በመሆኑ ዳንኤል “ፋሬስ [“ፔሬስ፣” NW] ማለት፣ መንግሥትህ ተከፈለ፣ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው” ሲል ተንብዮአል።—ዳንኤል 5:28
22. ብልጣሶር ለእንቆቅልሹ ፍቺ ምን ምላሽ ሰጠ? ምንስ ተስፋ አድርጎ ሊሆን ይችላል?
22 በዚህ መንገድ እንቆቅልሹ ተፈታ። ኃያሏ ባቢሎን በሜዶ ፋርስ ኃይሎች እጅ ልትወድቅ የቀራት ጊዜ ጥቂት ነው። ይህ የጥፋት ፍርድ ሲነገር ብልጣሶር ኩምሽሽ ቢልም ቃሉን አከበረ። አገልጋዮቹ ዳንኤልን ሐምራዊ ግምጃ እንዲያለብሱትና በወርቅ ሐብል እንዲያስጌጡት እንዲሁም የመንግሥቱ ሦስተኛ ገዥ መሆኑ በአዋጅ እንዲነገር አደረገ። (ዳንኤል 5:29) ዳንኤል ክብሩ ለይሖዋ እንደሆነ ስለተገነዘበ የተደረገለትን ነገር በጸጋ ተቀብሏል። እርግጥ ብልጣሶር የይሖዋን ነቢይ ከፍ ከፍ በማድረግ ከይሖዋ የመጣበትን የቅጣት ፍርድ ለማለዘብ አስቦ ሊሆን ይችላል። እንደዚያ አስቦ ከነበረ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ዓይነት ሆኖበታል።
የባቢሎን ውድቀት
23. የብልጣሶር ታላቅ ግብዣ በመካሄድ ላይ በነበረበት ወቅት እንኳ የትኛው ጥንታዊ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ነበር?
23 ብልጣሶርና ባለሟሎቹ ለአማልክቶቻቸው መለኪያቸውን ሲያጋጩና በይሖዋ ላይ ሲሳለቁ ከቤተ መንግሥቱ ውጭ ባለው ጨለማ ውስጥ አንድ ታላቅ ድራማ እየተከናወነ ነበር። ከሁለት መቶ ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ በኢሳይያስ አማካኝነት የተነገረ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ነው። ባቢሎንን በሚመለከት ይሖዋ በእርሷ ምክንያት የሚመጣውን “ትካዜውን ሁሉ አስቀርቻለሁ” ሲል አስቀድሞ ተናግሯል። አዎን፣ ያቺ ክፉ ከተማ በአምላክ የተመረጡ ሕዝቦች ላይ ታደርስ የነበረው ጭቆና ሁሉ ሊያበቃ ነው። እንዴት? ይኸው ትንቢት “ኤላም ሆይ ውጪ፤ ሜዶን ሆይ ክበቢ” ይላል። ከነቢዩ ኢሳይያስ ዘመን በኋላ ኤላም የፋርስ ግዛት ሆናለች። ብልጣሶር በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰውን ትልቅ ግብዣ ባደረገበት ወቅት ፋርስና ሜዶን በባቢሎን ላይ ‘ለመውጣትና’ ‘ለመክበብ’ ኃይላቸውን አስተባብረው ነበር።—ኢሳይያስ 21:1, 2, 5, 6
24. የኢሳይያስ ትንቢት የባቢሎንን አወዳደቅ በሚመለከት ምን ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል?
24 እንዲያውም የእነዚህ ኃይሎች መሪ የሚጠቀምበት ስልትና የግል ስሙ ሳይቀር ማን እንደሚሆን አስቀድሞ ተነግሯል። ቂሮስ የሚባል ሰው በባቢሎን ላይ ይነሣ ዘንድ ይሖዋ እንደሚቀባው ኢሳይያስ ከ200 ዓመታት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። በዘመቻው ወቅት እንቅፋቶች ሁሉ ይወገዱለታል። የባቢሎን ውኃዎች ‘ይደርቃሉ’፤ ታላላቅ በሮችዋም ክፍት ይሆናሉ። (ኢሳይያስ 44:27–45:3) ደግሞም ይህ ተፈጽሟል። የቂሮስ ሠራዊት በወንዙ ውስጥ ማቋረጥ ይችል ዘንድ የውኃው መጠን እንዲቀንስ የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ አስቀየረው። የባቢሎን ቅጥር በሮች ግዴለሽ በሆኑ ጠባቂዎች ክፍት ተትተው ነበር። ከተማይቱ የተወረረችው ነዋሪዎቿ ፈንጠዝያ ላይ በነበሩበት ጊዜ መሆኑን የታሪክ ሰዎችም ይስማሙበታል። ባቢሎን የተያዘችው ያለምንም ተቃውሞ ነው ለማለት ይቻላል። (ኤርምያስ 51:30) ይሁንና ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱ ይታወቃል። ዳንኤል እንዲህ ብሏል:- “በዚያ ሌሊት የከለዳውያን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ። ሜዶናዊውም ዳርዮስ መንግሥቱን ወሰደ፤ ዕድሜውም ስድሳ ሁለት ዓመት ነበረ።”—ዳንኤል 5:30, 31
ከግድግዳው ላይ ጽሕፈት መማር
25. (ሀ) የጥንቷ ባቢሎን ዛሬ ላለው ምድር አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ሥርዓት ተስማሚ ጥላ የሆነችው እንዴት ነው? (ለ) በዘመናችን የአምላክ አገልጋዮች በባቢሎን በምርኮ የነበሩት በምን መልኩ ነው?
25 በዳንኤል ምዕራፍ 5 ውስጥ የሚገኘው ዘገባ ለእኛ ትልቅ ትምህርት ይዟል። የጥንቷ ባቢሎን የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች መናኸሪያ እንደመሆኗ መጠን ለዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ትክክለኛ ምሳሌ ትሆናለች። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ደም እንደተጠማች ጋለሞታ ተደርጋ የተገለጸችው ይህቺ የማታለያዎች ጥርቅም “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ ተጠርታለች። (ራእይ 17:5) አምላክን ስለሚያቃልሉ የሐሰት ትምህርቶችዋና ልማዶቿ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ቸል በማለት በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት የሚሰብኩትን አሳድዳለች። በካህናቱ ቆስቋሽነት በተነሳው ስደት አማካኝነት የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ያበቃለት መስሎ በታየበት በ1918 የቅቡዓን ክርስቲያኖች የታመኑ ቀሪዎች እንደ ጥንቷ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ ነዋሪዎች ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ግዞት ሥር የነበሩ ያህል ሆነዋል።
26. (ሀ) “ታላቂቷ ባቢሎን” በ1919 የወደቀችው እንዴት ነው? (ለ) እኛ ራሳችን የትኛውን ማስጠንቀቂያ ልንቀበልና ለሌሎችም ልናካፍል ይገባል?
26 ይሁንና “ታላቂቱ ባቢሎን” በድንገት ወደቀች! በ539 ከዘአበ የጥንቷ ባቢሎን ያለ ምንም ድምፅ ለማለት ይቻላል እንደወደቀች ሁሉ የታላቂቱ ባቢሎንም አወዳደቅ ድምፅ አልባ ነበር። የሆነ ሆኖ ይህ ምሳሌያዊ ውድቀት ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሏል። ይህ የተከናወነው የይሖዋ ሕዝቦች በ1919 ከባቢሎን ግዞት ነፃ ወጥተው መለኮታዊውን ሞገስ በማግኘት በተባረኩበት ጊዜ ነው። ይህም “ታላቂቷ ባቢሎን” በአምላክ ሕዝቦች ላይ ያላት ሥልጣን ያከተመበትና እምነት የማይጣልባት ማታለያ መሆኗ መጋለጥ የጀመረበት ጊዜ ነው። ይህ ውድቀቷ በፍጹም ሊጠገን የሚችል ዓይነት አይደለም። የመጨረሻ ጥፋቷም ቢሆን እጅግ ቅርብ ነው። በመሆኑም የይሖዋ ሕዝቦች “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ” የሚለውን ማስጠንቀቂያ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል። (ራእይ 18:4) ይህንን ማስጠንቀቂያ ተቀብለሃልን? ለሌሎችስ እያሰማህ ነውን?f
27, 28. (ሀ) ዳንኤል የትኛውን ወሳኝ እውነት አልዘነጋም? (ለ) ይሖዋ ዛሬ ባለው ክፉ ዓለም ላይ በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድ ምን ማረጋገጫ አለን?
27 እንግዲያው ዛሬም በቅርቡ ጥፋት እንደሚመጣ የሚገልጸው ጽሑፍ በግድግዳው ላይ ታይቷል ለማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ‘ለታላቂቱ ባቢሎን’ ብቻ አይደለም። በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የጎላው መሠረታዊ ቁም ነገር የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ገዥ መሆኑን አስታውስ። በሰው ልጆች ላይ ገዥ ለመሾም መብት ያለው ብቸኛ አካል እርሱ ነው። (ዳንኤል 4:17, 25፤ 5:21) የይሖዋን ዓላማ የሚጻረር ማንኛውም ነገር ይወገዳል። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ይሖዋ እርምጃ መውሰዱ አይቀርም። (ዕንባቆም 2:3) ዳንኤል ይህን ዓይነቱን አጋጣሚ ለማየት የታደለው በዘጠናዎቹ ዕድሜው ነበር። በዚያን ጊዜ ይሖዋ የዓለም ኃያል የነበረውንና ከዳንኤል ለጋ ዕድሜ አንስቶ የአምላክን ሕዝቦች ሲጨቁን የነበረውን መንግሥት ሲያስወግድ ተመልክቷል።
28 ይሖዋ አምላክ በሰማያዊ ዙፋን የሰው ልጆች ገዥ መሾሙ ሊታበል የማይችል ሐቅ ነው። ዓለም ይህንን ንጉሥ ቸል ማለቱና አገዛዙንም መቃወሙ ይሖዋ የመንግሥቱን ግዛት በሚቃወሙት ላይ በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። (መዝሙር 2:1-11፤ 2 ጴጥሮስ 3:3-7) የጊዜውን አጣዳፊነት በመገንዘብና እርምጃ በመውሰድ ትምክህትህን በአምላክ መንግሥት ላይ አድርገሃልን? ከሆነ ከግድግዳው ጽሕፈት ትምህርት አግኝተሃል ማለት ነው!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ተቀርጾ በተገኘ አንድ ጥንታዊ ጽሑፍ ላይ ንጉሥ ቂሮስ ብልጣሶርን በሚመለከት “በአገሪቱ ላይ [ገዥ] ሆኖ የተሾመው ደካማ ሰው ነው” ብሏል።
b ዳንኤል የተናገረው ይህ ዝርዝር ጉዳይ እንኳ ሳይቀር ትክክል መሆኑ ተረጋግጧል። አርኪኦሎጂስቶች የጥንቷ ባቢሎን የቤተ መንግሥት ግድግዳዎች በሸክላ የተሠሩና ከላይ የተለሰኑ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
c የባቢሎናውያን አጉል እምነቶች ደግሞ ይህንን ተዓምር ይበልጥ አስፈሪ ሳያደርጉት አልቀሩም። ባቢሎኒያን ላይፍ ኤንድ ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “ባቢሎናውያን ከሚያመልኳቸው በርካታ አማልክት በተጨማሪ በመናፍስት የማመን ዝንባሌ በእጅጉ የተጠናወታቸው ሰዎች ከመሆናቸው የተነሣ የሃይማኖታዊ ጽሑፎቻቸው አብዛኛው ክፍል ለእነዚሁ መናፍስት በሚቀርቡ ጸሎቶችና ድግምቶች የተሞላ ነው።”
d ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “ባቢሎናውያን ኤክስፐርቶች በሺህ የሚቆጠሩ የገድ ምልክቶችን በዝርዝር አስፍረዋል። . . . ብልጣሶር በግድግዳው ላይ ያለውን ጽሑፍ ትርጉም ለማወቅ በጠየቀ ጊዜ የባቢሎን ጠቢባን እነዚህን የገድ ኢንሳይክለፒዲያዎች እንዳገላበጡ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ የፈየዱላቸው አንዳች ነገር አልነበረም።”
e የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች እንደሚሉት እዚህ ላይ የተሠራበት “ተደናገጡ” የሚለው ቃል የተሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ ግራ በመጋባት ታላቅ ሽብር ላይ መውደቁን የሚያመለክት ነው።
f ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 205-71 ተመልከት።
ምን አስተውለሃል?
• ጥቅምት 5/6, 539 ከዘአበ ምሽት ላይ የብልጣሶር ግብዣ የተቋረጠው እንዴት ነበር?
• የግድግዳው ጽሕፈት ትርጉሙ ምን ነበር?
• የብልጣሶር ግብዣ እየተካሄደ እያለ ፍጻሜውን በማግኘት ላይ የነበረው ስለ ባቢሎን የተነገረው ትንቢት የትኛው ነው?
• ስለ ግድግዳው ጽሕፈት የሚናገረው ዘገባ ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
[በገጽ 98 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 103 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]